Tuesday, March 30, 2021

ንጉሠ ነገሥት አብይ አሕመድ ዓሊ ስለ በዓለ ሢመቱ ትንሽ ወግ... አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) Ethio Semay 3/30/21

 

 

ንጉሠ ነገሥት አብይ አሕመድ ዓሊ 

ስለ በዓለ ሢመቱ ትንሽ ወግ...

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) 

Ethio Semay

3/30/21


Photo Ethio Semay

ከኢትዮ ሰማይ አዘጋጅ ማስታወሻ፡

ጸሐፊው አምባቸው ደጀኔ በዚህ ግሩም ጽሑፉ ላይ “ይልማ በቀለ” ስለሚባል “ተሳላሚ” ለበርካታ አመታት የሚሰነዝራቸው አስተያየቶች ስቃወመው የነበረ ሰው ነው። ዛሬ አምባቸው ደጀኔ ስለዚህ ማፈሪያ ሰው አብይ አሕመድን አስመልክቶ “በእንግሊዝኛ” የጻፈው አሽቃባጭነቱን ያሳየበት ጥቅስ ስመለከት “ይልማ” ዛሬም “አድሮ ጥጃ” ሆኖ ሳየው ገረመኝ። “ይልማ በቀለ” የወያኔን ፋሺስታዊ ሕገመንግሥት አክባሪ አለቃው ኮ/ል አብይ አሕመድን ለማሞገስ የሄደበት ርቀት በሦስት አመት የታየው እልቂት እና ዋይታ፤ “የሰው ስጋ የሚበላባት” “ምጽአተ ኢትዮጵያን” ወደ “ውብ አበባነት ተለውጣለች” ሲለን እጅግ አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን cognitive dissonance በተባለው የግንዛቤ ቀውስ በተው የሕዝቡን ዋይታ “እልልታ” ሆኖ የሚሰማቸው ለሕክምና የሚያቃስቱ የውይ ምሁራኖች ድምፅ ነው።  3/30/21

 

ዶክተር አቢይ አመድ የ3ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ሊያከብር ጉድ ጉዱ መጧጧፉን በሚዲያ እየሰማን ነው፡፡ አሳፋሪ ነው፡፡ አሳፋሪነቱን ማስረዳት እችላለሁ፡፡ የዚህ ሰውዬ ነገር እጅጉን የሚደንቅ ነው፡፡ የከበቡትም አሻንጉሊቶች እንጂ ሰዎች አይመስሉኝም፡፡

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

በ Ethio Semay የተለጠፈ

“በባዳ ቢቆጡ በጨለማ ቢያፈጡ” (ዋጋ የለውም) ቢባልም የተሰማኝን እንደልማዴ እጮሃለሁ፡፡ ቢያንስ ተናግሬው ይውጣልኝ፡፡ እንደጠባብ ዕድል ሆኖ ለነገ አዳሪ ከሆንኩም “እኔም ባቅሜ እንዲህ ብዬ ነበር” ብሎ ለመጎረር ያመቸኛል፡፡ እንግዲያማ ተናጋሪ እንጂ አድማጭ በጠፋበት ወቅት ይህን ያህል መድከም አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም፡፡ ጊዜው ይታወቃል፡፡ የዘመኑ ምንነት ግልጽ ነው፡፡ 

 

በዓለ ሢመት ሲከበር የማውቀው የንጉሦች፣ የፓትርያርኮችና መሰል የሥልጣንና የሹመት ሰዎችን ነው - ሥልጣናቸው ዕድሜ ይፍታህ የሆነ ግለሰቦች፡፡ ኢትዮጵያን በመሰለች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለዓለም በማስተማር ላይ በምትገኝ ሀገር በምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣ ጠ/ሚኒስትር ግን በዓለ ሢመት ሲያከበር ማየት አልተለመደም፡፡ የቀደሙት ፍጹማን ዴሞክራሲያዊያን መሪዎቻችን ለምሣሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከነሙሉ ክብሩ፣ ግርማ ሞገሱና ጥቅሙ እንዲሁም የአዛዥ ናዛዥ የሥራ ኃላፊነቱ ጭምር እርሳቸውን ተክተው የነበሩት ጠ/ሚኒስትር ደሳለኝ ኃ/ማርያም (ሣቄ ሊያመልጠኝ ነው እናንተዬ ኧረ እባካችሁን ጸልዩልኝ!) አዎ፣ እነዚህን መሰል የዴሞክራሲ ፋና ወጊ መሪዎቻችን እንኳን በዓለ ሢመታቸውን ለማክበር አልደፈሩም - ምንም እንኳ እናቶቻቸው መሪዎቻችን እንደሚነግሡ የንግሥና ተራ ቁጥራቸውን ሳይቀር ጠቅሰው ቀድመው ባይተነብዩላቸውም፡፡ አቢቹ የማያሳየኝ ተዓምር ላይኖር ነው፡፡ ይህ ሰው በ16 ዓመቱ የዶክትሬት ዲግሪውን ይዞ በ17 ዓመቱ የሞተውን አንድ የከውካዋ ሕይወት ሰለባ ታዳጊ ወጣትን ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ ሲያሳዝን!

 

እውነትን ለመናገር ለይስሙላም ይሁን ከእውነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመረጠ የተባለ የአንድ ሀገር መሪ ይህን መሰል ቅሌት ውስጥ አይገባም፡፡ አንዱም የአሜሪካ መሪ ሥልጣን የያዘበትን ቀን በቤቱ ውስጥ ከሆነ እንጂ በጀት መድቦና ሕዝብን በግዴታ አሰልፎ በአደባባይ ሲያከብር አላየሁም፤ አልሰማሁምም፡፡ ይህን የጠ/ሚኒስትር አቢይን በዓለ ሢመት ለየት የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እናንተም መርምሩና ድረሱባቸው፡፡ ዐፄ አቢይ አመድ በዓለ ሢመታቸው በበርካታ ንጹሓን አማሮች ዕርድ መታጀቡን ታዲያ በቀዳሚነት እንድታስቡ ይሁን፡፡ አቢይ የነካው ተክል ሁሉ በፍጥነት እንደሚደርቅም ትዝ ይበላችሁ፡፡ ከዚህ በላይ ብጨምር የናንተን የማስታወስ ችሎታ እንደመናቅ ይቆጠርብኛል፡፡

 

ለስሙ አማካሪዎች አሉ፡፡ እነዳንኤል ክብረት እዚያ ቁጭ ብለው ይህንን እንኳን “ኧረ ጌታየ ይህስ እኛንም ጭምር ያዋርደናል ይተውት! መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንኳን ነፍስ አውቆ ያላደረገውን ነገር እርስዎ ሲያደርጉት ሕዝብን ብንንቀው ሌላው ዓለም እኮ ይታዘበናል፤ ጥርሱን በዘነዘና ተወቅሮ ነው የሚስቅብን ጌታየ” ማለት ነበረባቸው፡፡ ሰው ጤፉ አቢይ ባይሰማቸውም አሁንም ይሞክሩ፡፡

 

ሌላ ጉዳይ ላውራ፡፡ ኪራይ ቤቶች ከዘበኛ እስከ ዋና ማጂነር አክራሪ ኦሮሞ ነው አሉ የወረሰው - የይስሙላውን የመጣያ ዓይነት ሹመት ትተን፡፡ በዚያም ምክንያት የኪራይ ቤቶች ንብረት የሆኑ የመንግሥት ቤቶች ለኦሮሞ ሀብታሞች ባወጡ እየተቸበቸቡ ነው፡፡ ድንቁ ደያስ የተባለው የዲግሪ ወፍጮ ባለቤት ከኪራይ ቤቶች የወሰደውን አንድ ቤት እንዴት አድርጎ እንዳሳመረው ራሴ አይቻለሁ፡፡ አዲስ አበባና አካባቢዋ እንዳለች በቄሮ ቅርጫ እንደጉንዳን ተወርራለች፡፡ አሁን ያልከበረ ኦሮሞ መቼም አይከብርም የተባለ ይመስላል፡፡

 

አዲስ አበባ አሥር የትራፊክ ፖሊሶችን ሰብሰብ ብለው ካየህ አሥሩም ኦሮሞ ለመሆናቸው ብዙም አትጠራጠር፡፡ አሥር የመንገድ ላይ ፖሊሶችን ካየህ ቢያንስ ዘጠኙ ኦሮሞ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ አይግባህ፡፡ አሥር የአሥር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ታላላቅና ወሳኝ ባለሥልጣናት ሰብሰብ ብለው ቡና ሲጠጡ ብታይ አሥሩም ኦሮሞ መሆናቸውን ለማወቅ ማንንም መጠየቅ አይጠበቅብህም፡፡ የአሥራ ምናምኑን ክፍለ ከተማ ዋና ዋና ባለሥልጣናት ብታይ ከኦሮሞ ውጭ አይሆኑም፤ ወረዳና ቀበሌዎችንማ ተዋቸው፡፡ የመከላከያን አሥር ዋና ዋና ባለሥልጣናት ድንገት ሻይ ሲጠጡ ብታይ ከኦሮምኛ ውጪ ሲናገሩ የመስማት ዕድል የለህም፡፡ ወያኔ ሞትኩ አትበል፤ ዐይኗን ባይኗ አይታና ራሷን ተክታ ነው ፍግም ያለችው፡፡ እነዚህም እንደፈጣሪያቸው ፍግም እስኪሉ ጉድ እያሳዩን ነው፡፡ ምን አለፋህ አቢይ እላይ ሆኖ “ኢትዮጵያ የጋራ ናት” ይልሃል ከሥር ግን በእርሱ ዕውቅናና ሽፋን ሰጪነት ለአንድ የቀን ጅብ ተሰጥተን የትህነግን ዘመን እየናፈቅን ነው፡፡ “ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ አይመሰገንም” የሚባለው እውነት ነው፡፡ “በይሉኝታቢስነት ከወያኔ የሚበልጥ የለም” በሚል ብዙ ጊዜ እከራከርና እጽፍም ነበር፡፡ “የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ” ነው ወንድሜ፡፡ እነዚህ ብሰው ቁጭ አሉ - ኖቤል ከሚያሸልም የጅልነት ጭካኔ ጋር፡፡ እንዴ! ወያኔዎች እኮ ብልጥ ነበሩ - ማስመሰልን ይችሉበት ነበር፤ በተለይ ከ97 ምርጫ በፊት፡፡ ይበልጥ የተግማሙት ከ97 በኋላ ነበር፡፡ አሁን የምናየው ይህ ሁሉ የአንድ ነገድ የበላይነት የተፈጠረው ባጋጣሚ ቢሆን ምንም አይደለም፤ በሥራ ችሎታና በብቃት ቢሆን ምንም አይደለም፤ ሌላው ያልተማረና ብቁ ሆኖ ባለመገኘቱ ቢሆን ምንም አይደለም ... ግን ያ አይደለም፡፡ “ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡” 

 

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንድትሆን በርግጥም መፍረስ አለባት፡፡ መፍረስ ሲባል ደግሞ አካላዊ መፍረስ አይደለም፡፡ አእምሯችን ፈርሶ ከእንደገና መሠራት ይኖርበታል፡፡ ለምሣሌ ዶክተር አሸብርን የመሰለ እምብርት የለሽ ሰው ይዘህ አገር ልትፈጥር አትችልም፡፡ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሀኪም ይንቀለኝ ብሎ የገገመው ይህ ሰውና መሰሎቹ ምን እንደሚሠሩ እናውቃለን፡፡ የኮሚቴ ሊቀ መንበርነታቸውን ለግል ቢዝነሳቸው ለመጠቀም ሲሉ የማይሠሩት ሸርና ተንኮል እንዲሁም ከባለሥልጣናት ጋር የጥቅም መሞዳሞድ የለም፡፡ በሚሊዮኖች ምናልባትም ከዚያም በበለጠ የሚቆጠር ገንዘብ አላቸው፡፡ ግን እምብርት ብሎ ነገር ስላልፈጠረባቸው በቃኝን አያውቁም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ የሀገራችን ነጋዴዎችና ባለሥልጣናት እንደዚህ ናቸው - የቀን ጅቦች፡፡ እነዚህ ፈርሰው ካልተሰሩ ሀገር አትኖረንም፡፡ አንድ ሰው በቃኝን ካላወቀ ደግሞ ሀገርንና ሕዝብን ተወውና ሚስቱንም ልጁንም አባትና እናቱንም ከመሸጥ ወይም ለዲያብሎስ ጭዳነት ከመገበር አይመለስም፡፡ የሚታየው ግድያና የዘር ዕልቂት ሁሉ መባቀያው እንግዲህ ይሄው ነው - ሆድና የሆድ መዘዝ፡፡ ሌላውና በየፖለቲከኛው አንደበት የሚተረከው ሁሉ ማስመሰያ ነው፡፡ እንጂ ህዝብማ ዱሮም ሆነ አሁን አብሮ እየኖረ ነው፤ ወደፊትም አብሮ መኖሩን ይቀጥላል፡፡

 

ግን ግን እባካችሁን የነገ ሰዎች አንድ ነገር ላሳስባችሁ፡፡ ሀገር ሲኖረን የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ አዲስ መሥፈርት ይውጣ፡፡ ድሃ ወደ ሥልጣን አይምጣ፡፡ ድሃ ድህነቱን እንጂ እምነቱን አያስብም፡፡ ክብረቱን እንጂ የሥራውን እንከን አያይም፡፡ ገንዘብ እያሳዩ ገደል የሚከቱት ይበዛሉ፡፡ ያኔ አገርና ሕዝብም አብረው ገደል ይገባሉ፡፡ ድህነት ይሉኝታን ያጠፋል፤ ማጣት ሀፍረትን ያሸጣል፡፡ የሰውን እጅ ማየት ኅሊናን ያሣውራል፡፡ ሀብት የማግኘት ጉጉት የሥራ ኃላፊነትን ያስረሳል፡፡ ስለዚህ ሥልጣን የሚይዝ ሰው በዕውቀትም በትምህርትም በሀብትም የተደላደለ ቢሆን ሀገር ትረጋጋለች፤ ፍትህ ትነግሣለች፡፡ ከሌሎች ሀገራትም እንማር፡፡ በበርካታ አገሮች ማንም ነጫጭባ ድሃ ከመሬትም በለው ከቆጥ አልጋ እየተነሳ ሥልጣን ላይ ፊጥ አይልም - ህግና ሥርዓት አለው፡፡ እንደኛ ሀገር በተገዛ ወይ በተጭበረበረ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ ልባስ ምድረ ማይም ሥልጣን ላይ እየወጣ “we supporting they equivocally” በሚል “is”ን እና  “was”ን በቅጡ ባልለዬ እንግሊዝኛው የድንቁርና በጠጡን ሕዝብ ላይ አያራግፍም - ሰምታችኋል!! እንደሕዝብም እንደሀገርም በቁማችን እኮ ሞተናል፡፡ የባለሥልጣናትን የአመራር “ብቃት”ና ሀብትና ንብረት የማከማቸት ስግብግበነት ሳይ በኢትዮጵያዊነቴ አፍራለሁ፡፡

 

 አሁን በዚህን ዘመን ሙስና ውስጥ የማይገባ ሰው ዕብድ ወይም ወፈፌ ነው - እንደጤነኛ አይቆጠርም፡፡ ለነገሩ ለትራንስፖርትም የማይበቃ ወርኃዊ ደሞዝ እየተከፈለው አትሞስን ማለትም በሰው ኅልውና መፍረድ ነው - ችግር እኮ ነው ጎበዝ፡፡ የአምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋና የአንድ ሻይ ቤት አስተናጋጅ ወርኃዊ ደሞዝ ተመሳሳይ መሆኑን ስንቶቻን እንደምናውቅ አላውቅም፡፡ የአንዲት ሚጢጢዬ ክፍል የወር ኪራይ 2000 ብር ሆኖ ሳለ ለአንድ የቢኤ ዲግሪ ምሩቅ ብር 3000 የሚመድብ ሲቪል ሰርቪስ ያቋቋመ መንግሥት ያለን የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥልጡናን እኮ ነን እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡ የሚገርመው ባለሥልጣናት በስርቆትና በሙስና እንጂ በደሞዝ ስለማይኖሩ ይህ የሕዝብ ችግር አይገባቸውም፡፡ ፈርዶብን!

 

ምርጫ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ካለም በደም የጨቀዬ ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ መጥፊያው ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ መነሳቷ እርግጥ ነው፡፡ ... ይልማ በቀለ የሚባለው ጉደኛ ፍጡር የሚያመልከው አቢይ አመድና መንግሥቱ ዕድሜያቸው እያለቀ ነው፡፡ ብዙ ነገር ለማየት፣ ብዙ ለማልቀስ፣ ብዙ ስቃይ ለመቀበል .... እንዘጋጅ፡፡ “የማን ሟርተኛ ነው” ደግሞ አትበል፡፡ አንተም የምታውቀውን ወይም ልታውቀው የማትፈልገውን ነው የነገርኩህ፡፡ ያለንበት ጊዜ “ዝም በል የኔን እግር እየበላ ነው” ከሚባልበት ደረጃም አልፏል፡፡  በቃኝ፡፡

 

 

ከፍ ሲል የጠቀስኩት የአቢይ አመድ አሽቃባጭ (አሽቋላጭ የሚለው ቃል ሲያስጠላኝ!) ሰሞኑን ስለአቢይ መልኣክነት በዘሀበሻ ድረገጽ ላይ ከጻፈው የሚከተለውን ሳልጋብዝ ላለማለፍ ለራሴ ቃል አለብኝና እባካችሁን ኮምኩሙልኝ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን ሆዳም ወይንም በሆዳምነት የማይታማ ከሆነም የሕዝብንና የሀገርን ተጨባጭ ኹነት ሊረዳ የማይችል ፍርደ ገምድል ገልቱ ዜጋም ፈጥራለች፡፡ አዝናለሁ፡

“We are blessed to have a fair and gracious foreman during this transition from chaos to order. The last three difficult years, Dr. Abiy Ahmed has proven he is a born leader. No one would have predicted such a beautiful flower to bloom from Woyane’s toxic garden.”  

“The sun is rising over Ethiopia.” (Yilma Bekele)

 

ልተርጉመው ይሆን? እስኪ ልሞክረው፡-

“ከዚህ ካለንበት ሥርዓት አልበኝነት ወደ ሥርዓታዊ ሀገራዊ ኑባሬ ሊያሸጋግረን የሚችል ዶክተር አቢይን የመሰለ ፍትኅ ዐዋቂና ግርማ ሞገሱ የሚያርድ አሻጋሪ ማግኘታችን በውነቱ መባረክ ነው፡፡ ያለፉት ሦስት አስቸጋሪ ዓመታት ዶክተር አቢይ ሙሤያዊ አሻጋሪነቱን አረጋግጠውልናል፡፡ እንዲህ ዓይነት በውብ አበባ ሊመሰል የሚችል ድንቅ ዜጋ በወያኔ መርዛማ ማሕጸን ውስጥ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ቀድሞ የገመተ ሰው አልነበረም፡፡”

“በኢትዮጵያ ፀሐይ እየወጣች ነው” ይልማ በቀለ