Monday, April 19, 2010

ሁሉም የራሱን ግማደ መስቀል ይሸከም!

ሁሉም የራሱን ግማደ መስቀል ይሸከም! (ከገብረወልድ አብነት)
ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፣ በሐሰት የሚናገርም አያመልጥምመጽሀፈ ምሳሌ ምዕራፍ 19
ድሮ በአጼው ዘመን በህግ አምላክ፡ በንጉሱ አምላክ ይባል ነበር። ነውናም ለዚያ ዘመን ሰዎች ምናልባትም ከሚያምኑበት መጽሐፍ ብጠቅስ ህሊናቸውን ይኮረኩር ይሆን በሚል ተስፋ ከመጽሃፈ ምሳሌ ጠቀስ አድርጊያለሁ። ንስሐ መግባት ለነገ ተነገ ወዲያ የሚተላላፍ ወይም ተድብስብሶ የሚቀርብ አይደለም። አጠፋን ብሎ አምኖ ይቅርታን ከሰውም ከፈጣሪያቸውም በመጠየቅ ፈንታ ዛሬም ሊዋሹና ሊክዱ የሚነሱ ወይም ሁሉንም ጥፋት በሰለባቸው ላይ ሊጭኑ የሚቃጡ ሁሉ በሕዝብም ሆነ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ናቸው። በቅርቡ ራሱን መድረክ ብሎ የሚጠራው ስብስብ መሪዎች በሰሜን አሜሪካ ከተሞች እየተዘዋወሩ ድጋፍን ሲጠይቁ፣ ሀገርና ወገን ገና ያልረሳው ክፍል ስላላፈው ጥፋትና ወንጀላቸው፤ ደብዛቸው ስለጠፋ እስረኞች፤ በስልጣን ላይ ሳሉ ስላደረጉት ሁሉ መጠየቁና ንስሐ ግቡ ማለቱም አልቀረም። የሚመለከታችው ግለሰቦች ለዚህ የሰጡት ምላሽ የተለያየ ነው። ዶክተር ነጋሶ ኦነግም፤ ኢስፓም፤ ኢሕአፓም ተጠያቂ ናቸው ማለትን መርጠዋል። አቶ ስዬ አብርሃ በበኩላቸው አጠፋሁ ይቅርታ ብያለሁና እንኳን ደህና መጣህ በሉ እንጂ አትጨቅጭቁኝ ባይ ነው አመላለሳቸው። አቶ ገብሩ ሲደመጡ የወያኔ ድርጅት አባል ነበሩ ማለትም እስኪያዳግት ድረስ ለሁሉም የማውቀው የለም ባይ ሆነዋል። ይህ ጉደኛ የሽማግሌ ቀላልና የኢስፓው አባል ዶክተር ሀይሉ አርአያ በበኩሉ (ራሱን ያቀለለን አንቱ ባልል ይቅርታ) ቀይ ሽብር መካሄዱን እንኳን ሸምጥጦ ክዷል። ንስሓ መግባት ቀላል አለመሆኑን ሁሉም በየፊናቸው ጠቁመዋል።
ሸምጥጦ የሚክደው ያው በወንጀሉ እንደቀጠለና እንደጸና ተደርጎ ተወስዶ ክህዝብም ከታሪክም ቅጣቱን መቀበል እንዳለበት የታወቀ ነው። እነ ዶክተር ሀይሉና አቶ ገብሩን ዓይነቶቹን የህዝብ ወገን ብሎ መቀበሉ ወይም ማቀፉ ከሞኝም ሞኝ የሚያስብል ነው። ሞኝና ውሀ እንደወሰዱት ይሄዳል ያሰኛል። ሞኝ ውሀ ሲወስደው ይስቃልም ይሆናል። በተለይም ያን ሁሉ ህይውት የቀጠፈውን ሽብር መካድና ሰለባዎችን ለመወንጀል መቃጣት ወንጀል ነው። ወንጀለኛ ደግሞ የሕዝብ መሪ ልሁን ሲል በዝምታ መታየት ያለበት አይደለም-- መወገር ቢቆይ መወገዝ አለበት። ጥፋቱን ከሚክደው ጋር ባይፈረጅም በቅጡ ጥፋቱን ሳያምን አድብድብሶ ሊያልፍ የሚቃጣውም እንዲሁ ዝም ሊባል አይግባውም። አቶ ስዬ አጥፋሁ ያሉት በልጓም ስርቆት እንጂ ከልጓሙ ጋር ስለነበረውና ስለሰረቁት ፈረስ ምንም አላሉም። አቶ ስዬ ከመለስ ዜናዊ ጎን ሆነው ለዓመታት በወያኔ ወንጀሎችና ጥፋቶች ሁሉ ተካፍለዋል። አያሌ የወያኔ ገበናዎችና ምስጢሮችን ያውቃሉ። ያጋለጡት ካለ ኢምንት ነው። አዎ አጠፋሁ ያሉት ካለም ትንሽ ነው። ገና ሂሳብ ማወራረድ አልጀመሩም፤ አልደፈሩም። አሁን ከመለስ ተጣላን የሚሉን የሶስተኛው ወያኔ -የአረና ትግራይ (አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት የትግራይ ደጀን) አባላት ትላንት ባለስልጣን በነበሩ ጊዜ ያሰሯቸው ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደታሰሩ ነው። እነሱም እነማንን የት እንዳሰሩም አልነገሩን። ትላንት ያፈኗቸው ኢትዮጵያዊያን ዛሬም የገቡበት አይታወቅም። እነሱም የት እንዳደረሱዋቸው አልነገሩንም። ወይም እዚህ እዚህ በግፍ ታስረው የሚማቅቁትን በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ እስረኞች የመለስ ቡድን ይፍታ የሚል አንዲትም ቃል ሲተነፍሱ አልሰማንም። አብረው በነበሩ ጊዜ ይደረግ ስለነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት አንዲትም ምስጢር ሲያወሩ አልተደመጡም። ዞሮ ዞሮ ዘወትር የሚነግሩን በእነሱ ላይ ስለደረሰው እስር፣ መለስ አፍቃሪ-ኤርትራ ስለመሆኑ፣ ስለአንዲት ብርቱካን መታሰር፣ ስለኢትዮጵያ የባህር ወደብ የለሽ መሆን ነው - ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀውን ጉዳይ። ለዚህ ለዚህማ እነሱም ብዛት ያላቸው ጽኑ ኢትዮጵያዊያንን አብረውት ሲገድሉ፣ ሲያፍኑ ነበር። ኢትዮጵያን የባህር በር የሌላት ለማድረግ የተዋጉትና ይህ መሆን የለበትም ያሉትን ከመለስ ጋር በመሆን በግንባር ቀደምነት ይገሉ የነበሩት እነሱም ጭምር ናቸው። ለአፍቃሪ-ኤትራዊነትማ፣ ለሻዕቢያ የጦር ማገዶ ይሆኑ ዘንድ የትግራይ ወጣቶችን ሰብስቦ ናቅፋ የወሰደው የወያኔ ጦር መሪ ስዬ እኮ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ እናቶች የጓሮ ጎመን የሚወልዱ መሰለቸው እንዴ «ትላንት ተዋግተን ያዘጋነውን የባህር በር፣ ዛሬ ደግሞ በእኛ አዝማችነት እና አገዛዝ ስር እናንተ ሙቱና እናስከፍትላችሁ» የሚሉን ያሰኛል። እኛ የምንላቸው ትላንትም አብራችሁ ስለገደለቻችሁዋቸው ወይም ስላስገደላችሁዋቸው፣ ስላሰራችሁዋቸው ወይም ስላሳሰራችሁዋቸው ወገኖቻችን ንገሩን ነው። እኛ የምንላቸው ሳትቀላቀሉን በፊት የፈጸማችሁትን ግፍ ተናዘዙና ለተገደለው እንባችንን እናፍስ፣ በየዋሻው ጨለማ እስር ቤት ካጎራችሁዋቸው ወገኖቻችን እግርና እጅ ላይ ሰንሰለቱን ለመበጠስ ትግላችንን እናጠናክር ነው። በሌባነት የተያዘ በቅጽበት ተመልሶ የዚያው ቤት ጠባቂ አይሆንም -የባለቤቱ ጤነኛነት የተቃወሰ ካልሆነ በስተቀር። ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ቆመናል የሚለውን ወገንም የምንመክረው የመለስን ዳግማዊ ወያኔ በስዬ ሳልሳዊ ወያኔ በመተካት ሀገርና ሕዝብን ለሌላ ዙር አገዛዝ ለመዳረግ በተሸረበ ተንኮል አትታለል ነው። የወያኔ ዘረኛ ስርዓት እንዲቀጥል የሚመኙ ጠባቦችና የክልል አንድ ተወላጆች ለነ አቶ ስዬና ገብሩ ታዳሚ፤ አዳናቂና፤ አጨብጫቢም ቢሆኑ ያሳዝናል እንጂ አያስገርምም። ወያኔ ቤተመንግስት ከመግባቱ ከመቅጽበት የስልጣን ትርፍራፊ ተችሯቸው የነበሩትም (የት/ሚ ምክትል ሚኒስትርነት ለዶ/ር በየነ፣ ምክትል ኮሚሽነርነት ለኢንጂነር ግዛቸው ተስጠቶ እንደነበር ያስታውሷል)አሁን ደግሞ ለሌላ ዙር መሰል እደላ ቢቋምጡም የለመደባቸው ነውና አይገርምም። ዶክተር ነጋሶ በበኩላቸው እንደሚያጠግብ እንጀራ መሰሉና ወዲያው ደግሞ ባረጁበት መንገዱን ተያይዘው ጥፋታቸውን መደባበቅና ሌሎችን መወንጀልንም ተያያዙት። ጎዶሎ እንጎቻ ሆነው ቁጭ አሉ።
ሁሉም የራሱን ግማደ መስቀል መሸክም አለበት ስል ቢያንስ የቄስ ጊዳዳ ልጅ እንደሚረዱልኝ እተማመናለሁ። ጥፋት አለ፣ ወንጀል አለ --ሁሉም ሚዛኑና ጉዳቱ አንድ አይደለም። ጥፋት ሌላ፣ ወንጀል ሌላ --መቸም ቢሆን በአንድ ሚዛን ሊቀመጡ አይችሉም። ስለዚህም ዶክተር ነጋሶ በስልጣን የነበሩና ከወያኔም ስልጣን የተጋሩ እንደመሆናቸው በዚያን ወቅት ያጠፉትን ከድርጅቶች -- ያውም ስልጣን አጠገብ ደርሰው ከማያውቁት ጥፋት ጋር ሊያወዳድሩ አይችሉም። ማጭበርበርና ሐሰትን ማቀንቀን ይሆንባቸዋል። ኢስፓም በስልጣን የቆየና ገዢም የነበረ ነው --የእሱ ወንጀልና የሰለባው የኢሕአፓ ጥፋት (የሚሉት ዶክተሩ) በምንም መስፈርት ሊወዳደር የሚችል አይደለም። ኦነግም ቢሆን ለአሶሳ ፍጅት ተጠያቂ መሆኑ ተገቢ ሲሆን፤ ከወያኔ ስልጣን ሲጋራ ለፈጸማቸው የበደኖ ዓይነት ወንጀሎችም መጠየቅ ቢኖርበትም እንደወያኔ የስልጣን ባለቤት አልነበረም። የድርጅቶች ስህተትና ጥፋት ከአገዛዞች ወንጀል ጋር በአንድ ክብደት ሊፈረጅ አይችልም። በዚህ ላይ ዶክተር ነጋሶ ተሳስትዋል፤ መታጠብ ጀምረው ወደ ጭቃው ተመልሰዋል። ከመለስ ተጣልተናልና እጃችሁን ከፍታችሁ ተቀበሉን የሚሉት እስካሁን ሊረዱት ያልቻሉት ይቅርታ ጥየቃ፣ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ነው። ለህዝብ ትግል ግን ወሳኝነት ያለው ነው። ከመለስ መጣላታቸው በራሱ ለህዝብ ያለው ጠቀሜታ አገዛዙን የሚያዳክም ከሆነ ነውና ይህ ጥል እንዲከር ህዝብ ይፈልጋል። በዚያው ልክና ከዚያም በላይ የሚፈልገው ግን የወያኔ አገዛዝ መውደቅ መንኮታኮት ነው። መታደስና መጠገን ሳይሆን። መለስን አስወግዶ ሳልሳዊ ወያኔን ማስፈን ሳይሆን። የትግራይ የበላይነትን መቀጠል ሳይሆን። እነስዬና ገብሩ (አልፎም እነ ነጋሶ) ከመለስ ከርኩሱ ሰውዬ ብቻ ሳይሆን ከወያኔ ስርዓት ጋር መጣላታቸውን ለሕዝብ ማረጋግጥ የሚችሉት ላጥፉት ሁሉ ይቅርታ ከሕዝብ ሳይሸፋፍኑና ሳያወላዱ ሲጠይቁና የወያኔንም ጎጂ ምስጢሮች ሲያጋልጡና ወያኔን አክ እንትፍ ብለው ሲተዉ ብቻ ነው። ለዚህም ነው በነሱ የተነሳ ሰቆቃና ዋይዋይታን መስማት ተገዶ ይቆየው ጆሯችን አጠፋንን እና ይቅር በሉን ሰምቶ ይደሰት የምንለው። የደርግንም የወያኔንም ጥፋት ክዶ ወይም አድበስብሶ የለም እነ ኢሕአፓ ይቅርታ ይጠይቁ ብሎ መለፈፍ ራስን ዳግም ለቅሌትና ትዝብት ለማጋለጥ እንጂ ማንንም አያደናግርም። ኢሕአፓ ሆን ሌሎች ድርጅቶች ለሕዝብ ብለው ሲታግሉ ላጠፉት ጥፋት የሚሽከሙት መስቀል ገለባ ነው -- ከደርግና ወያኔ ወንጀል ሲመዘን። ይህን መጻርር ሐሰት መናገር ነው --ሐሰት ደግሞ ይቀጣል። የሰማዕት ደም ፍትህን እስኪያገኝ ይጮሃልና ሆዳቸው ጆሯቸውን ያልደፈነባቸው ዜጎች ያዳምጡታል። ዋ ያቺ ቀን ስትመጣ! ዋ ለወንጀለኞች ሁሉ!!