Saturday, February 5, 2022

የተለመደው የትግራይ አክራሪ ብሄረተኞች የታላቅነት መዝሙር ትችቴ ለፕሮፌሰር ዘረሰናይ አለምሰገድ ጌታቸው ረዳ (ETHIOPIAN SEMAY) 6 February 2022

የተለመደው የትግራይ አክራሪ ብሄረተኞች የታላቅነት መዝሙር 

ትችቴ ለፕሮፌሰር ዘረሰናይ  አለምሰገድ

ጌታቸው ረዳ

(ETHIOPIAN SEMAY)

6 February 2022


 

የዛሬ ትችቴ አሜሪካ ውስጥ የችካጎ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆነው በኢትዮጵያ ከርሰምድር ውስጥ 3 ሚሊዮን አመት ያስቆጠረች የሰው ልጅ ዝርያ ያላት “ሰላም” ብሎ ለሰየማት የሉሲ ልጅ ናት ተብላ በቁፋሮ ያገኘ የአክሱም ከተማ ተወላጁ የመሬት “ስነ-ከርስ” (አርኪኦሎጂሰት/ ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት) ተመራማሪ የሆነው ፕሮፌሰር ዘረሰናይ አለምሰገድ ንግግሮችን በሚመለከት ነው። ከትናንት በስትያ ድንገት አንድ ነገር ስቃኝ በዩቱብ ያገኘሁት ቺካጎ ከተማ ውስጥ በቺካጎ የትግራይ ምሁራን ማሕበረሰብ ግንኙነት (TPN) ስብሰባ በጠራው ስብሰባ ላይ ፕሮፌሰር ዘረሰናይ አለምሰገድ ያደረገው ንግግርአንድምታዎቹ ደጋግሜ ሳደምጠው የደረስኩበት ድምዳሜ አስነብባች ለሁ።

ዶ/ር ዘረአሰናይ የደረሰበት “አካዳሚ አቺቭመንት” እጅግ ከፍተኛ ጣራ የደረሰ ቢሆንም፤ ዘረሰናይም ልክ እንደተቀሩት የትግራይ ምሁራን በትግራይ ትምክሕታዊ አክራሪ ብሔረተኛነት የተዘፈቀ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

አክራሪ ብሕረተኛነት ምን ማለት እንደሆነ ካሁን በፊት ደጋግሜ የማነሳው አውሮጳ ውስጥ የአምስተርዳም ኗሪ የሆነው የስነኣእምሮ ሊቅ በሆነው በዶ/ር አሰፋ ነጋሽ ትንታኔ መሰረት አክራሪ ብሄረተኛነት ማለት “አንድ ህዝብ ራሱን የዓለም ምርጥ ዘር አድርጎ እንዲመለከት፤ ስለራሱ ነገድ ምርጥነት በአደባባይ እንዲሰብክ፤ እንዲዘፍን፤ እንዲፎክር ያደርገዋል። በአክራሪ ብሄረተኛነት ህመም የተለከፈ ህዝብ የራሱን ምስል እንደ ጣዖት ያመልካል ይላል።

ይህ ሃቅ ነው። ባለፉት አርባ ሰባት ዓመታት በትግራይ ክልል የበቀለው አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን የዚህ አዲስ የአይምሮ ህመም ሰለባ አድርጓል። ዘረሰናይ የተባለው  የትግራይ ምሁር (እንዲያውም ፕሮፌሰር) አክራሪ ብሄረተኛነት በሚፈጥረው ድፍረት ተነሳስቶ ከኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው 1500 ዓመታቱ የትግራይ ህዝብና በተወሰነ ደረጃ የኤርትራ ድርሻ ነው ይለናል። ለተነተነው “ስግብግብ የኔነት ማግበስበስ” እንደማስረጃ የሚሰጠው ደግሞ (I am archeologist, I know what I am talking about.) “አርክዮለጂሰት ስለሆንኩ የምናገረውን አውቃለሁ” የሚል ነው።

አርኪኦሎጂስት ስለሆንኩኝ እኔ የምለውን አምናችሁ ተቀበሉኝ ከማለት ውጭ ከኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው 1500 ዓመታቱ የትግራይ ህዝብና በተወሰነ ደረጃ የኤርትራ ድርሻ እንዴት ሆኖ ሌላውን የቅርብ ተጓዳኝ አካባቢ ሕዝብ እንዳላካተተና የቺ አካባቢ ብቻዋን ታጥራ እንዴት የዚያ ዘመን አስተዳዳርና ጥበብ በብቸኛ ባለቤትነት “ጌታ” ሆኖ አንደኖረ በረዢም የእንግሊዝኛ ንግግሩ “አንዲትም ማስረጃ” ሊያቀርብ አይችልም ወይንም አላቀረበም።

ጥልቀት የማያውቀውን የፍልስፍና ትምሕርት እንደገና ይገባና አባ እስጢፋኖስንና ዘርያቆብን በሚመለከትእንዲሁም በሙዚቃ ፈጠራ በኩል “ቅዱስ ያሬድን የመሳሰሉት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ከማስረገጡም በላይ በዓለምም ደረጃ ከሚታወቁት ታላላቅ ሰዎች ቅድሚያ የነበራቸውን እነዚህን ግለሰቦች ትግራይ እንዳፈራች በኩራት ተናግሯል።

በሚገርም ኢ-ምሁራዊ በሆነ ንግግር ዘረሰናይ እነዚህን በኢትዮጵያዊነት ራሳቸውን ይገልጹ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች በትግራይ ብሄረተኛነት አጥምቆ አቅርቦልናል።

በወታደራዊ መስክም እነ አሉላ አባነጋን ከሞቱለት የኢትዮጵያዊነት ማማ አውርዶ ትግራይ የምትባል አንድ አነስተኛ የኢትዮጵያ አካል ጀግና አድርጎ አቅርቦልናል።አክራሪ ብሄረተኞች ከምክንያታዊነትና ከእውነት ጋር የተጣሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ህጻን ልጅ ሁሉ ነገር የእኛ ነው ብሎ ማልቀስ ይቀናቸዋል።

በዚህም ስሜት ብሄረተኛነት ባልሰፈነበት ዘመን የነበሩ ታላላቅ ሥራ ሰርተው ያለፉ ኢትዮጵያውያኖችን ሁሉ ከመቃብር አውጥተው በብሄረተኛነት ማጥመቅ ጀምረዋል። ትህነግም ሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዩቹ፤ ምሁር የተባለውንም ዘረሰናይንም ጨምሮ አክራሪ ብሄረተኛነት በሚፈጥረው የአይምሮ ህመም የተለከፉ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክ አሻራቸውን ያሰፈሩትን ትልልቅ ሰዎች ሁሉ የእኛ ናቸው በሚል የድንቁርና ውጤት በሆነ ድፍረት የእኛ ናቸው ማለት ጀምረዋል። ይህ አክራሪ ብሄረተኛነት የሚፈጥረው የአይምሮ ህመም ሰው ህሊናውን አሽቀንጥሮ በመጣል በኢአመክኖያዊነት(irrational sentiment) ስሜት እንዲመራ ያደርጋል።

መማርና ፕሮፌሰር ወይም ዶክተር መሆን ሰውን አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ ሊፈጥር ከሚችለው ህሊናቢስነትና ኢአመክንዮታዊነት (irrational sentiment) ሊያድነው አይችልም። ማርቲን ሃይደጋር የተባለው በዓለም እጅግ የታወቀ የሃያኛው ክፍለዘመን ፈላስፋና የፍራይቡርግ በሚባለው ታዋቂ የጀርመን ዩኑቨርሲቲ መምህርና የዩኑቨርሲቲው ቻንስለር ወይም ፕሬዚዳንት የነበረ ፈላስፋ ነበር። ይህ ሰው የየታዋቂዋ ሃና አረንት የምትባል በርካታ የፓለቲካ መጽሃፍቶችን የጻፈች አይሁዳዊ ምሁር አስተማሪና የፍልስና ፕሮፌሰር የነበረ ሰው ነው። ይህ ሰው በሂትለር የአገዛዝ ዘመን ዋነኛ የናዚ መንግሥት ደጋፊ ነበር።

ይህ ሰው ሂትለር የሚባል አንድ አስተሳሰቡ አደገኛ የነበረ (የጀርመን ህዝብ ምርጥ ስለሆነ ዓለምን መግዛት ይገባዋል የሚል አስተሳሰብ ያራም ትንሽ ሰው ነበረ) በፈጠረው የናዚ ድርጅት መርዘኛ የጀርመን አክራሪ ብሄረተኛነት ተማርኮ በአመክንዮታዊ አስተሳሰብ መመራትን አቁሞ የናዚ ፓርቲ ጀሌ ሆነ። ዛሬ ቀለም ቆጥረዋል በሚባሉት የትግራይ ተወላጆች ዘንድ የምናየው የጅምላ እብደትና በስሜታዊነት ተጠልፎ እውነትን ለማየት ያለመቻል ልክፍት ከዚህ ዘረኛነት ከሚፈጥረው ህሊና አሳዋሪ የሆነ የናዚና የፋሽስት ሥርዓቶች በሰፈኑባቸው ጀርመንና ጣሊያን ውስጥ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።

በጀርመን ሀገር በሺዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ተወላጆች ናዚዎችን በመቃወም ባደረጉት ትግል ህይወታቸውን ሲገብሩ፤ ባለፉት 30 ዓመታት በትግራይ ግን እንኳን በሺዎች ቀርቶ በቁጥር አንድ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ፊት ለፊት ወጥተው ወያኔዎችን ሲቃወሙ አላየንም። ይህ በዓለም ታሪክ ውስጥ ያልታየ አስገራሚ ነገር ነው።

የአክራሪ ብሄረተኛነት ስነልቦና የሚፈጥረው የፍራቻና የመከበብ፤ የጥፋት ሰለባ የመሆን ጭንቀት

ዘረሰናይ ደጋግሞ በዚህ በደማቅ የትግራይ ታሪካችንና ባህላዊ ቅርሳችን ምክንያት በሰሜንም ሆነ በደቡብ ያሉ ጎረቤቶቻችን ይቀኑብናል፤ የእኛ ነው ብለው ሊነጥቁን ይፈልጋሉ፤ ቅርሳችንን ሊያጠፉብን፤ ሊያወድሙብን ይፈልጋሉ። የታሪክ ቅርሶቻችንን አውድመዋል፤ ቤተክርስቲያኖችንና መስጊዶችን አፍርሰዋል፤ የሰማእቶቻችንን መቃብሮች ጭምር አርክሰዋል ወዘተ የሚል ክስ አስደምጧል።“ሁሉ ጥሩ ነገር የእኛ ነው” በሚል እብሪትና እብደት ውስጥ የገባው ትህነግና  በሚሊዮን የሚቆጠሩትና ይህንን ድርጅት በጭፍንነትና በጀሌነት የሚከተሉ ተከታዮቹ አክራሪ ብሄረተኛነትና በሚፈጠርው “በታሪካዊ ጠላቶቻችን ተከበናል” በሚለው የፍራቻና የጭንቀት ስሜት ውስጥ ከገቡ ሰላሳ ዓመታት አልፈዋል።

የወያኔ ተከታዮች አክራሪ ብሄረተኛነት ባስከተለባቸው በጠላት ተከበናል በሚለው የሰለባነት ስነልቦና (psychology of victimhood) ተጠቂ ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል (አንዳንዱ ለዘመናት እንደተከበቡ አድርገው ያቀርቡታል)። አንድ በዚህ የሰለባነት ስነልቦና የሚሰቃይ ድርጅትም ሆነ መሪዎቹ ተረጋግተውና ወደህሊናቸው ተመልሰው የሚገኙበትን ማህበራዊ እውነታ (appreciating and evaluating the social reality they find themselves in a balanced manner and correcting their mistakes) በሚዛናዊ ሁኔታ ለመቃኘትና ስህተቶቻቸውን ለማረም ይሳናቸዋል።

በዚህም ምክንያት ጠላት ያሉትን ከእነሱ ውጭ ያለውን ሁሉ በመወንጀል በዚያ ጠላት በሚሉት ላይ የበለጠ ጥቃትና ጥፋት ለማድረስ ይተጋሉ። ዛሬ ወያኔዎች በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየገቡ የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው። የዘረሰናይ ንግግርም ይህንን የወያኔን ድርጊት የሚያበረታታ እንጂ እንደ አንድ ራስ-በቅና ነጻ ምሁር (self-reliant and independent intellectual) ትግራይም ሆነ አጎራባች የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙበትን እውነታ በአመክንዮታዊ መንገድ ተረድቶ መፍትሄ የሚሰጥ ሆኖ አላገኘሁትም።

የዘረሰናይ በተቃርኖ የተሞላ ንግግር (the self-contradictory speech)

ዘረሰናይ ስለ አባ እስጢፋኖስና ዘርዓያቆብ ፍልስፍና ሲናገር፤ እነዚህ ሁለት እሱ የትግራይ ብቸኛ ፈርጦች አድርጎ የሳላቸውን ሁለት ግለሰቦች አስተምሮ እንኳን በተግባር ለመከተል አልሞከረም።

ስለ ዘርአያዕቆብ በተመለከተ አርሱ ከሚለው የተለየ ያቀርብኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሁን በፊት በማንም ደራሲ ያልተጻፈ “ደቂቀ ተወልደመድኅን” በሚል ርዕስ የጻፍኩትን መጽሐፍ ማንበብ ይረዳል። በመሰረቱ “ደቂቀ እስጢፋኖስ የሚለው ተሰርዞ እንደ ሌሎቹ እንደ እነ ሳይይንቲስቱ “አልበርት አነስታይን ሁሉ” “ፍልስፍና እስጢፋኖስ”  በማበል አለበት ሲል ያልሆነውን ነገር ሲያገናኝ ተደምጧል። ደቂቀ እስጢፋኖስ ማለት የደቂቀ እስጢፋኖስ ተከታዮች (ዲሳይፕልስ) ማለት ነው። ተከታዮቹ ከመነኩሴው ስነ ሕይወት ሊለዩ አይችሉም። ምክንያቱም ተከታዮቹና መኖክሴው አባ እስጢፋኖስ ያገኙትን ስቃይና ቅጣት ተያያዥና የማይነጣጠል ስለሆነ ነው።  “ባዮግራፊያቸው” ነጥሎ ማቅረብ የሰውየው ታሪክ ቁንጽል ያደርገዋል።  አነስታይን ፍርድቤት ቀርቦ ለምን ይህንን አስተማርክ ተብሎ ከተከታዮቹ ጋር (ባይኖሩትም) አልተቀጣም፤አልተሰቃየም። ዘረሰናይ ግን የሳይንስ ተመራማሪው “አልበርት አነስታይን” ጋር እንዴት ሊያያይዘው እንደቻለ ግራ የሚገባ ዕውቀት ነው።

ላንተ እጅ አልነሳም ብለው አባ እስጢፋኖስ ስለመቀጣታቸውም ያደንቀዋል። ከባህል እና ከሕግ አንጻር የተሳሳቱ መሆናቸውን ዘረሰናይ አላወቀም። በትግራይ ማሕበረሰብም ይሁን በማንኛውም ዛሬም ቢሆን “ፍርድቤትና ቤተ መንግ ት/ቤት ሕዝበ/ ቀርቶ ቤተክርስትያን ስትገናኝ፤ሃዘን ስትደርስ እንደምን አደራችሁ ሲባባሉ “እጅ በመንሳት” ትህትና ማሳየት የጨዋ፤የተማረ የትሁት ማሕበረሰብ ማሳያ ተግባር እንጂ እሳቸው ለንጉሥም፤ለፍርድቤትም እጅ አልነሳም በሚሉት ከሚገባው በላይ የለጠጡት ‘ተጻራሪ ባህል’ ነው።

በነገራችን ላይ ፋሺሰቱ ጀነራል ግራዚያኒን “ንሴብሆ” እያሉ አክሱም ማርያም ቤተከርስትያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የጥንት ነገሥታትን ዘውድና የሙሴን ጽላት ተሸክመው በወረብ በሽብሸባ እጅ የነሳን ሕዝብ ብምን ልንገልጸው ይቻለናል?

ዛሬ ዘረሰናይ የሚደግፈው ትህነግ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት አስፍኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ያጨለመ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በተለይ ከትግራይ በታች ባሉት የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሞት፤ ለመፈናቀል፤ ለስደት፤ ለመከራና ለሃዘን የዳረገ መሆኑን አይቀበልም።

 ዘረሰናይ የኩራት ምልክት ያደረገው ዘርዓያቆብ ከሞት ተነስቶ ወያኔ ትግሬዎች ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን በኢትዮጵያ ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ውድመትና ጥፋት ቢያይ ኖሮ ያፍርና ይሸማቀቅ ነበር እንጂ እንደ ዘረሰናይ ከተንቤን ተራራዎችና ዋሻዎች ወጥተው አማራንና አፋርን በመውረር ባወደሙት፤ የአራት ትውልዶች ሴቶችን ከሰማንያ አምስት ዓመት የአማራ መነኩሲት እስከ 8 ዓመት ሴት ህጻናትን በደፈሩት የትግራይ አክራሪ ብሄረተኞች ጀግንነትና አሳፋሪ ድርጊት አይኮራም ነበር።

 

ዘረሰናይ በአመክንዮታዊ አስተሳሰብ (rational philosophical thought) ላይ የተመሰረተ ፍልስፍና ያራምድ የነበረውን የፈላስፋውን የዘርዓ ያዕቆብን አስተሳሰብ ተከታይ ቢሆን ኖሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የዕውቀት መሰረት የሆኑ ትምህርት ቤቶችን፤ ዩኑቨርሲቲዎችን፤ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ የሚቆጠሩ የጤና ተቋማትን በአማራና አፋር ክልሎች ያወደሙና ያፈረሱ የትግራይ ፋሽስቶችን ድርጊት ባወገዘ ነበር።

ዘረሰናይ የአክራሪው ብሄረተኛ የትህነግ አፈቀላጤ ሆኖ እነሱ በኦሮሙማ መንግስት ውሳኔ ከተንቤን ዋሻ እንደገና አገግመው በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸሟቸውን ድርጊቶች እንደ ጀግንነት ሲቆጥር እነ ዘርዓያቆብ ከሚያስተምሩት የአመክንዮታዊነት አስተሳሰብ የወጣ ሰው መሆኑን እንኳን የተረዳ አይመስልም።ይህ ሰው ህሊና ያለውና ለሙያው እንኳን አክብሮት ያለው ሰው ቢሆን ኖሮ ትህነግ ሆን ብሎ በአማራና በአፋር ክልሎች ስላፈራሳቸው የታሪክና የባህል ቅርሶች ይጨነቅ ነበር።

ከሺህ ዓመት በላይ እድሜ ያለውን የጨጨሆ መድሃኒ ዓለምን ያፈረሱት ዘረሰናይ ከተንቤትን ዋሻዎች እንደገና አንሰራሩ የሚላቸውና በጀግንነት የሚያወድሳቸው ወያኔዎች ናቸው። ዘረሰናይ እንደ ነጻና ህሊናውን አሽቀንጥሮ እንዳልጣለ ሰው ማሰብ ቢችል ኖሮ በእነዚህ የወያኔዎች የጥፋት ድርጊቶች ያፍር ነበር እንጂ ይህንን ድርጊት የፈጸሙትን ድርጅት መሪዎች በጀግንነት ባላደነቀ ነበር። ባጭሩ ዘረሰናይ እሱ የትግራይ ተወላጅ ብሎ የሚመካበት ፈላስፋው ዘርዓያቆብ ከዛሬ አራት መቶ ዓመት ያስተማረው የአመክንዮታዊነት ፍልስፍና ትርጉም እንኳን ገብቶት ይህንን ገንቢ አመለካከት ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር በወጉ እንኳን ለመረዳት አልተጠቀመበትም። ይህ የዘረሰናይድርጊት ስለበጎነት እየሰበከ የክፋትን ድርጊት ብቻ ፈጻሚ የሆነውን ሃሰተኛ ሰባኪ እንድናስታውስ ያደርገናል።

ዘረሰናይ ቺካጎ ላይ ተቀምጦና እሱን መሰል ሰላም በሰፈነበት አሜሪካ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን ሰብስቦ “ትግራይ ትላንት ነበረች፤ አለች፤ ወደፊትም ትኖራለች” ብሎ ይመጻደቃል፤ ወጣቱ የትግራይ ትውልድ የትህነግን ፋሽስታዊ፤ የተስፋፊነት፤ የጦረኝነት፤ የዘራፊነትና የወንጀለኛነት ድርጊት እንዲቀጥሉበት ያበረታታል። በቅርቡ እንኳን ትህነግ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ በፈጸመው ወረራ የጥይት ማብረጃ አድርጎ ከላካቸው የትግራይ ተወላጆች ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ቁጥር ያላቸው ህይወታቸውን ማጣታቸው በወያኔ ሰዎች ሳይቀር እየተነገረ ባለበት ወቅት ዘረሰናይም ሆነ እሱን የመሳሰሉ የትግራይ ምሁራን ዛሬ የትግራይ ማህበረሰብ የገባበትን እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ተገንዝበው ይህን ህዝብ ከዚህ ከትህነግ የጥፋት ጎዳና የሚመለስበትን መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በዚሁ የጥፋት መንገድ ግፋ በለው እያሉት ነው

ዘረሰናይን የመሰሉ ከአመክንዮታዊነት አስተሳሰብ የራቁና በስሜትና በጥላቻ የሚመሩ ምሁራን የሚያደርጓቸው ንግግሮችና ቅስቀሳዎች የትግራይም ሆነ የእሷ አጎራባች የሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ነዋሪዎች ሰላም እንዲርቃቸው፤የመከራናየሥቃይ ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል። የትግራይ ምሁራን በአመክንዮታዊ አስተሳሰብ እንዲመሩ ዛሬም በተደጋጋሚ እጠይቃለሁ።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ (ETHIOPIAN SEMAY)