Monday, August 16, 2021

ዜጎች መንግሥትን የመቃወም እንጂ “መንግሥትን የማመን ግዴታ” ሕግመንግሥቱ ላይ የለም! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) 8/16/2021

 

ዜጎች መንግሥትን የመቃወም እንጂ “መንግሥትን የማመን ግዴታ” ሕግመንግሥቱ ላይ የለም!

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)

8/16/2021

እንደምን ሰነበታችሁ።

 በወያኔ ጦር ጫሪነት ትግራይን ለመገንጠልና ኢትዮጵያ እና አማራን ለማጥፋት እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሚገርም ሁኔታ ወደ አማራ “አውራጃዎች” ድረስ በመምጣት ጡንቻው እያዳበረ የዜጎች መፈናቀልና ሞትን በማስከተሉ ምክንያት በኦሮሞዎች የብልጽግና ኦሕዴድ መንግሥት እየተመራያለው ዳካማ የመከላከል የጦርነት በአመራሩ የብቃት ማነስ ብዙ ጉዳት ደርሷል።

ጉዳት በመድረሱ ምክንያት፤ አንዳንድ የአማራ ተወላጆችና ወጣቶች፤ በራሳቸው አካሄድ ተደራጅተው የወያኔን ጦረኛ ሃይል መመመከት እንደላበቻው ሊደራጁ ሲሞክሩ፤ የወያኔ ትግሬ አገልጋይ የነበረው ዛሬ ደግሞ “የአማራ ነገድ ወኪል” ነን የሚሉ “የኦሮሞ ኦሮሙማ” መንግሥት “አገልጋይ” ከሆኑት ከደመቀ መኮንን እና የተመስገን ጥሩነህ ድርጅት ዕውቅና ውጭ በግል ተደራጅቶ ወያኔን መውጋት አይፈቀድም ሲባል ሰምቻለሁ። ካድሬዎቻቸውም  እንዲህ ሲቆሽሹበት ታዝቤአለሁ።

አብሶ የገረመኝ የነዚህ “የመንግሥት ተብየው” ወኪሎች ውሳኔ ሳይሆን የገረመኝ፤ “ኢዜማ” ብሎ ራሱን የሚጠራ  “አማራውን ማሕበረሰብ መጤ” ብሎ የሚጠራው “ኢንተርሃሙዌው የግንቦት 7 ድርጅት” የነ ደመቀ  መኮንን ቅዠት ደግፈው “ማንም አማራ ብግል ተደራጅቶ ከመንግሥት እውቅና ጎን ከመሆን ውጭ ወያኔን በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ መዋጋት ክልክል ነው” ሲሉ እነ የሺዋስ አሰፋ እና ግርማ የተባለው (አማራ ይሁን አይሁን አላውቅም) አንዱአለም አራጌ……ድርጅት የስተላለፉት ውግዘት ከመገረም በላይ ገርሞኛል።

እነዚህ “ቃኤሎች” አብይን ለማስደሰት ሲሉ ብዙ ርቀት እንደሄዱ ባለፉት 3 አመታት ታዝበናል። ማንም ይበል ማንም ዜጎች “ቤቶቻውን፤ማሳቸውን፤ ሚስቶቻቸውን፤ ከብቶቻቸውን፤ አካባቢያቸውን፤ቤተ እምነታቸውን፤ድምበራቸውን” በግልም ይሁን በጋራ ተደራጅተው የመጣባቸውን ጠላትን የመመከትንም ሆነ የማያምኑትን መንግሥት መመከትና ከሥልጣን ማስወገድንም ጭምር ተፈጠጥሮአዊ መብታቸው ነው።

እኛ ዜጎች በየትኛውንም ዓለም ያለው ፍጡር “መንግሥት” የሚለውንና የሚያስተላልፈውን አዋጅና ቅስቀሳም ይሁን ዜና ሁሉ የመቀበል ግዴታ የለብንም።

እውነተኛ የሆነውን የዚህ የጥፋት ዘመን እንቆቅልሽ እስከዛሬ መፍታት ያልተቻለ፤ ኢትዮጵያ  በ30 አመት ውስጥ ከዓለም ሙሉ የተለዩ ሁለት ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ  መሪዎች ነግሠውባታል። መለስ ዜናዊ (ለገሰ ዜናዊ) እና አብይ አሕመድ  (አብዮት ካሳዬ)። እነዚህ ሁለቱም መሪዎች የሚመርዋቸው መንግሥታዊ ድርጅቶች (የትግራይ እና ኦሮሞ ምንግሥቶች) መሪ ሆኖው የአገሪቱን ዳር-ድምበር፤ ክብር፤ ታሪክና ሰንደቃላማ በዓለም መድረክ ፊት በድብቅም በግሃድም የሚያንቋሽሹ “ስትረንጅ” መሪዎች ናቸው።

 አገሪቱን ለማፍረስ በሕግ የተደነገጉ 44 የጎሳ ባንዴራዎች አዘጋጅቶ፤ ለሚገነጠሉ ጎሳዎች አንቀጽ አዘጋጅቶ አገር ለማፍረስና ያገሪቷን ጥንታዊ የባሕር በሮቿን ለጠላት በማስረከብ የሚኩራራ ርዕሰ ብሔር የታየው በኢትዮጵያ ብቻ ነው። አብይ አሕመድ በመለስ ዜናዊ አካሄድ እና ሕገመንግሥት የሚጓዝ የፋሺሰትና ናዚ ስልት አራማጅ ግለሰብ  ነው።ስለ ፋሺስቶች እና ናዚዎች አሰራር መጽሐፍት አንብቡ። ሰውየውም ሆነ ወያኔዎች የናዚና ፋሺስቶች የአብሮነታቸውን ርዕዮት በግልጽ በነዚህ መጽሐፍቶች ውስጥ ብግልጽ ታዩዋቸዋላችሁ።

ኦሮሞ ተብሎ በተከለለው ክልል አማራዎች ሲጨፈጨፉ አብይ አሕመድም ሆነ ሽመልስ አብዲ በሩዋንዳ ውስጥ “ሙጎኔሮ፤ ክብሊራ ፤ ኪጋሊ፤….እና የመሳሰሉ የሩዋንዳ ገጠሮችና ከተሞች  በቱትሲ  ነገድ ላይ የዘር ጭፍጨፋ የተካሄደ ያህል እነዚህ ሁለት ሰዎች  በሚያስተዳድሩት አገርና ክልል “አማራዎች ፤ ጋሞዎች፤ ክርስትያኖች እንዲሁም ጉራጌዎች..” ጭፍጨፋ ሲካሄድባቸው “ድርጅታቸው እና አንዳንዴም በግሃድ እራሳቸው በቀስቃሽ ንግግር” ተባባሪዎች ነበሩ።

አባገዳዎች ልክ እንደ ሩዋንዳ ካቶሊክ ፓስተሮች “ባሌ” ውስጥ አማራ ባሌን ለቆ እንዲወጣ አዋጅ ሲታወጅ ተባባሪዎች ነበሩ።  የቱሲዎችን ጭፍጨፋ ያካሄዱ “ዜሮ ኔትወርክ እና ቡሌት ግሩፕ” የተባሉ ኢንትረሃሙዌ ወረበሎችን አደራጆች የሚመስሉ  እንደ እነ “ጃዋር መሓመድ እና ኦነግ” የመሳሰሉ “የዘር ጭፍጨፋ መሃንዲሶች” በመንግሥት ወጪ በሪፑብሊካን ጋርድ ጠባቂዎች እንዲጠበቁ ያደረጉ “ነበሰገዳይ ወረበሎችን” ሲያሞካሹ የነበሩ ወንጀለኞች ናቸው። ስለዚህም አማራው መንግሥትን አንወጋም፤ ግን ብግል እንደራጃለን፤ አናምናችሁም ካላቸው ምክንያት አላቸው።መከራከር አያስፈልግም። በቃ! የመርሳት ሱስ አለን እንዴ!!      

በዚህ ግለሰብ መመሪያ የሚመሩ እነ ደመቀ መኮንን እነ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ተመስገን ጥሩነህ ወዘተ….ባለጊዜዎቹ እኛ ነን ስለዚህ በኛ ስር የሚሰጥ ነፃነትና መደራጀት እንጂ ከኛ ውጪ ነፃ ዜጋ የራሱ ነፃነት የለውም ይላሉ።  ‘እኛ  መንግሥት ነን” ፤ መንግሥት ማለት “ሕዝብ” ማለት ነው ይሉናል።

 ፈላስፋው ጀርመናዊው ፍሬዴሪክ ኒቺ ደግሞ  “መንግሥት የክፉዎቹ ሁሉ ክፉ አውሬ” መሆኑን ይነግረናል።  እንዲህ ይላል።

“መንግሥት ማለት በሁሉም ቋንቋዎች የሚዋሽ አፍ ነው። መንግሥት የተፈጠረው ለኒህ እልፍ አእላፍ ሰዎች ነው። ግን …  እንዴት እንዴት እንደሚያባብላቸው ብቻ ተመልከቱልኝ። ሲያላምጣቸው፤ መልሶ መላልሶ ሲያኝካቸው አያችሁልኝ?“ ይላል ‘ኒቺ’።

አዎን በአውሬዎች መሃል ተከብበን በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያላመጡ መልሰው መላልሰው አኝከውናል። “ኒቺ” መንግሥት ሲሞት ቀስተደማና ይወለዳል’ ይላል። ኢትዮጵያም በቀስተዳመና መቀነትዋ ዙርያ ብቅ ብላ እንደጥንቱ ሰንደቃላማዋን ይዛ የዚህ ስርዓት ሞት ታበስራለች።  አንድ ቀን! 

ስለዚህም በዚህ በዛሬው ጦርነት ማንኛውንም ዜጋ ወያኔን ለመውጋትም ሆነ ቤተሰቦቹን እና አካባቢውን ለመጠበቅ በግልም ይሁን በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ የወያኔን የብረት አጥር ለመስበር (ለጊዜውም ቢሆን መንግሥት ተብየውን ለመውጋት በይደር አቆይቶ) መንግሥት ተብየውን እስካልወጋ ድረስ የመደራጀት መብቱ ተፈጥሮአዊ እንጂ “አፍግፍግ” እያለ ሕዝብን ለጥቃት አጋልጦ፤ ጦሩን እያስማረከ የሚያስፈጅ እና ጠላትን ከሚያስታጥቅ መንግሥት ጎን የመሰለፍ ግድቴ የለውም።

የአማራ ገበሬና ወጣት ተማሪ በጎበዝ አለቃ ልደራጅ ካለ ጥሩ ተደራጅቶ አገሩን ይከላከል። መንግሥት አስፈላጊውን ትጥቅ እና ስንቅ ጫማና ብርድልብስ ከለገሰው እሰየው፤ ካልሆነ ግን እንደ ጥንቱ ወላጅ አርበኞች ወላጆቻችን ምንም የሚያነጥፈው አንሶላም ሆነ ብርድልብስ ባይኖሮውም በደረቁ መሬት ላይ በተከፈተው የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የተዘረጉትን የወላጆቹ ኮከቦች ደርቦ ኢትዮጵያን የመከላከል መብቱ ተፈጥሮአዊ ነው።

ዜጎች መንግሥትን የመቃወም እንጂ “መንግሥትን የማመን ግዴታ” ሕግመንግሥቱ ላይ የለም!

አመሰግናለሁ

ኢትዮጵያ ለዘላም ትኑር!

ጌታቸው ረዳ Ethio Semay