Tuesday, January 20, 2009

የትግራይ ሕዝብ ሆይ!

የትግራይ ሕዝብ ሆይ! ገዛኢ ረዳ አቶ ገዛ ራዳ፡ ወያነ ትግራይ በእሳት እና በፈላ ዉሃ ሰዉነታቸዉን በማቃጠል ኢሰብአዊ ምርመራ አካሂዶባቸዉ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸዉ አንዱ የትግራይ ተወላጅ ናቸዉ። ከእኝህ አባት አዛዉንት ጋር በትግርኛ የተደረገዉ የቴሌፎን ቃለ ምልልስ፤ በቅርቡ ለሕዝብ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለንባብ ስለሚቀርብ-እንድትከታተሉን እያሳሰብኩ፦ ከዚህ ቀጥሎ አቶ ገዛኢ ረዳ ለትግራይ ሕዝብ ያስተላለፉትን ራሳቸዉ የጻፉትን አጭር መልዕክት ሕዝቡ እንዲያነብበዉ አስተላልፈናል።

የትግራይ ሕዝብ ሆይ! ወያኔዎች ትግራይን ነጻ እናወጣለን በማለት አዛዉንቶችን፤ታዳጊ ህጻናትን፤ የዜጎች እና የአገሪቱን ክብርን በተለያየ መልክ እና በተለያየ ጊዜ የተዳፈሩ መሆናቸዉን ከእንደ እኔ የመሳሰሉት የወያኔ አረመኔ ጭካኔ የደረሰባቸዉ ሰለባዎች የሚሰወር አይደለም።
የትግራይ ህዝብ ሆይ!
ስለ ወያኔዎች አረመኔነት ከእኔ እና እንደ እኔ የመሳሰሉት የዓይን ምስክሮች በላይ ሌላ ሰዉ ሊነግርህ ከቶ አይችልም። ቢሞከርም ሙሉዉን አረመኔ ገበናቸዉ እንደ ራሳችን ሆኖ ጭካኔአቸዉን እና ያደረስቡን ስቃይ ዘርዝሮ የሚያስረዳህ ክፍል አይሆንም።ለዚህም ነዉ ቃሌ ለሕዝብ እንዳስተላልፍና ስሞታየም በአንዳንድ የተባረኩ ኢትዮጵያዉያን የትግራይ ልጆች በኩል እንድታዳምጡት የፈለግኩት።
የደረሰብንን ግፍ ለሕዝብ እና ለዓለም መግለጽ አልቻልንም። ለዓመታት በዉጭ አገር ብንኖርም የደረሰብንን ኢሰብአዊ ግፍ ለዓለም የሚያስተጋቡልን ወገኖቻችን ካሉ በጣም እጅግ ጥቂት እና ከሁለት ሦስት የተባረኩ ሰዎች በላይ አይሆኑም።እነሱን እያመሰገንኩ የተቀረዉ ምሁር ግን በእኛ በዜጎች ላይ የደረሰብን ግፍ ሊመለከትልን ፍላጎቱም ጥረቱም አላሳየም።ለምን?
የትግራይ ህዝብ ሆይ! በስምህ እየነገዱ ነጻ አዉጥተንሃል የሚሉህ ታሪክ አርካሽ ጥቂት ግለሰቦች፤ በጣምኑ ደፍረዉሃል! በጣም ታግሰሃቸዋል። ጀግንነትህ አትንኩኝ ባይነትህ እንዴት አስቀማኸዉ? በሚለዉ ጥያቄ ልጀምር።የሞቀዉ ወኔህንስ እንዴት እና ለምንስ በረደ? ቁጡነትህ እንዴት ዛለ? “ወይ ኣነ!!!) (እኔ ወንዱ!!!) የሚለዉን የቁጣ ስሜትህ ወዴት ጠፋ?
ቆፍጣና ቀበቶህስ እንዴት በእነዚህ ሊላላ ቻለ? ወደ ሗላ መለስ ብለህ በ እነዚህ ጉዶች የተደረጉት ነዉራማ ስራዎች ብታስታዉሰዉ-እጅግ አሳፊሪ ተግባሮች ተፈጽመዋል።ሃይማኖትህ ደፍረዉታል፡ቅዱስ ገዳማት እና ቤተክርስትያናትን የፖለቲካ መስበኪያ፤ የዘፈን እና የመጨፈሪያ መድረክ ሆነዉ ሲራከሱ፡የቤተክርስትያን ቅዱስ መጋረጃ እየተገነጠሉ የጨዉ እና የበርበሬ መቋጠሪያ ሲሆን፤ቀሳዉስት እና መነኮሳት ሲገደሉ፤ ጠመንጃ አንግተዉ በግድ ወደ ጦር ሜዳ እንዲሄዱ እና መንፈሳዊ መመሪያቸዉን እንዲጥሱ ተደርጎ የሃይማኖት ማአዲዎችህ በየምክንያቱ ተመናምነዉ እንዲጠፉ እርስ በርስ እንዲጋጩ ተደርጓል።
ይህ ሁሉ ዝምታህ አስከመቸ ነዉ? ይህ ሁሉ ቻይነት የወንድ ሃሞትክን ተሟጥጦ ነዉ ወይስ መጠን የሌለዉ ቻይነትን ማሳየት ነዉ? ምን ያህል የወንድነት ሃሞትህ ቢፈስ ነዉ ከማሃልህ ዉስጥ እየኖሩ እነዚህ አረመኔዎች እንዲህ እያፌዙ የሚኖሩት? ለመሆኑ- የምትወዳትን የቃል ኪዳን ሚሰትህን ሲነጥቁህ ዝም ማለት እንዴት አስቻለህ? ሽማግሌ አባትህ እናትህ ወንድም እህት አጎትህ አክስትህ ጓደኛህ ጎረቤትህ በኢሰብአዊ ጭካኔ ተደብድቦ በፈላ ዉሃ እራሱ ላይ እየተደፋበት፤ በእሳት ተቃጥሎ፤ ተለብልቦ፤ ሽባ ሆኖ ተሰቃይቶ፤ ለሞት እና ለአካለ ጎዶሎነት ሲዳርጉት እያየህ ታሪካቸዉን በጀሮህ እየሰማህ ዝምታዉ ምን ይሆን? አዛዉንት የሚደፍሩ፤ ህጻናትን የሚገድሉ፤ እነዚህ አረመኔዎች በማሃልህ ቁጭ ብለዉ፤ ተጠያቂነት በሌለዉ ነጻነት ተደላድለዉ ሲያፌዙብን ዝምታዉስ አስከመቸ ሊቀጥል ይሆን?
ዛሬ ከሃላፊነት ቢሸሹ እና ቢደበቁም- ነገ “መስከረም-ይጠባል!” ብርሃን ሲታይ ከእግዚአብሔር እና ከፍትሕ የሚያመልጥ ከቶ የለምና አስከዛዉ ግን በእኛ በትግራይ ተወላጆች ላይ በወያኔዎች የተፈጸመብንን አረመኔአዊ ግፍ ሕዝቡ እንዲያዉቀዉ እና ፍትሕ እንዲጠይቅልን እና እነዲተባበረን መልእክታችንን እናስተላልፋለን። ኢትዮጵያ በነጻነት ለዘላለም ትኑር ገዛኢ ረዳ አቶ ገዛኢ ረዳን ለማነጋገር ለማንኛዉም ጥያቄ መልስ ለማግኘት “የኢትዮጵያ ሰማይ” የሕዋ ሰሌዳ ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ጌታቸዉ ረዳን በሚከተለዉ አድራሻ በመገናኘት መልስ ማግኘት ይቻላል። getachre@aol.com http://www.Ethiopiansemay.blogspot.com

የትግራይ ሕዝብ ሆይ! ከአቶ ገዛኢ ረዳ