Thursday, May 9, 2019

ይድረስ ለወሰንና የማንነት ኮሚሽን! የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ምን ዓይነት የመንግሥት አደረጃጀት ብንከተል ይጠቅማል?


                   


ይድረስ ለወሰንና የማንነት ኮሚሽን!
የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ምን ዓይነት የመንግሥት አደረጃጀት ብንከተል ይጠቅማል?

  • ዛሬ ባለንበት ነባራዊ የፖለቲካ አየር በዓለም ካሉት የመንግሥት አደረጃጀት ቅርጾች ማለትም ከአሐዳዊነትና ከፌደራሊዝም የቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እና ዕኩልነት እንደሚጠቅም የሁለቱም የመንግሥት ቅርጾች ጥቅምና ጉዳት ታሪካዊና ፖለቲካዊ ፋይዳዎች በግልጽ ተብራርተው የቱ ጠቃሚ እንደሆነ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት ሳያገኝ በፖለቲካ ድርጅቶች ጩኸት ፌደራሊዝም ብቸኛው እና ትክክለኛው አዋጭ የመንግሥት አደረጃጀት እንደሆነ ያለድምፅ! ድምፅ የተሰጠበት ያህል ሲስተጋባ ይሰማል:: ይህ ግን ውጤቱ “ የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበልጥ” ከሚለው የቆየ አባባል የተለየ ይሆናል ለማለት ያስቸግራል::
  •  
  • አስቸጋሪ የሚያደርገውም ሥልጣን የሕዝብ ነው ብለን ካመን  ሕዝቡ የትኛው የመንግሥት አደረጃጀት ቅርጽ  ነባር ባህሉን  ነባር መልካም ግንኙነቱን  ታሪካዊና ባህላዊ ቁርኝቱን  ተከታታይነት ልማትና አንድነቱን  የበለጠ ማስጠበቅና ማረጋገጥ የሚችለው በምን መልክ ሥርዓተ መንግሥቱ ቢደራጅ  ነው ብሎ የግራ የቀኙን ሰምቶና በትክክል ተረድቶ በሕዝበ ውሳኔ እንዲወስን ዕድል የተሰጠው አለመሆን ነው::
  •  
  • በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ሁለት እና ከሁለት በላይ የሆኑ ነገሮች ለምርጫ ሲቀርቡ ምርጫው ቀድሞ ታሳቢ የሚያደርገው ባለፉ ዘመኖች ሕዝቡ በመልካምነት ይዞአቸው የዘለቁትን መልካም ዕሴቶች  ባህሎች  ግንኙነቶች  ታሪኮች ወጎችና ትውፊቶች ነው:: ከዚህ አንፃር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ተጠብቆ መዝለቅ የሚሹ እና ሥልጣንም የሕዝብ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖችና ኃይሎች በጥላቻ ፖለቲካ የተመረዙ ቡድኖች  ለኢትዮጵያ አንድነት መቀጠል የሚበጀው “ፌደራሊዝም” ነው ብለው በሥፋት ያሰራጩትን ፕሮፓጋንዳ እንደ ሐቅ ተቀብሎ ስለፌደራሊዝም ከመዘመራችን በፊት የሁለቱን የመንግሥት አደረጃጀት ቅርጾች ጥቅም ጉዳትና አስፈላጊነት ውይይት ሊደረግበትና ሕዝቡ ይሁንታውን ሊሰጥበት ይገባል::
  •  
  • የአሀዳዊና ፌደራሉዝም አማራጮች ለሕዝብ በሚገባው አኩዋሓን ተነግሮትና ውይይት ተካሂዶበት ሕዝባችን ፌደራሊዝም ይበጀኛል ካለ  የፌደራል አካል መንግሥታቶቹ መመሥረቻ ቀመር ምን መሆን እንዳለበት የጋራ መግባቢያ ሀሳብ መኖር ይኖርበታል::   የፌደራል አደረጃጀትን ሕዝቡ ከተቀበለ ወይም ፖለቲከኞቹ ባሻቸው መልኩ ከወሰኑ የአገሪቱን አንድነት ተከታታይነት ጠብቆ ለመዝለቅ እንዲቻል የሚከተሉትን መሥፈርቶች ሥራ ላይ ቢውሉ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል::
  • እነዚህም:-

1.     ነገዳዊ መመዘኛዎች
ü የነገዶች ብዛት እና ሥርጭት
ü የቁዋንቁዋ አንድነትና ልዩነት
ü የባህል ተመሳሳይነትና ልዩነት
ü የነገዶች ታሪክ /አንድነትና ግጭቶች ውኅደትና መገፋፋት!
2.    ኢኮኖሚያዊና መልከዓምድራዊ ተያያዥነት
ü የሕዝብ ብዛትና የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሀብት ተመጣጣኝነት
ü የሀብት ልዩነትና ተመሳሳይነት
ü የልማት ማዕከሎች ዓይነትና መጠን
ü የኢኮኖሚ መተሳሰርና የገበያ ቁርኝት
ü የልማት ወይም የዕድገት ደረጃ
3.    የአስተዳደርና የደኅንነት አገልግሎት ቅልጥፍና እና ጥራት
ü የአስተዳደር አካሎች ሥፋትና ቅርጽ
ü ለልማት ተግባሮች አመችነትና ብቃት ያላቸው አመችነት
ü ለማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች አቅርቦትና አደረጃጀት ያላቸው አመቺነት
ü ከሌሎች አካሎች ጋር ለሚመሠረት ግንኙነት ያለው አመቺነት
4.    የመከላከያና የደኅንነት ጥበቃ አስተማማኝነት
ü የአስተዳደር አካባቢውን ከውስጥና ከውጭ ለሚነሱ ጥቃቶች ለመከላከልና ደኅንነቱን ለማስጠበቅ ያለው አመቺነት
ü ለጠረፍና እጅግ ሁዋላ ቀር ለሆኑ አካባቢዎች ልዩ ሁኔታን ግምት ውስጥ ማስገባት
ü የየአካላቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና ለዚሁ ተጨባጭ መፍትሔት የሚሰጥ

እዚህን መሥፈርቶች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ዛሬ ያለውን በቁዋንቁዋ ብቸኛ መሥፈርት የታጠረውን “ክልል” ንደን  ለአንድነታችን የተሻለ ፌደራላዊ ቅርጽ የያዘ አደረጃጀት እንደሚኖረን ይታመናል::

ለዚህም አደረጃጀት ከሚከተሉት የተሻለውን በሕዝብ ማስወሰን ይበጃል

አማራጭ አንድ:-
1       የጥንቱን ትግራ ክፍለሀገር (ከዚህ ላይ የጥንቱ ክፍለ-ሀገር ስንል በንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ የመጨረሻ ዘመን  ጠቅላይ ግዛት ይባሉ የነበሩትን ወይም  በደርግ አገዛዝ የመጀመሪያዎቹ የአገዛዝ ዘመን ክፍለ-ሀገር ይባሉ የነበሩትን ለማመልከት መሆኑ ግንዛቤ ያዝ)
2     የጥንቱ ወሎ ክፍለሀገር (ይህም ዛሬ አሰብ ድሮ አውሳ አውራጃ ይባል የነበረውን 12ቱን የወሎ አውራጃዎች የሚይዘውን ነው)
3     የጥንቱ ሸዋ እና አርሲ ክፍለሀገሮች (ይህም 11ዱን የሸዋ አውራጃዎች እና 3ቱን የአርሲ አውራጃዎች ባንድነት የያዘ ማለት ነው)
4     የጥንቱን ጎንደርና ጎጃም ክፍለ ሀገሮች
5     የጥንቱን ኢሉባቡርና ከፋ ክፍለ ሀገሮች
6     የጥንቱን ሐረርጌና ባሌ ክፍለ ሀገሮች (ይህ ማለት ዛሬ ሶማሊያ የሚባለውን የኦጋዴንን አውራጃ ያካተተ ማለት ነው)
7     የጥንቱን ሲዳሞና ጋሞጎፋ ክፍለሀገሮች
8     የጥንቱ ወለጋ ክፍለ ሀገር
አማራጭ ሁለት:-
1       የጥንቱ ትግራይ ክፍለ ሀገር
2     የጥንቱን ጎጃም ክፍለ ሀገር  የጥንቱን ጎንደር ክፍለ ሀገርና ደቡብ ወሎ ዞንን ባንድ በማድረግ
3     የጥንቱን ሸዋ ክፍለ ሀገር ከጥንቱ አርሲ እና ባሌ ክፍለ ሀገርና ሰሜን ወሎ ዞን በመጨመር
4     የጥንቱ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር
5     የጥንቱ ወለጋ ኢሉባቡር እና ከፋ ክፍለ ሀገሮች
6     የጥንቱ ሲዳሞ እና ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገሮች
አማራጭ ሦስት:-
§  በንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ዘመን የነበሩትን 13 ጠቅላይ ግዛቶች እያንዳንዳቸውን የፌደራል አካል ማድረግ ይህም ማለት 13 የአስተዳድር  አካላት መመሥረት ማለት ነው::
አማራጭ አራት:-
§  በደርግ የመጨረሻው ዘመን ወይም በኢሕዲሪ ሕገ-መንግሥት የተዋቀሩትን 24 አስተዳደራዊ አካባቢዎችና አምስት የራስ ገዝ አካባቢዎችን በድምሩ 29 የፌደራል መንግሥቱ አባል ማድረግ

ሌሎች አማራጮችም ሊኖሩ ይችላሉ:: ዋናው ነገር የሕዝቡን ነባር ትስስር  የአብሮነት ስሜት  የባህል እና የኢኮኖሚ ቁርኝት የበለጠ በተከታታይ ሊያዳብር የሚችል መሆኑ ማረጋገጥና ይህም በአብዛኛው ሕዝብ የተደገፈ መሆኑን ማረጋገጥ ነው::