Saturday, April 23, 2011

እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ!!!!!!


እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ!!!!!! ጌታቸው ረዳ
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተከስቶ በገሃድ በመታየት በመንግሥታት መሪዎችና በሕዝቡ መሃልም ፈጣሪያቸውን እረስተው ብዙ ግፍና ኩነኔ ይፈጸም ስለነበር፤ ከኃጢያታችን ለመዳን ይረዳን ዘንድ ልቦና እና ብልሕነት ረጋ ያለ ህይወት፤ለጋስነትና መተሳሰብ እንዲኖር ካለ እኛ ፈጣሪ የለም በማለት ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ መሪዎችና ፍጡራን ለማስታገስና ለማስተማር የጌታነቱን ክብርና ኃያልነት ለኛ ሲል በግፈኞች ግርፋትና የስቅላት ፍርድ ተሰቃይቶ በፈጣሪ መመሪያ እየተመሩ ለሕግ በመታዘዝ ሕዝቦች ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ያስተማረበት ክስተት ስለነበር፤ እኛም የሱን ፈለግ በመከተል አስተዋዩች፤ሰላማዊና፤የዋሃን እንድንሆን 50ቀኖች በመፆም ረዢምና ፈታኝ የሥጋ ማስታገስ መስዋዕት በማድረግ በዛ ፈተኝ የመለኮት ፈተና ጾማችሁ ፋሲካ ለተፈሰከላችሁ ክርስትያኖች እንኳን ደስ ያላችሁ! መልካም ፋሲካ!! በሚቀጥለው ጊዜ ፖቲካው በስፋት ስለምገባበት ላሁኑ ግን ለዚህ በዓል ስትሉ ፈታኝ የጾም ትግል በማድረግ በሰይጣን ላይ ድል ለተቀዳጃችሁ ወገኖች ድጋፍ እንዲሆን የተዋህዶ ትርጉም በማይገባ ትርጉም በመግባት እምነታችሁን ለማሳነስ ለሚጥሩ ሃጢአን የተዋህዶ ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ የማውቃትንና ሊቃውንት ያስተማሩትን በመመርኮዝ ተዋህዶ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ በመመለስ የተዋህዶ ትርጉም በቀላሉ አስረድቼ እንኳን ደስ አላችሁ ብየ ልደምድም ነው። ክርስቶስ ማን ነው? ተዋህዶ ምን ማለት ነው? በተዋህዶ የከበረ የእግዚአብሔር ልጅ፤ሲባል ትሰማላችሁ፤ በተዋህዶ የከበረ ሲባል ትሰማላችሁ፦ ይሄ ምን ማለት ነው? የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኖ የታየበት ምስጢር ማለት ነው። አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ይሄን አባባል ሲያናንቁት ሲቀልዱ ይደመጣሉ/ይነባበሉ። እንዴት ሰው አምላክ ይሆናል? እንዴት አምላክ ሰው ይሆናል ሲሉ ይሳለቃሉ። ነገሮችን ለመመርመር ፍለስፍናዎችና ሃይማኖቶች በብስለት በትእግስት ካላጤኑት ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ የሚሉ አባባል ምን ማለት ነው? ባጭሩ ላመስረዳት እነሆ። የሃይማኖት ኣባቶች እንዲህ ይላሉ፦ አምላክ ሰው የሆነበት ሰው አምላክ የሆነበት ምስጢር የተከናወነበት፤የተፈጸመበት ነው። ሁለት አካል የሚባለው አምላካዊው አካልና ሰዋዊው አካል ነው። አምላካዊው አካል “ምሉዕ በኩልሔ (በዓለም ሁሉ የሞላ ነው) ውሱን አይደለም፤አይዳሰስም፤ አይታይም፤አይጨበጥም። የሰው አካል ግን ይጨበታል ይዳሰሳል ይታያል፤ ውሱን ነው። የማይወሰነው አምላክ ነው። የማይወሰነው አምላካዊ አካል የሚወሰነውን የሰው አካል የራሱ ገንዘብ/ባሕሪ አደረገው። ተዋህዶ የሚለው ቃል አባቶቻችን ከጥንት ጀምሮ ይህንን ለማስረዳት በቀላል ዘዴ ሲጠቀሙበት የነበረውን ምሳሌ ያነበብኩትን ልጥቀስላችሁ።ለምሳሌ ብረትን ወስዳችሁ እሳት ውስጥ ብትከቱት ብረቱ ብረትነቱን አይቀይርም። ነገር ግን የእሳቱን ባሕሪ በመወሀዱ የሚያቃጥል ሆኖአል። እንዲህ ደግሞ ብረቱን ስታዩት “ፍም”ነው። አሁንም የብረቱን አካል አካሉ አድርጐ በመወሀዱ ሙሉ ብረቱ ላይ ታዩታላችሁ። እኛም ተዋህዶ የምንለው እንዲህ ነው። ከሁለት አካል ከሁለት ባሕሪ አንድ ባሕሪይ የተነሳት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። መንግሥት እንኳ ባቅሙ ሰላዩችን በማሰራጨት ሁለት ባሕሪ ያለቸው ሰዎችን ለሚፈልጉት ተልዕኮ እንዲሰልሉ እያደረገ ሁሉም ማድረግ የማይሳነው ጌታ እየሱስ ሰው ተመስሎ የማይጠጋበት/የማይታይበት ምን ምክንያት አለ? እውቅ ታዋናያኖች እንኳ ባቅማቸው ኮስመቲክ/ጭምብል በማጥለቅ ማንነታቸውን ሸፍነው የሌላ ሰው ምስል ለመምሰል ፊታቸውን በቅባትና በዱቄት ለውጠው ገበያ ላይ ይታያሉ? ሰው አያውቃቸውም። ለምን ይመስላችኃል? ትምህርቱን ከማን ነው ያገኙት? ጌታም መጀመሪያ ሰው ተመስሎ ሲያድግ ሲንቀሳቀስ ማን መሆኑን ያወቀው ሰው አልነበረም?ለማኝ ተመስየ፤ ሕፃን ተመስየ፤ ሽማግሌና ጐረምሳ ተምስየ ከማሃላችሁ እንቀሳቀሳለሁ ሲል አንብባችሁ አታወቁም? ወላጆቻችን እንደዚያ ነው ያስተማሩን። ለዚህም ነው እኮ ስታረዝ አልብሰችሁኛል? ስጠማ አጠጥታችሁኛል? ስቸገር እረድታችሁኛል? ስታመም ጠይቃችሁኛል? ሲል ያስተማረው። ትርጉሙ ምን ይመስላችኃል?በቀላሉ ማግኘት ካቃታችሁ ፤ ታምራቱና ትምሕርቱን እንዲገለጽላችሁ ቀላሉን ነገር “መጸለይና መስገድ”ነው፤ ይላሉ የተባረኩ ወላጆቻችን።ፊደል ሲቆጠር በቀላሉ እንደማይገን ሁሉ ይህ ከባድና ጥልቅ እውቀት ለማወቅም ትዕግስትና ከፈጣሪ ጋር ግንኙነትን ይጠይቃልና። ፈተናውን ለማለፍ፤ መመራመርና ማጥናት ያስፈልጋል!በተለይ ደግሞ ቅን እና የዋህነትን መከተል ዓይነተኛ የባሕሪው መለኪያ ጎዳናው ነው። እንግዲህ ሰብዓ ሰገል ወድቀው የሰገዱለትን ጌታ ኰቴአቸውን በመከተል እናንተም በጾም እና በስግዳን ከፈጣሪያችሁ ጋር ስትነጋገሩ የሰነበታችሁ ምዕመናን ሁሉ እንኳን ለፋሲካው በዓል ከመላ ቤተሰቦቸአችሁና ከምትወዷቸው ወዳጆቻችሁ በደስታ አደረሳችሁ። ሃሌ ሉያ! አሜን! አምላክ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ በጥበቡ ኢትዩጵያን ይጠብቅ። ጌታቸው ረዳ ኢትዩጵያን ሰማይ አዘጋጅ።Getachre@aol.com http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/