ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የመሪዎቻችን ባሕሪ
ጌታቸዉ ረዳ
በሕዳር ወር 2000/ ማርች2010 በአሜሪካ ሃገር በሳንሆዘ ከተማ በካሊፎርኒያ ክፍለሃገር ኗሪ በሆነዉ ቅን አሳቢዉ እና አገር ወዳዱ በአቶ አበበ ገላጋይ አነሳሽነት የተጀመረዉ የኢትዬጵያዊያንን እና የኤርትራዊያን የሕዝብ ለሕዝብ ማገናኘት ሃሳብ አብረዉት ሌት ተቀን በገንዘብና በጉልበት ጊዜያቸዉን ሰዉተዉ የሱን ተነሳሺነት ቅን አሳብ በመደገፍ በአሜሪካ በሳንሆዜ ከተማ በካሊፎረኒያ ክ/ሃገር በኢትዬጵያ እና በ ኤርትራዊያን ዜጎች መሃል የሞቀ ወንድማዊ እና እህትማዊ የሃሳብ ልዉዉጥ እንዲካሄድ እንዲሳካ የረዱትን ኩሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ወንድሞች ሳላመሰግን አላልፍም። አበሮ ከዚህ ጋር ጥሪያችንን አክብረዉ ከተለያዩ ያሜሪካ ከተሞች እና የዓለም አገሮች ተጉዘዉ በጉባዉ የተገኙትን ተናጋሪ ምሁራንና የጉባዉ ምንነት ለማዳመጥ በስብሰባዉ ተገኙ እንግዶች ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸዉ እያልኩ የተዘጋጀዉ የሁለቱም ወንድማማች/እህትማማች ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጉባኤ ለሦስት ቀናት የቆየ የምሁራን እና የሕዝብ ለሕዝብ የሃሳብ ልዉዉጥ መደረጉ (የትግርኛዉ ቪ ኦ ኤ በስተቀር- “ዉስጡ ለቄስ(?)” አብዛኛዎቹ ማለትም ባሜሪካ ድምፅ ያማርኛዉ ክፍል እና የዶቼቬለ አማርኛዉ ክፍል እንደዚሁም በሕዋዉ የዜና ሰሌዳ ማለትም በኢንቴርኔት የዘገቡትን ሁሉ አብሬ እያመሰገንኩ ስለ አዘጋጆቹ እና ለተቀደሰዉ ተግባር ትብብራቸዉን ላሳዩ ሁሉ ኮሚቴዉ ልዩ ምስጋና ለማስተላለፍ በራሱ ስም ስለሚያወጣ ያንን ለኮሚቴዉ እየተዉኩ
ከጉባኤዉ የቀሰምኩትን “ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የዘመናት ችግራችን” በሚል ርዕስ ልንነጋገርበት ያቀረብኩትን ርዕስ እነሆ።
ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የመሪዎቻችን ባሕሪ
ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com
በኤርትራና በኢትዬጵያ ሕዝብ መሃል ለዘመናት የቀጠለ ደም ያፋሰሰ ለረዢም ጊዜ የተካሄደ አሁንም እየቀጠለ ያለዉ ጎጂ ጦርነት ሁላችንም አሰልችቶን አንድ ምዕራፍ ላይ መቆም እንዳለበት የጦርነቱና የግጭቱ ሰለባ የሆኑት ሁለቱም ዜጎች ወደ መስማማቱ ላይ እንደሉ ሁኔታዎች ያሳያሉ።ግጭቱ ዛሬም ነገም ተነገ ወዲያም ለዘላለም እንዲቀጥል በሁለቱም በኩል ያሉት በመንግሥት የተሰየሙ የሻዕቢያና የወያኔ መሪዎች ምኞትና ሴራ ቢሆንም ሰፊዉ የሁለቱ ማሕበረሰብ ዜጎች ከግጭቱ የተጠቀሙት አንዳችም አመርቂ ዉጤት ስላላዩበት፤ግጭቱ ቢቀጥል የትም እንደማያደርሳቸዉ ስለተገነዘቡ እልባት እንዲደረግበት በሰላም እና በመነገጋገር ችግራቸዉን እንዲወያዩ አዲስ ምዕራፍ ይሄዉ ጀምረዋል።
እንደሚታወቀዉ በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ካጼ ዮሃንስ ዘመን ጀምሮ በኤርትራ በኩል የገቡ በዉጭ ተስፋፊ ሃይላት ምክንያት የተጠነሰሰዉ የሁለቱን ሕዝቦች የርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ሴራ ፍጻሜ ግቡን እንዲመታ በተዋረድ የጀብሃ፤የሻዕቢያ እና የወያኔ መሪዎች ሴራዉን በማስፈጸም በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል።በሌላ በኩል ችግሩ እንዲባባስ እና እንዚህ ክፍሎች ለአመጽ እንዲነሳሱ ምክንያት እና አመቺ ሁኔታ የፈጠሩላቸዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩ (አሁንም ያለዉ) የተለያዩ ስርዓቶችም ለግጭቱ መባባስ እኩል ድርሻ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ግጭቱ ከተራ ጦርነት አልፎ ሕዝቦች በጎሳ እና በቋንቋ እንዲናናቁ ተደርጎ ለጥላቻ ፖለቲካ ተዳርገዉ የማንነታቸዉ መታወቂያ የሆነዉን “ሰብአዊነትን” ጥለዉ “የአዉሬነት” ባህሪ በመላበስ እንደጠላት በጎሪጥ እየተያየ ቂም ቋጥሮ ለዘላም የማይበርድ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ጥላቻ እንዲይዙ በመደረጉ ከዚያ አዉዳሚ ግጭት እና የጥላቻ አዙሪት እንዴት መዉጣት እንደሚቻል በጉባዉ ላይ የተጋበዙ ወደ 10 ያህሉ ኤርትራዉያንና ኢትዬጵያዊያን ምሁራን ያበረከቱት የመፍትሄ ሃሳብ ከላይ የተጠቀሱት የሚዲያ ዘገቢዎች የተነተኑዋቸዉን የተጋበዙ ምሁራን ያቀረቡዋቸዉ የመፍትሄ ሃሳቦች እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለየት ባለ መልክ ሚዲያዎቹ ልብ ያላሉት (በስፋት ያልተነተንዋቸዉ) በጉባኤዉ ላይ የቀረቡ የሁለቱ ምሁራን ማለትም የፕሮፌሰር ተስፋጽየን መድሃኔ (የትዉልድ መንደር ሓማሴን) እንዲሁም ምሁሩና አምደኛዉ አቶ የሱፍ ያሲን (ትዉልድ መንደር ዓሰብ-ዓፋር) ለጉባዉ ያቀረቧቸዉ ሃሳቦች ለግጭቱ የመፍትሄ ሃሳብ ምን መሆን እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ግጭቱ መፍትሄ እንዳያገኝ ደንቃራ/እንቀፋት ሆኖ ለዘመናት እንዲቀጥል ምክንያት የሆነ ያላወቅነዉ የመሪዎቻችን ባሕሪ ሕዝቡ እንዲመረምራቸዉ ጠቁመዋል። በዚህ ምዕራፍ 1 ላይ የምንመለከተዉ የፕሮፌሰር ተስፋጽየን መድሃኔ ሲሆን፤ በምዕራፍ 2 (በሚቀጥለዉ ሳምንት ይቀርባል) የምንመለከተዉ ደግሞ አቶ ያሲን የሱፍ “የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች-ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ሚና” በሚል ርዕስ ለጉባዉ የላኩትን ወረቀት እንመለከታለን።
ፕሮፌሰር ተስፋጽየን ከላይ የጠቀሱት ካንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የሚሉትን በምሳሌ ሲጠቅሱ
“ለምሳሌ ፕሮፈሰር ያዕቆብ ሃይለማርያም ባለፈው ታህሳስ ወር በታተመ ጽሁፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባለፉት 30 ዓመታት ልዩነቶቻቸውን በመግባባት ፈትተው ሊጓዙ አልቻሉም፣ የዚህ ችግርና ውድቀት ምክንያትም የአጀማመራቸው ሂደት በማርክሰ-ሌኒንነት የተቀረጸ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ከዚህ ጋር በማያያዝም የኛን ትውልድ፡ አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት ኢህአደግን ጨምሮ፡ ያሳደገ ማርክሰ-ለኒኒዝም፡ ጨዋነት እና በድርድር ስምምነት ላይ መድረስ፡ እምብዛም የማይፈቅድ አመለካከት መሆኑን ይገልጻሉ።”
በማለት ዶ/ር ያቆብ ያቀረቡትን አመለካከት ፕሮፌሰር ተስፋጽየን በመጠኑ ቢጋሩትም የችግሩ መንስኤ ያ እንዳልሆነ ሲገልጹ እንዲህ በማለት ይገልጹታል
“ችግሮቻችን ከ60ዎቹ በፊት የተነሱ በመሆናቸው፤ ያጠፉትና ስህተት የፈጸሙትም ማርክሲሰት ነን ባዮች ብቻ ሳይሆኑ፡ ማርክሲስት ያልሆኑና ጸረ-ማርክሲስት አቋም የነበራቸውም ጭምር ስለሆኑ፡ ያስተሳሰብ ችግሮቻችን መንስኤ ወይም መግለጫ ምን እንደሆነ ለመረዳት ከማርክሳዊ ርዕዮተ-ዓለም ውጪ በሆኑ ዘርፎች ማፈላለግ ይኖርብናል።” ሲሉ ለምሁራንም ሆነ ለኛ ለተራ ዜጎች ይህ አዲስ ጀሮ የሆነዉ የችግራችን ዋናዉ እምብርት ለመቃኘት እንዲመቸን ወደ ምርምሩ የህሊና አቅታጫቸዉ እንድናተኩርበት የችግራችን ምንነት እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፤
“ …ችግራችን "ማኒኪያዊ አመለካክት" ነዉ” ካሉ በሗላ - የመኒከይዝም ባሕሪ ሲገልጹም “
ማኒከዪዝም ፍጹማዊ የሆነ፡ ሁሉንም ነገር ከሁለት ተጻራሪ መርሆዎች ወይም ምርጫዎች አኳያ የሚያይ አስተሳሰብ ነው። ድሮ፡ ማለት በ3ኛው ክፍለ-ዘመን፡ እንደ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ቢጀምርም፡ አሁን ማኒከዪዝም ሲባል ማንኛውንም ሁኔታ ለሁለት የማይታረቁ ተጻራሪ ሃይሎች -አንዱ በጎ፤ ሌላው መጥፎ- እንደተከፈለ አድርጎ የሚመለከት እይታ ማለት ነው። ሁሉም ነገር ከሁለቱ አንዱ ተብሎ ይገለጻል። ለምሳሌ፡ ጥሩና መቅሰፍት፤ ነጭና ጥቁር፤ መጥፋት ያለበት ጠላት እና ወገን የሆነ ወዳጅ ወዘተ ወዘተ። ከሁለቱ አንዱ መሆን ብቻ ነው የሚቻለው። ሶስተኛ፡ ማለት አሻሚ ወይም መሀከለኛ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ይህንን ግንዛቤ ወይም ጽንሰ-ሃሳብ በምሁራዊ ደረጃ ተገልጾ ያየሁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት እና በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በጻፉት በየካቲት 2001 በአዲስ ነገር ጋዜጣ በታተመው አንቀጽ ነው። ዶ/ር አሰፋ እንደጻፉት፡
“ “ከባህላዊ አመለካከት አኳያ እስከዛሬ ያልተቸነው እና ለብዙ ዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው (የኖረው) ‘የሴማውያን ዕይታ’ ተብሎ የሚታወቀውን የማኒኪያን አስተሳሰብ ነው። ማኒከይዝም ‘ዓለም ከጥንት ፍጥረት ጀምሮ በሁለት ተጻራሪ እና ተፋላሚ ሃይሎች መካከል ተወጥራ ትገኛለች’፡ ብሎ ስለሚያምን ሁሉንም ነገር የሚመለከተው በሁለት አጽናፎች ላይ ብቻ ተወስኖ ነው። እነዚህም ብርሃንና ጨለማ፤ በጎና ክፉ፤ አጥፊና ጠፊ ሲሆኑ፡ እነዚህ ሁለት አጽናፎች የሚጋጩበት እና በአጠቃላይ ተቃርኖ የሰፈነባት ዓለም ውስጥ እንዳለን ያቀርባል፤ በሁለቱ አጽናፎች ያለ ሶስተኛ እውነታ ሊኖር አይችልም ብሎ ያምናል። ይህ አይነቱ አመለካከት በአንድ ማህበረ-ሰብ ውስጥ የሚነሱ ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከሁለት አጽናፎች ውጭ ለመመልከት አይችልም። ስለሆነም፡ይህ አይነቱ ግንዛቤ በባህል በስነ-ምግባር፡ እና በፖለቲካ ህይወት ዙርያ (ላይ) ተጽእኖውን ያሳርፋል።”
ይህ ታዲያ ችግር ለመፍታት ይረዳል ወይስ አይረዳም ለሚለዉ ጥያቄ ስመልሱ
“አይረዳም…።” …እንዲያውም ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ የቅርብ የፖለቲካ ታሪክ ስንመረምር ችግሮቹ እንዲባባሱ “ማኒከየዝም” ሚናዉ ከፍተኛ እንደሆነ ያምኑበታል።
ይህ ባሕሪም ከተወሳሰበ የህይወት ዕውነታ ጋር ሲገለጹ።
“ለምሳሌ..” በማለት “ለምሳሌ በዕውቀቱ ስዩም የተባለ ደራሲ “በራሪ ቅጠሎች” በተሰኘው መጽሃፉ “የቅጠል ቤት ታዳሚዎች” ብሎ ስለሚጠራቸው ገጸ-ባህሪዮች (characters) እንዲህ ይላል፡
“እነሱ ዘንድ መፍረድ ቀላል ነው። ሲፈርዱ ጥግ እንጂ አማካኝ መኖሩን አያውቁም። ቆላ ካልሆነ ደጋ ነው ይላሉ፤ ወይናደጋ መኖሩን አይረዱም። ብርሃን ካልሆነ ጨለማ ነው ይላሉ፤ ከጨለማ የፈካ፡ ከብርሃን የደበዘዘ ድንግዝግዝ መኖሩን አያውቁም። ንፍር ካልሆነ በራድ ነው ይላሉ፤ ለብታ መኖሩን አያስተውሉም፡፤ ጠላት ካልሆነ ወዳጅ ነው ይላሉ፤ መሃል ሰፋሪን አይቀበሉም።”
ይህ ትዝብት ማኒከዪዝም በህብረተ-ሰቦቻችን በተለያዩ ዘርፎች ያለ የባህላችን አካል ወይም ያአስተሳሰባችን ባህርይ መሆኑን ነው የሚያመለክተው። ይህ ማኒኪያዊ አስተሳሰብ የባህላችን አንድ ባህሪ በመሆኑ ባሁኑ ፖለቲካችን ላይም ትልቅ ተጽእኖ ያደርጋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንዳሉት፡ “ይህ የማኒከይዝም አመለካከት በአገራችን ለረጅም ጊዜ ስር ሰዶ የቆየ፣ ባህላዊ መሰረት ያለው ከመሆኑ አኳያ አገራችንን በሚያስተዳድረው ፓርቲ ላይ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡”
በማለት ማኒከዩዝም የተባለዉ የግትርነት ባሕሪ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሳይቀር የሚንጸባርቅ በመሆኑና ይህ ለድርድር እንቅፋት የሆነ መጥፎ ባሕሪ ካልተወገደ ዉጤቱ የከፋ እንደሚሆን ያስጠነቅቃሉ።
“በኢትዮጵያ ፖለቲካና በኤርትራ ፖለቲካ የዲሞክራስን፡ የብሄርተኝነትን፡ እና የብሄረ-ሰብን ያጠቃለሉ ብዙ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ዝምድናን በተመለከተም እንደዚሁ ከብዙዎቹ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የታሪክ አተረጓጐምን የሚመለከት አለመግባባት አለ ማለት ይቻላል፡፡ በዚሁ አለመግባባት፡ በዚሁ ትግል ከማኒኪያዊ አመለካከት የመነጨ ድክመትና ስህተት በሁሉም በኩል ይታያል፡፡”
በማለት ማኒከዩዝም ለሁለቱም ሕዝቦች መራራቅ ለቅራኔዉ ሸካራ ግንኙነት የላቀ ሚና እንደተጫወተ እና ይህ ባሕሪ ከተራ ዜጋ እስከ የፖለቲካ መሪዎች እና የሃገር መሪዎች እንዲሁም ሊሂቃን እንዲዋጉት አጥብቀዉ ካሳሰቡ በሗላ ፕሮፌሰሩ ስለ ሁለቱም ህዝቦች ግንኙነት በሚመለከት በወቅቱ ስለነበረዉ በተባበሩት መንግሥትታት ዕዉቅና የተሰጠዉን የራስ (የዉስጥ) አስተዳደርን በተመለከተ በሰፊዉ ያተቱት ሲሆን፤ አንዳንዶቹን አንመልከት።
በማኒከዩዝም ያስተሳሰብ ባሕሪ ምክንያት ከኤርትራ ሕዝብ ተነጠቀ የሚሉትን የራስ አስተዳደር መብት እንዴት እንደተነጠቀ ፕሮፌሰሩ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ ባሳተሙት በመጽሃፍቸዉ ለሕዝብ በገበያ ስለተሰራጨ ሁኔታዉን በስፋት ለማጤን ለሚፈልግ መጽሃፉን አግኝቶ ማንበቡን ጠቃሚ እንደሆነ እየጠቆምኩ፤- ባጭሩ ፕሮፌሰሩ “በፌደሬሽኑ” መፍረስ ምክንያት በሀለቱ ወገን ስለታየዉ ቅራኔና አለመረዳዳት እንደዚሁም በሕዝቦቹ ስም አስታክከዉ እንወክልሃለን በማለት ጦርነቱን የመሩ የነጻ አዉጪ ግምባሮች ግትር ባህሪ የሕዝቡን ግንኙነት ምን አህል እንደጎዱት በሰፊዉ ካተቱ በሗላ ሕዝቡ ለነጻነት እንዴት እንደበቃ ከነፃነት በሗላ የተጠበቀዉና ሲነገርለት የነበረዉ ይትግሉ ፍሬ እንዴት እንደተኰላሸ በስፋት የገለጹትንም ጭምር እዚህ አልተቅስም። ሆኖም በብዙ ሰዎች ሕሊና ሲታመንበት የነበረዉ “ኤርትራ ፌደረሽን” ነበረች የሚለዉን በተጻራሪ ሲመልሱ እንዲህ በማለት ግልጽ ያደረጉታል
“ፌዴሬሽን የተባለው የኤርትራና ኢትዮጵያ ዝምድና ሙሉ አንድነት ነበር፡፡ ኤርትራ በዚሁ አገር ባለው ስርዓት እንደነካሊፎረኒያ ወይም ኒውዮርክ ፈደረትድ ስቴት አልነበረችም፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ስር የራሷ የውስጥ አስተዳደር “ሎካል አውቶኖሚ” ብቻ ነው የነበራት፡፡ ይህ ፍፁም አንድነት ነበር፡፡ ነገር ግን ኤርትራ ‘ጠቅላይ ግዛት’ ካልተባለች ለአባ ጠቅል አንድነት አልነበረምና ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ ተደረገ፡፡” ካሉ በሗላ፤ ፈረሰ ሲባል ዉጤቱ ምን ነበር? ሲፈርስስ ምን ትርጉም አስከተለ? ይላሉ። “ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ 14ኛዋ ጠቅላይ ግዛት ሆነች ሲባል ምን ማለት ነበር? ፌዴሬሽኑ በመፍረሱ ለኤርትራ ህዝብ ምን ነበር የጐደለው? ፌዴሬሽኑ በመፍረሱ ኤርትራውያን የራሳቸው የራስ ገዝ መንግስት እንዳይኖራቸው ሆኑ፤ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ተገፈፉ፤ ባንዴራቸውን ተነጠቁ፤ ኦፊሺያል ቋንቋዎቻቸውን -ትግርኛና አረብኛ- እንዳይጠቀሙ ተከልክለው፡ የአማርኛ ቋንቋ ተጫነባቸው፤ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶቻቸው - የፕረስ፡ የመናገር፡ ፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም፡ ለስልጣን ለመወዳደር የመሳሰሉትን አያሌ መብቶቻቸውን እኮ ነው የተነጠቁት! ባጭሩ ነጻነታቸውና መብቶቻቸው ተወሰዱባቸው፡፡ ይህ ጭቆና ነበር፡፡”
ከዛ በሗላ የታየዉ ክስተት ፌደሬሽኑ በመፍረሱ ያስከተለዉ የጥላቻ እርሾ ፕሮፌሰሩ በእንዲህ ይገልጹታል።
“ የዚህ ውጤት ምን ነበር? ተጨቆንን፡ ተዘመትን ያሉ ቡድኖች የነጻነት ንቅናቄ አስነሱ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ፌዴሬሽኑ በተለይም ለእስላማዊው ወገንና ሊበራላዊ እሴት በትንሹም ቢሆን ቀማምሰው ለነበሩ ልሂቃን ዋስትና ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ሲፈርስ ዋስትናው ጠፋብን ብሎ የበረገገው ይህ አካል ነበር፡፡ ቆይተውም ድሮ አንድነት ይደግፉ ከነበሩትም ሳይቀሩ ንቅናቄውን ተቀላቀሉ፡፡ ንቅናቄው አድጎ ጀብሃ ተፈጠረ፡፡ አባትና እናት ትባል የነበረችው ኢትዮጵያ ጠላት ሆነች፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን ናት! ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን፡ ወገኖቻችን ናቸው! ብለው አንድነትን የተቀበሉ ሳይቀሩ እንዴት ጠላት ይሉናል ያሉ ነበሩ፣ እስካሁንም አሉ፡፡ እንዲህ የሚሉ ኢትዮጵያውያን መብቱ የተገፈፈና የተጨቆነ ህዝብ፡ በማንኛውም ህብረተሰብ፡ ጨቋኙን፡ ወገን ይሁን ባዕድ፡ እንደ ጠላት ማየቱ የማይቀር መሆኑን ይረሳሉ፡፡ ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ፡ ሟቹ አቤ ጉበኛ፡ አልወለድም በሚለው መጽሃፉ እንዳለው፣
“ወንድም ሲሆንና፡ መልካም ሲሰራ እንጂ ከባዕድ የሚለየው፡
ነጻነትንና መብትህን ከነሳህ፡ ወገንም ጠላት ነው፡፡”
ወገን “ወገን” በመሆኑ ብቻ ጠላት ሊሆን አይችልም የሚል ግምት ስህተት ነው፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ መብት ገፍፎ ጠላት በመሆኑ ምክንያት ወገን “ወገን” መሆኑ ይቀራል የሚል አስተሳሰብ ስህተት ነው፡፡ ሁለቱ የተሳሳቱ ግምቶች ማኒኪያዊ አመለካከትን ያንጸባርቃሉ ማለት ይቻላል፡፡”
ደርግ ከመጣ በሗላም ቢሆን ሁኔታዉን ወደ ነበረበት ማስተካከል ሲችል ወይንም ቢያንስ ሰብአዊ በሆነ ሕዝባዊ አያያዝ/አስተዳደር ከማስተዳደር ይልቅ በማኒኪያዊ አስተሳሰብ/ባሕሪ ሁኔታዉን እንዳባባሰዉ ሲጠቁሙ፤ደርግ በተከተለዉ ማኒኪያዊ ባሕሪ እና ጭፍጨፋ
“የኤርትራውያንን ልብ አሸፈተዉ፡፡ የነጻነት ግንባሮቹ ጠነከሩ፡፡”
እንዲያዉም ይላሉ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተስፋጽየን መደሃኔ
“ማኒኪያዊ ከሆነው ጠባብ አመለካከቱ የተነሳ የደርግ መንግስት የኤርትራ ፖለቲካዊ ችግር ምን እንደነበረ በትክክል ወይም በበቂ አልተረዳም፣ ስለዚህም ሊፈታው አልቻለም፡፡ ፖለቲካዊ ችግሩን በተግባራዊነት ሊፈታ አለመቻሉ በሁሉም በኩል ለአደጋ አጋለጠው፡ ለኤርትራ መገንጠልም አስተዋጽኦ ሆነ፡፡”
ሆኖም ይላሉ
“ኤርትራ የተገነጠለችው ግን የአፄውና የደርጉ መንግስታት ስህተቶች በመፈጸማቸው ብቻ አይደለም፡፡ የኤርትራ ቡድኖች ለዚሁ ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረጋቸውም ጭምር ነው፡፡” ሲሉ የኤርትራ ቡድኖች እንዴት ለመገንጠሉ እና ለአደገኛዉ ግጭት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ እንደሚከተለዉ ያስቀምጡታል። “የኤርትራ ቡድኖች፡ በተለይ ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ)፡ መገንጠልን እንደ ብቸኛ አማራጭ ከሚያደርግ ጠባብ አመለካከት ተነስተው ድርድር የማይፈቅዱ አቋሞች ወሰዱ፡ ለእርቅ እንቅፋት የሚሆኑ ድርጊቶችም ፈጸሙ፡፡”
ሲሉ ማኒከዪዝም በተግባር እንዴት ዉሎ ሌላ አማራጭ እንዳይገኝለት እንቅፋት እንደሆነ በምሳሌ ያቀርባሉ።
“አንዳንድ ምሳሌ ልጥቀስ፣
1. የኤርትራ ቡድኖች፡ በተለይ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ፡ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት የሚል፡ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው አቋም ያዙ፡፡ ኤርትራ ቅኝ ግዛት ሆነች ከተባለ ለችግሩ መፍትሄ ነጻነት (መገንጠል) ብቻ ነው፡፡ ወይ ቅኝ ገዢው ይወጣል፡ ወይ ቅኝ ግዛቱ ይቀጥላል፡፡ መሃከለኛ ሁኔታ የለም፡፡
2. የኤርትራ ቡድኖች (በተለይ አቶ ኢሳያስ የሚመራው ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ) የኤርትራን ችግር ከሶሺያሊሰት ጐን ተሰልፋ የነበረችውን የደርግ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከፈለጉት ሃያላን መንግስታት ስትራተጂ አቀላቅሎ የቀዝቃዛው ጦርነት ማኒኪያዊ ትግል አካል እንዲሆን አደረገው፡፡ በዛው ማኒኪያዊ ትግል የተፈለገው ደርግን ወይም ስርዓቱን መጣል ስለ ነበረ ለዕርቅና ድርድር የማይፈቅድ አቋም ወሰደ፡፡ ለምሳሌ ደርግ ፋሺስት ነው አለ፡፡ ከፋሺስት ጋር ዕርቅ የለም፣ ፋሺስትን እስኪወድቅ ድረስ ትታገለዋለህ እንጂ ሌላ ምርጫ የለህም፡፡
3. ቡድኖቹ፡ በተለይ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ፡ ብዙ ጊዜ የህዝቦቻችንን ታሪካዊና ባህላዊ ዝምድና በኤርትራውያን (በተለይ በወጣቱ) እንዳይታወቅ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህንንም ከመገንጠል በስተቀር ሌላ ምርጫ እንዳይታሰብ ለማድረግ ተገለገሉበት፡፡
4. ኤርትራ በሴራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ቢደረግም ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ፡ ባጠቃላይ ሲታይ፡ የተከበሩ እንደነበሩ ከመግለጽ ተቆጥበው፡ ኤርትራውያንን እንደተጨቆኑ አድርገው ብቻ አቀረቡ፡፡ ኤርትራውያን ከእጅ ወደ አፍ የሚኖሩ ብቻ ሳይሆኑ ሚኒስትሮች፡ ጀነራሎች፡ የቀናቸው ባለሞያዎች፡ የተሳካላቸው ነጋዴዎች፤ በማህበራዊ መስክም ያልተናቁና ያልተወገዱ እንደነበሩ ከመመስከር ተቆጠቡ፡፡
5. ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤርትራ የፈጸሙትን ግፍ ብቻ እየጠቀሰ ራሱ በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ እንዳልፈጸመ ሆኖ ቀረበ፡፡ ለፕሮፓጋንዳና ለዓለም-አቀፍ እርዳታ ብሎ አንዳንድ ምርኮኞችን ደህና አድርጎ ቢንከባከብም፡ ባጠቃላይ በምርኮኞች ላይ ጭካኔ አሳይተዋል፤ አንዳንዱን እንደ ባርያ አሰርተዋል፡፡ ታደሰ ቴለ ሳለቫኖ “አይ ምፅዋ” በተባለው መጽሃፉ እንደገለጸውም በኤርትራውያን ሬሳና በኢትዮጵያውያን ሬሳ መሀከልም አድልዎ ፈጽሟል፡፡
6. በግንቦት 1991 አስመራን እንደተቆጣጠረ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራ አባረረ፡፡ አንዳንዱ ባዶ እግሩን ነበር የተባረረው፡፡
7. በረፈረንደሙ ጊዜ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ ምርጫውን ጨርሶ ማኒኪያዊ አደረገው፡፡ ሂደቱን ምርጫው በነጻነትና በባርነት መሃከል መሆኑን በሚያሳምን ረገድ አከናወነው፡፡ ባርነትን የሚመርጥ የለም፤ ግማሽ ነጻነት፡ ግማሽ ባርነት ደግሞ የለም፡፡
ከላይ የተመለከቱት አቋሞችና ድርጊቶች ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር የመቀራረብ መንፈስ እንዳያዳብሩ፡ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን በኩል ደግሞ ጥላቻ እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ሚና የነበራቸው ይመስላል፡፡ እንዲህ በመሳሰሉት አቋሞችና ድርጊቶች ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ የመገንጠል አጀንዳውን ለማሳካት ችለዋል፡፡” በማለት በ ኤርትራ ነጻ አዉጪ ግምባሮች በኩል የታየዉ ማኒኪያዊ አስተሳሰብ ለግጭቱ መባባስ እና ለኤርትራ መገንጠል ቁልፍ ቦታ እንደያዘ አስቀምጣሉ።
በኢትዬጵያ በኩልም እንደዚሁ ለመገንጠሉ ሁኔታ እኩል ጥፋት እና አስተዋጽኦ ተደርጓል።ከንጉሡ እና ከደርግ ግፍና የተሳሳተ ፖሊሲ እና የማኒኪዩዚም ባሕሪ እንዲሁም ጭፍጨፋ ሌላ ተጨማሪም አስተዋጽኦ ያደረገ ክፍል ኢሕአዴግን/ህወሓት እንደዚህ ሲሊ ይወቅሳሉ።
“….የኢህአዲግ መንግስት (ወይም ህወሃት) ደግሞ ዲሞክራስያዊ ባልሆነ፡ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ባላሳተፈ፡ ለኢትዮጵያ ህዝብም ለውይይት እንኳን ዕድል ባልሰጠ፡ ረፈረንደም ተብዬ ኤርትራን በኢሳያስ አፈወርቅ እንድትገዛ አሳልፎ መስጠቱ የኤርትራ ህዝብን ለማመን ለሚያስቸግር ጉዳት ዳርጓል፡፡”
በማለት በኛ በኢትዬጵያ በኩል የታየዉ የቅርብ ፖለቲካ አያያዝና ግንኙነት አፍራሽ አስተዋጽኦ ከገለጹ በሗላ፤ ፌደራላዊነትን በተመለከተ ደግሞ በሁለታችን በኩል የሚደመጡ አባባሎች ወይንም እምነቶች/አቋሞችም እንዲታረሙ አበክረዉ እንዲህ ይላሉ፡
“ፌዴራላውነትን በተመለከተ በኢትዮጵያውያንም በኤርትራውያንም በኩል ችግሮች አያለሁ፡፡ ከድሮ (ማለት ከ 40ዎቹ አንስቶ) የነበረው የፖለቲካ አመለካከት ችግር አሁንም ገና ያለ ይመስለኛል፡፡ የአጼው መንግስትም ሆነ ደርግ የኤርትራ ጥያቄ ከነበሩት ጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለ-ሃገሮች ጉዳይ ወይንም ብሄረ-ሰቦች ጥያቄ የተለየ መሆኑን መቀበል አልተቻላቸውም፡፡ ይህንን ባለመቀበላቸው አላስፈላጊ እርምጃዎችን ወስደው ኪሳራ አደረሱ፡፡”
ካሉ በሗላ በሁለቱም በኩል መታረም አለባቸዉ አበይት ነገሮች በመጠቆም ሃሳባቸዉን እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል።
“ ኢትዮጵያውያን ልሂቃንም (በተለይ ምሁራኖቹ) በበኩላቸው ኤርትራውያን ጥለውን ሄዱ እያሉ ማጉረምረም ቀንሰው የኤርትራውያኑን ስሞታ እንደሚረዱ ማሳየት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ በሴራ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት እንድትሆን መደረጉ፣ ኤርትራውያን የሲቪልና የፖለቲካ መብታቸው ተገፎባቸው እንደተጨቆኑ፣ የረጅም ዘመናት ታሪካችን አንድ ቢሆንም የኤርትራ ጉዳይ ከሌሎቹ ክፍለ-ሃገራት የሚለይበት ገጽታ እንዳለ፣ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ተከብረው፡ ተሹመው፡ ቀንቷቸውና ተሳክቶላቸው ብቻ ሳይሆን፡ እነርሱም ለኢትዮጵያ ዕድገት በሁሉም ረገድ ብዙ እነዳበረከቱ መመስከር ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ የልሂቃን ሚና ለኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት፡ ለወደፊቱም በሁለቱ አገሮች መሃከል ለሚከሰት ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል”፡፡
ሲሉ ልንፈትሸዉ የሚገባን አስካሁን ድረስ ያልተፈተሸ ያስተሳሰብ ባሕሪ እንድንፈትሽ እና እንድንነጋገርበት ምሁራዊ ምርምራቸዉን ለጉባኤዉ አስሰምተዋል።
ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከተዉ የአፋሩ ተወላጅ ምሁሩ እና በብዕር ችሎታዉ ኢትዬጵያንን እና ኤርትራዊያንን ያስመረቀነዉ አቶ የሱፍ ያሲን ተጋብዘዉ ነበር፤ ነገር ግን ባጋጣሚ እጉባኤዉ ድረስ ለመገኘት ባለመቻላቸዉ ለጉባኤዉ ያዘጋጁትን ጽሑፍ በመላክ እኔ እንዳነብበዉ የተደረገዉን ጽሑፋቸዉን በሚቀጥለዉ ሰሞን በምዕራፍ 2 እንመለከተዋለን። የሁለቱም ምሁራን ጽሑፎች በኢንተርኔት ይለቀቃሉ የሚል እምነት ስላለኝ ሙሉዉን ጽሑፎቻቸዉን/የቪድዬ ንግግራቸዉን ማንበብና ማዳመጥ ተችላለችሁ። አመሰግናሉ። ጌታቸዉ ረዳ ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ ሕዳር 2002።www.Ethiopiansemay.blogspot.com