Sunday, July 8, 2018

አብይ ወደ አስመራ ሄዶ ለደረስው ጥፋት እና ግድያ በኢትዮጵያ ስም ለኤርትራኖች ሓዘኑን መግለጹ በኤርትራኖቹ ዓይን ጥፋተኞች አስደርጎናል! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


አብይ ወደ አስመራ ሄዶ ለደረስው ጥፋት እና ግድያ በኢትዮጵያ ስም ለኤርትራኖች ሓዘኑን መግለጹ በኤርትራኖቹ ዓይን ጥፋተኞች አስደርጎናል! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

ወደ ርዕሱ ከመግባቴ በፊት በመከታተል እያቀረብከት ያለውን ወያኔ እና ትግሬዎች አንድ ናቸው አይደሉም? ትግሬዎች በዘመነ ወያኔ ተጠቃሚዎች ናቸው አይደሉም? ወያኔ አፓርታይድ ነው አይደለም? … የሚለው ክርክሬ ባለፈው ሰሞን ክፍል አንድ ገልጫለሁ። ሁለተኛው እየሰራሁ ባለሁበት ወቅት ነው ይህ ወቅታዊ ዜና ፊቴን እንዳዞር ያደረገኝ ስለዚህ በሚቀጥለው ሰሞን ይቀርባል ተከታተሉኝ።

አብይ አስመራ ሄዶ ሁለቱም ሕዝብ ኢትዮጵያ እና መረብ ምላሽ እንደልባቸው እንዲዘዋወሩ አደርጋለሁ ብሏል። እኔ የተሰማኝ “ተዘወሪ ማኪና ተዘወሪየ አስመራን ሽዋን ኮይኑ መዛወሪየ” የሚል ጥንት የቆየ የዘፈን አስታወሰኝ። ገጣሚና ዘፋኙ ታዋቂው ኤርትራዊው አብራሃም ሰጊድ ናቸው። ገናናው ሃይለስላሴ አስመራና አዲስ አባባ ባቆራኙት ዕለት ሕዝቡ እንደልቡ አስመራ አዲስ አባባ መዘዋወር በቻለበት ወቅት ደስታውን ለመግለጽ የተዘፈነ ዘፈን ነበር። ዛሬም ያንን እደግማለሁ እያለ ነው አብይ አህመድ።  ወደ “ሪል ዲል” (እውነታዊ ድርድር) ስንገባ ‘ግን ግን…..’ የምንለው ወደ ላ የምንመዘው “ግን… ግን...ጥርጣሬአዊ ካርዳችን” እንዳለ በቀረጢታችን አስቀምጠን ለዛሬ ግን “እሰየው” ብለናል። ፖለቲከኞች ነን እና ኣትጠርጥሩ’ አትበሉን። ያውም በኢሳያስ እና በወያኔ የተጎዳች አገር ይዘን።

ዛሬ አብይ ወደ አስመራ ስለ መሄዱ ነው የምንወያየው። ስለ አብይ ኣሕመድ መተቸት ቀርቶ ስለ ኢሳያስ አፈወርቂ እና ባንዴራው መተቸት በኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ተራ ሰዎች የሚያስወቅስ እና የሚያስሰድብ ብሎም ገለል የሚያስደርግ እና በጠላትነት የሚያስፈርጅ ስለሆነ ዛሬ ዛሬ ተቺዎች ከመሰደብ እና ከመወቀስ እያሉ ብዕራቸውን ማስታገስ ጀምረዋል። ከአዲስ አባባ አንድ ታዋቂ ጸሐፊው አምሳሉ ገ/ኪዳን ብቻ ነው የተሰማውን ከመግለጽ ወደ ላ የማይለው እንጂ የተቀረነው መሸማቀቅ ይዘናል።

ከማይሸማቀቁት አንዱ “Yours Truly” እኔ ብቻ ነኝ እና የሚሰማኝን ከማለት አልተቆጠብኩም፤ የሚገድበኝም አንዳችም ሃይል የለም። ስለሆነም ስለ ኢሳያስና እና አብይ ጉዳይ አንስተን እንወያያለን። እውጭ አገር ያሉት የከሰሩት የተቃዋሚ ሚዲያዎች ጽሑፋችንን ሊያግዱት ቢሞክሩም አፍነው ሊያፍኑት ስለማይቻላቸው ለሕዝብ ይደርሳል። ጸሎቴ እነዚህ የውጭ ተቃዋሚ ሚዲያዎች (አክራሪዎቹም ሆኑ ቡድንተኞቹ ፓርቲዎቻቸም ጭምር) ወደ አገር አንዳይገቡ እና እዚህ እንደሚያደርጉት በለመዱት ቡዱናዊ ባሕሪያቸው አገራችንም እነደዚያ እንዳያበላሹት ብቻ ነው ጸሎት የማደርገው። 

አብይ በሚከተለው እጅግ መረን የለቀቀ ሰለማዊ ባሕሪው በፖለቲካው ሜዳ ላይ ‘ሪል ዲል’ ብለን በምንጠራው ድርድር ላይ ሊያደርሰን ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ሁሌም ይጭርብኛል።  የተጀመረው የተስፋ ጭላንጭል ወደ እዚያው የሚያደርሰንን መንገድስ ‘ጅቦቹ’ እንዳይነጥቁን የመዝጊያ በሮችን የሚዘጉ እርምጃዎች ለመዝጋት እያፋጠናቸው ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ሁሌም የሚረብሸኝ ሁኔታ ነው። ወያኔዎች ፋሺስቶች ስለሆኑ እና ተሎ አጅ መስጠት የማይፈልጉ፤ ያልሰለጠኑ “ያልለመዱ የበረሃ አራዊቶች” ስለሆኑ አገሪቷ ወደ ጠምንጃ ፍትግያ እንዳያስገብዋት የሁሌም ስጋቴ ስለሆነ አብይ ጋር ያለኝ ስጋት ይህ ነው። ስጋቴ ባጭር አገላለጽ “አገሪቷ የተረጋጋች አይደለችም” ለማለት ነው። ይህ ካልኩኝ ዘንድ አሁን ወደ አስመራ እንገስግስ።

አብይ ወደ አስመራ ሄዶ ከሃያ አመት በፊት ለደረስው ጥፋት ግድያ በኢትዮጵያውያን ስም ኤርትራውያኖችን ሓዘኑን ገልጿል። ይህ ምን ማለት ነው? ይቅርታ እየተየቀ ነው ማለት ነው። ተመሳሳይ እና ቀጥተኛም ባይሆን ዛሬም የወያኔ ታሪክ ደግሞታል፡ የሚያስብል ነው። ለምን? ይህ መልስ ለማግኘት ከመባዘኔ በፊት እንዲሕ ያለ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው “ሰላማዊ’ አገላለ እሳት እየተንቦገቦገ ባለበት የሁለቱ ፖለቲካ ግንኙነት ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት።

ይህ እራሱ ቀጥተኛ ይቅርታ ነው አይደለም የሚለው ክፍት ሆኖ ለክርክር ብንተወውም፡ አብይ ያደርገዋል ብየ ባልልም በእርሱ ትዕዛዝ መሰረት ወደ አስመራ አብረውት የሚሄዱትን ይቅርታ እንዲጠይቁ  እንደሚያደርግ ጥርጣሬየን ወደ አስመራ ከመሄዱ በፊት ገልጫለሁ። ወቅቱም እነ የማነ አዲስ አባባ ገብተው ንግግር ሲያደርግለቸው አብይ ወደ አስመረራ ከመሄዱ በፊት ቀደም ብየ በጽሑፍ ይህንን ጥርጣሬዬን እውን እንደሚሆን ጽፌ ነበር። ይህን ስለ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ አስመልክቼ ስለ ጻፍኩት ትችት ተነተርሼ የጻፍኩት እውነተኛ ጥርጣሬየን በገለጽኩበት ወቅት ነበር። ይህንንም ዋሽተሃል እንዳትሉኝ ልጠቅስ እና ላስታውሳችሁ፡

ከጉብኝቱ የምንጠብቀው ግን ምናልባት መለስ ዜናዊ አማራ ያልሆኑትን ሰብስቦአስመራ እና ከረንድረስ ሄደው አማራ ለኤርትራ ሕዝብ ስቃይ ተጠያቂ ስለሆነ  የአማራ ሕዝብ ወክሎን ይቅርታ እንድንጠይቅ መጥተናል፡ ብለው እንዳሉት ቅጥረኞች ዛሬምአብይ ወደ አስመራሲሄድ አብረውት የሚሞሸሩት እነ ዳዊት /ጊዮርጊስ  አስመራ ሄደው ያንን ይደግሙ ይሆን? ወይንስ የቀድሞ ወታደር ይቅርታ እንድጠይቅ ልኮኛል ብሎለነፃነታችን፤ ላንድነታችን፤ ለፍትሕ እና ለዲሞክራሲ ላደረጋችሁልን ትብብርበወታደሩ ስም ይቅርታ ሊጠይቅ መጥቻለሁሊል  ይሆን ወይንስ ሌላ ያልሰማነው አሳዛኝ ልሳን ልንሰማ ይሆን?” (ወታደሮቹን ከድቶ ከሻዕቢያ ጋር የወገነው ዳዊት /ጊዮርጊስ ዛሬም ሳያፍር ለኢሳያስ ማሽቃበጡን ብሶበታል! (June 30/2018) ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን Ethiopian Semay) ብየ ነበር።

አሁን እናዝናለን የሚለው የአብይ አገላለጽ ለክርክር የሚቀርብ ቢሆንም እኔ የገለጽኩት ጥርጣሬየን እውን ሆኖ ይኼው ዛሬ አብይ በሌሎች ተላላኪዎች ሳይሆን በራሱ አንደበት እንዲህ ሲል ያልጠየቅነውን በስማችን ያላልነውን የሓዘን አቅራቢነት  እንዲህ ጠይቆአቸዋል።

“ የኤርትራ ሕዝብ ከሃያ አመት በፊት ባጋጠመው ግጭት ህይታቸውን ላጡ አካላቸው ለጎደለ ኤርትራውያን የተሰማኝን ጥልቅ ሓዘን ለቤተሶባቻቸው ማድረስ እፈልጋለሁ።”
ይኼ ምን ማለት ነው? ገዳዮቻቸው  እኛ ነን እና  ስለገደልናችው እና አካላታችሁ ስላጎደልናቸው ጥልቅ ሓዘኔን ለማድረስ እፈልጋለሁ፡ ማለት እንግዲህ አብይ አህመድ ለኤርትራኖች ያዘነበው የፍቅር ዝናብ ይህ እና ዋነኛው ሓላፊነት የጎደለው የሓዘን አድርሱልኝ መልእክት ነው። ይህ አባባል ለትችት የቀረበው በኢሳያስ በኩል ተመሳሳይ የሐዘን መግለጫ ቢቀርብ ኖሮ ለትችት አይቀርብም ነበር። ግን ባንድ በኩል የቀረበ ስለሆነ ኤርትራኖቹ በሚገርም ሁኔታ በሚከተለው ሁኔታ ‘መስከረም” በተባለው የሻዕብያ ታማኝ ድረገጽ ጋዜጣ አብይ እንዲህ ከለማለቱ በፊት አብይን አንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር፦

Meskerem 07/08/2018 10:46:19 PM
As Eritrea welcomes the Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed, the honorable guest is called upon to apologize for the atrocities and crimes committed against the Eritrean people by the last three ruthless Ethiopian administrations…

እዚህ ለመዘርዘር ሰፊየሆነው መግለጫው ባጭሩ ይህ ድረገጽ እየነገረን ያለው፤ ኢትዮጵያውያኖች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከፈለጉ ይህ የታሪክ አጋጣሚ የተገኘው የጉብኝት ዕድል ተጠቅሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስተር አብይ አሕመድ በሦስት የኢትዮጵያ ስርዓቶች በኤርትራ ሕዝብ ላይ የደረሰው እና የተፈጸመው የጭፍጨፋ ወንጀል (አትሮሲቲ) ይቅርታ መጠየቁ የኤርትራ እናቶች እና አባቶች ልብ አለሳልሶ ለዘላቂ ሰላም መፍትሄ ስለሚየስገኝ ይርታ እንዲጠይቅ እንጠይቃለን፡” በማለት አስቀድሞ አብይን ጠይቀውታል። ስለሆነ ይሆን ሓዘኑን ሊገልጽ ያነሳሳው እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች አስቀድመው ቀርበውለት ስለነበር ይሆን? የሚል ጥያቄ ይጭራል። ሐዘኑን በመግለጹም ሌሎች ድረገጾች በዚሁ በተመሳሳይ “ቀጥተኛ” ይቅርታ እንደጠየቀ አድረገው ሓተታቸውን በሰፊው አስተጋብተውታል። ያውም እኮ ጦርነቱን የለኮሰው ኢሳያስ መሆኑን የድምበር ኮሚሽኑ ያረጋገጠው ሃቅ ሆኖ እያለ ነው።

ይህ እንዳይበቃ ደግሞ “ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አድርጎ ሹሞኛል”ብሎ እርፍ! ወይ ጉድ! ቀልደም ለካ ቦታ የለውም ሲባል የሰማነው ልክ ነው። ትንሽ ቆየት ብሎ ኢሳያስም ኢትዮጵያን እንዲስተዳድር ስለተፈቀደልኝ መሪያችሁ ነኝ ሊለን ይሆን። ጊዜ መስተዋቱ የሚባለው ይኼው ነው።  ዶናልድ ትራምፕ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኝየ ተሹሜአለሁ፤ ቢል በቀልድም ቢሆን ፕሮቶኮሉ ይፈቅድለታል? ያምርበታል?

ይህም ሆኖ ጉብኝቱ ደስ ይላል። ፋሺስቱ ኢሳያስ ባለፈው በአንድ ሕዝባዊ ንግግሩ የ60 አመትዋ ዕድሜ ያላት ኢትዮጵያ ብሎ በቆሸሸው አንደበቱ ያሳነሳት የገዛ አገሩ (አገራችንን) ያፈለቀቺው ሰላማዊው ሰው ዶ/ር አብይ አሕመድ አስመራ ከተማ ድረስ ሄዶ ሲጎበኘው ታፍኖ የነበረው ብዙ የኤርትራ ሕዝብ በደስታ እያቀፈ ሲሳለመው ማየት እጅግ ደስ ይላል። ሰንደቃላምችን ምንም እንኳ የወያኔ የሰይጣን ኮከብ ምልክት ያረፈባት ብትሆንም ‘በኢትዮጵያ ሰንደቃላማነትዋ’ በየአመቱ ኤርትራኖች የነፃነት (የባርነት) በዓላቸው ሲያከብሩ ሲጠየፍዋት፤ በእግራቸው ሲረግጧት እና ምራቃቸው ሲተፉባት የነበሩዋትን ሰንደቃላማችን ብትሆንም በክብር ሲያብለበልቡዋት ማየት ደስ የሚል ነው።

እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን፤ ሰንደቃላማ እንደትረገጥ ያዘዘው ፋሽስቱ ኢሳያስ እንደሆነ ካሁን በፊት ደጋግሜ በጽሑፎቼ ገልጬ እንደነበር ታስታውሳላችሁ። አሁን ግን በራሱ ትዕዛዝ መሰረት የረገጥዋትን ሰንደቃላማ በክብር አንዲያውለበልቡዋት ትዕዛዝ በማሳለፉ በክብር ሲያውለበልቡዋት አይተናል። መሪዎች ሕዝባቸው በፈለጉት መንገድ እንደ ወንዝ ውሃ መጠማዘዝ እንደሚችሉ ማስረጃ ነው። ለዚህ ነው መሪዎች ካልተለወጡ ሕዝብ ሊለወጥ አይችልም፤መጀመሪያ የመሪዎች ባሕሪ መለወጥ አለበት ስል የነበርኩት። ዋና ተዋናዮቹ መሪዎቹ ሳይለወጡ ሕዝብ ለሕዝብ እናገናኝ እያላችሁ ከንቱ አትድከሙ ስል የነበርኩት ለዚህ ነው። በሕዝብ ላይ ብዙም የሚተኮር ነገር ቢኖር በመሪዎች ላይ ነው።

ስለ እኔ ስሜት ለማወቅ ለምትፈልጉ ዜጎች እንድታውቁልኝ የምፈልገው  ግንኙነቱን መፍጠር አልቃወመውም፡ ግን “የጠላታችን ሻዕቢያ ባንዴራ ትናንትም፤ዛሬም ነገም ለወደፊቱም ብንሞት አናውለበልባትም”። የወያኔን ባንዴራ ለማውለብልብ እንደምጠየፈው ሁሉ የሻዕቢያ ባንዴራም ለኔ እኩል ናቸው እና አሽቃባጮች ይንን እወቁልኝ። ያ ብቻ አይደለም፡ አብይ አሕመድ ምጽዋ ሄዳችሁ መዋኘት ላማራችሁም ሄዳችሁ መዋኘት ትችላላችሁ ብሎ ቢናገርም እነ ጀኔራል ተሾመ እና እነ ሺዎቹ ስንት ሺ ኣእላፍ “እምየ ኢትዮጵያ” እያሉ ሰንደቃላማውን ለብሰው እራሳቸውን በጥይት እያጠፉ፤ በድን ሬሳቸው ወደ ባሕሩ እየዘለለ ቀዩ ደማቸው የምጽዋን የባሕር ባቀለመው ውሃ ውስጥ ሄጄ ኢሳያስ በሥልጣን ላይ እያለ እየዋኘሁ ደማቸውን መጠጣት የጀግኖችን ደም ማርከስ እንደማልፈቅድ ካሁኑኑ ስገልጽ የሻዕቢያ አሽቃባጮች የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ሃቁን ስንነግራችሁ ከመራራው እውነታ ጋር ነው። ከወያኔ ጋር አብሮ ሲዘርፍ የነበረው ምድረ “ፔቲ ቦርዥዋው” ይኼኔ ምጽዋ ሄዶ ለመዋኘት ክንፎቹን እያኮበኮበ እንደሚገኝ እርግጠኛ ነኝ። ምድረ አቃጣሪ ከያኒም እፍ እፍ ፍቅሩን ከመጠን ያለፈ እያቀነቀነ የዘመዶቹ  አጥንት በተረጨበት ምድር ላይ ቆሞ በላያቸው ላይ እየጨፈረ ጭፈራው እልልታው ሰማይ ያደርሰዋል። ያዝማሪ ነገር!

ስለ አብይ አሕመድ አንድ ነገር ብየ ወደ ኢሳያስ እገባለሁ። በተለያዩ ውቅቶች እንደገለጽኩት አብይ አዋቂ፤ ጥሩ ሰው እና የዋህ ሰላማዊ ሰው ነው። በገራገርነቱም ወያኔዎች እና ተንኮለኞች እንዳይገድሉት ስጋቴን በገለጽኩ ሰሞን አብዮት አደባባይ (አዲስ አበባ ስታድዮም ?) ተገኝቶ ንግግር ሲያደርግ የተሞከረው አስነዋሪ ግድያ ስጋቴን ትክክል እንደነበር ማሳያ ነበር። ዛሬም ጠንካራ ጥንቃቄ እንዲደረግለት የተሻለ ነው። ምክንያቱም ጅቦቹ ዛሬም በዙርያው እያየናቸው ነው፤ ከፍተኛ  የወታደር አመራሮች፤ አማካሪዎቹ፤ አጃቢዎቹ፤አምባሳደሮቹ እነሱ ናቸው:: ስለሆነም በቀላሉ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። እግዚሓር ይጠብቀው ከማለት ሌላ ‘አማራጭ ምክር’ የለም።

ዶ/ር አብይ አስመራ አየር ማረፊያ ከደረሰበት ጀምሮ እስከ መሃል ከተማዋ ድረስ ተሰልፎ የነበረው ሕዝብ በጭፈራ፤ በዕልልታ አልፎም እስኪደክመው ድረስ እየሳቡ ሲስሙት ማየት የሚያስታውሰን አንድ ነገር ቢኖር ጥንታዊው የመረብ ምላሽ ሕዝብ እንደ አምላክ ሲመለከታቸው እና ሲወዳቸው የነበሩትን የኢትዮጵያ ንገሠ ነገሥት መሪ የነበሩት ኤርትራን ሲጎበኙ የተቀበላቸው ቀዳማዊ ሃይለስላሴን ያስታውሰናል። ልዩ ማራኪ ባሕሪ ያለው አብይ አሕመድ ክርስትያኑ እና አስላሙ ኤርትራ ሕዝብ በሚገርም ሁኔታ በፍቅር ጥሎአቸዋል። ይህም ለኢትዮጵያቀ የተሰጣት አለፍ ብሎ የሚወርድላት ታአምራታዊ ስጦታዋ እና ክስተት መሆኑንም ተጠራጥረን አናውቅም። መለስን እና አባት ነብሱን አብሮ በአንድ ወር ወደ ሰማየ ሰማያት ድንገት ሲጠራቸው ያሳየን ተአምር፤ በዛው ፈንታ የተበደልነውን ያህል  “ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪዋ እጆችዋን ትዘረጋለች” የተባለው ሃቅ ሆኖ ይህ ታምር እንድናይ በቅተናል።

ስለ አብይ ይህ ካልኩ ስለ ፋሺስቱ ኢሳያስ አንድ ለበል። ከዚያ በፊት ግን ማወቅ ያለባችሁ ስለ ጉብኝቱ ስንነጋገር ተጠቃሚዎቹ ኤርትራኖች ዕልል ቢሉ ያምርባቸዋል። እኛ ግን የሰማነው ነገር ስለሌለ “በግን .. ግን” መቆየታችን የሚጠበቅ ነው። ምክንያቴን እገልጻለሁ።

እየሳቀ የሚገድል ጨካኙ እና ፋሺስቱን ኢሳያስ ስቆ የማያውቀው ልቡ እስኪፈነዳ ድረስ በአብይ ልዩ ባሕሪና ተዋዛይነት (ቀልደኛነት) እያሳቀ ሳያስበው ተመርኳል። የአብይ ያልተዘጋ የበር ልብ ተማርኮ ግባ ሲለው ሳያስበው እያንጨበጨበ ሲገባ እየተነዋል። ይህ ግን ምን ማለት ነው? አብይ ወደ አስመራ ሲመጣ ለዓለም እና ለሁለቱም ሕዝብ የሚገልጽ ፖሊሲ የሚከተለው የምጣኔ ሃብት፤ የፖለቲካ እና ማሕበራዊ መርሃ ግብር በጽሑፍ አዘጋጅቶ የመጣበትን ዓላማ እያነበበ ነግሮናል። በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሰለማዊ መርሃ ግብር አውቀናል። ያላወቅነው ግን ያው የኢሳያስ ድብብቆሽ ባሕሪው በአጸፋው ኤርትራ ምትሰጥንን ወይንም የምትከተለው መርሃ ግብር አልገለጸልንም፤ ግልጽ አልሆነልንም።
 
በሚገርም ንቀት ወይንም ደደብነቱ ብቻ ሁኔታው በማናውቀው ምክንያት ‘ኢሳያስ’ የነገረን ነገር “ለጽሑፍ ንግግር ስላልተዘጋጀሁ እንዲሁ በቃሌ አንዳንድ ነገር ልብል’ ብሎ የራሱን እና የሕዝቡን ደስታ ብቻ ነበር የገለጸው።

ከዚህ አልፎ አብይ የወሰደው ምርጫ/እርምጃ ‘ቀላል የሚባል እንዳለሆነ’ እንጂ ኢሳያስ በበኩሉ ‘ቀላል የማይባል ምርጫ የወሰደበት መርሃ ግብር ግን አልነገረንም”። አብይ ሙሉውን መድረክ በአማርኛ እና ትግርኛ ኢትዮጵያ ልትተገብራቸው ያቀደቻቸው ውሳኔዎች አንድ ባንድ ሲገልጽ ኢሳያስ በሚከተለው የዘወትር ድብቅ ባሕሪው የተነሳ እንኳን በጽሑፍ በቃልም የወሰደበት የንግግር ርዝማኔ በደቂቃዎች ብቻ የተወሰኑ ነበሩ። ለምን?

ምክንያቱም አንደኛ ነገር ኢሳያስ በተቃዋሚዎቹ እና አሽከሮቹ በኩል ‘ተምበርካኪ’ ተብሎ እንዳይታይ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ እራስዋ ለምና ለዕርቅ እንደመጣች እና አመራሩ (ኢሳያስ) በአሸናፊነት መወጣቱን ለማሳየት የወሰደው ድብቅ ተንኮል ነው። የትዕግስት ውጤቱ ይኼው ኢሳያስ አሳይቶናል እያሉ ኤርትራኖች በሰልፉ ላይ በተጠየቁበት ቃለ መጠይቅ ሲናገሩ ሰምተናል፤ (በትግርኛ)። የኢሳያስ ብዙ ያለመናገር እና ምን አንደሚሰጠን ያለመግለጹ ወይንም አብይ በተናገረው ላይ ዝርዝር ነጥቦች አንስቶ ያለመግለጹ የሚያሳየን “ክፋት እና አሸናፊነቱን” ለማሳየት የተጠቀመበት አጉል ተንኮሉ እና የዘወትር ባሕሪው ነው። ይህ የሳይኮሎጂ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች የምታውቁት ነው ብየ እገምታለሁ።

እንኳን ለሃያ ምናምን አመት ተራርቆ የነበረ፤ በጦርነት እና በጥላቻ የተቋሰለ ሕዝብ ቀርቶ ‘ለሦስት ቀን’ የስራ ጉብኝት ላመድረግ የሱዳን፤ የካታር፤ የ….. አገር መሪዎች ለሚመጡ እንግዶች የሚያደርገው ንግግር በጽሑፍ የተዘጋጀ ንግግር ነው። እዚህ ደርሶ አብይ የሚያክል ትልቅ እንግዳ መምጣቱ እያወቀ “በጽሑፍ አልተዘጋጀሁም ነበር” ብሎ አጭር ንግግር ማድረጉ ግን ለአሽቃባጮች ግልጽ ባይሆንም ለኛ ግን ያው የተካነበት የተንኮል እና የትዕቢት ባሕሪው መሆኑን ለምናውቀው የአካባቢው ሰዎች ድብቅ አይደለም። አጉል ኩራቱ በምናውቀው ሰዎች እንጂ ባሽቃባጮች ለነሱ ትልቅ ደስታ እና ፈንጠዚያ ነው (የሚያውቁትም አይመስለኝም)። መሪያችን ያንተ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ነኝ ሲለው ኤርትራን ሴቶች “ወዲ አፎም…የ… እያሉ ነበር እያሞካሹ ሲዘፍኑለት የነበረው። የስነ ልቦና ተመራማሪዎች ካልሆኑ በስተቀር አሽቃባጮቹ (ኢትዮጵያውያን) ግን የኢሳያስ ስነ ልቦና አያውቁትም እና በፈንጠዚያ ሲያሞካሹት እና ባንዴራውንም ሲያውለበልቡለት አይተናል። አሁን ጥያቄው አብይ የሚሰጣቸው ነገሮች ነግሮአቸዋል፤ ኢሳየስ ግን ምን አንደሚሰጠን አስካሁን የነገረን ነገር የለም። ለወደፊቱ ሲገለጽልን የዚያ ሰው ይበለን እና “ሪል ዲሉ” እንቀበለዋለን አንቀበለውም የሚለውን ያኔ እናየዋለን።
ምን ጊዜም የናንተው ጌታቸው ረዳ ነኝ Ethiopian semay