Monday, April 11, 2011

ዝገርም እዩ! ዝገርም ዝገርም!ወይ ትጉዱ!

ዝገርም እዩ! ዝገርም ዝገርም! ወይ ትጉዱ! ከጌታቸው ረዳ ኢትዩጵያን ሰማይ አዘጋጅ www.ethiopiansemay.blogspot.com (408) 561 4836 (ከኦነግ በላይ ኦነግ ከሻዕቢያ በላይ ሻዕቢያ እየሆኑ ያስቸገሩን ተቃዋሚዎች ምን ይሻላል?) መጀመሪያ አንባቢዎቼን እጅ እነሳለሁ! የሁዳዴው ፆም እንዴት እያረጋችሁ ነው? ለምትፆሙ ብርታቱን ይስጣችሁ፤ አምላክ ከናንተው ጋር ይሁን፤ቡራኬውም ለኛው ለከርሳሞች በናንተው በኩል ለኛው ይድረሰን። የዛሬ ዘገባ ረዘም ስለሚል ጊዜ ወስዳችሁ አንደምታነቡኝ አደራ እላለሁ። ዛሬ የምናወራው ከሻዕቢያ በላይ ሻዕቢያ ከኦነግ በላይ ኦነግ ከአክራሪዎች በላይ የአክራሪዎች አቀንቃኞች እየሆኑ የሚያስቸግሩንን ግለሰዎችና ድርጅቶች ዛሬም ደግምን ደጋግመን የምናተኩርበት ዓብይ ጉዳይ ይሆናል። ባንዳንድ ተቃዋሚ ክፍሎች ኦነግን የማወደስ አባዜ የሰሞኑ ዓብይ ትኩረት ሆኖ ቀልባችን እየሳበው ነው። እንዲህ ሊሆን ትልቅ የውጭ ሃይል እንዳለበት ረዢም የፖለቲካ ተሞክሮ ያላችሁ ሰዎች አታጡትም የሚል እምነት አለኝ። የሆኖ ሆኖ ኦነግን ተንከባከቡ እያሉ በየድረገጻቸውና በየራዲዩኑ እየጮሁ የዋሁን የፖለቲካ አጋሰስ አብሮአቸው እንዲጮህ የሚያደርጉት እነማን እንደሆኑ ከመወያታችን በፊት መጀመሪያ ይህንን እንመለከት። ብዙውን ጊዜ ይሄ ተቃዋሚ አንድነት ያጣ ለምን ይሆን የሚል ጥያቄ መልሶ መላልሶ ይመጣባችሁ ይሆናል። የውጭየውጭ እኛኑን የሚመስሉ የኛው ጉዶች እየመለመሉ የሚያዳክሙን ኃይሎች እንዳሉበት ላንዴም እንዳትረሱ። ያም ሆኖ ትኩረቴ አሁንም ውጭ አገር በሚገኘው ተቃዋሚው ላይ ነው። ማን ነው እያዳከመን ያለው? መልሱ ቀላል ነው። መልሱን ከማግኘታችሁ በፊት ግን ስለ አንድነትና የድርጅት ሁኔታ ታሪክ በውጭ አገር ተቃዋሚ የሚባለው ድርጅት እንዴት እንደተጠናከረ/ህይወት እንደዘራ አንድ ነገር ልብ እንድትሉ እፈልጋለሁ። ከመኢአድ በቀር አሁን በተቃዋሚነት ተደራጅቶ ውጭ አገር ትንፋሽ ዘርቶ/ሕይወት አግኝቶ በኢትዩጵያዊነት የሚጮኸው የዛሬ “ኖይዚ” ተቃዋሚ ሁሉ አስቀድሞ ቅንጅት በሚል ስም ሲጠራ የነበረው ነው (አብዛኛው)። አሁን በየፓልቶኩና ድርጅት ነኝ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ያለው የድርጅት አባል ትንፋሽ እንዲዘራ ሥሩ ውሃ እያጠጣ ነብስ ዘርቶ አግር እንዲተክል ያደረጋቸው ኢህአፓ ነው! ተቃዋሚ የሚባል ቻፕተር /ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንዲመሰረት፤ ሕዝብ እንዲሰባሰብ፤አገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች ውጭ አገር እየመጡ ከሕዝብ ጋር እንዲተዋወቁ በየሬስቶራንቱ እንዲዝናኑና ከኗሪው ጋር እንዲወያዩ ያደረገው እግዚአብሔር ከክፉ ይጠብቃቸውና የኢሕአፓ አመራሮችና በየእስቴቱና በየአሕጉሩ ያሉት አባሎቹ ናቸው።ኢሕአፓ ከአረጋዊ በርሔ፤ግደይ ዘርአጽዩን፤ኮሎልጐሹ ጀምሮ እና ሌሎቹ (ድርጅትም ግለሰዎችም) እስካሁን ድረስ እስካሉ ማጅራታቸው ገትረው የሚቀደዱት ሁሉ ኢሕአፓ ነበር አካባቢው እንዲለማማዱ ክፋት እንዳይደርስባቸው አድርጎ የተንከባከባቸው። አሁን በቅርቡ እንኳ ኢሕአፓ በየእስቴቱ የራሱን አባሎችና ጽ/ቤቶች እየለገሠ በራሱ አባሎች አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ጥረት አድርጎ አሁን በተቃዋሚ የማይታወቁ የነበሩ ታይተው የማይታወቁ በየሥራቸው ተወሽቀው መልካም ኑሮ ምቹ ሕይወት ሲመሩ የበሩ “እንግሊዝ ተናጋሪ ሁሉ!” አሁን ወደ ማይነኩ አንበሶች ሆነው ብርሃኑ ነጋ በጀመረላቸው የስድብና የውሸት መቀደድ ባሕል ሕይወት የዘሩላቸውን ኢሕአፓዎችን “ፋራ ፖለቲከኞች” በማለት ሌሎቹንም “ቆሻሸችን ከመንገዳችን እያስወገድን ፋረውን ፖለቲካ እንሳለቅበታለን” በማለት “የሻዕቢያ ሥልጡን ፖለቲካ ለመከተል” የግንቦት 7 ቼ ጎቬራ የ“ጋሸ ብርሃኑ” ተከታዮቹም ከሰማይ የወረደ “አሜሪካዊው ኦባማ” አስመስለው ሊሰብኩን በየአዳራሹ በማይክሮፎናቸው ሲቀደዱና የስድብ ውርጅብኝ/ናዳ እያወረዱ ቆይተው፤በየአዳራሹ በየራዲዩኑ አንድ ቃል በተናገረ ቁጥር ናላቸው ተቦውዞ “የጭብጨባ ሱሰኞች” መሆናቸውን ራሳቸውን ሲያስገምቱ ቆይተው፤ ጋ”ሸ ብርሃኑም “አሜሪካኖች አትመለስ ቁጭ ብለህ ትምህርትህን እየተማርክ፤የምትበላውና የምትጠጣው ወጪ አታስብ በኛ ይሁንብህ፤ አርፈህ ተራራ ላይ ወጥተህ ተፈላሰፍ ስላሉኝ አልመለስም” ሲላቸውም አዳራሹን በጭብጨባ አቅልጠውለት ሲታዘብ አጨብጫቢዎቹ “ፒስ ኦፍ ኬክ” ናቸው ብሎ አንድያውም ስከሩ ብሏቸው፤መጨረሻ አገር ውስጥ የነበሩ ሽርከኞቹን ተሰባስበው ግማሹ በበቦሌ በወያኔ ፈቃድ ታጅበው ቅንጅትን አፍርሰው፤ ወደ ውጭ አገር ፈርጥጠው በመምጣት በስንት መከራ የገነባነውን አንድነታችን አናግተው አቃቅረውን ሲያበቁ፡ቡራ ከረዩ እያሉ ቆይተው ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት መስርተው $500.00 የከፈለ የአርበኝነት ምሥክር ወረቀት ይሰጣችኋልና ክፈሉ ብለው ሲያውጁላቸው፡ ብዙ አገር ወዳድ ያንን የአርበኝነት የምሥክር ወረቀት ሳያልቅበት እንቅፋት እየመታው ተጠድፈው እየተሽቀዳደሙ ጓጉተው የአርበኞች የምሥርክር ወረቀት የገዙ እንዳሉ ይታመናል። ከዛም ወደ ሻዕቢያ ኰብልለው ነፃነት እናመጣላሃለን ብለው ዋሽተው፡ በዓለም መንግሥታት በዓለም አቀፍ ጥቁር ገበያን በማጧጧፍ ንግድና ከጽንፈኞች ጋር መዳራት፤ ጠመንጃ ማስተላለፍ፤ ሰብአዊ ጥሰትን የመሳሰሉ አስከፊ ሕገ አራዊት በመከተሉ ምክንያት የተወገዘው “ወዲ አፎም” (ኢሳያስ) ላይ ማዕቀብ ሲደረግበት “በሻዕቢያ ስም ‘ሞተን’ እንገኛለን” በማለት ከሻዕቢያ፤ከኦጋዴንና ከመሰል አክራሪ ደጋፊዎቻቸው ጋር ኒውዩርክና ዋሽንግተን እንዲሁም አውሮጳ ሳይቀር የኢትዩጵያ ሰንደቃላማ ይዘው አክራሪዎቹ እነ ሻዕቢያና ደጋፊዎቹ ባዘጋጁት ሰልፍ በመገኘት ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ከሰንደቃላማችን ጠላቶች ከሻዕቢያ፤ከኦጋዴን ከሶማሊ ነፃ አውጭ እና ከኦነግ ባንዴራዎች ጋር እያስተሻሹ (እያውለበለቡ) ከሻዕቢያ በላይ ሻዕቢያ በመሆን ሲጮሁና ሲሰለፉላቸው አይተን አዘንን። ይህ አሳፋሪ ትዕይንት ለታሪክ ተቀርጾ በስዕለ ድምፅ ተዘግቦ You Tube በተባለው በማሕበራዊ የሕዋ ሰሌዳ ተለጥፎ ይገኛል። “አነስ ዝዓጥረለይ ዘይስእን” ይላሉ አንዳንድ የትግራይ ሴቶች ሲገርማቸው ፡ አማርኛው (“የኔ ዕጣ ፈንታ ሆኖ መቸም ቢሆን በሃዘኔ ጊዜም የሚያሽኮረምመኝ ጎበዝ አላሳጣኝም”)። አሁንም ወዲ አፎም በሃዘኑም ጊዜ ማዕቀብ ሲደረግበት ሞተን አንገኛለን ብለው ሳያገባቸው ገብተው እየቀበጡ ከሻዕቢያ በላይ ሻዕቢያ ሆነው ሲጮሁ ለመታዘብ እግዚአብሔር አበቃን። በ$500.00 አርበኝነትን በመሸጥ የሕብረተሰቡን ሕሊና ያነሆለሉት አርበኝነትን በየሃገሩ ባቋቋሙት የድረ ገጽ ሱቅ የሚነግዱት እነ ግንቦት 7ቶቹም አስመራ ሄዶው ኢሳያስ ሸካራ መሆኑን ሲገምቱት የሻዕቢያ ወዳጆች የሆኑ ኢትዩጵያውያን ውስጡ ለቄስ መሰሪዎችን (ስማቸውን ላለመጥቀስ) ኢሳያስ እንዲለሰልስላቸው ሽምግልና ለመላክ እየተዘጋጁ ነው። ውስጠ ሰሪዎችን አስልከው ለስለስ እስኪልላቸው አንዳርጋቸው አሁንም <<አስመራ ከተማ ፅቡቕ እዩ ዕድለኪ _ ምንአስ ንሎንድራ ንፓሪስ መሲልኪ>> (ታድለሽ አስመራ ከተማ መልክሽ ሎንደንና ፓሪስ ከተማ መስለሽ ተውበሻል) እያለ ኤርትራዊው የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ባንድ/ መጨረሻም ማትአ (ማሕበር ትያትር አስመራ) በኃላም የጀብሃ ታጋይ የነበረው ከዚህ ዓለም የተለየው <<የኑስ ኢብራሂም>> ብሎ ድሮ ወጣቶች እያለን የተዘፈነላት አስመራ ከታማ ውስጥ ብፃይ አንዳርጋቸው (በትናቸው ጽጌ) ኮፍያት አድርጎ የክቡርነታቸው ለስላሳ ባሕሪ ረገብ እስኪል ደጅ እየጠና እንደሆነ የደረሱን ዜናዎች ይገልጻሉ። የተያያዛው አዲስ ስልት ደግሞ ኢሳት-ቲቪ እየተባለ በሚጠራው የነ አበበ በለውና የነ ብርሃኑ ነጋ የነ….የነ…. ሳተላይት ቲቪ ቀርበው በቃለ መጠይቅ መልክ “አለና!!!” እያሉ ሲያሞኙን ቆይተው ጦራችሁ የት አለ? ሲባሉ “ሙሽሽ ብለው” ፈረንጆቹ እንደሚጠቀሙበት “አቅጣጫ/ቀልብ ቀልባሽ” (Attention deflector) በሚባለው ዘዴ በመጠቀም ዛሬ ድግሞ “ኦነግ ኦነግ” እያሉ “ስለ ኦነግ አንድነት” ደስታችሁን ግለጹላቸው እያሉ ሕዝቡን በማምታታት ኦነግን ማሞካሸት አዲስ ዘመቻ አድርገው ተያይዘውታል። ዝገርም እዩ! ሰሞኑን አዲስ ድምፅ እየተባለ የሚጠራው በአበበ በለው አማካኝነት የሚያናፋ የኪራይ ራዲዩን ዶ/ር “በያን አሰቦ” ለተባለው ጸረ ኢትዩጵያ የኦነግ አፈቀላጤ በኩል ኦነግ ለኢትዩጵያ የቀመመው መርዝ ራሱን አስክሮት ሲበጣበጥና በየመኔሶታ ፍርድ ቤት ሲካሰስ የዘበነው የተበታተነው ኦነግ አንድነት መመስረቱን እና ድስታውን ለመግለጽ በያንን እንግዳውን አድርጎት የተለመደው የቀረና እጅ እጅ የሚለውን የኦነግን ውሸት የተቀደድክበትን በራዲዩኑ እንድናዳምጥለት ጋብዞት ነበር። በጣም ይገርማል! ወይ ትጉዱ! አሉ እናቶቻችን ትግሬዎች ለካ እውነታቸውን ነው እንዲህ ያለ ኪሳራ ሲያገኛቸው ወፍጮ ቤት ሄደው ሊየስፈጩ እህላቸው ተጎርዶ፤“ሳይሰስን” ሚዛኑ ቀንሶ ጐደሎ ሚዛን ይዘው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ። እውነትም “ዝገርም! ዝገርም! ወይትጉዱ! የሚሉት። ኢትዩጵያን እበትናለሁ እያለ በማኒፌስቶው አውጆ 40 ዓመት ሙሉ የባዘነ የመሳፍንት ዘመን ሕሊና ባላቸው እንግሊዝኛ የሚናገሩ “የፖለቲካ ገሪባዎች” የሚመራ ኦነግ የተባለው አድሃሪ ድርጅት ወረዳ ምርዛሙ ሊጭርብን እርስበርሱ ሲማማ “ጥሩ ዜና” እያለ የማንቆላጫ እስክስተው ያወረደለትን የአበበ በለውን አሳፋሪ ፖለቲካዊ ማንቆላጫውን አድምጡልኝ። እንዲህ ያለ የፖለቲካ ሽርሙጥና ከቶ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? አድምጡት እነሆ፦ አበበ በለው - አዲስ ድምፅ ራዲዩ፦ የተከበራችሁ አድማጮቻችን በመግቢያው ላይ አስቀድሜ እንደገለጽኩላችሁ፤ የዛሬ እንግዳችሁ ዶ/ር በያን አሰባ ናቸው። ዶ/ር በያን ለግዜዎትን አመሰግናለሁ።መቸም ዶ/ር በያን መቸም <<አንዳንድ ጊዜ ከጥሩ ዜና ይልቅ እንዳንድ ጊዜ መጥፎ ዜና -ዜና እየሆነ ብዙ ጊዜ መጥፎ ላይ እናተኩራለን ጥሩ ሲገኝ እንደ ግዴታ እየወሰድነው እንደሆነ አላውቅም የመጥፎውን ያህል አናራግበውም። በነገራችን በኦነግ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ክፍተት ካንድም ወደ ሁለት ተሸጋገራችሁ ወይንም ተከፋፈላችሁ የሚባል ነገር ሰምተን ብዙ ተወያይተንበት ነበር አሁን ደግሞ ያን ልዩነት አስወግዳችሁ ተመልሳችሁ አንድ መሆናችሁ ስንሰማ መቸም “ከተጣሉ ታረቁ ያስደስታል፤ ከተበተኑ ተሰበሰቡ አንድ ሆኑ ያስደስታልና” በኛ በኩል ደስ ብሎናል እንናንተንም ደስ እንደሚላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ እንዴት ነበር “ጥሩ ነበር”?>> ይህ ጉድ ምን ትሉታላችሁ? ተከፋፈላችሁ ሰምተን አዘን ይላል፡ አንድነት ፈጠራችሁ የሚል ዜና ስንሰማ ደግሞ ደስ ብሎናል፡ በማለት ኢትዩጵያን ለማፍረስ የተነሳን war criminal የጦር ወንጀለኞች፤ ብሔራዊ ወንጀሎችና በዘር ማጥፋት የሚጠየቁ በሰብአዊ ምብት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ጽ/ቤቶች ወንጀላቸው የተዘገበ፤ ኦነግ የተባለው በደም የተነከረ እጁና ደም የጠማው ከሃዲ ድርጅት አንድነቱን በማጠናከሩ ደስታውን በመገለጽ እንኳን ደስ አላችሁ ደስ ብሎናል በማለት ሕብረተሰቡን ለማወናበድ አበበ በለው የተነሳበት ዓላማ ምን ይሆን?
ይህ ሰው የጎንደር ኦሮሞ ኖሮት የዘር ሐረጉ አንደ ድመት እየጨኸ ተጣርቶት ይሆን? ብሎኛል አንዱ ጓደኛየ፡ እኔ ምን አውቃለሁ አልኩት። እኔ የምገምተው ግን የፖለቲካ አድማሱ ከአፍንጫው የማይርቅ ድፍን ቅል ስለተሸከመ ይሆናል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ይኼ ድንቁርናው እንዲመልስልኝ አበበ እራሱን በኢመይል ጠይቄው መልስ አላገኘሁም። ኦነግ ማን መሆኑን ስለማያውቀው መልስ እንደማይኖረውም ስለምገምት ከአበበ በለው የመሰለ “የፖለቲካ ገሪባ” የምጠብቀው ነገር ያለ አይመስለኝም። መለፍለፍና ማሰብ ለየብቻ ናቸው። እንደው አይገርማችሁም <<እንዴት ነው ጥሩ ነበር?>> ብሎ ሲጠይቅ የዳንስ ምሽት፤ የሠርግ የበዓል ዘገባ እንዲነግረው የሚጠይቅ ጠያቂ አይመስልም <<እንዴት ነው ጥሩ ነበር?>> ብሎ ሲጠይቅ? ዝገርም! ወይትጉዱ! ዶ/ር በያን የመለሰውን መልስ ደግሞ የሚከተለው አድምጡልኝ። በያን አሰቦ (ኦነግ ነገረ ፈጅ) <<አዎን አንተ እንዳልከው አትራክት የሚያደርግ የመከፋፈል ጉዳይ የብዙ ሰው (ቀልብ) ይስባል። ለወሬ ይመቻል መሰለኝ! እና የዛን ያህል የሰላም መውረድና የስምምነት ጉዳይ የዛን የህል ባይሆንም የሰዎችን አቴንሽን ስቧል።>> አየ በያን! እንዴት ሰው በደም የተጨማለቀውን እና የማንነቱን ካባ ጥሎ የባዕድ ፊደል አምላኪ ድርጅት አንድ ሆነ ዌኢም ፈረሰ ምን ደንታ ይሰጣል ብለህ ነው የኦነግ አንድነት ቀልብ ሊስብ የሚችለው?የኦነግ አንድነት የሚያስስታቸው ኦነጎችና አንቋለጮቹ እንጂ እኛን አይመለከተምና እውነት ብለሃል ስትፈርሱ ቀልባችን ስቦ እንዳስደሰተን ሁሉ አንድ ስትሆኑ ግን የአንቋላጮቻችሁን ቀልብ ብቻ መሳቡን አውነቱን ብለሃል። በያን ቀጠል ያደርግና <<አቶ አበበ እንደምታውቀው ያንድ ድርጅት መከፋፈል የድርጅቱን አቅምና ጥንካሬ እንደሚያዳክም ምንም ጥያቄ የለውም። በኦሮሞ ነፃነት ግምባር አመራር መሃከልም የተደረገው ክፍፍል ያለ መታደል ነው፤ ልናስቀረው አልቻልንም እና ትግሉን ጐድታል ጥያቄ የለውም። ይሄንን ደግሞ መልሰን በሰላም ችግሮችን በመፍታት ተመልሰን ለመዋሃድ፤ተመልሰን አንድ ድርጅት ለመሆን ከፍተኛ ትግል ጥረት ጠይቋል። አሁን ሁኔታዎች መስመር ይዟል። ስምምነት የመዋሃድ ወደ አንድ ደረጃ ወደ መድረስ ደረጃ ደርሰናል። በዚህ በኩል ሁሉም ወገን ከፍተኛ ትምህርት አግኝቷል። የኦነግ መከፋፈል በእውነቱ ለወያኔ አምባ ገነን አገዛዝ ካልሆነ በስተቀር በእውነቱ ለማንኛውም የሕዝብ ወገን ቆምንለት ለምንለው ሕዝብ ምንም ጠቀሜታ እንደሌለው ተገንዝበናልና በኛ በኩል የተደሰተ “ወያኔ” ነው። ወያኔንም እንግዲህ አንድ ሆነን ባንድ ጡንቻ እነሱን ለመታገል፤ለመጋፈጥ የተዘጋጀን እንደሆነ እንደሚከፉ ይከፉ እያልኩ እንደሚከፉም እጠብቃለሁ። እኛም ደስ ብሎናል “ለድስታ መግለጫህም” አመሰግናለሁ።>> አየ በያን መቸ ይሆን ይህንን ውሸት ከሕሊናሕ የምታስወግደው? ወያኔ ብቻ ነው የኦነግ መከፋፈል የሚያስደስተው? እኔ ወያኔ አይደለሁም እንደኔ ያሉ ሚሊዩኖች አሉ፤ግን የኦነግ መበታተን ዜና ስሰማ ደስ ይለኛል። መች አኔ ብቻ በኦነግ የዘር ማጽዳት ዘመቻ መርሃ ግብር /ማኒፌስቶ ምክንያት በሚሊዩኖች የተገደሉ የተፈናቀሉ ቤተሰቦቻቸው ካደጉበት ከተወለዱበት መንደራቸው የተበተኑ ሁሉ፤በኦነግ እየታፈኑ፤ የጠፉ፤የተሰቃዩ ሁሉ የኦነግ መፈረካከስ በደስታ እንደሚቀበሉት አጥተኸው ሳይሆን የለመደብህ የደርጅቱን የመዋሸት ባሕል ተጠናውቶብህ እንደሆነም አናጣውምና የናንተን መፈረካከስ ወያኔ ብቻ ነው ደስ የሚያሰኝ እያልክ ተሞኝተህም ከሆነ ራስክን አሞኝተህ ሌላውን ባታሞኝ መልካም ነው። አንድ እውነቱን የተናገርካት ነገር ግን ሳልገልፅ አላልፍም፡ <<አቶ አበበ እንደምታውቀው ያንድ ድርጅት መከፋፈል የድርጅቱን አቅምና ጥንካሬ እንደሚያዳክም ምንም ጥያቄ የለውም። በኦሮሞ ነፃነት ግምባር አመራር መሃከልም የተደረገው ክፍፍል ያለ መታገል ነው ልናስቀረው አልቻልንም እና ትግሉን ጐድታል ጥያቄ የለውም >>
የኦነግ መከፋፈል ኦነግን እንዳዳከመው አበበ በለው ተረድቶት ይሆን? ኦነግ ሲዳከም ማን ነው የሚጠቀመው ኢትዩጵያን ለማፍረስ 40 ዓመት የዘበነው፤ደም የተቃባው፤የዘር ፖለቲካ ያራመደው፤ የዘር ማጽዳት ዘመቻ በግልጽ በማኒፌስቶው ያሰፈረው ኦነግን ወይስ የኦነግ ጉዳተኛ (ቪክተም) የሆነቺው ኢትዩጵያ? አበበ የኼን ያወቀው አልመሰለኝም? ካልሆነማ በመፈራረሱ የደከመውን የኢትዩጵያ ጠላትና ወንጀለኛ ደርጅት <<ደስ ብሎናል! እንናተስ ተደስታችኋል እንዴት ታዩታላችሁ?>> ብሎ ሲጠይቅ ትንሽ ማፈር ነበረበት። ኣለመታደል የማፈር ትርጉም የጠፋበት ዘመን ነን ያለነውና ጠላትን ደስ አለህ ብለህ ማበሰሩና አብሮ ማንቋለጡ ኣበበ ከመጤፍ አልቆጠረውም። ዶ/ር በያንም በአበበ በለው ኩፉኛ ኦነግን የማንቆላፐሱን ሁኔታ ገርሞት እኛም ደስ ብሎናል “ለድስታ መግለጫህም” አመሰግናለሁ።>> ብሎታል። አበበ በለው (አዲስ ድምፅ) እውነትም ኦነግ ብቻ አልነበረም የተከፋፈለው፡ ከተከፋፈሉት ኦነግ የመጨረሻው ነበር ማለት ይቻላል።ከሱ በፊት ብዙ ድርጅቶች ተከፋፍለዋል። እኔ እንዳውም “ይቅርታ” ያድርጉልኝና SURPRISE ያደረገኝ ያስገረመኝ ብነግረዎ “ቅር” እንደማይለዎ ይመስለኛል። ሌሎች የተከፋፈሉ እንደተከፋፈሉ ሲቀሩ ኦነግ ግን መከፋፈል የመይጠቅመና የሚጎዳ መሆኑን አውቆ ከሌሎች ይልቅ ቀድሞ አንድነቱን እንደገና የበለጠ (ያጠናከረ) ኦነግ መሆኑን ነው የማውቀው፣ሌሎቹ እንደተከፋፈሉ መቅረታቸውን ነው የማወቀውና በዚህ በኩል መቸም ያንድነትን ጥቅም ኦነግ “አራአያ” መሆኑን በኔ በኩል “ደስ” ብሎኛል። ….ብዙ ኢትዩጵያውያን በኦነግ ላይ ሁለት ዓይነት ስሜት አላቸው፡ ታግለው የሚያታግላቸው ይፈልጋሉ፡የኢትዩጵያን ችግር እንደማንኛውም ድርጅትም ኦነግም መፍትሄ እንዲሰጥ ይፈልጋሉ፤ እና ‘ በ “አጽንኦት” የሚያዩት ድርጅት ነው። እና በዚህ በኩል ሌሎቹ ተከፋፍለው ሲቀሩ ኦነግ ግን “የለም!” ብሎ አንደነቱን መጀመሪያ መሆኑን “በጣም አስደስቶናል”፡ በዚህ በኩል አይታችሁታል? ሌሎች አንደተበተኑ (ተበትነው) ነው የቀሩ! በያን አሰቦ ( ኦነግ ነገረ ፈጅ)፦>>አይ- እንደዚያ አላየነውም! Actually በጣም ያተኰርነው የኛን የውስጥ ችግር ማሸነፉ ላይ ነበረ። እኛ ከተሳካልን ምሳሌ መሆን በጣም ጥሩ ነገር ነው። …በታሪክ ውስጥ ቀድሞ ወጣቶች ሆነን በነበርንበት ጊዜ ኢፒአርፒ እና መኢሶን ደም የተቃቡ፤የተጋደሉ የፖሌካን ጦርነት ወደ ጦርነት የቀየሩ እንደነበሩ እናስታውሳለን ግን እነዚህም ድርጅቶች ያ ሁሉ ቁስልና ጠገግ እየዳነ መጥቶ በጋራ ሲሠሩ አይቻለሁ። ያም አንድ ትምህርት ነው።>> ዝገርም! ዝገርም! ዝገርም! አያችሁልኝ ወንድሞቼ? የፖለቲካ ሽርሙጥና ከዚህ የባሰ የዘቀጠ አድርባይነት፤ አለማፈርነት የት አለ? በያን እንኳ እራሱ ገርሞት አበበ በለው << እኔ እንዳውም “ይቅርታ” ያድርጉልኝና SURPRISE ያደረገኝ ያስገረመኝ ብነግረዎ “ቅር” እንደማይለዎ ይመስለኛል። ሌሎች የተከፋፈሉ እንደተከፋፈሉ ሲቀሩ ኦነግ ግን መከፋፈል የመይጠቅመና የሚጎዳ መሆኑን አውቆ ከሌሎች ይልቅ ቀድሞ አንድነቱን እንደገና የበለጠ (ያጠናከረ) ኦነግ መሆኑን ነው የማውቀው፣ሌሎቹ እንደተከፋፈሉ መቅረታቸውን ነው የማወቀውና በዚህ በኩል መቸም ያንድነትን ጥቅም ኦነግ “አራአያ”መሆኑን በኔ በኩል “ድስ” ብሎኛል ሌሎቹ ተከፋፍለው ሲቀሩ ኦነግ ግን “የለም!” ብሎ አንደነቱን የ ያጠናክር የመጀመሪያ (ድርጅት) መሆኑን “በጣም አስደስቶናል፤>> ብሎ ሲል ያውም እኮ <<እኔ እንዳውም “ይቅርታ” ያድርጉልኝና SURPRISE ያደረገኝ ያስገረመኝ ብነግረዎ “ቅር” እንደማይለዎ ይመስለኛል>> ሲል <<እየዋሸሁ እናንተን ለማመገስ ይፈቀድልኝ በመዋሸቴም ቅር እንደማይለዎት አምናለ እያለ ኦነጎች “የአንደነት አርአያ ናችሁ” ሌሎቹ ተበታትነው በተበተኑበት ተበታትነው በዛው ሲቀሩ ኦነግ ቆራጡና ብልሁ ግን “የለም!” አይሆንም ብሎ ልዩነቱን አስወግዶ ቅራኔ እንዴት ሊፈታ እንደሚችል አርአያ የሚሆነን የመጀመሪያ መሆኑን እየዋሸ "ፖለቲካዊ ማንቋለጡን" ሲበዛበት የኦነጉ ዶ/ር በያን አሰቦ በአበበ በለው SURPRISED መሆን አግራሞት ተገርሞ አንዲህ ሲል ያሳፍረዋል። በያን አሰቦ፦
<<…በታሪክ ውስጥ ቀድሞ ወጣቶች ሆነን በነበርንበት ጊዜ ኢፒአርፒ እና መኢሶን ደም የተቃቡ፤የተጋደሉ የፖለቲካን ጦርነት ወደ ጦርነት የቀየሩ እንደነበሩ እናስታውሳለን ግን እነዚህም ድርጅቶች ያ ሁሉ ቁስልና ጠገግ እየዳነ መጥቶ በጋራ ሲሠሩ አይቻለሁ። ያም አንድ ትምህርት ነው።>> በማለት አበበን ውሸታም የሚል ቃል ሳይወጣው የመጀመሪያ አርአያዎች ኢሕአፓ እና መኢሶን ናቸው ትምህርቱም ከነሱ ነው የቀሰምነው፤በምሳሌነቱ ሱሰሩም ዓይቻቸዋለሁና ብዙም አቆለፓፐስከን ሲል ውሸቱን በመረጃ አጋለጠው። ጉድ እዩ! ዝገርም!!! እንዲክ ያለ ዘመን! አሉ ወሎየዎች! እንዲክ ያለ ነገር ሲያገኙ አደል! ወይትጉዱ! ዝገርም! ዝገርም! በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ፡ <<….ብዙ ኢትዩጵያውያን በኦነግ ላይ ሁለት ዓይነት ስሜት አላቸው፡ ታግለው የሚያታግላቸውይፈልጋሉ፡ የኢትዩጵያን ችግር እንደማንኛውም ድርጅትም ኦነግም መፍትሄ እንዲሰጥ ይፈልጋሉና ኦነግን በ“አጽንኦት” የሚያዩት ድርጅት ነው። >> ብሎ አበበ በለው ሕብረተሰቡን ላመወናበድ እንዲመቸው ያምታታውን ጥያቄ ኦነግ ለኢትዩጵያ ተቆርቋሪ ነው ታግሎ ሊያታግለን ነው የሚሉ ኢትዩጵያን አሉ፤ኦነግ መፍትሄ ሰጪ ነው፤ አንድነት ሲፈጥር ስለ ኢትዩጵያን አንድነት በሚመለከት ነው የተወያዩት፤ ስለዚህም ነው እንኳን ደስ ያለህ ያልነው፤ በአዲስ ፕሮግራም ይዞ የድሮውን ፋሽስታዊ ዘረኛ ፕሮግራሙን ሰርዞታል፤ አዲስ ኦነግ አዲስ መንፈስ አዲስ ኢትዩጵያዊነት መንፈስ ታጥቆ ነበር፤ ስለ ኢትዩጵያዊ ክብርና ዜግነት ተነጋግሮ አንድነት የፈጠረው ብሎ ለማምታታት እንዲመቸው ሲጠይቅ በያን ደግሞ ደህና አደርጎ የባሰውን ሐፍረቱን እንዲከናነብ በሚከተለው መለሰለት፤ <<አይ- እንደዚያ አላየነውም! Actually በጣም ያተኰርነው የኛን የውስጥ ችግር ማሸነፉ ላይ ነበረ።>>
ዕርፍ!!! እሰየው! አበበ በለው እንኳን እቅጩን ነገረህ! አሁን ታዲያ ምን ይሻልህ ይሆን? እንኳን ደስ ያለህ ስትለው እሱ ደግሞ “አታንቋልጥ” ኢትዩጵያ የምትባል ከኦነግ ፕሮግራም በፊት አትመጣም እኛ እንደዚያ አላየነውም >>
ብሎ እረፈው አለሃ! ዝገርም! ዝገርም! ወይትጉዱ! ወይትጉዱ! ከማአቱ ይሰውረን የሚባል እኮ እንደዚህ ያለ ነገር ነው ወንድሞቼና እህቶቼ። አበበ በለው (አዲስ ድምፅ) … አሁን እርስዎ ያሉትን ‘ወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ነው የሚጠቀመው ያሉትን ፤ አንዱን ባንዱ እያሰፈራራ ነው ያሉትን .፣…በደርግ ጊዜ ወያኔና ሻዕቢያና አገር ሊገነጥሉ ነው፡ ሊያፈራርሱ ነው የሚል ደርግ ይናገር ነበር Somehow በተወሰነ ደረጃ እውነት የሆነበት ጉዳይ አለ። የባሰ አይመጣም ብለው ያሉ ሰዎችም የባሰ የመጣበት ሁኔታ አለ። ይሄንን ያዩ ሰዎች እነ አቶ መለስ አሁን በደርግ ሁኔታ ራሳቸውን ያስቀመጡበት ሁኔታ ያለ ነው የሚመስሉት። ሻዕቢያን የኤርትራ መንግሥት እንዲሁም ኦነግ በኢትዩጵያ ለውጥ ሊያስነሱ ነው፤ ሊበታትኑህ ነው፤ እያለ ወያኔ ያንድነት ጠበቃ ሆኖ ሻዕቢያና ኦነግ ሌሎችም የመሳሰሉት “ኢትዩጵያን ሊበታትኑን እንደሆነ ይናገራል፡ “ሕብረተሰቡ በዚህ ላይ ጥርጣሬ ቢኖረውም” የባሰ አይመጣም እያለ የባሰ ሲመጣ አይቷል እዚህ ላይ በናንተ በኩል ፖለቲከኞች በኩል ማንኛውም ተቃዋሚ ፖለቲከኛ የሚጠበቅባችሁ ሥራ ያለ ይመስላል።ምን ይመስለዎታል? በያን አሰቦ (ኦነግ ነገረ ፈጅ)፦
<< በጣም ትከክል! …ኋላ ኋላ የመጡት የባሱ ከሆነ የቀደሙት ሳይሻሉ አይቀሩም እንደሚል አስተሳሰብ በሕዝብ ዓዕምሮ እንዳለ ግልፅ ነው። ሕዝብ የባሰ ይመጣል ብሎ ቢፈራ ሕዝብ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ሕዝብ የባሰ ይመጣል ብሎ እንዳይፈራ …የማሳመኑ ግዴታና ሃላፊነት በኛ ላይ ነው የሚወድቀው፤ ሸክምና ሃላፊነት በኛ ላይ ነው። ይሄን መንግሥት የምንቃወም ሃይሎች ጥለን ምን ዓይነት መንግሥት ነው የምንመሠርተው? የሚለው ጥያቄ በግልፅ ለሕዝብ መመለስ አለብን። ሁለተኛ የሚፈጠረው ሥርዓት አንዴት ነው ካሁኑ አምባ ገነነን መንግሥት አሪስቶክራሲ አምባገነኖች የሚለየው? በግልጽ ማስቀመጥ ይጠበቅብናል። ይሄ የኛ ሸክም ነው፤ (በርደን ነው)የማሳመኑ ጉዳይ የማሳመኑ ግዴታ የኛ ግዴታ ነው የምለው።>>
እንዴ <<ሻዕቢያና የኤርትራ መንግሥት እንዲሁም ኦነግ በኢትዩጵያ ለውጥ ሊያስነሱ ነው፤ ሊበታትኑህ ነው፤ እያለ ወያኔ ያንድነት ጠበቃ ሆኖ ሻዕቢያና ኦነግ ሌሎችም የመሳሰሉት “ኢትዩጵያን ሊበታትኑን እንደሆነ ይናገራል።>><<ሕዝቡ በዚህ ጥጣሬ ቢኖረውም>> ይላል አበበ በለው።
እንዴ ይህ ፍራቻ እኮ አይደለም “እውነታ ነው! ወያኔ ብቻውን አይደለም እንዲህ ዓይነት እውነታ የያዘው፤ እኔ እና ወያኔ ያልሆኑ ሚሊዩኖች ናቸው። ፍርሃት እና አውነታ የተለያዩ ናቸው; ፍርሃት ስጋት ነው፤ እውነታ ደግሞ የሚደረግ ነው። እውታነቱ ወደ ተግባር እንደሚለወጥ መረጃው ማኒፌስቶው ነው። ወያኔ ትግራይ በፕሮግራሙ የነደፋቸው ሁሉ ተግባራዊ አድርጓቸዋል። ኦነግም ፕሮግራሙ እስካልለወጠ ድረስ በማኒፌስቶው መሠረት እንደሚያከናውንባቸውና አደርጋቸዋለሁ ብሎ ኣሁንም የሚታገልበት መርሃ ግብርና ትግል ስለሆነ በቀላል ቃላት “ፍራቻ” በሚል በቀላል ስጋት የሚሰናበት ጉዳይ አይደለም! አበበ በለው አንተና ኦነግ በውሸት እንደምታሽቃብጡት ዓይነት እንድናምን አታወናብዱን! ይህ በማይገባ ሕዝብን እያቀለሉ ማወናበድ በጣም ወንጀል ነው። ሕዝቡ አገር እንዳይፈርሰ ስጋት እንዳይሰማው የማሳመኑ ግዴታ የኛ ጉዳይ ነው ብሏል የኦነግ ነገረ ፈጅ ዶ/ር በያን አሰቦ። አስገራሚ! አናንተ እና ሻዕቢያ አንዲሁም የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግምባር አገር እንደምታፈርሱ በፕሮግራማችሁ አስፍራችሁ ጦር ሰብቃችሁ አርባ አመትና ሌሎቹም የናንተን አሰር/ ኰቴ ተከትለው ኢትዩጵያውን ከ ኦሮሞ እና ኦጋዴን ኣካባቢ እንዲወጡ እየገደላችሁ ነው፡ እንዲባረርም በፕሮግራማችሁ ቁልጭ ብሎ ሰፍሮ ቅጁ እጃችን ላይ አለ። ስለዚህ ይህንን መርሃ ግብራችሁ እስካልተለወጠ ጊዜ ወያኔም ይሁን ማንም ዜጋ የናንተን ማኒፌስቶና እንቅስቃሴ እያየ “አገር ሊያፈርሱ ነው” ብሎ ቢወነጅላችሁ፡ እንዴት ውሸቱ ነው ብላችሁ ሳታፍሩ ደረቅ ውሸት መዋሸት ትችላላችሁ? ማኒፌስቶው ቁልጭ ብሎ አፍጦ፤ አግጦ፤ አፍ አውጥቶ፤ በሕይወቱ ነብስ ዘርቶ፤ ወረቀታችሁ እየተናገረን ወያኔ እየዋሸ ነው ማለት እንዴት ይቻላል? ትገርምኒ! አለ የኔ ሰው። ዝገርም እኮ እዩ!!!! ወይ ትጉዱ! አበበ በለው (አዲስ ድምፅ ራዲዩ)
<<በዚህ ላይ እንዳውም የወያኔ አገዛዝ ከሚጠቀምባቸው ነገሮች እኛም ሳናውቀው ተባባሪ የሆንባቸው ጥቃቅን የፖለቲካ ጥቅማጥቅም ለወያኔ የሚሰጥ ሁኔታ ይታየናል። አሁን በቅርቡ በርካታ ኦሮሞዎች ታስረዋል፤ ካሁን በፊትም በጎጃም በጎንደር አካባቢ መሬት ተወሰደብን እንዲህ እንዲህ በመሳሰሉ በመከራከር የታሰሩ አሉ አና አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካል ጠቀሜታ የሌለው መስሎን ዝም ብለን እንተዎው እንደሆን እንጂ ለወያኔ የሚጠቅም ነገር እኛም ስንፈጽም እናያለን። እነዚህ የታሰሩ ሰዎች በ ኦጋዴንም እንደዚሁ በርካታ ኢትዩጵያውያን የተገደሉበት ሁኔታ አለ እና በኦጋዴን በኩል ተገድለውብናል ስንል የኦጋዴን ክልል ተወላጆች እንደተጎዱ ወይንም ደግሞ 25 የኦሮሞ ተወላጆች ታሰሩ 250 አማሮች ታሰሩ እያልን ነው የምንናገረውና ችግሩን የዛ አካባቢ ችግር ብቻ ያለ የሚያስመስል ቃና ያለው ይመስለኛል ይሄ (አዘጋገብ)። ሁላችንም በሚያስነሳ መልኩ ያንድ ኢትዩጵያዊ መታሰር የትም ይሁን የትም ኦሮሞ ይሁን ያፈለለገው ብሔር ዓይነት ይሁን እዚህ ላይ ራሳችንን አክቲቭሊ ኢንቮልቭ አንሆንም። አልተጎዳንም አይመስለዎትም?>> በያን አሰቦ፡ <<በጣም አንጂ፤በጣም ትክክል ነህ አቶ አበበ። ወያኔ የሚፈልገው ኤግዛግትሊ ይሄንኑ ነው። ስለራሳችን ብቻ እንድናስብ ስለ ሌላው መጨፍጨፍ አንደ ምንም ነገር እንደማንቆጥር ይሄ ዓይነተኛ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ነው።…>> ይላል በያን አሰቦ። አየ አበበ በለው! አሁንስ ወደ ማሰቁ ወስደከኝ። ሁለታችሁም አስገራሚ ፍጡራን ናችሁ ልበል? ኦነግ በጠባብ ብሔረተኛነት በወያኔ ላይ ሲያመካኝ? ይገርማል! አያሰኝም ወይ? ኦነግ ! ኦነግ! ያ የምናውቀው ኦነግ በወያኔ ላይ ሲያመካኝ አይገርማችሁም? ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ ወያኔ ነው ያስተማረኝ ብሎ ኦነግ ለጠባብነቱና ለዘረኛነቱ በወያኔ ሲለጥፍ ወንደሞቼ በዚህ ፖለቲካ አልሳቃችሁም? ለመሆኑ ወየኔ ነው ያወናበደኝ ብሎ ኦነግ በወያኔ ፖሊሲና ባሕሪ የሚመራ አራዊት ከሆነ ምን ፖለቲከኛ ሆነው? 40 አመት ሙሉ ወያኔ ነው ስለ ራሳችን ብቻ እንድናተኩር፤ያደረገን፤ አማራ ከኦሮሞ አካባቢ እንዲወጣ በፕሮግራማችን እንድናሰፍር ያደረገን ወያኔ ነው፤ አማራውን ነፍጠኛ እንድንል ያስተማረን ወያኔ ነው…..ስንቱን ወንጀል እንዘርዝር.. ሲል ኦነግ ወያኔ የራሱ ችግር ቢኖረውም ኦነግ ለዘረኛ ባሕሪውና ተግባሮቹ በወያኔ እንዴት አመካኝቶ ማምለጥ መሞከር ይቻለዋል? አለን አልሞትን የአይን ምስክሮች እኮ ነን፤ የ ኦነግ ፕሮግራም አልሞተ አልረሰረዘ፤አልተለወጠ የኦነግ ፕሮግራም እኮ አሁንም ደዚችው ሰኮነድና ደቂቃ ይፋ ለሕዝብ በየድረገጹ እየተነበበ ነው። ምነው እስከ እዚህ ሕዝብን ጨቅላ ባታደርጉት? ነውር አደለም ወይ! አበበ በላው የተባለው ሌለው በስሜት የሚዋዥቅ መናፍሕ/ራዲዩነኛ እያለን ያለው ደግሞ አስገራሚ ነው። ይህንን ስሙልኝ አንብቡልኝ፦ <<እንዳውም የወያኔ አገዛዝ ከሚጠቀምባቸው ነገሮች እኛም ሳናውቀው ተባባሪ የሆንባቸው ጥቃቅን የፖለቲካ ጥቅማጥቅም ለወያኔ የሚሰጥ ሁኔታ ይታየናል።>> ሲል ለኦነግ ተባበሪነት የሆነበትን ጥቅማጥቅም ሰጪነት ሁኔታ ግን ሊታየው ባለመቻሉ ሰውየው ከዛ መናፈሕ/ራዲዩን ሥራ ቢለቅና የራዲዩን ትምሕርት አጥንቶ ቢመለስ በጣም ጥሩ ነው እላለሁ።በማታውቀው መሥክ ገብተህ ማጉልያ ደምፅ አፍህ ላይ አስጠግተህ ፖለቲካን መፈትፈት በጣም በጣም ጎጂ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ዘገባ ሲዘግብ ምን ብሎ እንዲዘግብ ትፈልጋለህ አቶ አበበ በለው? <<የኦሮሞ ተወላጆች ታሰሩ 250 አማሮች ታሰሩ እያልን ነው የምንናገረውና ችግሩን የዛ አካባቢ ችግር ብቻ ያለ የሚያስመስል ቃና ያለው ይመስለኛል ይሄ (አዘጋገብ)።>> ትላለህ፤ ታዲያ 250 አማራዎች በኦነግ ከተገደሉ 250 አማራዎች በኦነግ ወይንም በወያኔ ተገደሉ ትላለህ እንጂ ምን ብለህ ነው የምትዘግበው? የጥቃቱ ሁኔታ ነው የዘገባው አዘጋገብ ስም የሚያስሰጠው። የዘር ጥቃት ሲሆን በዘር ነው ዘገባው የሚዘገበው። የሃይማኖትም ከሆነ አንዲህ ያህል ቁጥር ሰዎች በ እስላም አክራሪ ወይንም በክርስትያን አክራሪ ጥቃት ደርሷል፡ ብለህ ትዘግባለህ እንጂ ምን ትለዋለህ ታዲያ?ይግረም ብሎ ደግሞ <<ሁላችንም በሚያስነሳ መልኩ ያንድ ኢትዩጵያዊ መታሰር የትም ይሁን የትም ኦሮሞ ይሁን ያፈለገው ብሔር ዓይነት ይሁን እዚህ ላይ ራሳችንን አክቲቭሊ ኢንቮልቭ አንሆንም። አልተጎዳንም አይመስለዎትም?>>ብሎ ከከፋፍለህ ተደራጅ አቀንቃኙን በያን አሰቦን ይጠይቃል። በያን ደግሞ “በጣም እንጂ ፤አበበ ትከክል ነህ”ይለዋል ሲያሞኘው። መጀመሪያ ነገር የከፋፍለህ ተደራጅ ተከፋፈለህ አገር መስርተህ ለየብቻ ተነጣጥለህ ቤተሰብ ተበትነህ ኑር፤ የተዋለድክ ካለህም ጉዳያችን አይደለም ቤተሰብህ በታትነህ ከፈለግክ ኦሮሞ ሆነህ ኦሮሚያ ሪፑብሊክ ውስጥ ኑር ካልሆነ ከአቢሲኒያዎቹ ወግነህ ወደ ሰሜን ተጓዝ፤ እያለ የሚያስተምር አፓርታይድ ፋሺስታዊና ናዚ፤ መስፍናዊ፤ ጠባብና አድሃሪ መርሃ ግብር በተግባር አንዲውል 40ዓመት በተከፋፍለህ ኑር የሚያውጅና ተነጥሎ እንደ ኤርትራኖቹ ለብቻው ባንዴራውና ኮሚኒቲውና ስፖርት ፌደረሺን ለ 40ዓመት መስርቶ የሚንቀሳቀሰው ኦነግና ኦሮሞያ ሪፑብክ እንጂ ኢትዩጵያ የምትባል ኢምፓየር አገር መደምሰስ አለባት የሚል ግለሰብና የኦነግ ነገረፈጅ “እውነትክን ነው ፤በጣም አንጂ ትከክል ነህ አበበ”ብሎ ሲል “መዋሸትና ሕዝብን መግደል” በዛሬ ዘመን በሕግ ባያስቀጣም በሰማዩ ጌታ እንኰነናለን ብላችሁ ትንሽ እንኳ ሰብአዊ ስጋት አታሳዩም? ተሳስተናል አዎ እኛም ለስሕተቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገናል፡ ማለት ከፈጣሪና ከሕዝብ እንዲሁም ከሕሊና ጋር ያስታርቃል እንጂ እየዋሹ እየተደበቁ ከእውነት እየተደበቁ ዳር ዳር እየሸሹ ወያኔ ነው ፕሮግራማችንን ቀርጾ ለብቻችን እንድንድንደራጅና እንድንሰበሰብ ያደረገን እያሉ በወያኔ ላይ እየለጠፉ ከእውነት ለማምለጥ መሞከር ጊዜያዊ እንጂ ዝንተ ዓለም ከፈጣሪና ከሕዝብ ከእውነት አምልጠው አያምልጡትም። ወይኔ! የኢትዩጵያ ሕዝብ ምን ይበጅህ ይሆን? ወይ ትጉዱ! ዝገርም እኮ እዩ!//-// ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com