Friday, March 26, 2010

የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና

የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና ዩሱፍ ያሲን ኦስሎ ኖርዌይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ወዳጅነት ኮንፊረንስ ሳን ሆዜ፣ ካሊፎርኒያ ማርች 12 እስክ14፣ 2010 የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና የዛሬ 19 ዓመት ገደማ ከኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን በማወጅ ኤርትራ ተብላ የዓለም የመንግሥታት ማሕበረሰብ የተቀላቀለችው የአህጉራችን አዲሲቷና የመጨረሻይቱ ሃገር በታሪክ ወስጥ በተለያዩ ስሞች ነበረ የምትታወቀው።ነገር ግን በዚሁ “ኤርትራ” በተሰኘው መጠሪያ ተጠርታ አታውቅም። ከበርካታዎቹ በታሪክ ከሚትታወቅበት ስሞች ጥቂቶቹን እንመልከት።ምድሪ ባሕሪ፤ ባሕረ ነጋሽ፤መረብ መላሽ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው። ክፍለግዛቱ በሙሉ ሓማሴን ተብሎ የሚጣራበት ጊዜም ነበረ።ሓማሴን የተሰኘው አንድ አውራጃ ስም ለጠቅላላው አካባቢ መጠሪያና መታወቂያ የተሰጠበት ሆኔታ አልፎ አልፎ እንመለከታልን።በመሓል ኢትዮጵያም ሆነ በአጓራባቿ ትግራይ ሓማሴን ትናንትም ዛሬም ለደጋው ኤርትራ ነዋሪ በተለይም ለክርስትያኑ ማሕበረሰብ መለያ አድርገው መጠቀማቸው ከዚሁ አጠራር የመነጨ ነው።በማህል ሃገርም አልፎ አልፎ ሓማሴን የሚለውን ስያሜ ለአካባቢው ሁላ በጥቅም ላይ ሲወል ይታያል። አንድ እውነታ ግን ልያከራክረን አይገባም። በ1890 ጣልያን ይህንን አካባቢ በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ለአዲሲቷ ቅኝ ግዛቱ ኤርትራ የተሰኘ ስያሜ ከመስጠቱ በፊት ኤርትራ የሚባል ቦታ፤አካባቢ ወይም ሃገር አልነበረም።አራት ነጥብ።ከዚያ በፊት ኤርትራ እንደ ሃገር ኤርትራውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ አካባቢ ነበሩ ከሚሉት ጋር ጉንጭ አልፋ ክርክር ለመግጥም ዝግጁ አይደለሁም። በዚህ እውነታ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ዛሬ ኤርትራ ወስጥ ካሉት 9ኙ በሔሮች አንዱና ዋነኛው የሆነው ትግሪኛ የተሰኘው በሔረሰብ ጣልያን ከመምጣቱ በፊት ነበረው ወይ ነው ቀጣዩ ጥያቄያችን።ካልነበረ እነዚያ በኤርትራ ደጋ አካባቢ በትክክል በሓማሴን፤ በሠራዬና በአከለጉዛይ አውራጃዎች ነዋሪ የሆኑ ወገኖቻችን በምን ስም ነበረ የሚጠሩት ወይም የሚታወቁት? ሰበረ፤ ሰብ ቀድሚ ምስባሩ፤ ስሙ እንታይ ነበረ፤ ጓያ (ሰበረ) ሰው ከመስበሩ በፊት ስሙ ምን ነበረ እንደሚሉት መሆኑ ነው።ይህ አባባል የዬተኞቹ ትግርኛ ተናጋሪዎች አባባል እንደሆነ አትጠዩቁኝ። በትክክል አላውቀውም።አሁንም ለክርክር መቅረብ የሌለብት አንድ ሌላ ጉዳይ አለ። ስማቸው ምን ይሁን ምን ጣልያን በመጣበት ጊዜም ሆነ ዛሬ ይህ ማሕበረሰብ የሚናገረው ቋንቋ ምንነት ላይ ብዥታም ሆነ ጥያቄ አይነሳም።ቋንቋቸው ልክ በአጎራባቹ ትግራይ የሚነገረው ትግርኛ ቋንቋ ነውና ።ልክ በአጎራባቹ ትግራይ ወንደሞቻቸው የሚናገሩበትን ቋንቋ ተንጋሪዎች ናቸው፤ ያለጥርጥር።ሰለዚህ እነሱም ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው።በኢትዮጵያ ትግራይ ነዋሪ የሆነው ብሔረሰብ ራሱን ተጋሩ ወይም ትግራዎት ብሎ ይጠራል። ይህ በሔረሰብ በአጎራባች በሔረሰቦች በተለያዩ መጠሪያዎች ይታወቃል።ይህም በኢትዮጵያቸን በበሔረሰቦች መካከል ያልተለመደ አይደለም።በማሓል ሃገር በአማርኛ ተናጋሪው ዘንድ ትግሬ ተብሎ ይታወቃሉ።በሔረሰቡ በራሱ ማንነትም ሆነ ሰለሚናገረው ቋንቋ የሚያሻማና የሚያነታርክ ቁም ነገር የለም።የሚያከራክርም ጉዳይም የለም።በአንፃሩ በኤርትራ ሰላሉት ተመሳሳይ የትግርኛ ተናጋሪዎች ይህንኑ ማለት አንችልም፤አያስኬድም።የሚናገሩት ቋንቋ ያው ከመረብ ወንዝ ሻገር በትግራይ የሚነገርው ራሱ ትግርኛ መሆኑን አይክዱም።የእኛው የትግርኛ አነጋገር ዘዬ የጠራና የተለየ ነዉ የሚሉትን እንደተጠበቀ ሆኖ ማለታችን ነው።የሚያከራክረን፤የሚያነታርከንና አሻሚ ሆኖ ለጽሁፋቸን መነሻ የሆነው ግን በኤርትራ ወስጥ ያሉት ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ልዩ ማንነት መለያና የብሔረሰቡ አሰያየም ጉዳይ ብቻ ነው። ሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪዎች እንደ ማሕበረስብ አንድ ቋንቋ እንጂ አንድ መጠሪያ ስም የላቸውም።ይህንን በአጽንኦት የሚናገሩት የኤርትራ የፖሎቲካ አድራጊዎች ማለት የፖሎቲካ ፓርቲው ፤ መንግሥትና የሕብረተስቡ መሪዎች ናቸው።ሕዝቡም ይህንን ተከተሎ የጋራ መጠሪያ ስም የለንም ባይ ነው።ሰለሁለቱ በምናወሳበት ወቅት ትግሪኛ ተናጋሪዎች ብለን ለመጥራት የተገደደነውም ለዚሁ ነው።ለምን ትግሪኛ ተናጋሪዎች እንላቸዋለን? ሌላ የወል መጠሪያ የላቸውም ወይ? ለምን የላቸውም? ከሌሎቹ ድንበር ሻገር (ዘልል) ብሔረሰቦች በምን ይለያሉ? በምንስ ይመሳላሉ? በዚሁ ረገድ ድንበር ዘለል ከሆኑት ከኩናማ፤ከአፋርና ከሳሆዎቹ በምን ይመሳሰላሉ? በምንስ ይለያያሉ? ለጹሑፋችን መንደርደሪያ መነሳት ያለበቸው ጥያቄዎች ናቸው። የሁለቱ ሃገሮች ድንበር ሻገር የሆኑት ሌሎቹ እንደ ኩናማ፤ ሳሆና አፋሮቹ ዘንድ ይህንን ዓይነቱ አንድ የመሆንና ያለመሆኑ ጉዳይ ሲያከራክር ወይም ሲያሻማ አንመለከትም።አያከራክርምም አይሻማምና።ኤርትራ እንዳንድ ነጻ ሃገር ሆና እውቅና ከተጎናጸፈች በኋላ እንኳን በሁለት ሃገሮች የምንኖረ አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸው አልቀረም።አፋሮቹ በጀቡቲም ጭምር ቅርንጫፍ ሰላላቸው በሶስቱ ሃገሮች የምንገኝ አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸው አልተውም። አፋር፤ሳሆና ኩናማ o አንድ ቋንቋ ያለን o አንድ ባሕል ያለን o አንድ መጥሪያ ስም ያለን o አንድ ሕዝብ ነን ሲሉ እናዳምጣለን።ትናንተም ዛሬም።አግባብነቱ አጠያያቂ አልሆነም። ለምን ታዲያ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ አሰያየም የተለየ አቃቂር አስፈለገው መባሉ አልቀረም።ጉዳይ ከፍተኛ የፖሎቲካ እንደምታም አለው ።ዛሬ የኢትዮጵና የኤርትራ ሕዝብ ለማቀራረብ በምናደርገው ጥረቶች ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለን። ሰለዚህ ብዙ ምክኒያቶችን መደርደር ይቻላል።በኤርትራ ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ከሃገሪቷ 9 ብሔረሰቦች አንዱ ብቻ ቢሆንም ቅሉ ፤ከኤርትራ ሕዝብ እኩሌታ ይሆናል፤ በቁጥር ደረጃ።ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቷ ኤርትራ አፊሰላዊ ቋንቋ ነው። የኤርትራ ሕዝብ ቁጥርም ሆነ የሕዝቡ የብሔረሰብም ሆነ የሃይማኖት ስብጥር ስሜት ቀስቃሽ የሆነ በነፃይቷ ኤርትራ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚያዙት ጉዳዮቹ ዋናው ነው።ምክኒያቱ እምብዛም አያመራምርም።ግልጽ ነውና።ትግርኛ ተናጋሪው በአማዛኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ በዚሁ ወገንና በሙስሊሞቹ መካካል ያለው ግንኙነት ይመለከታል።የኤርትራ ፖለቲካ ድርጀቶች ብሔራዊ አንደነት የሚሉትን ለሃገርቷ ሕልወና ሲባል በጥንቃቄ የተያዘ ጉዳዩ ነው።ለዚህም ነው የሙስሊሙና የክርስቲያኑ የቁጥር ምጥጥን አምሳ፤ አምሳ ፐርሰንት ተብሎ የሚታለፈው፤ዝንተዓለም። ልክ ሰለ ሊባኖሱ ስብጥር እንደሚነገረው መሆኑ ነው። ስብጥሩን ማወቁም ሆነ ይፋ ማድረጉ አይታሰቤና አይነገሬ ነው። ሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ ያካባቢ መሳፍንቶች መካከል ሲጧጧፍ በነበረው ቁሩቁስ ባንድ ወቅት እንድ ትግራይ አካል በሌላ ጊዜ ደግሞ ራሱን በቻለ አሰላለፍ ተካፋይና ተዋናይ የነበሩ መሳፍንቶች እንደነበሯት የሚካድ አይደለም።በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው የታሪክ ጊዜ ይህንን ግዛት የማስፋፋቱ፤ ማስገቡሩ፤ካንዱ መስፍን ጋር ወግኖ በሌላው ላይ መረባረቡ፤ ተለዋዋጭ የወደጅና የጠላት አፈራረጅና አሰላለፍ ወስጥ የደጋው ኤርትራ መሳፍንት ነበሩበት። በዘመነ መሳፍንቱ ማብቂያ ላይ አጼ ቴድሮዎስ ሃያልነቱን በጦር ሜዳ አስመስክሮ ሁሉን በመጠረንፍ በአክሱም ከተማ ነጉሠ ነገሥት በተባሉበት ሂደት የሃዘጋ ጸዓዘጋ መሳፍንት ነበሩበት።እነ ራስ ወልደሚካል በአብነት መጥቀሱ በቂ ይመስለናል። በኋላ ላይ አጼ ዩሃንስና አጼ ምኒልክ የዘውድ ይገባኛልና የሥልጣን የመነጣጠቁ ቁሩቁስ ወሳኝ ሚና ባይጫወቱም ከጫውታው ውጭ አልነበሩም። እነዚያ መኮንንትና መሳፍንተ ሚወዛገቡት ከላይ በተመለከትናቸው በእነዚያ በአራቱ ወይም በአምስቱ ማዕከላዊው በዚያኑ ዘመን የሃገርቷ እንብርት በነበሩት ትግራይ፤ጎንደር፤ሸዋ፤ጎጃምና ወሎ ባማከለ አካባቢ ነው።እንዚሁ ግዛቶች ናቸው እንግዲህ በተለያዩ መጠሪያዎች ቢታወቁም የታሪካዊቷና ነባሯ ኢትዮጵያ እንብርት ሆነው የሚቆጠሩት፤ በታሪክ ጸሓፊዎች ዘንድ።በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አበሲኒያ ፕሮፕር፤ አበሲኒያ ሃርትላንድ ትብለው የሚታወቁት 5 ቱ ኮር ግዛቶች ማለታችን ነው።ላስታና ዋግ ምንም እንኳን የወሎ አንዱ ክፍል ሆኖ ቢታወቁም ቅሉ እንዳንድ ራሱን የቻለ ግዛት ሆኖ መታየቱ አልቀረም።ከአምስቱ በተጨማሪ ማለታቸን ነው።ልክ እንደዚህ ኤርትራም ከላይ በተመለከትናቸው የተለያዩ ታሪካዊ መጠሪያዎች ታውቃ እንዳንድ ራሷን የቻለ ግዛት ሆና የታየችበት ጊዜ ነበረ ማለት ነው። ይህንኑ የዘመነ መሳፍንት እርክቻና ቁሩቁስ ወደ ማብቃቱና አዘንብሎ አጼ ምኒሊክ የነጉሥ ነገሥት ሥልጣንን ጠርንፈውና አጠቃልለው ባንድ ጠንካራ ማዕከል ባማዕከሉበት ወቅተ ላይ ነበረ የኤውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ወደ አካባቢው ብቅ ማለት የጀመሩት።በአድዋ ጦርነት ዋዜማ እኔ ካንተ አላንስም የመሳፍንቶች ፉክክር በቅኝ ገዢቹ አይዞህ ባይነትና የዘመናዊ መሳሪያዎች እርዳታ ታክሎበት ቅጥሎዋል። ያም ሆነ ይህ እስከ ዓድዋ ጦርነት ዋዜማ ድረስ፤ o የጋራ ቋንቋ (እሱም አነጋጋሪ ነው ባዮች አልታጡም) o በሓባሻነት ላይ የተመሰረቱ የጋራ የእሴቶች ሥርዓት o የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ቤተክርስቲያን ቁርኝት o መረብ ሻገር ታሪካዊና ቤተሳባዊ ዝምድናዎችና መወሳሰቦች o ዓዲ፤ ርስቲ፤ የጉልቲ የጋራ ሥሪት o ልማዳዊ የእንዳ አባ ሕጎችና ትድድር ሥርዓቶች ትሥሥሮች በጥብቅ ያቆራኘው አንድ መለያ ማንነት ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ማሕበረስብ ነበረ ማለት ያስደፈራል። ከጣልያን ቅኝ ግዛትነት በኋላ ግን ትግርኛ ተናጋሪው ከሌላው ድንበር ተሻጋሪ ማሕብረሰቦች በተጻረረ መልኩና አኳኋን በጋራ እንኳን የምንጠራበት ስም የለንም እስከ ማለት የደረሰበት ፖሎቲክዊና ባህላዊ አዲስ ማንነት አፈጣጠርና የመጎልበት ሂደት ዋና ዋና ምክኒያቶች መመለከቱ ተገቢ ነው።በተለይም ዓድዋ ጦርነት ማግሥት።በቅድሚያ ለዚህ ያበቁ ነበራዊ ሆኔታዎቹን ገረፍ ገረፍ አድረገን እንመልከት።በኋላ ላይ በፖሎቲካ ኤሌቶች ወይም ልሂቃን ሆን ተብለው የተሃነደሱና እንዲፋፋ የተደረገ ግፊቶችን ለጥቆ መመልከቱ ተገቢ ነው። ሁለቱም ማለት የጣልያን ቅኝ ግዛትነት ያስከተለው ለዉጥና በኋላ ለኤርትራ ነፃነት የታገሉ የፖሎቲካ ሃይሎች ለየቅል የሆኑ ጫና አሳደረዋል፤አስተዋፃኦ አብርክተዋል፤ያለ ጥርጥር።ለዚህ ዓለምሰገድ ዓባይ የተጣመሙ ማንነቶች (Jilted Identities-Re-imagined) በተሰኘውና በ1998 በጻፈው መጽሓፉ እየራሳቸውን ሁለት ደርጅቶች ማለት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርና ሕዝባዊ ሓርነት ኤርትራ የተለያዩ የማንነት መለያ አቅጣጫዎች መከተላቸውን ያትታል።በሌላ በኩል ሸቲል ቱሮንፎል የተባለ ኖርዌጂያዊ ሶሻል አንቱሮፖሎጂስት War & the Politics of Identity in Ethiopia በተሰኘው አዲስ መፅሓፉ ከደም አፋሳሹ የ1998/2000ጦርነት ወቅትና በኋላ ሁለት ወንድማማች ሕዝቦች የጋራ ትሥሥሮች ከሥር መሠረቱ የሚያናጉ እድገቶች እንደነበሩ በሰፊው ተችቶዋል።ጦርነቱ በማንነት ላይ በተለይም ትግራይ ያሉት ተጋሩ ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች በኤርትራውያኑ የቋን ተጋሪዎቻቸው ላይ የቋጠሩት ቂም አስመልክቶ ጦርነት በጠላትና ወዳጅ ምስል ቀረፃ ላይ የሚያሳድረው ጫና በሰፊው አብራርተዋል። እነዚህ የጋራ ቋሚ የማንነት መገለጫዎቹ የተሸረሸሩ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩት አዲስ ፖሎቲካውና ማሕባራዊ ሆኔታዎች ግፊትና አስገዳጅነት አዲስ የማንነት መፈጠር መጀመሩ አሌ የማይባል ሓቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩትና በኋላ ኤርትራን ለማስገንጠል በ1962 የነጻነት ጦርነት የተያያዙት ነጻ አውጪ ድርጅቶች ለዓላማቸው መምቻ አዲስ ኤርትራዊ ማንነትና አንድ የተለየ ሃገርና የተለየ ሕዝብ ስሜት እንዲያብብ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገዋል።የተወሰነ ውጤትም አስመዝግበዋል፤ያለ ጥርጥር። የሁለቱ ተግባራት ተደጋጋፊ ቢሆኑም ቅሉ ለየብቻቸው መመለከቱ ተገቢ ይመስለኛል።በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው በአሰብ ወደብ ላይ በዚያን ወቅት አንዲት ትንሽ የዓሳ አጥማጆች መንደር አንድ የጣልያን የመርከብ ካምፓኒ ወኪል ከሡልጣን ኢብራሂም ጋር አደረጉ በሚባለው ስምምነት የተወጠነው የኤርትራን ቅኝ ግዛት የማድረጉ ሂደት በ1890 በቀይ ባሕር ዳርቻ ኤርትራ ብለው ስም ያወጡላት መሬት በቀፈፉበት ጊዜ ፍጻሜ ላይ አድርሰዋል።በኋላ በ1893 በውጫሌ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ታክሎበታል። በውጫሌ ውል መፍርስ ሳቢያ የአድዋ ጦርነት ተቀስቅሶ ድሉ የኢትዮጵያ ቢሆንም ቅሉ በኤርትራ ጣልያናዊ ቅኝ ግዛትነት ይዞታ ላይ ያስከተለው ለውጥ አልነበረም።አንድ እውነታ ግን መረሳት የለበትም።ከወራሪው ቅኝ ገዢዎች ጎንም በማበራቸዉና በመሰለፋቸው በንጉሡ አይቀጡ የአካል ቅጣት ደርሶባቸው ወደ ዘመዶቻቸው የተመለሱት ኤርትራውያኑ ሰለ ኢትዮጵያና ንጉሡ ያስተላለፉት ኩፉ የጠላት ምስል እንደነበረ መዘንጋት የለበትም።በአማራ ላይ በጥቅል፤ በሸዋ አማራ ላይ በተለይ ባነጣጠረ ጥላቻ የተበጃጀ ሰእል። ከሌላው ትግርኛ ተናጋሪ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት አፈጣጠር ሂደት በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤ መታወቂያና መለያ መበጃጀቱ ሂደት ወስጥ ከዚህ የሚከተሉት ድርግቶችና እርምጃዎች ልብ ማለት ልያስፈልግ ነው፤ o ኤርትራ ዓድዋ ድል በኋላ በአስከሪዎቹ ላይ የተወሰደ የቅጣት እርምጃና በነጉሡ፤ በአትዮጵያና በሸዋ ላይ የፈጠረው ጥላቻ፤ o ኤርትራውያን ከተቀረው ሃገሬው (Indigenous ) ሕዝብ የተለዩ ማህበረስብ አድርጉ የፈረጀው በ1937 ጣልያን ቅኝገዢዎቹ ያወጡት አዋጅ፤ o በ1936 ለኢትዮጵያ ተብጅቶ ኤርትራና ትግራይ ባንድነት ኤርትራ ተብለው የተካለሉበት አዲስ የአስተዳደር ክፍፍል፤ o አስከሪ ተብለው የሚታወቁት የኤርትራ ተወላጅ የጣልያን ወታደራዊ ተመልማዮች ወደ ሊቢያና (ትሩፑሊ) ሶማሊያ መዝመት፤ o ኤርትራን ጠቅላላ ኢትዮጵያ ወረራ ማንኮባኮቢያ መሬት የማድረጉ መሰናዶ በአጧጧፉበት ወቅት በቅኝ ግዛቷ እንዱስትሪ፤የትምህርት፤የከተማና ታሕታይ መዋቅር ግንባታ ያስከተለው ለውጥ፤ o የአጋሚ አውረጃ ተወለጆች ወደ አሥመራ በብዛት መፍለስና በዝቅተኛ ሠራተኛነት መሰማራት፤ ኤርትራዊ የሚባል ማንነትና ሃገራዊ ስሜት ሥር የመሰደዱ ሂደትና የመገንጠሉ ትግል በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤ መታወቂያና መለያ ሥር የሰደደ የመምጣቱ ሂደት ወስጥ ደግሞ ክዚህ የሚከተሉት ድርግቶችና እርምጃዎች ልብ ማለት ልያስፈልግ ነው፤ o የኤርትራ ሕዝብ የተ.መ.ድ.የክፍፍሉን ሓሳብ አለመቀበሉና ዕደሉን እንደ አንድ ሕዝብና አሃድ ለመወሰን የመረጡብት ሂደት፤ o ከ1962 እስከ 1991 ለሰላሳ ዓመታት በመጀመሪያ በ ኢ.አል.አፍ በኋላ በ ኢ.ፒ.አል.አፍ መሪነት በተደረገው የነፃነት ትግል የተፈጠረው ሃገራዊ ማንነትና ስሜት፤ o እነ ኢሳያስ “ንሕናን ዓላማና” የተሰኘው ማኒፈስቶ በክርስትያኖች ላይ በ ኢ.አል.አፍ. የደረስባቸውን ግድያና ጫና ለብቻቸው ተደረጅተው መመከቱ እቅድ፤ በኋላ ላይ የኤርትራ ሕዝባዊ ሃይል(ሻዕቢያ) መፈጥር o ትግርኛ ተናጋሪው በሔረ ትግርኛ ያስኘው ፖሎቲካዊ ትምህርት ለኢ.ፒ.አል.አፍ ምልምሎች መሰጠት መጀመር፤ o ከወያኔ ሓርነት ትግራይ መስርታ ወዲህ ደግሞ የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ትግል ዓላማና መደምደሚያ የመለያያቱ አስፈላጊነት ፤ o የ 1998.2000 የድንበሩ ጦርነቱና ከኢትዮጵያ ኤርትራውያን በጅምላ ማባረሩ በሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪውች መካከል የፈጠረው የጥላቻ ድባብ፤በዚሁ ሳቢያ ትግራይ ትግርኚ አስተሳሰብና መቀራረብ መኮሰሰ፤ o ዛሬ እንደገና በኤርትራ በሁለቱ ሃማኖቶች መካከል በመፈጠር ላይ ያለው ውዝግብ ክርስትያን ወጎኖቸን ማሳሰብ መጀመር፤ እንዚህና ሌሎች በርካታ እክተሮች በኤርትራ የብሔረ ትግርኛ ኤርትራዊ ብሔርተኛነት እየጎሎበት ነጥሮ እንዲወጣ አመቺ ሆኔተዎችን ፈጥሮለታል። ከነጻነት በኋላ በሔረ ትግርኛ የተሰኘው አጠራር ለትግርኛ ተናግሪው እየተዘወተረና የተለመደ መጥቶዋል። ይህ በትክክል መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም ኢ.ፒ.አል.አፍ ድርጅት ፖሎቲካ ትምህርት ማስተማሪያ ብሎ ባዘጋጃቸው ጽሁፎች አካል እንደ ነበረ መዛግብት ያሳያሉ።በዚሁ ላይ ብቻ መቼ ቆመ። በሔረ ትግርኛ አነሱ አዲሱ ኤርትራዊነት የማንነት መንፍሰ ባለቤቶች መሆናቸው ይበልጥኑ ለማስመሰከር ይጥራሉ።በተልይም ኤርትራ ተገንጥላ ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቱ ሃገር ቋንቋ ከሆነ በኋላ ትግርኛውን “ኤርትርኛ” ማሰኘት ይዳዳቸዋል።ከእነሱ ቁጥር እጥፍ ደርብ ቁጥር ያላቸው ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዎት በኢትዮጵያ ትግራይ መኖራቸው እየታወቀ፣ ኤርትራውያን አዲሱ ሃገራዊ ማንነትና ምንነት ለማጎልበትና ከትግራዊ ማንነት በተቃራኒው ተለይቶና ነጥሮ እንዲወጣ ልዩነቶችን ሆን በለው ያገዝፋሉ።በአንፃሩ የጋራ ትሥሥሮችና እሴቶችን ያንኳሰሳሉ።አሁንም ሆን ተብሎ። በጋራ ትግላቸው ጊዜ የተፈጠረው ወዳጅነት ክደው ከጦርነቱ በኋላ አንዱ ሌላውን ጭራቅና የክፉ ከፉ አድረገው ይስላሉ።በኤርትራና በኢትዮጵያ መረብ ሻገር ያሉትን ሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪ ስብስቦችን በመካለልና በማጠር የተለያዩ መለያ መታወቂያዎች የመፍጠሩ ሂደት በምር የተያያዙ ይመስላሉ። ሁለቱም ገዢ ፓርቲዎች በዚሁ በማካለሉና በማጎልበቱ ተግባር ቢጠመዱም በኤርትራ ያለ የትግርኛ ተናጋሪ ወገን ነው ይህንን ሥራዬ በሎ የተያየዘው። በሁለቱ ሕዝቦች መሃል የነበሩትና ያሉት ተመሳሳይነትና ትሥሥሮች የሚክዱትም እነሱ ናቸው። ለዚሁ በቂ ምክኒያቶች ማፈላለግና ማገኘት የሚሳነን አይመስልም። የተለያዩ ተፎካካሪ ማንነቶች እርስ በርስ እየተላተሙና የእተፋጩ ነጥሮ ለመውጣት ቅርጽ ለመያዝ የሚሞክሩበት ፖሮሰስ እንመለከታለን። አንዳንድ ጊዜ “ማንነት የማይዳሰስና የማይጨበጥ ምናብ ወለድ የፈጠራ ውጤት ነው” ይሉናል ማሕበረዊ ሳይንስ ተመራማርዎች።ይህ ደግም ሂደቱን ውስብስብ ያደርገዋል። በሔረ ትግርኛ ማንነት ከተለያዩ አጓራባች ማነቶች ጋር እያላተመ ነው።ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ፤ o ተመሣይ ትግርኛ ቋንቋ ከሚናገሩት ሙስልም ከሆነው ጀበርቲ ማንነት፤ o ትግረ ቋንቋ ተናጋሪ ባመዛኙ ሙስሊም ከሆኑት መታሕት ማንነት o ከኤርትራውያን ቆላ ሙስልሞች በጅመላ ይፎካከራል፤ o ከትግርኛ ተናጋርው ትግራዋይ ብሔርተኛነትና ማንነት ጋር ይፎካከራል፤ o ከሸዋ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ታሪካዊ ፎክክሩ አሁንም ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላም እንዳለ ነው፤ o ከዓባይ ኢትዮጵያዊ ሃገር አቀፍ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ጋር ሕልውናዊ ስጋት አለው፤ በዚሁ ሂደት ኤርትራዊው ትግርኛ ብሔርተኛነት ኤርትራዊ ቡሉኮ ለመደረብ ለምን እንደሚሻ ማወቁ አያስቸግርም።ኤርትራዊነት ወደ በሔረ ትግርኛነት ለመወሰና ለማውረድ ሙከራው ግልጽ ነው።ትግርኛ ቋንቋውንም ኤርትርኛ ማሰኘቱ ከዚሁ ፍላጎቱ የመነጨ ሆኖ እናገኛለን።ካላይ ከተመለክትነው በርከታና ወስብስብ ሂደቶች ለምን ኤርትራ ወስጥ ያለው የትግርኛ ተናጋሪዎች ማንነትና አሰያየም አሻሚና አነታራኪ እንደሆነ በመጠኑ እንረዳለን። በጭሩ ውስብስብ የማንነት አፈጣጠርና አጎሎባባት ሂደት ለመቃኘት ሞክረናል።እውነትኛና ጋህድ የሆኑ ወይም የምናብ የፈጠራ ዉጤት የሆኑትም ሁላ። ማንነት በምናብ የተሳለ የፈጠራ ውጤጥ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭና በመቀያየር ያለ ፍርጅ ነው።ውስብስበነቱም ከዚሁ ጸባዩ የሚመነጭ ነው። ከትግራዋይ ጋር የጠመዱበት የፍቅርና የጥላቻ ፍርሪቆሹ ለመረዳቱ ሊረዱን የሚችሉ መንደርደሪያዎች አቅርበናል። አንዱ ሌላውን ዝቅ አደርጎ የመመልከት በተለያዩ አልባሌ ስሞች መሰጣጠቱ ሚስጥርም ገለጥ ይላል ብለን እንገምታለን። ማጠቃሊያ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ባንድ ሃገር ልጅነትም ሆነ በሁለት ሃገር ልጅነት ጎን ለጎን መኖር የጂዮግራፊና የታሪክ ግዴታቸው ነው።የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች እነዚህ ሁለት አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ሳይነጋገርና ሳይቀራረብ ይቀራረባሉ ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው። እንዴያውም በእኔ እምነት ለሁሉም መቀራረብ ጥረቶች ቅደመ ግዴታ ነው፤ የእነሱ መቀራረብ። አንድ የትግርኛ አባባል አለ ።እንቁጩን አላውቀውም እንጂ።የተጣሉ የአጎት ልጆች ወንድማማች ወላጆቻቸው ሳይነጋገሩ ልጆቻቸው ይነጋገራሉ፤ ይደራረሳሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው የሚል ።ትክክል ነው። ባንዳንድ ሃገር ወዳዶች ለኢትዮጵያ ሕልውናና አንድነት ጠንቅ ሆኖ የሚታያቸውን የሁለት ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደገና እንዲወዳጁና እንዲቀራረቡ ማድርግ ጸረ-ኢትዮጵያ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱ መርዳት የሚመስላቸው የፖሎቲካ የወሃን አይታጡም። አሻግሮ መመለክት የተሳናቸው ናቸው። በተቃራኒው መቀራረቡና መነጋገሩ ወሳኝነት ያለው እርምጃ ነው፤ የሁለቱን ሃገሮች ሕዝቦች ለማቀራረብ።ዛሬ የዚህ የተሰበስብንበት ዋናው ዓላማ። አመሰግናለሁ!!!!