Thursday, August 21, 2008

From AYalnesh Regarding Azeb Gola

ኦገስት 22/ 2008 ወይ ጣጣ! እውነት ተጋዳሊት ወይስ የቤት እመቤት! ከአያልነሽ
አጀብ! እግር ሄዶ ሄዶ . . . አሉ በዚህ ሰሞን የአናት ኢትዮጵያን አዳርና ውሎ ልጎበኝ ወደ ድረ ገጾች ዘንድ ጎራ ስል፣ ድንገት የወያኔ/ህወኃት ንብረት የሆነው አይጋ በጥፊ ብሎ አጠናገረኝ። እንደ አገሬ ባህል ቢሆን ኖሮ ምች ላጠናገረው ድንገተኛ የምቹን መድኃኒት ፍለጋ ስንት ቦታ ላይ በተወጣና በተወረደ ነበር። ከደደቢት በፈለሰው ምች ተመትቸ ''እኔን'' የሚለኝ ባላገኝም አይጋ ላይ አወዳደቄ ግን ድንገትና ሳላስብ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም፤ ይባስ ብሎ ከወደቅሁበት ቀና ብዬ አይጋን ስቃኝ ደግሞ " ኢንተርቪው ከፈርስት ሌዲ አዜብ መስፍን ጋር'' ይልና የተጋዳሊት አዜብ ጎላ ምስልም አብሮ ተለጥፏል። ሶስቴ አማተብኩና ስፈራ ስቸር ዘልዬ ይህንን መጠይቅ ከፈትኩ። መቼስ የአነ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ኢትዮጵያ ዛሬ በእነ አዜብ ጎላ እጅ ወድቃለችና የምዬ ኢትዮጵያን አዳርና ውሎ በየጊዜው መከታተልና ማዳመጥ ለነገ የማንለው፣ ጊዜ የማይሰጥን ጉዳያችን በመሆኑ የኢትዮጵያዊያኖች በሞላ ግዴታና ኃላፊነት መሆኑ አልቀረም። እዬዬም ሲደላ ነው ተብሎ የለ።
ዛሬ እናት ኢትዮጵያ በወያኔ አገዛዝ ሥር እግር ከወርች ታስራ እየማቀቀች በምትገኝበት ሁኔታ፣ የጎላ ልጅ አዜብ እንደምትለውና እንደነገረችን አይደለችም ኢትዮጵያችን። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህጻናት የሚቧርቁባትና በደስታ የሚፈነጥዙባት ሳትሆን ይልቁንም በግልባጩ እይታ ስንቃኛት ሚሊዮኖች በ “አረንጓዴው'' ረሃብ የሚረግፉባትና ሕጻናት የሲቃ ለቅሶ እያሰሙ ልብ የሚሰብረውን ዋይታቸውን የሚያሰሙባት ሲኦል ናት። ይህንን እውነታ በAሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች ሳይቀሩ በፎቶ ግራፍ አስደግፈው እየዘገቡት የሚገኘውን ሐቅ በዘረፉት ሀብቷ ለሚምነሸነሹት ዘመነኞች ለነ አዜብ ጎላ ግን ዛሬም ድብቅ ነው። እስቲ ወደ ቁም ነገሬ ከማለፌ በፊት እግረ መንገዴን እንድ ያስደነቀኝን ትዝብቴን ላካፍላችሁ።
የኢትዮጵያን ፈርስት ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ አዜብ ጎላን ከልክ በላይ ሄዶ ያለ የሌለውን ሙገሳ Aጎናጽፎና እንዲህ ተጨነቆና ተጠቦ ከስሟ በፊት ''ቀዳማይ እመቤት" በማለት ሊጠራት የሞከረው ጋዜጠኛ (ልብ ብሎት ከሆነ) ከጤፍ ፍሬ እጅግ አሳንሶ በሚያሳይ መንገድ ይህንን አጓጉል የሆነ ከንቱ ውዳሴን እንዲህ በማለት አጣጥላዋለች።
''ቀዳማይ እመቤት ማለት የእገሌ ሚስት ነሽ ለማለት ነው፣ ይሄ ደግሞ ማንነቴን ስለማይገልጸው አባባሉ ግምት ሰጥቶኝ አያውቅም፤ አላስብበትምም እና ለእኔ ይህ አጠራር ትርጉም አይሰጠኝም''
በማለት ጋዜጠኛውን ጥፍሩ ውስጥ እንዲገባ አድርጋዋለች። ቅሌት። ወይዘሮ/ ወይዘሪት የተባሉት አባባሎቻችን ምን አጠፉና ነው ይሄ ሁሉ ጭንቀት ጃል። ጋዜጠኛ! ቂ! ቂ! ቂ! ቂ! ቂ ! አቤት መጥኔ ሳይቸግር ጨው ብድር አሉ። አጃይብ! እንዲህ እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ያለ የሌለን ከንቱ ውዳሴ በማዥጎድጎድ ይካኑና ሰውን ከሰውነት እንዲወጣ ያደርጉታል። ባለፈው ሥርዓትም እንዲሁ ደካማ የሆኑ ግለሰቦች ውዳሴ ከንቱን አንግሠው የደርጉ ዋና ቁንጮ ለነበረው መንግሥቱ ኃ/ማርያምን አሳብደው አንድ ትውልድ ተቀጥፏል።
የቅርብ ትዝታዎቻችን መለስ ብለን ስንቃኝ ''ቪቫ መንግሥቱ ኃ/ማርያም! ከጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር ወደፊት! ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!'' የሚሉትና የመሳሰሉትን የቃላት ሰይፎች ያስታውሷል። ሰውን ከሰውነት የሚያወጣ የግብዞች ልክ የሌለው የከንቱ ውዳሴ ስጦታ። አዜብ ጎላን እንግዳው አድርጎ ያቀረባት “የኢትዮጵያን ፈርስት” ጋዜጠኛ ደግሞ እንዲሁ ኢትዮጵያን እያፈራረሰ ያለውን የወያኔ ቡድንና አገዛዝ ቁንጮ ለሆነችው ሴት ይሄን የመሰለ አስገማች ውዳሴን ማንቆርቆር እንኳን ለታዛቢ ቀርቶ ይሉኝታ ላልለመደባትና ላላሳደጋት አዜብ ጎላም ጭምር ውዳሴው አስደምሟታል። አጀብ! የጉድ አገር። ውድ አንባቢዎች! ሌላም ገጠመኝ ልጨምራችሁ። እስቲ በጥሞና ተከታተሉት እባካችሁ! ገጠመኙ እንዲህ ይነበባል።
ጥቅምት 14 ቀን 1989 ዓ.ም ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የአቶ ታምራት ላይኔን ''ኃጢያት" ዘርዝረው ''ከም/ጠ/ ሚኒስትርነትና ከመከላከያ ሚኒስትርነቱ እንዲነሳ ወስኛለሁ'' በማለት ለምክር ቤት ሲናገሩ የም/ቤቱ አፈ ጉባዔ ዳዊት ዮሐንስ ፈጠን ብለው “የአቶ መለስን ውሳኔ የምትደግፉ የምትቃወሙ'' በማለት የምክር ቤቱን አባላት ድምፅ አሰጡ። በህገ መንግሥቱ እንደሠፈረው ም/ጠ/ሚኒስተሩንም ሆነ ሚንስትሮችን ከሥልጣን የማንሣቱ መብት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያልተሰጠና ለጠ/ሚኒስትሩ የተተወ ሆኖ ሣለ አቶ ዳዊት ዮሐንስ ከሕገ መንግሥቱ የወጣ አሠራር ሲከተሉ፣ ሁሉም የም/ቤት አባል እጁን በማውጣት ለሕገ መንግሥቱ ባእድ መሆኑን አረጋግጧል። ከዚያ ሁሉ የም/ቤት አባል የአቶ ዳዊት ዮሐንስ አካሄድ ሕገ-ወጥ ነው ብለው ያረሟቸው ራሳቸው ጠ/ሚኒስትር መለስ ብቻ ነበሩ" ይላል (ኢትኦጵ ቅፅ 3 ቁ.ጥር 026 ሀምሌ 1993ዓ.ም) አያችሁ! ጩሉሌው ለገሠ ዜናዊ አስቀድሞ እንዲቀል ያስደረገውን ዳዊት ዮሐንስ፣ ተመልሶ አራሚና አስተካካይ ሆኖ ቀረበና ዳዊት ዮሐንስን የለመደበትን ቅሌት አከናንቦ ተጠቅልሎ እንዲተኛ አድርጎታል። ወይ መቸገር! ''ሳይቸግር ጨው ብድር'' የሚያሰኘው እንዲህ ዓይነቱ ቅሌት ነው። አያድርስ! ነውየሚባለው።
በጄ! የተከበራችሁ አንባቢዎች ሆይ! ወደ ቁም ነገሬ ልመልሳችሁ፤ የኢትዮጵያን ፈርስት ጋዜጠኛ እንግዳ የሆነችው ተጋዳሊት አዜብ ጎላ ቆይታ ስላደረገችበት ጉዳይ እንዳልወስዳችሁ የአዜብ ጎላ ጨዋታ እንቶ ፈንቶ ሆነብኝና ቁም ነገር ባጣበት እሳት ካየው ምን ለየው እንደተባለው ከባለቤቷ ከለገሠ ዜናዊ የተለየ ነገር ሳታወራ ሄደች። ነገር ግን የተለመደው ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ዲስኩር በለመድነው አባባል "በኢትዮጵያ ሠላም፣ ልማትና እድገት በከፍተኛ ፍጥነት እየተተኮሰ ነው፤ ነገር ግን እርግጥ ነው ይሄንን የጀመርነውን ልማታችንና እድገታችንን ለማሳካት ከዚህ በተሻለ ቅልጥፍና እንዳናስኬደው ማነቆዎች ገጥመውናል፤ ትልቁ እንቅፋትና ማነቆ ደግሞ መጀመሪያውኑ ከደርግ የተረከብናት ኢትዮጵያ ደሃና ባዶ የነበረች መሆኗ ነው" አለችን እመት አዜብ። ወይ እድሜ ዘልዛላው! ጆሮ መዝጊያ የለው ጎበዝ! ምን የሚሉት አማርኛ ነው? እንዴት እንዴት ነው ጨዋታሽ አዜብ? በባዶ እግራቸው ያለጫማ የገቡት የደደቢት ዘመነኞችን ዓመት ሳይሆናቸውና ሳይሞላቸው ሚሊየነር ያደረገች፤ ባለሃብትና ባለጸጋ አድርጋ ውበትን ላላበሰች፣ ያ የመከራና የስቃይ ዘመንን አራግፋ ያስጌጠች ቅድስት ኢትዮጵያ እንዴት ዛሬ በአዜብ ጎላ ድሃ ናት ተብላ ትታማ? ኧረ የሰው ያለህ! ''አፍን ይበሉበታል እንጅ ከፉ አይናገሩበትም'' የተባለውን ብሂል የጎላ ልጅ አዜብ ባትሰሚ ይሆናል። ይቅር ይበልሽ እቱ።
የሕዝብ ድምጽ ይከበር!
የታሰሩ የፓለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ቸር ይግጠመን!