የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ
Ethio Semay
አንተነህ ጌትነት ሙላቱ (የሶማው)
አውስትራሊያ
ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ ውጭ ሀገር በተማሩ ደናቁርት ፍጹም አደርባይነት በማዘኔና እጅግ ግራ በመጋባቴ እንደሆነ ታሳቢ ይሁንልኝ ። በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ በዶ/ር ፈቃዱ ዋቅጅራ፣ በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ወ/ሮ ብርቱካን ሚዴቅሳና ዳንኤል ክብረት የመሳሰሉ አሽርጋጂነት እጅግ ቆሽቴን በማረሩ ነው!!! ለምን አሻርጋጅ ሆኑ? ቢባል ዶ/ር አብይ ኢንሳ ውስጥ ሲሰሩ ብዙ ሚስጢር ስለሚያውቁ እነዚህን ግለሰቦች እያስፈራሩዋቸው ይሆን የሚል ግምት አለኝ ምክንያቱም “ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ዝላይ አይችልም” ይባል የል። ዋናው ጉዳዬ ግን ጥር 23/2020 በአንዳፍታ የቀረበው የዶ/ር ዳኛቸው ፍልስፋና በማለት የስጡት አድርባይ የፖለቲካ ትንታኔ ነው። በተደጋጋሚ እንደምለው “ መማር በራሱ አዕምሮ አይደለም የአዕምሮ መደገፊያ እንጅ” ይህቺ ጥቅስ እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አይነቱ ለሰብዕና ቅንጣት ያህል ደንታ የሌላችውን በትክክል ትገልጻቸዋለች።
ዶ/ር ዳኛቸው አቶ ያሬድ ጥበቡንና ጋዜጤኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬን ስም ማጥፋቱ ግለሰቦችን አጠልሽቶ ያለፈ እንደሆነ አድርገን ካየነው እጅግ ተሳስተናል። ይህ በኢትዮጵያዊነት ጭንብል ተደብቆ እውነትን ለመግደል የተቃጣ ጅምላ ጨራሽ ቅጥፈት ነው። በኢትዮጵያዊነት ስም ሀገርን መግደል ኤርትራ ምድር ውስጥ ዶ/ር ብርሃኑና አቶ አንዳርጋቸው እንዴት ይፈጽሙት እንደ ነበር አስቀድሜ በአካል ያየሁና የተረዳሁ በመሆኔ ከ2013 ጀምሬ ብጽፍና ብጮህም ስሚ አጥቼ ነበር። ምክንያቱም ሰው የሚለካው በያዘው እውነትና ሰብዕና ሳይሆን ፈረንጂ በሰጠው የወረቀት ክምር አምላኪ በመሆኑ ሰሚ በማጣቴ ቆሽቴ እያረረ በዝምታ ለመቀመጥ ተገደድኩ።“ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራው ይምከረው” እንደተባለው ጊዜ ቁልጭ አድርጎ እውነቱን ቢያሳየንም አሁንም ለመታለል ዝግጁ በመሆናችን ዶ/ር ዳኛቸው እንድፈለገ ሲቀልድብን እጃችንን አንስተን ማጨብጨባችን ቀጥለንበታል። አብይ የወደቀ አሻግራችኋለሁ ሲልና አሜሪካ በመጣ ጊዜ ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ከሩቅ የአሜርካ ስቴት ከነ ባሌቤታቸው መጥተው ለመገናኜት ቢሞክሩም ዶ/ር አብይ ግን ለማናገር ሲጠየፏቸው ነበር ኦነግነታቸውን በግልጽ ያስመሰከሩት የዚያን ጊዜ ነበር። ይህንን ሁሉ እያዩ አሁንም በጭፍን የሚደግፉት ፈረንጅ ምሁራን ብሎ ወረቀት የካበላቸ የፈረንጅ ተመሪዎች መሆናቸው ደግሞ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው ነው።
የተነሳሁበትን ርዕስ እንዳልዘነጋ ወደ ጉዳዬ ልግባ ዋና ጉዳዬ አንድአፍታ በዩቲዩብ ባውጣው በዶ/ር ዳኛተው ፈላስፋዊ ትንታና ነበር። ትንተናው እንዲህ ነው “ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ለመባል የግድ ምርጫ ማሸነፍ አለባቸ” የሚለው ስቦኝ ነበር። ሲቀጥል “ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ እንዲሆኑ ምርጫ በምርጫ ማሸነፍ አለባቸው ይህንን ነግሬአችኋለሁ ይህ ወዲያ ወዲህ የሌለው ነው ሲሉ ምን ማለት ፈለጋው ነው በማለት ስከታተለው እዛው መልሱን ስለሰጡኝ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ። “ምርጫ በምርጫ እና ይህንን ነግሬአችኋለሁ ይህ ወዲያ ወዲህ የሌለው ነገር ነው ብለው ረገጥ አድርገው ያላዘኑብን። ”በግልጽ ቋንቋ ከአብይ ውጭ ምርጫ የላችሁም በማለት እቅጩን ነግረውናል። ድሮ በእናንተ ቋንቋ ንዑስ ከበርቴው መሃል ሰፋሪ ነው ትሉን ነበር። መሃል ሰፋሪነቱን መርጠውት ከሆነ አርፈው ቢቀመጡ የተሻለ ነበር። የገደል ማሚቶ ጭሆቶ ግን መልሶ የሚያስተጋባው ለእርሶ እንጅ ለሌላ ኢትዮጵያዊ እንደማይሰማው እርምዎን ያውጡ!!!
ሌላው ደግሞ ወ/ሮ ብርቶካን ሚዴቅሳ ይቅርታ ወ/ርት ነው ለካ ያሏት? የዲሞክራሲ አጋፋሪ የምርጫ ቦርድ ቁንጮው ላይ ተቀምጣለችና አትጨነቁ ይሉናል። አንድ አባባል ትዝ አለኝ “ እኔ የማዝነው አሁን ሰላታለልክኝ ሳይሆን ወደፊት ላምንህ ባለመቻሌ ነው” የምትለው ጥቅስ ብርቱካን የዲሞክራሲ አጋፋሪ ነች ላሉን ምላሽ ይሰጠናል። ወ/ሮ ብርቱካን የዲሞክራሲ አጋፋሪ እንዳልሆኑ በዚህ በሁለት ማስረጃዎች አረጋግጥልዎታለሁ፦ 1ኛ፣ የአዲስ አበባ ከተማን ምርጫ ከፀጥታ ችግር አንጻር ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ያሉት የዲሞክራሲ አጋፋሪ የሲዳማን ሪፍረንደም እንዲካሄድ ማድረጋቸው ምን ይሉታል? 2ኛ፤የብልጽግናን ፓርቲ ሌላው ይቅርና ሊቀመንበሩ ማን እንደሆነ እንኳን ሳይታወቅ እንደ ፓሪቲ መቀበላቸው ምን ይባላል? ሆድ አዳሪ በጌታው ሳንባ ይተነፍሳል እንደሚባለው ጌታዎ አብይ እኔ ዲሞክራሲያዊ መሪ ስለሆንኩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንድትወስኑ እለምናለሁ እንዳሉት ማለት ከሆነ እናንተ ተቀበሉት ኢትዮጵያዊያን ግን “ ክላልን አሪዎስ” ከማለት ውጭ ሌላ ልንልዎት አንፈልግም።
ሌላው እጂግ የሚገርመው የታከለ ንጉሱ ጥላሁን ሆኑ እንዴ? ለማለት ያበቃኝ ቃል በቃል የተናገሩት አሳፋሪ የሚጋጭ ንግግሮዎን በመስማቴ ነው። የተናገሩትንም እንዲህ ቃል በቃል አቀርበዋለሁ “ ወጣቱ ኢንጂነር ታከለ ኩማ ዶ/ር ዳኛቸ እንደጠሩት 27000(ሃያ ሰባት ሺ) የአዲስ አበባ ዩንቬርሲቲ ምሩቃንን ክፍተኛ ውጤት ላመጡት 7000( ሰባት ሺ) ወደ ከተማ አስተዳደር እንዲካተቱ አድርገዋል፤ 20000( ሃያ ሺዩን) ደግሞ በከተማው ዘርፍ ላይ በዚህ ሦስት አራት ወር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጋቸው ሃሳቡ ምንድን ነው ብትሉኝ እንኚህ 27000 ልጆች ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ እንዲጀምሩና አንዳንድ በብሔርና በነገድ የተስባሰቡትን የደከማቸውን ሰዎች ዕረፍት ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው እላችኋለሁ። ሲሉን እጅግ መሰሪነት ያለው ድስኩራቸውን ከተናገሩ በኋላ 1ኛ.እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን እነዚህ ልጆች የተመረጡት በብሔር፣በሐይማኖት ወይም በሌላ መስፈርት ሳይሆነ የዩንቨርስቲ ምሩቅና የኢትዮጵያ ዜጋ በመሆናቸው ብቻ ነው 2ኛ.ከንቲባው እንደነገሩኝ እነኚህ ወጣቶች እንዳልኳችሁ በቅርቡ ቦታውን ይራካባሉ ብለዋል። ይህ ፊት ለፊት የምናየው ነው። ይህንን አፕርሺየት( appreciate) ማድረግ አለብን” ነው ያሉት። እንደነገሩኝ ከሚሉ ጽፈው እንደሰጡኝ ቢሉ የተሻለ ነበር። እንደሳቸው አባባል የደክሙትን ኦነጎች በአዲስ የኦነግ ኃይል እየተኩ ስለሆነ እባካችሁ ይህንን አድንቁልኝ ይመስላል። የእሳቸው ጌታ ታከለ ኩማ/ ኡማ/ እንዴት መጡ? ስሞኑንን የገቢዎች ሚኒስትየር ምን አደረገ? የሚለውን መስማት ብቻ በቂ ነበር። እሳቸው ግን የታከለ ኩማ/ ኡማ/ ንጉሱ ጥላሁን ስለሆኑ ይህንን የመጠየቅ የሂሊናም ሆነ የሞራል ብቃት ስሌላቸው እነ አቶ ያሬድን፣እነ ቴዎድሮስን በቀጥታ ስማቸን በመጥራት፣እነ አቶ ልደቱንና አቶ ይልቃልን ደግሞ ወጣቶቹ በማለት ሲያንቋሽሹ ህዝብን እየተሳደቡ መሆኑን ቢያውቁም ባሌቤቷን የተማመነች እንድሚባለው በድፍረት ሲናገሩ ፍጹም የህዝብ እልቂት፣ስደትና መከራ ቁብ የማይሰጣቸው አሪዮስ እንደሆኑ አስመስክረዋል።
ምርጫን በተመለከተ አብርሃም ሊንከን ብለው ለምን እሩቅ ይዳክራሉ? ውቂያቢያቸው ውጭ ውጭ ያሳያቸዋል እንጂ ምርጫ በኢትዮጵያ ባለጉልበቶች የሚያሸንፉበት መሆኑ እንድተጠበቀ ሆኖ ደርግ በሻቢያና በት.ነ.ግ ተወጥሮ ተይዞ በነበረበት ጊዜ ምርጫ አካሂዷል። ለምን ቢባል ሀገሪቱ የነበራት አንድ መንግሥት ብቻ ስለነበረ። አሁን መንግሥት አለ? ሀገሪቱ በማን ነው የምትመራው በማለት ግራ እየተጋባንና በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ባለንበት ሰዓት ምርጫ መካሄድ አለበት ብለው አሜሪካንን ከመጥቀስ ይልቅ ከኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አሳማኝ በሆነ መልኩ ቢገልጹልን እንቀበልዎት ነበር። እርሶ ግን የእርስዎን ደካማ ስነልቦና ተጠቅመው አብሻን የአሜሪካን ስም ካነሳሁለት ይቀበለኛል ከሚል ንቀት የተነሳ እንደሆነ ግልጽ ነው።
የሽግግር የምትለውን ቃል እንደ አብይ አምርረው የሚጠሏት ለምን ይሆን? የአዲስ አበባ የፖሊስ ኮሚሽነር ቢሆኑ ከሚያሳስሩት ይልቅ የሚያስገድሉት እጅግ እንደሚበዛ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ እንደሆነ ሁለቱን ወጣቶች አምርረው የሚከሱበት ክስዎ በግልጽ ያስረዳናል።
ሌላው ደግሞ ፌስ ቡክን ምን ያህል አምርረው እንደሚጠሉ የተረዳሁን ኮንቦልቻ ዩንቨርስቲ ሄደው በነበሩበት ጊዜ ፌስቡክዎን ሲያነቡ የደረሰቦትን ወቀሳ ለመቀበል ስላልደፈሩ በንዴት ጦፈው መተኛት አቅቶት እንደነበረና አንድ ስልክ ሲደወልሎት አሁን ደግሞ ማን ሊሰድበኝ ነው ብየ ሳነሳው ፍቅረአዲስ ነበረች። ፍቅረአዲስም ያቀረብከውን አዳምጨው በጣም ወድጀዋለሁ ስትለኝ ንዴቴ ሁሉ ጠፍቶ ሰላማዊ ዕንቅልፍ ወሰድኝ ብለውናል። ፍቅረአዲስ የባህል ዘፋኝ እንጂ የባህል ፖለቲከኛ መሆኗን ባለማውቄ ለጊዜው ግራ ገብቶኝ ነበር። ነገሩ ወዲህ ነው ለካ “ የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ” እንደሚባለው መሆኑ አይደለም?
“እግዚአብሔር ሂሊና ቢሶችን ወደ ሂሊናቸው፤ወኔ ቢሶችን ወደ ወኔአቸው ይመልስልን”
አንተነህ ጌትነት ሙላቱ( የሶማው)
ከባዕድ ሀገር አውስትራሊያ
ትችታችሁን በዚህ ኢሜል ጻፉልኝ፡muluadamche@gmail.com