Tuesday, September 28, 2010

ውጥንቅጥ ነፃ አውጪዎቻችንና ሻዕቢያ (ክፍል 2)

ይድረስ ለጎጠኛው መምህር (አማርኛ) እና ሓይካማ (ትግርኛ) መጽሐፌን ለመግዛት ዕድሉን ያላገኛሁ ካላችሁ በሚከተለው አድራሻ ደውላችሁ ማግኘት ትችላላችሁ Telephone (408) 561 4836 (Getachew Reda P.O.Box 2219 San Jose, CA 95109) getachre@aol.com

ውጥንቅጥ ነፃ አውጪዎቻችንና ሻዕቢያ (ክፍል 2)(Getachew Reda ጌታቸው ረዳ) ይህ ጽሑፍ “በአልጌና በምፅዋ በዓይደር የተዘሩ ዓጥነቶች ዕሾህ ሆነው ይውጓችሁ”ከሚለው የቀጠለ ተመሳሳይ ትችት ነው። ጽሑፉ የቀረበበት ምክንያት “አሁንም ኤርትራ መዳኛችንም መጥፊያችንም ትመስላለች:ኤርትራ፤ አርበኞች ግንባር፤ ግንቦት7”በሚል በልጅ ተክሌ (ኢጋድ ፎረም/ካረንት አፈይርስ ዌብሳይት/ፓል ቶክ ባለቤት)ለቀረበው ጽሑፍ ቀጣይ ትችት ነው። ካናዳ አገር የሚኖረው ተክሌ (ልጅ ተክሌ/ፊታውራሪ ተክሌ……)በማለት ራሱን የሚጠራ ወጣት ኤርትራ ድረስ በመሄድ ተዋጊ ሃይል እንዲያሰለጥንልን ሻዕቢያን ካልተማጸንን መለስን ማስወገድ አንችልም ባይ ነው። በማያሻማ አገላለጽ “በዚህ ዘመን በኛ ዕዴሜ በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአመጽ ለውጥ መምጣት ካለበት፤ ቢከፋም ቢለማም ያንን የማሳካት አቅም ያለው ግንቦት ሰባት ብቻ ነው ባይ ነኝ።” ብሎ ነበር። ለዚህ አባባሉ ነበር ክፍል አንድ ጽሑፌ ነካ ነካ አድርጌ የተቸሁበት። በዚህ ክፍል ሁለትም የዛኛው ቀጣይ መደምደሚያ ሆኖ በሌላ ሳምንት ሌላ ወቅታዊ ጉዳይ መጥቶ ከላስተላለፍኩት በቀር በቀጣዩ የሚቀርብ ጽሑፌም የግንቦት7 ጥብቅ ወዳጅ የሆነው ተስፋየ ገብረአብ የተባለው የሻዕቢያ ሰላይ በሚመለከት እንዳስሳለን። የተክሌ አማራጭ ብቸኛ ነፃ አውጪዎቼ ናቸው ብሎ የሚመካባቸው ውጭ አገር ስራ እየሰሩ ሕይወታቸው የሚመሩት የግንቦት7መሪዎችን መተማመኑ የገንዘብና የፕሮፓጋንዳ ድጋፉን ምኞቱን መግለጹ መብቱ ተጠበቀ ቢሆንም፤ እኔ ከተክሌ ጋር ያለኝ ችግር “ግንቦት ሰባት በግልጽ ባደባባይ ከኤርትራ መንግስት ጋር መነጋገርና መስራት ካልጀመረ፡ሌሎች የስራ መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋልና ትግላችን እዚያው ባለበት መርገጥ ነው ባይ ነኝ።” “በጸረ ወያኔ ትግል ውስጥ የጎረቤት መንግስት እገዛ ካስፈለገን፡ ያለችን ብቸኛ አጋር ኤርትራ ብቻ ነች።”ስላለው አባባሉ ክፉኛ ይጎረብጠኛል። ለምን? የሚከተለውን እንመለከት። ተክሌም ሆነ እኔ እና በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አገራችንን የማጣቱ ምክንያት ወያኔ ብቻ ሳይሆን ሻዕቢያም ጭምር መሆኑን በድጋሜ ማስታወስ ሊኖርብኝ ነው። “ማየት ማመን ነው” የሚሉት የወያኔዎች ደንቆሮ ፖለቲካ (“የሶፊስቶች ፍልስፍና” የሚከተሉ) “ማሰብ ያቆሙ” ነብሳት ዛሬም ለወያኔም ሆነ ለሻዕቢያ ያላቸው አመለካከት በጎ መሆኑን ስመለከት ያንዳንዳችን አፈጣጠር የሰው ልጅ ሕሊና ዛሬም ከእንሰሳ ጭምትነት ያልመጠቀ በኤሊ የጉዞ ፍጥነት ሂደቱ እያዘገመ እንደሆነ ስመለከት ለዳተኛው ጉዞአቸው እንዲህ እንዲያዘግሙ ምክንያታቸውን ለማወቅ ብሞክርም አለትን ለማርጠብ የሚደረግ ፈተና ያህል ይከብደኛል። እዚህ በዲያስፖራም/ውጭ አገር እየኖሩም ለወያነም ሆነ ለሻዕቢያ መሪዎች ያላቸው አመለካከት የተለሳለሰና በጎ መሆኑን ስታዘብ የእኛነታችን ውጥንቅጥነት (ናቲ ጊቲ) እኛነታችንን በጉልህ የማየት ችግራችን ማጣት ተደማምሮ ነፃነት የመቃረቡ ዕድሜው ይበልጥኑ ረዢምና ውስብስብ አድርጎታል። ጎረቤቶቻችን ለኛ በጎነት አልተሰለፉም። የኼ የምናውቀው ሓቅ ነው።ለዚህም ምክንያቱ መለስ ዜናዊ ያገሪቱን መሬቶች እና ውሃ ነክ ጥቅማ ጥቅሞች ለጎረቤት አገሮች በነፃ እየለገሰ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን፤ለም የእርሻ መሬቶችን ያለ ምንም ገድብ ለጎረቤት አገሮች በመለገስ በልዋጩ መለስን የሚቃወሙ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች እየተያዙ ከተጠለሉበት የጎረቤት አገሮች እየተያዙ ወደ መለስ ዜናዊ እስር ቤቶች እየተወረወሩ መሆኑን ለትግሉ አመቺ እንዳልሆነ ሁላችንም እንስማማበታለን። ያለን አማራጭ ዛሬም ነገም ለውጥ መምጣት ካለበት አገር ውስጥ በሚደረጉ ትግሎች ነው፡ እላለሁ። ይህ ለማድረግ ያለፈው የትግል አካሄድና አካሄዱን የመሩት አመራሮች በጥልቅ መመርመር አለበት። ሥልጣን በሚፈልጉ ግለሰቦችና በጭፍን ስሜት በሚጓዙ አመራሮችና ተከታዮች ምክንያት ተጠናክሮ የነበረው የተቃዋሚ አንድነት ፈርሶ ለመለስ ዜናዊ ለምለም (ለም) መስክ ሆኖለት ይኼው እስከ ዛሬ ድረስ ያገሪቱ ሕዝብ ችግር ውስጥ ገብቶ የመናገር የመውቀስ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች ተዘግተው አገሪቱ የውስጥ እና የውጭ አገር (neo-colonialist)የጥቂት ዘራፊ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በቧረቂያ ገነት (ሴፍ ሔቨን)ሆና ሕዝቧም “በቀይ ቢጫ ለባሽ”ፋሽስቶች ያስተዳደር ቀንበር ስር እየተረገጠ ይገኛል። ለምክንያቶቹ ዝርዝር ለተቃዋሚዎች አንድነት መፍረስ ምክንያት ብዙ ትችቶች የተካሄዱ ስለሆነ አሁን አልመለስበትም። አዲስ አበባ ያክል ትልቅ ከተማ፤የነቃ እና የተለያዩ አስተሳሰቦች ያያዘ ሕሊና ያለው ኗሪ ሕዝብ ወያኔን ባንድ የምርጫ ቀን “አክ እንትፍ” ብሎ ተፍቶ ትብያ ላይ ጥሎ ተቃዋሚዎቹን በመምረጥ “ቀይ-ቢጫ” ለባሾችን የሓፍረት ማቅ አስለብሶ ጥፍራቸው ውስጥ እንዲገቡ ያደረገበትን ያንድነት ትግል ዛሬ በፋሸስቶች ቀንበር ዳግም እንደገና የመረገጡን ጉዳይ ሁላችንም አሳስቦናል። ይህ ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ክፍል ነው።ሕዝቡ ለትግሉ ያለውን ዝግጁነት ሲገልጽ፤በተፃራሪ የተቃዋሚ መሪዎች “በሙሉ” ሃላፊነታቸውን በመጣል “ሰላማዊ ሰልፍ/የተቃውሞ ሰልፍ እንዳያደረግ በመወስን በመለስ ጉራና ዛቻ ተደናግጠው ትግሉን ከመመምራት ይልቅ ያለ መሪ በመተው ሕዝቡ በፋሽስቶች ጥይት እንዲቆላ ምክንያት መሆናቸው የምንስማማበት ነው።ባለፈው አምስት ዓመት በፊት ቀይ ለባሽ የወያኔ ፋሽሰት ግልገል ወታደሮችም ሴት ህፃን ሽማግሌ ሳይል ረሽኗቸዋል። ወጣቱ እና ታዳጊ ህፃናቱንም የባንክ ዘራፊ በማለት ሌባ እና ወረበላ አድርገው የፖለቲካው ተቃዋሚውን በመትረየስ አጨዱት።አሁን እዚህ ላይ እንገኛለን።የዛሬውንም ምርጫ እንደዚሁ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ መሪዎች አንድ ሁለት ሳይባል “ሁሉም”በፍርሃት ተሸማቅቀው ትግሉን በመተው ለወያኔ ሰጡት። እጅግ አስገራሚ እና ካለፈው የባሰ አስገራሚ ጉድ! እነኚህ የተቃዋሚ መሪዎች፤ትግሉን እስከ መጨረሻው መግፋት ካልቻሉ ወይ ካገር ለቆ እንደ ግንቦት7 መሪዎች ኑሯቸውን ውጭ ማደላደል፤ ከመጀመርያውኑ ምርጫ ውስጥ መሪ ሆኖ አለመመዝገብ፤አለመፎከር፤አለመወዳደር፤አለመከራረከር!ከገቡም የተጭበረበረውን ምርጫ ለማጋለጥ እና የሕዝቡን መብት ላለማስረገጥ ሕዝቡን ለመጨረሻ ወሳኝ ትግል አመጽ አስነስቶ የለየለት የታሪክ መሰነድ/ማስመዝገብ ነበረባቸው። ያ አላደረጉም፤፡ ይበልጥኑ ለፏሲስቶቹ ጥቃት ራሳቸውንም ሆነ ሕዝቡ አመች ሆነው ይገኛሉ። ከዚህ ወዲያ ወዴት እንሂድ?ለሚለው ጥያቄ ብዙ ተጽፎበታል ዛሬም በቀጣይ እየተጻፈ ነው። እንቅልፍ አጥተው መፍትሔ ለመፈለግ የሚጥሩ በተከታታይ ሃሳቦችን በየሚዲያው እየቀረቡ ነው። በየትም ወገን ይሁኑ ለጥረታቸው ምስጋና ይገባቸዋል። ወሳኙ ጥያቄ ግን “በሻዕቢያ በኩል አድርገን መለስን እናስወግድ?” ወይስ “አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ በመቀስቀስ ሕዝባዊ አመጽ አስነስቶ መብቱን ማስከበር?” የሚሉ ሁለት አማራጮች ላይ ደረስናል። የመጀመሪያው መፍትሔ “የጨነቀው ዕርጉዝ ያገባል” ነውና መፍትሔ አይደለም (በተለይም ከወያኔ ያልተናነሰ ተፃባኢ)።ሁለተኛው ግን አማራጭ የሌላው 17 ዓመት ሙሉ በደምብ ያልተገራ፤መሪ ያጣ፤ በፈታኝ ትግል ተፈትነው የወደቁ መሪዎች የተገራ ትግል ስለሆነ ያንኑ አትኩሮት በመስጠት የፋሽስቶችን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና እና ብዝበዛ በሕዝብ አመጽ የሞት የሽረት ትግል እንዲያደርግ የችግሩ ምክንያቶች ከድርጅት ወገንተኛነት ስሜት የራቀ ምርመራ (ዲያግኖስቲክ/ትራብል ሹተር) የሚቀየስበት ጥናት እንደገና መታየት ያስፈልገዋል እላለሁ። ሕዝብ ሲያምጽ መሳርያ እንደማይገታው የትግል ታሪኮች ህያው ምስክሮች ናቸው። (መሣርያ ታጥቆ ጎሰኛ/ፋሺስቶቹን ከስልጣን ማስወገድ ባልተጠላ፤ ነገር ግን ተክሌም ሆኑ ሌሎቹ በገለጿቸው ምክንያቶች አልተቻለም። ያም ቢሆን/ፍላጎቱ ካለም ኤርትራ የሚያስኬድ የለም። አገር ውስጥ የትጥቅ ትግል ማድረግ ይቻላል ባይ ነኝ) ያ ለማድረግ ሕዝቡ የግድ መሣርያ መታጠቅ አለበት ማለት አይደለም። ሕዝቡን በማዕበል ለማስነሳት የፕሮፓጋንዳው ስራ እጅግ በስፋት በመቀጠል እና በፋሺስቶቹ ወጥመድ “ማሰብ ላቆመ ሕብረተስብ”አዳዲስ የማታለያ ወጥመዶች ሲያጠምዱለት በወቅቱ ተከታትሎ ማጋለጥ የመጀመርያውና ቅድሚያ የሚሰጥ ትግል ሲሆን። ቀጥሎ አገር ውስጥ ያሉት የተቃዋሚ መሪዎች በሌሎች በሳልና ፈጣን እጅግ ደፋር እና ፍርሃት የማይበግራቸው በጥበብ የሚጓዙ መሪዎች መተካት አማራጭ የለውም። እስካሁን ያየናቸው መሪዎች መሸጋገርያ እንጂ “ፈታኝ” ፈተና ሲጋረጥባቸው ሸርተት የሚሉ ደካሞች እና ፈሪዎች ሀኖው ትግሉን ስላበላሹት የድክመታቸው ስፋት ሰፊ በመሆኑ፤ጊዜ ሳይወስድ እነሱን የሚተካ ሃይል አማራጭ የለውም። የሚተካቸው እስከሌለ ድረስ ፖለቲካው በተቆጣጠሩት ቁጥር ይበልጥ ትግሉን እየጎተቱ ፤መለስ ዜናዊ በደነፋ ቁጥርም “ጭራቸው እየቆሉ”እርስ በርስ እኔ አይደለሁም “ሃይሉ ነው፤ግዛቸው ነው፤ መስፍን ነው፤ልደቱ ነው፤ያዕቀብ ነው፤….”በሚል የማምለጫ ምክንያት “ሸብረክ”እያሉ የጉዞ ጉቶዎች/መሰናክል/ሃርድል የመሆናቸውን ጨዋታ ይቀጥሉበታል (ምክንያቱም አይተናቸዋል፡ what you see is what you get) ይላል ፈረንጁ።በዚህ መንገድ “ቀይ ቢጫ ለባሽ” ፋሺስቶቹም ያገሪቱ አንድነት በቦረቦሩት የልጆች እና የቅጥረኞች የጨዋታ ትልም መቀጣላቸው እውን ነው። ስለዚህ ትልሙ አሁንም በመለስ ዜናው ብቻ ማትኮሩ ሳይሆን በተቃዋሚው የመምራት ችሎታ ላይ ማትኮርና ጥራት ያላቸው መሪዎች ለማውጣት ዘዴ መፈለግ አለበት። የጫት መደብሮች በመላ አገሪቱ እንደ ወረርሺኝ በተስፋፋበት “ግደ ቢስ”ስርዓት አልበቃ ብሎ፤ ወያኔ (ኢትዮጵያን አይድል) ሻዕቢያ ደግሞ (ሽንግርዋ) የሚሏቸው የወጣቱን የማሰብ ሕሊና በመዝናኛ መድረኮች ፍጥኝ የማሰርያ ዘዴያቸው እንደሚያደርጉት ሁሉ እኛ ተቃዋሚዎችም በተለይ አገር ውስጥ ያሉት ዜጎች አገርን “ከቀይ ቢጫ ለባሽ” ፋሽሰቶች ፕሮፓጋንዳ ለመስበር የፖለቲካ ዲቤት/ክርክር የሚደረግበት መድረክ ከፍቶ ሕብረተሰቡ የማሰብ ችሎታው በወያኔዎች የማዘናጊያ ሱስ እንዳይጠመድ ማዘጋጀት አዲስ የትግል ረድፍ መክፈት ነው። በጥንቷ ግሪክ ተደርጓል። ክርክሮች በየገበያው በየአደባባዩ ሲደረጉ ገበያተኛው እና ኟሪ አላፊ አግዳሚ ተሰብስቦ እንደ ሲነማ ያዳምጥ ነበር።እርግጥ ለዛ ሲሉ ፈላስፎቹ ሕይታቸው ገብረዋል። እርግጥ ወያኔ ይፈቅዳል ወይ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ትግል ነውና አይፈቅድም። ከጭንቅላቴ በስብሻለሁ ብሎ ኑዛዜ የተናዘዘ “ግም” “ግም” የሚሸት ቡድን ግማቱ እንዲነገረው አይፈቅድም። ቢሆንም ወያኔን በጋዜጣ በራዲዮን በመጽሔት በየጠላ ቤቱ በየክለቡ በአዝማሪ አሽሙረኛ-(በማሲንቆ/በሃረሚኒካ እየተሸኘ) (በመጠኑም ቢሆን-እየታሰሩም እየተፈቱም) ማጋለጥና መግጠም ከተቻለ “የፖለቲካ-አይድል” መድረክ ለመክፈት ጠይቆ ማስፈቀድና ወያኔን እልክ ማስጨረስ አንዱ ትግል ነው።ወያኔ የተቃዋሚዎች የክርክር መድረክ ብሎ ለስሙም ቢሆን መድረክ ከፍቶ የራሱን ቆሻሻነት ሳይወድ እንዲያደምጥ የተገደደበትን መድረክ ማስከፈት/መክፈት አንዱ ትግል ነው።በወያኔ መንግሥት በየአምስት አመቱ አንዴ የሚካሄድ ሳይሆን በተቃዋሚዎች ወይንም በገለልተኛ ባለሃብቶች ድጋፍ መድረክ ከፍቶ በቀጣይነት በማዘጋጀት ለሚቀጥለው ትግል ተረካቢው ትውልድ (ወጣቱ)ዝግጁ ለማድረግና ወጣቱ ማሰቡን እንዳያቆምና ያገሩን መቦርበር፤ውድቀት፤አንደነት መላላት፤ያገሪቱ መጪ ዕጣ ፈንታ ምን ላይ ሊወድቅ እንደሚችል፤የጎሰኛ ፖለቲካ አደጋ ለማጋለጥ ወጣቶች የሚገኙበትና የሚከራከሩባቸው መድረኮች ቢዘጋጁ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።(በተለይ ውጭ ያሉት ሚዲያዎች ጥሩ አርአያ ሊሆኑ ይችላሉ)። ወጣቱ የታሪክ ተረካቢ እና ወሳኝ ሃይል ሊሆን ስለሚችል ወጣቱ የትግሉ ትኩረት ጎሰኛ/ፋሺስት ከመሆን እንዲጠነቀቅ (ጎሰኛነት ለወያኔ ትኩስ ዳቦ ነውና)የፖለቲካ አይድል (ትኩስና ፈጣን፤ብልህና አገር ወዳድ ወጣት የሚያስገኝ መድረክ)ተከራካሪዎች የሚከራከሩበት መድረኮች መዘጋጀት አለባቸው። የኮመዲ/የቀልድ/መዝናኛ መድረክ ባለቤቶች ትብብር ቢያደርጉ “ፓን ኢትዮጵያኒሰት” ወጣቶች በማፈላለግ አዲስ/ተኪ ሃይል በማፍራት ክፍተቱን ማሟላት ይቻላል። ውጭ አገር የሚኖሩ ግንቦት7ውስጥ የተደራጁ አንዳንድ ወጣቶች በሻዕቢያ እርድታ ነፃ ካልወጣን ሌላው ሁሉ ተስፋችን የተዘጋ ነው የሚለው አባባል በጽኑ መቃወም ይኖርባችሗል። በሻዕቢያ መንደር የተሰራ የነፃነት መንኮራኩር ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በበረራ ላይ ስለሚገኝ ለነፃነት እንዘጋጅ! የሚለው የሰከረ የካልቶች ሰበካ ሞኝነት መገታት አለበት። ሻዕቢያ ጠላት እንጂ ከቶ ወዳጅ ሊሆን ወይንም አዳኝ/ረዳት ሊሆን እንደማይችል የግንቦት7 ደጋፊዎችና ወጣቶች መረዳት ይኖርባቸዋል (በቅርቡ የግንቦት7 “ሸሪክ”የነበረው ኮሎኔል አለበል የተባለ አስመራ ከሻዕቢያ ጋር ያደረገው አሳፋሪ ቃለ መጠይቅ ማድመጡ የሻዕቢያ /ብላሰፎሚ/ይቅር የማይባልበት እርኩስ ሓጢአት በቂ መረጃ ነው። የአማራ ነፃ አውጪ አድርጎ አደራጅቶታል!!)። ውጭ አገር ውስጥ በሚኖሩ የሻዕቢያ ባለስልጣኖች እየተታለሉ (አቶ አብርም ያየህ ሞክረውታል)እንደ እነ ብርሃኑ ነጋ እንደ እነ ወጣት ተክሌ እንደ እነ አንዳርጋቸው ጽጌ ኤልያስ ... የመሳሰሉት የዋሆች ሻዕቢያ ላገራችን በጎ አሳቢ ስለሆነ፤አማራጭ ስለሌለን አማራጩን ተጠቅመን መለስን እናስወግዳለን (ከሰይጣንም ቢሆን እንደራደራለን የሚል የከሰሩ ሰዎች አማራጮች)የምትሉት አማራጭ “ከንቱ ኡቱ” ልፋት ነው። ልፋታችሁ ከንቱ እንደሚሆን እና የሻዕቢያ ባሕሪ እኔ ከምነግራችሁ የኤርትራ መሪዎች ምንነት በሚገባ የሚተነትኑ በሳል ያገራችን ጻሓፊዎች አንዱ ከሆኑት ጸጋየ ገብረመድህን “አርአያ (ዛሬ ከናንተ ጋር ሙጫ ዓይነት ፍቅር እንዳላቸው እገምታለሁ -ከታዘብኳቸው አንዳንድ የድክመት ምልከቶቻቸው እንደታዘብኩት) “አፍቃሪ- ኢትዮጵያዊነትን ማረጋገጥ-ከባዱ ሸክም”በሚለው በጦቢያ አምደኝነታቸው ሲያስተምሩን ከነበሯቸው ጽሑፎቻቸው አንዱ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ያልተጠናቀቀ ፍቺ፤ያልተሳካ ጉርበትና” (ሌላው የሓሰን ዑመር አብደላ ትችትም ፈልጋችሁ ብታነቡ ይጠቅማል)ያሉትን ከዚህ በታች ልጥቀስና የሻዕቢያ ጠላትነትና ስለ ኢትዮጵያ ያለው ጥላቻ ካነበብን በሗላ ሁለቱ ማለት ሻዕቢያም ሆነ መለስ ዜናዊ ዙሮው ዙሮው መታረቃቸው የማይቀር መሆኑና አንዱ ሌላውን እየናፈቀው መሆኑን በተለይም ከመለስ ዜናዊ አንደበት የተናገረውን ጠቅሼ ጽሁፌን ልግለጽና፤ሁለቱ ሲታረቁ ሻዕቢያን አምነው ሳዋ/ተሰነይ ስልጠና የሚወስዱ ኢትዮጵያዊያን ታጣቂ ሰልጣኞች (መሪዎቹ ማለቴ ነው።አብረው ከተራው ምስኪኑ ተጋይ ጋር እየኖሩ ከሆነ ለማት ነው።)፤እንዲሁም ሻዕቢያን እንጥላለን ብለው መቀሌ እና ሽሬ በመሰብሰብ ብሔር ብሔረሰብ እስከ መገንጠል የሚለው ፋሺስታዊ ኮሚኒሰት መመርያ ይዘው የሚፎክሩ ኤርትራዊያን በሁለቱም ስምምነት ተቃዋሚዎቻቸው እንዲያስረክቡ/እንዲለዋወጡ ስምመነት ቢገቡ ዕጣ ፈንታችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ግምት ውስጥ አስገብታችሁት ታውቃላችሁ?። መጀመርያ ስለ ሻዕቢያ ማንነት ለማታውቁ ወጣቶች ጸጋየ ገብረመድህን አርአያ “አፍቃሪ- ኢትዮጵያዊነትን ማረጋገጥ-ከባዱ ሸክም” በሚል የጻፉት ትምህርታዊ ጽሑፍ ልጥቀስና ከዚያ መለስ ዜናዊ ከስምንት ወራት በፊት ከሻዕቢያ ጋር የሚፈልገው ወዳጅነት ምን አይነት መሆኑን በትግርኛ ቃለ መጠይቁ የተናዘዘውን ልጠቅስና ልሰናበት። “አፍቃሪ ኢትዮጵያዊነትን ማረጋገጥ ከባዱ ሸክም“ ባለፉት ሰባት አመታት የሻዕቢያ ግልገሎች በአገራችን ተቀምጠውና በአገራችንም አምጸው የበኩር ልጅ ድርሻ እየወሰዱ መልሰው ሲዘልፉን ነበር። ኢሳያሳቸው በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ቤተመንግሥትና መንግሥቱ ሃይለማርያም ባሰራው ሰፊ አዳራሽ ፈነጩ። ሽማግሌዎቻችንን በደፋር ቋንቋ ደፈረ። ታሪካችንን ተረት ተረት አለው። አሰኘው።የዚህን አገር ቅድስና ዘለፈብን። እንደሚባለው አምላክ በመለኮቱ ላይ ለሚመጡበት ሥርየት ሌለው ሃጢአት (Blasphemy) እንደ ፈጸሙ በማመን ይበቀላቸዋል።የአገርን ክብርና የሕዝብን ማንነት የሚደፍሩ በተመሳሳይ ዓይን መታየት ይገባቸዋል።ይኸ ነው የደረሰብን።…” በማለት የጦቢያው አምደኛ ጸጋየ ገብረመድህን አርአያ አፍቃሪ- ኢትዮጵያዊነትን ማረጋገጥ-ከባዱ ሸክም” በሚል የጻፉት ሻዕቢያ ላገራችን ያለው ንቀት እንጂ በጎነት እንደሌለው ማንነቱን ገልጸውልናል። መለስ ዜናዊም በበኩሉ የሻዕቢያ ፍቅሩ አሁንም እንዳለው አስረግጦ በቃለ መጠይቁ የተናገረውን በመረጃ ልጥቀስ። ንግግሩ የተገኘው አዝማሪኖ.ካም ተብሎ በሚታወቀው የኤርትራ ተቃዋሚ የሕዋ-ሰሌዳ (ዌብ ሳይት) አዘጋጅ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት ድረስ በመሄድ መለስ ዜናዊን ለቃለ መጠይቅ ጠይቆ ከመለስ ጋር ያደረገው የትግርኛ ሰፊ የአውዲዮ-ቪዲዮ ቃለ ምልልስ Meles Zenawi's interview with Asmarino.com - part 3” በሚል ርዕስ ጉጉል ቪዲዮ ውስጥ የተገኘው ማስረጃ እነሆ።ከትግርኛው ቃለ መጠይቅ ወደ አማርኛ የተረጎምኩትን አንዲህ ይነበባል። ““የድምበር ኮሚሽን የወሰነው ውሳኔ ወደን ሳይሆን ሕግ ስለሆነ ባንወደውም ሳንወድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ተቀብለነዋል።የድምበር ኮሚሽኑ በሰጠው ውሳኔ መሠረት መፈታት አለበት። ይሁን እንጂ ነገ ጥዋት የሁለቱም አገሮች ድምበር በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ተግባራዊ ከሆነ በሗላም ቢሆን ሰላም አናገኝም። በተደጋጋሚ የኤርትራ መንግሥት ያወጀው ነገር አለ “የወያኔ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ካልፈረሰ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሰላም መረጋጋት የሚባል ነገር አይኖርም።ስለዚህ አማራጭ ነገር ስለሌለ የኢትዮጵያ መንግሥት ማፍረስ ነው፡ የሚል ነው አጀንዳው። በበኩላችን የኤርትራ ሕዝብ መሪያችን ብሎ ያስቀመጠው መንግሥት/ሃይል ወደድነውም ጠላነውም የኤርትራ ሕዝብ መሪ ነው። እንደ መሪ እና እንደ መንግሥትም ከእርሱ ጋር ተነጋግረን በሰላም ለመኖር ዝግጁ ነን። የጎረቤት አገር መሪዎችና መንግሥታት የመውደድ ግዴታ የለብንም፡ወደድናቸውም ጠላናቸውም የጎረቤት መንግሥታት ስለሆኑ ከነሱ ጋር ተከባብረን ተስማምተን እንኖራለን ከሚለው የመተከል/መስመራችን እምነት እንከተላለን። በነዚህ መተከላችን መሃል ያለው ጋግ ወይንም ክፍተት ባልኩት መሠረት ካልተሸጋግርነው ከኤርትራ ጋር ዘላቂ ሠላም አይኖርም።ስለዚህ ዋናው መደረግ ያለበት ትኩረት የኤርትራ መንግሥትም ቢሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት ወይንም የመወሰን ሓላፊነትና መብት እንደሌላው አምኖ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም ተግባብቶ መኖር (ይጠበቅበታል)።በበኩላችን በኢትዮጵያ ማለት በኛ በኩልም ቢሆን ተመሳሳይ ዝግጁነታችንን ለሰላም ያለንን ዝግጁነቱ ዛሬም ቦታው ላይ ነው ያለው እንላለን።በኛ በኩል በተግባር ለማሳየት ዝግጁ ነን። እንደዚህ ስንል ደግሞ በኤርትራ መንግሥት በኩል ተግባራዊ ለማድረግ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዞ ቢጠጋን ኖሮ ዝግጅነቱ “ከልቡም ይሁን አይሁን”ለማወቅ በቻልን።እንዲህ ቢያደርግ(ቢጠጋን/ልቡ ቢያሳየን) ያኔ እኛም ከሱ ጋር የሰላም ዕርቅ ለማድረግ ያለንን ብርቱ ጉግት(ለማሳየት ያስችለን ነበር)።እሱ “ትያትራዊ” ነው በማለት ሁሌም እንደሚወነጅለን “ትያትራዊ”መሆኑን ወይንም ከልባችን የምር መሆናችንን እቅጩ በታወቀ ነበር። ይህ እስካልሆነ ጊዜ ድረስ (ሁለታችን እስካልታረቅን ድረስ)ድምበሩ ቢካለል፤ባይካለል መፍትሔ አይሆንም የሚል እምነት ነው ያለኝ።” Meles Zenawi's interview with Asmarino.com - part 3 ይላል “የቀይ ቢጫ ለባሽ ቡድን” መሪ የሆነው መለስ ዜናዊ ለሻዕቢያ ያለው ፍቅርና የሰላም ጉጉት ሳይደብቅ ሲገልጽ። በመለስ ፍላጎትና ጉጉት ድንገተኛ የናፍቆት ትቅቅፍና ዕርቀ ሰላም በሁለቱም ሽፍቶች ቢወርድ ነፃነታችን ይዛ አዲስ አበባ ልታደረሰን ነው የምትሏት የነፃነት መንኮራኩር አቅጣጫዋን ቀይራ ወድየትኛው የማረፊያ ግቢ አንደምታወስዳችሁ የምትስቱት አይመስለኝም። ካሁን በፊት በመለስ ዜናዊ ከዳተኛ እና እስስተኛ አቋም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በኤርትራ ተቃዋሚ ሃይሎች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ዕልቂትና ሽብር ሳታስታውሱት የቀራችሁ አይመስለኝም።አጥብቄ አደራ የምላችሁ ግን ፖለቲካችሁ እንዳይበላሽ ከፈለጋችሁ “መለስ (ትግሬዎች ለማለት ነው) እንዴት ጮማውን ለመድከው ተብሎ ሲጠየቅ በመከራ” አለ አሉ፡ ብሎ የትግሬ ጠሊታነቱና የሻዕቢያ ዘረኛ ባሕሪው በመለስ በኩል አሳብቦ የትግራይን ሕዝብ መዝለፍ አንድ ብሎ እንደ አጀንዳ የጀመረው ሰላዩ ተስፋየ ገብረአብን ከሚዲያችሁና ከመሪዎቻችሁ ጓዳ መርመስመሱ እንዲያቆም ማስራቁ ብልሕነት ነው። በተረፈ ውጥንቅጥ ነፃ አውጪ ሆኖ ከሻዕቢያና ከመለስ ዜናዊ ተጎዳኝቶ ነፃነትን መመኘት በራስ ላይ እና በአገር ላይ ሐዘን መጨመር ነው።ከሁለቱም በጋሚዶዎች/ወረበሎች ጭካኔ አምላክ በጥበቡ ከመዓቱ ይሰውራችሁ። ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ ሰማይ ዘገባ አዘጋጅ። www.ethiopiansemay.blogspot.com getachre@aol.com ይደረስ ለጎጠኛው መምህር( አማርኛ) እና ሓይካማ (ትግርኛ) መጽሓፎቼን ለመግዛት የምትሹ አማርኛው $25.00 ሲሆን ትግርኛው $15 ነው (ይኼኛው አምስት ዶላር የፓስታ መላኪያ ሳይጨምር ነው።አሜሪካ ላሉት ብቻ)። የፖስታ ቤት አገልግሎት እየጨመረ ስለሚሄድ ዋጋው ሳይጨምር ካሁኑኑ ብትገበዩ እና ማን እየገዛን እንደሆነ ለማወቅ ራሳችሁ እንድትመረምሩ ይረዳችሗል የሚል ግምት አለኝ።አመሰግናለሁ።(408) 561-4836 (Getachew Reda p.o.Box 2219 San Jose, CA 95109 U.S.A )