Wednesday, August 19, 2009

ቀዳዳ ጨረቃ (ደራሲ ሀማ ቱማ)

http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/ ኢትዮጵያ በመከራ አምጣ ከወለደቻቸዉ ጥቂት ወጣት አገር ወዳድ አርበኞች፤ አንዱ አቶ እያሱ አለማየሁ ነዉ፡፡ የብዕር ስሙ “ሀማ ቱማ” በመባል ይታወቃል፡፡ በብዙዎቻችን የ የዛዉ ዘመን ትዉልዶች ታዋቂነቱ የጎላ ነዉ። በዚህ አዲስ ትዉልድ (ማለትም በወያኔ 18 ዓመት ጫት ቃሚ እና ክልልተኛ ትዉልድ ዘመን ባሉት) ብዙ የሚታወቅ አልመሰለኝም። ይህ ኢትዬጵያዊ አፍሪካዊ አርበኛ ፣እዉቅ ዓለም አቀፍ ገጣሚ፤ደራሲ፤የፖለቲካ መሪ ታጋይና የሕዝብ አጋር፤ የወያኔ ሥርዓት ባማገጠዉ ዘረኛ ትዉልድ እንዳይታወቅ እና ጽሑፎቹ እና ድርጅቱ (ኢሕአፓ) ኢትዬጵያ ዉስጥ እንዳይነበቡ እና እንዳይንቀሳቀስ በሕግ ወጥነት በወያኔ ሕገ መንግሥት በመታገዳቸዉ ወጣቱ እንደ እነ ሀማ ቱማ የመሳሰሉት “በ አፍሪቃ እና በአለም አቀፍ” ደረጃ እዉቅ፤ዝና እና አክብሮት ያተረፉ አንቱ የተባሉ መተክያ የማይገንላቸዉ ረቂቅ ምሁራን እንዳያወቃቸዉ ሆን ተብሎ የተለያዩ ደባ በመጎንጎንና ይህ እዉቅ አርበኛ ስሙ እንዳይገንን ጥረት መደረጉን በፖለቲካ መድረክ የቆየን ሰዎች የምናዉቀዉ ምስጢር ነዉ፡፡ ደባዉ በወያኔ ብቻ ሳይሆን የወያኔ መሰሪ የማጥላላት ተንኮልም በማስፈፋት እና በማሰረጨት ተቃዋሚ ነን በሚባሉ ‘ቀዳዳዎችም” ከወያኔ በባሰ ሁኔታ ስም የማጥፋት ዘመቻ ሲደረግበት የማየታችንም ሌላዉ አስገራሚ እና አሳዛኝ ክስተት ነዉ፡፡ ወያኔም ሆኑ እንኚህ “ቀዳዳዎች” የሚያጥላሉት እጅግ አድርገዉ የሚፈሩት ምሁራዊ እና ቀጥተኛ ብዕሩ መሆኑን አትዘንጉት። “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ተብሏል አይደል? ያም ሆኖ ደራሲዉ ሀማ ቱማ “በቀዳዳ ጨረቃ” መጽሃፉ ምዕራፍ ዘጠኝ -ገጽ 73 -…84 “ማን ቢወልድ ማ?” የሚለዉን ክፍል ሙሉዉን ሳይሆን “ቀንጭቤ” ላስነብባችሁ፡፡ መልካም ፖቲካዊ የስነ ምርምር ንባብ ይሁንላችሁ።እነሆ፦ ማን ቢወልድ ማ? “የጫካ ጉዞዬ እያበሳጨኝ እያተከረኝ መጣ፡፡እብደት ያጠቃዉ ቢራቢሮ ሊዉጠኝ ፈልጎ በሩጫ አመለጥኩ። አደናቅፎ የጣለኝ ድንጋይ “እንግባ” ብሎ ሲከታተለኝ ዋለ። ወደ ሗላ የሚራመዱ ሰዎች ወደ ፊት በመሄዴ እስኪንፈራፈሩ ድረስ ሳቁብኝ። ርስበርስ እየተደዋወሉ የሚያወሩ ቴሌፎኖች ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ሆነዉ ተፉብኝ።አንድ ጠቋራ ጉምም እየተከታተለ ሲዘንብብኝ ቆየ።የቁራ መነኩሴ መስቀል ላሳልምህ ብሎ ልሳለም ብል በብረቱ መትቶ ዘረረኝ። ከግንባሬ የፈሰሰዉ ደም ስጠርገዉ ወፍ ሆኖ በረረ።በግንባሬ ስንጥቅ አንጎሌ ልዉጣ ብሎ አስቸግሮኝ እጄን ግንባሬ ላይ ለጥፌ መጓዝ ተገደድኩ። ጭንቅላታቸዉ ባእጃቸዉ ይዘዉ የሚጓዙ ሰዎች ሲያዩኝ እየሳቁብኝ አለፉ። በድመቶች ላይ ተሳፍረዉ የሚጓዙ ዓይጦች ጠጠር ወረወሩብኝ። ጠጠሮች እስፒል ሆነዉ ተሰኩብኝ። እስፒሎቹ ስነቅል እባብ እየሆኑ በድንጋጤ ወረወርኳቸዉ። በዚህ ክልል አታልፍም ብለዉ አረንጓዴ ዝንቦች ጫካ-ቦዳ እንድጥስ አስገደዱኝ። ዛፎች ከሥራቸዉ እየተነቀሉ መንገድ በመዝጋት አናሳልፍ አሉኝ። ያየሁት መከራ ብዙ ነዉ።እንደ ወፍ የሚበሩ አፍንጫ-የለሽ ሴቶች ሊጠልፉኝ ሲቃጡ መሸሽ ነበረብኝ። የተደገፍኩት ዛፍ በቅርንጫፎቹ ተብትቦ ሊያስቀረኝ ሲል ማምለጥ ነበረብኝ። ልብሴ ተቦጫጭቆ እርቃኔን ልቀር የቀረኝ ትንሽ ነበር። ጫማዬ ከእግሬ ተፈትልኮ ታቅፎ ተገጣጥሞ እሽኮኮ ሆኖ ዛፍ ወጥቶ ጠፋብኝ። ሳሩን እግሬን እየቆረጠ ደሜን ይልሰዉ ገባ። ሰዉነቴ “እረፍት” እያለ ጮኸብኝ። ደከመኝ ተሰላቸወሁ። የእግርና የእጅ ቦታ የተቀያየረባቸዉ ሰዎች በእጃቸዉ እየሄዱ እግራችንን ጨብጥ ሲሉኝ እጄን ስዘረጋ እጄን ሲነጥቁኝ እየቃጡ ግብግብ መግጠም ነበረብኝ። ቆም ስልም ምስጦች በላዬ ላይ ኩይሳ ሊገነቡ እየሞኩ ስላስቸገሩኝ ቆም ብዬም ማረፍ አልቻልኩም። በጥንዚዛ ላይ ተሳፍረዉ የሚበሩ ዳንኬራ የሚረግጡ ቢምቢዎች አፏጩብኝ። ዘንግ መስሎ የተጋደመ እባብ ረገጥከኝ ብሎ አሳደደኝ። ቀሚስ ያጠለቀች ንብ “አይ ሰዉ ድንቄም ሰዉ/ ማስመሰሉን ምነዉ ብትተዉ/እያለች ጆሮየየ ላይ ዘፈነችቢኝ። ልይዛት ብቃጣ አቃተኝ።ስልቻ ተሸክመዉ ቆመዉ የሚሄዱ አሣዎች አፋቸዉን ከፍተዉ ጥቁር ዉሃ ረጩኝ። ከዉሃዉ ክርፋት የተነሳ አፍንጫዬ ወልቆ ወደቀ። ቶሎ ብየ አንስቼ የወረሩትን ጉንዳኖች አራግፌ ከፊቴ ለጠፍኩት። ሰማዩ ድንገት ዝቅ ብሎ ራሴን ተጫነኝ። ለረዥም ጊዜ መዳህ ተገደድኩ። ቀዳዳዋ ጨረቃ ከፊቴ እየተንከባለለች ብርሃን ሰጠቺኝ። በረዥም ቱቦ ዉስጥ ገብቼ የምጓዝ መሰለኝ። እየሄድኩ ስጓዝ በርካታ የጉንዳን;የምስጥ፤የልዩ ልዩ ትሎችን መንደሮች አለፍኩ። ሰማይ እና ጨረቃ ከቦታቸዉ ተመለሱ። ተነስቼ ቆምኩና እጅ እግሬን አፍታታሁ። ጫካዉን ጨርሼ መዉጣቴን አየሁ። ለጥ ያለ ሜዳና ኮረፍታ አየሁ።ከኮረፍታዉን ወጥቼ ስጨርስ ተጉዤ ያለፍኩት ተጠቅልሎ መጥቶ ከፉቴ ይዘረጋል። እወጣለሁ። ጨረስኩ ስል እንደገና ይዘረጋል። ሳልታክት ቀጠልኩና በመጨረሻ ከኮረፍታዉ ጫፍ ደረስኩ። ጎጆ መሳይ በእንጨት የተሰሩ ቤቶች ኩታገጠም ሆነዉ አየሁ። አስራ አንድ ቤቶች። ቤቶቹ መብራት አላቸዉ።ስለደከመኝ አንድ ዓለት ላይ ቁጭ አልኩና አረፍኩ። ከፊቴ፤በግራና በቀኝ ያሉት ቤቶች ፀጥ ያሉ ናቸዉ። ምንም ፍጡርም ላይይ አልቻልኩም። ተንፈስ ልበልና ተነስቼ በየቤቱ እየዞርኩ አያለሁ ብዬ ሳስብ የተቀመጥኩበት ዕለት በላዩ እንዳለሁ ተንከባልሎ ሳይሆን በፍጥነት ተንሸራትቶ ካንደኛዉ ቤት ዉስጥ አስፈንጥሮ ወረወረኝ። ከወደቅኩበት ስነሳ በዙፋን ዓይነት ወንበር ላይ የተቀመጠዉን ሰዉ አየሁት። ሰዉየዉ ራስ ከግንባሩ ወደታች ገባ ያለ ሆኖ ጆሮዎቹ ወጣ ወጣ ብለዋል። ራሱ ድቡልቡል ሳይሆን ወጣ ገባ ሆኖ ታየኝ። አፉን ገለጠ። በጥርሶቹ ላይ “ዉሸት ሳቅ” የሚል ተጽፎ አነበብኩ፡ አፉን ዘጋ። በግራ እና ቀኙ ክላሺን የታጠቁ አረንጓዴ የወታደር ልብስ የለበሱ የአህያ ራስ ያላቸዉ ሰዎች በተጠንቀቅ ቆመዋል።የክፈሉ መብራት በአየር ላይ አለገመድ ከተንጠለጠለ የክፍሉ አምፑል መሆኑን አየሁ። ማን ነህ? አለኝ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠዉ ሰዉ። “ሰዉ? “ምን ዓይነት ሰዉ?” “የሰዉ ሰዉ።” “ እንዲሁ ሰዉ የለም” አለኝና አፉን ከፈተ። በጥርሶቹ ላይ በጥቁር “ቁጣ” የሚል መዳፍን አሳየኝና አፉን ዘጋ። “ኢትዬጵያዊ” አልኩት። “ኢጦ…” ማለት ጀመረና ቆመ። ሲያጨበጭብ በእጆቹ ትልቅ መጽሃፍ ገባ። አገላበጠ። “ኢ ኢ…” አለ ፍለጋ ገባ።መጽሀፉን ዘጋ።መጽሀፉ ተሰወረ። “ያልከዉ ነገር የለም።” “ ኢትዬ ጵያ? ኢትዬጵያዊ?” መገረሜ ግልፅ ነበር፡፤ “መጽሀፍዎ ጎደሎ ነዉ።” “የመጽሀፉ እዉቀት ከ ሀ እስከ ፐን ያዘለ ነዉ። ያንተ ቃል የለም። ያንተ ቃል የለም። “ሀገር ነዉ።” “አልተመዘገበም፡” “ታሪክ አለዉ” “አይታወቅም።’ “ኢትዬጵያ…” “የሌለ ነገር ነኝ ካልክ ያንተ የራስህ ጉዳይ በጣም አጠያያቂ ነዉ፡” “እንዴት?” “መመርመር አለብህ።” “ለምን?” “መኖር አለመኖርህን ለማወቅ።ማንነትህን።” “ማንነቴን መቼ አጣሁት?” “ይመስልሃል። የአንተን ማንነት ወሳኙ እኔ ነኝ።” “እንዴት ሊሆን ይችላል…?” “ነዉ። ነህ ያልኩህን ትሆናለህ። የምሰጥህ ማንነት ይገልጣልሃል።” “አይቻልም።” በዙፋኑ የተቀመጠዉ ሰዉ አፈጠጠ። ዓይኖቹ ዱቡልቡል ኳስ የሚያክሉ ነበሩ። ከቦታቸዉ ወጥተዉ በርረዉ መጥተዉ ከፉቴ ቆመዉ አፈጠጡብኝና ተመልሰዉ ከቦታቸዉ ገቡ። “ደም!” ሲል ሰዉዬዉ ጮኸ። ሁለት ሃኪም መርፌዎች የብረት ዘንግ አክለዉ እየተንሳፈፉ መጡብኝ። “ለደም መርማሪዎች አትበገር” የሚለዉ የሽማግሌዎች ምክር ትዝ አለኝ። መርፌዎቹ በልቤ ሊሰኩ ሲጠጉ በፍጥነት ያዝኳቸዉና አዙሬ ወደ ሰዉዬዉ ወረወርኳቸዉ። አንዱ በልቡ አንዱ በአንገቱ ተሰካ። ኳስ ዓይኖቹ ከመሬት ወደቁ። አንደኛዉ ወታደር በጫማዉ አፈረጣቸዉ። በሰዉየዉ ላይ የተከሉት መርፌዎች በጥቁር ፈላሻ ተሞሉ። ሰዉየዉ እየሟሸሸ ሄዶ ዝንጅል የሚያክል ዓይጥ ሆነ። ሌላኛዉ ወታደር ዓይጡን ከዙፋኑ አነሳና ከመሬት ፈጠፈጠዉ። ወለሉን በስቶ ጠፋ። የሚደረገዉን ሳላስብበት ዙፋኑ ላይ ሄጄ ቂጥ አልኩኝ። በጣም ቆንጆ ሴት ከፊቴ ቆማ ፈገግ ብላ ስትሰግድና እግሬን ስትሰመኝ አየሁ። ከንፈሯ እግሬን ሲነካኝ ሰዉነቴን በሞላ ሙቀቱ ወረረ ። “ጌታዬ” አለችኝ በጣፈጠ ድምፅ። ከተጎነበሰችበት አነሳሗት። የፍላጎት ንዝረት ተሰማኝ። ዙፋኑ ተዘርግቶ አልጋ ሆነ። ሳብ አድርጌ ከጎኔ አጋደምኳት።ትንፋሽዋ የመቅደስ ዕጣን ሆኖ ሸተተኝ። ልቤ ጠፋ፤ራሴን ሳትኩ ብል ማጋነን አይሆንም። ልስማት ስጠጋ የሽማግሌዉ ድንክ “ሽፋኑ ዉስጡን አይጋርድህ” ማስጠንቀቂያ ታወሰኝ። ቆንጆዋ ሴት ዓይኗን ጨፍና ስትተነፍስ ትርንጎ ጡቶቿ ብድግ ዝቅ ይሉ ነበር።በጣቶቼ ከንፈሯን ከፈት አደረግኩ። የላይና የታች ጥርሶጫ ተለያይተዉ በርካታ የእባብ ምላሶቻ ቀልተዉ ብቅ አሉ። “ስልጣን!” ብዬ ጮሄ አንገቷን አነቅኳት።ዓይኖቿን ከፈተች። ፊቷ ተለዉጦ የ እናቴን መልክ ያዘ።”እማዬ!” ብየ በድንጋጤ እጆቼን ሳነሳ ፈትለክ ልትል ስትነሳ እንደገና አነቅኳት። ከእናቴ መልክ ወደ ፈንጣጣ የቦደሳት አሮጊት መልክ ተለወጠ። ማነቄን ቀጠልኩ።እንደገና ፊቷ ተቀይሮ በትሎች የተሞላ የ እባብ ራስ ሆነ። ዓይኔን ብከፍት እጄን በእጄ እየጨመቅዩ መሆኑን አየሁ። የስልጣን ደብዛዋም የለም። ዙፋኑ የለ፤ አህያ ወታደሮች የሉ፤ ቤት-መብራት የለ። ጠምዝማዛ መንገድ ላይ ተንበርክኬ እጄን በእጄ ስጠመዝዝ ስጨምቅ አገኘሁት። “አሞህን ነዉ?” አለኝ አንድ ቁጥቋጦ፡፤ “የዛፍ ልፍለፋ ሰለቸኝ” አልኩ በቁጣ እየቆምኩ። “ዛፍ አይደለሁም።” “ታዲያ ምንድነህ?” “ቁጥቋጦ።” “ቁጥቋጦ ዛፍ ሁሉም ያዉ! ቁጥቋጦ በብስጭት ተርገበገበ። ቅጠሎች ተወራጩ። “ሁሉም ያዉ አልከኝ” አለ በድነገት ድምፅ። “አንተ ማንነትህ ቢሰረዝ ምን ይሰማሃል? ስንት ዛፍ የፀረ -አብዮት ባንዴራ አንጠለጠለ ተብሎ መቆረጡስ አይሰማህም?” የቁጥቋጦዉ ንዴት ተሰማኝ እና “ይቅርታ አልኩት”። “ምንም አይደል” አለ ቁጥቋጦዉ። “ብዙ መንገደኛ አይቻለሁ። ወዴት እየሄድክ ነዉ?” “ልወጣ።” “አሃ! የት መድረስህን ታዉቃለህ?” “አላዉቅም።” “ከጉዞህ አጋማሽ ላይ ነህ። ሆድ አካባቢ ልበልህ።” “እንዴት አወቅክ?” “አለሁበትን እንዴት ልጣ? ቁጥቋጦዎች ደግሞ እንነጋገራለን። እኔን ማወቅህን ከነገርካቸዉ ሌሎቹም ያመለክቱሃል።” “ማነህ ልበላቸዉ?” “ሳትላቸዉ ያዉቃሉ።” “ይኸ ጠመዝማዛ መንገድ ይወስደኛል?” “ይሰድሃል። መንታ መንገድ ስትደርስ ምርጫዉ ያንተ ነዉ።” “ምኑን አዉቄ?” “ፈትሽ ማወቅ ነዋ! ግራ ወይ ቀኝ ዞሮ ዞሮም ሊገጥም ይችላል። ዋናዉ ወደ ሗላ አለመመለስ ነዉ። “መልካም ጉዞ” አለኝ። አመሰገንኩትና ጉዞየን ተያያዝኩት።ከስልጣን አዙሪት ባስቸኳይ መዉጣት እንዳለብኝ አመንኩኝ። ረዥም መንገድ ተጓዝኩ። ወደ መጣሁበት ሲሄዱ ያገኘሗቸዉ ሁሉ ሲያዩኝ በሀዘን ራሳቸዉን እየነቀነቁ ያልፋሉ። ሰዎች፤ አዉሬዎች፤ግማሽ አዉሬዎች ግማሽ ሰዎች ሁሉም ያዝኑልኝ ነበር። በስጋት ወደ ሗላ መመለስን አልመረጥኩም። ጠመዝማዛዉ ጎዳና በሜዳ በኮረፍታ፤በሽንጥሮ. በምንጮች ላይ እየተጠመዘዘ ወሰደኝ። ምንጮችን ስሻገር እንቁራሪቶች ’ተመለስ” እያሉ መከሩኝ። ሳሮች በጋራ “አትበድ” ተመለስ” ሲሉ ጮሁብኝ። አካላታቸዉን የሚታጠቡ ድመቶችም “የወጣ የለም ተመለስ” ብለዉ ነገሩኝ። ዛፍ ላይ የተኛ ኣዞ “ጥፍርህም አይገኝ ጉዞ ከቀጠልክ” ብሎ አስፈራራኝ”” ጉዞየን ቀጠልኩኝ።ከአባበ አበባ የምትዘል ንብ ተከተለችኝ። “አልደከምክም?” አለችኝ “አንች መች ደከመሽ?” “እኔማ ሸርሙጣ ነኝ” አለች ቆምጨጭ ብላ። “ካበባ አበባ ካልዘለልኩ እሞታለሁ።” “በሽታ አትፈሪም?” “ከአበባ በሽታ የለም።” ከቆንጆ በሽታ የለም ብለዉ ጉድ የሆኑት ጓዶኞቼ ትዝ አሉኝ። “ተጠንቀቂ ለማንኛዉም” ስል ንቢታን መከርኳት። “አንተም እንዲሁ” ብላኝ ብዙ አበባዎች ካሉበት በረረች።…………………..”
እያለ የዘመኑ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ባሕሪ አስከ ገጽ 84 የቀጠለዉን (እኔ የቆረጥኩት ትረካ) ባስደናቂ የስነ ጽሁፍ ቋንቋ በቀዳዳ ጨረቃ መጽሀፉ ማንነታችንን ገልጾናል። ሀማ ቱማ! “ምንም ጊዜም ቢሆን አንተን ክፉ አይንካህ!!!!!!!!” በማለት የምትጣራህን ኢትዬጵያ አገርህ ሁሌም ለዘላም በአክብሮት ስራዎችህን ተንከባክባ ለትዉልድ ትዉልድ ታስተላልፋለች። አገርህን ለማየትያብቃህ! በርታ! ሁሌም ከጎንህ የቆመዉ ጌታቸዉ ረዳ የኢትዮጵያ ሰማይ አዘጋጅ። www.Ethiopiansemay.blogspot.com