Tuesday, March 14, 2023

የሀገሪቱን አንድነት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ትግሬዎችና ኦሮሞዎች የሚከተሉት አደገኛው የአፓርታይድ ፖለቲካ ፓተርያሪኩ ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ (ካለፈው ክፍል 1 የቀጠለ) ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 3/14/2023

 

የሀገሪቱን አንድነት ዋጋ ያስከፈለ ያለው ትግሬዎችና ኦሮሞዎች የሚከተሉት አደገኛው የአፓርታይድ ፖለቲካ  ፓተርያሪኩ ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ (ካለፈው ክፍል 1 የቀጠለ)

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

3/14/2023

ክቡር ብፁእ ወቅዱስነትዎ  ሆይ!

ኢትዮጵያውያን 27 አመት ሕዝብን በቋንቋ በዘር፤በሃይማኖት ከፋፍሎ የገዛውን ወያኔን ለመመከት  ጥቅምት 24/2012 በሰሜን ዕዝ ጦር የፈጸመው  ድንገተኛ ጭፍጨፋ በመቃወም ኢትዮጵያውያን ባንድነት የቆሙት ለምንድነው? ብለው እራስዎ ቢጠይቁ መልሱ ለማግኘት ትንሽ ጥልቅ ምርመራ ቢያደርጉ ለምን እንደሆነ ይረዱታል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሊዮኖች በየቦታው ለጦሩ ድጋፍ ድምጹን ሲያስተጋባ የወያኔ የኦነግ ዘረኛ ፖለቲካ ጡጦ እየጠባ ላደገው ወንጀለኛው አብይ አሕመድ በመደገፍ ሳይሆን የሀገሪቱ ጦር በሰሜናዊ ክልል ጥቃት ስለደረሰበት ጥቃት ፈጻሚውን  የትግራይ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ጦርን በመቃወም ነው።

ወያኔ ሥልጣኑ ከተቀማ በኋላ በቀጥታ የገባው “ኢትዮጵያ እና ትግራይ” ወደ እሚለው የሁለት አገር ፖለቲካ  ስንጠቃ በመግባቱ ሕዝቡ ይህንን አገር የማፍረስ ሴራ ማክሸፍ ስለነበረበት መላው አገሪቱ ሆ ብሎ ባይሆንም ብዙ አርበኛ ከውጭም ከውስጥ አገርም ወደ ጦር ግምባር ዘምቶ በአሜሪካኖችና አውሮጳ የስለላ ሳተላይቶች የተደገፈው የወያኔ አንድ ሚሊዮን ተኩል ጦረኛ እንቅስቀሴው እንዲገታ በማድረግ በመጨረሻም በተደረገው የአንድነት ርብርቦሽ ከጦርነቱ በፊትና በኋላም በጥቅምት 24 ሰራዊቱ በተኛበት አዘናግቶ ጨፍጭፎ የታጠቃቸው ከባድ መሳሪያዎቹን እንዲፈታ እና እንዲያስረክብ ተደረጓል።

10 ሺሕ ሕዝብ ሆን ተብሎ ምግብ ዕርዳታ በመዝጋት በርሃብ ምክንያት አልቋል እየተባለ የተነዛው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ውሸት መሆኑን ባለፈው ክፍል አንድ ጽሑፌ የአለም አቀፍ የምግብ ተራድአ ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬከተር አስተባባሪ ኬኒያዊው “እስቲቭ ኦሙማ” (At the Center of the World – Ethiopia) በሚል በጻፈው አስገራሚ መጽሐፍ ዓይን ያወጣ የወያኔዎችና የተባበሩት የአለም አቀፍ የውሸት ቋቶች ያራገቡት ዜና መሆኑን ነግሮናል።

እርስዎን ካሳዘነዎት አንዱ የትግራይ ሴቶች መደፈር መሆኑ ተናግረዋል። ይህ እውነት ነው። ሴቶች በወታደሮች እንደተደፈሩ እውነት መሆኑን እራሱ አብይ አሕመድም ነግሮናል። የታሰሩ እንዳሉም ተናገሯል። ምን ያህል በፍትህነት እንደተከናወነ ግን አላውቅም። ወያኔዎች ግን 150000 ሴቶች እንደተደፈሩ ሲነግሩን፤ እንዲህ ያለ ብዛት ግን፤ ገለልተኛ አጣሪ እስካልነገረን ድረስ እውነትነቱን ለመቀበል ያስቸግራል።

ሌላው በንግግርዎ እርስዎ የጠቀሱት የማሕበረዴጎይ (ናዕዴር ወረዳ አክሱም) የሰላማዊ ሰዎች ዩጅምላ ርሸና አንዳሳሰበዎት እውነት ነው። ትግሬዎች በመሆናቸው ብቻ እየተለቀሙ በጦሩ እየተረሸኑ ወደ ገደል እየተጣሉ በቪዲዮ የተደገፈ ወንጀል አይተናል። ያ ደግሞ ካሁን በፊት በለጠፍኩት ቪዲዮ ላይ ድርጊቱን የፈጸሙ ወታደሮች በወያኔ እስር ቁጥጥር በነበሩበት በመቀሌ ከተማ እንደተናገሩት << መንግሥት ሰላማዊ ሰው እንዳይገድሉ በደብዳቤ የተላለፈ ጥብቅ ወታደራዊ ትዕዛዝ ከታች እስከ ታች ያሉት ዕዞችና ወታደሮች በደብዳቤና በገላጻ እንደተገለጸላቸው በድርጊቱ በየተሳተፉት ወታደሮች ተናግረዋል።

ነገር ግን ድርጊቱን የፈጸሙት የበታች አዛዦች በራሳቸው አነሳሽነት እንጂ ሆን ተብሎ በመንግሥት የታዘዘ ድርጊት እንዳልሆነ ድርጊቱን ካዘዙትና ከፈጸሙት አንዱ አምሳለቃ ማዕርግ ያለው ወታደር “እራሴ ሁለት ሰዎችን ረሽኛለሁ ወደ ገደል እንዲጣሉም ሆኗል” የሚለው አምሳለቃ ወታደር ወያኔዎች ባደረጉለት ቃለ መጠይቅ ይፋ አድርጎታል። ስለዚህ ወታደሮቹ የጀኖሳይድ ወንጀል ትዕዛዝ እንዳልፈጸሙ ሲናገሩ በሕግ ዓይን “የጦር ወንጀል” ፈጽመዋል ማለት ግን ያስኬዳል።

ትግራይ ውስጥ ጀነሳይድ (የዘር ማጥፋት) ወንጀል ተፈጽሟል የሚለው ደግሞ በገለልተኛ ምርምራ እስኪጣራ ድረስ እንቆይ። አብይ አሕመድ እና ወያኔዎች ግን ምርመራው የሚፈልጉት አይመስሉም (ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው)

ብጹእነትዎ ሆይ!

ትግሬዎች ከኢትዮጵያ ለመነጠልና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነጻነት መዝሙር ሲዘምሩ እና አለም አቀፉ የቄሳሮች ቡድን ወያኔ በመደገፍ አገር ለማፍረስ ሲሯሯጡ በአንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አገራዊነቱን ላለማስደፈር በቁጭት “ቄሳሮችን” በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ የተቃውሞ ጥሪ በማስተጋባት አንድታቸውን አሳይተዋል።

 ያ ዓለም አቀፍ ጥሪ ግን የአብይ አሕመድ ካድሬዎች ለአብይ አሕመድ ድጋፍ እንዲሆን ጠልፈውት ፕሮፓጋንዳ ሲሰሩበት መኖራቸው ሃቅ ነው። በዚህም ማሕበረሰቡ ለሁለት ተከፍሎ እንደ ነበር ይታወሳል።

ወያኔዎች ባገኙት የሳተላይትና የራዲዮ ግንኙነት መሳሪያዎችና  የስላላ እገዛ እስከ ደብረብርሃን ድምበር ቢደርሱም ህዝቡ አብይ አሕመድን በመቃወም ከፓርክና ከሰላጣ ችግኝ ተከላ ጨዋታ ተሎ እንዲወጣና ጦሩን እና ሕዝቡን እንዲያስተባብር ጥሪና ቁጣ ስለተላለፈለት “ተሎ ደንግጦ” ሕዝቡን በማስተባባር በህወሓት ላይ በቆራጥነት ሕዝባዊ መከታውን ጸንቶ በመላ አገሪቱ በአንድነት በመቆም የኢትዮጵያን ሰራዊት በመቀላቀል ሚሊዮኖችም ለዚሁ አላማ የስንቅና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ በመስጠት ወያኔን ኣይቀጡ ቅጣት አግኝቶ አሁን ላላው ሁኔታ ደርል። ሰሞኑ ጌታቸው ረዳ ከሚጠላት ኢትዮጵያ ደሞዝ ተልኮለት ፤ የመጀመሪያ ደሞዙ ለሲጋራና ለመጠጥ እንዳዋት” በዝማሬ ለሕዝቡ ሲዘፍንለት አይተናል። ለሚሊዮን ሕዝብ ዕልቂት ምክንያት ለሆኑ ወንጀለኞች ደሞዝና አንክብካቤ የምትሰጥ አ ብቸኛዋ ኢትዮጵያ አለቀስኩላት፤አዘንኩላት (ኢትዮጵያ አገሬ  ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ)።

አሳዛኙ የዚህ ጦርነት ገጽታ ግን “ኢትዮጵያዊው ጦር እና ሕዝቡ” በሁለት ጠላቶች ማለትም በኦሮሙማው አብይ እና በወያኔ ትግሬዎች ጦር መሃል ተከብቦ በሴራ ተጠቅቶ ወያኔ እስከ መጨረሻው ተከብብቦ እያለ ፍጻሜው ከመፈጸም ይልቅ ‘ግማሽ መንገድ” ትቶት ዛሬም በወያኔ ቁጥጥሩ ሥር ያሉት ማሕበረሰቦች ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ።

አባ ማትያስ ሆይ!

ብፁእነትዎ ህወሓት ለ27 አመታት ሀገሪቱን በጭካኔ መግዛቱን ያውቃሉ።እርስዎን የሾመውም እራሱ በወያኔ ፈቃድነት እንጂ ባይፈቅድ አይሾሙም ነበር። በትግሬዎች ዘመን ሁለት ትግሬ ጳጳሶች ተሽሟል፡ አንዱ እርስዎ ነዎት።

በዚህ ወቅት ትግሬዎች መንግሥታቸው አድርገው ሲቀበሉት ብዙዎቹ ግን ለጥቂት ውቅት ካልሆነ በስተቀር ተቀባይነት አልነበረውም። የትግሬ ወያኔ መሪዎች በነገሡበት በ27 አመት ወቅት ኢትዮጵያን ዘርፈው አገሪቱ አይታው በማታውቀው ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ፣ ችግሮች ውስጥ አስገብተዋት ሄደዋል። በተለያዩ ብሄረሰቦች መካከል አለመተማመንን የመዝራት ፖለቲካን ያራምዱ እንደነበር እርስዎ ያወቃሉ። በሁለቱ ትልልቅ ብሄረሰቦች በኦሮሞ እና በአማራ መካከል አለመግባባት ለመፍጠር በአደባባይ በመስራት ሁለቱም እርስበርስ የሚቃረኑ መሆናቸውን በመግለጽ የሀገሪቱን አንድነት ዋጋ ያስከፈለ አደገኛ እርምጃ በማራመድ ጣሊያን ሲከተለው የነበረው ፖለቲካ በመተግበር የሕዝብ እልቂት አስከትሏል። አሁን የእርስዎ መንበር እየተናጠ ያለው የሰበቡ ምንጭ ወያኔዎች የተከሉት የዘር አስተዳዳር ነው።

በ27 አመት ውስጥ የሕወሃት አባላት የፖለቲካ ምህዳሩን ከመቆጣጠር በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች ቁልፍ የጸጥታ መዋቅሮችን ተቆጣጥሮት እንደነበር ያውቃሉ። ዛሬም በምትኩ የተተኩ ኦሮሞዎች ያንኑ የትግሬዎች ፈለግ ተከትለው ጦሩን በቁጥጥር ስራቸው አድረገውታል።ሃይማኖቱም እንዲሁ ከሞላ ጎደል ተቆጣጥረው በከፊል ወደ እርስዎ መጠተው መንበርዎንም እያወኩት ይገኛሉ።

 እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ካሉት 49 ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች 34 (70 በመቶው) በህወሓት የተሾሙ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ይታወቃል።

የሕወሃት ብሄር ተወላጆች በሌሎች ወሳኝ የመከላከያ ክፍሎች ማለትም በመሀል እና ዝቅተኛ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተመሳሳይ አብላጫውን ይዘው ነበር። በዚህ የሙሉ በሙሉ ቁጥጥር በመነሳት የሰሜን ዕዝ ጦር በተኛበት ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም ሙሉ በሙሉ ጦሩ አዘናግተው ከነመሳሪያው እና ከፍተኛ አገር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን ሁሉ በቁጥጥር አውለው የአገሪቱ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ሱዳኖች ድምበር አልፈው ቦታ ይዘዋል። ወያኔ ከሱዳኖች የጋራ ሴራ መፈጸማቸው ይታወቃል። አሁንም ሙሉ ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው።

ክቡር ፓትርያሪክ ሆይ!

በግዛት ክልል ህወሓት ኢትዮጵያን በመዝረፍ፣ አዋጊ ጀኔራሎችና ኮለኔሎቹንና እንዲሁም አለም አቀፍ የሰላም ጓድ ወታደሮች (በብዛት ትግሬዎች ስለነበሩ) ተመድበው የነበሩ ወታደሮች ሳይቀሩ በገፍ ተጠራርተው አገሪቱን ከድተው ያንን ሁሉ የሰው ሃይል ተጠቅሞ የትግራይን ወሰን ማስፋት፣ ታላቋን ትግራይን የመመስረት አላማ እንደሆነ እርስዎ አይስቱትም። ስለሆነም ጦርነቱ አገርን የማዳንና አገር በማፍረስ መካክል የታየ ጦርነት ነበር አርስዎ አይስቱትም ብየ እገምታለሁ።

 ብፁእነትዎ እንደሚያውቀው ህወሓት ከቀደመው አላማው ጋር የተጣጣመ የሚመስሉ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል። ህወሀት ከወሎ እና ከጎንደር አጎራባች ክልሎች መሬቶችን በተሳካ ሁኔታ ያጠቃለለበት ምክንያት አገር ለመመስረት እና ወደ ሱዳን በር ለመክፍት እንደነበር እርዎም አይስቱትም።

ትግሬዎች ኢትዮጵያን እስከገዛ ድረስ (እርስዎም ከገዢው አንዱ የዘርፍ መዋቅር ነበሩና (በሃይማኖቱ በኩል) ጸንቶ ይቆያል’ ሥልጣን ከተነጠቀ ግን ወደ ግንጣላ እንደሚያቀና አስቦበት ስለነበር፤በኢኮኖሚው ዘርፍ ህወሓት ስልጣን እንደያዘ ብዙም ሳይቆይ ትግራይን መልሶ ለመገንባት ኢንዶውመንት ፈንድ ፎር ሪሃቢሊቴሽን (EFFORT) በማቋቋም አገሪቱን በዝብዞ በትግራይ በርከታ ተቋማትን መስርቶ በመንግሥታዊ ሌብነት የተመሰረቱ የሃብት ምንጮች ወደ ትግራይ በማስጋዝ (The pillage of Ethiopia by Eritreans and their Tigrean surrogates Assefa Negash, (PhD) 1996 ) መጽሐፍ ይመልከቱ (ዛሬም አማዞን የመጻሕፍት መደብር ገበያ ውስጥ ይገኛል) በዘረፋ በተገኘ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ካፒታል የተደገፈ ትግራይን እንደ አገር ለማስቆም ብዙ ሴራ ተፈጽሟል።

ትግሬዎች እንደልባቸው ተንደላቅቀው ያለ ስጋት ሲኖሩ ንግዱን ተቆጣጥረው ብዙ ቪላዎች ሲገነቡ ሌለው እሰርቤት እየገባ ግፍ ተፈጽሞበታል። ይህንን ግፍ እርስዎ ያውግዙ አያውግዙት ያየሁት ነገር የለም።

ትግሬዎች ጦርነቱን ከወያኔ ወንጀለኞች ጋር የወገኑበት ምክንያት ግልጽ ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት ሃብትና የአለም አቀፍ እርዳታ ለብዙ ሚሊዮኖች ህወሓት ግለሰቦችና አመራሮች የዕድገት ምንጭ ነበር።

የወያኔ መሪዎቹ ብዙዎቹ (በወታደሩም በሲቪሉም) የነበሩ ባለሹመኞች በአሜሪካ የስላላ ድርጅት አባልነት ተመልምለው የነሱ ተላላኪዎች ሆነው “ዲሞክራሲያኖች” ናቸው በሚል ሽፋን “የምዕራባዊያን እና አሜሪካኖች”  ተላላኪ ስለነበሩ የፈለጉት የብድር ገንዘብ ፈቅደውላቸው  ከኢትዮጵያ መንግሥት ባንኮች ለኢትዮጵያ የተበደረውን ከፍተኛ መጠን ያለው ዓለም አቀፍ ዕርዳታና ብድር ዘርፈውታል።  ከሕወሃት ጋር ግንኙነት የነበራቸው ፕሮጀክቶችና ግለሰቦች ላይ መጠቀሚያ እንዲውል ተደርጓል።በዚህ ምክንያት ከማዕድን እስከ ኮንስትራክሽን ያሉ ዋና ዋና የንግድ ድርጅቶች ከትግሬዎች አልፎ የተረፈው ለህወሓት አጋር የጎሳ የንግድ ድርጅቶች ፍጆታ ውሏል። ይህንን ከእርስዎ የሚሰወር  ምስጢር አይደለም።ሁሉም በዓይኑ ያየው አስገራሚ ምዝበራና የትግሬዎች ቅጥ ያጣ ትምክሕታዊና ስግብግብ የበላይነት ነበር። (ዛሬም ኦሮሙማው አብይ አሕመድ ያንኑ ስግብግብነት ለኦሮሞዎች ፍጆታ እያስቀጠለው ነው)

ባለፈው 27 አመት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ሙሉ በሙሉ የተዘጋ እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በጅምላ በማሰር፣ እስረኞች ላይ ግብረሰዶም ሲፈጸም  ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲፈጸም አሁን ለትግሬዎች  እንደሚያነቡ እርስዎ  በዘመነ ወያኔ አንድም ቀን ውግዘት ሲያስሰሙ እኔ አልሰማሁም። ካለም ለመስማት ዝግጁ ነኝ።

በሕወሃት እጅ ውስጥ የነበረችውን ጥንታዊና ታሪካዊ ኢትዮጵያ ከመበታተን ለመታደግ ውስጥና ከውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ባንድነት በመነሳት ተቃውሞ ያስሰማበት ምክንያት እርስዎ በ27 አመት ውስጥ ደምጽ ሳያስሙ ዝምታን መርጠው በነበረበት ወቅት (ካለም ለስሕተቴ ይቀርታ እጠይቃለሁ) ወያኔ በሰሜን ዕዝ ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሂድ ተመልሶ ወደ ሥልጣን እንዳይመጣ ሕዝቡ ስጋት ስላደረበት፤ ዜጋ ሁሉ በትግሬ ተዋጊዎች ላይ የተባበረ ክንዱን አስተባብሮ ግስገሳውን ለጊዜውም ቢሆን አሁን ባለበት እንዲቆም ሆኗል።

ብፁእ ፓትርያሪክ ሆይ!

ኢትዮጵያ ዛሬም ከትግሬዎች የድጡ አገዛዝ ወደ ኦሮሞ የማጡ  አገዛዝ (ከትግሬዎች የበላይነት የውስጥ የቅኝ አገዛዝ ወደ  ኦሮሞዎች የበላይነት ውስጥ አገዛዝ) እየተጎተተች እንደሆነ ከእርስዎ የበለጠ የዓይን እማኝ የለም። ትግራይ ውስጥ የተፈጸመ የጦር ወንለጀል ሙሉ በሙሉ ተጠያቂዎች ወያኔ መሪዎች እና አብይ አሕመድና ሹሞኞቹ መሆናቸውን እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ።  

ዐቢይ አገሪቷን ወደ አንድነት ለማምጣት ሳይሆን እየጣረ ያለው ጦርነቱ መነሻም የሁለቱ ሕገወጦች የሥልጣን ጥም ሹኩቻ ያስነሳው ጦርነት እንደሆነ እንዲያውቁት እጠይቀዎታለሁ።

ትግራይ ውስጥ ያሉት ውጭ አገርም ያሉት ምሁራን እና አዲሱ የትግራይ ትውልድ ኢትዮጵያን በመጥላት የተመረዘ ሕሊና ይዘው አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው እርስዎ ግንዛቤ እንዲያደርጉ ስጠይቅ፤ አሁን ያለው የትግራይ ምሁርና አዲሱ ትውልድ አገር ከማፍረስ ካልተቆጠበና ከዚህ ጦርነት ጉዳት ያስከተለው መዘዝ ትምህርት ካልቀሰመ እና የትግራይ ሕዝብ የሚያደርገው የጦርነት አንቅስቃሴም ሆነ አገር የማናጋት እንቅስቃሴ ራሱን መልሶ ወደ ከፋ ጭለማ እና ጉዳት የሚመራው እንደሆነ አባታዊ ምክርዎን በጽኑ እንዲመክሩ አደራ እያልኩ፤ ትግራይ ውስጥ ያሉ ቀሳውስቶችም ከጠመንጃ ፍቅር፤ቅድስት ኢትዮጵያን ከመዝለፍ ወጥተው ከኮሚኒስታዊ አስተሳሰብና ከአገር ግንጣላ ወጥተው ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ጉዞ እንዲያተኩሩ የእርስዎ ምክር ወሳኝ ስለሆነ በዚህ ላይ ትኩረትዎ እንዲበረታ አደራ እያልኩ፤ በመጨረሻም ትግራይ ውስጥ የደረሰው ጉዳት እንዳሳሰበዎት ሁሉ እርስዎም እንደ የሁሉም ዜጋ አባትነትዎ ወደ ዓፋርና አማራ ሕዝብ ሄደው በትግራይ ተዋጊዎች የደረሰውን ጉዳት እንዲያዩና የሕዝቡን ዕንባ የልጃገረዶች መጠቃት ፤ የሴት መነከሳትና አረጋዊያን እናቶች በትግሬ ተዋጊዎች የደረሰባቸው መጠቃት እና የንግድና የሕክምና ተቋማት፤ በአብያተ ክርስትያናትና መስጊዶች የተፈጸመ ጥቃትና የፈራረሱ መኖርያዎች የንብርት ዘረፋዎች ጥልቀት ለመረዳት እንዲችሉ የሕዝቡን እሮሮ እንዲያደምጡ እዛው ድረስ በአካል እንዲጎበኙና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲያገኙ አጥብቄ እንደ ልጅዎ ድምጼን በማስሰማት እጠይቀዎታለሁ።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ