Thursday, January 1, 2009

ጭካኔ 17 -ጭካኔ 18 እና ላዉንቸር የተባሉ አድማ በታኝ ልዩ ሃይሎች ጌታቸዉ ረዳ ከወያኔ ገበና ክፍል 3 -ካለፈዉ የቀጠለ በመጀመሪያ እንኳን ለአዲሱ የፈረንጆች ዓመት አደረሳችሁ! ይላል የኢትዮጵያ ሰማይ የህዋ ሰሌዳ።ዓመቱ ኢትዮጵያን በጠላትነት ሲፈርጃት እና ታሪክ አዛብተዉ ራሳቸዉን አታልለዉ የዋህ ከብት እረኞች ኢትዮጵያዉያን ኦሮሞዎችም በማይዘለቅ እሳት አስገብተዉ ለ40 ረዢም ዓመታት ለሞት እና ለዉርደት ራሳቸዉንም(መሪዎችም ጭምር) ለስደት ዳርገዉ አገር አልባ አድረገዋቸዉ ከረዥም ዉርደት በሗላ ወደ ሰብአዊ ሕሊናቸዉ በመመለስ የመሰረቱት እና የገነቡት “ኦነግ”ን በማዉገዝ ወደ ጤናማ ማሕበረ ሰብ እና ጤናማ ፖለቲካ በመመለሳቸዉ ለኢትዮጵያዉያን ሆነ ለራሳቸዉ ለኦነግ መስራቾቹ ጥሩ ጅምራ እና ተስፋ ሰጭ በመሆኑ በዚህ የፈረንጆች “አዲሱ ዓመት” ኦነግን ኮንነዉ ለተዉት እና በማታለል ባልሆነ የፖለቲካ ዕምነት ተዘፍቀዉ ኖረዉ ሕሊናቸዉን ነጻ ያወጡ ሁሉ “እንኳን ድስ አላችሁ! መልካም አዲስ ዓመት!” ይሁንላችሁ እያልኩ፤
-በዚህ አጋጣሚ ባዶ የቀረዉ የኦነግ ድርጅንት ለመጠቀም በመኔሶታ/አሜሪካ እና በአዉሮፓ ከተሞች የሚኖሩ ስለ ኦሮሞ ኢትዮጵያነት ታሪክ ያልተማሩ የኦነግ ዉሸት ፕሮፖጋንዳ ያታለላቸዉ የዋህ ወጣት የኦነግ ተከታዮችን “ገንዘብ” ለመበዝበዝ የሚሯሯጡትን “የቁም ሙታን ዉሸተኞችን” ወጊድ ብላችሁ አገራችሁ ኢትዮጵያ እንጂ “መኔሶታ ወይም ስቴክሆልም” ያለመሆኑ ተረድታችሁ፦ “ለሻዕቢያ ኮሎኔሎች ዉሃ አመላላሽ እና እንጨት ፈላጮች” ከመሆን እንድትድኑ፤ አጋጣጣሚዉን ተጠቅማችሁ “ከዉሸት ቀፎ” ራሳችሁን አስወጡ። ፖለቲካዉ ካልሰራ፤ ሌላ ፖለቲካ መለወጥ ደመብ ነዉ። “ባለህበት ርገጥ” -እዛዉ መዘፈቁ እንደ “ማሙሽ” ራስን ማታለል እና መበደል ነዉ። ከወደቁ በሗላ መፈራገጥ ለመላላጥ!! እነ “አሰፋ ጃለታ” የአሜሪካን *ሳብ-ወይ* “ሳንድ-ዊች” እየገመጠ ልጆቹን እያስተማረ ራሱን ከመከራዉ ከልሎ በአሜሪካን ጎዳናዎች እና ዩኒቨርሲቲዎች እያዝረጠረጠ “ሌንጮን እየኮነነ” “ግፋ በለዉ” ሲላችሁ <ኦሮሚያ የሚባል “አገር” ነጻ ለማዉጣት ና ወደ ጦር ሜዳ ምራን፤አብረሀን እንሂድ በሉት! የም ቢሆን “ባለ ሃሞት” ሄያጅ ካለ ማለቴ ነዉ።>- ያኔ የቃሉን እዉነትነት ትሰሙታላችሁ>> “መልካም አዲስ ዓመት” (ካዉንት ዳዉኑ ይቀጥል! Let the Countdown contiunue!Who is Next?)::
ወደ ዋናዉ ርዕሳችን እንግባ። ባለፈዉ ክፍል ሁለት በወያኔዉ ስርዓት በአዲስ አበባ ፖሊስ የወረዳ 20/ የምርመራ ሹም እና አዛዥ የነበሩት የመቶ አለቃ አበረ አዳሙ መኮንን የነገሩን ወያኔ አብደል መጂድ ሑሴን እና የወያነዉ ጀነራል ሓለፎም አርአያን የመግደል ሙከራ እና ግድያ እንዴት ለፖለቲካ መጠቀሚያዉ ለማድረግ እንደሞከረ አስረድተዉናል። ዛሬ በዚህ ክፍል ደግሞ ስለ ሕግ የበላይነት በወያኔ አተሮጓጎም እና ጭካኔ 17፣ ጭካኔ 18፣ ላዉንቸር ወዘተ…የተባሉ ልዩ ሃይሎች ለአድማ ብተና ሲሰማሩ በሰለማዊ ሰልፈኞች ላይ “ላዉንቸር” እንዲጠቀሙ ነጻነት እንዳለቸዉ የጠቆሙበት ቃለ ምልልስ ነዉ። አንዳንዶቹ ከንግግር/ከቃለ መጠይቅ የተወሰዱ ስለሆኑ ለስርዓተ ንባብ አመች ሁነዉ ሳይገኙ ሳያቸዉ ለንባብ እንዲመች አስተካክየ አቅርቤአቸዋለሁ። እንቀጥል፦
"ሕግ ማለት ምን ምን ማለት ነዉ? ሕግ ማለት ጉዳዮችን በበላይነት ያለ አድልዎ ህብረተሰቡን የሚያገለግል የሕዝብ ተቋም ነዉ። አንዳንድ ባለሞያዎች ሕግ ማለት ለገዢዉ መደብ የሚያገለግል የማስከበሪያ ተቋም ነዉ ይሉታል። የሗላኛዉ ትርጉም “ሕግ ማለት ለገዢዉ መደብ የሚያገለግል ማሳሪያ ነዉ” የሚለዉ ለኢሕአዴግ ይሰራል። ለድርጅቱ መገልገያ ስላዋለዉ። የዜጎችን መብት እናከብራለን በሚሉት አገሮች ግን የሕግ ትርጓሜ “ሕግ” ማለት ምን ማለት ነዉ? ሕግ ማለት ማሕበራዊዉን ፖለቲካዊዉን እና የአስተዳደራዊ ተቋማቶችን ለዜጎች በእኩል የሚያስተዳድር ተቋም ማለት ነዉ። ሕግ ማለት በኢሕአዴግ ኢትዮጵያ -ሕግ- *የበታች* ነዉ፤ ፖለቲካዉ ደግሞ *የበላይ* ነዉ። ሕግ ያለዉ ታች ነዉ፡ ፖለቲካዉ ደግሞ እላይ ነዉ ያለዉ። ሕግ የበላይ ቢሆን ኖሮ የዜጎችን መብት በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ሕግ እንዲጣስ አይፈቀድም ነበር።
የሕግ የበላይነት ቢኖር ኖሮ እነ ስየ አብርሃ እስረ-ቤት ሲገቡ ብቻቸዉን አይገቡም ነበር። አብረዉ እነ አቶ መለስ ዜናዊም ጭምር ነበር የሚገቡት። ምክንያቱም የፈጸሙት ወንጀል ዕኩል ነዉ።ምክንያቱም ለመከሰሳቸዉ ምክንያት ሙስና ፈጽመዋል ከተባለ ያን ያህል ከባድ እና ሰፊ ወንጀል ከተፈጸመ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሙስና እንዳይስፋፋ/እንዳይፈጸም ባለመከላከላቸዉ እኮ በሕግ ያስጠይቃቸዋል (ሌላዉን ጉዳቸዉን ትተን ማለት ነዉ)።
እነ ስየ አብርሃ፤ አሰፋ አበርሃ፤ እነ አባተ ኪሾ ቢተዉ በላይ ወዘተ..ወዘተ.. የሚባሉ ባለስልጣናት ያ ሁሉ ከባድ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ከተባሉ፤ ያን ሁሉ ብሄራዊ ጉዳትና ጥፋት እንዳይፈጸም የመቆጣጠር ሃላፊነት ያለዉ ማነዉ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነዉ። ስለዚህ ሙስናዉን እና ከባድ ከባድ ወንጀሎችን እንዳይፈጸሙ በወቅቱ በላመቆጣጠራቸዉ እና ባለመከላከላቸዉ በስራቸዉ ላይ እንዝህላልነት ስላሳዩ በብቃት ማነስ ብቻ ከሃላፊነታቸዉ መወገድ ብቻ ሳይሆን ለሙስና በር ከፍተዉ በማመቻቸታቸዉ በሕግ ያስጠይቃቸዋል። ሃላፊነት መዘንጋት በሕግ ፊት ያስጠይቃል።
አንድ ጦር አዋጊ ምሽጎችን ካልተቆጣጠረ ለጠላት ጥቃት ምቹ ሁኔታ ከከፈተ በጦር ሜዳ ሕግ ያስጠይቀዋል። ይሄም አስተዳደራዊ ሕግ አለዉ። የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳሽም ጠያቂም የላቸዉም።የሕግ የበላይነት ቢኖር በዚህ መንገድ ለግል ጥቃት እስር ያስገቡዋቸዉ ብቻ ሳይሆኑ የህወሓት መአከላዊ አመራር አባሎች እንዳለ በሙሉ ተለቅሞ አስር ቤት ይገባ ነበር።
እነ ታምራት ላይኔ ብቻቸዉን ያጠፉት ነገር አይደለም። አንዴ ሱካር አንዴ ምን እያሉ ሰማቸዉን በማራከስ ራሳቸዉን ንጹህ ለማድረግ ከመሃላቸዉ ለማጥቃት የፈለጉዋቸዉን ግለሰቦችን መርጠዉ ወደ ህዝቡ ወላፈን በመወርወር ራሳቸዉን ንጹህ እና እዉነተኞች ለማድረግ ተንጫጩባቸዉ።
ቀደም ብየ እንዳልኩት የሕግ የበላይነት ቢኖር ኖሮ ሁሉም ተለቅመዉ እስር የመግባት ዕድላቸዉ በእርግጠኝነት ማስረገጥ ይቻላል። አንድ እታች እጅግ በጣም እታች ያለዉ “ተራ ዜጋ” (በሕዝብ ቋንቋ) እና እላይ ያሉት በ“ዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲ” የሚታዩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዜጎች አሉ። ተራ ዜጋ እና “ዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲ” ያለዉ ዜጋ ለምሳሌ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ የመሳሰሉት ሰዎች በሕግ ፊት ሲቀርቡ ሁሉም እኩል ናቸዉ።
በሃገሪቱ ዉስጥ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ፤ በሃገሪቱ የተፈጸሙ የተለያዩ የሙስና ተግባሮች እና የንብረት ምዝበራዎች፤ ቅድም ስጠቅሳቸዉ የነበሩት በእነ “አቶ ተስፋየ ናሁ ሰናይ” ጋር በመሆን (የኢትዮጵያ መንገዶች ዋና ስራስክያጅ ባለስልጣን) ትራክተሮች-ቡልደዘሮች የመሳሰሉት ከባድ-ከባድ ንብረቶች ከወደብ እንደ መጡ ወደ ሌሎች ክልሎች ከመሄዳቸዉ በፊት-ወደ ትግራይ እየሄዱ ለትግራይ ክልል መገልገያ እንዲዉሉ የተደረገዉ የሕግ በላይነት ያልተከተለ አድላዊ አሰራር ስንመለከት አሰራሩ “ሙስና ነዉ”! “ምዝበራ ነዉ”! “አድልዎ የተከተለ አሰራር ነዉ”። ይህንን ያደረጉት ደግሞ እነ “አቶ ተስፋየ ናሁ ሰናይ” እና እነ “አቶ መለስ ዜናዊ” ናቸዉ። የሕግ የበላይነት ቢኖር ኖሮ እነዚህ ሰዎች ለምን አልተጠየቁም? ምክንያቱም የሕግ በላይነት የለም።
በአንድ አገር የሕግ የበላይነት ካለ ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበራል፤ በሙስና የተዘፈቁት ባለስልጣኖች ሁሉ ከተራ አስከ ዲፕሎሚቲክ ማዕረግ የያዙ በምዝበራ በአድልዎ ፍርድ በማዛባት የተዘፈቁ ሁሉ በሕግ እኩል ይዳኛሉ። በኢትዮጵያ ይህ የለም። አቶ መለስን መክሰስ እና ፍርድ ቤት ማስቆም አይቻልም! ያገሪቱ ሕግን በመጫምያቸዉ በመርገጥ አሳቸዉ ከላይ ሆነዉ ህጉ ግን ከታች በስራቸዉ ስለሚደፈጠጥ ነዉ። ፖለቲካዉ ደፍጣጭ-ሕግ ተደፍጠጭ!
በጣም የሚገርመኝ፦ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሕግ የበላይነት በሌለበት ሃገር “ማልቲ -ፓርቲ” ሲስተም/ስርዓት እናሰፍናለን ብሎ ለይስሙላ አዉጆ “ዲሞክራሲ” አለ ብሎ ለዓለም ሲዋሽ “ድርቅናዉ-ድፍረቱ” ግርም ይለኛል! ከሕግ እና ከ “ማልቲ- ፓርቲ ዲሞክራሲ” የትኛዉ ይቀድማል? ይህንን ሰብአዊ፤ የማሕበረሰብ የሕግ ሙሁራን ይተቹበት፡ ለነሱ ልተወዉ።
እኔ በፖሊስ ሙያየ ግን ትንሽ ልበልበት። የቱ ነዉ መቅደም ያለበት- ሕግ ወይስ ዲሞክራሲ? አንድ ዳኛ የሚዳኘዉ በሕግ ነዉ። ዜጎች የሚዳኙት በሕግ ነዉ ወይስ በማልቲ-ፓርቲ ሲስተም? ሕግ ሰዎችን መብት ማስጠበቅ ካልቻለ፤ እንዴት “ዲሞክራሲ” የዜጎችን መብት ሊጠብቅ ይችላል። ዲሞክራሲ ሕግ አይደለም። ሕግ የዲሚክራሲ ጠባቂ ነዉ። ጠባቂ በሌለበት ደካማዉ ተቋም በራሱ መቆም እና መከላከል አይችልም። ሕግ እና ዲሞክራሲ አለ ባሉን የኢትዮጵያ ምድር ዜጎች ይደበደባሉ፤ይዘረፋሉ። መደብደብ አልቀረለትም፤መገደል አልቀረለትም። እነዚህ ሁሉ ሰብአዊ መብቶች ናቸዉ። ነገር ግን ተጥሰዋል። እነዚህ ሰብአዊ መብቶች በሚጣሱበት አገር ላይ “መናገር፤መጻፍ መሰብሰብ መቃወም እና መደራጀት” የምትችለዉ በየትኛዉ ታምራዊ መንገድ ነዉ? የትኛዉ ነዉ መቅደም ያለበት? እነዚህ የሚሰሩት እኮ ሕጉ ሲሰራ ነዉ። ዲሞክራሲ የሚንቀሳቀሰዉ “በሕግ የደም ስር ዉስጥ ነዉ” ።ቀዳሚዉ ተቋም መሰረቱ እየተጣሰ ስለ ሁለተኛዉ መንፈስ ስለ “ማልቲ ፓርቲ” ላዉራችሁ ሲለን ‘የንቀቱ፤የማይምነቱ ብዛት’ *ክት* የለዉም።
እኛ ፓርቲ እና ዲሞክራሲ መመስረት መብት አይነሱ ማለታችን አይደለም። እያልን ያለነዉ- የሕግ ተቋማት ዜጎችን ያገልግሉ፡ ነዉ የምንለዉ። መብቴ ተከብሮልኛል፤ ገዢዉን መደብ በድምጽ አሸንፈዋለሁ ወደ ሚለዉ ፖለቲካዊ እምነት የሚከደዉ እኮ ሕጉ ሲሰራ ነዉ። የዲሞክራሲ መብታችን ከመጠየቃችን በፊት እንደ ዜጎች “ሕጋዊነታችን” በሕግ ጥላ ስር ምን ያህል አጥልሎናል? ሕግ የዲሞክራሲ ምርኩዝ ነዉ፡ ሙርኩዙ ከተሰበረ ዲሞክራሲ አይሰራም፤እሩቅ መራመድ አይችልም።
ባለፈዉ የኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ፍትሕ ፍለጋ የጎጃም ገበሬዎች ከጎጃም በእግር በመከራ ተጉዘዉ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ያካባቢያቸዉ አስተዳደር በብልሹነቱ ሕግ በመጣስ ተጭኖናል፤ፍትሕ ኩፍኛ ተዛብቷል በማለት አቤቱታቸዉን ባሰሙበት ወቅት፦ የአዲስ አበባ ወጣት ተማሪዎች ከጎናቸዉ በመቆም ምግብ እና ዉሃ ከማቅረባቸዉ ሌላ በአብዩቱታዉም ጭምር ሰላማዊ ሰልፍ በመደገፍ አብረዋቸዉ ስለጮሁ፦ -አስቀድሜ በቃለመጠይቁ ላይ “መዶሻ” የሚባሉ ልዩ ታጣቂ የሰዉ ጭንቅላት ለመፈርከስ ለመቀጥቀጥ በሰለጠኑ ልዩ ሃይሎች ተይዘዉ ራስ ቅላቸዉን በሰደፍ እና በዱላ እየተቀጠቀጡ “ሸጎሌ” በሚባለዉ ቦታ ታፍሰዉ ታስረዉ “ሌሊት-ሌሊት” እየተደበደቡ በዛዉ ብርድ በላያቸዉ ላይ “ዉሃ” እየተደፋባቸዉ፤ በዉሃዉ ብዛት ከረጠቡ በሗላ በማግስቱ አፈር በበዛበት መረት እና ጠጠራማ መሬት እንደ አህያ “ተንከባለል!” እየተባሉ በአመድ ላይ እንዲንከባለሉ በማድረግ ዉሃዉ እና አመዱ ልብሳቸዉን በጭቃ ለዉሶ “ተነስ፤ተኛ፤ተንከባለል፤ሩጥ!!” እያሉ የትምርት ቤት ህጻናትን በጭካኔ እየተቀጠቀጡ ለስቃይ ተዳርገዉ፤ አንዳንዱም ለአካለ ጎዶሎነት ተዳርገዋል። ይህ ተግባር የሚፈጽሙት ደግሞ እነ “ገዛኢ-ገብረአነንያ” ናቸዉ። ገዛኢ ገብረአነንያ ደግሞ ሌቦች እና ወረበሎችን መሳሪያ እያስታጠቀ ዝረፉ እያለ ሲያሰማራቸዉ ነበር ብለን አስቀድመን የተወያየንበት የወያኔ ከፍተኛ ፖሊስ ኮሚሽነር ነዉ።
እናንተ “ትምክህተኞች” እያለ በ18፣ 19፣ 20 የዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉት ህጻናት ተማሪዎችና ልጃገረድ ተማሪዎችን በዱላ ቀጥቅጧቸዋል። በብረት ሰደፍ እየገጩ “ይቅርታ ጠይቁ!” “አጥፈተናል ብላችሁ እየፈረማችሁ ጠይቁ!!” እያለ ካስጨነቃቸዉ በሗላ፤- “አጥፍተናል መንግስት በድለናል ብለዉ ተማሪዎቹ ጽፈዋል ተብሎ፡ በአዲስ አበባዉ ከንቲባ በአቶ ዓሊ አብዶ የይቅርታ ጽሁፍ ተናጋሪነት በኩል “ጥፋተኞች ነን ይቅርታ ይደረግልን” ብለዋል ተብሎ ሕግን በመጣስ ለሕዘብ እንዲነገር በሕዝብ መገናኛ አስተላለፉት።
እንግዲህ ተማሪዎች የመሰብሰብ እና የሰላማዊ መንገድ ተከትለዉ ከገበሬዎቹ ጋር ቆመዉ አቤቱታቸዉን ለዓለም ማስተጋባት መብታቸዉ መሆኑ እየታወቀ- ፍዳቸዉ እንዲያዩ ፤አካላቸዉ እንዲጎድል ከተደረገ ሕግ ተጥሷል እና የሕግ የበላይነት የለም። ቢኖር ኖሮ ተማሪዎቹ ባልታገዱ፤ሲታገዱ እና ሲጎዱ መክሰስ እና መብታቸዉን ማስከበር “ካሳ” መጠየቅ መብታቸዉ ይሆን ነበር። መንግስት እና አድማ በታኝ ፖሊሱ ተማሪዎች እና ለገበሬዎቹ እንዲሁም ለተማሪዎቹ ወላጆች “ይቅርታ” መጠየቅ ነበረበት። አልሆነም። ለምን? ሕግ ከታች ፖለቲካዉ ከላይ ሆኖ ወያኔ ሕጉን እንዴት ለራሱ መገልገያ ስለሚጠቀምበት ነዉ።
ፖሊሱን ስትፈልግ “ግደል” ስትፈልግ “ዝረፍ” እያለ በዜጎች ሕይወት እና ኑሮ ነጻ እርምጃ ያስወስዳል። የፖሊሱ ሃይል ለግል መገልገያዉ አድርጎታል። አንድ ተከሳሽ ከፍርድ ቤት እንዲቀርብ ለጥያቄም ሆነ ‘ክስ’ ተመስርቶበት መጥሪያ ከማግኘቱ በፊት- ፖሊሱ ከእላይ ካሉት ባለስልጣኖች ታዝዞ ይዞ ለድበደባ ይዳረገዋል። ይደደበድበዋል! አካሉ ያጎድለዋል! ፖሊሱ የፈለገዉ አድርጎ ሲለቀዉ “ጠያቂ” የለዉም።
ስለዚህ ዲሞክራሲ ለማስፈን ፤ዜጎች ሰላማዊ አድማ ሲመቱ - የሰለጠነ አግባብነት ያለዉ አድማ በታኝ (መበተን ሕጋዊ ሆኖ ከተገኘ) የፖሊስ ሃይል በቦታዉ መንግስት ሲያሰማራ ነዉ ዲሞክራሲ ተከብሯል ሕጉ እየሰራ ነዉ የሚባለዉ። የኢሕአዴግ በታኝ ፖሊስ ግን የሚሰለጥነዉ “እርምጃ” እንዲወስድ ነዉ። “መበተን” ሳይሆን የሚያዉቀዉ “መግደል” ነዉ። መበተን እና መግደል ልዩነቱ ጭራሽ አያዉቀዉም። መግደል እና መበተን ለየብቻ ናቸዉ። ዓለም አቀፍ ሕጉ የሚለዉ አድማዉ የዜጎቹ እና የአገሪቷን ሕልዉና የሚፈታተን ከሆነ አስጊነቱ ታይቶ “በትን” ነዉ የሚለዉ እንጂ “ግደል” አይልም። የወያኔ ፖሊስ ግን ልዩ ነዉ። “በታኝ” ሳይሆን “ገዳይ” ነዉ። ”Special Commando” ነዉ። ወደ ጦር ሜዳ የሚሄድ ልዩ ኮማንዶ ነዉ የሚመስለዉ። የተለያየ ስም አለዉ። ጭካኔ 17፤ጭካኔ 18፤ ላዉንቸር ወዘተ …የሚባሉ ሃይሎች አሉት።እነዚህ ለአድማ ብተና ሲሰማሩ ላዉንቸር ይዘዉ ተኩሶ የመግደል ትዛዝ እና መብት ተሰጥቷቸዉ ተጠቅመዉበታል።
ላዉንቸር- በጦር ሜዳ ዉስጥ የሚተኮስ ከባድ ጥይት ነዉ። ወያኔ ግን በሰላማዊ ዜጎች ላይ በ አድማ ወቅት ተኩሰዉ ህጻናትን እና ተማሪዎችን እንዲገድሉበት ይታዘዛሉ። እነዚህ ጭካኔ 17፣ ጭካኔ 18 ፤ላዉንቸር እና ወዘተ የሚባሉ ቡድኖች አድማን ለመበተን ሳይሆን የሚሰለጥኑት ለመግደል ነዉ። ይህ ደግሞ የዜጎችን መብት የሚጻረር ነዉ። ለዜጎች ያልቆመ ለሕግ የበላይነት ለማስከበር ሳይሆን የተቋቋመዉ የገዢዎች መገልገያ እንዲሆን ሆን ተብሎ የተዋቀረ ነዉ። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበር ከመሰረቱት እና ከፈረሙት መሃል አንዷ ናት። ያችን አገር ነዉ ወያኔ እየገዛት ያለዉ። በዚህ አንጻር በፖሊስ እና በደህንነት ክፍሎች ዜጎች እየታፈኑ በጭካኔ ያለ አግባብ ሕግ አልባ እየተያዙ እንዲሰወሩ እና እንዲገደሉ እንዲደበደቡ እና እንዲጨፈጨፉ በተፈቀደበት ተጠያቂነት በሌለዉ ሕግ አልባ ስርዓት የምንኖር መሆኑን እያወቅነዉ “የማልቲ-ፓርቲ” ሲሰተም ከመሰረቱት አገሮች አንዷ በኢሕአዴግ የምትመራ ኢትዮያጵያ ናት ብሎ ሳያፍር ለዓለም ሲዋሽ የ“ሕግ” እና ከሕግ ጋር ንክኪ ያላቸዉ ምሁራን እና ባለሞያዎች ዉሸቱን ሲያደምጡ ልቦናቸዉን ምን ያህል እንዳሳዘነዉ የሚያዉቀዉ ያዉቀዋል።ወያኔ ያችን አገር የሚመራት በእንደዚህ ዓይነት የሕግ ረገጣ ነዉ"። በሚቀጥለዉ ክፍል 4- ስለ ታጋዮቹ መልሶ ማቋቋም እና በንግድ ቤቶች እና በክራይ ቤቶች የታየዉ አድልዎ ይቀርባል። ይቀጥላል…