Sunday, November 28, 2021

ጽንፍ የረገጠ ምጎሳ ተጠያቂነትን የማስወገጃ ዘዴ ጌታቸው ረዳ ETHIO SEMAY 11/28/2021

 

ጽንፍ የረገጠ ምጎሳ ተጠያቂነትን የማስወገጃ ዘዴ

ጌታቸው ረዳ

ETHIO SEMAY

11/28/2021


ቤተመንግሥት ያለው ኦሮሞ ነው፤ ሲለን የከረመው ጸረ አማራና ጸረ ትግሬው የአፓርታይዱ ሥርዓት መሪ ፋሺሰቱ አብይ አሕመድ ሰሞኑን ወደ ጦር ግምባር መሄዱና ኮቴው ተከትለው ክላሽ ይዘው ሲንገዋለሉ ያየናቸው ማንንታቸው አጥርተን የምናውቃቸው አሽቃባጮቹ እንደዘመቱ እያየን ነው።

በዚህ ጊዜ መሪያችንን መውቀስ አያስፈልግም የሚሉ አሉ። ምናልባትም 98% ይሆናሉ የሚል እገምታለሁ። በስሜት የተጠለፉ የተሰለቡ ሕሊናዎች በዚህ ፋሺሰት ላይ  ሃሳብ መሰንዘሬም የተለመደው ላሃጫቸው የሚረጩብኝም አይታጡም። ሆኖም ለሹመት የምቋምጥ አይደለሁምና “የአሜሪካ ባሕል ያስተማረኝን የመናገር ትጉህ መብቴን በመመርኮዝ” ማለት ያለብኝን እላለሁ።

መዝመቱ ጥሩ ነው? አዎ! ግን ዘግይተዋል? በደምብ ከሚገባው በላይ ‘የፓርክ ችግኝ’ ሲተክል ፤ፎቶ ሲነሳ ከርሟል። በዚያ ባሳለፋቸው “ሓላፊነት ያልተወጣቸው ወቅት የስንት ሽህ ሕይወትና ንብረት ጠፋ? ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቀለ? ስንት መቶ ሴቶች በወረበላዎቹ ወያኔዎች ተደፈሩ? ብለን ብንጠይቅ፤ የተጠቀሱት ሁሉ ተፈጽመዋል።

ይህ  ሁሉ ጥፋት ደርሶ “ሪፑብሊክ ትግራይ” ለመምስረት እየተጋ ያለው ‘ወረበላው ወያኔ’ አዲስ አበባ በር “አፋፍ ላይ” መቃረቡን ሲያይና ሥልጣኑን ወደ መቀማቱ አዝማምያ እና ሊማርኩት እንደሚችሉ ሲገነዘብ “የሚጋጓላትን የሥልጣን ጉዳይና በሕይወት ላለመያዝ ፈተና” ሆነበትና “ተከተሉኝ ሄጃሎህ” ብሎ ለብሶት የማያውቀውን  የጦሩን ደምብ ልብስ ለብሶ ጫካ ውስጥ ከአዛዥ ወታደሮች ጋር ተቀላቅሎ ስልክ ሲያወራ ፎቶው ተለቀቀ።

በዚህ ላይ ጽንፍ የረገጠ አክብሮትና የምስጋና ጋጋታ ከተከታዮቹና አዲስ ገቢ አድናቂዎቹ ተችሮታል። ይህ ጽንፍ የረገጠ ከሚገባው በላይ የተንጋጋ “የምስጋናና የጀግንነት ቃለ አጋኖ” የሰውየው ወንጀሎችና ተጠያቂነትን ለማስረሳት ስለሚረዳ ይህ እጅግ አደገኛ የመካብ ባህል መጠን እንዲኖሮው ሃሳብ እለግሳለሁ:

ጦረኞቹ ሰው ከሚያርደው “ኦነግ” ጋር ግምባር ፈጥሮ ሰሜን ሸዋ ድረስ እስኪመጡ ድረስ ደካማ አማራር ሲሰጥ  ነበር ወይንም ጀሮ አልሰጠውም ነበር ማለት ነው። 

አማራዎች በኦሮሞዎቹ ምድር እንዲታረዱ ተከብበው “የመንግሥት ያለህ” የአብይ ያለህ! ከዚህ ከበባ አስወጡን!” እየሉ ሲጨሁ፤ የሚደርስላቸው አጥተው “በመቶወቹ ታርደው ተጨፈጨፉ። በዚያም በዚህም ከፍተኛ ጥፋት ሲፈጸም አድፍጦ ቆይቶ አሁን ሰዎቹ አጥሩ ድረስ ሊንጠላጠሉ ሲሉ ‘የአልሞት ባይ ተጋዳይ” ወደ ጦር ግምባር ተቀላቀለ።

እዚህ ላይ የሚገርሙኝ ሰዎች አሉ። ወይ ዝምት ወይ አፍህን ክደን የሚሉ ጺምና ሽበት ያወጡ ልክ እንደ ህጻኑ  አፓርታይዱ መሪያቸው “የሸመገሉ ህጻናት” በፌስቡክ ሲለፋደዱ ማንበብ ከገረሙኝ የሰው ትንሾች አሉ።

ይህ ሁሉ ጉድና ኪሳራ ሲደርስ አፋችሁ ክደኑ እያሉ የአለቃቸውን ቃል እየተከተሉ “ተጠያቂነት እንዳይኖር” ለማድረግ ተጨማሪ ኪሳራ ከመከሰቱ በፊት “መሻሻል ያለባቸው” ነገሮች እንዳይሻሻሉ”  አፋችሁን ክደኑ ማለት “አሁንም ልድገመው------ተጠያቂነት እንዳይኖር” የሚደረግ ሽፋን ነው።

መሪ መሆን ማለት ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ዉጤት ሐላፊነት መውሰድ ማለት ነዉ። ሃሳቦች እና ወቀሳዎች እንዲሁም ሂሶችና ዘለፋዎች ከዜጎች ሲደመጡ መሪዎች የሚጠቅማቸውን መያዝ የማይጠቅማቸውን “ወደ ጎን” በመተው ሰምተው እንዳለሰሙ ከመሆን ይልቅ “ጭራሹኑ ወይ ዝመት ወይ አፍህን ክደን” ብሎ ነገር አስቂኝ ዘመን ነው።

ተጠያቂነት ማለት ከዜጎች ሃሳብን መቀበል ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ እና የወደፊት ውጤቶችን ለማሻሻል የተወቀሱበትና የተማሩትን ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው።. የተለያዩ የዜጎችን ስሞታ እና ወቀሳ መቀበል ለወደፊት በሚደረጉ ዘመቻዎች ስለሚያተኩሩ ገንቢ ሃሳቦች ከሆኑ መቀበል፤ ካልሆኑ ንቆ መተው እንጂ “አፍህን ክደን፤ ሂድ ውጣ ወይ ዝመት” ማለት “አባታዊ ባህል” ነው።

በነገራችን ላይ አብይ ሲዘምት ካሁን በፊት ያልተጠቀመበት የጦርነት ስልት ነድፎ ነው የሄደው ወይስ “አፋፍ በሩ” ላይ በመቃረባቸው የፈጠረው “ድንጋጤ? የምታውቁ ጠበቆች ካላችሁ አስረዱን!

አንድ የታዘብኩትና የገረመኝ የታማኝ በየነ ንግግር አደምጥኩና “አየ ታማኝ አልኩኝ!”። ተዋጊው ምስኪን ወገኔ በተሰበሰበው ሜዳ ተገኝቶ “ከዚህ በሗላ እስከ መቀሌ ድረስ እንገባለን” ይላል። ጥያቄ አለኝ፡ “በአብይ አሕመድ ትዕዛዝና መሪነት “ትግሬዎች በመሆናቸው ብቻ’ ‘በምኑም ፖለቲካ በሌሉበት’ ብዙ ንጹሃን የትግራይ ዘመዶቻችን፤ ንብረታቸው ተዘርፎ፤ አንዳንዱም ተገድሎ፤እመጫቶች፤ ዕርጉዞች፤ በሽተኞች፤ ህጻናት ልጆች ለጎረቤት አስረክበው በገፍ የታሰሩ እናቶች፤ አራጋዊያንና፤ ወጣቶች” መቀሌ ስትገቡ የመቀሌ ሕዝብ ምን ይሰማዋል ብለህ ትንሽ ተመራምረህበት ይሆን? 

ይህ የጅምላ ዕስራት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ንጽሃን ትግሬዎች አላሰርንም “ያሰርናቸው በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው”  ብለው ተደጋግሞ ባለሥልጣኖቹ ተናግረዋል (ይቅርታ ተሳስተን አስረናል እንኳ በሌለበት ንግግር!)። ስሜትና ፖለቲካ እንደማይጣጣሙ እናውቃለን። መቀሌ ስትገቡ ፤ የትግራይ ሕዝብ የሚጠይቃችሁ “በስሜት የተናገራችሁት” ሳይሆን “የሚያቀርብላችሁ “የፖለቲካ ጥያቄ” ነው። ልጆቻችን በገፍ ለምን አሰራችሗቸው? ብለው ቢጠይቁዋችሁ “በትግሬነታቸው ሳይሆን ወንጀለኞች ስለሆኑ ሁሉም ትግሬ አስረናል” ነው መልሳችሁ? 

ይህ በጣም በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ፖለቲካ በስሜት የሚጋልብ መሪ ተይዞ “መቀሌ” ተግብቶ እንደበፊቱ “በሕዝቡ ብትከበቡ”- “ሰብል የማጨዲያው” ወቅት ነውና ገበሬው አጭዶ እስኪጨርስ “የተናጠል ቶክስ” አድርገናል፤ “መከታ ወደ እሚሆነን ሕዝባችን አፈግፍገናል!” ይሆን መልሳችሁ?

ለመሆኑ እነ አንዳርጋቸውና እነ ንአምን ዘለቀ “መቀሌ” ይዛችሁ ልትገቡ ይሆን? እነዚህ ሰዎች በትግራይ ሕዝብ ምን ያህል በጠላትንት እንደሚታዩ ታውቃላችሁ?


አስቀድማችሁ መሰራት ያለበትን ፖለቲካ ሳትሰሩ “አስክንድር ነጋን” በውሸት አስራችሁ፤ “በርካታ ንጹሃን ትግሬዎች በትግሬነታቸው ብቻ አፍሳችሁ ለመከራ ዳርጋችሁ”፤ በስሜት ብቻ እየጋለቡ መቀሌ  መግባት የሚቻልበት ታአምር ለኔ ግልጽ አይደለም። 

በዚህ የጋጋታ ጦርነት በሳል መሪ ሳይያዝ ድል ማምጣት አይቻልም። ለኔ እንቆቁልሽ ነው። ቤተመንግሥትና ደህንነት ቢሮ ተቀምጦ “ቀፍድድልኝ እፈስልኝ የስሜትና የጥላቻ ፖለቲካ” ብታምኑኝም ባታምኑኝም የኔ ዕይታ “በትዕግስትና በጥበብ ማሸነፍ ይቻል የነበረው ጦርነት በአያያዝ ብሉሽነት አበላሽቶታል”።

ሥልጣን ላይ የተቀመጡት “መሪዎች” ጠላት እንዳይጠቀምበት ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን አያያዝ በደም ፍላት ኳስዋን ለጠላት በማቀበላቸው ምክንያት ታማኝ በቀና ልቦናው እንደሚጓጓው “መቀሌ ለመግባት ለሚደረገው ጉዞ ካለፈው የደርግ ዘመን የተከሄደው \ያመነም ያላመነም የጅምላ እስራት\ አብይ አሕመድ እንደገና ያንን “የድንቁርና ዑደት” ሲደግመው “ተከታዮቹ” የሚያስክትለው “ፖለቲካዊ ሰበብ” በፍጹም አልገባቸውም።

“እነ አብይ አሕመድ፤ እነ ንአምን እነ አንዳርጋቸው ጽጌ” መቀሌ ሲገቡ፤ ሕዝቡን እንዴት እንደሚያነጋግሩት የዚያ ሰው ይበለን “ትዕይንቱ” አብረን የምናየው ይሆናል።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

 ETHIO SEMA