Sunday, December 28, 2008

ዜጎች ሲገደሉ ወደ ዲሞክራሲ የሚወስድ የሽግግር ሂደት ገበያዉ ሲንርም የዕድገት ምልክት ነዉ ይሉና ኩርር ኩርርር! ጀሮ ያሳምማል።

ዜጎች ሲገደሉ ወደ ዲሞክራሲ የሚወስድ የሽግግር ሂደት

ገበያዉ ሲንርም የዕድገት ምልክት ነዉ ይሉናል!
ኩርር ኩርርር! ጀሮ ያሳምማል
ጌታቸዉ ረዳ
ትችቱ ለቀድሞዉ የወያኔ መስራች ዛሬ በአሜሪካን ሀገር በሎስ አንጀለስ ከተማ ለሚኖሩ ለአቶ ሃይሉ መንገሻ ነዉ።
ወደ መነሻ ጉዳየ ከመግባቴ በፊት ዓምና የሰማሁት ሁላችሁም የምታዉቋት ዶክተር ሙሉወርቅ ቀጸላ የተባለችዋ “ወያኔ” (የትዉልድዋ ከተማ -“አክሱም”) ይግረማችሁ ብላን “ሃያ የአፍሪካ ድሃ አገሮችን በልማት ማፋጠን ጉዳይ እወክላለሁኝ”-የምትለዋ ስለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕድገት ምጥቀት “ገዛ ተጋሩ” (የትግሬዎች ቤት) ተብሎ በሚጠራዉ ብዛታቸዉ ከ10 እሰከ 20 የተሰብሳቢ ብዛት አድጎ የማያዉቀዉ “የወያኔ-ኩታራዎች እና ወፈፍተኞች”–የሚጯጯሁበት “የኢንተርኔት ገበታ” በእንግዳነት ተጠርታ ስታወራ፦”ከጨቅላዎቹ” አንደኛዉ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት እንዳደገ ከተስማማ በሗላ እንዲያም ሆኖ ገበያዉ “ለምን አልቀመስ”-እንዳለ እንድታብራራለት ሲጠይቃት “ማደጉን በተለመደዉ በወያኔአዊ ዉሸቷ “በመቶኛዉ”-የተወሰ ስሌት በየአመቱ ያደገዉን መጠን ካስቀመጠችለት በሗላ -ለዋጋዉ ንረት ምክንያት “የሕዝቡ ኑሮ እየተሻሻለ በመምጣቱ እና የመግዛት አቅሙና ፍላጎቱም በዛዉ መጠን እያደገ በመምጣቱ ዋጋዉ *ሊንር* ችሏል” ስትል-
በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔን ከመሰረቱት አንዱ የሆነዉ “አቶ ሃይሉ መንገሻ” የተባለዉ፤ከ7 ዓመት በፊት እነ ስየ አብርሃ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተጣልተዉ ለሁለት ሲከፈሉ መለስ ዜናዊ የሚመራዉ ስርዓት *ዘረኛ/አፓርታይድ/ከፋፍለህ ግዛ እና ጎጠኛ እና አምባገነን* ስርዓትን ነዉ ብሎ የሰየመዉን የወያኔ መንግሥት ዛሬ ግን ዶክተር ሃይሉ መንገሻ በቪኦኤዉ የትግርኛ ፕሮግራም ቀርቦ “የወያኔ መንግስት ሰዉ መግደሉን ማሰሩን ማፈኑን፤ዜጎችን አፍኖ ማጥፋቱን የሚታማዉ እዉን ከሆነ (ወያኔ ጥፋተኛ ይሁን አይሁን የማዉቀዉ ነገር የለኝም ይል እና፤-ያዉም ባሁኑ ሰዓት ወንጀለኛዉ ፤ጥፋተኛዉ “እየተጣራ” መሆኑን መረጃ አለኝ ሲለን) እንደችግር ሆኖ- ድርጊቱ ብቃወመዉም የዲሞክራሲ ሂደት ፕሮሰስ ነዉ” ሲሉ ለመለስ ዜናዊ ስርዓት ጥብቅና በመቆም ለትግርኛ ተነጋሪዉ የትግራይ ህዝብ አቋሙን ይፋ አድርጎልናል።
- ዶክተር ሙሉወርቅ ቀጸላ እና ዶክተር ሃይሉ መንገሻ የተማሩት ዱክትርና የሗሊት ሩጫን እንደ ዕድገት መቁጠራቸዉ ከማስገረሙ በላይ ለኩታሮቻቸዉ የሚያስተምሩትን ግብዝነታቸዉን እና ዉሸታቸዉን ወደ ህዝቡ ለማሸጋገር ሲሞክሩ ዝም ማለት ስለማይገባ በዚህ አንድ ልበላችሁ።
ወደ አቶ ሃይሉ ከመግባቴ በፊት የሙሉ ቀጸላን አባባል እንመልከት። ዕደገት ገበያ አስወድዶ ንረት የሚያስከትል ከሆነ “የማደግ ትርጉሙ” *ድህነት* እንጂ እንዴት አደግን ሊባል ይቻላል? ድህነት እና ዕድገት ደግሞ በትርጉምም በሚሰጡት ዉጤትም የተለያዩ ናቸዉ። *የገበያ ዉድነት* በሰዉ ልጆች ኣእምሮ ከባድ ጫና የሚያስከትል ሕሊናን ወጥሮ ዕረፍት ነስቶ ኑሮን የሚያቃዉስ፤ጭንቀትና ብስጭት ጥበት እና ንዴት የሚያስከትል ክስተት መሆኑ እየታወቀ “አንድ አገር በምጣኔ ሃብት አድጓል ከተባለ እና የሕዝቡ የመግዛት አቅም እና ፍላጎትም አድጓል ከተባለ ፤በአንጻሩ ግን የገዡዉ አቅም አድጎ የመግዛቱንም ፍላጎት በዛዉ መጠን አድጎ *ገበያዉን” የሚያስወድደዉ ከሆነ *ከማደግ* ይልቅ *መደህየቱ* ቢመረጥ ጥፋቱ እምኑ ላይ ነዉ? የዕድገት ዋነኛ ፍላጎቱ ህዝቡ በተመጣጣኝ በለዘብተኛ እርከን እቃዎችን ሸምቶ ቤተሰቡን አስተዳድሮ በልቶ ጠጥቶ *ጭንቀት እና ብስጭትን ጥበት እና ንዴትን* ከሕሊናዉ እና እህል አምሯቸዉ በመወደደዱ ምሳ ባለማግኝታቸዉ ከሚያለቅሱ ልጆቹ ሕሊና ለማስወገድ ነዉ። የወያኔ ካድሬዎች የሚሉን ግን “ዕድገት አለ- ነገር ግን ዋጋዉ አልቀመስ አለ” ይሉናል። ለምን ቢባሉ ደግሞ ሕዝቡ “በገንዘብ ስለተምበሸበሸ” “የሕዝቡ የመግዛት አቅም ስለጎለበተ” “ሃብታም ስለሆነ” “ዕቃ መግዘት ስላማረዉ” እቃዉ ተወደደ ይሉናል። የመግዛት አቅም መጎልበት እና የፍላጎት ጉግት የእቃ እና የገበያ ንረት አስከትሎ የሚያስወድድልን ከሆነ “ዕድገት” የሚሉት “ገደል ይግባ” ማለታችን እንዴት ስተተኞች መሆን እንችላለን? ኢኮኖሚዉ ብቻ መሰላችሁ በተሳሳተ የትርጉም ሃዲድ የሚያስኬዱት ፖለቲካዉም ጨምሮ፤ሰብአዊ ረገጣዉንም ጨምሮ ያዉም እኮ *መግደል፤ማፈን፤መደብደብ፤አፍኖ ማጥፋት* የሰብአዊ መብት መርሆ መረገጥን *የዲሞክራሲ መሸጋገርያ ምልክት ነዉ* ይሉናል። ዜጎችን መረሸን ማሰር መደብደብ ጋዜጠኛን ማዋከብ ፍርድ ቤቶችን በመዳፍ ማሽከርከር በሽግግር ወቅት የሚከሰቱት የዲሞክራሰቲክ ሂደቶች ናቸዉ እና ዲሞክራሲ ባንድ ቀን ስላማይገነባ *ስንገድላችሁ፤ስናንገላታችሁ ‘ዋጥ’ አርጉት* ይሉናል።
“ወያኔ በሩን ገርበብ አድርጓል እና እናንተ ዉጭ ሀገር ሆናችሁ አትጨሁበት አትዉቀሱት አትክሰሱት” የሚሉንን እንደ እነ ሃይሉ መንገሻ ዓይነቶቹ “ግርምቢጥ ፖለቲከኞች” እና ደም የጠማዉ ቡድን አፈቀላጤዎች ላለመወቀስ ላለመከሰስ የሚሰጡን *የወንጀል ማምለጫ* ምክንያታቸዉ ‘ግድያ እና የመብት ረጋጣ’ “ወደ ዲሚክራሲ ሚሸኘን የሽግግር ምልክት ነዉ” ይሉናል።ኩርር ኩርርር! ለጀሮ ይቀፋል።
ባለፈዉ ሁለት ሳምንታት በተከታታይ የቪኦኤዉ የትግርኛዉ ክፍል-አራት ኢትዮጵያዉያን ትግርኛ ተናጋሪዎችን ስለ ሰብአዊ መብት መረገጥ ወይንም አለመረገጥ እና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማደግ በወያኔ ስርዓተ ዘመን የሚታዩት ክስተቶች ለአድማጮች እንዲያሰሙ ጋብዟቸዉ ነበር።በ እንግድነት የቀረቡት ሦሰት የህወሓት መስራቾች “ዶክተር አረጋዊ በርሄ” “አቶ ግደይ ዘርአጽዮን” “ዶክተር ሃይሉ መንገሻ” እና አራተኛዉ “መስፍን አየለ” የተባሉ ካሁን በፊት ሰምቻቸዉ የማላዉቃቸዉ እንግዳ ተጋብዘዉ ተከራክረዋል። አራተኛዉ እንግዳ ሙሉ በሙሉ ወያኔዊ ድጋፍ ስላሳዩ አሳቸዉን ትተን እኛ በምናዉቃቸዉ በሦስቱ የወያኔ መስራቾች ክርክር አናትኩር።
ሦስቱም የወያኔ ገበና ያጋልጣሉ ብየ ጠብቄ ነበር። ከግምቴ ዉስጥ ቃላቸዉ ጠብቀዉ ያገኘሗቸዉ ሁለቱም ዶክተር አረጋዊ በርሔ እና አቶ ግደይ ዘርአጽዮን ሲሆኑ ዶክተር ሃይሉ መንገሻ ግን አገር ከማስተዳደሩ በፊት የአእምሮ ጠንነቱ በአእምሮ ሃኪም መመርመር አለበት” በማለት የመለስ ዜናዊ “ንክነት” Who is Meles Zenawi? በሚለዉ ሃይሉ በጻፈዉ ጽሁፉ ድሮ “ንክ” ያሉዉን ‘ሰዉ በላዉ’ የመለስ ዜናዊን “የንክ” ስርአት እንደገና ሲደግፉ ተደምጠዋል ። እስኪ ሦስቱም ሰዎች ከተናገሯቸዉ ጥቂቱን ላስነብባችሁ እና የአቶ ሃይሉ መንገሻ አስተያየት ወደ መጨረሻዉ እንሄድበታለን። አነሆ-
ቪኦኤ- ጥያቄ፦በኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ መብት ረገጣ አለ የምትሉት ነገር ካለ ከያንዳንዳችሁ ብታብራሩልን? አቶ ግደይ ዘርአጽዮን
* በኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ መብት ረጋጣ እንዳለ በሰፊዉ ከተለያዩ የኢንተርናሽናል ድርጅቶች የሰብአዊ መብት ረገጣ በከፋ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ተረጋግጧል። * ስርአቱ ፍረድቤቶቹን ወደ ፈለገበት አቅጣጫ በመጠምዘዝ “ሆን ብሎ” ነጻ ዳኝነት እና ነጻ ዳኞች እንዳይኖሩ የሚያግድ ነዉ። * በሺዎቹ ታፍሰዉ እና ታፍነዉ አስካሁን ድረስ የት እንዳሉ ድራሻቸዉ የማይታወቁ አሉ። * ሲቪክ ተቋማት ሆን ብሎ የሚዘጋ፤ጋዜጠኞች ሚያስር፤የሚያፍን ስርዓት ነዉ። * ሕዘብ የመረጣቸዉ ተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ያለ ምክንያት የሚያስር ነዉ።
ዶክተር አረጋዊ በርሄም በተማሳሳይ የመለስን ስርዓት ኩፍኛ የተጠናወተዉ አምባገነን ለመሆኑ እንደሚከተለዉ በማስረዳት ተከራክረዋል። * ሰብአዊን መብት በሚመለከት ጉዳይ ካነሳን ዘንዳ እንደዚህ ዓይነቱ መንግሥት የከፋ መንገሥት ከቶ ተፈልጎ አይገኝም። ለምሳሌ ጋዜጠኞች በማፈን እና በማሰር ከአፍሪቃ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 2ኛ ደረጃ የጋዜጠኞች መብት ረጋጭና አፋኝ ተብሎ ተሰይሟል። ከዚህ የከፋ ስም ምን አለ? የመናገር የመደራጀት መብት የሚረግጥ መሆኑን ተረጋግጧል።
* ይህ መንግሥት ከመሰረቱ ስንመለከተዉ በማፈን ብቻ ሳይሆን በመግደልም ያምናል።ለምንድነዉ ተቃዋሚዎቹንን የሚገድላቸዉ? ከእርሱ የተለየዉን ሃሳባቸዉ ስለገለጹ *ብቻ*።ዜጎች በማሰር እና በማፈን አጥፍቷቸዋል ስንል በሺዎቹ የሚቆጠሩ ናቸዉ።የለ ፍትህ ይይዛል፤ ያስራል፤ ይሰዉራቸዋል።ስየ አብርሃም ሆነ የቅንጅት መሪዎች ሲያስራቸዉ ያለ ምንም የወንጀል ጥፋት ነበር ያሰራቸዉ።ሲያስራቸዉ ሕግ ያልተከተለ የማን አለብኝ ያምባገነንነኖች ስራ ነዉ።
ቪ ኦ ኤ፦ ዶክተር ሃይሉ መንገሻ በዚህ ረገድ ያለዎትን አስተያት?
+++ይህ መንግሥት በአንድ ጀምበር በአንድ ንጋት አዉሮፓዊ እና አሜሪካዊ አይነት ዲሞክራሲ መልክ መያዝ አለበት ብሎ መከራከር ተገቢ አይደለም። ይህ መንግሥት “ፖዚትቭ” መንገድ እየተከተለ ነዉ ወይ? Yes! ፕሮሰሱን Processን ነዉ ማየት ያለብን እንጂ በአንድ ሌሊት “ዲሞክራቲክ” መሆን አለበት ብሎ መከራረከር ልክ አይደለም።እኔ የኢትዮጵያን መንግሥት የምመለከተዉ የዲሞክራሲዉ “ፕሮሰስ” የችግሮች አፈታት “ካልቸር” ከተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ከሚከተሉት አስተዳደር የማወዳድረዉ እንጂ “ግደይ” ኖርወይ ሆኖ ወይም “አረጋዊ” ሀላንድ ሆኖ “እኔ” አሜሪካ ሆኘ በምንለዉ ወይንም በምናየዉ የኢትዮጵያን አስተዳደር መፍረድ አንችልም። በእርግጥ “ግደይ” እንዳለዉ በምርጫዉ ጊዜ ብዙ ሰዉ አልቋል።ቢሆንም ለእልቂቱ ለወንጀሉ ተጠያቂዉ እና ጥፋተኛዉ ማን ነዉ ለሚለዉ ለመለየት “ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አዉቃለሁ”peace and order ለማምጣት የግድ አንድ ነገር ለማድረግ ትገደዳለህ (ልብ በሉ- ‘ፒስ ኤንድ ኦርደር’ ለማምጣት ወደዳችሁም ጠላችሁም የመግደል አማራጭ የለዉም እያለን ነዉ። እሱ በሚያስተዳድረዉ በአሜሪካ ት/ቤት ረብሻ ቢነሳ የ197 ሰዎች ሕይወት በፖሊስ ጥይት ቢጠፋ “ፒስ ኤንድ ኦርደር” ለማስያዝ “የግድ /መግደል/ ነበረባቸዉ ማለት ነዉ።ወታደሮቼ ከጫካ ስለመጡ ትምርት ስላነሳቸዉ የስብሰባ መበተኛ መሳሪያ ስላልነበራቸዉ የግድ “መግደል ነበረባቸዉ” ብሎ ያለንን መለስ ዜናዊ ነዉ ዛሬም ሃይሉ መንገሻ በደመቀ መልኩ በደማቅ ቅብ ቀብቶ እያቀረበልን ያለዉ።- /ሃይሉ መንገሻ ወያኔ መስርቶ “ዓዲ ሃገራይ” (ሽሬ አዉራጃ ዉስጥ) ሲፈልጥ ሲገዛ አሰቃይቶናል ያሉትን ሰዎች ልያስታዉሰን ነዉ/አንዳንዶቹ እማ የተሰወሩት ሰዎች ስም እየጠሩ አፍኖ ያጠፋቸዉ ዜጎች እና በከባድ የጭካኔ ምርመራና ዉሳኔዉ ይከስሱታል- “ይሄነን በይደር እናቆዉ”)። ይቀጥል እና ሃይሉ መንገሻ እንዲህ ይላል <“ይህ ማለት አፍኖ መዉሰድ መግደል ተደርጓል የሚባለዉ እንዲያ እንዲአደርግ አልደግፈዉም፦ነገር ግን “የዲሞክራቲክ ሂደት process ነዉ”።ይህ መንግሥት የዲሞክራቲክ ሂደት ፕሮሰስ ከጀመረ በግምት ከ15/16 ባጠቃላይ ከ12 ዓመት አይበልጥም። in fact እኔ የማየዉ በሚከተለዉ መንገድ ነዉ፡_ “ኢንስቲትዩሽኖች አሉ ወይ? ተከሳሾች በሕግ ፊት ቀርበዉ ጠበቃ ቁሞላቸዉ እንዲሞግትላቸዉ የፈቅዳል ወይ? የሄ መንግሥት accommodating /አኮመደቲንግ ነዉ ወይ? ዲፈረንስስ ወይም ያለ መረዳዳት ሲከሰት ልዩነቶች ለመፍታት በሰለማዊ መንገድ ይሞክራል ወይ? ሌላ ቀርቶ *ጠላቶቼ የሚላቸዉ ሞገደኞች/አመጸኞች የሆኑት እነ ቅንጅት ጋር ሆኖ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የሞከረ ምንግሥት ነዉ*። ተቃዋሚዎች እንደልባቸዉ እየተሳደቡ ዉጭ አገር እየሄዱ ወደ አገር ዉስጥ እየገቡ በነጻነት እየወጡ እየገቡ መዉጣት እና መግባት የሚችሉ ከሆነ “አስተያታቸዉ” መግለጽ ከቻሉ “ወደ ጤነኛ” መንገድ እየመራን ነዉ ማለት ነዉ የሚል እምነት ነዉ ያለኝ።ለኔ የዲሞክራቲክ በር መክፈቱ ቢቂ ነዉ። እነኚህ ለዉጥ የለም የሚሉን ሰዎች “ጭፍኖች” ናቸዉ። እኔ ካልገዛሁ እሾህ ይብቀልበት የሚሉ ሰዎች ናቸዉ።>>
ዉድ ወገኖቼ እንግዲህ አቶ ሃይሉ መንገሻ ያነበነበዉ የወያነ መጽሃፍ ቅዱስ አንድ ባንድ ስህተቱን ለማሳየት ብንሞክር መጽሃፍ ሊያስጽፍ ነዉ እና ካሁን በፊት ወደ መለስ ዜናዊ አጋርነት ከመጠምዘዙ በፊት መለስ ዜናዊን ይተች በነበረበት ወቅት፡ የገዛ ብዕሩ እና ካደረጋቸዉ ቃለ መጠይቅ ምን ብሎ ይነግረን እንደነበር አንዳንዶቹን ለማስረጃ እንሂድባቸዉ።
ዛሬ በ ቪኦ-ኤ ቀርቦ አቶ ሃይሉ እየነገረን ያለዉን የመለስ ዜናዊ ዲሞክራትነት መሆን የጀመረዉ ቀደም ብሎ 15 እና 16 ዓመት በጠራ መንገድ ግን የዲሞክራቲክ ፕሮሰስ ከጀመረ 12 ዓመት ሆኖታል ብሎናል። አቶ ሃይሉ መንገሻ መለስ ዜናዊን - “ንክ” ወይም የአእምሮ በሽተኛ ስለሆነ አገር ማስተዳደሩን ትቶ መጀመሪያ “የአእምሮ ሃኪም ማየት አለበት” በማለት Who is Meles Zenawi? በሚለዉ ጽሁፉ ብዙ ብዙ የነገረንን ዘንግቶ ያዉም ከነገረን 6 ዓመት ባልሞላዉ ጊዜ ዉስጥ ዛሬ እየነገረን ያለዉ ደግሞ የ “ንኩ” ሥርዓት *ዲሞክራቲክ ፕሮሰስ* እየሆነ ዲሞክራቲክ መሆን ከጀመረ “ነገሮችን በሰላም መፍታት ከጀመረ፤ተከሳሾችን በነጻ ዳኛ በነጻ ፍርድ ቤት ያለ ጣልቃ ገብነት መዳኘት ከጀመረ እና መግደል ካቆመ ተከሳሾች በፍትህ ማሰር ከጀመረ… 12 ዓመቱ ሆኖታል፤ ዉጭ አገር ምትኖሩ“ጭፍኖች” የት ነበራችሁ 12 ዓመት “ጭፍንተኞች” ሆናችሗል። እያለን ነዉ ሃይሉ መንገሻ። (ስለ ስየ መታሰር ከ12 ዓመት በፊት ሳይሆን ከ6 ዓመት በፊት ግን ስለ ፍትህ አንስቶ እራሱ ሃይሉ መንገሻ ምን እንደተናገረ ዘንግቶታተል)
አሁን እያሞገሰዉ ያለዉን መለስ ዜናዊን የአእምሮ በሽተኛ ስለሆነ አገር ከማስተዳደሩ በፊት የአእምሮ ሃኪም ማየት አለበት ብለዉ ያዘዘለትን ሕክምና አጠናቅቆ መቸ እንደተመለሰ ማን ወደ ሚሉት “ሓኪም” ሄዶ ታክሞ ድኖ መምጣቱ የምስክር ወረቀት መያዙን ባይነግረንም፤ዛሬ “ቀዊሳዉ” መለስ ዜናዊ “ሙሉ ጤንነቱ” እንደተጎናጸፈ አቶ ሃይሉ እየነገረን ነዉ። አቶ ሃይሉ “እንኳን ደስ አለህ!”
አስኪ እነ ስየ አብርሃ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሲለያዩ አቶ ሃይሉ “ኢትኦፕ” ከሚባለዉ መጽሄት ጋር ያደረገዉ ቃለ መጠይቅ በራሱ አንደበቶች እና ቃላቶች አሁን እያሞገሰዉ ላለዉ የ“ንኮች” እና “የከፋፍለህ ግዛ/አፓርታይድ ስርዓት” (የሃይሉ መንገሻ ቃል ነዉ) ምን ይለዉ እንደንደነበረ ልጥቀስ እና በትዝብት እቺ መጥፎ የዋሾች ዓለም እንለያት።ከዚህ ወደ ታች ያለዉ ቃለ መጠይቅ የተገኘዉ ከ ኢትኦጵ መጽሄት ከቅጽ 3ቁጥር 027ነሓሴ 1993 ዓ.ም/ በኢትዮጵያችን አቆጣጣር ነዉ።
ኢትኦጵ፦አሜሪካ በሚመራዉ የምዕራበዊ ምነግሥታት አሁንም አቶ መለስ በተሃድሶ ፕሮግራማቸዉ አማካይነት እንደገና ሁሉም እያስተባበረ ማንንም ገለልተኛ የማያደርግ አዲስ የሽግግር ጅማሬ ላይ እንዳሉ በመግለጽ አገሪቱን በመምራት ሃላፊነት መሸከም የሚችሉት ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸዉ የሚሉ ይመስላሉ_ እረስዎ ይህንን ይጋራሉ?
አቶ ሃይሉ መንገሻ _ይህነን አስተያየት አልጋራም።የመለስ የመምራት ብቃት አጠያያቂ ደረጃ ከደረሰ ቆይቷል።ምዕራባዊያን አገሮች መለስን የሚመርጡት በተቃዋሚነት የቆሙት የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ጠንካራ ግምባር ባለመፍጠራቸዉ ነዉ።>>
ዛሬ ደግሞ አቶ ሃይሉ እያለን አለዉ “የመለስ ዜናዊ አገርን የመምራት ብቃት አጠያያቂ አይደለም- ዲሞክራቲክ ፕሮሰሱ ከጀመረዉ 12 ዓመቱ ሆኖታል>> እናንተ ጭፍኖች ናችሁ አይታያችሁም ይለናል። ቃለ መጠይቁ ከማድረጉ በፊት ከ5 ዓመት በፊት መለስ ዲሞክራቲክ ፕሮሰስ ጀመሮት ነበር በዛሬዉ በሃይሉ መንገሻ አባባል። ያኔ “ንክ” እና “ብቃት የጎደለዉ ፤አጠያያቂ” ብሎት በነበረበት ወቅት ነዉ። ኩርር ርርር!
ይህ ዲሞክራቲክ እያለዉ ያለዉን ስርዓት ከበረሃ ጀምሮ “ዘረኛ” እንደነበረ እና አሱን በዘረኝነት/ በ አዉራጃዊነት ግፊት ምክንያት ከበረሃዉ ትግል እንዲገለል የተጫነዉን ዘረኛ ቡድን በአንድ ጀምበር ከዲሞከራሲ፤ከፍትሕ እና ከአንድነት ጋር መቸ ወዳጅነት እንደፈጠረ አልነገረንም። አንደገና ከቃለ መጠይቁ ልጥቀስ። << በ1969 አጋማሽ የታየዉ ሕምፍሽፍሽ/ትርምስ በሚባል የሚታወቀዉ በታጋይ አባሎች እና በአመራሩ የታየዉ ልዩነት መንስኤዉ አመራሩ ይፈጽም ነበረዉ “ጎጠኛ” አመለካከት “አድልዎ” የበዛበት አሰራር በመቃወም የተከሰተ ነበር>> <<ህወሓት በትጥቅ ትግል 17 ዓመት መታገሉ ሳይሆን ስሕተቱ በትረ መንግስት ከጨበጠ በሗላ የሕዝብን መብት መግፈፍ እና የኢትዮጵያን ህዝብ በከፋፍለህ ግዛ ማተራመሱ ነዉ።>> ጎጠኛዉ እና አፓርታይድ ስርዓት ያለዉን ቡድን “ሃይሉ መንገሻ አዲስ አበባ ትግራይ ደርሶ ከመጣ በሗላ “የኢያን ስሚዝ” ጎጠኛነት እና አገሪቱን በከፋፍለህ ግዛ እያተራመሳት ነዉ ያለንን ዛሬ ደግሞ “አሌ” ብሎ “አኮመዴቲንግ” ነዉ እያለን ነዉ።>>
ወገኖቼ፡ አይሰልቻችሁ ትንሽ ትግስት ስጡኝ እና ጉዳችንን አንብቡት፤- ልቀጥል፡ <<የስብሓት ነጋ የ10 ዓመታት (በ1971-1981) የህወሓት ሊቀ መንበርነት ዘመን እንኳ የመገንጠሉን ፍላጎት በትግራይ ሕዝብ እና በታጋዩ ኣእምሮ ዉስጥ ማስረጽ ስላልቻለ በኢሕአዴግ ስም ሚኒሊክ ቤተመንግስት ዉስጥ ሆኖ *አገሪቱን ማተራመስ* መርጧል>>ብሎን ነበር ሃይሉ መንገሻ ያኔ አዲስ አበባ ደርሶ ከመምጣቱ በፊት።
ጥያቄዉ፤ ስብሓት ነጋ ወዴት ሄደ እና ነዉ አገሪቱን ከመተራመስ የዳነችዉ? አቶ ሃይሉ ሲነግረን የነበረዉ እና ዛሬ እየነገረን ያለዉ ልዩነት እየገባዉ ነዉ? ነዉ ወይስ ስብሓት ነጋ እንደ መለስ ዜናዊ በሃይሉ መንገሻ የአእምሮ ጠበብትንት ታክሞ ከጎጠኝነት በሽታዉ ተፈዉሶ “የምስክር ወረቀት” ይዟል? ወይ ጉድ- ወይ አገሬ! እቺ አገር ምን ይሻላት ይሆን! ወይ አትሞት ወይ አትድን!
<<እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለዉ የህወሓት አመራር አሱ የማይመራዉ የአንድነት ትግል እንዲኖር አይፈልግም>> ሲል ሃይሉ መንገሻ የወያኔ ዲሞክራቲክ መሆን እና አኮሞዴቲንግ ባህሪ መኖሩን እቅጩን ነግሮን ነበር እኮ! ወንድሞቼ ካሁን በፊት እና ዛሬ እየነገረንን ያለዉን እያዳመጣችሁት ነዉ?ልቀጥል!_ስለ ታንድ (ትደግ)<<ታንድ ይህን በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ያለዉን ጎጠኛ ስርዓት እንደማይደግፍ ለማሳየት የቆመ ነዉ>> በሎንም ነበር። “ጎጠኛ” የሚለዉ ቃል ስንት ገዜ በሃይሉ መንገሻ እንደተደጋገመ ልብ በሉ። ጎጠኛዉ ቡድን ዛሬ ማን እሚሉት ሃኪም ዘንድ ሄዶ እንደተፈወሰ ሃይሉ መንገሻ ሊነግረን ይገባዋል።
ሃይሉ መንገሻ አያይዞም <<ቋሚ የሆነ የዲሞክራቲክ አሰራር በሌለዉ ዘር እና ጎጠኝነትን የችሎታ መመዘኛ አድርጎ በሚወስደዉ የአጎት እና የአክስት ልጅ ድርጅት ከስድሳ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሆነዉን ሰፊዉን የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዳድሮ ለረጅም ጊዜ አይቆይም ብሎ መገመት እመብዛም ነብይነትን የሚጠይቅ አይደለም።>> ይህ እንደ ሮዴሽያዉ እና እንደ ደቡብ አፍሪቃዉ አፓርታይድ ስርዓት “ዘረኝነትን እና ጎጠኝነትን የመመዘኛ ችሎታ አድርጎ- በአጎት እና በአክስት ልጅ ተተብትቦ አገር የሚመመራ ድርጅት ነዉ ብሎ የነገረንን ዛሬ አቶ ሃይሉ ምላሱን በመቆርጠም የ አጎት የ አክስት ልጆች የሚመሩት መንግሥት “አኮመዴቲነግ” ነዉ። እያለን ነዉ። ይግረም ብሎ ደግሞ አናንት መብት የላችሁም ዉጭ ሆየኖራችሁ መለስ ዜናዊ የሚያሽከረክረዉ የወያነኔን መንገሥት “አትክሰሱት፤አትዉቀሱት፤አትዝለፉት” እያለን ነዉ። የ አክስት እና የ አጎት ልጅ የወያኔ ልኡላን እና ንጉሳዉያን ቤተሰቦች ከመንግስት ስልጣን ከህዝቡ ጫንቃ ይብቃን ብለዉ ወርደዋል እና “አትንጫጩ” አታጉረምርሙ እያለን ነዉ።እየተከታተላችሁኝ ነዉ?! የሚያስፈልጋትን ያህል ከፈጨች በሗላ “በዓለማርያም ነዉ” ትላለች ይላሉ የትግራይ እናቶች እና አዛዉነቶች ሲተርኩ። አሱ ዉጭ አገር እየኖረ ሲፈልግ “ቋሚ የሆነ የዲሞክራሲ አሰራር በሌለዉ “ዘር እና ጎጠኝነት መመዘኛ” በሆነዉ የአክስትና የአጎት ልጅ ድርጅት አገር እየመራ ነዉ” “ጎጠኛ ነዉ” “አፓርታይድ ነዉ” የማለት መብት ሲኖረዉ እኛ ጋር ሲደርስ ግን “ዉጭ እየኖራችሁ ቃል መወርወር አትችሉም” ይለናል። ወይ “ትጉዱ!” ምኑ ዘመን ደረስነዉ እባካችሁ?
<<የድርጅቱ አሰራር ቁንጽል የፖለቲካ ፕሮግራም ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብን ዲሞክራሲን የማያጎናጽፍና አንድነትን የማያጠናክር መሆኑን ድምጻችነን ስናስተጋባ ቆይተናል።>> ዛሬ ደግሞ ከመቅጸበት ዲሞክራሲን አኮመዴት እያደረገ ነዉ ይለናል። ከቶ ወያኔን አክሞ ያዳነልን ሃኪም ስሙ እንደዉ ማን ይባል ይሆን? ወያኔን አክሞ የሚያድን ሃኪም እያለ እንዴት ሌሎች አገሮች በጎጠኞች አና በአምባገነኖች እያታመሱ ይዝለቁት? አረ ጎበዝ ሃኪሙን ፈልጉት እና ሌሎችም እንዲድኑ እንድንጠቁማቸዉ አቶ ሃይሉ የሃኪሙን ስም እና አድራሻ እንዲነግራቸዉ ጠ ይቁት!
<<እነዚህ አስር የህወሓት መአከላዊ ኮሚቲ አባለት በሙስና መፈረጃቸዉ ሃቅ እንደሌለዉ እና የመለስ/ስብሓት ሳይቀድሙኝ ልቅደም ፕላን ነዉ>> ይሄ ሰዉ ዘሬስ በቪ-ኦ-ኤ ምን እያለን ነዉ_? ልጥቀስ << ስየ ተከስሶ ታስሮ ነበር ጥፋት ፈጽሟል አልፈጸመም እኔ አላዉቅም። “ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የሞከረ ምንግሥት ነዉ- አኮመዴት ያደርጋል (ይህን አዉቃለሁ)።” ባንድ እራስ ሁለት ምላስ_ይሉታል ይሄ ነዉ።
<<ፖለቲካዊ ችግሮች በተወሳሰበበት የሥራ አጡ ቁጥር በየዕለቱ በሚጨምርበት ኢኮኖሚዉ ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ባሽቆለቆለበት በዚሁ በቀዉጢ ሰዓት የመለስ መንግስት አማረጭ እየጠበበ እንደሄደ የፖለቲካ ጠበብት በግልጽ ሚያዩት ነዉ።>> ዛሬ ደግሞ ኢኮኖሚ አድጓል እያለ ነግሮናል። ከሰብአዊ ነክ ጉዳኦች ሌላዉ በ ቪ ኦ ኤ ተከራከሩበት ጉዳይ የኢኮኖሚዉ ማደግ ጉዳይ ነበር። ባኮኖሚዉም በሰብአዊ ነክ ጉዳይም “ለዉጡ የማይታያቸዉ የወያኔን መትፎ ጎን ብቻ የሚያዩ ጭፍኖች”-ብሎናል። (ድሮ የባሪያ ጌቶች ባሪያቸዉን ምሳ እንዲቀምስ ሲፈቅዱለት፦ ይሄዉ ሲርብህ ምሳ እያበለሁህ ነዉ እና ነጻ እወጣለሁ ተጨቁኛለሁ አትበል_ አታማርር! የምገርፍህን ብቻ ሳይሆን ማበላህንም ምሳ ጥሩ ጎነኔንም አስተዉል!) አይነቱ ነዉ ሃይሉ የወያኔ “በጎ ጎኑንም” ጭምር አዉሱለት እያለ አጓጉለኛዉን ፍልስፍናዉን ወደ ህዝቡ የረጨዉ።
<<ይህ አንደነቱን ወዳድ የሆነ ቻይ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት ያካበተዉን አምባገነኖችን ጠባቦችን አሽቀንጥሮ የመጣል ልምዱን እንዲቀጥልበት እስገነዝባለሁ>>---ዛሬ ደግሞ “ማሽቀንጠሩን እንተወዉ እና “ዝም በሉ” “አትክሰሱት አትዉቀሱት” ይለናል። ብረት ያላነገበዉ ቅንጅትን “አመጸኛ” በማለት ሲኮንነዉ “ለዘመናት ያካበተዉን አምባገነኖችን አሽቀንጥሮ የመጣል ልምዱን እንዲቀጥልበት” እየመከረዉ የነበረዉን “ህዝቡ ያካበተዉ ልምድ “ብረት አንግቶ” አመጽ አስነስቶ እመቢተኝነት ማሳት አንጂ ሌላ ከዚህ ዉጭ ምንም ልምድ እንዳልነበር እያወቀ “አምጹ- አሽቀንጥሩት” ሲለን ከርሞ ዛሬ ዞር ብሎ ደግሞ ሃይሉ ዉጭ አገር ኖርወይ ሆላንድ አሜሪካ ስለምንኖር “አፋችሁ ክደኑ” ይለናል።
በመጨረሻ ሁለት አስገገራሚ አባባሎቹን ልጥቀስ እና ልሰናበታችሁ_
<<የመለስ መንግስት በአንድ እግሩ ብቻ መቆሙን መገንዘብ እና ካሁኑ ለመጻኢዉ መዘጋጀት ነወ!>> ሃይሉ መንገሻ ተናገረዉ ቃል ነዉ። የመለስ መንገስት ከ12 ዓመት በፊት የዲሞክራሲ እና የፍትህ ፕሮሰስ /ሂደት በር ከፍቶልናል ሲል በ ቪ ኦ ኤ የተነፈሰዉ የዛሬዉ ወያኔአዊ ፕሮፖጋንዳዉ ከ7ዓመት በፊት በ አንድ እግሩ መቆሙን ተገንዘቡ ያለንን ከ 7 ዓመት በፊት ደግሞ እንዲህ ብሎ ነግሮዋል <<አሁን ያለዉ ስርዓት ለከፋፍለህ ግዛና ከእዚያም አልፎ ወደ ጥፋት እልቂት እየመራን መሆኑን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ነዉ>> በማለት በ1993 ዓ.ም ሲነግረን ዛሬ ግድያዉ አፈሳዉ ክብደት አትስጡት ወደ ዲሞክራሲ የሚወስደን የሽግግር ምልከቱንም አትኩሩ “ያ ለእኔ በቂ ነዉ” ይለናል። እኛ ደግሞ የምንለዉ “ቁስላችን ዘወትር ለማስፋት የምትፈልጉ ወገኖች ግድያ ሲፈጸም የገበያ ንረት ጣራ ሲነካ “እያደግን ነዉ”-“ወደ ዲሞክራሲ የሚያመራን የሽግግር ጊዜ ምልክት ነዉ” እያላቸሁ ከተጠያቂነት እየሸሻችሁ በዜጎች ሕይወት እና ሰብአዊ መብቶች አታላግጡብን መለስ ነጻ አወጣችሁ አትበሉን እንላችሗለን።
እስቲ ቢገባቸሁ በዝነኛዉ በጦቢያዉ ጸሃፊ በጸጋየ ገ/መድህን አርአያ ብዕር ልሰናበተችሁ፦ “….ሩረሲያን ከሶቪየት ክንድ አዉጥተዉ ነፃ ወጣች-አሉ።ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዉያን መዳብ ዉስጥ ፈልቅቀዉ በማዉጣትና ኢትዮጵያን ዘላለም በሕይወት እና በደም ካስከበሯት ጀግኖች ልጆቿ ብብት ዉስጥ በመስረቅ መለስ ነፃ አወጣናችሁ ይሉናል።
እልቂትን ትርምስን የሰብአዊ መብት መረገጥን “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥም ምልክት ነዉ” ይሉናል። የሗሊት የማራቶን ሩጫዉን የብሔራዊ ልዕልና አጀንዳ፤ ድህነቱን የፍትሕና ርትእ ዉድቆ መሰበርን ፤የአንድነትን የፍትህ መኮስመንን እኛ ዉርደት እንለዋለን፡እነሱ ዕድገት እና ግስጋሴ ይሉታል፤ ሁላችንም በየጀሮአችን የሚጮህ ድምፅ እንሰማለን ኩርር ኩርርርር! ተዋርደናል!>> ጸጋየ ገ/መድህን አርአያ/ጦቢያ። <ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!-ጌታቸዉ ረዳ ethiopiansemay.blogspot.com>