Friday, January 11, 2019

የአብይ እና የደብረጽዮን መተሻሸት ሳየው ከኋላቸው የብዙ ሺህ ሰዎች የተቆረጡ ራስ ቅሎች እግር እግራቸው እየተከተሉ “በሕግ አምላክ እያሉ የሚጮሁባቸው ምስሎች ታይተውኛል ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)


የአብይ እና የደብረጽዮን መተሻሸት ሳየው ከላቸው የብዙ ሺህ ሰዎች የተቆረጡ ራስ ቅሎች እግር እግራቸው እየተከተሉ “በሕግ አምላክ እያሉ የሚጮሁባቸው ምስሎች ታይተውኛል
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)
ሰሞኑን ኢሳያስ እና አብይ በኡምሓጀር እና በሑመራ በኩል የኢትዮጵያ እና የሻዕቢያ ኤርትራ ድምበር መተላለፊያ መከፈቱን ሰምተናል። መከፈቱ በጎ ነው። ግን በመክፈቻው ክንውን ካየናቸው ፎቶግራፎች መካከል የፋሺስት ትግራይ ድርጅት መሪው /ክሪሚናል/ ደብረጽዮን ገ/ሚካል እና ኢትዮጵያዊው አብይ አሕመድ መካከል አጅ ለእጅ እየተባበጡ፤ትከሻ ለትከሻ እየተሻሹና ጥርስ ለጥርስ  እየተሳሳቁ የልጅዋን ሠርግ እንዳማረላት እናት ብሉልኝ ጠጡልኝ እንደምትል አይነት “የፊታቸው ገጽ በፍስሃ ተሞልቶ ብርሃን ሲያንጸባርቅ” አይተናል። ከዚያ አልፎ ከሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ ጋርም የውሸት ይሁን የእውነት ከፋሺስት መሪው ከደብረጽዮን ጋርም እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲራመዱ በጀርባቸው የተነሱት ፎቶግራፍ አይተናል። የኢሳያስ እና የደብረጽዮን መተሻሸት ጉዳየ አይደልም፤ እኔ የገረመኝ ግን የአብይ እና የደብረጽዮን መተሻሸት ማየት ሕግ የጣሰ ነው። አብይን ለምን ትቃወማለህ የምትሉኝ ልትኖሩ ትችላለችሁ፡ እኔ አልተቃወምኩትም- እኔ የምለው አሰራሩ መሰረታዊ ለውጥ እየሳተ ትዕግስት ላይ እያተኮረ ሕዝብ እያሰጨረሰ ነው! ነው ክርክሬ። እንደምትረዱኝ ተስፋ አለኝ። ምክንያቴን ላቅርብ።

በየጊዜው ከዚህ ሰው ደብረጽዮን ከሚባል እርኩስ እና ደባሪ ወያኔ የሚያደርገው እሽሩሩ ለአብይ ያለኝ ድጋፍ ሁሉ እየሟሸሸ እንዲሄድ አድርጎታል። መሳሳቃቸው፤መተሻሸታቸው “ፖለቲካ” እና ዲፕሎማሲያዊ ስልት ነው” የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለኔ “ሁለቱም ሰዎች ክሕደት የፈጸሙ እና የሕግ ንቀት ያሳዩ ናቸው”። ይሕ በሕግ ጥሰት ያየሁት ስዕል፤ እኔ ሳየው ከላቸው በነዚህ ድርጅቶች (ወያኔ እና ኦሕዴድ) ውሳኔ የተፈጸሙ የብዙ ሺህ ሰዎች የተቆረጡ ራስ ቅሎች እግር እግራቸው እየተከተሉ “በሕግ አምላክ እያሉ የሚጮሁባቸው ምስሎች ታይተውኛል”።

ደብረጽዮን በወንጀል ተፈላጊው ጌታቸው አሰፋን አላስረክብህም ብሎ አብይን እቅጩን መንገሩ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እስከማፍረስ ግልጽ ዛቻ እና ደጋግመን ለማረክናቸው የድሮ ሙርከኞቻችንን የትግሬው ጀግና ጌታቸው አሰፋን አናስረክብም ማለቱ ይታወቃል። ደብረጽዮን እና ተከታዮቹ በዚህ ሳያበቁ፤ አብይ አድሃሪ እና ጸረ ትግራይ ሕዝብ ብሎ ወርፎታል (መሰረተ ቢስ ውንጀላ ቢሆንም)። አንዳንዶቹ’ማ እንደ እነ አሉላ ሰለሞን የመሳሰሉ የታወቁ ወጣት የትግራይ የፋሺዝም ርዕዮት አቀንቃኞች “አብይ በስርቆት/ በሌብነት ነው ከቀድሞ ስራው የተባረረው” ብሎ በትግርኛ በቪዲዮ አውድዮ በይፋ (ዩትና በተባለ የኢንትርኔት ቲቪ) ወንጅሎታል (ማስረጃ ግን አላቀረበም)። ወያኔዎች እና ጭፍራዎቻቸው እንዲህ ያለ ውርደት እያከናነቡት አለቃቸው ደብረጽዮንም “ተጠርጣሪ ወንጀለኛን አላስረክብህም” ብሎ አገር አፈርሳለሁ እያለ ከሚዝት የፋሺሰት ድርጅት ተወካይ ጋር አብይ አሕመድ ተቃቅፎ ምግብ ተጋብዞ በደስታ ሲፈነድቅ የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለምን በሰላማዊ ሰልፍ አብይ አሕመድን መቃወም እንዳልፈለገ ለኔ እንቆቁልሽ ነው። ምክንያቱን የምታውቁ ካላችሁ እባካችሁ ንገሩን። ለአንድ ሰው ስንል ለምን ሰው እንዲሞት እናዛለን ብሎ አበይ አፋችን እንድንይዝ ሲሞክር ፤ጌታቸው አሰፋን እና መሰል ወንጀለኞችን ግን እንዴት ወደ ፍትሕ እንደሚያመጣቸው ግን አልነገረንም። 

በዚህ አይነት ስልት በየ ክልሉ በሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል በመቶዎቹ ሞተዋል። ለምን ተብለው ሲየቁ አንዳንዶቹ የዜና ተንታኞች መንግሥት ሲለወጥ የሚታይ አይቀሬ ነው ብለው እንደ ሕግ አጽድቀው ሊያሰምኑን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ታግሰህም ቢሆን ሚሊዮን ሕዝብ ከተፈናቀለ እና ከሞተ በሌላ መልኩ ደግሞ እንቅፋቶችን ለማስቆም ግን የሚከፈለው መስዋእት እና ኪሳራ ዕጥፍ ነው ብሎ የሚናገር የፖለቲካ ተንታኝ ሊያሳምነን የሚችል መላምት ሆነ ማስረጃ እስካሁን አልሰማንም። አሸባሪዎቹ እና ወንጀለኞች “በቃችሁ” የሚባሉት ጊዜ መቸ ነው?እያልን አፋችን ደም እስኪያወጣ ድረስ ጠይቀናል። መለስ ግን አላገኘንም።
 

 ዳወድ ኢብሳ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ፤ ደብረጽዮን ፤ ጌታቸው ረዳ ፤አርከበ ዑቑባይ፤ ፍተለወርቅ (ስንቱን እንጥራ) አዲስ አባባ አለማቸው እየቀጩ ምን እሚሉት “ለውጥ እንደሆነ አላውቅም” እውነትም “የጥገና ለውጥ”!

የሚገርመው ደግሞ፤- አንድ ተጠርጣሪ ተብሎ እስር ውስጥ የሚገኝ ቤተሰብ ላይ ሰነድ ለመሸሽ ወይንም ተጠርጣሪን ለማሸሽ ወይንም ለመደበቅ ተባባሪዎች ናችሁ ተብለው መላ ቤተሰብ የታሰሩበት ሁኔታ በዜና አንብበናል።አዲስ አበባ ወጣቶች በሺዎቹ ተለቅመው ታስረዋል፤ በሌሎች “የፋሺሰት አፓርታይድ ክልል ግዛቶችም” ውስጥም በግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ለቀማ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ “አብይ አሕመድ” ደብረጽዮን እና አጋሮቹ ጋር ሲደርስ ግን ያውም ኢትዮጵያን እየመሩ ካሉት ከ4ቱ ድርጅቶች አንዱ ተወካይ ሆኖ ፌደራል ተብየው መንግሥት ከሚመሩት አንዱ ደብረጽዮን ሆኖ እያለ፤ ፌደራል ፍርድቤት የሚፈልጋቸው ተጠርጠሪዎችን አናስረክብህም እያለ በሕግ እና በአብይ አሕመድ ላይ የሚያላግጠውን ደብረጽዮን ጋር መሞዳሞድ የሚገርም ነው። እንዲያ ከሆነ ባለብረት ያሻውን መስራት ከተፈቀደለት ሁሉም ብረት እየገዛ ወደ ፍርድ ቅረብ ሲባል በቡድን ተደራጅቶ “ፖሊሱን ዞር በል” ማለት ሊጀምር ነው ማለት ነው። እየተሰጠ ያለ ትምሕርት ያ ነው። 

 ያውም “ኢትዮጵያ ምን ታማጣለች” እያለ በትግርኛ የሚዝት ጋጠወጥ የወያኔ ጭፍራ ጋር እየተቃቀፉ እጅ ለእጅ ‘እሸሸ ገዳየ’ ሽር ጉድ ሲል ማየት ጥፋቱ ደብረጽዮን እና ተፈላጊ ጭፍሮቹ ሳይሆኑ “ከእምቢተኞች ጋር አብሮ ሽር! ፏ!” እያለ የምናየው አብይ አሕመድም ነው። በሕግ ሊጠየቅ በተጋባ ነበር (ሕግ ቢኖር ኖሮ!!) ወንጀለኞችን አናስረክብም ብሎ ከደበቀ ግለሰብ ጋር ዊስኪ መጫለጥም ሆነ መተሻሸት አይቶ እንዳላየ ማለፍ ተባባሪነት ነው።

ወያኔ በድርድር እና በዲፕሎማሲ የተጠየቀው ነገር ያስረክባል ብሎ ማለት በ"ፋንታሲ" አለም ገብቶ አጉል ቅዠት መቃዠት ነው። ለፋሺስቶች ድርድር እና ዲፕሎማሲ ይበልጥ ያስቃቸዋል/ያኩራራቸዋል/። ለዚህ ነው ትግሬዎች አብይ ላይ እያላገጡ የምንሰማቸው (ክሩ ሲጠብቅ ግን ድምጻቸው ምን አንደሚሆን ውስጣቸው ለምናውቃቸው ሰዎች እንግዳ አይደለም (የነ ጻድቃን ግበረተንሳይ ወያኔዎችን ጥንካሬ ከሚገባው መካብ የራሱ የማይጨው/ራያ/ ቢራ በማዕቀቡ ፋብሪካው እንዳይዘጋበት ስለሚሰጋ ‘የአብይን ሰዎች ለማስፈራራት’ እንጂ ወያኔ አቅም ኖሯት አይደለም። እኛ ትግሬዎች የምንለው ምሳሌ አለ፤-- ከም ቀደም ይመስለክን ውሕጅ ይወስደክን(እንደ ድሮ መስሎሽ ጎርፍ እንዳይወስድሽ!!!) ይባላል። 


እኔ የገረመኝ የሶሞኑ ሌላ ክስተት ነው።በሽሬ እና ዛላምበሳ ድምበር የሚገኝ መከላከያ ሠራዊት ከምድቡ ሲንቀሳቀስ ወዴት ጥለኸን ትሄዳለህ አትሄድም ብሎ ሕዝቡ ማስቆሙን ሰምተናል። እንዴ!!? ኢትዮጵያ ጋር እገጥማለሁ ፤ድሮ ከማረክናቸው ጋር መግጠም እናውቅበታለን የሚል የወያኔ ጭፍራ እና ጉረኛ ሁላ ዛሬ ደርሶ ለምን መከላከያውን እባክህ ጠብቀን ብሎ ለምን ሊማጸነው ፈለገ? ሻዕቢያ እንዳይመጣ ነው? ሻዕቢያን ከፈራ ከመላዋ ኢትዮጵያ ተዋጊ ጦር እና ኢኮኖሚ ማዕቀብ ሲጣል ታዲያ የትግራይ ወያኔ እንዴት ሊሆን ነው?(እንደ ድሮ መስሎሽ ጎርፍ እንዳይወስድሽ!!!) የምለውም ለዚህ ነው። ትግራዋይ አፍረቃን በመላ ሊቆጣጠር የሚችል የተፈጥሮ ልዩ ዲ ኤን ኤ” አለው እያሉ የትግራይ.ኔት ድረገጽ አጋዚያን ሲፎክሩ የሰማናቸው ያህል “ወታደሩን ትተኸን አትሂድ እባክህ ጠብቀን ብሎ መማጸኑ” አለን ከሚሉን “ዲ ኤን ኤ” ጋር አብሮ አልሄድ ብሎኛል። 

 በደርግ ጊዜ እና አሁን ሁኔታዎች ለየብቻ ናቸው። ድሮም ቢሆን “ጥቂት ቆፍጣና ገበሬዎች ወያኔን ገትረው የይዝዋት ነበር:: ያጠፋቻቻው አድፍጣ በሰላዮችዋ ማታ ሲተኙ ነበር ያጠፋቻቸው ወይንም በሰላዮችዋ በኩል በሚመገቡት መርዝ እያስገባች እንጂ አቅም አግኝታ አልነበረም። ያም ሆነ ይህ  ወያኔ ሁሌም ዕድለኛ ነው፡ መረን የለቀቀ ተለማማጭ ቡድን ሁሌም አያጡም! የሚገርም ዕድል ነው!!)።

ለነገሩ ዝም ብየ ድከም ብሎኝ እንጂ አብይ አሕመድ በወያኔዎች ላይ የሚጨክን ልብ የለውም። አብይ መቀሌ ከተማ ተገኝቶ እንዲህ ብሎ በትግርኛ የተናገረውን ላስታውሳችሁ፦

"ትግራይ ለፍትህና ለእኩልነት ሞትን ተጋፍጠው ክቡር መስዋዕትነት የከፈሉ፤ ለኢትዮጲያን ግንባታ ቤዛ የሆኑ ጀግኖች፣ እንደነስሁል (ወደ ስሁል ፎቶ እየጠቆመ)፣ ሙሴ፣ ዋልታ፣ ሀፍቶም፣ ቀለበት፣ ሀየሎም፣ ብርሀነ መስቀል፣ ቀሽ ገብሩ፣ አሞራ፣ ጥላሁን ግዛው፣ በተለይ እንደ ጓድ መለስ ዜናዊ ያሉ (ጭብጨባ)፤ በአጠቃላይ ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖችና ታጋዮች ሀገር ናት። (ጭብጨባ)"

መለስ ዜናዊ ማነው? እነ መለስ የመሳሰሉ ከጫካ ጀምረው የሰው ፍጡር በተለይ አማራ ምርኮኛ ወታደር “በሳዮናይድ በመርዝ” ሲገድሉ (የታላቁን ሴራ ቃለ መጠይቅ አንብቡ) አንጨት አቀጣጥለው ሳር ከምረው አዛውንቶችን እሳት ውስጥ ቀቅለው ሲያሰቃዩ አገር ሲያፈርሱ ወደብ ሲዘጉ ለሻዕቢያ ወግነው  የኢትዮጵያ ሠራዊትን በጥይት ሲቆሉት የነበሩትን ባንዳዎችን ለኢትዮጵያ ሲሉ ቤዛ የወደቁ ብሎ የሚያሞግሳቸው አብይ አሕመድ አሁን  እንዴት ብሎ ይጨክንባቸው? ትናንት እንደህ ስትለን አልነበረም ወይ እያሉ የፋሺስት ግልገሎች ሊጠይቁት ይችላሉ። መለስ ዜናዊን “በተለይ እንደ ጓድ መለስ ዜናዊ  ለኢትዮጵያ ሲሉ ቤዛ የወደቁ” ብሎ ማለት ?/?/፧! በስመአብ! ለመሆኑ የሃያ ሰባት አመት ጉድ ማን አመነጨው እና ነው?! መለስ ዜናዊ /ህወሓት/እንዲያ ለአገር ቤዛ ሲል የወደቀ ከነበረ ለምን መጀመሪያ ስልጣን ስትይዝ “ሽብርተኞች ነበርን ይቅርታ እንጠይቃለን” ትላለህ? ሽብር እና በሕር ወደብ ማስዘጋት እንዱት ሆኖ ነው ለአገር ቤዛ መውደቅ ሆኖ የሚታይ? እንደው ተከድኖ ይብሰል።

የአብይ አሕመድ ሕግን በማስከበር ላይ ቸልተኛነቱን በወያኔዎች በነ ደብረጽዮን ብቻ እልተወሰነም። አስመራ ከተማ የቀረቺው ዕድሜ በጡሮታ ቁጭ ብሎ ሲቆጥር በነበረው አንድ አርብ የቀረቺው ‘አንድ እግሩ ጉድጓድ ያስገባ’ የኦነጉ መሪ ክሪሚናል ዳውድ ኢብሳ ላይም የሚገርም (ቃላት የሚያሳጣ ግርምት!!) እንዝሕላልነት ሰላሳየ ብዙ ነብስ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። አብይ አሕመድ የኦነግ ትግል ተረካቢ/ አስፈጻሚ/ መሆኑንዶ/ር ብርሃነ መስቀል የተባለ እዚሁ አሜሪካ የሚኖር የአብይ አሕመድ ደጋፊ ‘የሕግ ጠበቃ’ ደ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ እንዲህ ሲል በግልጽ ነግሮናል፡”አብይ አሕመድ የኦነግ ዓላማ ተረካቢ” ሲል አሞግሶታል። እንግዲህ ኦነግ  ዓላማው እና ተግባሩ ምን እንደነበር እና አሁንም ምን አንደሆነ መግለጫ ከኔ የምትፈልጉ አይመስለኝ (ለበርካታ አመታት ሳጋልጠው ስለነበር)። እንኳን ድሮ ዘሬም በአብይ እና በለማ መገርሳ እገዛ ከሽንፈቱና ከውርደቱ ተገላግሎ በምሕረት አዲስ አበባ እንዲገባ ተፈቅዶለት ገብቶም ቢሆን ኦነግ ምን እየሰራ እንደሆነ የምታዩት ዜና ነው ማለቴ ነው። አብይ እስከዚህ ለኦሮሞ እና ለትግሬ ነፃ አውጪ የነገድ ፌደራሊስቶች ልቡ አይጨክንም።

በተጫማሪም በስፋት አብይ ምን አይነት እንዝሕላልነት እየተጫወተ እንዳለ በጥልቀት ለመረዳት እንዲረዳችሁ ይህንን የአቻም የለህ ታምሩ ጽሑፍ አንብቡ እና ፍርዳችሁን ስጡ!፤
አቻም በሚከተለው ርዕስ እንዲህ ይላል፦

«. . . ማንም ቢመጣ የሚገድለው አማራውን ነው» ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ
(Achamyeleh Tamiru)

የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ የፋሽስት ወያኔን የአፓርታይድ አገዛዝ ከተካ ወዲህ [ልክ እንደበፊቱ ሁሉ] ባለፉት ስምንት ወራት ስናያቸው የሰነበትናቸው የጭካኔ አይነትቶች ለመናገር እንኳ የሚሰቀጥጡ ናቸው። ከቡራዩው ጭፍጨፋ የተረፈች አንዲ እናት «በዚህ ዘመን ልጅ ወልዶ ማሳደግ መረገም ነው፤ ሰው ሆኖ መፈጠርም እጅግ ያስጠላል» ያለችው ባሳለፍናቸው ስምነት ወራት ያየናቸውን ጎሰኛነት የወለዳቸው የጭካኔ አይነቶች መጠን የሚገጽ ነው።

በምዕራብ ጎንደር በመከላከያ ጦር ጥይት ተመቶ ህክምና ላይ ከሚገኙ ሃጻናት አንዱ በዐቢይ አሕመድ የአገዛዝ ዘመን ከጅግጅጋው ጭፍጨፋ እስከ ቡራዩው የዘር ማጥፋት፤ ከሻሸመኔ የመንጋ ፍርደኞች ባደባባይ ዘቅዝቀው ከሰቀሉት የድሃ ልጅ በዚያው በሻሸመኔ እስከተካሄደው የአዛውንቶ የልጅ ልጆቻቸው በሚሆኑ አሳዳጊ የበደላቸው ዘረኞች የተካሄደው ዘግናኝ ድብደባ፤ በአዋሳ ከተካሄደው የወላይታና ሲዳማ ያልሆኑ ወገኖች ጭፍጨፋ እስከ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በኦነግ የሚታዱ የአማራ ገበሬ ልጆች ባለፉት ስምንት ወራት ያየናቸው ጎሰኛነት የወለዳቸው ጭካኔዎች ናቸው።

ከመስከረም ወዲህ ደግሞ በዐቢይ አሕመድ አገዛዝ መልካም ፍቃድ ከነትጥቁ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኦነግ ምዕራብ ኢትዮጵያን እያተራመሰ ይገኛል። አገዛዙ ራሱ እንደነገረን ከሰላሳ በላይ የአገዛዙ ባለሟሎች በኦነግ ሲገደሉ፣ በወለጋ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው የኦነግ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ሲሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በኦነግ ሲዘረፍ፣ ንጹሐን ዜጎች በኦነግ ሲታፈሱ፣ ዳዎድ ኢብሳ አዲስ አበባ ተቀምጦ የኦነግ ሠራዊት ከመንግሥት ጦር ጋር እንዲዋጋ ትዕዛዝ እንደሰጠ በአደባባይ ሲያውጅ እኛ «የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር» የምንለው ዐቢይ አሕመድ «ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድል» በማለት እሱ የሚመራው [የኦሮሞ መንግሥት] ኦሮሞውን ኦነግን ስርዓት ለማስያዝ [መከላከያ] ሰራዊት እንደማያሰማራ ነግሮናል።

በየዩኒቨርሲቲው ካለክልላችሁ መጣችሁ ተብለው የአማራ እንቦቀቅላዎች በኦነግ ሲታረዱ ወለጋ ሄዶ ቢገደል ኦሮሞ ይከፋፈላል ብሎ የሰጋው «ኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ» ዐቢይ አሕመድ ዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራል መንግሥት ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችን አዝዞ በዩኒቨርሲቲዎች የንጹሐን ሕይዎት በኦነግ እንዳይቀጠፍ ሲያደርግ አልታየም። ጅግጅጋ ቤተ ክርስቲያኖች ሲቃጠሉ፣ ንጹሐን ሲጨፈጨፉ፣ ሕጻናት ሲታረዱ፣ ሴት አያቶች ሲደፈሩ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ መረጃ የነበረው ዐቢይ አሕመድ የሚቆጣጠረውን የፀጥታ ኃይል ልኮ ዜጎች እንዳይታረዱ ማድረግ አልቻለም ወይንም አልፈለገም ነበር።

ፋሽስት ወያኔ አሳልፌ አልሰጠውም ያለችው የቤርሙዳው አዛዥ ጌታቸው አሰፋ መቀሌ በሰላም ተቀምጦ ሕገ መንግሥት ተብዮውን ለማስጠበቅ ቃለ መሀላ የፈጸመው ዐቢይ አሕመድ ግን በከፍተኛ ወንጀል የተከሰሰውን ጌታቸው አሰፋን ለመያዝና ለፍርድ ለማቅረብ ሰራዊት አለማዘዙ ሳያንስ ጌታቸው አሰፋን አሳልፌ አልሰጥም ካለውና ዐቢይ አሕመድ ሊያስፈጽም ቃለ መሀላ የፈጸመበት ሕግ «ለወንጀለኛ ከለላ መስጠት ወንጀል ነው» የሚለው የሕግ አግባብ ወንጀለኛ ካደረገው ከደብረ ጺዮን ጋር ትናንትና እጅ ለእጅ ተያይዞ ሽር ብትን እያለ ነበር።

የጅግጅጋው እልቂት ለማስቀረት፣ የቡራዩውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለመቆጣጠር፣ የአዋሳውን ጭፍጨፋ ለስቆም፣ የኦነግን እብሪት ለማስተንፈስ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከመታረድ ለመታደግና በከፍተኛ ወንጀል የተከሰሰውን ጌታቸው አሰፋን ለፍርድ ለማቅረብ ያልተንቀሳቀሰው በዐቢይ አሕመድ የሚታዘዘው የጦር ሰራዊት ጎንደር ፋሽስት ወያኔ ያሰማራው ሱር ኮንስትራክሽን የሚያካሂደውን ቅናንትና አማራን የማጋጨት ፕሮጀክት ለመቃወም በወጡ የአማራ ልጆች ላይ ግን መከላከያ ሰራዊቱን አዝዞ እንቦቀቅላዎችን አስጨፍጭፏል።

የጎባጣ አሽከር አጎምብሶ ይሄዳል ለምን ቢሉት ጌታየን ለመምሰል አለ እንደሚባለው አዲሱን ጌታውን ኦዴፓን ለመምሰል ስም የለወጠው ብአዴን የሚባለው ነውረኛ ድርጅትም የአማራ ጉዳይ ባለጉዳይ ስላልሆነ የትናንትናው የመከላከያ ሰራዊት ጭፍጨፋ ሊያሳስባቸው አይችልም። ባለጉዳይ ቢሆኑ ኖሮ እስካሁን «ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ሳይሆንና ለፌዴራል መንግሥቱ ጥያቄ ሳናቀርብ መከላከያ ገብቶ ጭፍጨፋ አካሂዷል» የሚል ወገንተኝነትና ኤታማጆር ሹሙ ወርዶ እዙን ለግድያ ያሰማሩት ወንጀለኞችና ገዳዮች ለፍርጅ ይቅረቡ ሲሉ እንደማ ነበር።

እንግዲህ! ይህ ሁሉ አርበኛው ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ያሉንን ነው የሚያስታውሰን! አርበኛው ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ከዛሬ ስድሳ አመታት በፊት «… ማንም ቢመጣ የሚገድለውና ጠላት የሚያደርገው አማራውን ነው» ብለው ነበር። ፋሽስት ወያኔ ቢመጣ በድሚያ ሰራዊት አሰማርቶ የገደለው አማራውን ነው። ኦነግ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተመሰረተው ያልታጠቁ ንጹሐን አማሮችን ለመግደል ነው። ይኼው ዛሬ ደግሞ ዐቢይም ቢመጣ «ኦሮሞን ኦሮሞ አይገድለውም» በማለት እስካንፍንጫት የታጠቀውው ኦነግ በሚያሸብርበት ምዕራብ ኢትዮጵያ ጦር ያልላከውን ወደ ጎንደር ግን ሰራዊቱን በብርሃን ፍጥነት በማሰማራት የሚገድለው አማራውን ነው። ስለሆነም ዛሬም ቢሆን አማራው ከሌላው በተለየ መልኩ ሰራዊት እያሰማራ የሚገድለው ጨካኝ አራጅ እንጂ የሚያስተዳድረው መንግሥት የለውም!” ሲል አቻም በጥልቀት የአብይ እንዝሕላልነት ተንትኖታል።
 (አትዮ ሰማይ)