Wednesday, October 2, 2024

ጦርነቱ አማራ ክልል ብቻ ከመሰለን ተሳስተናል! ይነጋል በላቸው Ethiopian Semay 10/2/24

 

ጦርነቱ አማራ ክልል ብቻ ከመሰለን ተሳስተናል!

ይነጋል በላቸው

Ethiopian Semay 10/2/24

      የኦሮሙማ መንጋ ኢትዮጵያን በአጠቃላይ፣ አማራን ደግሞ በተለይ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የአራት ኪሎን ቤተ መንግሥት ከተቆጣጠረ ስድስተኛውን ዓመት አጠናቆ የሰባተኛው እኩሌታ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ የጥፋት ጉዞው ብዙ ነገር ተምረናል፡፡ ዋናውና ትልቁ ትምህርት - ለማልማት ከሚወስደው ጊዜ ለማጥፋት ወይም ለማውደም የሚወስደው ጊዜ እጅግ አጭር መሆኑን ነው፡፡ በስድስት ዓመታት ተኩል አማራና ኢትዮጵያ ከየት ወዴት እንደተሻገሩ ተመልክተናል - ዕድሜ ለወፈፌው ጭቅላ አሻግሬ፡፡ (ይህ ልጅ የበቃኝ እኮ ምርኮኛ አሥር አለቃን ፊልድ ማርሻል ሲል ነው - ሊያውም ከመቀሌ ሸኖ ድረስ ስለሮጠ፡፡)

      “ለሰው ጉድጓድ አትቆፍር - ከቆፈርክም አታርቀው፤ ቀድሞ የሚገባበትን አታውቀውምና” የሚለውን ነባር ብሂል መረዳት የተሣናቸው የአእምሮ ድኩማኑ ሕወሓቶች በአባታቸው በአቶ ስብሃት ነጋ በኩል ለኢትዮጵያ ቃል የገቡላትን ቃል- እጠቅሳለሁ - “እኛ ኢትዮጵያን መግዛት ካልቻልን ሥልጣኑን ለኦሮሞ አስረክበን ወደ ትግራይ እንገባለን” እውን መሆን ማረጋገጥ ከጀመርን ዓመታትን አስቆጠርን፡፡ ግን እነሱም የዘሩትን አጨዱና ብዙ የጮህንበት የሰላምና የፍቅር አማራጭ ገደል ገብቶ ሀገራችን ለማንም ሳትሆን በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ልትገኝ ቻለች፡፡ በጥላቻና በበቀል ተኮትኩቶ ያደገው የትግራይ ወያኔና የኦሮሞ ኦነግ/ኦህዲድ ተራ በተራ ኢትዮጵያን አነደዷት፡፡ በነዚህ የጅል ብልጦች ምክንያት ሁሉም ነገር ያላት ሀገራችን ሁሉንም እንድታጣና ዜጎቿ ተንከራታች እንዲሆኑ ተፈረደባት፡፡ የዘረኝነትና የጎጠኝነት፣ የድንቁርናና የድህነት፣ የሙስናና የንቅዘት፣ የስደትና የጦርነት፣ የክፋትና የምቀኝነት፣ የአጋንንታዊ ሥርዓተ መንግሥትና የሊቀ ሣጥናኤል ንግሥና ምሣሌና የልጅ ማስፈራሪያ ጭራቅ ሆና አረፈችው፡፡

      ትግራይ ልታንሰራራ በሚያዳግታት የውድቀት ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ ነገሩ “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ቢሆንም ያሣዝናል፡፡ አሁንም ድረስ ዘረኞች ልጆቿ ወጉ አይቅርብን ብለው በልማት ሥራ ከመጠመድ ይልቅ ልክ እንደዱሮው ለወራት በሚዘልቁ ስብሰባዎች ተጠምደው አሉ፡፡ አለመለከፍ ነው፡፡ ሠላሣ ክልል ተፈጥሮ፣ ሠላሣ ምክር ቤት ተዋቅሮ፣ ሠላሣ ቦታ ልዩ ኃይልና የክልል ፖሊስ ተመድቦ … ለዕድገትና ለልማት መዋል የነበረበት ወጣት ኃይልና ውሱን ሀብት እርስ በርስ ለመዋጋት ሲውል እንደማየት መፈጠርን የሚያስጠላ ነገር የለም፡፡ ዐርባና ሃምሣ ሚሊዮን ሕዝብ ይልሰውንና ይቀምሰውን አጥቶ በጠኔ እየተንጠራወዘ የሀገር ሀብት ተሟጦ በትሪሊዮን ለሚገመት ቅንጡ ቤተ መንግሥትና ለገዛ ወገን መግደያ ጦርነት ሲውል እንደማየት ሰው መሆንን የሚያስጠላ ክስተት የለም፡፡

      ብዙ የአዲስ አበባ ሰው አማራው ላይ ብቻ ይመስለዋል ጦርነት የታወጀው፡፡ የአቢይ ሰይጣናዊ የኢሉሚናቲ መንግሥት አማራን ብቻ ለማጥፋት አይደለም ጦርነቱን በአማራ ክልል እያካሄደ የሚገኘው፡፡ አማራን ለመጨረስ በወለጋም፣ በኢሉባቦርም፣ በሐረርም፣ በአዋሣና ሻሸመኔም ካካሄደው የዘር ማጽዳት ዘመቻ ቀጥሎ አማራ ክልል በሚባለው ሥፍራ ባለፈው ዓመት በግልጽ ጄኖሣይድ ማወጁ በይፋ የሚታወቅ ሆኖ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ በተለይ የሚያራምደው ዘር ተኮር የቤት ፈረሳና ዜጎችን ሜዳ የማስቀረት ኦሮሙማዊ ዕኩይ ተግባር ብዙው ዜጋ የተረዳው አይመስልም፡፡

      በመሠረቱ ጦርነት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ዜጎችን ከነባር ይዞታቸው ማፈናቀልና በዚያም ሰበብ ራሣቸውን እንዲያጠፉና ጨርቃቸውን ጥለው እንዲያብዱ ማድረግ ትልቅ የጦርነት ሥልት ነው፡፡ በዚህ ኦሮሙማዊ የዘር ማጽዳት “ጥበብ”እጅግ ብዙ አማሮች ከአዲስ አበባና አካባቢዋ እየተወገዱ ነው፡፡ በኮሪደር ልማት ሰበብ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ አማሮች ከአዲስ አበባ እምብርት ተባርረዋል፤ መግቢያም አጥተው አብደዋል ወይም በገመድና በመሳሰሉ ራስን የማጥፊያ ዘዴዎች ወደዚያኛው ዓለም ሄደዋል - ሁለት ኪሣራ፡፡ አዲስ አበባ ቤት አለኝ ማለት የሚችል በግልጽ ቋንቋ  ለመናገር ኦሮሞ የሆነና ኦሮሞነቱንም ማስመስከር የሚችል ነው፡፡ ማንኛውም አማራ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ብቻ ሣይሆን አዲስ አበባ ውስጥ ለመኖርም የኦሮሙማ ቡራኬና ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ደግነቱ ያኛው እንዳለፈ ሁሉ ይህም በቅርቡ ያልፋል፡፡ ችግሩ ነገን ከትናንት የማያገናዝቡ ደናቁርት አራት ኪሎን መቆጣጠራቸው ነው፡፡

      ሌላውና ትልቁ ጦርነት የኑሮውድነቱን በብርሃን ፍጥነት እንደኳስ ሽቅብ ማጓን ነው፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት በኪሎ አምስት ብር የገዛኸው ቀይ ሽንኩርት አሁን 170 ብር ብትባል ለውጥ የሚባል በማያውቃት የሀበሻ መጽናኛ “ይብስ አታምጣ” ብለህ ከመግዛት በቀር ሌላ ምርጫ የለህም፡፡ ጤፍ አይነሣ፡፡ ሥጋም አይታሰብ፡፡ አትክልት በሆድ ይፍጀው ይቅር፡፡ ንዑስ ከበርቴ ይባል የነበረው የመንግሥት ሠራተኛ ዛሬ በቀን አንዲት ዳቦ በሻይ እልፍ ሲልም አንዲት የመንገድ ዳር ሽሮ ካገኘ ብዙ ሰው የሚቀናበት ባለፀጋ ነው፡፡ እንደኢትዮጵያዊ ግፈኛ መንግሥትንና አምባገነን መሪን የሚሸከም በሌላ ሀገር ካለ አግራሞቴ መለኪያ አይኖረውም፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የጦርነቱ አካል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

      የመንግሥት የአገልግሎትና የቀረጥ/የግብር ክፍያዎች ሰማየ ሰማያትን አልፈዋል፡፡ በአንድ ምሰሶ በዘጠና ብር የገባልህና በወር ብር 15 ትከፍልበት የነበረው የመብራት ዋጋ በየደረጃው ከአለቃ እስከምንዝር ሠራተኛ የምትወታትፈው መቁሽሽ ሳይጨመር ዛሬ በስምንት ሽህ ብር ገደማ አስገብተህ በወር ለአነስተኛ የአንድ ቤተሰብ ፍጆታ ሰባት ሽህ ብር ድረስ ልትጠየቅ ትችላለህ፡፡ እንደምንሰማው ለመንጃ ፈቃድ ዕድሣት፣ ለቴሌ፣ ለንግድ ባንክ፣ ለሰነዶች ማረጋገጫ፣ ለመታወቂያ ማደሻና ማውጫ … ምን አለፋህ ለማንኛውም አገልግሎትና አቅርቦት የሚጠበቅብህ ክፍያ እጅግ ንሯል፡፡ ነገሩ ሁሉ “የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዲሉ ነው፡፡ ይህ ነገር ሆን ተብሎም ይመስላል፡፡ “ምን ያመጣሉ? ”ከሚል ዕብሪትና የሀገርና ሕዝብ ጥላቻቸውን ለመወጣት፡፡ አማራንና የኢትዮጵያን የቀድሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንዴት እንደሚጠሉ ደግሞ አትጠይቁኝ፡፡ እነዚህን በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ሲያዩ ሊያስታውካቸው ይደርሳል፤ ሊያስታውኩም ይችላሉ አላውቅም፡፡ እንዴትና በማንስ ቢረገሙ ይሆን?

      ይህ ፈርጀ ብዙ ጦርነት በቅርብ እንደሚጠናቀቅ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳች መንፈሣዊ ኃይል ሹክ ይለኛል፡፡ እነዚህ ደደቦችና የአጋንንቱ ዓለም አጋፋሪዎች የሚሠሩት ሁሉ ሲታይ ውኃ ውስጥ እየሰመጠ ያለ ሰው የሚያድነው መስሎት ውኃው ላይ የሚንሳፈፍን ገለባ ወይም አረፋ እንደሚጨብጥ ዓይነት ነው፡፡ ሥራቸው ሁሉ የመቃብራቸውን መቃረብ የሚጠቁም ከመሆኑም ባሻገር ብዙዎቹ የጅል ተግባሮቻቸው የሚያሳዩን ሥርዓተ ቀብራቸው ራሱቅጥ ያለውና የማይታዘንላቸው መሆኑን ነው፡፡

      በመጨረሻም ለነጌትነት አዳነና ለመንገሻ ማንትስ የሚባሉ የብአዴን ኮንዶማውያን የትሮይ ፈረሶች  የምለው አለኝ፡፡ ብአዴናውያን የብልግና “ባለሥልጣናት” በጣም እየመሸባቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም በሚባል ደረጃ ልክ እንደ ጌቶቻቸው ማይማን ደናቁርት ናቸው - አማራን የሚያሰድቡ ጋብቻ ከልክል ማፈሪያዎች፡፡ በአማራ ስም ኦሮምያ የምትባል የህልምና የቅዠት ሀገር በምሥራቅ አፍሪቃ ሊያውጅ የተቃረበውንብልጽግና የተባለ ቡድን በመደገፍ የአማራን ዕልቂት የምታራምዱ ብአዴኖችና ሆዳም ባንዳዎች በቶሎ ወደየኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ የፋኖን ትግል ባታግዙ እንኳን እጃችሁንና አንደበታችሁን በመሰብሰብ ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን አድኑ፡፡ የእስካሁኑ ጥፋታችሁ ይበቃል፡፡ በኦሮሙማ እንደቆረባችሁ የመቀጠል መብታችሁ ግን የተጠበቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትንሣኤ በዳንዴል ክብረት ብዔልዘቡላዊ ትዕቢትና በአቢይ አህመድ የ666 ፊታውራሪነት የሚቀለበስ አይደለም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም የዘረኝነትንና የጎጠኝነትን ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የሚከረፋ ጎራ ተፀይፈው ከአማራ የነፃነት ትግል ጎን የተሰለፉ ትግሬዎችና ኦሮሞዎች፣ የውጪውና የሀገር ውስጡ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ የወለዳቸውን ሸሮችና የተንኮል ሤራዎችተረድተው እየተደረገ ያለውን የነጻነት ትግል ከአማራዎችም በበለጠ ሲደግፉ እያየን አማራ ሆናችሁ የአማራን ዕልቂት ማስተባበራችሁ ለእናንተም ብቻ ሣይሆን ለቀጣይ ሰባት ትውልዳችሁ የምታተርፉት የሀፍረት ማቅና ሸማ ከሞታችሁና አሟሟታችሁም በላይ የከፋ መሆኑን ልትገገነዘቡ ይገባል፡፡ የታወረው ዐይነ ኅሊናችሁ ይብራ፤ የተደፈነው ዕዝነ ልቦናችሁም ይከፈት፡፡ በየ30 ደቂቃ ለሚሸና መጠጥና በየ4 ሰዓት ዕዳሪ ለሚሆን እህል ብላችሁ ታሪክ ይቅር የማይለውን ስህተት ከመሥራት ተቆጠቡ፡፡ በእናንተ ምክንያት ነፃነት ልትዘገይ ትችል ይሆናል እንጂ አትቀርም፡፡ እሳት እየመጣባችሁ ነው፡፡ እናንተ ግን በትዕቢት ስለተወጠራችሁ እሳቱ ሊታያችሁ አይችልም፡፡ …