እውነቱን ለማወቅ ስቃይ እንድትናገር ፍቀዱላት
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian seamy)
ከላይ ተጠቀምኩት ርዕስ የተናገረው ጥቁር አሜሪካዊ ፈላስፋው
ከረነል ዌስት ነው። “you must let suffering speak if you want to hear the truth”
(Professor Cornel West)። እየተናገርኩ ያለሁት ለናንተ ነው (ለኢትዮጵያውያን አፍቃሬ ሻዕቢያ)። አገራችን ከወያኔ
ስርዓት ወደ አልታወቀ አቅጣጫ እየተጓዘች እንደሆነች እያየን ነው። አብይ አሕመድ እኔም እንደ እናንተው ሚሊዮኖች አድናቂው ነኝ።
የምለይበትም የምደግፈውም ጎን አለኝ። ሰሞኑን ያለሉጓም በፍቅር ስሜት እያስጋለባችሁ እና እየስጨፈራችሁ ያለው ወደ ሻዕቢያነት የተለወጣችሁ
ኢትዮጵያውያን አሽቃባጮች እናንተ እና ሻዕቢያ “ኢሱ” የምትሉት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ግን ‘መጽነታይ (ጨፍጫፊ) ብለው የሚጠሩት ኢሳያስ አፈወርቂ
ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ “ሁለት አገር አንድ ሕዝብ” መሆናችንን ሲገልጽላችሁ የስሜቱ ፈንጠዚያ ‘ሱሪያችሁን ባንገታችሁ ለማውጣት’ የቀራችሁ
ነገር የለም።
መፈንጨት ጥሩ ነው። በስሜት ለጦዘ ማሕበረሰብ አይታወቀውም
እንጂ አስገራሚ ያደረገው ግን የኤርትራ ባንዴራ ሳይሆን (የተባበሩት መንግስታት የሰጣቸው ጊዜያው ባንዴራቸው ሳይሆን) የሻዕቢያ
ባንዴራ ማውለብለባቸሁ አልበቃ ብሎአችሁ ሙታንታችሁን አላየነውም እንጂ
፤ ሎምቦጫችሁ እና ከንፈራችሁ በሻዕቢያ ባንዴራ ቀለም አቅልማችሁ
እንደ ገጣባ አህያ በደስታ እንጣጥ ስትሉ ማየት ከማዘኔ በላይ አስቃችሁኛል። እጅግ ያሳዘነኝ ግን በቴ/ቪዥን ሲተላለፍ ያየሁት ደረታቸው
በኢትዮጵያ መዳሊያ እና በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ያሸበረቀ አንድ አዛውንት አርበኛ አባት ባጌጡበት አርበኛዊ ሽልማታቸው ላይ አንድ
ወጣት የሻዕቢያን ባንዴራ ሊሰካላቸው ሲውረገረግ አይቼው ከሰቀጠጠኝ ትዕይንት አንዱ እና ቀዳሚዊ ይህ አሳዘኝ ክስተት ነበር።
እንዲህ ያለ ቅብጠት ካሁን በፉት ትግሬዎች ከሻዕቢያ ጋር ሲቀብጡ አይተናቸዋል።
ትግሬዎች “አማራ” ብለው የሚጠሩት ‘ደርግን’ (አብርሃ ደስታ አንዳረጋገጠው እና ብዙ ሰነዶች እንደሚያረጋግጡት) አሸንፈው ኢትዮጵያን
አምበረከክናት ብለው ከሻዕቢያ ጋር ሆነው የሚረግጧት ዓለም አልበቃ
ብላቻቸው በየአሕጉራቱ እየዞሮ ፈረንጅ አገር ውስጥ ‘ከበሮ’ እየደለቁ ፤ ትግሬዎች የኤርትራን እናቶች ልዩ ማሕፀንነት እያወደሱ
“ኤርትራን በቅኝ ግዛት የገዙ አማራዎች የወለደች የአማራ እናቶች ማሕጸን እያንኳስሱ” ሲፈነጥዙ ሰምተናቸው ‘ያልተገረዘው’ የጫካ
ምላሳቸው የኋላ ኋላ እራሳቸው በገዛ ጥርሳቸው እንደሚቆረጥሟት በተናገርን ልክ
7ኛው የጥጋብ አመታቸው ሲጨርሱ ዓለም አይቶት የማያውቀው አሰቃቂ
ጦርነት ከፍተው እርስ በርስ ተላልቀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ
የዕልቂታቸው ሰለባ አደረጉት።
ያ እንዲያ አልፎ ዛሬ ደግሞ እናንተም የትግሬዎቹ ቦታ ተክታችሁ እንደ እግር
ኳስ ‘ቲፎዞ” ሎምቦጫችሁ በሻዕቢያ የባንዴራ ቀለም ማቅለማችሁ ያስደምማል። ያስ ባልከፋ ነበር፡ ዋናው ጥያቄየ አብይ አሕመድ “ከኢሱ” ይዞላችሁ የሚመጣው “ፓኬጅ” ምን ይሆን?
የሚል ነው ለኔ ያጓጓኝ ጥያቄ። መልስ ከናንተ እፈልጋለሁ።
ምክንያቴንም ልግለጽ። እኔ የምፈልገው ፍላጎቴ ባለፈው ሰሞን
በግልጽ አብራርቻለሁ። የወደብ ጉዳይ በፍቅር በመደመር የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። እየተነጋገርን ያለነው ከሳሪ እና አትራፊ እየተደራደሩት ያለው ሉአላዊ ድርድር
ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ በግልጽ እስካልነገሩን ድረስ እንዲሁ በፍቅር ስካር የምናልፈው አይደለም። እኔ እና መሰሎቼ የምንፈልገው
አሳውቀናችኋል: እናንተ የምትፍልጉት ግን
አታውቁትም (አልነገራችሀንም)። የተማራችሁት እና የምታውቁት እና የምትፈልጉት ነገር “ፍቅር እና መደመር” የሚሉ ቃላቶች ተምራችኋል።
ያ አውቀነዋል። እነዚህ ነገሮች ለኢሳያስ አዲስ ክስተቶች አይደሉም።
አሁን አብይ እና ኢሳያስ እንደሚናገሩት፤ መለስ እና ኢሳያስ
ይህንን ሲናገሩ ሰምተናቸዋል።በአማርኛ መመዝገቡ ትዝ አይለኝም እንጂ በትግርኛው “አሰር” ጋዜጣ የተመዘገበ ነው (ኢሳያስ የተናገረበት ቃለ መጠይቅ፤ ቅጁ ከኔው ጋር አለ)። የዱሮው
እና የአሁን የግንኙነት ልዩነቱ፤ የዱሮዎቹ ትግሬ ለትግሬ
ስለነበር ወደ መሃል አገር ወደ አዋሳ ወደ ….ወደ…. ከተሞች እየተዘዋወሩ ሕዝብን
አላስጨፈሩም እንጂ ይህንኑ “የድምበር ትርጉም ወደ ሌለው ደራጃ
ደርሰናል” የሚለው የኢሳያስ እና የአብይ ንግግር ድሮም መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ ደጋግመው ብለውታል። አሁን ያለው ልዩነት ግንኙነቱ ትግሬ ያልሆነ ነገር ግን ትግርኛ መናገር የሚችል “ካሪዝማቲክ’ (ማራኪ) የሆነ የፍቅር
ሰው አብይ አሕመድ የተባለ ኢትዮጵያዊ ‘አማርኛ መናገር አላውቅም’ እያለ እንደ ፈረንጅ ባስተረጓሚ ሲነጋር የነበረውን ኢሳያስን
በአማርኛ እንዲናገር በታአምር እንድናደምጠው ካደረገ አስደናቂ መሪ ከሆነው ከአብይ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን በስፋት መጎብኘቱ ነው ልዩነቱ።
በሕይወቱ አድርጎት የማያውቀውን “አማርኛ” ለኢትዮጵያ ሕዝብ
መናገሩ እጅግ ከሚያስገርሙት እና ለየት ካደረጉት ይህ ክስተት እንጂ ሌላው “የመደመር እና ሁለት አገር አንድ ሕዝብ” የሚሉት ንግግር
ካሁን በፊት የተነገረ ነው። ከላይ እንደገለጽኩት እንዲያ ከተነገረ እና ከተጨፈረ በኋላ ግን የተከሰተው
ጦርነት ለናንተ የሚነገር አይደለም። አሁን
ከናንተው የምጠብቀው እየተጨፈረበት ያለው ፈንጠዚያ በምትኩ ምን እናገኝ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ስጠይቅ ብዙ ሰዎች በተለይ አሽቃባጨቹ
አብይን እንደምጠላ አድርገው የሚያዩ ሊኖሩ ስለሚችሉ- ከዚህ ልጠፋችሁ ታቀቡ እና የምጠይቀውን ጥያቄ ብቻ መልስ እንደትሰጡኝ እጓጓለሁ።
ከላይ በመግቢያየ እንደገለጽኩት በዚህ ሰውየ ምክንያት ብዙ
ሰዎች ስቃይ ተሸክመው ዛሬም አጭቀውት ይኖራሉ። ኢሳያስን መውቀስ በተቃዋሚ ጭምር የሚያስሰድብ፤ የሚያስደበድብ፤የሚያስሸማቅቅ ኖሮ
ቆይቷል (ግንቦት 7 በተደባዳቢ ግብረሃይሎቹ እና በኢካዴፍ
ፓልተኮቹ በኩል ዋናው ተጠቃሽ ነው)። እንደ እሚታወቀው የተቃዋሚ ሞዲያዎች እና የፓልቶክ መገናኛ
ዘዴዎች በግንቦት 7 እና በኦነግ ደጋፊዎች ስለተመረዘ ሻዕቢያ አባሎች እኛን
ኢትዮጵያውያንን እንዲዘልፉ ሙሉ ነፃነት ተሰጥቶአቸው እንደነበር እና ዛሬም በባሰ መልኩ ኢሳያስን መንካት “ለወረበሎች
ስድብ” ያጋልጣል።
ስለዚህ ኢሳያስን በዓለም ፍርድ ቤቶች ከስሰው ማስቀጣት ባይችሉም
በሰራው ወንጀል የሚጮሁ ስላሉ ቢያንስ የኢሱአችሁ ባንዴራ
በጉንጫችሁ መሸከም መብታችን ነው ብላችህ አንደነገራችሁን እኛም አክብረንላችኋል: ነገር ግን በኢሳያስ ጭካኔ የተጎዱ ወገኖቻችን ስቃያቸው
እንዲጮሁበት መብታቸውን አትጋፉ። ስለዚህ በሁለቱ አገሮች እየተደረገ ያለው ግንኙነትም ሆነ ተበድለናል ብለው ስለ ኢሳያስ ግፍ የሚናገሩ
ሰዎች ስቃያቸው እንዲጮህ መፍቀድ አለባችሁ። ምክንያቱም እውነቱን ለማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ ስቃይ እንድትጮኽ መፍቀድ አለባችሁ።
ኢሳያስ ጭራሽኑ ከሰይጣን ወደ መልኣክነት የለወጠው “የፍቅር
መደመር” መዘዙ በናንተ ኢትዮጵያውያን ሳይሆን በሲኦል ላይ ያለው ብዙ ኤርትራዊ ጭራሽኑ ኢሳያስን መውቀስንም ሆነ መነከካት ፍጹም
በባሰ መልኩ የሚያስኮንን ሆኖ መምጣቱ
ሌላው የፍትሕ አስፈሪ ጥሰት እየሆነ በትግርኛ ተናጋሪ ሻዕቢያ አሽከሮች እያስደመጡን ያለው አስገራሚ አዲስ የተከሰተ ክስተት ነው። የሻዕቢያው መሪ ኢትዮጵያ ውስጥ
ከነ ባንዴራው ሕዝብን ሲያስጨፍር ማየት አዲስ
ክስተት ቢሆንም ለኛ ይዞልን የሚመጣ ውል ምን እንደሚሆን ባናውቅም፤ ፍትሕ ለሚፈልጉ
ኤርትራኖች ግን በከፋ መልኩ በሩ ሁሉ ዝግ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሳያስ ከዲብሎሳዊነት ወጥቶ
እንደ መልአካዊ መሪ ሆኖ በዓለም መስኮቶች እንዲታይ ማድረጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠያቂ ነው።ይህ ስራ ደግሞ አሜሪካኖች ጂቡቲ ባለው የአለም አቀፍ ሃያላን
ሃይሎች የይዞታ መቀራመት ስላልተደሰቱ የቀይ ባሕር ኤርትራ ወደቦችን እና ቀጠናዎችን ብቸኛ ተቆጣጣሪ እንዲሆኑ ያቀናጁት አማራጭ
ዕቀድ ስለሆነ በአብይ በኩል ኢሳያስ ጨዋታው ውስጥ እንዲገባ መደረጉ የታወቀ ነው። በዚህ ስካር ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈንድሻ
እና ቀጤማ ነስናሽ ሆኖ እንዲቀርብ የተደረገ አስደናቂ ስልት ነው።
እዚህ
ላይ ለመጥቀስ የምፈልገው፤ አብይ የሻዕቢያ ተከታዮችን ሲያስደስት የሻዕቢያ ተቃዋሚዎችን
ግን አላነጋገረም፤ ምን እንዳሰበም የሚታወቅ ነገር የለም። የፍቅር መሪያችን አብይ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ከኢሳያስ ጋር ሊያስታርቃቸው
ይሆን ወይስ የራሳቸው ጉዳይ ሊላቸው ነው? አብይ እዚህ ላይ ከፍተኛ
ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲ ስራ መስራት አለበት። የኤርትራ ተቃዋሚዎች ተገቢ የዲፐሎማሲ ውይይት ካላደረገላቸው ያላቸው ዕጣ ፈንታ ከህወሓት
አክራሪ ክንፎች ጋር ተዳብለው/ተደምረው/ ትግራይ ውስጥ በመመሸግ በሁለቱ ሕዝብ እየተደረገ ያለው አዲስ የግንኙነት ክስተት እንዲሰናከል
ያደርጋሉ።አክራሪው የወያኔዎች ክንፍ ይህንን አጥብቆ ለትግራይ ትግርኛ ቅዠቱ እና አብይን ለማሰናከል ሊጠቀምበት ይችላል።
ወያኔዎችም ይህንን ምከንያት ስሚፈልጉ ከፍተኛ ትኩረት መደረግ
አለበት። ሆኖም ያ ከመሆኑ በፊት ከሁሉ በፊት የአብይ ግስጋሴ ‘የወያኔ ወንጀለኞች” ሊቆጣጠራቸው እና ወደ ፍትሕ ሊያደርስ የሚችልበት
ዘዴ ወይንም ስልት አለው ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ካላችሁ መልስ ስጡኝ። አብይ ደጋግሜ እንደገለጽኩት ህልውናው ለአደጋ ሳይጋለጥ
በጠና እንዲኖር እፈልጋለሁ። ከጭለማ አውጥቶ ኢትዮጵያዊንትን
ከፍ ያደረገ መሪ ስለሆነ ከነዚህ ከተሸነፉት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች (ሰማያዊ የሚባል ሐፍረተ ቢስ ድርጅት እንኳ ድሮ ለድሮ ከአፍቃሬ
ሻዕቢያ እና ኦነግ ጋር ከሆነው ኦከግንቦት 7 ጋር ጥምረት ፈጥሬአለሁ ብሎ “ኦነግ አሸባሪ አይደለም” ሲል አይገርማችሁም? ስንቱን
የአማራ ሕብረተሰብ የፈጀው ድርጅት ኦነግን?!) እነዚህ ከሚመሩን አብይ ቢመራኝ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ። ሆኖም አብይ ወዴት እየወሰደን
ነው የሚለው ደግሞ ጣቴንም ቀስ በል እያልኩት ነው
እና እናነትስ ምን ትላላችሁ?
እዚህ ላይ አብይ እየተከተለ ያለው የፖፕሊስት (ሕዝብ መስማት የሚፈልገውን
እየነካካ ማስጨፈር..) ፖሊሲ መውቀስ ብፈልግም አሁን አብይ ያለበት ሁኔታ ስመለከት ደግሞ የተሸከመው ጫና እጅግ ከባድ እና ከፖፕሊሰትነት
ውጭ ባሁኑ ጊዜ እኛም ሆነ እሱ ሊሰራቸውና ሊተገበሩ የሚፈልጋቸው
እና የምንፈልጋቸው ‘መሰረታዊ’ የሆኑ ለውጦች ማድረግ እንደማይችል ስለማወቅ “ፖፕሊሰትነቱን’ አቁሞ መሰረታዊ “ቢፍ” የሚሉት እኛ
““ሻኛ” (ብሩንዶ) የምንለው ለልብ እና ለዐይን የሚያጠግብ ነገር አሁን
ስራ ብንለው ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ድቅን ይልብኛል። በወንጀል የተጨማለቁ
የሰው ደም በእጃቸው ላይ እየጮኸ ያለው ለ27 አመት አገር ሲያምሱ የነበሩት ባለስልጣናት አብይን ከብበው አማካሪዎች እና አጀንዳ
ሰሪዎች ሆኖው እያየናቸው ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ዶ/ር አብይ አሕመድ
የሚያዋጣው የፖለቲካ እና ከብበውት ካሉት የቀን ጅቦች ቀለበት በጥሶ ለመውጣት አማራጩ “ሽሩድነት” (ብልጥነት) ወይስ “መደመር
መጦዝ እና መፋቀር”? የሚለው ጥያቄ ከባዱ እና ዋነኛው የአብይ ፈተና ነው።
ምክንያቱም አገሪቱ አሁንም አደጋ ላይ ነች። እባብ እና የሰው
እግር ዘንዶ እና አርግብ ጅብ እና አህያ ነብር እና ፍየል አብረው ባንድ በረት ታሽገው እየተደነባበሩ እየተሻሹ እያየንበት ያለው
የመንግሥት ስርኣት ነው። በጣም ሰትረንጅ/አዲስ ክሰተት/ እና ለመተቸት እጅ እግሩ የጠፋ ለመላምት የሚያስቸግር ክስተት
ነው አሁን አያየን የለነው ታይቶ ተሰምቶ የሚታወቅ አይመስለኝም። በአይነቱ ልዩ የሆነ አስገራሚ ትርምስ።
ይህ ጥያቄ መፍትሔ ለማግኘት ለሱ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን እያንዳንዳንዳችን
መነጋገር እና መፍትሄ መለገስ ያለብን ጉዳይ ነው። እንደ እኔ እንደ እኔ ግን ምንም ያህል አስቸጋሪ ውጥረት ብንገኝም እውነት በዙፋንዋ ለማስቀመጥቅ የምትፈልጉ ሁሉ “ስቃይ እንደትጮህ
ፈቀዱላት”። ያኔ “እውነታውን” ታውቁታላችሁ።
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian
Semay)