በዓድዋዉ ድል ትግሬዎች እንጂ አማሮች ሊኮሩበት አይገባም?
ጌታቸዉ ረዳ
እንኳን ለ113ኛዉ የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ። እንኳን አደረሰን ማለቱ የአባት ሆኖብን ነዉ እንጂ ፤አያቶቻችን ያስገኙልነን ድል ዛሬ ተመልሰን ኢትዮጵያ የጣልያንን ካርታ እና አስተዳደር በሚያወድሱ እና የሚቀበሉ በሙሶሎኒ መመርያዎች በቋንቋና በነገድ አስተዳደር የሚያምኑ ለቅኝ ገዢዎች ካርታ ቅድሚያ ሰጥተዉ የአባቶቻችነን አንጡራ መረጃዎች በማንኳሰስ በራሳቸዉ አገር የዘመቱ ከትግራይ እና ከኤርትራ የተወለዱ የዘመናችን “ትናንሽ ጣልያኖች” ሥር ወድቃ በምትገኝበት ወቅት “እንኳን ለድል አደረሳችሁ” ማለት አልነበረብኝም። ሆኖም እንዳልኩት ያባቶቻችን ሰናይ ገድል በወያኔ መሰሪ ሳይወደስ እንዳይቀር በማሰብ አባቶች በዚህ ወቅት በሕሊናችን እናስታዉሳቸዋለን።
ሰሞኑን የወያኔ የፕሮፖጋንዳ መድረኮች የተመለከታችሁ ሁሉ፤ “ተሾመ ቶጋ” የተባለዉ “የወያኔ አገልጋይ” በዓድዋ ድል መታሰቢያ አበባ ሲየኖር፤ ጌታዉ “የሻዕቢያዉ ሎሌዉ” ‘መለስ ዜናዊ’ ግን ተደብቆ በልቡ “ሲያሾፍ” እንደዋለ ብዙዎቻችን የምናዉቀዉ ነዉ።
ወያኔዎች ስለ ዓድዋ በዓል አከባበር “በሙዚቃ ማርሽ” አሳጅበዉ “አክብረነዋል” ቢሉንም በካድሬዎቻቸዉ እና በድርጅቱ መሪዎች በተደጋጋሚ በዓሉ የትግራይ ተወላጆች ድል እንጂ የነፍጠኞች ፤የኢትዮጵያዩያኖች እንዳልሆነ ያዉም (“ነፍጠኛ፤ትምክህተኛ፤የትግራይ ሕዝብ ጠላት፤4ኛዉ ጠላት (ቱርከ፤ግብጢ፤ጣሊያን እና 4ኛዉ ምኒሊክ) የሚኒልክ ተጋድሎ ድል እንዳልሆነ አበስረዉ ደጋግመዉ እንደጻፉ እና እንደተከራረከሩ አብዛኛዎቻችሁ የምታዉቁት በድምጺ ወያኔ ራዲዮ እና በተሓሕት የኪነት ቡድን የተዘፈነበት ፕሮፖጋንዳ ነዉ።
ለዚህም ነበር ወያኔዎች {“ትግሬ ከጠገበ እና አንድ ከሆነ አይገዛም} ወይም አይቻልም” የሚል እምነት ነበራቸዉ። በተጨማሪም {የትግራይ ህዝብ “ብዙ ብር” አለዉ፤ተብሎ ስለሚታመን ገበሬዉን “እየዘረፉ” ሃብት ማካበትና ሕዝቡን “ማደሕየትም” “እንደ ስልት” የተያዘ በመሆኑ አስፈላጊ ነበር}። አጼ ምኒልክ ወደ ትግራይ ያደረጉት ዘመቻም እነዚህን “ሁለት ነጥቦች” ለማሳካትና ተግባራዊ ለማድረግ ነዉ”} ምመህር ገብረኪዳን ደስታ (የትግራይ ሕዝብ እና የትምክሕተኞች ሴራ ከትናንት አስከ ዛሬ ገጽ 103)
እንግዲህ ከላይ በአህጽሮት የምታኑብቡት የወያኔዎች ያልተገረዘ አንደበት ወያኔዎች የዓድዋን ድል የተገኘዉ በትግራይ ህዝብ እና መኳንንት ብቻ እንደሆነ በማስመሰል፤ በመሪነት ከባለቤታቸዉ ጋር ወደ ረዥም እና አድካሚ የእግር ጉዞ ተጉዘዉ ከአዲስ አበባ ዓድዋ ድረስ ዘምተዉ “አላጄ”፤”እንዳየሱስ” እና “እምባ-ሰሎዳ” ድረስ ገስግሰዉ ራስ መንገሻ ዮሃንስን እየተከታተሉ ሲያባርሯቸዉ የነበሩትን ጣሊያኖች በተጠቀሱ ቦታዎችን የመሸጉት ጣሊያኖችን ከመላ ኢትዮጵያ ያሰባሰቡዋቸዉ ኢትዮጵያዉያን ተዋጊዎች አያቶቻችን በመምራት ለድል ያበቁትን ምኒልክ መሆናቸዉ ላለማሞገስ ተብሎ “ሚኒልክ ወደ ትግራይ የመጡት “ብዙ” ብር አለዉ ተብሎ የሚገመተዉ የትግራይ ሕዝብ ለመዝረፍ እንደመጡ ነበር እየነገሩን ያሉት።
ወያኔዎች ይቀጥሉና {“በአጼ ምኒሊክ ሴራና ሃገራዉ ክህደት ምክንያት (የትግራይ ሕዝብ) የጠላቶቹ መተረቢያና መሳቅያ ሆነ። አስመራ ከተማ ላይ ወድቆ ከኢጣሊያንኖች እጅ ፍርፋሪ ለመነ። በጎዳጉዲ፤በጉራዕ፤በሰሓጢ፤በኩፊትና በዶግዓሊ አዉደ ዉግያዎች አባቶቻችን ያስመዘገቡት የጀግንነት ዉሎ እና አኩሪ ታሪክ በአጼ ሚኒሊልክ ሃገራዊ ክህደት ምክንያት ተደመሰሰ። የአባቶቻችን ደም ፤ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ።”} ምመህር ገብረኪዳን ደስታ በተጠቀሰዉ መጽሃፍ ገጽ 104-105)
በሃገር ወዳድነት ፤የትግራይን ሕዝብ ከጣሊያን መንጋጋ ያላቀቀዉ፤ የትግራይ መስፍን የነበሩት “ራስ መንገሻ ዮሃንስን” ከጣሊያን እግር ብረት እና ግዞት አልላቅቀዉ ፤ የትግራይ ሕዝብ እንደ “ኤርትራዉያን” ባዶ እግሩ እየሄደ፤ ወይም ከሗላ የከተማ አቡቶበሶች ሲጛዝ ከጣሊያኖች ተከልሎ በመጋረጃ ተጋርዶ ከመጓዝ፤ ከአራተኛ ክፍል ወዲያ እንዳይቀጥል እና እናቶቻችንም የጣሊያን መጫወቻ እና ዲቃላ አምራች እንዳይሆኑ፤ ወንድ አያቶቻችንም የጣሊያን ሰላቶ ሆነዉ ትግራይ ዉስጥ የሰላቶ ባንዴራ እንዳያዉለበልቡ በማለት ከሸዋ፤ ከጎጃም፤ ከወሎ፤ ከአርሲ ከሐረር.. ከመላዋ የኢትዮያ ሕዘብ ክተት ብለዉ በእግር በበቅሎ እየመሩ ጣልይንን አባርረዉ “ለድል ያበቁት” በድል ታሪክ የሚዘከሩትን ጀግናዉ ሚኒልክን “በሃገር ከሃዲነት” ሲከስሱ፤ ያገር ክህደት የፈጸሙት የዘመናችን ከሃዲ “የወያኔ ባንዳዎች” ምኒሊክን ለመዉቀስ የሞራል ብቃት እንደሌላቸዉ መላዉ ሕዝብ እና በክህደቱ ዉስጥ እጃቸዉን ያስገቡ የወያኔ መሪዎች ሳይቀር የራሳቸዉ ክህደት ባያምኑም “ስህትት ፈጽመናል/ችኮላ” የሚሉ ቃላቶች በመተካት ሃጋረቸዉ ኢትዮጵያን እንደበደሉ/እንደካዱ “ያመኑበት ነዉ”።
የወላጆቻችን ደም -“ደመ ከልብ” እንዲሆን ያስቀሩት ሚኒልክ ሳይሆኑ፤ ከዛ በሗላ በደማቸዉ ያስመለሱት እና ያስጠበቁት ክፍለሃገር ኤርትራን (ምኒልክ በወያኔ የሚከሰሱበት ጉዳይ) ከመሰል ካሃዲዎቻቸዉ ጋር በመሆን ወላጆቻችን ጣሊያንን በተዋጉበት ስፍራዎች እና የባሕር ወደቦች ላይ ተመልሰዉ የገዛ አገራቸዉ ኢትዮጵያ ያዘመተቻቸዉ ተዋጊ ሃይሎችን ከአሜሪካኖችና እና በዓረቦች አይዟችሁ ባይነት እየተበራቱ “በጠላቶች የሳተላይት መረጃ” እየታገዙ የፈጁት ኢትዮጵያዊ ነብስ ወያኔዎች እንጂ ሚኒልክ እንዳልሆኑ ይታወቃል።
ባገር ክህደት በወደብ መዝጋት፤ ያትዮጵያ ልጆች ደም በማፍስስ የሚከሰሰዉ ወያኔ እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም። በዚህ ድረገጽ በአርካኢቭ/በመዛግብት ጓዳ፤ አሁንም የሰፈረዉ “አይ ምፅዋ!” የሚለዉ “ታሪካዊ የጦርነት ሰነድ” ላነበበ ሰዉ ባንዳዎቹ ምንኛ ሕሊና ቢስ ቅጥረኞች መሆናቸዉ ኢትዮጵያዊ ሕሊና ላልተለየዉ ፈራጅ በቀላሉ የሚፈርደዉ ነዉ።
ንጉስ ምኒልክ እና (በወያኔዎች ቋንቋ፤በአብራሃም ያየህ
በአታኽልቲ ሓጎስ በመምህር ገብረኪዳን ደስታ… ቋንቋ) “ደቂቀ ምኒሊኮች” ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ከሻዕቢያ ጋር ወግነዉ “ምጽዋ ድረስ አልጌና ድረስ”
‘የትግራይ ልጆች’ ይዘዉ ሄደዉ የ ኢትዮጵያን እና የትግራይን የገበሬዉ ልጆች አስፈጅተዋል? ምኒልክ ከዚህ የባሰ ክህደት ፈጽመዋል?
ዮሃንስም ፤ራስ መንገሻም ራስ ሥዩምም፤ራስ አሉላም፤ስብሓትም፤ደብብም ፤ሃይለስላሴ ጉግሳም ሁሉም እንደየሁኔታዉ ለጣሊያንም ለግብጽም እንዲሁም ከእንግሊዝም ተመሳጥረዉ ያገበደዱበት የተሞዳሞዱበት ሰነዶች ትተዉልን ሄደዋል።
ሌላ ቀርቶ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመለስ እነ ራስ ዳምጤን ማርኮ “ለኮሎኔል ቱቺ” አስረክቦ እንዲረሸኑ ያደረገዉ ማን ነዉ? ራስ ሃይሉ/ጀኔራል ሃይሉ ከበደን ማርኮ ለጣልያኖች በባንዳነት ሀገራቸዉን ከድተዉ የራስ ሃይሉን ራስ ቅላቸዉ በጣልያኖች ቢላዎ መቆረጥ ድረስ ያደረሰዉ የትግራዩ ሰዉ ማን ነዉ? አክሱማዊዉ የትግራይ ሰዉ “ደጃች ተኽሉ መሸሻ” አልነበሩም? ማን በማን ላይ ማማት ያምርበታል? ሁሉም የኛ ነገስታት ናቸዉ፤ሃበሾች ናቸዉ፤ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።ታዲያ በምኒልክ እና በምኒልክ አድናቂ ኢትዮጵያዉያን እና የታሪክ ጻሃፍቶች ላይ ዘመቻዉ ለምን በረታ?
በነገድ የፖለቲካ በሽታ ተለክፎ መስፍናዊነት ሕሊና ተከትሎ መወሻከት ምን የሚሉት ፖለቲካ ነዉ?
እንደርታዊዉ ተወላጅ የወያኔዉ ዘፋኝ ኪዳነማርያም ረዳ በወየኔ ፕሮፖጋንዳዉ ምን እያለ ነበር የትግራይን ገበሬ እያሞኘ ሲሰብከን የነበረዉ?
“ንአብነት ማይ ጨዉ ዓድዋ እንተዘከርና፤
ተምቤን ዓቢይ ዓዲ ሽረ እንዳባጉና፤
ኩይናት ምስ ገበሩ እቶም ወለድና፤
ጸላኢ ደምሲሶም ታሪኽ ሓደጉልና።
;..ጨቆንትና አምሓሩ ምስ ታሪኽ ፀሓፍቶም
ንዓና ዓብሊሎም ታሪኽና ጎቢጦም
አለዉ ይምክሑ ብደም ወለድና፤
ንቃለስ ተጋሩ ክንመልስ ቅያና “
(ሓቀኛ ታሪክ ተደብቆ አይቀርም ለምሳሌ የማይጨዉን፤ የዓድዋን፤የሽረ እንዳባጉናን ታሪክ ስንመረምር ወራሪዎችን ድባቅ በምመታት አኩሪ ታሪክ ትተዉልን አልፈዋል። ይሁን እንጂ፤አባቶቻችን ብብዙ ዓዉደ ዉግያዎች ደማቸዉን አፍስሰዉ ያስመዘገቡትን ታሪክ “(ጨቆንትና አምሓሩ ምስታሪኽ ፀሓፍቶም”) “ጨቋኞቻችን አማሮች እና ታሪክ ጸሃፊዎቻቸዉ” በአሁኑ ወቅት እየተኮፈሱበት ነዉ። ታሪካችንን ቀብረዉ በአባቶቻችን ደም/ታሪክ እየተመኩበት ናቸዉ እና የትግራይ ተወላጆች የሆንን በሙላ ታሪካችነን ለማሳደስ በፅናት መታገል አለብን) የሚል መልእክት ነዉ ዘፋኙ ያስተላለፈዉ።
እግዲህ እዚህ ላይ የምንመለከተዉ ልብ ብለን ማሰተዋል ያለብን (1-) ጨቆንትና አምሓሩ የሚለዉ ሐረግ ትግራይን የጨቆነዉ አማራ መሆኑን (2-) ይህ አማራ የተባለዉ ጨቋኝ ነገድ፣ ጉብዝና የሌለዉ፤ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ ሲል ደሙ ያላፈሰሰ፤ በመከራ ጊዜ ለትግራይ ሕዝብ ያልደረሰለት፤የጣሊያን ወራሪ መሪዎቹን እነ ራስ መንገሻ ዮሓንስ እያሳደደ አዲግራትን መቀሌን አልፎ እስከ አላጌ ድረስ ሲያስሸሻቸዉ አማራ የሚባል ክፍል ለወገኑ ለትግራይ ሕዝብ የወገን ደራሽ ሆኖ አምባላጌ፤ እንዳየሱስ፤ በእንዳባጉና፤ በሰለክላካ ጦር ሜዳዎች… ከጎጃም ከሸዋ ከወሎ ከጎንደር ገስግሶ ዘምቶ ደሙን እንደላፈሰሰ፤በመስበክ የታሪክ ዉሸት በጽሁፍ እየመዘገቡ አዲስዩን ትዉልድ ለማወናበድ ጥረዋል። ዘፈኑም የሚያመለክተዉ ይሄንኑ የዉሸት ጸረ-አማራ ስብከት ነዉ።
ያዉም-አርበኝነት የሚባል ወኔ አማራዉ ስለሌለዉ ወይንም የትምክህተኞቹ ወላጆች የሚባሉት “አማራዎች” አርበኛ ስላልበቀለባቸዉ “በትግራይ አርበኞች” እየተመኩ “የትግራይ አርበኝነት የአማራዉ በማስመሰል” እየተኮፈሱበት ነዉና “አማሮች በራሳቸዉ አርበኞች (ካሉዋቸዉ!!) ይኩሩ እንጂ በወላጆቻችን በትግራይ አርበኞች መኩራራት መኮፈስ የለባቸዉም።ይላል ዘፋኙ የወያኔዉ የኪነት ክፍል።
ይሄ ደግሞ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም!! ነዉ መልእክቱ።ይሄን ስታነቡ ብለጭ እንደሚልባችሁ ይገባኛል። ያልበሰሉ ትንንሽ ህሊናዎች አደገኞች በመሆናቸዉ ለምን እንዲያ እንደሚሰማችሁ ይገባኛል። ለመሆኑ አንዳባጉና ፤ሰለክለኻ ማይጨዉ ያልዘመተ አማራ ማን አለ? ትዝታ የሚለዉ የአቶ አዲስ አለማዮህ መጽሃፍ የሚነግረን በአማራ ዘማች እና አዝማች የተካሄደ ጸረ- ጣሊያን ጦርነት ነበር።እነ አዲስ አለማዮህ ፤እነ ራስ እምሩ ትግሬዎች ናቸዉ? ይህ ክህደት የዘለለዉ የክህደት መጠን ስትመለከቱ ጎሰኝነት በዉሸት ሕሊናን አስክሮ ሕዝብ ለሕዝብ እንደሚያባላ ምንኛ ሃይለኛ በሽታ እንደሆነ እንረዳለን።
ታሪክን እያጣመሙ ያሉት “ሰዉ መሳይ ባደባባይ” እነማን ናቸዉ? የሰዉ ልጅ እንደ በቀሎ እሸት እሳት ዉስጥ ጨምረዉ የሚቀቅሉ የዘመናችን የወያኔ ጉዶች/ትንንሽ ጣሊያኖች’ አይደሉም? ለመሆኑ አማራ የሚባል ጀግና ታጥቶስ ከትግራይ ጀግኖች እየተፈለጉ በትግራይ ጀግኖች ሰም እንደ “የአማራ ጀግኖች” እየተደረገ፤ አማሮች እየተኩራሩበት ነዉ ማለት ከዚህ ወዲያ የታሪክ ግብዝነት ምን አለ? የአማራ ነገድ ስም የሚያስጠራ የጦር ሜዳ ጀግኖች ስም የለም ብለዉ ማሰብ ከቶዉንም ራሱ የቻለ ልዩ ክህደት ብቻ ሳይሆን “የኩታራ ኩታራ ሕሊና ማራመድ ነዉ”።
ደግሞስ አማራዉ በትግራይ ጀግኖች ቢኩራራ እና ቢመካስ የሚያስከፋዉ ምኑ ላይ ነዉ። አማራዉ የትግራይ የሐረግ ዘር አይደለም?።ቢሆንስ፣ በወገኑ ጀግንነት ቢመካ ያስመሰግነዋል እንጂ እንዴት ያስወቅሰዋል? ሚኒልክ ዓድዋ ድረስ መጥተዉ እነ “አይነጥሩ መድፈኛዉ” ሊቀመንኳስ አባተ -“መቀሌ እንዳየሱስ ተራራ” ጣሊያን የመሸገበትን ምሽግ በመነጥር እያዩ ሚዛኑን እየመዘኑ የጣልያንን መድፍ መንኮራኩሩን ሲሰብሩት የነበሩት ጀግኖች በምን መለክያ በክህደት እና በፈሪነት ይመዝገቡ?ትግራይን ከጣሊያን ጥርስ መንጋጋ አላቅቆ “የተከላለከለት” አማራ/ነፍጠኛ ብሎ ወያኔ ሚጠራዉ ክፍል ደሙንና እና አጥንቱን እንዳላፈሰሰ ለምን አኩሪ ስራዉ ለምን ከመ “ደመ ከልብ” ይቆጠራል? ብልግናዉ በጣም አልበዛም?!
ወገኖቼ ሆይ- እነኚህ ጉዶች እንኳን በጠላትነት ሚያዩት አማራዉን የኛ የሚሉትን የራሳቸዉ የትግራይን ሕዝብ ሳይቀር “በጠባብ ብሄረተኛ” እና “በመስፍንንት ሕሊና” ይከስሱታል። ለመሆኑ ካሃዲዉ ማን ነዉ? ጠባብ ብሐረተኛ እና መስፍናዊ እና ትምክህተኛ በማለት ስለ የትግራይን ሕዝብ በሕሪ እና ማንነት የገለጸዉ ማን ነዉ? “ወያኔ ወየስ አጼ ሚኒሊክ?”
ድርጅቱን በግምባር ቀደም የመሰረተዉ ከድርጅቱ ባላመስማማት የወጣዉ በ“አረጋዊ በርሄ” ብዕር አስደግፌ ስለ ወያኔ ከሃዲ እና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ላቅርብ “በዓሰር አመት ግምገማዉ ዉስጥ…” ይላል አረጋዊ በርሄ በእነመለስ እና ስብሓት የሚመራዉ ወያኔ ትግራይ “የትግራይ ሪፑብሊክ” በምን መነሻ ለመመስረት እንደተገፋፉ ተጠይቀዉ ሲመልሱ “የትግራይ ሕዝብ ጠባብ ብሔረተኛነትና መስፍናዊ ሕብረተሰብ ዝንባሌ ስላለዉ፤ ለግንጠላዉ የመነሻ ምክንየት አድርገዉ እንደሆነ እና ሊነጠል እንደሚፈልግ የጻፉት የድርጅቱ ግምገማ ያቀረቡት ክርክር “በ10 ዓመት ግምገማዉ ገጽ 24-25 እንዲህ ይላል “ይህ የጠባብ ብሔራዊ አመለካከት ዝንባሌ የተከሰተዉ በሕዝቡ ላይ የነበረዉ ጠባብ ብሔራዊ ስሜት” እንደነበር ለሪፑብሊክ ምስረታ ዓላማቸዉ ከገፋፋቸዉ ካቀረቧቸዉ ጥቂት ሌሎች ምክንያቶች አንደኛዉ ከላይ የተጠቀሰዉ ምክንያት መሆኑን የ10ዓመቱ የግምገማ ሰነድ ይገልጻሉ።
እንግዲህ ሕብረተሰቡም ሆነ እራሱ ተሓትን የሚመሩ መሪዎች ጠባብ ብሄረተኛ ዝንባሌ እንዳለቸዉ ሳይደብቁ ሲነግሩን- ምኒልክን በጠባብ እና ትምክህተኛ ሗላ ቀር በሆነ መስፍናዊ አስተዳደር ሲከስሱ፤ ከሳሾቹ ምኒሊክን የመክሰስ ሞራል ሊኖራቸዉ አይችልም እያሰኘን ያለዉ ሁኔታ ታሪካቸዉንና ሰነዶቻቸዉን በመመርመር ነዉ።
በዚያዉ የግንጠላዉ ሁኔታ እና የ10 ዓመቱ ግምገማቸዉ ሰፋ ባለ አረጋዊ በጻፈዉ የቆየ ሰነድ በሚቀጥለዉ ሰሞን ይቀርባል ተከታተሉ።
የዓድዋ ድል የመላ ሀገሪቱ ልጆች ነዉ። በየትኛዉም ጦር ሜዳ ፤አንዱ ካንዱ የበለጠ መስዋእት ከፍሎ ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ድሉ ለአንድ ሃገር ልጆች የተከፈለ መስዋእትነት በመሆኑ ድሉ የጋራችን ነዉ። በኢትዮጵያ አርበኞች ደም እንኮራለን። ብንኮራም ኢት ዮጵያዉያን አባቶቻችን የሚያስኮራን ደም ስለከፈሉበት ብንኮራም ይገባናል።
ከላይ የቀረቡት የ1888 ዓ.ም የ ዓድዋ የኢትዮጵያን የካርታ ምሽጎች የሚያሳዩት በራስ መንገሻ ብቻ የሚመራ የትግራይ ጦር ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ክፍለሃገር ጦር ብዛት በላይ ተዋጊ እና አዋጊ ራሶች መኳንንቶች እና ባላባቶች ከመላ ኢትዮጵያ የተወጣጡ ዘማች ተዋጊ አርበኞች ጠቅላላ የዉግያ ቀጠናዎች/ወረዳዎች የተያዙት በእነዚህ አርበኞች እንደነበር እንድትመለከቱት ለማስረጃ ያቀረብኩት ነዉ (ምንጩ የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያ ጀግኖች ዉለታ” ደራሲ አቶ አበበ ሃይለመለኮት ናቸዉ)። በዚህ መረጃ አሌ የሚል የወያኔ ካድሬ ካለ ሜዳዉ ይሄዉ ፈረሱም ይሄዉ! ማስረጃችሁን አምጡ እንከራከር። መስፈናዊ ጠባብ የወያኔዎች የሕሊና አመለካከት ዞሮ ዞሮ የሚጎዳዉ የትግራይን ሕዝብ እንደሆነ ተገንዝባችሁ በጎጠኝነት የተተበተበ ሕሊናችሁ መልሶ ወደ ሃገራዊ እና ሰብአዊነት ሕሊና እንድትመልሱት ደጋግመን ምክራችንን ዛሬም በዚህ የዓድዋ ድል እንለግስላችሗለን። ነገር ካለፈ በሗላ እንደ ደርግ ብትቆጩ ትርፉ መቆጨት እንጂ ጉዳት ካደረሱ በሗላ መቆጨት ላመንም አይፈይድም።
የተፈጥሮ ሕግጋት ነዉና ወደ ላይ የወጣ ሁሉ አንድ ቀን ተመልሶ ከወጣበት ሥር ተመልሶ መዉረዱ አይቀሬ ነዉ።ዘረኛነትን ፤ነገድኝነትን እናሰወግድ። የኢትዮጵያ ጠላቶች እና የወያኔ ባንዳዎች ዉድቀት አይቀሬ ነዉ! ትግላችን ረዢም ነዉ ፤ድል ግን አይቀሬ ነዉ! Getachew Reda
http://www.ethiopiansemay.blogspot.com