Tuesday, July 10, 2018

የባሕር በራችንን እስከ ዘላለሙ ሊያስነጥቀን የመጣው ሌላው መለስ ዜናዊ አብይ አሕመድ እንደሆነ አልጠራጠርም! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


የባሕር በራችንን እስከ ዘላለሙ ሊያስነጥቀን የመጣው ሌላው መለስ ዜናዊ አብይ አሕመድ እንደሆነ አልጠራጠርም!
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)
 
በርእሱ የተመለከተው ስሕተተኛ ሆኜ ብገኝ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ግን ቢሞት ኢሳያስ በስጦታ በመለስ ዜናዊ እና በትግሬዎች የተሰጠው ሕጋዊ የባሕር በራችንን እና ሕጋዊ ጥያቄያችንን በአብይ አሕመድ “ሸጋ ባሕሪ እና የመደመር ፍቅር’ ተማርኮ ኢሳያስ መልሶ ያለ ምንም ጦርነት ለአብይ ያስረክባል በሎ ማለት ቅዠት ነው። እኔን የሚያሳዝኑኝ በአብይ ፍቅር የስሜት ስካር ተጠምደው እጅ ተወርች የተያዙ ኢትዮጵያዊያን አሽቃባጮች ወዴት እንደሚሄዱ ሳያውቁ መጠን የሌለው ማሽቃበጣቸው እጅ እጅ የማለቱ ጉዳይ እንደ ምጥሚጣ ‘እየሰነጠፈኝ’ ነው’። አብይ ምን ሊያደርግ አስመራ ሄደ? የሚለው ጥያቄ እና በማንስ ድጋፍ? የሚለው ሌላው ጥያቄ ለመመለስ ግልጽ እና የሚከብድ አይደለም። 

አብይ አስመራ የሄደው ለምን ድነው? መልሱ ይሄው፡-

መለስ ዜናዊ እና ወያኔ ለኤርትራ በማዳላት የባሕር ወደባችን እና ድምበሮችን ለኤርትራ በሚጠቅም መልኩ የኤርትራ መገንጠል እና ባሕር ወደባችንን ያስነጠቀን ሕገ ወጡ ‘ሴራ’ ( ከአልጄሪሱ በፊት) እንዲሁም ‘10 አመት ቆይተው’ ሁለቱ ወረበሎች ሆን ብለው ሕዝብ ሳያውቀው ተጠያቂ የሌለው የድምበር ግጭት እና ጦርነት አስነስተው፤ ሲያበቁ ‘ትግሬዎች’ ተወረርን እርዱን ብለው መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊን ሲለምኑት ፤ ሕዝቡም የሆዱን  በሆዱ አድርጎ ‘እሺ ብሎ’ ኢትዮጵያውያን ተዋጊ ሃይሎች ሻዕቢያን አባርረው ኢሳያስ እነጥቃቸዋለሁ ያላቸውን ድምበሮችን ወደ ባለቤቱ ወደ ትግራይ ሕዝብ ከስመለሱለት በ፤ ወራሪው ኢሳያስ ወደ አልጄሪስ መሄድ ሲገባው  እሱ ሳይሆን በተገላቢጦሽ በሚገርም እንቆቅልሽ ‘መለስ ዜናዊ’ የተባለው የትግሬዎች መሪ የነበረው እርኩስ ኤርትራዊው “እናት አገሩን ኤርትራን ለመጥቀም” ሲል (ባሕር የስዘጋብንን እንዳይበቃው) ወደ አልጄሪስ ሄዶ ሁሉም እሰጣለሁ ብሎ ኢሳያስ የጠየቃቸው አስፈላጊ ለም መሬቶችን እንዲያገኝ አስደረገለት።

ይህ ሴራ ደግሞ ባለፈው ወር በሰነድ ተገልጿል። የአሽቃባጮችን ሕሊና ለማስታወስ ያህል እዚህ እደግመዋለሁ። ይኼውም የአልጄሪስ ስምምነት ከመፈረሙ 4 ቀን በፊት (አሁን እደግመዋለሁ እንዲገባችሁ-“የአልጄሪስ ስምምነት ከመፈረሙ 4 ቀን በፊት”)  ትግሬዎች ነን የሚሉ አስመሳይ ትግሬዎች እነ መለስ እና አሽከሮቹ ሆን ብለው ከ 4 ቀን በፊት በፓርላማ እንዲጸድቅ ያደረጉትን ሴራ እውን ለማድረግ እና ሕጋዊ ለማድረግ ወደ አልጄሪስ ሄደው ሕግን በመተላለፍ ብሔራዊ ወንጀል ፈጽመው እዛውም በፌርማቸው ላመረጋገጥ ወደ አልጄሪስ ሄዱ። (የትግራይ ሕዝብም ምንም አላለም፤ አልተቃወመም ሰላማዊ ሰልፍ አላደረግም፤አንገዛም አላለም)።

ይህ ብሔራዊ የወንጀል ሰነድ ተደብቆ ቆይቶ ይፋ የሆነውም በጸሓፊው እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ስዩም ተሾመ አማካይነት ወንጀሉ የተፈጸመበት ቀን ከነ ፌርማው እና ቀን ማሕትም የፓርላማ ውሳኔ በማስረጃ ሰነዱን አስነብቦናል። በጥቂቱ እነሆ እንዲህ ይላል፤ በድረገጼም በመጠኑ ጠቅሼው ነበር፡-

"}
የአልጄርስ ስምምነት በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የኤርትራው ፕረዜዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ፊርማ የፀደቀው ታህሳስ 03/1993 ዓ.ም (እ.አ.አ. 12th December, 2000) መሆኑን ከላይ ካለው የስምምነቱ ሰነድ መገንዘብ ይቻላል (ጸሓፊው በማስረጃ የተደገፈ ሰነድ ለጥፎት ስለነበር ነው- ከላይ እያለ ያለው)። ይሁን እንጂ፣ የአልጄርስ ስምምነትን በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቆ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ የታወጀው ህዳር 29/1993 ዓ.ም (እ.አ.አ. 8th December, 2000) ነው። በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ አልጄርስ ላይ ከመፈረሙ አራት (4) ቀናት በፊት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቆት ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል። የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55(4) ምክር ቤቱ “የህግ አስፈፃሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች ያፀድቃል”

ይህ ሕገ ወጥ ብሔራዊ ወንጀል የአልጄርስ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት በምክር ቤቱ ፀድቆ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታውጇል። አይደለም እንዴ? ስለዚህ በሴራ የተከናወነ ድርጊት ስለሆነ ሕጋዊ አይደለም። ሆኖም አሁን አገሪቱ እየመራ ያለው አብይ ይህ ወንጀል መፈጸሙ አያውቅም ማለት አይቻልም። ካላወቀም፤ እንኳን እሱ እኛም አውቀነው ሰነዱን አንብበናዋል። ስለዚህ እዛ አስመራ ድረስ የሄደበት ምክንያት ፓርላማ አባለቶችን የተናገራቸውን ‘እናንተ ፈጽሙት ያለችሁን ነው እየፈጸምን ያለነው’ ብሎ ነው ወደ አስመራ የሄደው።  ሲሄድ ደግሞ ስምምነቱ ሕገ ወጥ መሆኑን እያወቀ ነው። ሌላ ቀርቶ “ዓሰብም ለሻዕቢያ” ሲበረከት ብ ያላማከረ ሕገ ወጥ መሆኑን እራሱ በፓርላ ውስጥ ነግሮናል። ስለሆነም እንኳን የድምበሩ ስምምነት ቀርቶ “ዓሰብን መጠየቅ ነበረበት”። ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን አስመራ ሄዶ “ኢሳያስን ተጎጂ ነህ ብሎ ሰምምነቱን እውን ለማድረግ እና በእግረ መንገዱም ኤርትራኖችንም ሓዘኑን ለመግለጽ አስመራ ሄዶ “ፍቅር ሊሰብክ ሄደ”።

ለመሆኑ ብምን ሂሳብ ነው የአልጄሪሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ነው የሄደው የምትለን ልትሉ ትችሉ ይሆናል። መልሴም ከአብይ አንደበት ላስነብባችሁ (ፓርላማ ውስጥ የተናገረው ነው) እንዲህ ሲል፤
“ሰላም ስንፈልግ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ ወይ? አዎ አለ። ሰላም በነፃ ከየት ይመጣል! የደምበር ኮሚሽን ሲወስን ለኛ የሰጠው አለ ፤ለነሱ የሰጠው አለ። እኛ እንደምንጠይቀው በዛ በኩል ያለው ሕዝብም ይጠይቃል ብየ አስባለሁ። እኛ ግን ለድርድር እና ለንግግር ‘ውሳኔውን ለመቀበል እና ለመሄድ መዘጋጀታችንን ማረጋገጣችን  የናንተን ውሳኔ የዘገየው ማስፈጸማችን  ብቻ ነው። ወስናችሁ አስፈጽሙ  ብላችል አስፈጻሚው የናንተን ስራ ካልሰራ መጠየቅ አለበት።” (ጠ/ሚ አብይ  አሕመድ” ሲል ፓርላማ ውስጥ አቁዋሙን በግልጽ ነግሮናል።

ስለዚህ የሄደበት ዋናው ዓላማ ‘ውሳኔውን ለመቀበል” ነው። ማለት ነው። ስለሆነም ኢሳያስ የሚፈልገው በማግኘቱ ፋሺስቱ ኢሳያስ ሆን ብሎ የማሃል አገር ሕዝብ የዋህ ገራገር እና በትንሹ ልቡ የሚለሰልስ መሆኑን ስለሚያውቅ “በለስ” ጋበዛቸው። ቁልቋል በሊታ እየተባልን በየፓልቶኩ ስንሰደብ የነበርነው ሁሉ ‘ወዲ አፎም’ ሆን ብሎ ጣፋጩን ቁልቋል ሲጋብዛቸው የፓርላማ ተጠሪ ሁላ “ምን እሚሉት ጉደኛ የፍቅር ፍሬ ነው” ብለው ‘ፈረንጅ ይመስል’ እየተገረሙ አንድ አልበቃ በሎአቸው ‘እየደጋገሙ’ ገመጡት! መልካም ምሳ!

ወደ ቁም ነገራችን እንግባ። አብይ የሄደበትም ከላይ በራሱ አንደበት እንደነገረን ‘አስፈጽሙ አላችሁን ሥራ አስፈጻሚው የናንተን ትዕዛዝ ይፈጽማል” ያለውን ነው ተግባራዊ ለማድረግ የሄደው።

ይህ ሁሉ ክንዋኔ በማን ድጋፍ ነው ቅጽበታዊ ክስተቶች ለማየት የበቃነው የሚለው ሁለተኛው ከላይ የጠቀስኩት ጥያቄ ለመመለስ፦ በአሜሪካኖች እና በአረቦች። ይሄው እና ድሮ ድሮ የተባበሩት መንግሥታት ሰውየ (አንቶንዮ) አዲስ አባባ ለመሄድ ሽር ጉድ እያለ ነው። ለምን? ኢትዮጵያ ባሕርዋን ለመጨረሻ እና ለዘላለሙ በክራይ እና በምጣኔ ሃብት ልውውጥ እንጂ በባለቤትነት እንደማታገኝ አብይ እና አሜሪካኖቹ (ከላ) ስለወሰኑት ያንን ለመመረቅ ነው አዲስ አበባ እየደ ያለው። ድሮ ለድሮ  እየተጣደፈም አብይ ለኢሳያስ እና ከፍተኛ የፖለቲካ እና የወታደራዊ አዛዦቹ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲነሳለት (ኤርትራ እራስዋ ሳታመለት) “አብይ ልክ አንደ መለስ ዜናዊ ማዕቀቡ ተሎ ይነሳለት ብሎ እራሱ ደብዳቤ ጽፎ ለተባበሩት መንግሥታት አመለክቶለታል”። ታሪክ ሲደገም ማለት ይሄ ነው።  ጦርነት ቀስቃሹ ኢሳያስ በአሸናፊነት ለመውጣቱ ሌላው ምልክት ይኼ ነው። አስቂኞቹ እነ ግንቦት 7ትም ሲጮኹለት የነበረው ዘመቻ እውን ሆነ እያለ ዳግማዊ ድል እያሉ ስለ ኢሳያስ መቦረቅ ጀምረዋል። አፈር ይብላ እና ሰማያዊ የተባለው እርስ በርስ ሲፈነካከት እና ሲሰዳደብ የነበረው ድርጅት ደግሞ ከዚህ አስቂኝ ድርጅት ጋር (ግም ለግም) የጋር ግምባር ፈጥሯል ተብሏል። ወይ አገር!

ስለሆንም ኢሳያስ በአሸናፊነት ስለወጣ የኤርትራ እናቶች አበባ እና ዘምባባ ይዘው በትግርኛ እንዲህ ሲሉ ዘፍነውለታል።

“ወዲ ኣፎም መዓረየ

ተዓዊትካላ አምበኣረየ”   

( ወዲ አፎም ወለላ ማራችን አሸነፍካት አሉ) ይላል። ቀጥተኛ ትርጉም “ተዓዊትካላ” የሚለው የትግርኛ ትርጉም “ተሸናፈዋ” ሴት ስትሆን አሸናፊው “ወንድ ነው” በሴት እየተጠራች ያለቺው (ላ ፊደል) ‘ኢትዮጵያ” ነች በወንድ እየተጠራ ያለው ተዓዊትካ (ካ) ወንዱ ኢሳያስ (ወዲ አፎም) ማለት ነው። “ላ” ሲጨመር ተሸናፊ አለ። “ላ” ለሴት ገላጭ ሆኖ “ሉ” ለወንድ ተሸናፊ በገላጭነት የሚጻፉ ቃላቶች ናቸው። ይህ የዘፈን ስንኝ ለማወቅ ትንሽ የትግርኛ ቋንቋ ጥልቀት ችሎታ ያስፈልጋል። ስለዚህ “ወዲ አፎም ወለላ ማራችን አሸነፍካት አሉ” ሲሉ ዘፍነውለታል። ተሸናፊዋ እምየ ኢትዮጵያ ዛሬም በልጆቿ ደጋግማ እየተሸነፈች እየተደቆሰች ነች። ኢትዮጵያ ህይቴ በሙሉ የቻልኩትን ታገልኳቸው- ምን አባቴ ላርግሽ?! 

በጣም እኮ ግልጽ ነው፡

ውሳኔውን ለመቀበል እና ለመሄድ መዘጋጀታችንን ማረጋገጣችን  የናንተን ውሳኔ የዘገየው ማስፈጸማችን  ብቻ ነው። ወስናችሁ አስፈጽሙ  ብላችል አስፈጻሚው የናንተን ስራ ካልሰራ መጠየቅ አለበት።” በሚል ነው ኢሳያስ ያሸነፈበትን ሴራ ለማስፈጸም  “ወሳኔውን ለመቀበል” አስመራ ድረስ የሄደው።


አሁን አየር መንገድ ወደብ ንግድ ወዘተ…. እየተባለ ያለው ወደቡን በቋሚነት ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ እንዳይሰጥ “ሽፋን” እና “ማስረሻ” ፤ “ማጃጃያ” የተደረገ የኢምፔሪያሊስቶች ስልት እና ምክር ነው። ዛሬም ሴራው ቀጥሏል። መደመር ለምስራቅ አፍሪቃ የተሰጠ የኢምፔሪያሊስቶች አዲስ “ቺፕስ” ነው።  አለም የብር/የገዘብ/የክሬዲት የመገበያያ ስልት ኖቶችን አስቀርቶ በቺፕስ አንዲሆን ስራው እንደተጀመረ ታውቃላችሁ አይደለም? ቆዳህ ውስጥ በመርፌ የሚተከል “የኮምፒተር ቺፕስ” ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የ14 አመት ወጣት አማራ ተተክሎላት ስቃይ ውስጥ እንደነበረች አንብበናል? አላነበባችሁም? በወዳጄ በዶ/ር አሰፋ ነጋሽ የዘጋጀው ሰነድ “ወልቀይት.ካም” በተባለው ድረገጽ እና ሌሎች ድረገጾች ወጥቶ ነበር። ካላነባችሁት ጠይቁኝ እና ካለኝ ካልሆነ ደግሞ  አፈላልጌ እልክላችለሁ ። ስለዚህ የምስራቅ አፍሪካ መደመር ግልጽ የቤት ስራ ነው። አብይ የለበሰው አረንጓዴ ከናቲራ የአፍሪካ ካርታው ‘አናቱ ላይ’ ምን ስዕል እንዳለው እዩልኝ። መደመር ማለት ያ ነው።
በባድሜ ጉዳይ የስትራቴጂና የስልት ጥያቄዎች” (መለስ ዜናዊ የተዘጋጀ ሰነድ ‘ባለ 10 ገጽ’) ትዝ ይላችሗል? መለስ ምን ብሎ ነበር የጻፈው ጥቂቶቹን ላስታውሳችሁ፡

“ባድመ የመሬት ወይንም የክብር ጉዳይ አይደለችም” የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ ናት ትክክለኛ መንገድ ላይ ቆመን” (ገጽ 4)      

መሬታችን ነው ብለው ለሞቱ የሺዎቹ ኣእላፍ ሕይወት እና በዛው በ1000 ኪ.ሜ ድምበር የሚኖሩ ባለመሬቶቹ “መሬታችን’ ነው ብለው ሲዋደቁ ፤ቤተሶቦቻችን በኢሳያስ ወራሪ ወታደሮች ተደፍረናል፤ ብሎ ስለ ክብሩ እና መሬቱ የተዋደቀውን ሕዝብ እና ኗሪውን ነው “የመሬት ወይንም የክብር ጉዳይ አይደለም” እያለ ትግሬዎችን ሲያሞኝ የነበረው። ያ የሕግ የበላይነት እያለ ሲያታልል የነበረው ሕግ የሚለው ደግሞ ኢሳያስ እና መለስ አልጄሪስ ሄደው በደላሎቹ ዓረቦች እና ኢምፔሪያሊስቶች አስማሚነት የፈረሙበት ቀን እና ፌርማው የፀደቀበት ቀን  ታህሳስ 03/1993 ዓ.ም (እ.አ.አ. 12th December, 2000) ሲሆን
የአልጄርስ ስምምነትን ተብሎ  በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቆ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ የታወጀው ደግሞ ህዳር 29/1993 ዓ.ም (እ.አ.አ. 8th December, 2000) ነው።  

አያችሁ ሕግ ማለት? ሻዕቢያ መለስ እና ስዪም መስፍን… የመሳሰሉ የሻዕቢያ  ቅጥረኞችን  አስሰርገው እንዴት አንደተጫወቱብን?

በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ሲያታልል እንዲህ ብሎ ነበር፦

 “ጥያቄአችን የሕግ እንጂ የመሬት ስላልነበረ ሻዕቢያ በሃል ካዳከምነው በላ ደግሞ አሻፈረኝ ያለውን ሕግ የበላይነት እሬት እሬት እያለው እንዲውጠው  አስገድደነዋል” ( መለስ ዜናዊ ገጽ 4) አያችሁ ወያኔዎች እንዴት ሲጫወቱብን እንደነበር?

በመቀጠል እንዲህ ይላል፤

“የመጣ ቢመጣ  መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም የሚለው ፀረ ሕዝብም ነው” (መለስ ዜናው ገጽ 7)።

በዚህ ቅስቀሳ የተነሳ ብዙ ጅሎችና የመለስ አሽቃባጭ ምሁራን ጭምር ያንን ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው “ሕግ ሕግ” እያሉ አሁን ወደ አለው “ሕግ አልባ” እና ሻዕቢያን በአሸናፊነት ያጎናጸፈውን ክስተት አድርሰውናል። ዛሬም ወደባችን ሕጋዊ እና ክርክራችን መሰረት ያለው ስለሆነ በሕግ ካልሆነም በሃይል ወደባችንን እናስመልሳለን የምንል ሁሉ ዛሬ በአብይ “የመደመር ፍቅር” ሰክረው እና ተጃጅለው እየተወላገዱ ከእንግዲህ ወዲህ “ጦርነት እና የጦርነት ወሬ ሁሉ በመደመር ፍቅር ተሽሯል

እና

“ተዘወሪ አመኪና ተዘወሪ

አስመራን ሽዋን ኮይኑ መዛወሪ”
ተብሏል
 እና

አየር መንገዳችን ጀምሯል ፤ምፅዋ ‘ጉርጉሱም’ እንድናዋኝ ስለተፈቀደልን “ጦርነት ናፋቂዎች” አፋችሁ ዝጉ እያሉን ነው።

 አሽቃባች ሁሉ- ወደዳችሁ ጠላችሁ ጦርነት የሰው ልጆች መፈጠሪያ እና ሕግ አስከባሪ ስለሆነ አይጠፋም። ሕግ አላስከብርላችሁም ያለውን ክርክራችን ጦርነት እና ሃይል በግድ ያመጣዋል። ስለሆነም ቅዠት አቁማችሁ “መጃጃላችሁን አቁሙ”። ኢሳያስ “ዓሰብም ሆነ ኤርትራ በብር ማንኪያ ያጎረስን ሕግ ሳይሆን “ በሃይል” ነው ያጎረሰን” ፡ ብሎ ነግሮናል። ጌታቸው ረዳም “በሃይል የሄደ ባሃይል ይመጣል” ይላል የዘወትር ክርክሩ።

 አብይ አሕመድ “ጦርነት እና የጦርነት መንገድ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ተዘግቷል” በማለት እንደ መለስ ዜናዊ “በፍቅር ቅዠት’ ቢናገርም “የባሕር ወደባችን ሕጋዊ ባለቤቶች እስካላደረገን ድረስ”  *በምጣኔ ሃብት ልውውጥ* የሚባለው “የአዲሱ አለም” “የቺፕስ” መገበያያ እና “የሕዝቦች ድመራ” ስልታዊ ቁጥጥር ከመሆን አያልፍም። የዘላለማዊ ባርነታችንን የፈረሙብንን ሴረኞችን እንቃወማለን፡በሃይል እና በሴራ የተነጠቁት የባሕር በሮቻችንን ጉልበት እንደተወሰዱት ሁሉ በሃይል እና በመራራ ረዢም እልክ እናስመልሳለን

አብይ ካላደረገው ሌላ ነብይ ሌላው “አፄ ሠርፀ ድንግል”  ከኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ወርዶ ‘የዘመናችን የባሕረ ነጋሽ ቱረኮችን’ ተዋግቶ ከማሃይማን ባንዳዎች እጅ ባሕሮቻችንን ያስለቅቃል። ሩጫው፤ ገራ ገርነቱ እና ፍጥነቱ ስመለከተው የባሕር በራችንን  እስከ  ዘላለሙ ሊያስነጥቀን የመጣው ሌላው መለስ ዜናዊ አብይ አሕመድ እንደሆነ አልጠራጠርም። ይህ ውሸት ሆኖ ከተገኘ ይፋው ይቅርታ እንደምጠይቀው ቃል እገባለሁ። ከአብይ ይልቅ  እኔን የጨነቀኝ በጊዜያዊ መደለያዎች እየተጃጃልክ ከገዳዩም ከጨፍጫፊውም ከቀጣፊውም ከገንጣዩም ከወንጀለኛውም፤ ከገራፊውም ሁሉ እየዶለትክ እና አብረህ እየዞርክ የምትደሰኩር “ፍቅር ፈቅር” እያልክ ‘ሕዝባችንን የምታጃጅል’ የኢትዮጵያ ምሁር ምን አባቴ እንደማደርግህ ጭንቅ ይለኛል። ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) getachre@aol.com