Sunday, October 6, 2019

አርፍደው ለተቀላቀሉን ለደረጀ ሀብተወልድ፤ለታማኝ በየነ እና ለአበበ ገላው ከጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ Ethio Semay)


አርፍደው ለተቀላቀሉን ለደረጀ ሀብተወልድ፤ለታማኝ በየነ እና ለአበበ ገላው
ከጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ Ethio Semay)

ርዕሱ የሚነበበው “አርፍደው ለተቀላቀሉን” የሚለው በተለይም “ለተቀላቀሉን” የምትለዋ ቃል እየተጠራጠርኩ ያስቀመጥኳት እንጂ ‘በአንደበታቸው ተቀላቅለናች” የሚል ማስረጃ ስላልነገሩን ቃልዋን የተጠቀምኩባት ምክንያት ከጽሑፎቻቸው መራራነት በመነሳት መሆኑን ይታወቅልኝ። የኛ ሰው እንደምታውቁት ሸርተቴ ላይ መጨዋት ያበዛል። ከዚህ በመነሳት “ምናልባት”  ተቀላቅለውናል ወይንም ሊቀላቀሉን ነው በሚል እንውሰደው።

የታማኝ ባላውቅም (ማለትም አንዲት ሐረግ ወርወር አድርጎ ነው ዛሬም ወደ አፎቱ የገባው!) ሁለቱ ግን ማለትም አበበ ገላውና ደረጀ ሀብተውልድ ባስተዳደሩ ላይ ግልጽ ምሬት አስደምጠውናል። እነኚህ ታዋቂ ሰዎች ድምጾቻቸውን በአብይ አሕመድ አካሄድ ላይ ‘በመረረ ቃል’ ሊያስተጋቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜአቸው ነው። ለምሬታቸውም የገፋፋቸው ምክንያት ባለፈው አንድ አመት ከስድስት ወር ጫማው ሥር የተደፉለት  አስተዳዳር  ስራየ ብሎ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ‘በዜጎቻችን ፤በሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች፤ በታወቁ የአማራ ማሕበረሰብ ታጋዮች ፤ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት እና በሰንደቃላማችን’ ላይ ያሳረፈወው ጨካኝ ብትር፤ እያሳረፈ በነበረበት ወቅት ሳይሆን ለቁጭታቸው መነሻ ዛሬ የተቃውሞ ምሬታቸው ያስተጋቡት፤ የኦሮሞ አፓርታይዳዊው ክልል መሪ ‘ሽመልስ አብዲሳ’ በተባለ “ጋጠ ወጥ  አክራሪ” እሬቻ በተባለው በተወሰኑ ኦሮሞዎች የሚመለክ ‘የሃይማኖት በዓል’ ላይ ተገኝቶ   ለበዓሉ ተካፋዮች የደሰኮረው ጸረ አማራ ንግግር በመናገሩ ለምሬታቸው መነሻ መሆኑን ተገንዝበናል።

ድምጻቸው እጅግ ከረፈደ በኋላ ቢሆንም የተሰማቸውን ቅሬታ ማስተጋባታቸው ቅቡል ቢሆንም፡ በምሬታቸው ላይ ግን ግልጽ ያልሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን አነሳለሁ።

ለምሳሌ የኢሳቱ ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተውልድ የተባለው ጋዜጠኛ  ሳተናው በተባለው ድረገጽ ላይ "በቃ!!! ዐቢይም ሆነ ተስፋ ያደረግንባቸው የለውጥ አመራሮች አልቻሉምደረጀ ሀ/ወልድ” October 6, 2019" በሚል የምሬቱ ድምጽ በጻፈው ውስጥ እንዲህ ይላል፡-

““ለኢትዮጵያ ስንል ከነ ችግሩም ቢሆን ልንደግፈው የሚገባ መሪ ነው” በማለት በያዝኩት የጸና አቋም ምክንያትም፤ ከሩቅም፣ ከቅርብም፣ ከወዳጆቼም ፣ከደጋፊዎቼም ፣ ክፉኛ ተነቅፌያለሁ። ተዘልፌያለሁ። መስቃ ተሸክሜ ቆይቻለሁ። ይህን ሁሉ ያደረኩት ግን ለሀገሬ ስል እንጂ ለማንም ስል ስላልሆነ -ባደረኩት ነገር አልቆጭም። ምናልባት እቆጭ የነበረው፤ ምንም በጎ ድጋፍ አድርጌ ሳልሞክረው እንዲሁ ብቃወመው ነበር” ይላል።

“መስቃ” የሚል ቃል ምን ለማለት አንደሆነ ባይገባኝም ‘መስቃ’ የሚል የትግርኛ (ምናልባትም ግዕዝ/አማርኛ) እገሌን በመግፋቴ ጡር ደረሰብኝ (ካርማ) ማለት ነው። በአብይ አሕመድ የተገፉ ዜጎች ሲያለቅሱ ለማድመጥ ባለመፈለጌ እና ግፍ ፈጸሚውን በመደገፌ “ስቃ” ደረሰብኝ ማለቱ ከሆነ እቀበላለሁ/ያስኬዳል። በማይገባ ተደሰድቤአለሁ ከሆነ ማለትም እርሱ እንደሚለው ለኢትዮጵያ ስል ተሰድቤአለሁ/ውግዘት ደርሶብኛል ከሆነ ከጥፋቱ እየሸሸ ነው ማለት ነው። ሰዳቢዎቹ እና አውጋዢዎቹ “እየተጓዝክበት ያለው ጉዞ “ስለ ኢትዮጵያ ሳይሆን ሕዝብና አገር እያደፈረሰ ያለውን ግለሰብንና ቡድንን ነው እየተከላከልክለት ያለኸው ተብሎ ስለተወገዘ “ስለ ኢትዮጵያ” ስል መስቃ ተሸከልሜአለሁ ብሎ ማምረር አሁንም ሙሉ በሙሉ ጥፋትን ላለማመን መሸሽ ነው። “አልቆጭም” የሚለው ቃል እራሱ አብይን መደገፉ አልተቆጨም። አልተቆጨም ምክንያቱም የስነ ልቦና ጠበብት “cognitive dissonance” (ኮግኒቲቭ ዲሶናንስ) የሚሉት ሁለት ዛፍ ላይ መንጠልጠል እንደማለት!

ሌላው አስገራሚው ደግሞ የሚከተለው አረፍተ ነገር ነው። እንዲህ ይላል፡-
“ምናልባት እቆጭ የነበረው፤ ምንም በጎ ድጋፍ አድርጌ ሳልሞክረው እንዲሁ ብቃወመው ነበር”   ይላል።

ሲደግፈው የነበረው ሥርዓት ጸረ ሕዝብ እና ሰይጣናዊ መንገድ የሚከተል ሥርዓት መሆኑን ከተገነዘበው በኋላም ቢሆን “ሳልሞክረው እንዲሁ ብቃወም….” ነበር የሚቆጨኝ የምትለዋ ዓረፍተ ነገር አሁንም እራሱን ለማጽናናት የተጠቀመባት ቃል ነች። ያንን ስንፍናውን ላለመቀበል ሲል ቀድሞውንም መግባት እና መደገፍ ያልነበረበትን አደገኛ ሥርዓት መደገፉ “የመቆጨት” ስሜት ማሳደር ሲኖርበት የመረረ ቁጭት ባስደመጠን አንደበቱ “መደገፌ’ ነውር አልነበርም ይለናል።

 ፋሲስቶችንና ናዚዎችን እያንጨበጨቡ ድጋፍ ሰጥተው እና ጫማ ተሳልመው ድጋፍ የሰጡ ሰዎች ‘እንዲህ በማድረጌ አሁን ሆኜ ሳስበው ‘እጸጸታለሁ እቆጫለሁ’ ይቅርታም እጠይቃለሁ” ብለው ማለት እራስን ማሳነስ ሆኖ ስለሚሰማቸው ቀደም ብየ የጠቀስኩት cognitive dissonance” (ኮግኒቲቭ ዲሶናንስ) መረብ ውስጥ ተተብትበው እግሮቻቸው በመራመድ እና በመተብተብ መካከል ያለ በሕሊና ትግል ውስጥ መወጠሩን ያሳያል። ብዙዎቹ እንደዚያ ናቸው። ታማኝ በየነም “ለምን አብይ አሕመድ ጫማ ስር ተደፍተህ ተሳለምክ” ሲባል “አሁንም አልቆጭበትም” ነበር ያለው። የስነ ልቦና ተማሪዎች ምን እያልኩ አንደሆን ይገባችል።  እንዲህ ያሉ ሰዎች ባንድ ሕሊና ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦችን ለማጣጣምና ለማሸናገል የሚሞክሩበት ሁኔታ ሲጋፈጡ የሚያንጸባርቁት ነው። ሲጋራ አጨሳለሁ፤ ግን ባልሞክረው ነበር የሚቆጨኝ” ወይንም “ሲጃራ አጨሳለሁ ለጤናም ጠንቅ መሆኑን እረዳለሁ ግን ጥሩ ምግብ እና እስፖርት እሰራለሁ” እያሉ እራስን ለማሸናገል እንደሚሞክር ”በኮግኒቲቭ ዲሶናንስ” የተወጠረ ሕሊና የሚታይ ድምዳሜ ነው።
የእነ ደረጀ እና የነታማኝ “ባላደርገው ኖሮ ነበር የሚቆጨኝ” (አይቆጨኝም) አባባል የሚመነጨው ምንጩ “ደካማ እንዳልባል” ከሚል ከራስ ላይ ግብግብ ሲገጠም የሚታይ ራስን የመሸንገል ነጸብራቅ ነው።

ለምሳሌ ታማኝ በየነ “እንደራጅ” ከማለት በቀር ምንም ያለው ነገር የለም። ለምን በዛች ቃላት ሊሰናበት ፈለገ? የሚለው አሁንም ከዚያ ኮግኒቲቭ ዲሶናንስ የራስ ፍትግያ ለፃ ያለመውጣት ነጸብራቅ ነው። ታማኝ ከአንድ አመት ከመንፈቅ ረዢም የጭቆና እና አገር የመደፍረስ አሰቃቂ ጊዜ “ዝምታ መርጦ/ አንዳንዴም ሙገሳ እየቸረ” ዛሬ አንዲት አጭር ቃል መርጦ “እንደራጅ” የምትል ቃል ወርውሮ አንባቢውን “ባዶ ቤት” ትቶት መሄዱ የሚያሳን ነገር ዛሬም ታማኝ ቅድም አንደነገርኳችሁ “ልውጣ አልውጣ” የቆመ መንገድ ነው።

ታማኝም ሆነ መሰሎቹ አንድ አመት ተኩል ለብዙዎቹ ጥፋቶች መጎልበት የነታማኝ መሞዳሞድ እንደሆነ ግልጽ ነው። አፋኝ ስርዓት የሚጎለብተው ተከታዮች ሲያገኝ እና የሚሞዳሞዱለት ታዋቂ ሰዎች እና ምሁራን ሲያገኝ መሆኑን እናውቃለን። አምባ ገነን ሥርዓት በነዚህ ታዋቂ ሰዎች ድጋፍ ምክንያት ጊዜ ሲሰጠው እየጎለበተ ጥፋት ያደርሳል። ሽፍታም ጊዜ ሲሰጠው ጉልበት እያገኘ መመከት ከማይቻልበት አድጎ ለያዥ ለመተመልካች ያስቸግራል።  ታማኝ ድሮ በደርግ ጊዜ ምን የሚል ምክር ሲያስታልፍ ነበር? የሚለውን ወደ ታማኝ መዘክር ልውሰዳችሁ።

በዛው ፈታኝ በደርግ ዘመን ወቅት ወያኔና ሻዕቢያ ተባብረው አገር ሲያውኩ ታማኝ በየነ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሜዳ ማይክሮፎን ይዞ በትርቢዩኑ እግርጌ ከጫፍ ጫፍ እየዞረ በጋለ ስሜት እየጮኸና ሕዝብን በጩኸት ስሜት በሚነካ ንግግር እያስነሳ የተናገረውን ከድምጽ ወደ ጽሑፍ ገልብጬ ላስነብባችሁ እና ልሰናበታችሁ፡

“ወትሮም ከዱር ቤቴ ጥረቱ ልፋቱ
ጊዜ መስጠታችን የኛ ነው ጥፋቱ
ያገር ህልውና በሽፍታ ሲደፈር
ከዚህ በላይ ውርደት ምን ይመጣል ማፈር?
ስንቅ እስከሚዘጋጅ አንቀመጥ አርፈን
እንሂድ እንበላለን ዘራፊውን ዘርፈን” (ነበር ያለው)

ውድ የኢትዮጵያን ሰማይ አንባቢዎች ሆይ!
ታማኝ በየነ የተናገራትን “ጊዜ መስጠታችን የኛ ነው ጥፋቱ” የምትለዋን
ምክር የምትጠቁመን ነገር ቢኖር ለአዋኪ ቡድንም ሆነ ለአዋኪ ሥርዓት ጊዜ መስጠት የባሰ ጥፋት እንደሚያስከትል ይነግረናል። ታማኝም ያውቃል። ዛሬ  በአብይ አሕመድ የሚመራው ፋሺስታዊና አፓርታይዳዊ ሥርዓት አንድ አመት ተኩል ጊዜ መስጠቱና በሕዝባችን ላይ ለሕሊና የሚቀፉ ግፎችን እስኪደርሱ ድረስ “ተው ስንላቸው” ጊዜ እንስጠው ሲሉን የማን ነው ጥፋቱ?
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ Ethio Semay)

   
   

  

ቀላሉን ድክመት ማሶገድ ያልቻለ ከባዱን ችግር አያሶግድም፤ ቀጠሮ ይከበር! By Agere Addis መስከረም 26 ቀን 2012 ዓም (03-10-2019) Posted Ethio Semay


ቀላሉን ድክመት ማሶገድ ያልቻለ ከባዱን ችግር አያሶግድም፤
ቀጠሮ ይከበር!
By Agere Addis
መስከረም 26 ቀን 2012 ዓም (03-10-2019)
Posted Ethio Semay
የሰው ልጅ አቅምና ችሎታ የሚለካው ትንሽዋን ችግር ወይም ድክመት ማሶገድ ሲችል ነው።ያንን በተግባር ያላሳዬ ለትልቁ ችግር ብቃት አለው ብሎ ለመገመት ያዳግታል።በመቶ ሜትር እሩጫ ላይ ያለከለከ እሩዋጭ ማራቶንን ይዘልቃል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።በትንሽዋ ተፈትኖ ወድቋልና!
በተመሳሳይ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ከባድ አገራዊ ችግሮችን ለማሶገድ ብዙ ጥረትና ድካም እናደርጋለን፤ከስኬቱ ውድቀቱ እያመዘነብን ሄደ እንጂ ችግሩን እዬቀረፍነው አልመጣንም። ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ዋናው ግን በራስ አለመተማመን፣ ቁርጠኝነት፣ ቃልኪዳንና ቀጠሮ አለማክበር ዋናዎቹ ናቸው።እነዚህ ደግሞ በራስ ውሳኔ የሚሻሻሉና የሚወገዱ ድክመቶች ናቸው።ከፍተኛ ትምህርት ወይም ዕድሜን የሚጠይቁ እውቀቶች አይደሉም።የግል ግንዛቤን እንጂ!
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ላነሳና እንዲወገድ የምሻው ነገር የቀጠሮ ሰዓትን ባለማክበር ዙሪያ የሚታይብንን ድክመት ነው።ጊዜ ውድ ነው፣ጊዜ ወሳኝ ነው።ጊዜ የዕድሜ መለኪያ አሃዝ ነው።በጊዜ ሊያገኙት ወይም ሊያጡት የሚችሉት ነገር ብዙ ነው።መፈጠርና መወለድ መኖርና መሞት የጊዜ ድርሻ ነው።ሁሉም በጊዜው የሚከናወን ሂደት ነው።የእለታዊ ኑሮዋችን በጊዜ ክፍፍል ካልተጠናቀቀ ዕለቱ ትርጉመቢስ ይሆናል።አንድ ቀን የእንቅልፍ፣ የስራ፣የእረፍት፣የምግብ፣የቀጠሮ ሰዓቶች የሚከናወኑበት ዕለት ነው።ቀኑ በነዚህ ክንውኖች ይጠናቀቃል።ሁሉም እለታዊ ክንውን ተራውን ጠብቆ ይጠናቀቃል፣ መጠናቀቅም አለበት።ፈረንጆች የጊዜን ዋጋና ትርጉም ሲገልጹ ጊዜ ወርቅ ነው(Time is Gold)ወይም ጊዜ ገንዘብ ነው  (Time is Money)ይሉታል።እኔ ግን ከዚያም በላይ ነው ብዬ አስባለሁ፤ጊዜ ህይወት ነው።

ኢትዮጵያውያን እንደ አለመታደል ሆኖ የቀጠሮ ነገር አይሆንልንም።ሰዓት አናከብርም።ሆኖም  በውድ ገንዘብ የገዛነው  ሰዓት በጃችን ላይ አስረናል ግን ትርጉምና ጥቅሙን የተረዳነው አይመስለኝም።ወይም ለቀጠሮ የማይሰራ ለጌጥ ያሰርነው አድርገን ቆጥረነዋል ማለት ነው። ሚዜው ብቻ ሳይሆን ሙሽራው የሰርጉን ቀን ፕሮግራም አክብሮ በቦታው አይገኝም፣የተጋባዡ ነገርማ አይነሳ!በሽተኛው የሓኪም ቀጠሮውን አክብሮ በሰዓቱ አይደርስም፤የአገር ጉዳይ ለመወያዬትማ ከሆነ ስብሰባ ከተጠራበት ሰዓት ሁለት ሰዓት ዘግይቶ መድረስ መለመዱ ብቻ ሳይሆን የሚኮሩበት ባህል እዬሆነ መጥቱዋል። የስብሰባው ተሳታፊ ሳይሆን የስብሰባው አዘጋጅና ተናጋሪ እንግዳ ከተሰብሳቢው ዃላ ዘግይቶ እንጂ ቀድሞ አይደርስም።ታዲያ ዘግይቶ በተጀመረ ስብሰባ በቂ ውይይት ሳይደረግ የአዳራሹ ቦታ ሳይዘጋ” በሚል ሩጫ ለብ ለብ የሆነ ፈረሰኛ ውይይት ይደረግና እልባት ሳይኖረው መበተን የተለመደ ነው።

“የአበሻ ቀጠሮ” በሚለው ደካማ ምክንያትና ስያሜ እራሳችንን ከአበሻነት  ነጥለን አውጥተን የሌሎች አድርገን የማዬት ይዘነው የመጣነው ልክፍት  መታረም አለበት።በተለይ እውጭ አገር የምንኖረው ብዙዎቻችን ለምንኖርበት አገር ሕዝብ የቀጠሮ ባህል ባዳና እንግዳ ነን። ስብሰባ ሲጠራ ” አበሻ በሰዓቱ አይመጣም፣ለምን ባዶ አዳራሽ ውስጥ እጎለታለሁ” በሚል ሰበብ ዘግይተን እንደርሳለን።ስብሰባ ትልቅ አገራዊ ወይም ማህበረሰብአዊ ጉዳይን የሚመለከት፣ችግርን ለማሶገድ የሚደረግ  ሲሆን በቦታውና በጊዜው የመገኘት ግዴታ ይጠይቃል።ሆኖም ግን በተደጋጋሚ በዬቦታው  ሰዓት ያለማክበር ድክመት ይታያል።ለትልቁ ችግር ስናስብ  ትንሹዋን የሰዓት አለማክበር በሽታ ግን ለማሶገድ አልቻልንም። ሳናርመው አብሮን የሚኖር ክሮኒክስ በሽታ ሆኑዋል።በራሳችን ተሸክመን የምንኖረውን ትንሹን ችግርና ድክመት ሳናሶግድ ትልቁን አገራዊ ችግር እናቃልላለን ማለት ዘበት ነው።በጊዜ መከናወን ያለበት ጉዳይ ከዘገዬ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው።በአንድ ዘመቻ ላይ በተወሰነው ሰዓትና ቦታ ካልደረሱ ግዳጁ(ሚሽኑ) ይሰናከላል።ለአደጋም ያጋልጣል።የበጋ፣የክረምት፣የጸደይና መኸር ወቅትም ጊዜን ያከብራል፤ጨለማና ብርሃንም እንዲሁ።ሰዓት ማክበር ያቃተን፣የጊዜ ትርጉም ያልገባን እኛ ሰዎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ነን።እዚህ ላይ ሁሉንም በጅምላ ማውገዝ አይገባም፤ቀጠሮና ቃላቸውን የሚያከብሩ አሉ።ለነሱ ክብርና አድናቆት አለኝ።ሌሎቻችን የነሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል።

እባካችሁ ቀጠሮ እናክብር!የሰዓት፣የቀን፣የሳምንት፣የወርና የዓመት  ትርጉሙ ይግባን።ዕድሜያችን የሰከንድ፣የደቂቃና የሰዓት ጥርቅም ወይም ድምር መሆኑን እንረዳ።ጊዜ የሚንቁት የአቡዋራ ክምር አይደለም።የመኖርና ያለመኖር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በጊዜ ገደብ ነው።አፈጣጠራችን ሳይቀር በሰከንድ ውስጥ በሚከናወን አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም ቅንብር ነው።ስለዚህ ጊዜ ትልቅ ትርጉምና ዋጋ አለው።ቃላችንንና ቀጠሮ ስናከብር ኩሩና ሙሉ ሰዎች እንሆናለን።ዘግይተን ስንደርስና ቃላባይ ስንሆን በይሉኝታ  ውስጣችንን እንደሚነዝረንና  እንደምንሰቀቅ አንካድ።ከዚህ ሁሉ በራሳችን ላይ ሂስ አቅርበን እንታረም።ሰዓት የማክበሩን ባህል ወርሰን እናውርስ። በጊዜው መድረስ የማይቻልበት ብዙ አጋጣሚ ይኖራል፤ ድንገተኛ አደጋ፣የትራፊክ ጫና፣የመጓጓዣ መስተጓጉል፣ የመሳሰሉት ያልተጠበቁ ደንቃራዎች ይኖራሉ።ያም ቢሆን ሁኔታውን በመንገድ ላይ እያሉ እድሜ ለዘመኑ ሞባይል ስልክ መግለጽ ይቻላል።

የቀጠሮ ሰዓት በማያከብረው ላይ ማህበራዊ ቅጣት ይጣልበት፣ ዘግይቶ ሲመጣ ለመሰብሰቢያ አዳራሹ ኪራይ የወጣውን ወጭ ለማካካስ የሚረዳ የገንዘብ ቅጣት፣  ወይም  ዘግይቶ የመጣ  የሚቀመጥበት ቦታ ተለይቶ ቢዘጋጅ እራሱን በራሱ እንዲታዘበው ይረዳል።
ቃላቸውንና ቀጠሮ ለሚያከብሩት ሁሉ ክብርና ምስጋና አይለያቸው!
ቀጠሮ ያለማክበር የጋራ ድክመታችንን በጋራ እናሶግድ!ዘግይቶ ሳይሆን ቀድሞ ለመድረስ እንዘጋጅ!
አገሬ አዲስ