Tuesday, April 24, 2018

ወያኔው ኢሕአዴግ ጠ ሚኒስትር ዛሬም በባሕር ዳር ላይ የማይረገጠውን ጥያቄ እየረገጠ ሄዷል (ክፍል 2) ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ)



የወያኔው ኢሕአዴግ ጠ ሚኒስትር ዛሬም በባሕር ዳር ላይ የማይረገጠውን ጥያቄ እየረገጠ ሄዷል (ክፍል 2)
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ)

 እንደምን ሰነበታችሁ። ይህ ጽሑፍ ካለፈው ጽሑፌ “አስገራሚ  አስደናቂም   አሳፋሪም ባጭር የተቀጨው የአታላዩ ጠቅላይ ምኒስትር የማታለለል ችሎታው ላያንሰራራ ላንዴም ለመጨረሻም መቀሌ ላይ ተቀብሯል!” ከሚለው ክፍል 1 የቀጠለ ትችት ነው።አብይ በጎንደር እና በባሕርዳር ከተሞች ተገኝቶ ያደረገው ውይይት ብዙ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል። በሳላም ሰነፍ የሆኑ አስተያየቶችንም ተሰንዝረዋል። (እነኚህ በየ ዩቱብ የሚለጥፉት ዶክተር ተብዎች፤ አብይን ደግፉት፤ከሰማይ የወረደልን አምላክ ነውና ምድሩን ባሕሩን አየሩን ምግቡንም እስኪለምደው ጌዜ እንስጠው፤ እርስዎም ክቡር ጠ/ሚነትዎት እባክዎትን ክቡር ጠ/ሚ አደራዎትን፤ አባክዎትን የሚሉትን አስገራሚ ፓስተር አይሏቸው ምሁራን መላቅጡ የጠፋባቸው የዩቱብ ዶከተሮችን ሳይጨምር ማለቴ ነው)። የገረመኝ ነገር ቢኖር አብይን ለመጠየቅ የተጋበዙ የባሕርዳር ኗሪዎች ጥያቄ ሲጠይቁ ሙሉ በሙሉ ሳይቆራረጥ በደምብ መስማት ችለናል። አስገራሚ ያደረገው ነገር ግን አብይ ለተጠየቃቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች መልስ ሲሰጥ ግን “ሆን ተብሎ”  እየተቆራረጠ ለመስማት በሚያስቸግር አቀራረብ ተቀርጾ “በዩ ቱብ” ተለጥፏል። ማን እንደለጠፈው አይታወቅም ማንስ እንደቀረጸው አይታወቅም ማን አየቆራረጠ እንዲሰማ እንዳደረገ ኣይታወቅም። የኛ ነገር ..የኛ ነገር….ብዙ..ብዙ  ይቀረናል።

በጎንደር እና በባሕርዳር ከተሞች ለወያኔ ኢሕአዴጉ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረቡት አቤቱታዎች አስተያየቶች እና ቡራኬዎች የነዚህ ከተሞች ኗሪዎች ብልህ ኣእምሮ የተመሰከረበት አጋጣሚ መሆኑን ታዝቤአለሁ።ባሕርዳር ከተማ የተደመጠው እማ ደግሞ እጅግ የበሰሉ ያስተሳሰብ እና የአቤቱታ አቀራረብ ምጥቀት የታየባቸው ሕሊናዎች ናቸው። አማራዎች ለ27 አመት በእንደዚያ ያለ ለመስማትም ለማየትም በሚዘገንን የጭካኔ ግፍ ተፈጽሞባቸው እያለ፤ ብሶታቸውንና ውስጣዊ ቁጣቸውን ተቆጣጥረው  ሰብሰብ አድርገው በስሜት ሳይሸነፉ በሳላ ንግግሮችን እና ጥያቄዎችን ለወያኔው ጠ/ሚኒስትር አብይ ሲያቀርቡ አድምጬአቸው የተሰማኝን አድናቆት በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል። እውነትም እነዚህ ዜጎች የጥንታውያን ገዳማት ፍሬዎች መሆናቸውን የሚያሳው አንደበተ ርቱእነታቸውና ያቀራረብ ስልታቸው ያስሰሙዋቸው ስሞታዎቻው በማራኪ ውብ ቃላት ተደግፈው ያለ ምንም መንገራገጭ ሰተት ብለው ወደ ጆሮ ሲገቡ ሄደው የሚለጠፉባቸው ዘጋቢ ግድግዳዎች በቀላሉ የሚደመጡ ለዝንተ ዓለም የማይረሱ ነበሩ።

ያ ሁሉ ብሶት አስሰምተው ጠይቀው ካበቁም ቢሆን አብይ “አማራ አማራ” የምትሉት ነገር ትቼ..የኢትዮጵያን ነገር እንዲህ እያንገበገባችሁ መልሳችሁ አማራ አማራ ስትሉ ታፈርሱታላችሁ!” የሚለውን አስቀያሚ ረገጣው ለኔ ከአስቀያሚም አስቀያሚ መልስ ነበር።

<“ለ27 አመት ሙሉ ወያኔ የሚባል ታጣቂ አክራሪ ብሔረተኛ ከመሰል አክራሪዎች ጋር ተባብሮ በአማራ ላይ ግምቱ በሚያስቸግር ግፍ “የዘር ማጽዳት” ወንጀል ተፈጽሞብናል፡ ኦሮሞዎች ማለትም አብይ አንተ በመራኸው እና በተሳተፍክበት ድርጅት (ኦሆዴድ) በተባለ ወንጀለኛ ድርጅት “ኦኖሌ” የተባለ የጥላቻ ሃውልት በኢትዮጵያ ምድር በአርሲ ውስጥ ተተክሎ በእኛ በአማራ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ዘመቻ ተካሂዷል፡ ለብዙ አማራዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡ የኦሮሞ ወጣቶች “አማራን” እንደ ቀንደኛ ጠላት አድርገው እንዲመለከቱት ያበረታታ የጥላቻ ሃውልት ይፍረስ፡ ያንድ አገር ልጆች በጎጥና በዘር ተካልለን  ዓይን እና አፈር ሆነን እስከመቸ ነው የምንኖሮው? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ባለውለታ ናት ፡ እገለ ወገሌ ሳትል ሁሉንም በየእምነቱ ፊደል ያስቆጠረች አንጋፋ ባለ ውለታ የሁሉም እናት ቤተክርስትያን በዚህ ስርዓት “ግፍ” ተፈጽሞባታል፡ በሃይማኖት እኩልነት በነፃነት ስም እንርገጥሽ ተባለችበት ዘመን ደርሰናል።  በርስዎ ዘመን ይህን እንድያበቃ እንጠይቃለን። ይህ አንዲሆንም አንመኛለን፡ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድም ይጨመርበት፡ የሚናገሩትን በተግባር ከዋለ ‘ቅን ካሰቡ” ሺሕ አመት ያንግሥዎ፡”>  

ብለው ላሉ ብልሕ የዐማራ ብሶት አብየት ባዮች ። እንዴት “አማራ.. አማራ” አትበሉ አማራ አማራ ብላችሁ ኢትዮጵያዊነትን እንደገና ታፈርሱታላችሁ፡ ብሎ መልስ መስጠት ለምን እንደፈለገ ለኔ አስገርሞኛል።

 አብይ “አማራ አማራ እንዲህ ሆኗል፤ አልቋል፤… የሚል አቤቱታ ክስ አልተመቸውም”። እነ መስፍን ወልደማርያም አማራ የሚል ስም ላለማንሳት “አሮሞ፤ትግሬ….” ይሉ እና ከዚያ አማራ ላለማለት (ሆን ብየ ስሙን ላለመጥራት የዘለልኩት) እያሉ እንደሚጽፉት ሁሉ አብይ ደግሞ “አማራ፤አማራ” የምትለወዋን ስም እና ብሶት አልተመቸቺውም። ለምን? የሚል ጥያቄ መልስ ይሻል።  እስከገባኝ ድረስ ‘የእርሱ ድርጅት” (ኦሆዴድ) በወንጀሉ ቀንደኛው ተከሳሽ ወንጀለኛ ድርጅት መሆኑን ስለሚያውቅ ፤ የዘር ማጥፋት ፈጽማችሁብናል ብሎ ለሚጠይቅ ሕዝብ “አማራ ፤ አማራ የምትሉትን ትቼ” ብሎ መልስ እየሰጠ ያለበት ምክንያት ግልጽ ነው። ምክንያቱም እራሱ ወይንም ድርጅቱ በዚህ ወንጀል እየተከሰሰ መሆኑን በደም ስለሚያውቅ ፤ ብሶታቸው እርሱንም ስለሚወነጅል፤ የተቀሰረቺው ጣት ወደ እርሱ እያመላከተች መሆኗን ስላወቀ አልጣመውም። ስለሆነም “ቁጣውን አምቆ” “አማራ አማራ የምትልዋትን ……ትቼ በማለት ለከባዱ ጥያቄ መልስ ላለመስጠት ተገዷል። (ሳይኮሎጂስቶች ይህንን በደም ይረዳቸዋል ብየ እገምታለሁ)፡ ልክ የኦነጉ ወንጀለኛው ‘ሌንጮ ለታ’ ከባንዳው ብርሃኑ ነጋ እና ከነዶ/ር ዜሮ (ጌታቸው በጋሻው) ጋር በየአዳራሹ እየዞረ ስለ ድርጅቱ ወንጀል ሲነገረው ወይንም ለሚጠይቁ ሰዎች ሲጥመው በግልጽ ሳይጥመው “በአግድሞሽ” መልስ እንደሚሰጠው ዓይነት ዘዴ ማለት ነው።

አማራ ጋር ሲደርስ “አማራ፤አማራ” አትበሉ የሚሉ ቡድኖች እና ሰዎች ከጀርባቸው ያለው መነሻ ማወቅ አያስቸግርም። እርግጠኛ ነኝ ኦሮሞዎችን ሲያነጋጋር “ኦሮሞ አሮሞ” የምትልዋትን ትቼ……ብሎ እንደማይላቸው እርግጠኛ ነኝ። ግን ጊዜ በጣለው ማሕበረሰብ በአማራው ላይ ሲደርሱ ግን ሁሉም የተማረውም፤ያልተማረውም ደደቡም ተረባርቦ “አማራ” የሚባል ስም ሲደመጥ (ሲነሳ) አይመቸውም። ወደዱም ጠሉም አማራው ስሙ በማይደበቅበት ሁኔታ አድርሰነዋል (ቢያንስ እኔ ስለ አማራ መብትና መነሳሳት የጮኹኩባቸው ዘመኖች ሲቆጠር ፤ እየተሰደብኩም ቢሆን ረዢም ጉዞ ተጉዘናል) ዛሬ በየከተማው የራሱን ብሶት ማንሳት በድፍረት ወደ ፊት መጥቷል። ይኼው ዛሬ የኔ እና የጥቂት ጓዶቼ ውጤታችን አይተን ተዝናንተን “ሶፋ ላይ ቁጭ ብለን” ቦታውን በኩራት ባለዋናዎቹ ለቅቀን፤  ፊት ለፊት መጥተው እየተጋፈጥዋቸው ናቸው። ይመስገነው ለፈጣሪ እና  ጽናታችን  ሌታየበት ለትግላችን!

<< ‘አማራው ሞቷልቆስሏል? አዎ ሞቷልቆስሏል። አማራ ብቻውን አልሞተም አልቆሰለም ብቻውን ይህች አገር አላቆማትም፡>>፡ ይላል አብይ።

 ወደ መተሳሰብ ከሄድን ብዙ የሚያከራክሩን ነገሮች አሉ። ትግሬዎችን እንደተከራከርኳቸው (ኢትዮ-ሚዲያ ድረግጽ ላይ የተለጠፈውን እና አሁንም በተከታታይ እየቀጠለ ያለው የትግርኛ ክርክሬን ተመልከቱ) አብይንም በሰነድ እከራከረው ነበር ግን እሱን ወደ ጎን ልተወው እና ጥያቄው፡ አማራው በገፍ ተገድሏል ተጨፍጭፏል (በኦሮሞ ምድር)  ነው ጥያቄው ሲቀረብለት የነበረው ጥያቄ። ኦኖሌ የሚባል ሃውልት እኛን የሚያስሰድብና የሚያስገድል ሕጋዊ ፍርድ ቤት ላይ ቀርቦ እሰጥ አገባ ‘ክርክር እና ክስ’ ሳይደረግበት ሕገ ወጥ ሃውልት ቆሟል! እያሉ ነው አቤቱታ እያቀረቡ ያሉት። ወደ አገር ማቅናት ማዞሩ ለክርክር መጋበዙ ለምን አንደፈለገ አልገባኝም። እነዚህ ሰዎች በደማችን አገር አቅንተናል፤ ፊደል አስቆጥረናል ሃይማኖት አስተምረናል ስነምግባር አስተምረናል ሰውን መግደል የወንድ ብልትን መስለብ በሃይማኖት ነውር ነው … ወዘተ…ወዘተ…ብለን መልካም መልካሙን አስተምረናል በአገር አስተዋጽኦዋችን ጉልህ ሚና አለው! ስላሉ ብቻችሁን አላቆማችሁትም፤ብቻችሁን አልቆሰላችሁም ብሎ ክርክር ምን ማለት ነው?፡ መቀሌ ሄዶ መለስ ዜናዊን ጀግና ብሎ ባወደሰበት ርካሽ አድርባይ ምላሱ ሲናገር “ብቻችሁን የተሳዋችሁየቆሰላችሁ ብቻችሁን ተዋግታችሁ ወርቅነታችሁን ያስመሰከራችሁ” ወርቅየዎች ሲላቸው አልነበርም? አማራው ጋር ሲደርስ አማራ ብቻውን አልሞተምአልቆሰለም ብቻውን ይህች አገር አላቆማትም፡”  ብሎ ነገር ትርጉሙ ምንድነው?

አብይ በዚህ አልተገታም፡  ሌላው ካስገረሙኝ መልሶቹ አንዱ የሚከተለው ነው፦
 <“መልካም መልካሙን እናንሳ”> ይላል።

እኔ በጣም እየጨነቀኝ ነበር ንገግሩን ያደመጥኩት። ባሕርዳር/ጎንደር ተገኝቶ ሕዝባዊ ስብሰባ ሲያደርግ መነሻው ምን ለማድመጥ ነው የተገኘው? መልካም መልካሙን ወይንስ ብሶትን? እነዚህ ኗሪዎች ለ27 አመት ማንም ያልተነጣጠረበት በአማራ ላይ የግፍና የጥላቻ ጥቃትና ዘመቻ ተነጣጥሮብናል ነው እያሉት ያሉት። ሕዝባችን እስከ 5 ሚሊዮን ያክል ጠፍቷል (አስገራሚው ደግሞ መረጃው እንዲቀርብልኝ እፈልጋለሁ ከማለት ይልቅ ክሕደት ውስጥ ገብቶ ሲዳክር “በማስረጃ ያልተደገፈ ንግግር በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ፊት መቅረብ አልነበረበትም” በማለት ብሶተኛውን አጣጥሎታል )። በተቃዋሚ አማራ ማሕበራት የተዘጋጁ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። እሱን አልቀበልም ካለም በገለልተኛ እና በራሱ በወያኔ የሕዝብ ቆጠራ ሰነድ የተነገረውና የተዘገበው በቀላሉ ማቅረብ ይቻላል፡)።

አዎን ኢትዮጵያዊነትን በማሞገሱ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ሰዎች የፋሲካ የተሸጠ ከሰማይ የተላከ ስጦታ ነው ብያለሁ። አብይን ሳይሆን “ኢትዮጵያዊነትን እና ፈጣሪን” በማንሳቱ የተደመጠውን ንግግሩ። ግን መቀሌ ሄዶ ኢትዮጵያዊነትን እና ሰንደቃላማዋን ሃይማኖትዋን ታሪኳን አብሮነትዋን ያፈረሱት እና የተዋጉትን ጸረ ኢትዮጵያ መሪዎች እነ መለስ ዜናዊን በጀግንነት አወድሶ የገዛ ንግግርዩን ተመልሶ አፍርሶታል። ለዚህም አብይ እንዲህ ይላል።  

“የኢትዮጵያ አንድነት የማይፈልጉ ሰዎች አሉ፤ አሁን የሚነገረው ነገር የማይፈልጉት ሰዎች አሉ።” ይላል። ልክ ነው። ግን እነማን ናቸው? አንዱ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ወይንም የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ አንድነት የማይፈልጉ ቡድኖች እና ምሁራኖች አንዱ አብይ የሚመራው “ኦሆዴድ ነው”። አይደለም እምዴ? አይደለም ካለን እንከራከር። ሃሳብ ወደ ቃል ተተርጉሞ ቃል በድንጋይ ተጽፎ ሃውልት ቆሞ፤ በአማራ ማሕበረሰብ ላይ ኦሮሞው በአማራ ላይ እንዲያቄም ሆን ተብሎ በነ አብይ መሪነት እና አስተባባሪነት አልፎም ይሁንታ ተሰጥቶት “ኦኖሌ” ሃውልት ቆሟል። አይደለም እንዴ? የዚያ ሴራ አካል አልነበርኩም ይበለን እና በግልጽ ይንገረን እንመነው። ግን ይህ አንድነትን የማይፈልጉ ሰዎች ያቆሙት የጥላቻ ሃውልት “ይቁም” ቢባል እንኳ ኦሮሞዎች እራሳቸው ያደረጉት እንጂ አማራዎች ለማድረጉ ማስረጃ የለም። ይህንን ሃውልት እንዲቆም የፈለጉ “ደናቁርትና የጥላቻ ምሁራኖች” በክርክራቸው ተሸንፈዋል። ኦሮሞዎች እራሳቸው ተከራክረውዋቸው በክርክር ወድቃዋል። ምኒልክ ኦሮመነታቸውን የት  ጥሉት ነው። በኦሮሞ አዝማችነትና በጦርነቱ የተሳተፉት ከ80 እስከ 90 በመቶ ብዛት ለሚኒሊክ የገቡ የኦሮሞ ተዋጊዎች መሆናቸው በሰነድ ቀርቦ የሃውልቱ መስራቾች እና “ሰነፎቹ ተገንጣዮች” በማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም። ምስክራቸው “የሻዕቢያው ሰላይ የጻፈው ልቦለድ መጽሐፍ ጸሐፊው “የኦሮሞ ዜጋነት” የሸለሙት  ”ተስፋየ ገብረአብ ነው። በቃ! ስለዚህ የፍረስ! ነው የሚሉት።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ፦

<< “ጎጃም የውሃ ማማ ምንጭ ሆና ሌሎች በውሃው የመብራት ሃይል ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ጎጃምና ጎንደር ጭለማ ውጦታል ብሎ አብየቱታ ማቅረብ፤ ወጣቶች ስራ ፈት ሆነው በየሹሻ፤ጫት ቤት እየዋሉ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን “ድንጋይ ለቀማ” ተሰማአርተዋል፡ አማራው ሞቷል፡ የጎሳ ፖለቲካ ስርዓቱ ሕገመንግሥቱ ይለውጥ ክልል የሚባል ጠንቅ ነው አራርቆናል በቃ! አማራው ውጣ እየተባለ በገዛ አገሩ ተዋርዷል መሬቱ ተነጥቆ ለሌሎች ነገዶች እና ለሱዳን ተሰጥቷል ስለዚህ መፍትሄ ይፈለግለት! ስላሉ፡ አብይ ይህንን መስማት “አልተመቸውም”። እሱ ሊሰማው የፈለገው ባሕር ዳር (ጎንደር) በመብራት ደምቃ እንደ መቀሌዋ “ሎስ ቬጋስ” አሸብርቃ ሌሊት ሰማዩን አብርታለች የሚል መልካም መልካሙን ሊሰማ ይፈልጋል። አማራ አልተገደለም፥ በሚለዮኖች አልተሰወሩም፤ በትራኮማ አንድ  ሙሉ የገጠር ማሕበረሰብ ዓይነስውር አልሆነም፤ በአልጀዚራ የቀረበው አማራ ማሕበረሰብ ምናልባትም በዓለም የደኸየ ማሕበረሰብ መሆኑን የተገለጸው  ለም አቀፍ ዘገባ ውሸት ነው ፥ እናቶች አምካኝ መርፌ እየተወጉ እንዳይወልዱ አልተደረገም፥ አማራ አልተባረረምመሬቱ አልተነጠቀም፤ ማንንቱ በትግሬዎች እና በሌሎች እየተረገጠ አይደለም፤ ……እንዲሉ “መልካም መልካሙን” ንገሩኝ ነው እየለ ያለው።  እነ አለምነው- መኮንን የመሳሰሉ አማራውን የሚዘልፉ ጓዶቹን እንዲያመሰግኑ ይጠብቃል?

አለምነው መኮንን ምንድነው ሲል የነበረ? አቤቱታ አቅራቢዎች ይህ ሰው እንዳውም ከሥልጣኑ ይውርድ ማለት ነበረባቸው። እንዴት እንደተረሳ አልገባኝም። አለምነው መኮነንያለውን መልሼ ላስታውሳችሁ፦

<’አማራ ማለት “ስንፋጭ” ትምክህት የተጠናወተው ትምክሕትነቱን ያልተወው በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተግባብቶ መኖር የማይችል የሸተተው እግሩ እንዳይሸት ከጫማው ስር ‘የባሕር ዛፍ ቅጠል ያደረግበታል” /ዚስ ኢዝ ቴክኖሎጂ!/………ባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው። ልሃጩን ማራገፍ አለበት! ይኼ ላሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም። ማንኛውም ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መነሻው አማራ ክልል ነው።”>> ይላል አለምነው መኮንን። አማራዎች ከቤንሻንጉል ለማበበራቸው ምክንያቱን ሲገልጽ <“ትምክህተኝነትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው። ያንን ምግብም እየተመገበ ያቅራራል።”> (አለምነው መኮንን - ምንጭ “የዓመቱ ምርጥ ባለጌ ሰው” ጌታቸው ረዳ Ethiopian-Semay https://ethiopiansemay.blogspot.com/2015/09/blog-post.html)


 እያለ ተሰብሳቢ ካድሬዎቹን ሳቅ በሳቅ እያደረገ በሕዝብ ክብር ሲያላግጥ በድምፁ የተቀዳ ዋልጌ ግለሰብ ዛሬም ሥራው ላይ ተቀምጧል። እንዲህ ላሉ ሰዎች በሹመት ላይ ሹመት የሚሾም ጸረ አማራ ሥርዓት አብይ አሕመድ ከሕዝቡ ምን መልካም ነገር ሊያደምጥ ሲጠብቅ ነበር? የተበደለ ሕዝብ ብሶት የባሰበት ሕዝብ ምን መለካም ነገር ሊናገር ሲጠብቅ ነበር? ለ27 አመት ለተጎዳ ሕዝብ መልካም መልካሙን እንነጋገር! ምን ማለት ነው? ክልል የሚባል ከሰማይ የተላክልን ለአማራ ሕዝብ የመጣ መልካም የፍትሕ አስተዳዳር ነውጓድ መለስ ዜናዊ የኛ ጀግና ነበሩ? ሊል ይፈልጋል? ለመሆኑ ምን  ሊሰማ ኖሯል ባሕር ዳር እና ጎንደር የሄደው? 

አብይ እንደሚለው፤- “ኢትዮጵያ ውስጥ ስዞር የታዘብኩት ነገር የኢትዮጵያውያን የስሜት መራራቅ ይገርመኛልይላል።

 ለምን እንደገረመው ለኔ ግራ ገብቶኛል። የኢትዮጵያውያኖች በስሜትና በሃሳብ መራራቅ ማን ነው ምንጩ? እንዲህ እንዲራራቅ ማን ነው ተጠያቂው? አብይ መጀመሪያ ወደ ሥልጣን ሲወጣ ‘ይቅርታ ሲጠይቅ’ ታድያ መነሻው ምን ነበር? ድርጅቱ ስላላራቀን፤ስለገደለን አይደለም እንዴ ይቅርታ የጠየቀው?

አብይ እንዲህ ይላል፤-

“ያለው መራራቅ እንዴት ተደርጎ እንደሚሰበሰብ ይጨንቀኛል።” ይላል።

ለዚህ ነበር እኛ ወያኔ ሲገባ ይህ የመራራቅ ስሜት የሚሰብክ ቡድን የኋላ  ኋላ በሕዝቡ ላይ “መራራቅንየእርስ በርስ የጥላቻን ስሜት ስለሚያመጣ” መሰብሰቡ ሊያስቸግር ነው እና ካሁኑኑ ይህ ድርጅት አትቀላቀሉት፤ አስወግዱት፤ አውግዙት፤ አትከተሉት ስንል የነበረው። ግን እነ አብይ ሊሰሙን አልቻሉም እና “ወያኔን” አድንቀው የወያኔ ወታደሮች ሆኑ! ዘለግ ሲልም የስለላው መ/ቤት አዋቃሪ ሆነ ከዚያም “የወያኔዎች አሽከር” የሆነውን  የጥላቻ የመራራቅና የግድያ  ድርጅት መሪ የሆነውን “ኦሆዴድን” ተቀላቅሎ የዚህ ድርጅት መሪ ሆነ። አሁን ሥልጣን ላይ ሲወጣ፤ ሕዝቡ በመረረው ሰዓት መጥቶ የሕዝቡን መራራቅ እየዞረ ሲመከት “ያለው መራራቅ እንዴት ተደርጎ እንደሚሰበሰብ ይጨንቀኛል” ይላል። አንቺ ያመጣሺው አንቺው ፍቺው!

ሕዝቡ በመረረው ጣራ ላይ ስለመጣህ ምሬቱ ከመጠን በላይ ነው እና አንተንም ማስጨነቁ አልገረመኝም። አንዱን ያዝ፤ ጨክነህ ወያኔዎችን እና ስርዓታቸውን አፍርስ፤የጎሳ ክልሎችን እንዲፈርሱ አደርግ (ተከራከር) (እነ ለማ መገርሳ እና የሮሞ ጤነኛ ክፍሎችን እንዲሁም ሌሎችን አስተባብረህ ግብህን ምራ) አልፈታውም ስትል ግን “ፈቺዎች ይመጡና” በወንጀል ትከሰሳለህ ወይንም ከተገንጣዮች ጋር ትወግናለህ። ብዙዎቹ እንዲዚያ ነው ያደረጉት። አግልግለው አገልግለው፤ ወንጀሉ ወደ እነሱ ሲያዘነብል ወደ ውጭ እየሸሹ “ኦነግን” ወይንም “ኦብነግን” ይቀላቀላሉ። እነ ጁነዲን ሳዶ እና መሰል የኦሮሞ ወንጀለኞች እያደረጉት ያሉ ይህንን ነው። እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ ማንም ግሳንግስ ወንጀለኛን ሁሉ የሚጠራቀምበት ነው (አውጭ አገር ያሉት ተቃዋሚ ተብየ ድረገጾች ራዲዮኖች እና ቲቪ ሚዲያዎች ሳይቀሩ  እነ ጅነዲን ሳዶዎችን ከማጋለጥ ይልቅ እንግዶች እያደረገ ይክባቸዋል) ። አትገባም ማለት የለም። ብዙዎቹ ተገንጣዮች የወንጀል ድርጅቶች ስለሆኑ፤ ተባባሪን ይፈልጋሉ።

የሚገርም ነው።

<“አንድነት የሚመጣው ስንደምር ነው። መደምር ግን ባንድ ጀምበር አይመጣም፤ ተለያይተን ቆይተናል እና……”> ይላል እና ሥልጣን የወጣበት መንገድም “ይህች ሰላማዊ የሥልጣን ሽገግር” ይላታል።

አገር የሚያፈርስ ሥርዓት “በሕገመንግሥቱ” ተደንግጎ ያውም እንዳንደመር አንድ እንዳንሆን ደደቢት በረሃ ውስጥ ተጽፎ፤ በወንጀለኛው ኦነግ ሊጥ “አቡኪነት” ተጋግሮ የተደነገገው ከፋፋይ በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ላይ የዘመተ የስደብ ውርጅብኝ የሰነዘረ የናዚዎች ሕገ መንግሥትን ከሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ተረክቦ ሰግዶ “መርዘኘውን መጽሐፉ” ለሕዝብ እያሳየ ተለያይተን መቆየታችንን እራሱም ጭምር ያስገረመው መራራቅን እንደገና “መራራቅን” የሚሰብከው መርዘኛውን መጽሐፍ በአክብሮት ተቀብሎ “እፈጽማለሁ” ሲል ምን እንበለው?
   ለዚህ ደግሞ “ሠላማዊ” የሥልጣን ሽግግር ይለዋል። አልገረማችሁም?  አንድ መሪ ወደ ሌላ ስርዓት ሲሸጋገር ሌላ ሕገመንግሥት ይጽፋል እንጂ “ያንኑ አከብራለሁ” ብሎ እጅ ነሥቶ ይሰግዳል? የአብይ ሥልጣን ሽግግር ትርጉም ምን ይሆን? የሚገርመው ደግሞ ‘ከኛ የተለየ ሃሳብ ካላችሁ ወይንም ማንም ሰው ካለው እናንተም እኛም ሃሳባችን እናቅርብና አንከራከር….” ይላል። እኛ የሚለው ወያኔ እና እሱ የወከለው ደርጅት ማለት ነው። በሌላ አነጋጋር “ኢሕአዴግ” የሚባለውን ፋሺስቶች ጥርቅም ድርጅትን ነው “እኛ” እያለ ያለው። ለዚህም “ሠላማዊ ሽግግር” እያለ ይቀልድብናል። አንድ ልትዘነጉልኝ የማልፈልገው ነግረ አለ። አብይ ከውስጡ ኢትዮጵያዊነትን ለማንሰራራት ፍላጎት አለው ወይ ? ብትሉኝ በሚገባ ከሌሎቹ የትግሬ እና የሶማሊ ፋሺሰት መሪዎች በበለጠ በጣም በራቀ ስሜት አውንተኛ ስሜት አንዳለው አልክደውም። ግን ከማን ጋር ሆኖ ነው ይህንን ሊያጎለብተው የሚችለው የሚለው ጥያቄ ነው የሚያከራክረን። እሱም ዓላማው ግልጽ ማድረግ አለበት። ለለውጥ ነወ የመጣው “መሠረታዊ የሆኑ” ለውጦች አስቸኳይ እንዲታዩ ያድርግ። ደጋፊ አለው፤ ተባበሪዎች አሉት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዘዎቹን ንግግረሮቹ ለገበያ ቀርበው ተወድደውለታል ስለዚህ ወያኔን የሚፈራበት ምን መንገድ አለ? ሕዝብ ከጎኑ ቆሟል! ምን ይጠብቃል? “ቀስ በሉ ዝግ በሉ” መልካም መልካሙን እንነጋገር…..” ምን ማለት ነው?
    
(አማራ አማራ የሚለውን ብሶት) እሱ <<“ከረር ያለው ስሜት” (በሚል ይገልጸዋል) ፡ “ረገብ አድርገን ወደ ውስጣችን ብናይ ጥሩ ነው”>>

ሲል ብሶት የባሰውን ሕዝብ ወደ ውስጡ እንዲመለከት መክሯል። እንግዲህ ወደ ውስጥ እንዲመለከት ማለት ወደ ልባችሁ ተመለሱ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ከልባቸው ወጭ አልሄዱም። በነገዳችን ስማችን እየተጠቀሰ “አማራ አንተ ሽንታም ፤ገና እናሳያሃለን” እያሉ ትግሬ ገራፊዎች የወንዶችን ብልት እየቀጠቀጡ እንዳይወልድ አኮላሽተውታል፡ ሴት እህቶቻችን አማራ ስለሆኑ እርቃናቸው ወጥተው አንዲገረፉና አንዲዋረዱ ተደርጓል፡ ይህ ይቁም ነው እያሉ ያሉት። መልካም መልካሙን  ከየት ተከስቶ ነው፤ሕዝቡ ወደ ውስጣችሁ እዩ፤ መልካም መልካሙን እንነጋር የሚለው?

ከልባቸው ውጭ ቢሆኑ ኖሮ አበሮ የተቀመጠው አለምነው መኮንን እና፤ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የመሳሰሉ አድር ባዩ እና ወንጀለኛው ብእዴን መሪዎችን በጥይት ይፈጃቸው ነበር። የሰደቡትንም እሺ ብሎተቀብሎአቸው፤ ብሶት የባሰውን አንጀቱን ተቆጣቀጥሮ አዳራሽ ውስጥ ተገቢውን ጥያቄና ብሶት ነው ያስተጋባው። “ወደ ውስጣችሁ እንድታዩ” ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም። አኖሌ ሃውልት አፍርሰው ማለት “ስሜታቸውን እንዲያረግቡ” መምከር አልገባኝም።

እንዲህም ይላል፦

<“ይኸ መንግሥት ንግግር አሳምሮ ወሬ አሳምሮ ተግባር የለውም ብለው የሚያስቡ “አትሳሳቱ” ነው የምለው።ታስረው የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች ታስረዋል ተብሎ ሲጮህ የነበረውን ፈትተናል! ተግባር ነው ይኼ! ይህ ተግባር ነው።ቁጭ ብሎ በቲቪ ለሚሰማው ቀላል ነው።እንዴት መጣ? በድርጊቱ የተሳተፉት ያውቁታል።የመጣውን ሁሉ እያረካከስን፤ የመጣውን ሁሉ እያወዳደቅን፤……..”>  የሚለው ንግግሩ አሁንም ገርሞኛል።

እርግጣ ነው ያስመሰግናል፤ ግን ሙሉውን ስዕል ይገልጸዋል ወይ? ለመሆኑ በምን መመዘኛ ነው አሁን የተፈቱ ጥቂት ሰዎችን በሺዎቹ በየእስር ቤቱ ታጉተረው እየተገረፉ ያሉትን መለኪያ የሚሆነው? አንዲት ቀንም ቢሆን እዛ ውስጥ መታጎር የሌላቸውን ሁሉ አሉ። አገሪቱ የምትፈልጋቸው እና ያስተማረቻቸው የታወቁ የልብ ጥገና ዶክተሮችን ሁሉ አፍኖ እስር ቤት የሚጥልን ሰርዓት እንዴት ነው አብይ ይህንን ጥቂቶች የመፍታትን መመዘኛ የሚያደርገው? ጥቂቶችን መፍታት ያራከሰ የለም፡ ግን ተፈቺ እስረኞች በተፈቱ  በማግስቱ እያታፈኑ ወደ እሰር የሚወረውራቸውን “የጎስታፖ” ቡድን አብይ በምን ይገልጸዋል? ተፈትተው ወደ ውጭ ለሥራ ጉዳይ ለሚንቀሳቀሱ ፓስፖርታቸው በቦሌ አየር ማረፊያ አንዲታገድ ማድረግ ምን እሚሉት ነፃነት ነው? በኛ እና በአብይ ያለው ልዩነት እኛ ሥርዓቱን የምንተረጉመው “ፋሺስት፡ ነው እንላለን፡ እሱ ደግሞ ጥቂት ሰዎች ፈትተናል እና ዲሞክራት ነን እያለን ነው። ለዚህ ምን እንበል?

አማራ ተበድሏል፤ የዱር ባሕር ዛፍ ደናችን ተዘርፎ እኛ ተከልክለን፤ ወደ ትግሬ እየተጫነ ነው፡ እና አማራ በመሆናችን ተጠቅተናል አገር ያቀናውን አማራ “ነፍጠኛ”  መለያ ስም ተለጥፎበት ለጥቃት ተጋልጠናል ብሎ ላለ ሆድ ለባሰው አቤት ባይ።  እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል።

“አማራ አማራ የተባለውን ትቼ፤ ለሁላችን ፍትሕ ያስፈልገናል፤ዲሞክራሲ ያስፈልገናል፤ኢትዮጵያውያን በሕግ የምንዳኝበት ሥርዓት የሚል ከሆነ እቀበላለሁ። “የኛ ብቻ” የሚል እንዳይሆን።>> እነዚህ ሰዎች እውድየውም ላይ በግልጽ እየተናገሩ እንደተደመጡት “ከማንም ዜጋ እኩል እንድንታይ” ፍትሕ ይሰጠን ነበር ያሉት እንጂ “የኛ ብቻ” ብለው ሲሉ የተደመጡበት አንዲት ዓረፍተ ነገር አልተሰማም። ለኛ ብቻ አንዳይሆን፤አማራ አማራ የሚለውን…… ብሎ ማሳነስ ፡ጠባብ አመለካከት ሆኖ መተርጎም “መነሻው” ምንድ ነው?

<“የጠፋ ነገር ካለ፤ ይቅር ተባብለን”> ይላል አብይ። ካለ ብቻ ሳይሆነ “አለ”። እንዲህ ማለትም ጥሩ ነው። ግን እነሱም የሚሉት እኮ የጠፋ ብቻ ሳይሆን አንተ ያቆምከውን የፈረምክብት ፎቶግራፍ የተነሳህበትን ዛሬም ህያው ሆኖ ለጥፋት ቆሞ ያለውን የጥላቻ ሃውልት “አኖሌ” እና በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከተሞቹና ገጠሮች የቆሙ በርካታ የጥላቻ ሃውልቶች ይፍረሱ ከዚያ ይቅር ይቅር እንባባል፡ ካልሆነ ሃውልቶቹ ቆሞው እንዴት “የይቅር ይቅር የቃላት ሽምገላ እንቀበል” ነው እያሉ ያሉት። ይህ ትከክለኛ አባባል ነው!

ለጠቅ ብሎም ፤ <“ከእነ ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎች ጓዶች ጋር ተረባርበን መልካም ነገር ማምጣት እንችላለን” ይላል። እነ ገዱ እና ጓዶቹ የጥፋት ምንጮች እና በአማራ ላይ ብትር ሲወርድ ምንም ያላደረጉ የውም አማራውን መልሰው ሲዘልፉት የነበሩ የወያኔ አሽከተሮች ናቸው እና ከላይ እስከ ታች ያሉትን በሕዝባዊ አስተዳዳሪዎች ይተኩልን እያሉ ነበር ሲጠይቁት የነበሩት። ከነ አለምነው መኮነን እና ደመቀ መኮንን ፤ ከነ በረከት ስምኦን እና የደቡቡ ሰው አዲሱ ለገሰ…..ትብብር እንዴት ተብሎ መልካም ነገር ሊመጣ ይችላል። 27 አመት የችግሩ ምንጮች እነዚህ ነበሩ። አሁን ድግሞ አብይ ‘እነሱ ጋር ተባብረን መልካም ነገር ማምጣት ይቻላል” ይላል። ይልቁኑ የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው አስተናግድ እና ስምህን አሳድስ እንጂ በነበረው ቦይ እየተጓዝክ “እኛ” ኢሕአዴጎች የሚለው የሸተተ ግም ነገር ለ27 አመት አፍንጫችንን ሲያስከፋ ስለነበር “እኛ ኢሕአዴጎች” የሚለው ዳግም ልንሰማው ኣንፈልግም።

 አመሰግናለሁ - ጌታቸው ረዳ