Friday, October 10, 2014

ትችት በገብሩ አስራት መጽሐፍ ላይ 

Fascist Italian Incorporation Inside Eritrea of Gondar Territory North of Anghereb , 1936 (source Aleme Eshete)
 

TPLF or its consultants have done the necessary research, and have been good at copying Fascist tribal maps and borders. In this respect the most striking reproduction of Mussolini’s Fascist Italian colonial map is that of the transformation of the Fascist map of Eritrea (including Tigrai) as the map of Tigrai alone, (Source Aleme Eshete)
ትችት በገብሩ አስራት መጽሐፍ ላይ

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ)

ክፍል 1
ትችቱ በመጽሀፉ ላይ የተካተቱ የተለያዩ በርካታ ጉዳዮችን ስለሚዳስስ ጊዜ በመውሰድ በተለያዩ ክፍሎች ስለሚቀርብ ተከታተሉኝ። በመጀመሪያ ገብሩ አስራት የጻፈው “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” (2006 ዓ.ም) የተሰኘው ባለ 516 ገጽ መጽሐፍ በርካታ አገራዊ እና ድርጅታዊ ታሪክ ያካተተ ሰፊ ትንተና አድርጐ ለሕዝብ ማቅረቡ አመሰግነዋለሁ። ሌሎቹም አንዲሁ ካሁን በፊት ያላወቅናቸው፤ ያልተነገሩ የህወሓት ወንጀሎች የሚያጋልጡ ሰዎች አንዲመጡ ይረዳል። አስገደ፤ገብረመድህን እና የመሳሰሉ ሰዎች ከገብሩ በበለጠ የድርጅቱ ምንነት እና ከባድ ከባድ ወንጀሎችን አስጨብጠውናል። እነሱም ምስጋና ይገባቸዋል።

በመጽሐፉ ላይ በስፋት የተዘረዘሩ የድርጅቱ/ የህወሓት/ አንዳንድ ምስጢሮች እና አፋኝ ባሕሪ ካሁን በፊት በአንዳንድ የድርጅቱ ታጋዮች በመጽሐፍም፤በመጽሔትም፤በኢንተርኔትም እንዲሁም በራዲዮ ቃለ መጠይቆች ተገልጸው የነበሩ ባይሆኑ ኖሮ፤ ለጆሮአችን አዲስ ሆኖ አስገራሚ እጹብ ድንቅ የሚል መጽሐፍ ይወጣው ነበር። አርግጥ አሁንም ያም ሆኖ ያልሰማናቸው ምስጢሮች ተካትተውበታል። ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ አንደብዛቱ ለማንበብ አንደማይሰለች በየምዕራፉ የተመለከቱ ጉዳዮች አቀራረባቸው  ቀለል ባለ ትንተና በመቅረቡ መጽሐፉ ተነባቢ አድርጎታል። ደራሲው በታጋይነት እና በአመራር ደረጃ የተሳተፈበት ድርጅት በተሓህት ውሳኔ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተፈጸመ ደባ፤የባሕር ወደብ ማሳጣት፤ዲሞክራሲ፤ የሕዝቡ አንድነት በማደፍረስ ሂደት እና የጎሳዎች ግጭት እንዲስፋፉ የፈጸማቸው ወንጀሎች በግልጽ በማስቀመጡ መጪው ትውልድ ምን አንደተፈጸመ የሚያይበት ምሁራዊ ትንተና ያካተተ ጠቃሚ መጽሐፍ ነው።
ስሕተት
ያም ሆኖ፤ ከላይ አንደተቀስኩት በመጽሐፉ የተካተቱ ጉዳዮች አሉ። በርከት ያሉ ድርጅቱ የፈጸማቸው “ወንጀሎች” ለመግለጽ ደራሲው የሄደበት አጠቃቀም “ወንጀል” የሚል ቃል ሳይሆን “አሁን መለስ ብዬ ስመለከተው “ሰህተት” አንደሆነ እገነዘባለሁ”፤ በማለት “ስህተት” በሚል ቃል በተደጋጋሚ የተለያዩ የተፈጸሙ ከባድ አገራዊ ወንጀሎችን አቅልሎ በ “ስሕተት” ይመዝናቸዋል ። ለምን አንዲያ ሊሆን አንደቻለ ደራሲው የመግለጽ ሓላፊነት አለው።


ይህ አባዜ/አቋሙ በመጽሐፉ ብቻ ሳይሆን ካሁን በፊት በሰጣቸው ቃለ መጠይቆችም ጭምር “ስሕተት” የሚለው ይህንኑ ቀለል ያለ ቃል ሲጠቀም በተደገጋሚ ተደምጧል። ለማስረጃ ያህል ከጥቂት አመታት በፊት ከሪፖርተር ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ስንመለከት “…..As a result, we've committed numerous mistakes with horrendous consequences .When it comes to legal responsibility, I share the responsibility for the mistakes committed by the regime as long as I was in power.”  ይላል።
ጠላት
ገብሩ አስራት ተቃዋሚው ወያኔን (ወያኔ አትበሉት ተ.ሓህ.ት በሉት ይለናል፤ ለዚህ ሂፕክሪት የቃላትና የትርጉም ጨዋታ በሌላኛው ክፍል እመለስበታለሁ) በጠላትነት ሳይሆን መፈረጅ ያለበት “በአምባገነን” ስም መጠራት አለበት ይላል።

ይህንኑ ሲያብራራ አንዲህ ይላል፦


“ኢሕአዴግ የሚቃወሙትን ድርጅቶች ጠላት የሚል ስም ቢሰጣቸውም ተቃዋሚዎች፤በተለይም መድረክ፤ ኢሕአዴግን ከኢትዮጵያ አንደመነጨ የአገርን ጥቅም እንደማያስጠብቅ አምባገነን ሃይል ያዩታል አንጂ ጠላት አይሉትም።” (ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ፤ ገብሩ አስራት፤ ገጽ 454)። ደራሲው የመድረክ አባልና አመራር መሆኑን ብዙዎቹ የምታወቁ ይመስለኛል።


ደራሲው በመጽሐፉ ላይ በተደጋጋሚ በሰፊው ስለ ሻዕቢያ ባሕሪ እና ምንነት ሲገልጸው “እንደጠላት” ነው። ጠላት በመሆናቸውም በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙዋቸው በርካታ ጥቃቶችና ወንጀሎች በድብቅ እና በግልጽ ፈጽመዋል። ለዚህ ደግሞ ተባባሪው “ተሓህት” በሌላ ስሙ (“ኢሕአዴግ” በማለት ገብሩ የሚጠራው ) መሆኑን ገብሩ ስለ ድርጅቱ የቅጥረኛነት እና በአገር ጥቅም ላይ የአጥቂዎች ተባባሪነት ባሕሪው በሰፊው ገልጿል። ሆኖም ገብሩ በዚያ ሁሉ የጠላት ስራ ውስጥ ህወሓትን በሰፊው ሲወነጅል “የኢትዮጵያ ጣላት” ነው ለማለት ግን ከብዶታል።


በዚህ ረገድ በርካታ አገር ወዳድ ኢትዬጵያዊያኖች ከገብሩ የሚለዩት የወያኔ መሪዎች ተግባራዊ ያደረጉት ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የፋሺስት ጣሊያኖች የጎሳ/የቋንቋ አስተዳደር መርህ/ፖሊሲ በአገራቸው በዳግማይ ወያኔዎች የመንግሥት ዘመን “ሥራ ላይ” ከዋለ በሗላ ጀምሮ ነው “የወያኔን ሥርዓት” ጠላት ነው ብለው የፈረጁት።


ገብሩ አሁን ያለው የከፋፍለህ ግዛ ቋንቋን መሰረት አድርጐ የተዋቀረ  “ወያኔዊ አፓርታይድ” (በገብሩ ትንታኔ “አምባገነን” ይለዋል) አስተዳደር ለወደፊቱ አንዳንድ ጉድለቶቹን አስወግዶ ‘ትንሽ’ ማሻሻያ ከተደረገለት፤ለወደፊቱ “ብሔር ብሔረሰቦች” ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን የሚያስከብር “እፁብ ድንቅ የሆነ ዲሞክራሲ ነው” የሚል እምነት አለው።

 “ብሔር፤ ብሔረሰብ” ምን ማለት አንደሆነ ገብሩ በመጽሀፉ ባያስረዳንም፤ እውቁ የታሪክ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የነበሩ ሟቹ ፕሮፌሰር ዓለሜ እሸቴ በዚህ ላይ የሚሉት ነገር አላቸው። ይህ እነ ገብሩ ለኢትዮጵያ ያስተዋወቁትን “ፌደራላዊ የጎሳ አስተዳደር” የተቀዳው  Mussolini’s “Legge Organica” or “Basic Law” or Charter and Constitution drawn for the conquered Ethiopia in June 1936 was an instrument of “divide et Impera” (ከፋፍለህ ግዛ/divided and rule) following Prochazka ‘s strategy of tribal dismemberment.-ነው ይሉታል። በተግባር የታየው ይህ ግራ ዘመም የኰሚኒስቶች እና የፋሺስቶች “ክልላዊ” አስተዳዳር በ22 አመት ውስጥ ብዙ ጉዳት አንዳደረሰ ህያው ምስክሮች ነን። በዚህ መርህ እየተመራ አማራውን ማአከላዊ ጠላት አድርጎ ወደ ኦሮሞዎች እና ደቡቦች አንዲሁም ሶማሌዎች እና አደሬዎች በማዳላት ሰፋፊ መሬቶች እና ትላልቅ ከተሞች ለኦሮሞዎች ሲያድል አማራው አስተያየት አንዲሰጥ አልተፈቀደለትም። ከውሳኔው አንዲገለል ለማድረግ በተንኮል ኤርትራኖች እና ትግሬዎች አንዲሁም አገዎች የሆኑ ግለሰቦች የአማራ ሕብረተሰብን እንዲወክሉ አድርጓል።
ዲክታቶር ምን ማለት ነው።
በአማርኛ ቀጥተኛ ትርጉሙ ውሰኔዎችን በራሱ እየወሰነ የሌሎችን አስተያየት የሚጨቁን፤ በጉልበት የመንግሥትን መንበር የተቆጣጠረ ማለት ነው። እንግሊዝኛ ትርጉሙ ስንመለከትም A ruler with a total power over a country, typically who has obtained power by force. ይላል።
ላት ሲባል ምን ማለት ነው?
ጠላት ማለት አገርን፤ሰውን፤አካልን የሚጻረር፤የሚያወድም የሚበድል እስከ መግደል የሚደርስ፤ህልውናን የሚፈታተን፤ሰላም የሚነሳ “ተፃባኢ” ማለት ነው (ቀለል በኔ ትርጉም)። አንግሊዝኛው Enemy is a person who is actively opposed or hostile to someone or something. A hostile nation or its armed forces or citizens especially in time of war. A thing that harms or weakens something else. Harmful or deadly. ይህንን ‘የዲክሽኔሪ‘ ትርጓሜ ስንመለከት  ከተዘረዘረው ትርጉም ወያኔ የባሰ ተፃባኢ ሆኖ ስላገኘነው፤ወያኔ አምባገነን ብቻ ሳይሆን harmful የሆነ deadly ጠላት ጭምር ነው የምንለው ለዚህ ነው። የገብሩ እና የኛ ትርጉም ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው።


ወያኔ ለምን ጠላት ተባለ?
 ጣሊያኖች ያቀዱትን ኦርቶዶክስን እና ብሔራዊ ቋንቋችን አማርኛን እና የአማራ ማሕበረሰብ የማጥፋት ዘመቻ እውን በማድረጉ፤ በመንግስት ደረጃ ተቀምጦ አገሪቱን ለማበጣበጥ “ኢንተርሃሙዌ” ቅስቀሳ ማካሄዱን (ይህ ደግሞ ገብሩ በምጸሐፉ በገፅ 434 ላይ ነግሮናል) ስታገናዝቡት፤


አማራውን በጠላትነት የመመልከት ዘመቻው እና በተግባርም አማራውን የማጥፋቱ ማሕደር/ሪኮርድ ስናገናዝብ፤ክርስትያኖች የሆኑ የክርስትና ማተብም ሆነ ባንገታቸው የክርስትና ምልክት አንዳያጠልቁ ቅስቀሳ እና አዋጅ አንዲወጣ በከፍተኛ ስልጣን የተቀመጡ የወያኔ “ቡችዬዎች” ሰሞኑን የዘረጉት “አዲስ” ጸረ ኦርቶዶክስ ዘመቻቸውን  (በነገራችን ላይ ይህንን አዲስ ጸረ ኦርቶዶከስ ሽብር ስትሰሙ ወደ አስፈሪው የ1991 ዓ.ም የወያኔ ቻርተር አዳራሽ በድንገት ወደ ሗላ ጎትቶ አልወሰዳችሁም? ይህ ስትሰሙ “ሐሰን ዓሊን” አላስታዋሰችሁም?) ስናገናዝብ፤


የአማራን ሕብረተሰብን አንገት “በተለይ ህፃናትን፤እርጉዞችን እና ዓይነስውራን አረጋዊያንን” ከወያኔ/ከኦነግ/አብነግ/ከእስላመዊ ጽንፈኛ ጂሃዲስት “ቢላዎችና ጎራዴዎች” የአንገት ቆረጣና የጅምላ ግድያ ለማስጣል በግምባር ቀደም የቆሙትን ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን የሓሰት ሰነድ አዘጋጅቶ ከሌላ ማሕደር ፌርማቸውን ገልብጦ ወንጀል አንደፈጸሙ አስመስሎ ወደ ወንጀል ሰነድ በማገናኘት፤ በጨለማ እስር ቤት አስገብቶ መጨረሻ በሰበቡ አንዲሞቱ የማድረጉን ወንጅል ስታገነዝቡት፤


የመምህራን መሪው ፕሮፌሰር ታዬ ወልደሰማያት 5 ዓመት በጨለማ አጉሮ በሃሰት ወንጅሎ ማሰቃየትን፤ አሰፋ ማሩን በግፍ፤ በደህንንቱ ፈዳያን/ነብሰገዳዮች አሰማርቶ መግደልን ስታገናዝቡት፤


ያለ ፍርድ በማን ይጠይቀኛል ፋሺስታዊ ግፍ የኢሕአፓ አመራሮችን በስላዮች መረብ ተጠቅሞ አዘንግቶ በማፈን በግፍ ከሕዝብ ዓይታ ሰውሮ የረሸናቸው፤በቅርቡ በገብሩ አስራት መጽሐፍ አማካኝነት ይፋ የሆነ ይህ መረጃ የተገለጸልን ወደር የለሽ የጭካኔ ተግባራቸውን ስታገናዝቡ፤


በትግራይ በረሃ አዛውንቶችን በእሳት ለብልቦ ሲያሰቃይ የነበረውን እና ስልጣን ከያዘ ወዲህም ብዙ ዜጎች በዛው መልክ ማሰቃየቱን ስታገናዝቡ፤


ጋዜጠኞችን በሽብርተኛነት ወንጅሎ ማሰቃየቱን ስታገናዝቡት፤


የባሕር በር ለጠላት ፈርሞ መስጠትን እና እስከ ተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድረስ ሄዶ ለኤርትራኖች ጥብቅና ቆሞ “ወደብ አንድናጣ” ከህወሓት መንግሥት የተጻፈ “በታላቁ ሴራ” መርሃግብር የተከናወነ በደብዳቤ የተደገፈ መረጃ ስታገናዝቡት እና ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ ያላቸውን ፍቅር ስታገናዝቡት፤


ኢትዮጵያን በትግሬዎች ቁጥጥር የማዋሉን ዓይን ያወጣ የጥቅምና የሥልጣን ወረራ እና አድልዎ ስታገናዝቡ፤


ታሪካዊ ማስለጠኛ ጣቢያዎችን፤ገጠሮችን፤ጎዳናዎችን፤አደባባዮችን፤ወንዞችን፤የምርምር ተቛማትን፤ ተራሮችን፤ በታጋዮቹ ስም ወይንም በተገንጣይ ቡድኖች ውትወታ እና ሴራ የከተሞች ስም አዲስ አበባን ጨምሮ “ፍንፍኔ” ተብሎ እንዲሰየም ያደረገው ወንጀሉን ስታገናዝቡት፤


ብዙዎቻችንን ያስገረመው የወያነ የጥላቻ ዘመቻው የታየበት “የሃይለስላሴ ውጤት” የሆነውን “የአፍሪካ አንድነት ሕብረት ምስረታ” ሽልማት አሳልፎ ለጋናውያን ሰጥቶ የሃይለስላሴን ሃውልት አንዳይቆም የማድረጉን ሴራው ስታገናዘቡት፤


 ‘ዜጋ’ የሚለው “ጎሳ” በሚል ስም በመተካት “የማንንት መታወቂያ” ለሕዝቡ በማደል ለመጻኢ ጥፋት በኢንተርሃሙዌ የጎሳ ግጭት አንዲጨፋጨፍ ያቀደውን ማሕደሩን ስታገናዝቡት፤


ኦነግ እና ወያኔ ተመሳጥረው አማራውን ለማስጨፍጨፍ እና አራዊት አድርጐ በዓለም ዓይን እና ምንም በማያውቀው አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ዓይን “ጡት ቆራጭ” ነበር እንዲባል የጥንት 16ኛው ከ/ዘመን ጋላዎችን (ዛሬ ኦሮሞች ነን የሚሉ ከተለያዩ ጎሳዎች ደም የተዳቀሉ የዛሬዎቹ ኦሮሞ ዜጎቻችን) ባሕሪ/ባሕል ወደ አማራው በማስታከክ ለዘመናት እየተጋባ ተፋቅሮ፤ተቻችሎ የኖረውን አማራውን እና ኦሮሞ ህዝባችንን ለማፋጀት “አኖሌ” የሚል ሃውልት በማቆም፤ መጪው የኦሮሞ ትውልድ (ከሰማይ የወረዳችሁ ከምድር ፍጡራን ጋር ያልተዳቀላችሁ ከ“ንፁህ” የኦሮሞ ደም የተቀዳችሁ፤ኦሮሚያ የሚባል “የሌላ አገር ዘጎች”  ናችሁ ብለው በውሸት ለሚሰብኳቸው ወጣቶቻቸው) በአማራው ላይ  ጦርነት እንዲያውጅ፤ ጥላቻ ይዞ አንዲያድግ ለማድረግ የተፈጸመው አጅግ ዘግናኝ የሆነ የፋሽስቶች ፕሮፓጋንዳቸውን ስታገናዝቡት፤


እንዲሁም የአገራችን ሰፋፊ ለም መሬቶች በርካሽ ለዓረቦች፤ለህንዶች፤ለቻይና…ወዘተ የማደሉን ድርጊቶቹን ስትገነዘቡ፤ ድርጅቱ የፈጸማቸው ለመቁጥር የሚያሰለች በርካታ ወንጀሎቹ  “ጣልያን” ከፈጸመው ወንጀል በባሰ መልኩ “የጠላት ድርጊት” በመፈጸሙ እና  ለወደፊቱም ሕዝብ የሚያፋጅ መንገድ “የቀየሰ” ድርጅት ስለሆነ ‘ተሓህት’ ጠላት ብቻ ሳይሆን በኮሎኒያሊስቶች እንድትያዝ ቀጥተኛ ተባባሪነት እና የመሪነት ሚና የተጫወተ ቡድን ከመሆን አልፎ፤ ኢትዮጵያ የ100 አመት ዕደሜ ያላት አገር ነች ብሎ የጠላቶች እና የተገንጣይ ቡድኖች ፕሮፓጋንዳ በቀጥታ አንግቦ የአገሪቱን ክብር በዓለም ፊት በማዋረዱ እና ሕዝቡ ማንነቱ፤ገድሎ፤ባሕሉ እና ሞራሉ አንዲኰስስ በማንንቱ ዘመቻ ያካሄደ ድርጅት ስለሆነ ገብሩ እና ድርጅቱ (መድረክ/ዓረና) ጠላት ከማለት ቢሸማቀቁም፤ በእኛ በኩል ወያኔ/ተሓህት ጠላት ነው ብለን ማለታችን ሕጋዊ ትርጓሜ ያለው ትክክለኛ እና ምክንያታዊ/ሪዝናብል መሆኑን ኢትዮጵያዊያን የጠላት ትርጉም ምንነት ግንዛቤ አንዲኖራቸው በዚህ አጋጣሚ አሳስባለሁ።


በዲክታቶር እና በጠላት የሚፈረጅ ሥርዓት ትግሉ የሚከተለው ፈር እንደዛው ልዩነት ስላለው ኢትዮጵያዊያን ትግሉን የሚያዩበት መነፅር አስተካክለው አንዲያዩ ይረዳቸዋል። ስለሆ በሁለቱ ላይ ልዩነት ስንመለከት ትግሉን ያራዝመዋል ወይንም ያፋጥነዋል።
 
ገበሩ አስራት በዚህ ደካማ ፍልስፍናው ወያኔን “አምባገነን” መንግስት እንጂ “ላት” ብለን ከጠራነው “መድረክ ኢሕአዴግን ላት ቢያደርገው ኖሮ የሚከተለው ስትራቴጂም  የመጠፋፋት(Zero Sum Game) እንጂ ፉክክር አይሆንም ነበር።” የሚለውን ለወያኔ ርህሩህ ፓለቲካ የማሳየቱ “ሰላማዊ ቅዱስነት እና የፖለቲካ ፉክክር” ትንተናው የሚያሳየን፤ አሁንም ገብሩ አስራት ከድርጅቱ ጋር ሆኖ የፈጸመው ከባድ ብሔራዊ ወንጀችን "ስሕተቶች/mistakes/" በሚል ትርጓሜ ስለሚያየው ድርጁትን “በጠላትነት” ከመፈረጅ “አምባገነን” ብለን አንጥራው የሚለው አባዜው ከዚህ ትንታኔው የተነሳ አንደሆነ ግልጽ ነው።


ወያኔ ኢትዮጵያን ሲገድል “እንቁላል ለመብላት ዶሮዋን መግደል” በሚል የስልጣን ጉጉት እና በሸዋ አማራ ጠላቻነት አንግቦ የተነሳበት ጉዞ ስንመረምር የተጓዘው ጉዞ ፍጹም የጠላት ጉዞ መሆኑን ብዙዎቹ ይስማመሉ። አንዳንዶቹ ወያኔ ጠላት አይደለም ሲሉ መነሻቸው፤ ጠላትነቱን ላለማስተወቅ ሲል አንዳንድ በጐ የሰራቸውን አንደማስረጃ ይዘው ይሟገታሉ። ይህ ደግሞ የላሜ ቦራዋን አራቱን ጡቶቿን አልቦ ለራሱና ለተከታዮቹ ወተቷን ለመጎንጨት እንዲያመቸው የቀየሰው ዘዴ መሆኑን መረዳት ያዳገታቸው ሰዎች “የአፓሎጂስት’ ክርክር እንደሆነ ማወቅ አለብን። ጣሊያን ያንን አድርጓል። ወያኔም አንደዚሁ።


ገብሩ ወያኔን ለምን ጠላት ማለት አንደማይደፍር በርካታ ያልዘረዘርኳቸው ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ድርጅቱ ለገብሩ አስራትም ሆነ መሰል ጓዶቹ ከሞላ ጐደል የለሰለሰ ነው። ገብሩ አንዳፈለገው ይናገራል፡ መለስ ዜናዊ እና አሁን በስልጣን ያሉትንም ‘ጸረ ሉአላዊነት’ ‘ተምብረካኪዎች’ ብሎ ከቡድኑ ጋር ሆኖ መግለጫ ባወጣበት ጊዜም ሆነ የፈለገው ቢላቸው ምንም አይሉትም። ገብሩ እና አስገደን ስታወዳድሩ አስገደ በወያኔዎች እጅግ ስለሚጠነክር በራሱ እና በቤተሰቡ (በልጆቹ) በርካታ መከራዎች እና ግፎች ሲፈጽሙበት እያየን ነው።

ወያኔዎች አረጋሽ አዳነን ወይንም ገብሩን ከማንገላታት ገብሩ የሚመራቸው የዐረና ተራ አባላቶቹን መግደል/ማሰር ይቀለዋል። ገብሩ ከውጭ ወደ ውስጥ የመመላለስ መብቱ የተጠበቀ ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን አለምሰገድ ገብረ አምላክ፤ገራፊ እና አዛውንት እስረኞችን በእሳት ለብላቢው የወያኔ አየር ሃይል አዛዥ የነበረው ‘አበበ ተ/ሃይማኖት’ (ጆቤ ?)፤ ተወልደ ወ/ማርያም… ወይንም ማንኛውም ኤርትራዊ ተወላጅ የሆኑ አንደልባቸው ወደ አገራችን የመግባት፤ የመነገድ፤ የመስራት (ስራቸው ተመለሶላቸዋል፤ ለቤታቸው ንብረታቸው ጉዳት ካሳ ተክፈሏቸዋል) ፤ ተንደላቀው የሞኖር መብታቸው ተከብሮላቸዋል። የተጠቀሱት ክፍሎች በሙሉ ወደ ውጭ የመመላለስ ዕድል አላቸው። የተቀረነው መግባት አንችልም! አረጋዊ በርሄ፤ ኢህአፓ መሪዎች ወዘተ….ወደ አገር አንዳይገቡ ተከልክለዋል። ለምን? የሚል ጥያቄ ስንጠይቅ፤- መልሱ- እነ ገብሩ ወያኔን የሚመለከቱት “አምባገነን” አንጂ “በጠላትነት” ስላለሆነ “ዜሮ ሳም ጌም” በሁለቱም ጎራ የለም። በአፍ እስከተላላጡ ድረስ ፤ አይፈላለጉም።   

ወያኔን በጠላትነት የፈረጅን የኢትዮጵያ ልጆች ግን “ባሕላችን፤ ማንነታችን፤ ሉአላዊነታችችን፤አንድነታችን፤ሰንደቃላማችን ዝቅ አድርጐ የሞራል አንቁላላችንን ጨፍልቆ ውስጣችንን አስኳል አፍስሶ ለከፍተኛ ጭንቀት፤ ሞት፤ ስደት፤ውርደት፤ ባርነት፤ የቤተሰብ መበታተን አስከትሎብናል። ስለሆነም ወያኔ አምባገነን ብቻ ሳይሆን ጠላትም ጭምር ነው።


ይሸጣል...! ይሸጣል…!

ኑግዙ ጋሽዬ፤

ውሰዷት እትዬ።

መቶ የነበረው ወርዷል ወደ ሐምሳ፤

ነገ ተነግ ወዲያ ይሆናል ሠላሳ፤

ዘንድሮ በሽ ነው ረክሷል ሕሊና!

ለታለቅ ቅናሽ ዋጋው አሽቆልቁሎ፤

ለሠፊው ጨረታ፤

ቀረ እኮ መጨነቅ፤ቀረ እኮ ይሉኝታ።

ትርፍ በትርፍ ነው የሕሊና ቀረጥ፤

ከብልህ ገብይቶ ለየዋህ መሸቀጥ።

ሆነና ጉዳዩ ነግዱ ንነግድ፤

ባዳ እንዳያድር ያ መከረኛ ሆድ፤

ቅዠቱ አይጣል እንጂ የፍጻሜው ነገር

ባቋራጭ ያከብራል ሕሊናን መቸብቸብ፤ሕሊናን መቸርቸር።

ገጣሚ ነብሷን ይማር አረጋሽ ሠይፉ “የደራ ገበያ” ከሚል በህሊና ዙርያ የሚዞረው ግጥሟ የተገኘ። ክፍል 2 ትችት ይቀጥላል። ስላነበባችሁልኝ “አመሰግናለሁ”። ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ) ያለፈው ሰሞን ትችቴ አንብባችሁ የደስታ እና የድጋፍ ደብዳቤ የጻፋችሁልኝ በርካታ ወገኖች አጋጣሚውን ተጠቅሜ ላመሰግናችሁ እሻለሁ። getachre@aol.com     (Ethiopian Semay)