Wednesday, May 25, 2016

መልስ ለግንቦት 7/ኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አገና ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ብሎግ አዘጋጅ)



መልስ ለግንቦት 7/ኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አገና
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ብሎግ አዘጋጅ)

ቬገስ ከተማ ከሚገኝ ህብር በተባለ ራዲዮ ጣቢያ ተገኝቶ ጋዜጠኛው የመቶአለቃ ሲሳይ አገና ባደረገው ቃለ መጠይቅ፤ ራዲዮው እንዲህ ሲል ጠቅሶት ነበር። በዚህም መሰረት ሲሳይን እተቻለሁ።

<…ኢሳት እንደ ማንኛውም ሚዲያ እንቅስቃሴ ባለበት የበለጠ ትኩረት ይሰጣል። ከዛ ውጭ የማንንም ሀሳብ አናፍንም ነገር ግን በፖለቲካ ፓርቲ ስም የተቋቋመ ሁሉ መግለጫ ባወጣ ቁጥር ያንን ተከታትለን እንዘግባለን ማለት አይደለም።ቅሬታ ያላቸው ወገኖች የቅሬታቸው መነሻ ምክንያቱ የተለያየ ነውኢሳትን በዘረኝነት ለመክሰስ የሚሞክሩት የገዢው ፓርቲ ሰዎች የመከላከያ ሰራዊቱ ዋና ዋና ባለስልጣናት ከአንድ አካባቢ ከአንድ ብሄር መጡ ተብሎ ዕውነታው መዘገቡ ያበሳጫቸዋል።ዘረኛው ያንን ያደረገው ስርዓት ነው ወይስ ዕውነታውን የዘገበው? …> ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ለኢሳት ስድስተኛ ዓመት በቬጋስ ያደረገውን ቆየታ መሰረት አድርገን  ካደረግነው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ (ሙሉውንአድምጡት)” ይላል። 

እውን ኢሳት የማንንም ሀሳብ አናፍንም ሲል እየዋሸ ነው ወይስ እውነት እየተናጋረ ነው? እስኪ ውሸትና እውነት ለማወቅ የሲሳይንም ሆነ የኢሳት ማሕደሮችን እንፈትሽ። ጋዜጠኛ የእውነት ምልክት ነው ሲባል እንሰማለን። ግን እኮ የፖለቲካ ፓርቲ ጋዜጠኛ እና ነፃ ጋዜጠኛ የተለያዩ ናቸው። ካልተሳሰትኩ እንዲያ ይመስለኛል። የፖለቲካ ፓርቲ ጋዜጠኛ ልክ እንደ የህወሃት/ኦነግ/ግንቦት 7 ጋዜጠኞች የራሳቸው የሆነ ፓርቲን የሚከስ/የሚወቅስ/የሚያጋልጥ ጽሑፍ/ተቺ በጋዜጣቸው/በራዲዮናቸው ማስተናገድ አይችሉም። እራሳቸውም ድርጅታቸውን በይፋ መውቀስ ፤ማጋለጥ አይፈቅዱም። ነፃ ጋዜጠኛ ከሆነ ግን የሚቧድነው ወገን ስለማይኖረው፤ እንዳለ ትችቱን ያስተናግዳል። እውጭ አገር ያሉ ሚዲያዎች ቡድንተኞች ስለሆኑ በዚህ ችግር የተጠመዱ ናቸው (እጅግ ሳከብራቸው የነበሩትን ዋለልኝ መኮንን ተችተሃል ብለው ጽሑፌን በድረገጻቸው ያገዱት አሲምባ ድረገጽ አዘጋጆችን ልብ በሉ። በዚያ ተቆራርጠን ቀረን)። ኢሳትም የነዚህ ቡድኖች ወገን አንዱ አካል ስለሆነ፤ ‘የማንንም ሀሳብ አናፍንም’ ብሎ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲል ቢዋሽም ሃቁ እና ማሕደሩ የሚነግረን ተቃራኒው ነው።ብዙዎቹ ሚዲያዎቹ ከፍተኛ የቡድንተኛ ባሕሪነት ችግር አለባቸው።

“የኢሳት ወይም የግንቦት ሰባት ሁለገብ ጋዜጠኞች ክሽፈት በኮረኔል ታደሰ እና ሌሎች ጉዳዮች ከያሬድ ኃይለማርያም ሐምሌ 21፣ 2013” የሚለው ጽሑፍ አውሮጳ ውስጥ የሚኖር በሰብአዊ መብት ተሟጋች በወጣት ያሬድ ኃይለማርያም የተጻፈውን ትችት አንባባችሁ ከሆነ፤ ሲሳይ አገና በየሚዲያው እየተገኘ ከሚናገረው ተቃራኒ፤ ኢሳት እጀግ ክፉ ወገንተኛና አፋኝ የዜና ማዕከል/ሚዲያ መሆኑነን ጽሑፉ በግል ይነግራችሗል።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ኢሳት የተባለው ጣቢያ የማን መሆኑን ሲገልጽ “ኢሳት የማነው የሚለው ክርክር ጊዜ ያለፈበት ስለሆን በሱ ላይ ጊዜዬን ለማጥፋት አልፈልግም።” ይላል። እውነት ነው። ሁላችንም የምንስማማበት አባባል ነው።አቶ ያሬድ በትከክል አንዳስቀመጠው፤ ‘ኢሳት የማንም ቢሆን እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ለእውነት ወግኖ እየሰራ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ጭብጥ ግን ላልፈው አልችልም።’ ሲል ነበር ስለ ኢሳት ሚዲያ ከእውነት ጋር ወግኖ ሃላፊነት የሚሰማው መሆኑን አለመሆኑን  እንድንፈትሸው ከነ ማስረጃው ያስጨበጠን። ለዘሂም ነው ሲሳይ ከተከታታይ ውሸትና ወገንተኛነቱ እንዲታረም በተለያየን ጸሀፊዎች ምክራችን፤ትችታችን ብንለግሰውም፤ ቸል በማለት በንቀት በማን አለበኝነት በየሚዲያው ተገኝቶ “ኢሳት አያፍንም፤ ወገንተኛ አይደለም” ማለቱን ዛሬም ቀጥሎበታል።

 አቶ ያሬድ የኢሳት ባለቤት የሆኑት የግንቦት ሰባት ባለስልጣናት እና በኢሳት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ባደባባይ ውጥተው ሥራችንን በአግባቡ እየሰራን ነው ለሚለው ሚዛን የማይደፋ የመከላከያ ሙግታቸው ግን መልስ ለመስጠት እወዳለሁ። በማለት ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ በኢሳት ላይ የተቸውን ኢትዮጵያዊያን ልብ ብለን የጸሀፊው ድንቅ ክርክር ወደ ሗላ ተመልሰን ብናነብበው የኢሳት ጋዜጠኞች ማንነት አንደመስተዋት ያሳየናል።

ጸሐፊው የኢሳት ትክለሰውነት በሚገባ ሲገልጽ፤ ምንም እንኳን ኢሳት የተመሰረትኩብት አላማ በሚል ለሕዝብ በድህረ-ገጹ ላይ የገለጻቸ አላማዎቹ እና ግቡ ከላይ የጠቀስኳቸውን መርሆዎች የሚያንጸባርቅ ቢሆንም አፈጣጠሩ ግን ከመነሻው ይህን ግቡን እንዲያሳካ በሚያስችል መልኩ አልነበረም። ይላል። ምክንያቱን ሲገልጽ፤  ምክንያቱም ኢሳት የግንቦት ሰባት ‘ሁሉ አቀፍ የትግል ስልት’ አንዱ አካል ሆኖ ነው የተፈጠረው። ግንቦት ሰባት በአስመራ ብቻ ሳይሆን የዘመናዊውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ በየቤቱ ለመድረስ የከፈተው እና በግንቦት ሰባት የሬዲዮ ፕሮግራም የተጀመረው የሳተላይት ዘመቻ ቀጣይ አካል ነው። ይህ ደግሞ ኢሳት ከመነሻውም ጉዞውና መድረሻው በጠባብ የግንቦት ሰባት የፖለቲካ አጀንዳ ላይ የተወሰነ መሆኑን ነው የሚያሳየው።ይላል እውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ወንድም አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ።

አቶ ያሬድ ኢሳትን በግሩም አቀራረብ ከነማስረጃው ከሽኖ አቅርቦልናል።ግንቦት ሰባት ሲዋሽ፣ ሲሳሳት፣ አቅጣጫውን ሲስት፣ ለአገርና ለሕዝብ ዘላቂ ሰላም የማይበጅ ተግባራትና ጥፋቶችን ሲያጠፋ ከማረም ይልቅ “ኢሳትም አብሮ ይነጉዳል” ይላል። ኢሳትም የተመሰረተበትን ውሉን እንዳልሳተ ሲያሳይ “የግንቦት ሰባት የቴሌቪዥን ልሳን ሆኖ ቀጥሏል። በኢሳት ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችም፤ ሁሉንም ለማለት አልደፍርም፤ ልክ ወያኔ በኢትቪ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በፋና ሬዲዮ ባሰማራቸ ‘ልማታው ጋዜጠኛ’ ህዝብን እያደናበር እንዲሚጓዘው ሁሉ ኢሳትም ‘የሁሉ አቀፍ ትግል’ ጋዜጠኞችን ይዞ ጉዞውን ቀጥሏል።” ይላል።

አቶ ያሬድ በሚገባ አንዳስቀመጠው፤ ኢሳት የሚነዳብት ወይም እንዲከተለው የተደረገበት የተሳሳት የፖለቲካ አግጣጫ ወይም ቅኝት መኖሩን ያመላክታል። ወንድም አቶ ያሬድ ኢሳትን ሲገልጽና ሲተች የታዘበውን ትዝብት በማስረጃ ሲያቀርብ እንዲህ ይላል።

·       የኮረኔል ታደሰ ሙሉነህ ጉዳይ       
በደርግ መንግስት የአየር ኃይል አብራሪ የነበሩት እና ወደ ኤርትራ ተሰደው የአርበኞች ግንባር መሪ የነበሩት የኮረኔል ታደስ ሙሉነህ ጉዳይ የኢሳትን ተልዕኮ እና በተለይም በዚህ ጉዳይ በቀጥታ ተጠቃሽ የሆኑውን ቀደም ሲል የግንቦት ሰባት ሬዲዮ አቅራቢና አሁን የኢሳት አምስተርዳር ቅርንጫፍ ተጠሪና ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለምን ይመለከታል። ኮሎኔል ታደሰ በኤርትራ መንግስት ቁጥጥር ስር ወለው የደረሱበት ያልታወቀ መሆኑን የተሰማው በሆላንድ አገር ነዋሪ የሆነችም ልጃቸው በ2011 ዓ.ም. በምርጫ 97 የተገደሉ ወገኖቻችንን ለማስታወስ በአምስተርዳም ከተማ በተጠራ ሕዝባዊ መድረክ ላይ ተገኝታ አጋጣሚውን በመጠቀም (ለምን እንዲህ እንዳልኩ አክዮ እገልጻለሁ) ባልታሰበ ሁኔታ ድምጿን ክፍ በማድረግ “አባቴን አፋልጉኝ፣ የኤርትራ መንግስት አባቴን አፍኖብኛል፣ የኮረኔል ታደሰ ልጅ ነኝ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አባቴን እንዲያፋልገኝ እና የኤርትራ መንግስት አባቴን እንዲለቅልን አብራችሁኝ ድምጻጭሁን አሰሙልኝ” የሚል ጥሪ እያነባች ባዳራሹ ለተሰበሰበው ሕዝብ አቀረበች። የዕለቱን ዝግጅት ሊዘግቡ የሄዱ የኢሳት ጋዜጠኞችም የልጅቷን አቤቱታ በመቅረጽ በእለቱ ዜና ስርጭታቸው ላይ አያይዘው አቀረቡት። 

የልጃቸውን አቤቱታ ተከትሎ በተለያዩ ድህረ-ገጾች የኮረኔል ታደሰ ጉዳይ መዘገብ የጀመረ ቢሆንም በቂ ሽፋን አላገኘም ነበር። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በአምስተርዳም የተዘጋጀ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ያተኮረ ስብሰባ ለመካፈል ሄጄ በኢሳት አቤቱታ ያቀረበችውን የኮረኔል ታደሰን ልጅ ለማግኘት እድሉ ገጥሞች ስለአባቷ ሁኔታ አንስተን ለመወያየት ችለናል። በዚህ አጋጣሚ ልጃቸው በአባቷ ላይ ከደረሰው እና እየደረሰ ካለው ስቃይ ባልተናነሰ ስሜቷን እጅግ በሚጎዳ መልኩ በኢሳት በኩል፤ በተለይም በአቶ ፋሲል የኔአለም በኩል የደረሰባትን በደል እያነባች ሌሎች የስብሰባው ታዳሚዎች ባሉበት አጫውታኛለች። ነገሩም እንዲህ ነው። የኮረኔል ታደሰ ልጅ የአባቷን አያያዝ እና ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለሕዝብ ለመስጠትና እግረ መንገዷንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪዋን አብሮ እንዲያስተጋባላትና አባቷም እንዲፈቱ ጥረት እንዲደረግ በማሰብ ወደ ኢሳት አምስተርዳም ቢሮ በመሄድ እድል እንዲሰጣት ትጠይቃለች። ይሁንና ከኢሳት የተሰጣት መልስ አንቺን አናቀርብም፣ የአባትሽንም ጉዳይ በኢሳት ከዚህ በኋላ አናሰናጭም የሚል ነበር።

 የኮረኔል ታደሰ ልጅም ተስፋ ሳትቆርጥ ከኤርትራ ሸሽተው የመጡና የአባቷን መታሰር በአይናቸው የተመለከቱ ምስክሮችን በመያዝ ኢሳት ማስረጃ ፈልጎ ከሆነ በሚል ግምት በድጋሚ ወደ ኢሳት አምስተርዳም ቢሮ በመሄድ እድሉ እንዲሰጣትና ምስክሮቹም እንዲጠየቁ ላቀረበችው ጥያቄ የተሰጣት መላሽ በድጋሚ ወደ ኢሳት ቢሮ እንዳትመጪ የሚል ነበር። አቶ ፋሲል አክለውም ምስክር የተባሉትንም ሰዎች ወደ ኢሳት ቢሮ አንዳይመጡ በማስጠንቀቅ የመለሱዋቸም መሆኑን የኮረኔል ታደሰ ልጅ እያለቀሰች አውግታናለች።

ኢሳት የኮለኔል ታደሰ ጉዳይ በዝርዝር እንዳይተላለፍ በአቶ ፋሲል በኩል የከለከልው ጉዳዩ አንዴ ሽፋን ተሰጥቶታል ወይም በፕሮግራም መጣበብ ወይም በሌሎች የአሰራር ቀደም ተከተሎች የተነሳ አይደለም። ምክንያቱ ግልጽ እና ግልጽ ነው። በቅርቡም የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር እንዳረጋገጡልን ኢሳት የሚንቀሳቀሰው እና እነ አቶ ፋሲል የኔአለምም ደሞዛቸውን የሚያገኙት ከኤርትራ መንግስ በሚሰጥ ድጎማ ነው። ከዚያም በላይ የኢሳት ባለቤት የሆነው ግንቦት ሰባት ጎጆውን የቀለሰው በአስመራ ከተማ ነው። ስለዚህ የኤርትራን መንግስት ገበና የሚያጋልጡ ምንም አይነት ነገሮች ከሰብአዊ መብት ወይም ከፍትህና ከዴሞክራሲ መርሆዎች ቢቃረኑ እንኳ፣ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን ክብርና መብት የሚጎዱ ቢሆኑም እንኳ በኢሳት አይዘገቡም። የኮረኔል ታደሰም ልጅ ቀደም ሲል አጋጣሚውን ተጠቅማ ነው በኢሳት የመጀመሪያውን ድምጿን ያሰማችው። ሕዝብ በተሰበሰበበት መድረክ ላይ ስለሆን የተናገረችው እነ አቶ ፋሲል ቆርጠው ሊያወጡት አይችሉም። 

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ በ2011 ዓ.ም. ብራስልስ የምንገኝ ጥቂት ኢትዮጵያዊያንን ኢሳትን በገንዘብ በማጠናከሩ ጉዳይ ላናግራችሁ በሚል ጥያቄ አቅርበው በአንድ እለተ ሰንበት ብራስልስ በሚገኝ ካፌ ተገናኝተን አጠር ያለ ውይይት አድርገን ነበር። በውይይቱ ኢሳታቸውን ለማጠናከር ከገንዘብ የበለጠ ለሚዲያውና በውስጥ ለሚሰሩት ጋዜጠኞች የሚያስፈልገው ትልቁ ነገር የሚዲያው ነጻ መድረግ መሆኑን አበክሬ በመግለጽ ኢሳትን ከግንቦት ሰባት ፖለቲካ ነጻ እንዲያደርጉት በማሳሰብ በኮረኔል ታደሰ ልጅ ላይ የደረሰውን አጋጣሚ በምሳሌነት አንስቼባቸው ነበር። ግለሰቡም ይህንኑ ጉዳይ ወደ ኢሳት ቢሮ በመውሰድ ከአቶ ፋሲል ጋር ከተነጋገሩበት በኋላ አቶ ፋሲል በዚያው ሳምንት ውስጥ ለኮረኔል ታደሰ ልጅ ስልክ በመደወል አርፋ የማትቀመጥ ከሆነ ከኤርትራ አንድ ባለስልጣን በኢሳት በማቅረብ አቧቷ በኤርትራ መንግስት ያልታሰሩ እና ምንም ያልደረሰባቸው መሆኑን የሚመለከት የማስተባበያ ዘገባ የሚሰሩ መሆኑን በማሳሰብ ያስጠነቀቁዋት መሆኑን ልጃቸው ገልጻልናለች። የሚያስገረመው ከሦስት አመት ቆይታ በኋላ አቶ ፋሲል የኔ አልም አይናቸውን በጨው አጥበው እና አቶ አፍወርቅ አግደውን አስከትለው በኢሳት የጁላይ 18፣ 2013 “የድህረ-ገጽ ዳሰሳ” በሚል ፕሮግራማቸው ላይ አንድ ሰመረ አለሙ የተባሉ ጸሐፊ ስለ ኮረኔል ታደሰ የሕይወት ታሪክ እና ስለሚደርስባቸ ስቃይ የጻፉትን ጽሑፍ የፕሮግራማቸው አካል በማድረግ ስለ ኮረኔል ታደስ አቶ ፋሲል ተቆርቋሪ መስለው መቅረባቸው አስደምሞኛል። ነገር አለ ብዬ እንዳስብም አድርጎኛል። እዚህ ላይ ለአቶ ፋሲል የማነሳንው ጥያቄ፤ ምነው እስከ ዛሬ የት ሄደው ነበር፣ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተለያዩ ድህረ-ገጾች ላይ ስለ ኮረኔል ታደስ ሁኔታ ሲያትት እንዴት ሳይታይዎት ወይም ኢሳትን ሳይታየው ቀረ? ለምን ልጃቸ ለሕዝብ ብሶቷን እንዳታሰማ ማፈን አልፎም ማስፈራራት አስፈለገ? ዛሬ ምን ታየዎት? ነው ውይስ ይህም ድርጅታዊ ሥራ ነው? ምናልባት ግንቦት ሰባት ኮረኔል ታደሰን ለሕዝባዊ ንቅናቄው አስፈላጊ ሰው ሆነው አግኝቷቸው ከኤትርትራ መንግስ ጋር እንዲፈቱ መደራደር ጀምሮ ይሆን? ሰንብተን እንሰማለን።   

ከኢሳትና የኤርትራ ጉዳይ ሳልወጣ በተደጋጋሚ ጊዜ የታዘብኩትን ጉዳይ በአጭሩ ጠቆም አድርጌ ልለፍ። የአረብ ስፕሪን እየተባለ የሚጠራውና በርካታ የአረብ አገሮችን ሲያተራምስ የቆየም አብዮታዊ ንቅናቄ በጀማመረበት ሰሞን ኢሳት በርካታ የትንታኔ ዘገባዎችን ያሰራጭ ነበር። በነዚያ ዘገባዎቹ ላይ የአረቡ አልም ንቅናቄ ወደ አፍሪቃ አገሮችም ይዛመታል፤ በዚያም አምባገነናዊ ሥርዓት የሰፈነባቸው የአፍሪቃ አገሮች የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች ናቸው የሚል ትንታኔ በተደጋጋሚ በአቶ ፋሲል ይቀርብ ነበር። በሃሳቡ ይሁንም አይሁን ሊከሰት ይችላል በሚለው እስማማለሁ ይሁንና አቶ ፋሲል እየደጋገሙ አደጋው ያንጃበበባቸውን እና ለበርካታ አመታት ሥልጣን ይዘው አለቅ ያሉ የአገራት መሪዎችን ሲዘረዝሩ ከሊቢያ ተነስተው በኢትዮጵያ አድርገው ቁልቁል ወዳሉ የአፍሪቃ አገራት ሲያቀኑ ኤርትራን በፍጹም አያነሱም። እንግዲህ በአቶ ፋሲል ወይም በኢሳት ካርታ ውስጥ ኤርትራ የለችም እንዳልል የሱዳኑ መሪ አልበሽር አስመራ ለጉብኝት በሄዱበት ጊዜ እንደ ታላቅ ዜና ተደርጎ የተዘገበ ሲሆን ትንታኔውም የአልበሽር ኤርትራን መጎብኘትና ከአምባገነኑ ኢሳያስ ጋር መገናኘታቸው ለኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች ሰፊ የመፈናፈኛ ቦታን ያመቻቻል የሚል ነበር።

·       የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እና የዶ/ር ብርሃኑ ውይይት በኢሳት
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በቅርብ ጊዜው (ላለፉት ሃያ አመታት) የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ሕዝባቸውን ለማስተማርና የመረጃ ባለቤት ለማድረግ በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ባለሙያ ነው። ለሱ ያለኝን አክብሮትም ቀደም ሲል በጻፍኩት ጽሑፍ ውስጥ ጠቅሻለሁ። ይሁንና ሲሳይ ከበርካታ እንግዶቹ ጋር በሚያደርገው ውይይት ውስጥ የሚያነሳቸውን በሳል እና ደረጃቸውን የጠበቁ ጥያቄዎች ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር ሲያደርግ አላስተውለውም። አንዳንድ የሚያነሳቸውም ጥያቄዎች ውስጡ ምን እንደሚያስብ ቢያመላክቱም በአንጻሩ አንድ ሊጥሰው ወይም ሊያልፈው የማይችል እና የሚጠነቀቅለት የኢሳት የውስጥ ቀይ መስመር ያለ መሆኑን ውይይቱን በአንክሮ ለተከታተለ በግልጽ ይስተዋላል። ለዚህም ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስ፦
-      ጋዜጠኛ ሲሳይ የግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ንቅናቄን መመስረት ተከትሎ በቀናት ልዩነት ውስጥ ዶ/ር ብርሃኑን ለውይይት ጋብዧቸው ወይም እራሳቸው መድረኩን ጠይቀው ሊሆን ይችላል አቅርቧቸው ነበር። ንቅናቄውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜ እሳቸው ከሚመሩት ድርጅት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲነግሩት ላቀረበላቸ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሽምጥጥ አድርገው ክደዋል። ከእሳቸው ድርጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ለማስረዳት ምድር ጭረዋል፣ ሰማዩንም ለመቧጠጥ ጥረዋል። ይሁንና በዚያው ወቅት ንቅናቄው ከመመስረቱ ቀደም ብሎ የድርጅታቸው ም/ሊቀመንበር እና ሌሎች የአመራር አባላት አስመራ መግባታቸውን፣ ሰራዊት እያደራጁ መሆኑን እና በቅርቡም ዜናውን እንደሚያበስሩን የሚጠቁሙ ጽሁፎች በየ ድህረ-ገጹ ተበትነው የሕዝብ መወያያ ሆነው ቆይተዋል። የወያኔ ደጋፊ የሆኑ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ነገሩን ሲያነሱና ሲጥል ከርመው ነው የሕዝባዊ ንቅናቄው ዜና የተበሰረው። ታዲያ ወዳጄን ሲሳይ ምን ይዞት ነው ዶ/ር ብርሃኑ እኛ የለንበትም ብለው ሲክዱ የእርሶ ጀሌዎች ታዲያ አስመራ ምን ሊሰሩ ነው የሄዱት፣ ወይስ ሄዱ የሚባለው ውሽት ነው ወይ? ከሄዱስ ምን ሊሰሩ? የሚሉ ጥያቄዎችን እንደ አንድ ነጻ ጋዜጠኛ ማንሳት የተሳው? መቼም የአመራሩን ወደ አስመራ ሄዶ መከተም አቶ ሲሳል አልሰማሁም ነበር እንደማይል ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካለያማ …

-      ይህን ይሁን ብለን ባሳለፍን በጥቂት ወራት ውስጥ የዶ/ር ብርሃኑን ድምጽ የያዘ የስልክ ንግገር መሰራጨቱን ተከትሎ በድጋሚ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እና ዶ/ር ብርሃኑ ለጥያቄና መልስ (ድራማ) ኢሳት ቢሮ ተገናኝተው ነበር። በተሰራጨው የስልክ ንግግር ላይ የተነሱ አንዳን አሳቦችን በመጥቀስ ዶ/ር ብርሃኑ እረዘም ያለ እና ተደጋጋሚ ሃሳቦችን እየተነተኑ ማስተባበያ ሲሰጡ ሰምቻለሁ። ከአሁን ከአሁን ጋዜጠኛ ሲሳይ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያነሳል እያልኩ ስጠበቅ ነበር። ‘ዶ/ር ብርሃኑ በቅርቡ ባደረኩልዎት ቃለ መጠይቅ ላይ የግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ንቅናቄ ከእርሶ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው ወይ? በዮ ብጠይቅዎት በፍጹም በለው አስተባብለዋል። አሁን ደግሞ በዚህ የስልክ ንግግርዎ ላይ ሕዝባዊ ንቅናቄው የእናንተ መሆኑን፣ ለማደራጃም ገንዘብ መቀበልዎን፣ አንዳንድ ንቅናቄውን አንቀበል ያሉ ድርጅቶችንም መንቀፍዎን፣ ከገንዘቡም ላይ ገሚሱ የኢሳት ሥራ ማስኬጃዎ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ንግግርዎ አይጋጭም ወይ?’ ይሁንና ሲሳይ እነዚህን ነገሮች በራሱ ፈቅዶ ይሁን ለመገደድ ወዶ ሳያነሳቸው እረዥም ሰዓት የፈጀው ትርጉም አልባ ውይይት ተጠናቋል። ይህን ክፍተት ሲሳይ በሙያ ብቃት ማነስ ወይም በዳተኝነት የፈጸማቸው እንዳልሆኑ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። ሲሳይ ከነዚህ የጠነከሩ እና በሳል ጥያቄዎችን ለማቅረብ አቅሙም ችሎታውም አለው ብዮ ነው የማምነው። እንዳልኩት ግን ግንቦት ሰባት ለኢሳት ያሰመረለት ቀይ መስመርን ለማለፍ ብርታቱን ማጣቱ ግን ግር አሰኝቶኛል። ‘ሁለ ገብ ጋዜጠኛ’ እንደሆኑት የእነ ፋሲል የኔአለምን መንገድ ሊያያዘው ዳር ዳር እያለ ለመሆኑ ግን ምልክት ሊሆን ይችላል። 

ይህን ዳሰሳዮን በሌላ ክፍል እመለስበታለሁ። ለማጠቃለያ ያህል ግን አንድ ኢሳት አይደለም አስር እና ሃያ የኢሳት አይነት የመወያያ ሚዲያዎች እንኳን ቢኖሩን ተወያይተን ተነጋግረን የማንጨርሳቸው በርካታ ሃገራዊ ጉዳዮች አሉን። የመገናኛ ብዙሃን መኖር፣ መበራከትና መጠናከር ለዘመናት ተጭኞ ያጎበጡንን ጭቆናን፣ የአንባገነናዊ ሥርዓትን፣ መገለጫ የሌለው ስር የሰደደ ድህነት፣ የሞራል ኪሳራ እና ሌሎች ውርደትን ያከናነቡት ስንክሳሮች ከላያችን ላይ ለማራገፍ እና በሳይንሳዊ አስተሳሰብና በእውቀት የታነጸ ማኅበረሰብ ለመገንባት መገናኛ ሚዲያዎ ግንባር ቀደም ናቸው። ይሁንና በጥንቃቄ ባልተያዙበት፣ በጠያቂነት በጎደለው እና ለጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ስናውላቸው የሚጠቅሙትን ያህል ሞታችንን እና ውድቀታችንን ያፋጥኑታል። ወያኔን በምንወቅስባቸው መሰረታዉ ጉዳዮች ሁሉ እራሳችንንም መፈተሽ፣ መንቀፍ፣ ማረም እና ለመታረምም መዘጋጀት አለብን። 

የግንቦት ሰባት አመራሮችም ሆኑ አንዳንድ የኢሳት ጋዜጠኞች ኢሳት የማንም ቢሆን እንደአንድ ነጻ ሚዲያ እያገለገለ ነው ለሚለው ሙግርታቸው ከላይ የጠቀስኳቸውን ነገሮች ብቻ ማንሳቱ በቂ ላይሆን ይችላል። እነዚህን የመሰሉ በርካታ ምሳሌዎችን በነቂስ ለማውጣት ይቻላል። ወያኔን ስላወገዝንና የወያኔን ገበና ስላጋለጥን ለእውነት የወገንን ነን እና የነጻ ሚዲያ ኒሻን ይሰጠን የሚለው ሙግት አያዋጣም። እን አቤ ቶክቻው በወያኔ ባልስልጣናት የሚሳለቁትን አይነት ቁምነገር አዘል ጨዋታ በግንቦት ሰባት አመራሮች ላይ እንዲያደርጉ መፈቀዱን እጠራጥራለሁ፤ አላየሁም እና። 

ከየአቅጣቻው የተሰነዘሩትን አስተያየቶች ተቀብሎ እንደሰለጠነ ሰው እራስን ማረቅ እና የጎበጠውን ማቅናት ይበጃል። ይህ ሁሉ ሙግት የተነሳው ግን ያልሆናችሁትን ገለልተኞች ነን ስላላችሁ እንጂ ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን መሆኑን ሳይክድ ስራውን ቢቀጥል ይህ ሁሉ አተካራ ባልተነሳ ነበር።” ሲል ሲሳይ አገና “ኢሳት የማንንም ሀሳብ አናፍንም” የሚለውን ውሸት ቁልጭ አድርጎ “አፋኝና ወገንተኛ ሚዲያ መሆኑን አቶ ያሬድ በማስረጃ ቁልጭ አድርጎ አስደግፎ ነግሮናል። አቶ ያሬድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንደመሆኑ መጠን ግንቦት 7 በታጋዮቹ ላይ ያደረሰው ኢሰብአዊ በደል ለሕዘብ ይፋ እንዳይሆን ኢሳት ሲያፍኑው የነበረውን የሰው ልጆች እሮሮ ሚስጢር ( “ለግንቦት 7 ሆነ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ያለመተቸትን ከለላ ማን ሰጠ? የእነ “… ወይም ሞት” ፖለቲካ) በማለት ኢሳት አፋኝ ሚዲያ መሆኑን አቶ ያሬዩድ አስነብቦናል። በወቅቱ የኔ ጽሑፎችም በተከታታይ ይህነን አስመልከቶ የጻፍኩትን ትችት ይታወሳል።
የአቶ ያሬድ የወደድኩለት ቆንጆ ጥቅስ ልጥቀስ የፍትሕን ጥያቄዎች ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በዘለለ ለማየት ያለመቻላችን ነው።”  (ያሬድ ኃይለማርያም)። ሕዝባዊ ሃይል ተብሎ ሲጠራ ከነበረውየግንቦት 7 ተዋጊ ሃይል የመጀመሪያ የመጠሪያ ስሙ መብታችን ተነክቷል፤ ተደብድበናል፤ጓዶቻችን እየታፈኑ ለሻዕቢያ እተሰጡ መድረሻቸው አይታወቅም ወደ እርሻ ሸቅል ለሻዕቢያ ዕርዳታ እንድንሰራ ተደር ጓል፤ገንዘብ ባክኗል፤ የድርጅቱ መሪዎች ጸረ አማራ ክስ ሲደርስባቸው በጉባኤ እንዳይታይ አፍነውታል፡አንዳርጋቸው ጽጌ እና ብርሃኑ ነጋ አጅግ የከፉ “አፋኞች” ናቸው፤ ድርጅቱ በጓደኛና በዘመድ አዝማድ እከክልኝ ለከክልህ የሚሰራ ድርጅት ነው፤ ማዕከላዊ አመራሮች በተቀመጠው ሕግና ደምብ ከመከተል ይልቅ በጥቂት ግለሰቦች የሚሽከረከር፤ ዸምብ የሚጥሱ፤ አንዳሻቸው ሰውን የመሾም የማውረድ መብት ከድርጅቱ ደምብ ውጭ የሚሰሩ ናቸው፤ አንዳርጋቸው ጽጌ አስመራ እየኖረ አለፍ ብሎ በረሃ በየዳሱና ጎጆው በመሰንበት ጺሙን አሳድጎ ጸጉሩን አንጨፍርሮ የሚነሳው ፎቶግራፍ ብቅ እያለ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚዘረጋው ፎቶ እርሱ ከሚኖሮው የአስመራው ኑሮ ጋር አይጣጣምም፤ ሰሚራ ከተባለች ኤርትራዊት ጋር ከነ ተስፋየ ገብረአብ ጋር አብሮ በየመሸታው ሲቀብጥ ነበር ጊዜውን የሚያሳልፈው፤ ወዘተ..ወዘተ….በማለት ድርጅቱ ያደረሰባቸው የአካልና የሕሊና ጫና ዘርዝረው በሌሎች ሚዲያዎች ቀርበው ድርጅቱ ሲያጋልጡ፤ ኢሳት የነዚህ ሰዎች ክስ በማጣጣል “ወያኔዎች ናቸው” “ሰላዮች ናቸው” እያለ ሲደሰኩር መኖሩን ይታወሳል።
እጅግ የሚገርመው ደግሞ ጥቃት ደርሶብናል በማለት ስሞታቸውን ለማሰማት ከነዚህ ወገኖች ለኢሳት የጻፉትን ደብዳቤ ኢሳት ስላፈነው፤ እንደገና ለኢሳት መልዕክት በፓልቶክና በኢትዮፓትርዮቲክ ድረገጽ እና ራዲዮ ላይ በመለጠፍ “ውሸታምና እወነተኛ ማን መሆኑን ለሕዝብ እንዲቀርብ ያመች ዘንድ እኛ እና ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም መላው የድረርጀቱ አመረር በኢሳት ቴ/ቪዥን አቅርቡን እና እኛንም እነሱንም የፈለጋችሁት ጥያቄ አቅርባችሁ እንድንወያይ አድርጉ” በማለት ተደጋጋሚ ጥሪ ለኢሳት ቢያቀርቡም፤ እነ ሲሳይ አገና መሪዎቻቸውና ወዳጆቻቸው እንዲሁም አስተዳዳሪዎቻቸው በሕዝብ ፊት አንዳይጋለጡ ሆን ብለው እያወቁ እንዳይናገሩ አፍነዋቸዋል። አስገራሚው ደግሞ፤ሌላ ቀርቶ ዘ-ሐበሻ የተባለው ድረገጽ ጋዜጠኛ ነኝ የሚል ተበድለናል ካሉት እነዚህ ታጋዮች ሱዳን ውስጥ አግኝተውት “ወደ ሚዲያ አቅርበን እና እነሱንም እኛም ቃለ መጠይቅ አድርግልን” ብለው ሲሉት “ወደ ግንቦት7 አመራሮች ወደ ኤፍሬም ማዴቦና ንአምነ ዘለቀ” ደውሎ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር ካለ ሲጠይቃቸው “ዋሾች” ናቸው ስላሉኝ ልሳናቸውን ለሕዘብ ላቀርብ አልፈቀድኩም ሲል፤ ንአመን እና ኤፍሬም የተናገሩትን መለስ ሲጽፍ፤ ተበድለናል፤ተደብድበናል፤ኤርትራ ውስጥ  ሰዎች ታፍነው በሻዕቢያ እሰር እየተደበደቡ ናቸው፤ ደብዛቸው የጠፉም አሉ፤  እያሉ ሲጮኹ የነበሩት የግንቦት 7 ታጋዮች ለሕዝብ አላቀርባችሁም ብሎ ልሳናቸው እንዳይደመጥ ማድረጉ በዘ-ሓበሻ ድረገጽ ኑዛዜውን ሳያፍር በራሱ በዘ-ሐበሻ ጋዜጠኛው ብዕር  እና ድረገጽ በቅርቡ አስነብቦናል።
 ታዲያ ግንቦት 7 እና ኢሳት ታሪክ ተሸክሞ ነው የኢሳት ጋዜጠኛው ሲሳይ አጋና “የማንንም ሀሳብ አናፍንም” እያለ በሕዝብ ፊት እውነትን ለማደናገር እየሞከረ ያለው። 

ኢሳት የመናገር ነፃነትን ያፈናቸው ተበድለናል ያሉ የኢሳት ተዋጊ ሃይሎችን የድርጅቱ መሪ ብርሃኑ ነጋ “ከነዚህ ቆሻሻዎች ጋር”  እንዴት እሰራ እንደነበር አሁን ሳስበው ያንገሸግሸናል።ሲል “ቆሻሶች” በማለት ስሞታቸውን ላቀረቡ የድርጅቱ አባሎች ሰድቦአቸዋል።ግንቦት 7 እና አሲት የመናገር መብታቸውን በሚዲያቸው እንዳይናገሩ አፍነዋቸዋል።

ብርሃኑ ነጋ የመዋሸትና የመካድ ባሕሪው አዲስ አይደለም። አዲስ አበባ እያለ ካሁን በፊት አንዲት እስላም ተመሪት ሴት “የገለጽከው አገላለጽ አልገባኝም ፤ልትደግምልኝ ትችላለህ” ስትለው “እንዲገባሽ እራስሽ ላይ የጠመጠምሺውን ሕጃብ አውልቂው” ብሎ በማለቱ የከተማ ትኩስ ወሬ ሆኖ ሲነገር ነበር፤ አንተ ስለዚህ ምን ትላለህ? ብሎ የቢላል ራዲዮ ጋዜጠኛው ሳዲቅ ከሦስት ወር በፊት ቃል መጠይቅ ሲያደርግለት፤ ያልጠበቀው ጥያቄ ስለነበር ፤በመደናገጥ የሚሰጠው መልስ አጥቶ ወደ ሌላ ርዐስ ገብቶ ስለወያኔ ሲዘላብን ማድመጣችን በወቅቱ እኔ የተቸሁትን ጽሑፍ ይታዋሰል። 

ይህ ሁሉ ጉድ እየተሸከሙ ግንቦት 7ም ሆነ ኢሳት አድናቂ እና ተከታይ አላጡም። ያውም በሚገርም ሁኔታ በብዛት! አቶ ያሬድ ከዚህ በታች በትከክል እንዳስቀመጠው፤
1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የአገራችንን ፖለቲካ የተጠናወተው “…. ወይም ሞትአስተሳሰብ ከአስርት አመታት በኋላም አለቅ ብሎን ዛሬም እኔ ከምደግፈው ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ቡድን ወይም አስተሳሰብ ውጭ ያለው መንገድ ወይም አማራጭ ሁሉ ገደልና ሞት ነው ብለው የሚያስቡ ፖለቲከኞችና ዓጃቢዎችን ቁጥር በብዙ እጥፍ አባዝቶ ቀጥሏል። ደርግ ወይም ሞትየጀመረው የኼው የተወላገደ እና ጸረ-ዲሞክራቲክ የሆነው አስተሳሰብ ሳንወጣ ዛሬምወያኔ ወይም ሞትግንቦት 7 ወይም ሞትኦነግ ወይም ሞት ‘… ወይም ሞትበሚሉ ካድሬዎችና ስሜታዊ የድርጅት አምላኪዎች ተተክቶ እያደናበረን ይገኛል። ለአንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ በዲሞክራሲያዊ ጎዳና ለማቅናትም ሆነ እራሱን ከፍ ወዳለ የሥልጣኔ ባህል ለማደግ ትልቁ መሣሪያ ነጻ አስተሳሰብ እና ግልጽ ውይይት ነው።

ብዙ ጊዜ በእንዲህ ያለው ማኅበረስብ ውስጥ ኅብረተሰቡን በማንቃት፤ እንዲሁም ፖለቲከኞችን በማረቅና ለሚናገሩትም ሆነ ለሚሰሩት ነገር ተጠያቂ በማድረግ የፖለቲካው ባቡር ሃዲዱን ስቶ ሕዝቡንም ይዞ ቁልቁል መቀመቅ እንዳይወርድ ትልቁን ድርሻ የሚጫወቱት ነጻ የመገናኛ ብዙሃን እና ገለልተኛና ደፋር የአደባባይ ምሁራን ናቸው። ነጻ ሚዲያ በሌለበት ወይም በተዳከመበት እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ነጻ ባልሆኑበትና በማይከበሩበት አገር ሁሉ ጨለምተኝነት፣ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና አንባገነናዊነት ይነግሳሉ። በእንዲህ አይነቱ ማኅበረሰብ ውስጥ በጠመኝጃ አፈሙዝ ሥልጣን የተቆናጠጠ የወያኔ አይነት አምባገን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ትናንሽ አምባገነን ድርጅቶችና ግለሰቦችም እንደ አሸን ይፈላሉ። ምክንያቱም የሚፈሩት ሕዝብ የለማ። ትንሹ አምባገነን ትልቁን፤ ትልቁም ትንሹን ይፈራል እንጂ ሕዝብን አይፈሩም። የሰሉና የተደራጁ ነጻ የመገናኛ መድረኮችና ብቃት ያላቸውና ለሕሊናቸው ያደሩ ጋዜጠኞች ባሉበት አገር አንድ ግለሰብ በሕዝብና በአገር አናት ላይ ቆሞ ያሻውን መናገርና መዘባረቅ ይቅርና ገና የፖለቲካ ጎራውን ሲቀላቀል ከልጅነት እስከ አዋቂነት የሄደበትን ጉዞና የሕይወት ታሪኩን በማጥናት ሰው በሕዝብና በአገር ጉዳይ እጁን የማስገባት ሞራላዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብቃት ያለው መሆኑን ሕዝቡ እንዲመዝን ያደርጋሉ። ይህ የፖለቲከኞቻችንን ሥነ-ልቦናዊም መሰረትም ሆነ ምሁራዊ ብቃት እንድናውቅ ከማገዙም ባሻገር የተጠያቂነትንም ባህል ያጎለብታል። በአንድ ወቅት በሕዝብና በአገር ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ ወይም በመጥፎ ሥነ-ምግባር ውስጥ ያለፈ፣ ወይም ከቤተሰቡ አንስቶ በሚኖርበት አካባቢ በመልካም ተግባሩ የማይታወቅ ሰው በምንም መንገድ አገራዊ ኃላፊነት እንዳይጣልበት ያደርገዋል። እስኪ ዛሬ አገሪቷን ተቆጣጥረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም እንባ እያስለቀሱ ካሉት የወያኔ ባለሥልጣናት እና በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው ካሉት የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል ስንቶችን በቅጡ እናውቃቸዋለን? በሁሉም ጎራ ስለተሰለፉት ፖለቲከኞቻችን ያለን መረጃ ምን ያህል ነው? እንዴነ እጅግ ውሱን ነው፤ ስም፣ የትምህርት ድረጃ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የአንዳንዱን እድሜና ጥቂት ነገሮች። የእያንዳንዳቸውን ጀርባ እናጥና ከተባለ ጉዱ ብዙ ነው። በቅርቡ እንኳን ከሟቹ መለስ ዜናዊ እኩል ወይም በተወሰነ ደረጃ ባላፉት ሃያ መታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት ለፈጸማቸው አስከፊ የሰብአዊ መብቶች እረገጣዎች በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው እንደ እነ አቶ ስዮ አብረሃ (የጦር ሚኒስትር እና የሥርዓቱ ቁልፍ ሰው የነበሩ) አይነት ሰዎች ከወያኔ ጋር ስለጠጣሉ ብቻ በሕግ ይቅርና በፖለቲካ መድረክ እንኳን ያለመጠየቅ ከለላ ተሰጥቷቸውና ወቃሽ ሳያገኙ የዲሞክራሲ ኃይሉ አካል ተደርገው ትግሉን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።

ባጭሩ ያጎለበትነው የፖለቲካ ባህል ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ እጃቸው በንጹሃን ደም ለጨቀየ፣ በርሃብና በድህነት በሚሰቃየው ሕዝባችን ውድቀት ሞስነው ለጠበደሉ፣ በግል ህይወታቸውም ሆነ በሙያቸው ላልተሳካላቸው አዳዲስ እና ነባር ፖለቲከኞች መደበቂያ ጫካ ሆኗል። በቅርቡየፍርሃት ባህልን እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ” (https://humanrightsinethiopia.wordpress.com/) በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩትም የገዢዎቹንም ሆነ የነጻ አውጪዎቹን፤ በጥቅሉ የፖለቲካ መዘውሩ ዙሪያ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ጀርባ በቅጥ ማወቅ አለመቻል አንዱ ኅብረተሰብን ለፍርሃትና ከፖለቲካ ተሳትፎ እንዲቆጠቡ የሚዳርግ ምክንያት ነው። እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ከግምት በማስገባት ከዋናው ርዕስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ። በማለት አቶ ያሬድ ግሩም ትንተና አስነብቦን ነበር።

አቶ ያሬድ ኢሳትን እና መሰል ቡድንተኛ ሚዲያዎች የጋዜጠኛነት ሙያቸው ስተው የፖለቲከኞች መጠቀሚያ እየሆኑ እንዳለ በማስረጃ አስደግፎ ያስተማረንን ለማስታወስ እንዲረዳችሁ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፤ የወያኔ ሳያንስ የነፃ አውጪዎቻችን (የግንቦት 7) የግፍ ተግባር እና የመገናኛ ብዙሃን ዝምታ የሚለውን ጽሑፉን በድረገጹም ሆነ በጉጉል ልታገኙት ትችላላችሁ። “ኢሳት የማንንም ሀሳብ አያፍንም” ብሎ ሲሳይ ለሕዝብ ሲያደናግር እኛም የሕዝብ ልሳኖች እና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንደመሆናችን እና እንደ ዜጎች የሚመለከተን ስለሆነ፤ ጋዜጠኞች ያልሆኑትን ‘ነን’ እያሉ ሲዋሹ የማጋለጥ ሃላፊነት ስላለን ትችቴን በዚህ እንድትመለከቱልኝ አሳስባለሁ። ሲሳይ አገና የሚደነቅ የጋዜጠኛነት ችሎታው ወደ እውነት ክፍል በመዞር እውነትን አንዲያገለግል በዚህ አጋጣሚ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብለታለሁ።
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) getachre@aol.com