Wednesday, September 22, 2021

ዶ/ር ዳኒኤል በቀለን የበላ ጅብ ያየ ሰው ካለ ይንገረኝ! ጌታቸው ረዳ (Ethio Semay ድረገጽ አዘጋጅ) 9/22/2021 መስከረም 12/2014

 

                    ዶ/ር ዳኒኤል በቀለን የበላ ጅብ ያየ ሰው ካለ ይንገረኝ!

ጌታቸው ረዳ (Ethio Semay ድረገጽ አዘጋጅ)

9/22/2021 መስከረም 12/2014


ለወንድሜ ዶ/ር ያሬድ ኃይለማርያም የሰብአዊ መብት ጠበቃ ሰላም ካንተ ጋራ ይሁን

ስለ ወንድሜ መታሰር አስመክክቶ ሁኔታውን ስለጠየቅከኝ ጉዳይ በሚመለከት፡

አስቀድሜ ስለ ሁኔታው እንድትከታተልልኝ በኢመይል ጠይቄህ የምትችለውን ያህል እርደታህን ለግሰህልኛልና አመሰግንሃለሁ። ይህ ደብዳቤ አብረውኝ ስለ ወንድሜ መታሰር የተጨነቁ አንባቢዩዎቼ እና የፌስ ቡክ ተከታዮቼ እንዲመለከቱት ጭምር በራሴ ድረገጽ ለጥፈዋለሁ። ይህ የማደርግበት ምክንያት፤ ዜጎች ዳኒኤል በቀለ የተባለ የሰብኣዊ መብት ዋና ዳይረክተር የሚመራው “’ጽ/ቤት” የተጎጂዎች እምባ እያዳማጠ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው።

 ለብዙ አመታት ባሕርዳር ከተማ ኗሪ የሆነው ወንድሜ በነገዱ ትግሬ በመሆኑ የአብይ አሕመድ  ዓሊ መንግሥትና የደመቀ መኮንን  ዓሊ መንግሥት በወኪሎቻቸው በተመስገን ጥሩነህ እና አቶ አገኘሁ ተሻገር በሚያስተዳድርዋት ባሕርዳር ከተማ ውስጥ  “ጁንታ” በሚል መጠሪያ ተሰይሞ ያለ ሃጢያቱ ለወራት እስካሁን ድረስ “ታፍኖ ከቤቱ በማታ ተጠልፎ” ቤተሰብ እንዳያየው ተደርጎ እስካሁን ድረስ ደብድባ ተርጎበት ይሁን ይሙት፤ይኑር፤ ያለጠበቃና ጠያቂ ተይዞ እስካሁን “ሳባታሚት” በሚባል ወህኒቤት እንደነበረ/እንዳለ/ ይነገረናል። የቤተሰቡ ጧሪ የነበረው ወንድሜ በመታሰሩ የሚቀልባቸው አጥተው እየተጎዱ ነው።

ይህንን አስመልክቼ ለአዲሱ ዓመት በ Ethiopian Semay ድረገጽ ላይ የጻፍኩትን እና አንተም የፌስ ቡክ ጓደኛዬ በሆንክበት‘በፌስ ቡኬ’ ላይ በተከታታይ የለጠፍኳቸው ትችቶች እንዳነበብካቸው እገምታለሁ። አሁንም የተቻለህን ያህል ያገዝከን ቢሆንም ባንተ በኩል ለ ዶ/ር ዳኒኤል በቀለ አንድትነግረውና የተጎጂዎች ጩኸት ሊያዳምጥ ያልፈለገበት ምክንያቱን እንዲነግረን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባበ ዛሬም ደጋግሜ ጥሪዬን አቀርብለታለሁ። ዛሬ በፋሺስቱ አብይ አሐምድ ሿሚነት ተሰይሞ “ወንበር ሞቆት” የነጮችን ከንቱ ወዳሴ እየተበረከተለት ደልቶት ቁጭ ቢልም፤ ዳኒኤል ሲታሰር ጩኼለታለሁ። አሁን እኔን የማዳመጥ ተራው ነው።

በእውነቱ እኔ በስህተት ወ/ት የኮሚሽኑ ከፍተኛ አባል ወ/ት ሃና አንዳርጋቸውን አመስግኛት ነበር። እሷ አጋዥ መስሎኝ ነበር ፣ እንደ አለመታደል ሆኖ እሷም አይደለችም። እሷ በቅርቡ ምላሽ እሰጥሃለሁ ብላኝ ጠፋች። በአዲስ ዜና ትመልስልኛለች ብየ ብጠብቅ፣ አሁንም ከእርሷ  ጋር በኢሜል ካገናኘኸኝ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠችም።

ለኔ እንዲህ ጀሮ ዳባ የሰጡኝ ለተራው ሰው ምን እንደሚያንገላቱት ሳስበው በጣም ይከብዳል። እኔ በማላውቃቸው ዜጎቼ  ሲበደሉ ለበርካታ አመታት የምጮህ ያህል በራሴ ወንድም ዝም እንደማልላቸው ይወቁት። ይህ የነ ዳንኤል በቀለ ጀሮ ዳባነት እንደ ተራ የማልፈው ሳይሆን፤ እልባት ካላገኘ፤  በመጽሐፌም በኩል ከታሪክ እንደምዘግበው አያውቁ አንደሆነ ካሁኑ እንዲያውቁት አሳስባቸዋለሁ።

መስከረም 11/2021 በዕሜው ገና ወጣት የሆነ ታዳጊ የወንድሜ ልጅ እና የወንድሜ ባለቤት  ለአዲሱ ዓመት መስከረም 1/ 2014 (ቅዱስ ዮሐንስ) ወንድሜን እንዲጎበኙ ይፈቀድላቸው እንደሆነ ለማየት ወደ “ሳባታሚ” ባህርዳር ወህኒ ቤት ሄደው ነበር።

(የአቶ ደመቀ መኮንን ጌስታፖዎች/ የማረሚያ ቤት ጠባቂዎች) የወንድሜን ሚስት እና ልጁን በፕላስቲክ በተሸፈነ የብረት በትር ደበደቡዋቸው።  “ጁንታዎች” ከዚህ ጥፉ ብለው በመጥራት ደጋግመው ደበደብዋቸው። በደረሰበት ድብደባ ምክንያት ልጁ የአጥንት መሰበር እና የቆዳ  መተርተር ደርሶበት  በ 6 “እስቲች ተሰፍቶ” ደም ፈስሶበት ሆስፒታል መተኛት በሚያስፈልገው በአይን ቅንድብ አጥንቶቹ እና ደም ስሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። ይህንን ግፍ ለወ/ት ሃና አንዳርጋቸው ኢሜል አድርጌ ነበር ፣ ምንም ምላሽ አላገኘሁም። አንዴት አንደምታገኛቸውም ስለካቸውን ሰጥቻታለሁ። ታውቀዋለች። ሌላ ምክንያት ልተሰጠይ አትችልም።

ከዚህ ግፍ እና ሰሚ በማጣት ተነስተን ኢትዮጵያውያን ሪፖርት ማድረግ የሚችሉት ከየት ነው? ይህ እራሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ብለው የሚጠሩ የኛዎቹ ሰዎች “የሰብዓዊ መብቶችን ስም” መጠሪያ እየተጠቀሙ በደል የደረሰባቸው ዜጎችን የማያዳምጡ ከሆነ በንጹሐን ዜጎች ላይ የዘር ማጽዳት ሲካሄድ ኢትዮጵያዊ ሌላ የት ሪፖርት ሊያደርግ ይችላል?

ወንድሜን ወደ እስር ቤት ሲወስዱት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዘው አልነበረም ፣ ቤተሰቦቹ እንዲጎበኙት፤ ምግብ ይዘውለት እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም ፣ በሕይወት ይኖር ወይም ከሞተ ወይም፤ ድብደባ ደርሶበት  ከተሰቃየ የምናውቀው ነገር የለም። ማንም ጠበቃ እሱን አልወከለም። አንዲወከልም አልተደረገለትም። ለዚህ ሕገ ወጥ አሰራር ለማን አብየት እንበል?

የሚገርም ደግሞ፤ አንዳንድ እስረኞች በጉቦ ሲፈቱ ሰማሁ። የዚያች ከተማ ጌስታፖ ባለሥልጣናት እንደ ወንድሜ እና ቤተሰቦቹ በንጹሐን የትግራይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በባሕርዳር ውስጥ እየሆነ ያለው ይኸው ነው።

በአሁኑ ወቅት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው አዳጊ ወጣት በእስር ቤቱ ጠባቂዎች ለእስር የተዳረገውን አባቱን ለመጠየቅ በመደብደቡ ምክንያት በከባድ ሥቃይ ውስጥ ይገኛል። የዶ /ር ዳንኤል በቀለ ጽ / ቤት ተብዬው የዜጎችን የእርዳታ ጩኸት ችላ ካለ ዜጎች ከዚህ በላይ የት ይግባኝ ማለት እንችላለን?

ሼር በማድረግ ዜጎች የፍትህና የአስዳደር ሰዎች እንዲያዩት ለማድረግ ትብብራችሁ እጠይቃለሁ።

አመሰግናለሁ

Getachew Reda

Editor Ethiopian Semay