Sunday, January 22, 2012

ጠላ ቤቶች ብቻ ነው የቀሩት!

ጠላ ቤቶች ብቻ ነው የቀሩት!


የወያኔ ገበና ማህደር $30.00  (ደራሲ ጌታቸው ረዳ)
ይድረስ ለጎጠኛው መምህር $25.00 (ደራሲ ጌታቸው ረዳ)
ሓይካማ (ትግርኛ) $20.00  (ደራሲ ጌታቸው ረዳ)

በመላክ መጽሐፍቶቹን ማግኘት ይቻላል። ወደ አዲስ የሕትመት ዙር ካልገባሁ በስተቀር (የአንባቢው መጠን የሚወስነው ይሆናል) አሁን የቀሩት ጥቂት ቅጅ ካላገኛችሁ መጽሐፍቶቹ እንደልብ አይገኙም።አሁን እንደ ዋዛ የምናያቸው መጽሐፍቶች እንደተቀሩት የኢትዮጵያ መጽሐፍቶች ለትውልድ ሲተላለፉ እንደመርፌ በመከራ ይፈለጋሉ።
Getachew Redda
P.O.Box 2219
San Jose California
95109 
(408) 561-4836

 To view the fonts/pictures (page) bigger or smaller press your keyboard (Ctrl and + sign) (Ctrl and –sign)
ጠላ ቤቶች ብቻ ነው የቀሩት!
ጌታቸው ረዳ
የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አንባቢዎች፤ እንደምን አላችሁ? ዛሬ የማቀርብላችሁ ርዕስ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘመነ ወያነ እየታየ ያለው አሳፋሪ የባህል ወረርሺኝን በሚመለከት ነው፡፤ ወያኔዎች በረሃ ሲወጡ አንደኛው ምክንያታቸው “አማራ የብሔረሰቦችን ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን በመጫን ንግድ ቤቶች እና ተቋማቶችን፤የፍትህ እና የመሳሰሉ የሥራ መገናኛዎች በአማርኛ እንዲሆን “አማራዎች” ለብዙ ሺህ ዓመታት ተጽእኖ አድርገውብናል” በሚል ነበር ሁሌም ዛሬም ሲለፈልፉ የነበሩት(ዛሬም አለማፈር ያንኑ ሲደግሙት ታነባላችሁ/ታደምጣላችሁ)።
ሆኖም ዛሬ የሚታየው ባህል ወረርሺኝ ለምሳሌ በቅርቡ ትግራይ ድረስ ለጉብኝት የሄዱ ሰዎች ሲነግሩኝ “ጌሾ” ተብሎ የሚታወቀው የጠላ እና የጠጅ ቅመም ተክል ምትክ ከፍ ያለ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ማለትም ገዳማቱ እና ቤተክርስትያናቱ (ገጠር ሁሉ) የተለያዩ ደረጃ ያላቸው “ጫት”በማብቀል ለገበያ በማቅረብ በጌሾው ምትክ ብዙ ገንዘብ  እያገኙበት አንደሆነ እና፤ሲጃራ ማጨስ እንደ ነውር ሲቆጠር በነበሩባቸው ከተሞች ሁሉ ሳይቀሩ የጫት መሸጫ ሱቆች እና “መመርቀኛ” ቦታ ተከፍተው ሰዎች ማታ ከስራ ወዲህ የሚዝናኑባቸው ቦታዎች በብዛት ተስፋፈተዋል። መንገድ ላይ ስታልፍ “የሓሺሽ” ጭስ እንደሚሸታቸው የታዘቡ ሰዎች ነግረውኛል። በዚህ ጫት እና በመሳሰሉት ዕጾች ሰበብ “ብዙ ትዳር” እንደፈረሱ ነግረውኛል። የወያኔ ራዲዮ ጣቢያ “ድምፂ ወያኔ ትግራይም” በተከታታይ ሁኔታውን ዘግቦት እንደነበረ ትዝ ይለኛል።
የወያኔን “ቦሶሮ” ሰነፍ አስተዳደርን በማሕበራዊ ባህል ጉዳዮች ያስከተለው  ጥቃት ስትመለከቱ ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ መቀሌ ከተማ በሦሰት ማዕዝኖች ተዋቅረው በምስጢር ስም የሚጠሩ “ጋንጎች” /የከተማ ወረበሎች/ ከመንግሥት የፍትህ እና የፓሊስ አካላት በመመሳጠር  ከተማዋን በማወክ “በዝርፍያ፤እና ሰው በመደብደብ” እንዲሁም ለመቆጣጠር በሚሞክቸው ፖሊሶቹንም ሳይቀር በቀን ፀሐይ በድፍረት እንደሚደበዱቧቸው እንደሚያስፈራሩዋቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። ባንድ ወቅት (አምና) የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ/ኮሚሽነር
በጋንጎች ተደብድቦ ገደላማ ስፍራ ውስጥ ጥለውት ከነሽጉጡ እንደተገኘ መዘገቡ ታስታውሳላችሁ። የወያኔ አስተዳደራዊ ጉብዝና ሲመዘን አሳፋሪነቱ በግልጽ ማየት የሚያስቸላችሁ መረጃ ከዚህ ወዲያ ሌላ አያስፈልግም።
በሌላ በኩል ደግሞ የወያኔ የባህል እና የቋንቋ አብዮት የሚከተለው አሳፋሪ ወረርሺኝ ለኢትዮጵያ አስገኝቶላታል። ንባቡን ይከታተሉ።ዘገባው የተዘገበው ሁኔታው ያሳሰባቸው በወያኔ የዜና ማሰራጫ አውታሮች ተቀጥረው  በጋዜጠኝነት የሚተዳደሩ ዘጋቢዎች ያጠናከሩት ነው። የወያኔ የቋንቋ እና የባህል አብዮት ለኢትዮጵያ ያስገኘላት ዕድገት ይህ አሳፋሪ እርምጃ አንብቡ።
ዘገባውን ያጠናከረው ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ዘገባው ይጀምራል፡-
"ተጨባጭ ሁኔታው  ትናንት ወደ ጎን እንቃኛቸው የነበሩ ቤቶች ወደ እላይ ተመንጥቀው ቀና ብላችሁ ካላያችሁን የሚሉ ይመስላሉ።ይኼ እንግዲህ በታላላቅ ከተሞቻችን የምናስተውለው አስደሳች ሁኔታ ነው።ታዲያ ቀና ብለን ካስተዋልናቸው ግዙፍ ህንፃዎች ላይ ዓይናችን ሳይነቀል እይታውን ከቀጠለ፤ “ትኩረትን የሚስብ ሌላ ነገር አለ”፡ እዚህም እዚያም የተሰቀለ የተለያየ ስያሜ በደማቅ ቀለማት ያሸበረቁ አብዛኛዎቹ የንግድ ድርጅቶችና የሌሎቹ ስያሜዎች ከሌሎች በእርግጥም እይታ ይጠራሉ።ችግሩ ግን ከአገሩ ሰው ይልቅ የውጭ አንባቢ የሚሹ ይመስላሉ።
በባሕር ማዶ የሚገኙ ከተሞች ስም የተሰየሙ ባዕድ ሃገር ዝነኛ ሰዎችን ስም ስያሜ የተዋሱና ከኢትዮጵያዊ ባህል ይልቅ የውጩን ልምድ የተላበሱ በብዛት ይታያሉ።ነገሩ ዘመናዊ በሚባሉ አካባቢዎች የከፋ ይሁን እንጂ የውጭ ስያሜ ወረርሺኝ ግን የከተሞችን ጥጋ ጥግ በፍጥነት እያዳረሰ ነው። አንዳንዶች የሚሉት ከሆነ ደግሞ ከውጪው ስያሜ ይልቅ ሃገራዊ ስያሜዎችን ፈልጎ ማግኘት አዳጋች እየሆንም ነው።"
በባዕድ የባሕል እና የቋንቋ ወረረሺኝ ኩፉኛ እየተጠቁ የመጡት ከተሞችን አስመልክተው አስተያየታቸውን ተጠይቀው የመለሱት መምህር እና ደራሲ የሆኑት አቶ ኃይለመለኮት መዋዕል እንዲህ ይላሉ፡
“ከባዕድ የሚመጣ ስም ዓለም አቀፍ ስም ካልሆነ በስተቀር እኛ ላይ መጥቶ የሚለጠፍ ስም የኛ አይደለም።ራዲዮ ልንል እንችላለን ሳተላይት ልንል እንችላለን ዓለም የተቀበለው ነው። ካሜራ -አሁን ፊት ለፊቴ እንዳለው፡ ይኼ ዓለም በሙሉ የሚጠቀምበት ነው። ነገር ግን የትምህርት ቤቶችን፤አጸደ ህፃናትን፤አንደኛ ደረጃ፤ሁለተኛ ደረጃ ፤ከዚህ አልፈህ ደግሞ ለመዝናናት የምንኼድበት ቦታ “ቡና ቤቱ፤ሆቴል ቤቱ፤ካፍቴሪያው፤ሻይ ቤቱ ምኑ ቀረ? ጠላ በቶቹ ብቻ ናቸው የቀሩት። እነሱም ሳይጀምሩ አይቀሩም።
ለምሳሌ አንድ ጸጉር ማስተካከያ ቤት (ስሙን አላነሳውም) በአማርኛ ቢተረጉመው የተሻለ ስም ሊሆን የሚችል በእንግሊዝኛ ተጽፏል፤ ወደ ሰፈሬ ስኼድ መንገድ ሳልፍ የማየው ነው። ይኼነን አሁን በአማርኛ ቢጠራው የበለጠ ያምር ነበር።”
አንድ ታዛቢ መንገደኛ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት ደግሞ አስተያየቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል።
“እኔ እንጃ “ቴድሮስ””አራአያ” “ዘርአይ ደረስ”..የሚባል ስያሜ አይቼ አላቅም እስካሁን ድረስ ፤በእውነት ነው የምልህ።”
አዘጋጁ እንዲህ ሲል ትችቱን ይቀጥላል፡
“ያለንበት “የብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ቤት በሆነቺው ኢትዮጵያ ውስጥ ነን። የተለያዩ ቋንቋዎች እና የባህል ስብጥር ደምቆ የሚታይባት ድንቅ ምድር። የረጂም ዘመን አኩሪ ታሪካችንም ቢሆን ሌላው መለያችን ነው። ታዲያ ምኑ ቸግሮን ይሆን የውጭ ስያሜ የምንዋሰው? ሲል ከጠየቀ በላ ፡ አንድ ወጣት መንገደኛ አሁንም አስተያየቱን እንዲሰጥ አቁሞ ይጠይቀዋል። ወጣቱ እንዲህ ይላል።
“ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሰፍር ቁጥር የሌለው ታላላቅ ነገሮችን የሰሩ የጀግኖች አገርና ብዙ ታሪክ ያላት አገር ናት። ስለዚህ ከነዚያ ጀግኖች እና የታሪክ ስፍራዎች ስም በመጠቀም መሰየም ይቻላል ብየ አስባለሁ።”
አሁንም ደራሲ እና መምህር የሆኑት አቶ ኃይለመለኮት መዋዕል  አሁንም ከላይ ካቆሙት አስተያየታቸው በመቀጠል እንዲህ ይላሉ፡
“በወረራ ያልተያዝነው፡ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከክን ሕዝቦች፤በሰላሙ ዘመን በደህናው ጊዜ “ቅድመ ግሎባላይዘሽን ነው- አሁን ነው 16 እና 20 ኣመት ውስጥ የመጣው” በመምጣቱ ሰበብ የተነሳ “አውሮጳ ውስጥ የሚገኙ ስሞች፤ላቲን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ስሞች፤ ሰሜን አሜሪካኖች ውስጥ የሚገኙ ስሞች ካናዳ ትላልህ … የቀረ የለም  …የሚገኙ ስሞች፤ አልፎ ተርፎም እስከ ሩቅ ምስራቅ እስከ ጃፓን፤ጃፓን እና ቻይና ድረስ ኼዶ እዛ ድረስ ያለው ስም፤ወደ አገራችን እየገባ፤ ብሔራዊ ማንነታችንን በባህል ደረጃ ሊያጠፋ ወይንም ሊሸፍነው “ምንም ያህል አልቀረውም”።
የውጭ አገር ስያሜ ኢትዮጵያ ውስጥ መገልገል የስልጣኔ ምልክት እና አልፎም እንግሊዝኛ ቋንቋን ተሎ እንዲገባህ ይረዳል ሲል የባህል ወረርሺኙን እንደበጎ ነገር የተመለከተው አንድ “ምስኪን-ገራገር” አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ሲል ባለው ላይ ተጨማሪ ድንጋጤ ሲጨምርብን ታደምጡታላች ; እንዲህ ይላል፡
“እኔ እንዳውም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሳያቸው ደስ ይለኛል።ለምን? አፍ መፍቻ ቋንቋችን አማርኛ ስለሆነ እንግዘሊዝኛ ቋንቛዎችን ደግሞ እያወቅን እና ብዙ እየተማርን አንዳንድ የውጭ አገር ሰዎች ሲመጡ በእንግሊዝኛ ለማናገር ያፍ መፍቻ ይሆናል ብየ አስባለሁ።”
አሁንም መምህር እና ደራሲ የሆኑት አቶ ኃይለመለኮት እንዲህ ሲሉ ይቃወሙታል።
“እርግጥ አንግሊዝኛ አለም አቀፍ ቋንቋ ነው። ፈረንሳይኛ፤ዓረብኛ እነኚህ የትም ኼደህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትም ኼደህ የምትነጋገርባቸው ቋንቋዎች ናቸው። እነሱ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ሆነዋል እና የኔን አማርኛ፤ የኔን ኦሮምኛ የኔን ትግረኛ እና አፋርኛ…ወዘተረፈ.. እንዲያንኳስስብኝ እና ለቅራኔ እንዲለውጣቸው መፍቀድ የለብኝም። በምን ምክንያት? በተለይም እኛ - ትምክህት አይደለም ፤በተለይም እኛ ከቅኝ ግዛት አገዛዝ  የወረስነው ድሪቶ መልበስ የለብንም! አዲስ የባህል ድሪቶ እያመጣን የነሱን እየተሸከምን ነው። የራሳችን ጸጋ ለምን እናጣለን ነው ትልቁ ነገር።
ስለዚህ ቋንቋ ግንኙነቱ አይደለም ዋናው አሳሳቢው ፍሬ ነገሩ፡በዓለም አቀፍ ቋንቋ መገናኘት ባሕሪያዊ ነው፤ አግባብም ነው።  ዓለም በሚሰማህ ቋንቋ ስትናገር ልትደመጥ ትችላለህ፡ነገር ግን እኔና አንተ በምንገናኝበት ጊዜ ካልቸገረ በስተቀር ለምንድነው በባዕድ ቋንቋ የምንነጋገረው? ወይንም ደግሞ ሃሳቤን ለመግለጽ ካስፈለገ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ካልሆነ በስተቀር፤ ለምን የገዛ ቋንቋየን የሌላ ቋንቋ የምሰነቅረው?
እንግሊዝኛ የራሱ አገር አለው። ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኗል።በታሪክ ምክንያት። እኔ ግን እንግሊዝኛን የምጠቀምበት አንድ ቃል እንኳ የምወስደው ከራሴ ቋንቋ የምተካበት ቃል ሳጣ እና የማናግረው ሰው ያቺን ቃል ብጠቀም ያቺ ቃል ትጠቅመዋለች ስል ነው። ዛሬ፤ዛሬ በውጭ ስያሜ ያልተሰየሙ፤የንግድ መስኮች ለማግኘት የሚያዳግት ነው። እንደፋሺንም የተያያዘም ነው የሚመስለው።በተለይ ደግሞ በግል የትምህርት ተቋማት አካባቢ ነገሩ የከፋ ነው።ከአጸደ ህፃናት ጀምሮ፤ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ አዳርሶታል።...'
አሁንም ዳረሲ እና መምህር የሆኑት አቶ ኃይለ መለኮት እንዲህ ይቀጥላሉ።
“በጣም ጎጂው እና እጅግ አደገኛ የሆነው፤ ከስር ጀምሮ  የሚገኘውን ትውልድ የሚያበላሽብንና ቅኝ የተገዙ አገሮች አንኳ (ካገሬ ወጥቼ አላውቅም)ያደርጉታል ብየ ያልጠበቅኩትን ነገር እያየን ነው።የአጸደ ህጻናት ት/ቤቶች በሙሉ በመቶኛ መናገር አይቻልም እንጂ “በባዕድ ስም ሆኗል” ስማቸው መጥቀስ ይቻላል፡ አስፈላጊ አይደለም እንጂ፤ምክንያቱም እራሳቸው ያውቁታል፤ በፈረንጅ ስያሜ የሰጡ። ለመሆኑ ትምህርት ቤቶች በፈረንጅ ስም ካልተሰየሙ ትምህርት ቤቱ ትምህርት ቤት መሆን አይችልም ማለት ነው?” የፈረንጅ ስም ካላቸው ት/ቤቶች ውስጥ (ሙን ላይት ስኩል ) በዕድሜአቸው ወጣት የሆኑ ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ፈንታሁን ሀሰን የተባሉ እንዲህ ብለዋል፤፡
“የትምህርት ቤታችን ስያሜ ‘ሙን ላይት ኢንተርናሽናል አካዳሚ ነው።” ኢንተርናሺናል ከመሆኑ አንጻር፤ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ይማራሉ ብለን የምንጠብቃቸው፡የተለያዩ የኢንተርናሽናል አገር ዜጎች ለኖሩ ይችላላሉ። እና አንደ ኢንተርናሽናል ተቋምነቱ ለሌላው ተደራሽ እንዲሆን ከሚል አንጻር ነው እንግሊዘኛ እንዲሆን ያደረግንበት ስያሜ ምክንያት። እንደሚመስለኝ ቅድም ያልኩህ አንድ ነገር አለ።አንዳንድ ድርጅቶች/የትምህርት ተቋማት፤የሚሰቷቸው ስያሜዎች የራሳቸው የሆኑ የፍልስፍና ይዘቶች ይኖራቸዋል።ሁለተኛ የግሎባላይዘሽን ተጽዕኖ ይመስለኛል።ሌላው ደግሞ በት/ቤቱ እይታ በወላጅ ዘንድ በተጠቃሚው የበለጠ ለማስረጽ እና ት/ቤቱ የተሻለ ጥራት/ሲስተም አለው ለማስባልም የሚጠቀሙ ይመስለኛል የእንግሊዝኛው ስያሜ የሚጠቀሙት።
የወላጆች “አንፍልዌንስ” ያለው ይመስለኛል። የተጠቃሚው የትምህርት ቤቱ ወላጆች ከስያሜው የተነሳ የሚሰጡት ግምት ብዙ ባለ ሃብቶች ወይንም የትምህርት ተቋሞቹ ባለቤቶች ስያሜው ወደዛው እንዲሆን የመራቸው ይመስለኛል።”
አቶ ኃይለመለኮት መዋዕል
“አማርኛው ትግርኛው ወላይትኛው ከምባትኛው ዓፋርኛው ኦሮሚኛ ሶማሊኛ በለው ሁሉም ውብ የሆኑ ቃላቶች አሏቸው። በፈረንጅኛ የሚገለፁትን እንዳውም አሳምረው ሊገልፁ የሚችሉ።
ለምሳሌ “ቀጤማን” እንውሰድ ውብ ነው አደለ? ቀጤማ ካፈተርያ ቢለው ገና ስሙ ሲጠራ አያስደስትህም? ዘምባባ ምግብ ቤት ብሎ ቢሰይመው አያስደስትህም? …ዋርካ! ዋርካ ትልቅ ነገር ነው አደለም? ዋርካ ሆቴል! ብሎ ቢል አይታይህም ትልቅነቱ  ከነ ግርማ ሞገሱ!..ሾላ ሻይ ቤት! ከነተረቱ ሾላ አርግፍ፤እርግፍ እያልን ነው የምንጠራው፡ ከዚህ የበለጠ ስም የት አለ?
ሴዳር ካፍተርያ ከምትል፤ የኛው አይበልጥብህም፤ ፓልም ሆቴል ከምትል “ዘምባባ” አይመረጥም? እንደገና ደግሞ ትልልቅ የውጭ አገር ሰዎች በሚሰየሙት ላይ ለምሳሌ የነሱን ሰዎች ስም ስያሜ እዚህ አምጥተው ይሰይማሉ፡ የእኛ ትላልቅ ሰዎች መቸ አጣን እና ነው? ሞልቶናል ሰው! ፈልጎ ጠይቆ ማምጣት ይቻላል።”
የሙን ላይት ርዕሰ መምህር ፈንታሁን ሃሰን እንዲህ ሲሉ ይከራከራሉ።
“ከስያሜው በስተጀርባ ሃገራዊ የሆኑትን ነገሮችን የመስራት ስራ ነው ትልቁ ትኩረት መሆን ያለበት። ተማሪዎች ለአገራቸው ለወገናቸው አፍቃሪና አዛኝ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ከውስጥ መስራት ይጠበቅብናል ማለት ነው ከስያሜው በስተጀርባ። ብዙ ት/ቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ ኢትዮጵያዊ ስያሜ የያዙ። የሚሰሩዋቸው ስራዎች ግን “almost” ከኢትዮጵያውያን ባህል የማይሄዱ “systemሞች” ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ ከውጭ ከምትሰይማቸው ስያሜዎች  ይልቅ ከውስጥ የምትሰራቸው ስራዎችን ትኩረት ብናደረግ የተሻለ ነው እላለሁ።”
ጋዜጠኛው፡
“ ዕድሜ ለተረጋገጠው የመረጃ መረብ እያልን ዓለምን በየቤታችን ሆነን መዳሰስ ከጀመርን አመታት ተቆጥሯል።አሁን ባለንበት የጉለባላይዘሽን ደግሞ ምድራችን ይበልጡ የጠበበች መስላለች። ታዲያ በጎ ጎን እንዳለው ሁሉ ጣጣውም የከፋ ነው።በተለይም ለታዳጊ ሃገሮች። በተሌይም  ግን ስንቶቻችን ነን “ችግሩን” ያስተዋልነው?
ምንም ችግር አያመጣም የሚለው አንድ አስቀድሜ የጠቀስኩት “ምስኪን-ገራገር” አስተያየት ሰጪ ደግሞ ጋዜጠኛው ሲጠይቀው እንዲህ ብሏል።
ምንም የሚያሳስበኝ ነገር እኔ አይኖርም። የሚጠፋኝ ነገር አይኖርም ፤የሚያሳስበኝ ነገር ደግሞ ብዙም አይኖርም።”
ደራሲና መምህር አቶ ኃይለመለኮት መዋዕል ደግሞ “ብዙ የሚያሳስብ ነገር አለብን እንጂ! በማለት እንዲህ ይገልጹታል።
“እልፍ ኣእላፍ ቴሌቪዥን ጣብያዎች ከፍተው፤ ወጣቶቻችን አፋቸውን ከፍተው ቀኑን ሙሉ እነሱ ላይ አፍጠው እንዲመለከቱ አድርገዋቸዋል። እንዳይሰሩ እንዳይማሩ፤እንዳይመራመሩ፤ ሃገራዊ ማንነታቸው እንዳይረዱ ያደርጓቸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ “ወደ ላ ትቀራለህ። ወደ ላ በቀረህ ቁጥር ደግሞ “ሰብአዊ ጉልበትህንና ኣእምሮህን ይመዘብሩሃል”፡ ወይም በእነሱ እንድታመልክ ያደርጉል።በነሱ ካለመለክ ደግሞ “ለመገዛት ትሄዳለህ”። “ጠርተው ይገዙል፤ እዚህም ሆነህ ይገዙል”። ስለዚህ ከዚህ ለመውጣት የባህላዊ ነፃነት ትግል ያስፈልግሃል። ይህንን ደግሞ በአዋጅ አይደለም፡፤ ራሳችን ይህ ልክ አይደለም ብለን መውጣት አለብን! ሁልግዜ ምንም አይደል እያልክ የምትቀበለው ነገር፤እንደሚገነደስ ትልቅ ቅርንጫፍ “እላይህ ላይ ይወድቃል”።
ጋዜጠኛው፦
“በሃገራችን ስያሜ ምትክ ቦታው የውጭ ቃላት እየተረከቡ መምምጣታቸውን ጉዳይ በስፋት የቀጠለ ሲሆን፤የተለያዩ አስተያየቶችንም የሚያጭር ሆኗል። በርግጥ ሃገራዊ እሴታችን ለምን ይገፋል የሚለው የቁጭት አመለካከት ያመዘነ ቢሆንም፤ ምክንያታዊ መነሻ በተለያየ መልኩ ይገለጻል። የቋንቋ ፍቅር አንስቶ ከማንነት ጋር እስከተያየዘ ድረስ……ብሎ ጋዜጠኛው ወደ አንዲት ወጣት ሴት ልጅ አስተያየት በመዞር የሚከተለውን አስተያየቷን እንዲህ ትላለች።”
“አገርህን ስትወድ እኮ “ሁሉንም ነገር መውደድ አለብህ”። ሰለ እማናውቀው ነገር ከምንጽፍ የራሳችን የሆነ ብናስተዋውቅ የተሻለ ምጥቀት አለው።”
አንድ ወጣት ደግሞ እንዲህ ይላል፦
“በርካታ የንግድ ስቆች እና ተቋማት ስያሜዎቻቸው በእንግሊዝኛ ብቻ የምታስተዋውቅ ከሆነ የኛ መገለጫችን ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊነታችን ታዲያ ምንድ ነው?”
መምህር እና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ደግሞ እንዲህ ያጠቃልሉታል።
“የራሱን ክብርና ባህል ያልጠበቀ ዜጋ የሌላ ቀላዋጭ ነው የሚሆነው።ከመቀላወጥ ደግሞ የባሰ አፀያፊ ነገር የለም። ልመና ማለት ነው! የኢኮኖሚ ለማኞች ልንሆን እንችላለን። ሰርተን እስኪያልፍልን ድረስ።የባህል ለማኞች መሆን ግን የለብንም። ሲሆን ከኛ ነው መውሰድ ያለባቸው እየለመኑ።  ሃገሩን መንጠቅ ሲያቅታቸው “የባህል ቅን ተገዢዎች ያደርጉሃል”። የባህል ቅኝ ተገዥ መሆን ደግሞ ከዋናው ቅኝ ተገዢነት የበለጠ ይጎዳል። ያኛው “ኮተቱን ጭኖ ይሄዳል” በትጥቅ ትግልም በብሔራዊ ወኔም ታግለህ ሰንደቃላማህን ልትሰቅል ትችላለህ። “ሰንደቃላማ የማትሰቅልበት እንደወራሪ ጠላት የማታስወግድበት ወረራ የባህል ወረራ ትልቁ አደጋ ነው። ስለዚህ ይህ ችግር በመንግሥትም በሕዝብም ታስቦበት ሊታረም ይገባል።”http://www.ethiotube.net/video/17458/Must-Watch-Documentary--Ethiopian-Business-and-their-Foreign-Names-in-Ethiopia   ኢትዮጵያ ሰማይ ድረገጽ -ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com getachre@aol.com