Sunday, October 20, 2019

እዚህ ደርሰናል ኢትዮጵያዊያን! አንዱ ዓለም ተፈራ ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ቀን Ethio Semay


እዚህ ደርሰናል ኢትዮጵያዊያን!
አንዱ ዓለም ተፈራ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ቀን
Ethio Semay
barbarous society allowed to go this far under the Oromo  Abiy Ahmed  facistic system
በጋራ በሆነው ታሪካችንና የዕለት ተዕለት ተግባራችን እንደምንኮራ ሁሉ፤ ይሄውላችሁ የጋራ የሆነው የአሁኑ ተግባራችን። እየሰቀጠጠኝ፣ እንባዬ ዓይኖቼን እየጋረዳቸውና ጉሮሮዬን እየተናነቀኝ ያየሁት ይህ ተግባር፤ እውነት ይሄ ዛሬ፤ ፳ ፻ ፲ ፪ በኢትዮጵያ የተካሄደ የኢትዮጵያዊያን ተግባር ነው! ብሎ ማለቱ አስቸግሮኛል። ዛሬ በደረገጽ እየተሠራጨ ያለውን አንድን ወጣት የወጣቶች መንጋ በዱላ ሲቀጠቅጡት ያየሁት ቪዲዮ! ይቅርታ እኔ መልሼ እዚህ ልለጥፈው ቀርቶ፤ ሌሎች ሲያደርጉትም፤ ምን ያህል ልባቸው እንደቻለ ገርሞኝ፤ እዚህ ልለጥፈው አልቻልኩም። ግለሰቦች በአንድ ነገር ተበሳጭተው፤ ቆይተው የሚጸጸቱበት ዕርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ይሄ ያለ ነው። እናም፤ የግለሰቦች ተብሎና ተቀባይነት የሌለው ምግባር በመሆኑ ይነቀፋል። በኅብረተሰቡም ውስጥ የተለየ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ፤ እርም ተብሎ ይወገዛል። እዚህ ቪዲዮ ላይ ያየሁት የግለሰብ ተግባር አይደለም። ይህ የስብስብ ዕርምጃ ነው። የትም አካባቢ ተፈጸመ የትም፤ በየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪዎች ተፈጸመ በየትኛውም፤ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ሆነ ምዕራብ፣ ሰሜን ሆነ ደቡብ፤ ይህ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ ሊዘገንነንና ቆም ብለን የደረስንበትን የፖለቲካ ዝቅጠት እንድንመለከት ሊያስገድደን የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህ የወንጀል በቀል አይደለም! ይህ የፖለቲካ ክንውን ነው! ይህ፤ እኒህ በደሉን የፈጸሙት ግለሰቦች ራሳቸው ብቻቸውን በተናጠል የፈጠሩት የአመለካከት መላሸቅ አይደለም! እዚህ እንዲደርሱ፤ መጓጓዣና ቀለቡን የሰፈርንላቸው እኛው ሁላችን በድምር ነን። በዚህ ጉዳይ በግምባር ቀደም፤ ይህ ወንጀል በተፈጸመበት ቦታ ካሉት የቀበሌ መሪዎች ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ያሉት ሁሉም ተጠያቂዎች ናቸው! የልጁ ደም በጃቸው አለ! ሌሎቻችንም ነፃ ልንሆን አንችልም!

ዛሬ፤ ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ቀን ነው። ይሄን ተግባር ያየሁበት ዕለት፤ በሕይወቴ ዘወትር ከፊቴ ከሚደቀኑብኝ ዕለቶች አንዱ ሆኗል። ይህ ተደብዳቢ ወጣት ያሳለፋቸውን የስቃይ ደቂቃዎች ባየሁበት ጊዜ፤ ልቤ ውስጥ ያደረውን የተስፋ ስልብነት ለመረዳት፤ የተደብዳቢው ወላጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ የመንደሩ ሰው፣ የርሱ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን የለባችሁም። እናንተም ብትሆኑ ከኔ የተለየ ግንዛቤ አይኖራችሁምና! ኢትዮጵያዊ መሆናችን በቂ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ሰው መሆናችን በቂ ነው! ጣታችንን ቀስረን፤ “እኒህ ወንጀለኞች ናቸው!” ብለን የፍርድ ነጎድጓዶችን ለማውረድ መቋመጣችን አይቀርም። ከኢትዮጵያዊያን ውጪ ያሉት ሲመለከቱት፤ “ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ናቸው!” በማለት፤ ስለኛ የሚኖራቸውን ግንዛቤ፤ ለናንተው እተወዋለሁ። እኛ ግን፤ ረጋ ብለን ራሳችንን እንፈትሽ! ይህ የሚያሳየን፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን እዚህ መድረሳችንን ነው። ጃዋር፤ “በቆንጨራ አንገት አንገቱን እቆርጠዋለሁ!” ሲል፤ ቀልድ መስሎት ያለፈ ብዙ ነበር። “አይሆንም! ዝም ብሎ ሲዘባርቅ ነው!” ብሎ የተወው፤ ቁጥሩ ከዚያ የላቀ ነበር። ቄሮን አሰልፎ ከመንግሥት ትዕዛዝ ውጪ፤ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ሕገ-መንግሥቱን ሲጥስ፤ “የትም አይደርስም!” ብለው የናቁት ብዙዎች ነበሩ። ታጥቆና ታጅቦ በአዲስ አበባ ከተማ ሲንፏለል፤ እጅ የነሱት እየበዙ ሄዱ። “ጉልበት ወሳኝ ነው!” ብሎ አወጀ። በጀዋር ዓለም፤ ሕግና ደንብ ቦታ አጡ። ይህ ለወጣቶች ምን አስተማረ?

እንመርምረው! አምባገነኖች፤ ሊፈጠሩና ሊያይሉ የሚችሉት፤ ሁኔታው ሲመቻችላቸው ነው። ጥቂት ደጋፊዎች ሲያገኙና አብዛኛው ዝምታውን ሲያበዛ ነው። እናም እኛም አሁን ሁኔታውን አመቻችተነዋል። ነገ በኢትዮጵያ አምባገነንነት ተመልሶ ቢነግሥ፤ ልንደነቅ አይገባም! ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች የተለየን አይደለንም! ሌሎችም አምባገነኖች የተፈጠሩባቸው፤ እነሱ የተለዩ ሆነው ሳይሆን፤ ሁኔታውን ስላመቻቹላቸው ነው። እኛም ያንን እያደረግን ነው! የኒህ ወጣቶች እንዲህ ያለ ጭካኔ ማድረግ፤ ሊገርመን አይገባም። እኛ ኢትዮጵያዊያን እዚህ ደርሰናል!

በነገራችን ላይ የጽሑፌ ማጠንጠኛ ግለሰቦች አይደሉም። እኛው ራሳችን ነን! በድምራችን። እስቲ ካስቻላችሁ ደግማችሁ ይሄን ቪዲዮ ተመለከቱና፤ ራሳችሁን በዚህ ወጣት ሕይወት ውስጥ ክተቱና፣ ዱላውን ተሸከሙት! ስቃዩን እዘሉት! ኢትዮጵያዊ ነኝ በሉ! እስኪ አስቡ! ምንድን ነው ይህ በተፈጸመበት ቦታ ያሉ የቀበሌው አመራሮች ኃላፊነት? ፓሊሱስ? የከተማው አስተዳደርስ? የክልሉስ? የፌዴራል መንግሥቱስ? ይሄኮ የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥትና አስተዳደር ዋጋ ያሣጣ ተግባር ነው! ሀገር የለም! መንግሥት የለም! ወይንስ ይሄን ትክክለኛ የሕዝብ ግንኙነት ሂደት ብለን እየወሰድነው ነው!!!

ወገን! ያልዘገነነህ ካለህ፤ ይሄን ማንበቡ ዐቅልህን አይስበውም! እናም እዚህ ላይ አቁመህ ሌላ ጉዳይህን ተከታተል! ይሄን እንዲያነቡ የምፈልገው፤ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ! የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል! ሕግ ሲጣስ ያመናል! ወገኔ ሲጠቃ አልወድም! ምን ልርዳ!” የሚሉት ናቸው። እያንዳዳችን በተወሰነ ደረጃና ጥልቀት፤ በሀገራችን የሚካሄደው ያገባናል! ያሳስበናል! ይቆረቁረናል! የነዚህ ወጣቶች ተግባር ግን፤ ከልክ አልፎ “ሰው ነኝ ወይ!” የሚለውን ጥያቄ ነው በልባችን ውስጥ ያስገባው። አውሬ እንኳን ይሄን አይፈጽምም! ታዲያ ካውሬም በታች ሆነናል ማለት ነው! ይገርማል!

ይህ የፖለቲካ ልዩነት መግለጫ አይደለም! ከዚህ ተግባር አንጻር፤ በመንግሥት ደረጃም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ያለን፤ ሁላችንም በአንድነት ቆመን ራሳችንን መመርመር አለብን! ከኢትዮጵያዊነት አልፎ በሰውነት ብቻ እንኳን! ይህ አንድነት ካላስነሳን፤ ሰዎች ሳንሆን አውሬዎችና ከዚያ በታች ሆነናል ማለት ነው! በፖለቲካ ዓለም ወስጥ፤ የተለያየ አቋም መያዝና ወዲያና ወዲህ መሆን ችግር አይደለም። ጦርነት አውጆም ሥልጣን ለመውሰድ ጎራ ለይቶ መፋለም፤ ያለ ነው። መገዳደልም የትግሉ አካል ነው። ነገር ግን፤ አንድን ያልታጠቀ ወጣት፤ እንደመንጋ እየተነዱ ብዙዎቹ በአንዱ ላይ ይሄን የመስለ አረመኔ ተግባር መፈጸም፤ በባርነት ዘመን እንኳን ተመዘግቦ አላነበብኩም! በዚህ እንደማይቆም ማናችንም እንገምታለን። ግን፤ የት ይሆን መዳረሻችን! ሀገራችንስ ወዴት እየሄደች ነው? ማነው ሀገራችንን እያስተዳደረ ያለው? በተያዘው ግስጋሴስ፤ በዚህ ፍጥነትስ፤ መቆሚያ አለ ወይ!!!
አንዱ ዓለም ተፈራ