Saturday, October 14, 2023

ኢትዮጵያ የኤርትራ ፓለስታይን ሆና መቀጠል እስከመቸ? ስለ ቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ አብይ ያንሳው ሰይጣን ያንሳው ጥያቄውና አሳሳቢነቱ ሕጋዊ ነው! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/14/2023

ኢትዮጵያ የኤርትራ ፓለስታይን ሆና መቀጠል እስከመቸ?

ስለ ቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ አብይ ያንሳው ሰይጣን ያንሳው ጥያቄውና አሳሳቢነቱ ሕጋዊ ነው!

ጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay)

10/14/2023

ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር

አዲስ አበበ፤ ኢትዮጵያ፤

<< ዛሬም አሰብን እንላለን!>>

በያዕቆብ ኃይለ ማርያም

የአድህሮትና የክፍፍል በአንድ ጎራ፤ የነጻነትና የአንድነት ኃይሎች በሌላው ጎራ፤ሰቅዞ፤ በያዛቸው ትግል ዉስጥ ሆነው፤በሚፋለሙበት በዚህ ተስፋ ሰጪ ወቅት፤የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዛሬ ማንሳት፤ዋናው የተጀመረዉ በጎ እንቅስቃሴ፤ ማዘናጋት እንዳይሆን የሚሰጉ ሰዎች ይኖራሉ። ሆኖም የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ የአገር ሕልዉናና ልማት ጥያቄ አንዱ አካል እንደመሆኑ መጠን፤ዛሬ በተከሰተዉ ብዙ ተስፋ ከጫረዉ የዲሞክራሲና የአንድነት እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ ገና በጥዋት መነሳት ያለበት ጉዳይ ነዉ። የአሰብን ጥያቄ ግዙፍነት ተረድተዉ አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች በቅድሚያ አጀንዳቸዉ ዉስጥ እንዲያካትቱት በአክብሮት ለማሳሰብ ነዉ። ዛሬ የተነሱት የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያን ጥቅሞችና መብቶች የሚያስከብሩ ናቸዉ የሚል ፍንጭ ስለአየን ግዳዩን እንድናነሳ ቀሰቀሰን።

 

ኤርትራ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተገንጥላ፤ የኢትዮጵያን ሉዐላዊ ግዛት የነበረችዉን አሰብን ስትይዝ፤አሰብ በታሪክ፤በሕግና በስነመንግሥት እሳቤ የኤርትራ አካል እንዳልነበረችለማስረዳት ኢትዮጵያዉያን ምሑራን ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልማሱት ስር አልነበረም። በወቅቱ አሰብ የኢትዮጵያ ግዛት ለመሆኗ ለማስረዳት ያህል ኢትዮጵያዊ ጉዳይ አልነበረም። የአገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የኢሓደግ ባለሥልጣናት አቶ መለስ ዜናዊ፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና አቶ በረከት ስመዖን ከመንገዳቸዉ ወጥተዉ፤ አሰብ የኤርትራ ግዛት ነች፤ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ ምንም መብት የላትም ሲሉ መስክረዋል። ይኸ ስምማጥፋት ሳይሆን በሰነድ ሊረጋገጥ የሚችል ጉዳይ ነዉ።

... 2000 .. በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል በተደረገዉ አላስፈላጊና ትርጉም የለሽ ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት እንደሚደመደም ግምት ተወስዶ ስለነነበረ፤ ጦርነቱ አልቆ ወደ ድርድር በሚኬድበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ግበዐት የሚሆኑ፤

በሕግና በታሪክ የተደገፉ ሃሳቦች፤ ምሁራን በተለያዩ ሚዲያ አቅርበዉ ነበር። ጦርነቱ እንደተጠበቀዉ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ሲደመደም ኢሕአደግ ከመነሻዉ፤ኤርትራን ለማስገንጠል በብዙ የደከሙት የኢትዮጵያ ጠላት የአልጄሪያዉ ፕሬዚደንት ቡተፍሊካን አስታራቂ እንዲሆኑ ጠየቀ። ቡተፍሊካም አቶ ኢሳያስን አቶ መለስን አጨባብጠው ዉዝግቡ ዓለም ሁሉ እምነቱ ወደጣለበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court of Justice) ከመውሰድ ፈንታ በገንዘብ በተገዙ ግለሰቦች እንዲዳኝ የድንበር ኮሚሽኑ ጉዳይ ወደዚያ ተመራ።

 

እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ ምናልባትም በአገር ክሕደት ወንጀል የሚያስጠይቅ በደል መጠቀስ አለበት። የድንበር ኮሚሽኑ ዳኞች የቀረበላቸውን ማስረጃዎች ተንተርሰዉ ጾረና የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗን ዉሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት ተእዛዝ ኢትዮጵያንየወከሉ ጠበቆች፣የለም ተሳስታችኋል፤ ጾረና የኤርትራ ግዛት ነዉብለዉ በመከራከራቸዉ ዳኞቹ ምርጫ በማጣት ጾረናን ወደ ኤርትራ አካለሉት።በታሪክና በሕግ ሥነ መንግሥት የተካኑ ኢትዮጵያዉያን አገልግሎታቸዉን በነጻ እንደሚለግሱ ቢረጋገጥም፤ ኢሕአደግ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊና ወቅታዊ ግንኙነት ምንም ዕዉቀት የሌላቸዉ ዳኞች በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተቀጥረዉ፤ ጉዳዩ ወደነዚህ ዳኞች ችሎት ተመራ።

 በክርክሩ ወቅት ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች በአቶ መለስ ተዕዛዝ መሆን ይኖርበታል፤ አንድም ጊዜ አሰብ በክርክራቸዉ ዉስጥ አላነሱትም።ይልቅስ እጅግ በጣም አስገራሚ የሚሆነዉ ዉሳኔዉ ጣሊያኖች በታላቁ መሪ በእምዬ ምኒልክ ላይ በግድ በተጫኑ ዉሎች ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ጦር በማዝመቷ፤ በተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያም በአዋጁ ባሰረዘቻቸው ዉሎች ላይ በመመርኮዝ ነዉ። እነዚህ ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በዉሳኔ ቁ፤ 289(IV)የኢትዮጵያ ተገቢና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነት መብት ቢረጋገጥም ጠበቆቹ ከቁብ ሳይቆጥሩት ታለፈ። በተጨማሪም ማንኛዉም መንግሥት ወይም አገር፤ ከሻቢያና ከኢሕአደግ በስተቀር፤ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች ያለ የለም።ሻቢያ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝግዛት ነበረችካለ የሚያስከትለዉን ሕጋዊ ዉጤት መቀበል ነበረበት። ዛሬ የልማዳዊ ሕግ

(Customary law) አካል የሆነዉ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በካይሮ ስብሰባዉ በዉሳኔ . AHG/Res 61(1) ያሳለፈዉ የሕግ መርሕ፤አንድ በቅኝ ግዛትነት የተገዛ አገር፤ ነጻበሚወጣበት ጊዜ ቅኝ ግዛት በነበረበት ወቅት የነበረዉ ድንበር ማክበር ይኖርበታል፤ በማለት ደንግጓል።ይህ መርሕበያዝከዉ እርጋ (Uti possedetis) የሚል ድንጋጌ ነዉ። ኤርትራነፃበወጣችበት ጊዜ፤ አሰብ እራስ ገዝ የኢትዮጵያ አካል ስለነበረች፤ኤርትራ ነፃ ስትወጣ፤ አሰብ በኢትዮጵያ እጅ መቅረት ነበረባት። ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች ይህንን መርሕና ሌሎችንም ኢትዮጵያን የሚደግፉ የሕግ መርሆች ሳያነሱ ኮሚሽኑ ዉሳኔዉን ሰጠ። በዚህም ዉሳኔ ባድመን  ጾረናን ሌሎችንም ለኤርትራ ሰጥቶ፤ በእግር መንገድ እርቀት፤ ሁለት ወደቦች የነበሯት ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት፤ ከቀይ ባሕር አካባቢ ተገልላ ቀይ ባሕርም የአረብ ሃይቅ ሆነ።

 

የድንበር ኮሚሽኑ በወረቀት ላይ፤ የማካለል ሥራ ከሠራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፤ በስምምነቱ

መሠረት ኮሚሽኑ መሬት እረግጦ በወሰኖቹ ላይ ችካል መትከል ነበረበት። ሆኖም አቶ ኢሳያስ

በኤርትራ ተሰማርቶ የነበረዉን የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር በማባረራቸዉ፤

የድንበር ኮሚሽኑ፤ ከስምምነቱ ዉጭ፤ ወሰኑን በአየር አካልዬ የማስመሰል ችካል ተክያለሁ፡

(Virtual demarcation ) አድርጌአለሁ።ብሎ አካባቢዉን ጥሎ እብስ አለ። ይህ ማለት እንግዲህ የኢትዮጵያና የኤርትራ የማካለል ዉል የሚጥስ በመሆኑ ተካልሏል ማለት አይቻልም። ኤርትራ ግን መካለሉ ተጠናቋል በሚል፤ኢትዮጵያ የያዘችዉን ግዛቶች፤ በተለይም ባድመን ኢትዮጵያ እንድታስረክባት ለዓለሙ ሕብረተሰብ አቤቱታ ስታሰማ ቆታለች።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

 

በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ያመዘነ አገራዊ ጉዳይ ማሰብ አዳጋች ነዉ። ስለሆነም

አዲሱ ተስፋ እንድንሰንቅ ያደረገን የኢትዮጵያ መንግሥት አመራር ከኤርትራ ጋር ሁሉን አቀፍ

ድርድር ማድረግ ይጠበቅበታል። ድርድሩ ባለፈዉ እንደነበረዉ በብልጠትና በመሸዋወድ

የተጀነጀነ ሳይሆን፤ ጠቃሚነቱን አጉልቶ በማሳየት መከናወን አለበት። ምናልባትም ኤርትራን

ሊያማልሉ የሚትሉ ነገሮችን ማመልከትም ያስፈልጋል። አንድ ነገር ግን ግልጽ መሆን አለበት።

የድርድሩ አልፋና ኦሜጋ፤ አሰብን ወደ ኢትዮጵያ ማጠፍ መሆኑ ዉልፊት የማይባልበት

የመጨረሻ አቋም መሆን አለበት። ግልጽ ለመሆን ያህል፤ የአሰብ ወደብ በነፃ መጠቀም ማለትም

እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። ይህም ሲባል አሁን መገለጽ የማይገባቸዉ የኢትዮጵያን የአሰብ

ባለቤትነት ሊያስረግጡ የሚችሉ እርምጃዎችም ሊኖሩ ይችላሉ።

ክቡርነትዎ፤ለዚህ ጉዳይ ፍጹም የሆነ ትኩረት እንደሚሰጡት ተስፋ እያደረግሁ፤ ጽሑፌን በዚህ እዘጋለሁ።>>

የኔው አስተያየት፡

ያዕቆብ በዚህ ደምድሞታል።ስለ ቀይ ባሕር ወይንም ስለ ወደብ ባለቤትነት ጥያቄ አብይ ስላነሳው ተቃዋሚዎችአብይ አይታመንምና አትቀበሉትእያሉ ድረገፆችን ሲያጣብቡ አይቻለሁ። ኤርትራኖች ደግሞ እንደተረገጠች ዓይጥጺው! ጺውሲሉ አደምጫለሁ (የሚጠበቅ ነው) ተቃዋሚው በጊዜያዊ ሁኔታ ብቻ በማትኮር የመክነፍ ባሕል ስላለው ተቃዋሚውበመቃወም ስለሚተፋው ስለቀይ ባሕር ትችትብዙም ቀልብ አትስጥዋቸው። አብይ እያለ ያለው ወያኔ በደባ (ሴራ) የባሕር ወደቦቻችንን ስላስነጠቀን እዳው ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፤ ስለዚህ ይላል አብይ <<ስለጉዳዩ ዝም አንበል>> ነው። እኔ የምለው << ኢትዮጵያ የኤርትራ ፍለስጢኤም ሆና እስከመቸ እንደትቀጥል እንፈቅዳለን? ጥያቄው በወጣቱ ትውልድ ሕሊና እንዳይረሳ ዛሬም ትናንትም ለወደፊቱም መነሳት አለበት   አብይ አሕመድ ያጠነጠው ተንኮል አለው? <<የራሱ ጉዳይ!>> ጥያቄው ግን ስለ ቀይ ባሕር ወይንም ስለ ወደብ ባለቤትነት ጥያቄ አብይ ያቅርበው ሰይጣን ያቅርበው ጥያቄውና አሳሳቢነቱ ሕጋዊ ነው! በደሉ ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም። ስለዚህም አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀሬ ነው!

 

በክፍል ሁለት ይህንን እንመለከታለን UN-Resolution 390 Paragraph C ምን እንደሚል ተመልከቱ፡ ወያኔ ይህንን እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ሁለቱንም ወደቦች አስረከበ።የወንጀል ወንጀል ፤የክሕደት ክሕደት!

 ሰነዱን ተቀባበሉት

ጌታቸው ረዳ

Haile Selassie Accepts Eritrea (1952)

https://youtu.be/w9LCjfPrDW0?si=eetC5lR8F59o4A7U