Wednesday, January 11, 2012

የወያኔዎች ቀልብ በትግራይ ላይ የመዋለሉ መነሻ




  
 


የሚታየው የወያኔ ገበና ማህደር አዲሱ መጽሐፍ ለመግዛት $30.00 ዶላር ሲሆን ይድረስ ለጎጠኛው መምህር መጽሐፍ ደግሞ $25.00 ሓይካማ የሚለው የትግርኛ መጽሐፌ ደግሞ $15.00 ዶላር ብትልኩ መጽሐፎቹን ማግኘት ትችላላችሁ።Getachew Reda P. O.Box 2219 San Jose, CA 95109 getachre@aol.com Phone (408) 561- 4636


 

የወያኔዎች ቀልብ በትግራይ ላይ የመዋለሉ መነሻ

ጌታቸውረዳ

ኢትዮጵያንሰማይ አዘጋጅ

getachre@aol.com


በቅርቡ ኢትዮ ሚዲያ ፎረም.ካም ላይ ዴይቶን ዩኒቨርሲቲ ኦሀዮ ውስጥ የፍልስፍና አስተማሪ የሆኑት ክቡር ፕሮፌሰር ዶክተር መሳይ ከበደ“Meles’s Shame and the Dead-End of Hatred” በሚል ርዕስ “መለስ ዜናዊና ኢትዮጵያን የመጥላቱ እንቆቅልሽ! በሚል(ወደ አማርኛ የመለሰው ትርጉም ማን እንደሆነ ባላውቅም) የሚከተለው ትንታኔ ተችተው ነበር።

 

መለስዜናዊ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ዓይን-ያወጣ ጥላቻ ከምን እንደመነጨ የኢትዮጵያን ምሁራን ሲፈትን የሰነበተ ጥያቄ ነው, ሲሉ ፕሮፌሰር መሳይ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ለምን እንደሚጠላ መላምታቸውን ሲያስቀምጡ

 

“አንዳንዶቹ የጥላቻው ምንጭ ግማሽ ኤርትራዊ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ስር-ከሰደደ የብሔር ዘረኛነቱ ጋር የተዛመደ ነው በማለት ይደመድማሉ። በዙዎችም ሰውዬው ለሥልጣን ያለውን ከፍተኛ ጥማት ያነሱና የፖለቲካ ሥልጣኑ መሠረት የሆነችውን አገር የመጥላቱ እንቆቅልሽ ግራ ይገባቸዋል። ግን ሁሉም የሚስማማበት ነጥብ አለ። የሚመራባቸው ፖሊሲዎችም ሆኑ ዕለት-ተለት የሚወስዳቸው ርምጃዎች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት አሟጦና አጥፍቶ ትርፍራፊውን በዘረኝነት መርዝ ለተበከሉ ገንጣዮች ጥሎ መፈርጠጥን ያመላክታሉ። መለስ ብለን ብናይ ኢትዮጵያ ጨካኝ ገዥዎች እንዳጋጠሟት እናስታውሳለን። ይሁን እንጅ ሁሉም በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩና ለሀገራቸው ቀናኢ የነበሩ ናቸው። ይኸኛው ግን በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ በሆነ እሴት ላይ ያለው መንገፍገፍ መገለጫ አይገኝለትም።” ካሉ በ

 

 

“አንድ የመለስን የጥላቻ መሠረት የሚገልጽና ሁላችንም የምናውቀውን ነገር ማንሳት የቻላል። ይኸውም ከቤተሰቡ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። የቤተሰቡ ታሪክ ከወራሪው የኢጣለያ መንግሥት አሳፋሪ ታሪክ ጋር ቁርኝነት አለው። አያቱ ለኢጣሊያ መንግሥት ማገልገል ብቻ ሳያሆን ሹምና ተባባሪ ነበሩ። ታዲያ መለስ ከቤተሰቡ የወረሰውን ነውር በትከሻው እንዳንጠለጠለ ይገኛል። ቤተሰቡ በዚህ አሳፋሪ ተግባር መናቁና በሕብረተሰቡ መገለሉ በመለስ ጨቅላ አዕምሮ ውስጥ የበቀልና የጥላቻ ስሜት እንዳሳደረ ሥራው ይመሰክራል።”

በማለት መለስ ዜናዊ ጥላቻን እንደፖሊሲው የማራመዱ ምክንያት መላምታቸውን አስቀምጠዋል።

 

 

የፕሮፌሰሩ መላምት ሙሉ በሙሉ እንኳ ባልቀበለውም፤ እንደ ገፊ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆናል። ለጥላቻው መነሾ መሰረታዊ ምክንያቶች የፕሮፌሰሩ መላምቶቹ አነስተኛው የመነሾው ገመድ ቢሆንም ፤ የተበጣጠሱ የመነሾ መላምቶቹ ለማገናኘት የረዘሙ ምክንያቶችን አገናኝቶ ገመዶቹ ሲያያዙ የገመዱ መነሾቹ እና መድረሻ ጫፎች እሳቸው ያልዳሰስዋቸው ሁለት ምክንያቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።

 

በሁለተኛው ልጀምር። አንደኛው መነሾ ሰፋ ያለ ስለሚሆን ወደ ላ እተነትነዋለሁ። በሁለተኛው ልንጀምር።

 

 

የመለስ ዜናዊም ሆነ የተቀሩት ተከታዮቹ ኢትዮጵያን ለመጥላት እንደመነሻ የሆነው “አማራን” የመጥላት ምክንያት ነው። እንዲህ ስል መረጃህ ምንድር ነው? ብለው ለሚጠይቁ አንባቢዎች መረጃ ማሳየት የግድ ነው። ሁላችሁም እንደምታውቁት ወያኔ ሲመሰረት መነሻ ያደረገው ዋናው ምክንያቱ የሚከተለው እንደነበር ይታወቃል።

 

“የትግራይ ህዝብ ለረዢም ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጐ ሲጠላ እና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲደረግበት ቆይቷል። ይህ በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ የመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ ስትሰራበት የቆየች ሲሆን… የ ፫ሺ ዓመታት የሚያኮራ ታሪክና ባህላችን መመኪያቸውና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል። ይህ የታሪክ ስርቆት በአንድ በኩል የአማራው ብሔር መፎከሪያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይ ህዝብ ታሪክ እንደሌለው ህዝብ እንዲያስቆጥረው የተደረገ የመንግሥት መመሪያ ነው። የትግራይ ሕዝብ ክብሩና መብቱ እስኪመለስለት ድረስ ትግሉ አያቋርጥም። ጨቋኝዋ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋ እስካላቆመች ድረስ ሕብረተሰብዓዊ ዕረፍት አታገኝም”

 

 

(የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ ገጽ የካቲት ወር 1968 ዓ.ም.ገጽ 15-16} (ምንጭ የወያኔ ገበና ማህደር ገጽ 21 ደራሲ ጌታቸው ረዳ)።

 

 

ከላይ እንደተመለከታችሁት ለትግራይ ሕዝብ በባሕል፤በታሪክ ባለቤትነት፤ በምጣኔ ሃብት እና ስነ መንግሥታዊ አስተዳደር እየተዳከመ መምጣት ወይንም የተጠቀሱ እሴቶች “ባለቤትነት መነጠቅ” ምክንያት “ጨቋኝዋ የአማራ-ብሔር” እንደሆነች በማያሻማ አገላለጽ አስቀምጦታል።ለዚህም ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ዋነኛ ጠላት አድርጎ መመለክት ያለበት “አማራ” እንደሆነ ካስቀመጠ ላይቀር የአማራው ህልውና ክር እና ድሩ ከኢትዮጵያ ጋር ስለሆነ እሱን መበጣጠስ አስፈላጊ ሆኖ ኢላማ ውስጥ በማስገባቱ “ኢትዮጵያን” በጠላቻ እይታ መነፅሩ ክብ ወግቷታል።

 

 

ምን ማለት ነው ‘የአማራ ጥላቻው ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞታል” ስል? ወደ ዋናው ማኒፌስታቸው ስንመለከት አሁንም የሚጦቁመው ‘ጨቋኝዋ ብሔር” (አማራ) ኢትዮጵያ የምትባል አገር የተፈጠረቺው “በጨቋኝዋ ብሔር በአማራው ፤በተለይም በሸዋው አማራ በምኒልክ” እንደሆነ አስቀምጦታል። ሰለዚህ ኢትዮጵያን የፈጠረ “አማራው” የትግራይ ጠላት ስለሆነ የፈጠራት ኢትዮጵያም ከአማራው ባሕል፤ታሪክ (ምንም እንኳ አማራው የራሱ ታሪክም ባሕልም ስለሌለው ከትግራይ “የተሰረቀ” ባሕልና ታሪክ እያራመደ ነው ብሎ ቢወነጅለውም) ጋር በመያያዙ “ኢትዮጵያ” የምትባል “የጨቋኝዋ ብሔር” (የአማራው) አገር የትግራይ ሕዝብ ከጠላቱ እና ከጨቋኝዋ ብሔር/አገር ለመነጠል “አብዮታዊ ትግል” (ወያኔያዊ ትግል) በማካሄድ “…ከባላባታዊ ስርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ነፃ የሆነ” “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም” እንደሆነ በ1968 ያሰራጨው ጽሑፍ አረጋግጦልናል።

 

 

ስለዚህም ይህ ማኒፌስቶ ያወጣ ድርጅት የሚመራው መለስ ዜናው ጥላቸው እንደ ሁለተኛው ምክንያት መነሾው ከዚህ ይመነጫል። የታሪክ ስርቆት ፈጽሞብናል በማለት የከሰሰው የአማራውን ብሔር ወይንም “በአማራው ምኒልክ የተፈጠረቺው ኢትዮጵያ” ትግሬዎችን በደላለች በማለት ይህ መጠን ያለፈ የአማራ ሕብረተሰብ ከኢትዮጵያዊነት የስልጣን መንበር እና ከኢትዮጵያ ባለቤትነትነት እና ገምቢነት በማያያዝ ብቸኛ ጥላቻ መነሻቸው ብቻ ሳይሆን ስልጣን ከተቆጣጠረ ወዲያም በሽግግሩ መንግሥት አብረውት ሥልጣኑን ከተቀራመቱት የጐሳ ቡድኖች እና ተ.ሓ.ህ.ት. በመንግሥት መሪነት ከገባ ወዲህ ተረባርበው “የምኒልክ ኢትዮጵያ” በሚሏት ኢትዮጵያ ላይ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያቆራኙት የአማራው ሕብረተሰብ ላደረሱበት ጥቃት ስናጤን “ጨቋኙ የአማራው ሕብረተሰብ (በወያኔዎች ቋንቋ “ብሔር”) ሕብረተሰባዊ ሰላም አያገኝም” በማለት ከውስጡ ቋጥሮ ይዞት የቆየው እጅግ ሥር የሰደደ ቂም ከመነሻዉ አንዱ እንደነበር ባለፈው መጽሐፌም (ይድረስ ለጎጠኛው መምህርም) ሆነ (የወያኔ ገበና ማህደር) መጽሐፌ በዝርዝር ስለተብራራ መጽሐፉን ማንበብ ነው።

 

 

2ኛ- ሌላው ሁለተኛው እና ዓይነተኛ ኢትዮጵያን የመጥላት የመነሻቸው ምክንያት አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በላ አጼ ምኒልክ ራስ መንገሻንና የመሳሰሉት የትግራይ ገዢዎችን በስርዓታቸው ለማስገባት ባካሄዱት ውግያ የተሳተፉ “ይሓ” (ዓድዋ) ውስጥ የተወለዱ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት“ታሪኽ ኢትዮጵያ” የሚል በእጅ ጽሑፍ በ1891(ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) በ1899 (በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር) ናፖሊ/ ጣሊያን አገር የተጻፈ ባለ 169 ገፅ የያዘ ብደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ዓቢየዝጊ የጻፉት ላነበበ ሰው አንደኛው መነሻ ነው።

 

 

ደራሲ በዓይናቸው የተመለከቱት እና በሁለተኛ ደራጃ በወሬ የሰሙትን ታሪክ ያሰፈሩት የትግራይ ሕብረተሰብ አኩሪ “የመንግሥት አስተዳደር፤ ሥልጣኔ፤ ዕድገት፤ጥንካሬ፤ ጦርነት፤ ቅሬታ፤ሐዘን፤ድህነትና ውርደት” ያሰፈሩት የታሪክ ዘገባ በሰፊው ለመመለክት ታሪኩ ምናልባትም በሚቀጥለው አዲስ መጽሐፌ በሰፊው ስለሚተነተን አሁን አሳጥሬ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 

 

ደራሲው ሲገልጹ ደጃች ውቤ እና በጣም አድርገው የሚኮኑኗቸው አጎቦች (አገው) እንዲሁም አማራዎች ትግራይን በጦርነት ከመያዛቸው/ከመውረራቸው በፊት “ትግራይ ውስጥ የነበረ ሃብት/የአዝርእት ምርት ታፍሶ አያልቅም ነበር” ካሉ በላ በተለያዩ ወቅቶች በሦስቱም ወራሪ ጦረኞች የተጠቃቺው ትግራይ “አመዷን ካወጧት በላ” እያደረ ወደ ድህነት አዘገመች። በመጨረሻ ዮሐንስ ከሞቱ በላ ምኒልክ በመተካታቸው የትግራይ ሕዝብ ገጽታ የሌሊት ጨለማ እና የቀን ብርሃን ያህል ገጽታ በሸዋ እና በትግሬዎች መሃል ልዩነት ተከሰተ ይላሉ።

 

 

ቃል በቃሉ በትግርኛው እንዴት እንደገለጹት ልጥቀስ እና ትርጉም ይከተላል።በመጽሐፉ ላይ የቀረበው የትግርኛው ጽሑፍ ባንዳንድ አገላለጾች ላይ ከሞላ ጐደል አሁን ከሚነገረው ትግርኛ የተለየ ነው። ቃል በቃሉ ይኼው፦

 

“….ሽዕቱ ገጽ ሸወታይ ጥምት አቢልካ ናብ ገጽ ትግራዋይ ቁልሕ እንተበልካ ዳርጋ ክንዲ ናይ ለይትን ናይ ቀትርን ዚአክል ምፍልላይ ይርኤ ነበረ” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ (134) ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ-1891/ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 1899/ፈረንጅ ዘመን) ትርጉም (ጌታቸው ረዳ) ለወደፊቱ ከሚታተመው አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)።

 

 

“ያኔ የሸዌዎቹ ገጽታ ተመልክተህ ወደ የትግሬው ሰው ገጽታ ፊትህን ዞር ብለህ ስትመለከት የምትታዘበው የሁለቱ ሰዎች ገጽታ ልዩነት ልክ የቀን ብርሃን እና የሌሊት ጨለማ የገጽታ ልዩነት ይታይ ነበር።” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ 134)1891/ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 1899/ፈረንጅ ዘመን ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) ትርጉም (ጌታቸው ረዳ) ለወደፊቱ ከሚታተመው አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)።

 

ከላይ የጠቀስኩት ግልጽ ስዕል ምን ማለት እንደሆነ እና በወቅቱ የታየው የወደፊት መጻኢ ባሕሪው ወዴት እንደሚወስድ እና አሁን ካለው ነባራዊ ክስተት ስታገናዝቡት የወያኔዎች የገጽታ ተማሳሳይ ቅጅ ምንጩ “ያቺኛዋ ወቅት” እነደሆነች መገንዘብ ትችላላችሁ። ከላይ የተመለከተው የታሪኩ አጭር ዝርዝሩ በአማርኛ የተረጎምኩትን እነሆ ፡-

 

 

ደራሲው ራስ መኮንን ለዲፕሎማሲያዊ ስራ በአፄ ምኒልክ ናፖሊ/ከጣሊያን አገር ደርሰው በምፅዋ አድርገው ወደ መቀሌ ከተማ ሲገቡ አጼ ሚኒልክም መቀሌ ከተማ ውስጥ ስለነበሩ ራስ መኮንን ለመቀበል ደራሲው ደብተራ ፍስሃም በግራዝማች ዮሴፍ ስር ስለነበሩ ከሳቸው እና ከነደጃች ስብሐት እና ከመሳሰሉት ከትግራይ መኳንንት ጋር ሆነው ራስ መኮንን ወደ መቀሌ ለማጀብ ወደ ከተማዋ የሚወስደው ቁልቁል መንገድ ሲደርሱ (የመሶቦ ዳገት/ቁልቁለት ማለት ነው) እንዲህ ይላሉ።

 

 

<<ለደጃች ሥዩም ገብተው የነበሩ የተምቤኑ ደጃዝማች ሐጎስ ከሳቸው ጋራ የነበረው ተፈሪ የተባለ ዘመዳቸው አብሯቸው በነበረበት ወቅት ‘ሁለት ሰናድር’ ይዞ ወደ ግራዝማች ዮሴፍ በመግባቱ ‘አጠፋህልኝ’ ብለው ተማጸኑት። ዳኛውም ራስ መኮንን ሆኑ። ያኔ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አፄ ምኒሊክ ናቸው። ተማጓቾች ሁሉ በሙግታቸው ጣልቃ የተሟጋቻቸውን አንደበት ስርዓት ለማስያዝ ሲፈልጉ “ዝባን ዮሐንስ ” (በዮሐንስ አምላክ)እያሉ ተቸገሩ። ሆኖም “በዮሐንስ አምላክ” እንዳይሉ ዳኛው ራስ መኮንን ሆኑባቸው። በሚኒልክ አምላክ እንዳይሉ ደግሞ አዲስ ነገር ሆኖባቸው ከእጅህ ለማማልጥ ሙሉጭልጭ እያለ እንደሚያስቸግርህ ዓሳ “በዮሐንስ አምላክ” እያሉ እያዳለጠ ያመልጣቸው ነበር። ካፋቸው ሲያመልጣቸው ግን፤ ልክ አንድ ጎረምሳ ጎበዝ ጭቃ አዳልጦት ወድቆ ሲነሳ ሰው አይቶት እንደሆን አካባቢው ግራ እና ቀኝ በሐፍረት እንደሚቃኝ ሁሉ ተሟጋቾቹም ወደ አድማጩ ዞር ዞር እያሉ የሰውን ስሜት በሰቀቀን ሲለኩ ነበር።

 

ፍርዱ ላይ በችሎቱ አካባቢ የነበረው ተሰብሳቢ ሕዝብም እርስ በርሱ ራሳቸውን እየተጠቃቀሱ ይተያዩ ነበር። ሁኔታው ሰውን ሁሉ በጣም አቅል የሚያሳጣ ሆነበት። ያችን ችሎት ተሎ ባለቀች እያለ ያልተመኘ አንድም ሰው አልነበረም።በውስጡ በብዙ ሃሳቦች ተውጦ ይታይ ነበር።” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፪-፻፴፫/132-133 ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ-አቆጣጠር 1899/ፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር (ትርጉም ጌታቸው ረዳ ለወደፊቱ ከሚታተመው መጽሐፍ የተቀነጨበ)።”

 

 

ደራሲው ይቀጥሉ እና አጼ ሚኒልክ ራስ መኮነንን ሲቀበሉ በሚል ርዕስ ሲተነትኑ (ራስ መኮንን ከናፖሊ ጣሊያን አገር ዲፕሎማሲ ስራ ሰርተው በምፅዋ በኩል ወደ መቀሌ ሲመለሱ የተደረገላቸው አቀባበል ማለታቸው ነው)

 

“አጉላዕ በተባለች ትንሽ መንደር ለአዳር ሰፈራ አድርገን ትንሽ ቆይታ ካደረግን በላ በወቅቱ መቀሌ ከተማ ይገኙ ከነበሩት ከአፄ ጋር ለመገናኘት ጫን ተባልን።በወቅቱ ራስ መኮንን ከሐረርጌ ወደ ዜላ ከዚያ ወደ ናፖሊ ከዚያ ወደ ምፅዋ፤ ያ ሁሉ መንገላታትና አስቸጋሪ ጉዞ እና ባሕር አቋርጦ በሰላም መመለስ የሸዋ መኳንንትም ሆኑ በእነ ራስ ሐጎስ በኩል ከፍተኛ ደስታ ነበር። ይኼ ደግሞ ግልጽ ነው። …

 

 

…ወደ መቀሌ የሚያስገባው ቁልቁሉን መንገድ እንደ ጨረስን የአፄው ብዙ ጭፍራ ቆዩን። ደጃዝማች ስብሐት ግን ለራስ መኮንን የሚከተለው ቃል ተናገሯቸው “እኔ ቆየት ብየ እደርሳለሁ፤እርስዎ ግን ቅድሚያ ይሂዱ”አሏቸው። ራስ መኮንንም “እሺ ደግ ይኹን” ብለው በሃሰባቸው ተስማሙ።

ሰው ግን “አይ ተደርበው እንዳይገቡ” ብለው ነው። በማለት ተረጎመው። ወዲያውኑ ቁልቁለቱን ጨርሰን ታች እንደወረድን ወዲያውኑ ከሸዋ ሰራዊት ጋር ዓይን ለዓይን ተያየን። ጸንዓ ደግሊ እያለሁ ድሮ የማውቀው የአጋሜ የአጉዕዳይ ተወላጅ የሆነው ፊታውራሪ ተስፋይ የተባለ ጎን ለጎን እንጓዝ ነበር እና “ወይኔ! ይበለን! ራሳችን ያመጣነው ጣጣ ነው፤ አስታጣቂዎች የነበርነው አሁን ታጣቂዎችን ሆን!” አለ።

 

ከዚያ በላ ይህ ያዳመጡ ራስ መኮንን ለመሸኘት የተከተሉ እነ ‘ኮንቲ አንቶኖሊ’ እና ራስን አጅበው እየተጓዙ የነበሩት ትግሬዎች በሞላ ማለትም ዓጋሜውም፤አከለ-ጉዛዩም፤ሐማሴኑ፤የአሕሳአቴውም፤ ተምቤንቴውም ሁሉ ከየሸዋዎቹ ጭፍራዎች ጋር ዓይን ላይን ተገጣጥሞ ሲተያይ ‘ኪፍ’ አለው። (ደራሲው የተጠቀሙበት ቃል “ኪፍ” የሚል ነው። “ኪፍ” ማለት ድመት/ነብር ሌላ ጠላት/ ድምት ሲያይ/ስታይ ካንገቷ በላይ ያለው ጸጉር በማቆም በጉብታ ስሜት የጥላቻ እና የመከላከል ገጽታዋ እንደሚለዋወጥ የሚታይ ስሜት ማለት ነው) ስሜቱ ሁሉ ተለዋወጠ። ያኔ የሸዌዎቹ ገጽታ ተመልክተህ ወደ የትግሬው ሰው ገጽታ ፊትህን ዞር ብለህ ስትመለከት የምትታዘበው የሁለቱ ሰዎች ገጽታ ልዩነት ልክ የቀን ብርሃን እና የሌሊት ጨለማ የገጽታ ልዩነት ይታይ ነበር።

የደጃች ሐጎስ አሽከር የነበረ አንድ የተምቤን ሰው ይህ ትርኢት ሲመለከት የአፄ ዮሐንስ ሕልፈት ትዝ ብሎት “እንባው” ዘረፍ አደረገ። እውነት ለመናገር እንኳን የትግራይ የወንዝ ልጅ የሆነ የአከለ ጉዛይ እና የሐማሴን ሰው ሁሉ እንባ ተናነቀው። … (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ 134) 1891/ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 1899/ፈረንጅ ዘመን ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) (ትርጉም ጌታቸው ረዳ ለወደፊቱ ከሚታተመው አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)።

 

 

“…የትግራይ ሕዝብ ወቅቱ ንፍሮ ቆሎ የሚመገብበት እና በተቅማጥ ወረርሺን በሽታ ሲሰቃይ የነበረበት አስከፊ ወቅት ነበር። በወረራው ወቅትም ብዙ ሰው አልቋል። ወደ ትግራይ መሻገራቸውም ከሸዋ ሰራዊቶች መሃል ያልተደሰቱ ነበሩ።….ትግራይ ለምና እንዳመጣቻቸው ትግራይን መርገም ተያያዙ። የአማራ ወታደር ወደ አጋሜ ከዚያም ወደ አክሱም ሕዝብ እያጠፉ ለመሸጋገር አልመው ነበርና ፤ የአማራ ወታደር ወደ አጋሜ መሻገር አቀበት ሆነበት። ትግራይን መራገም ጀመሩ። ቋንቋውን ሁሉ መስማት አስጠላቸው።

 

ይህ እንደዚህ እያለ የራስ መንገሻ በሰላም እጃቸው መስጠት ደስታ ሆነ። በወቅቱ ራስ መንገሻ ዮሐንስ እጃቸው ለአፄ ሚኒልክ ሲሰጡ ራስ አሉላ እጄን ለሸዋ አልሰጥም ሲሏቸው ራስ መንገሻ ዮሐንስ ግን “ሰውና አገር ጠፍቶ እኔ ብቻየን ብቀር ምን ይረባኛል፡ እናንተ ግን የመሰላችሁን ቀጥሉበት፤እኔ ግን ገቢ ነኝ ብለው እጃቸውን ሰጡ።>>

 

ካሉ በላ ደራሲው በ፰መጋቢት፲፰፹፪ (መጋቢት 8/1882) ራስ መንገሻ ወደ ሚኒልክ ሲገቡ መቀሌ ከተማ የተደረገው ስነ ስርዓት በስፋት ከዘረዘሩ በላ (ያ አስገራሚ ትርኢት በሚታተመው መጽሐፌ ለማንበብ ዕድል ሲገጥማችሁ በዘርዝር ታነቡታላችሁ) ባጭሩ እንዲህ ሲሉ ያሰቀምጡታል፦

 

 

በ፰መጋቢት፲፰፹፪ (መጋቢት 8/1882) ራስ መንገሻ ወደ ምኒልክ ሊገቡ በመዘጋጀት እንዳሉ ከተነገረ በላ አጼው ወዲያ ወዲህ ሳትል በጥዋቱ ነገ በየአለቃህ ተሰልፈህ እንድትገኝ ብለው አዋጅ አስነገሩ። መቀሌ የሚገኙት አጼ ምኒልክ ይህን ካዘዙ በላ ጠዋት ጸሐይ ሰትወጣ ሰልፈኛው ከአፄው ደንኳን ጀምሮ በሁለት ረድፍ እንደ ግድግዳ ግራ እና ቀኝ ረዢም ረድፍ በመስራት ይጀምር እና ወደ ታች ራስ ስዩም ይመጡበታል ወደ ተባለው የተምቤን አቅጣጫ ሲደርስ ወደ አራት እና አምስት ረድፍ ሰልፈኛ ግራ እና ቀኝ በረዢሙ በመሰለፍ ረድፍ ያዘ። በዛው ላይ የራስ መንገሻን መልክ ለማየት እየተጋፋ በብዙ የሚቆጠር ሕዝብ እርስ በርሱ እየተጋፋፋ ነበር።

 

 

ቀጥሎም ትልልቆቹ ደጃዝማቾች እና ሹሟሙንቶች ወደ ንጉሱ ጃንጥላ ተሰበሰቡ። የንጉሡ ጃንጥላም ተዘረጋ። ከንጉሡ ዱንኳን ጀምሮ በሁለት ረድፍ ግራ እና ቀኝ እንደ ገመድ የተወጠረው የሰልፈኛው ጫፍ የት እንደ ሆነ ለዓይን እስኪያዳግት ድረስ ቀጥ ብሎ በረዢሙ እና በተንጣለለው ሰፈው ሜዳ ወደ ታች የዘለቀው ሰልፈኛ ስትመለከት በግራ እና በቀኝ በተሰለፈው እመሃል ላይ ለራስ መንገሻ ዮሐንስ መምጪያ ክፍት ቦታ ሰርቶ የተንጣለለ የማሳለፊያ ክፍት ቦታ ሰርቷል።

 

የአማራዎቹ ሠራዊት ብዛት ያኔ ነው ለማየት የተቻለው። ብዛታቸው የመሬት አፈር ያህል ነበር። ከዚያ በላ ረፋዱ ላይ ራስ መጡ። ቢያንስ ፼ (10,000) የሚሆን ሠራዊት አስከትለው መጡ።

 

እሳቸውን ለመቀበል ግራ እና ቀኝ በተሰለፈው ሰራዊት መሃል ለማሃል ሰንጥቀው በመጓዝ ወደ ንጉሡ ድንኳን ደረሱ። አፄ ምኒልክ ድንቅ ሰው ናቸው እና በብዙ አክብሮት ተቀበሏቸው፡መድፍ ተተኰሰ፡ ወዲያውኑ እያንዳንዱ እሳቸውን ለመቀበል የተሰለፈው ሠራዊት በነፍስ ወከፍ የደስታ መግለጫው ጥይት ወደ ሰማይ ተኰሰ።ሰማይ እና ምድር ድብልቅልቁ የወጣ መሰለ። እንዳይጠፉ ታስረው ከነበሩበት በረት ፈረሶች እና በቅሎዎች ማሰሪያቸውን እየነቀሉ እየበረገጉ እንጣጥ እያሉ ሸሹ።

 

በወቅቱ ራስ መንገሻ በአባታቸው (አፄ ዮሐንስ) ሞት ምክንያት ሐዘንተኛ ስለነበሩ በሰልፈኛው መሃል ሰንጥቀው ሲያልፉ የሐዘን ልብስ ለብሰው ነበር የመጡት። ይህንን ሲመለከት ሰው እንዳለ በሙሉ ምርር ብሎ ሐዘን በሐዘን ሆነ።……”

 

 

“… በወቅቱ ራስ መንገሻ እጃቸው ባይሰጡ ኖሮ ካሁን በፊት ከታየው ውጊያ በከፋ መልኩ ትግራይን ያጠፏት ነበር። ራስ መንገሻ ከመግበታቸው በፊት አፄ ምኒልክ አጋሜ አውራጃን ለማጥፋት ዝግጅት አድርገው ነበር። የአጋሜ አውራጃም ከአማራ ጋር ተናንቀን አብረን እንሞታለን እንጂ አይገዛንም ብለው ዝግጅት አድርገው በየምሽጉ እና ጉራንጉሩ መዋጊያ ቦታ ይዘው ተዘጋጅተው ነበር።

 

 

ከደጃች ሥዩም በቀር ከሸዋ ጋር የወገኑት እና ያልወገኑት መኳንንት መሃል መጠኑ ያለፈ ጥላቻ በትግሬዎች መሃል ይንጸባረቅ ነበር። ይህ ጥላቻ የርስ በርስ ጥፋት ማስከተሉን አይቀሬ እና ትርፍ እንደሌለው ከተገነዘቡ በላ ሕዝቡ ካለቀ በላ ብቻየን ብቀር ምን ትርጉም አለው በማለት እነ ራስ አሉላን የፈለጋችሁ አድርጉ ብለው እነሱን ትተው ራስ መንገሻ ዮሐንስ እጃቸውን ለመስጠት ነበር የተገደዱት። (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፵፪-/፻፵፬ 142-144) 1899/ፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) (ትርጉም ጌታቸው ረዳ ለወደፊቱ ከሚታተመው መጽሐፍ የተቀነጨበ)።

 

 

መደምደሚያ

በዚህ ላሳርግላችሁ፡-ሸዋ እና ትግሬ የሚለው የጥላቻ መነሻ ወያኔዎች ከየት እንደለቀሙት ታሪኩን እንደሚከተለው ባጭሩ ተመልክቱ።

 

 

“……ዓይባ የተባለ ቦታ ከመስፈራቸው በፊት እዚያው ዙርያዋ ሜዳ በከበባት አንድ እምባ በውስጧ የተጠናከሩ ምሽጎች ላይ 7 ትግሬዎች ሆነው የሸዋዎቹን ጦር እና መደፈኛ ገትረው አቆሟቸው። መድፍ ሁሉ ተተኩሶ ፍንክች ማለት አቃታቸው። የአፄው ጋላዎች ሱሰኞች ነበሩ እና ሰውን እየሰለቡ መፈከር ጀመሩ። ንጉሡም መሳሪያ ሳይማርክ “ገዳይ“ ብሎ የፈከረ ሰው ወዮለት! በማለት አዋጅ አወጁ። ቢሆንም ስለ ሕልፈተ ትግራይ ልብ ላለው ብዙ አሳዝኗል። እነኚያ የቤገምድር አማራዎች ግን በጣም ይቆጩ እና ያዝኑ ነበር።

 

 

…በዛች አምባ መሽገው ብዙ የሸዋ ሰራዊት የገደሉት 7 የትግራይ ተዋጊዎች መከላከላቸውን ቀጠሉ። ምሽጉ በድንጋይ በደምብ የተገነባ ሆኖ ከአፋፉ ምሽግ ደጃፍ ላይ ወራሪዎቹን ለመሳብ ሆን ብለው ሰዎቹ አስቀድመው እህል እና ጓዝ እቃ ከምረውበታል። ሲተኮስባቸው ዝም ብለው አድፍጠው ይቆዩ እና አማራዎቹ እየተጠጉ እህሉን እና እቃውን ዓይተው ለመጎተት ወደ ዳገቱ ጫፍ ሲጠጉ የጥይት ዶፍ በማውረድ ከገደሉ ወደ ተች እየወደቁ ብዙ ሰው ጎዱባቸው።

 

 

ይህ እንደሰሙ ንጉሡ ወደ ስፍራው በመሄድ ሲመለከቱት አብሯቸው የነበረ ‘ኢልግ’ የተባለ የኢስፏፀራ መድፈኛ መድፉን አነጣጥሮ ዳገቱ ላይ የተገነባው ምሽግ ላይ በመተኮስ አፈራረሰው። ከዚያ በላ ነፍጠኞቹ ነፍጣቸውን ወደ ታች ጣሉት።

 

ንጉሡም ደግ ሰው ነበሩ እና “ተው አትቶኩስባቸው” በማለት እንዳይተኩስ አገዱት። ከዚያ በላ ንጉሡ 7ቱ ታጣቂዎች በራሳቸው መታጠቃቸው ብዙ አዘኑ። ወዲያውኑ ከአካባቢው ዙርያ ከመሸጉ ባንደኛው አምባ ላይ አስተማማኝ ቦታ ላይ ሆኖ ወደ ታች ሜዳ ደምፁን ከፍ አድርጎ አንድ የትግሬ ሰው ንጉሡን እንዲህ አላቸው፦

 

 

“አንተ ሸዌ እንተዋወቃለን እኮ! የማንተዋወቅ እንዳይመስልህ። አሁንም አንላቀቅም። ዮሐንስ ቢሞት እኛ ወጣት ልጆች የሞትን እንዳይመስልህ! አላቸው።” ፻፴፱-፻፵-(139-140) ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊ - ታሪኽ ኢትዮጵያ 1899/ፈረንጅ ዘመን የእጅ ፅሑፍ ናፖሊ/ኢታሊያ)ትርጉም ጌታቸው ረዳ ለወደፊቱ ከሚታተመው አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)::

 

ከዚህ ፓተርን/አነጋገር/ቅሬታ/ቁጭት ለእነ መለስ ዜናዊ እና መሰሎቹ ምን የባሕሪ ለውጥ እና ግንዛቤ እንዳስተላለፈባቸው ግንዛቤ መውሰድ የናንተ ይሆናል። በእኔ በኩል የምንጩ መነሻ መጋረጃው ገልጬ እንድታዩት አድርጌአለሁ። በተረፈ ይህንን ሐተታ በሚመለከት እየሰራሁ ያለው መጽሐፍ ሲታተም ኢትዮጵያውያን (ምሁራን ጨምሮ) ማየንበብ ፍላጎታቸው ደካማ ቢሆንም በሕትምት ላይ ያሉ አድካሚ እልክ እና ጊዜ የሚያስጨርሱ ለመጪው ትውልድ የሚያስተምሩ የምናበረክታቸው መጽሐፍቶቻችንን በማግኘት ከምትጠጡት ቢራ እና ከምትጎርሱት የሬስቶራንት ክትፎ ቀንሳችሁ ለትውልድ ማስተላለፍ የናንተ ፈንታ ይሆናል።በመጽሐፍ መልክ ካልሰፈሩ የኢንተርኔት ጸሁፎች እና ጫጫታዎች ጊዜያዊ እንጂ ብዙም ስራ አይሰሩም።

 

 

ወያኔዎች ጥይት መተኮስ አቁመው የተያየዘዙት እሽቀድድም እና ጦርነት ለመጪው ትውልድ የራሳቸው እይታ ለማስተላለፍ እና በሄዱበት መንገድ መጪውን ትውልድ ለመበረዝ በገፍ መጽሐፍቶችን እያሳተሙ ነው። አባሎቻቸውም በገፍ ይገዟቸዋል። ለትውልድም ይተላለፋሉ። እናንተ ግን ከጥይቱም ከመጽሐፉም ትግል ስትታገሉ ብዙም አትታዩም። ሌላ ቀርቶ ረዢም ጽሑፍ ነው በሚል ደካማ ምክንያት ምን እንደሚጻፍም ሳታነቡ ፊታችሁ ወደ ፓል ቶክ ጭቅጭቅ ለማዳመጥ ይዞራል።

 

 

የጻፍናቸው መጽሐፍቶች እንኳ ካነበባችሁ በላ መገምገሙን አና ህዝብ እንዲማርበት ማድረጉን ተውት  አና ዝብ እንዲማርበት ማድረጉን ተውት እና መጽሐፍቶች እንዳይሰራጩ በድርጅት ፓርቲ ፍቅር ተተብትባችሁ እንዳታነቡ የተወገዛችሁ ሰዎች እንዳለችሁ እንድትገዙ ሲጠይቋችሁ የጀሮ ምስክሮች በስልክ ሲነግሩኝ ለወደፊት ትውልድ እና ያገሪቱ ዕጣ ፈንታ በጣም አዘንኩላት። በዚህ ከቀጠላችሁ፤ ወያኔዎች በውግያው መስከ የተቀዳጁትን ድል በመጽሐፍ ዓለምም የልባቸው እንደምያደርሱ አትጠራጠሩ። ያለኝን ወርውርያለሁ፤ ምክሩን የመቀበል የናንተ ፈንታ ይሆናል። አመሰግናለሁ። ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያ ሰማይ ድረ ገጽ አዘጋጅ) www.ethiopiansemay.blogspot.comgetachre@aol.com