የትግራይ ምሁራን እና የወያነ ትግራይ ሰመመን ፍቅራቸዉ ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com ዛሬም ይህ ዓምድ ይዞላችሁ የቀረበዉ ካለፈዉ የቀጠለ ተከታታይ ዓምድ ሆኖ፣ በየጎሳ ፖሊሲ እየታመሰች ያለችዉን አገር ምን ብናደርግ መከራዉ ባጭሩ ሊቀጭ ይችላል? ከሚለዉ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ እና አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ በነጻነት ራዲዮ አንስተዉት የነበረዉን ዉይይት የሚመለከት ነዉ፣፣ እንደምታስታዉሱት በዉይይታቸዉ ላይ ብዙ ቁም ነገሮችን ተወስተዋል፣፣ አካባቢን ቋንቋን ባማከለ የተዋቀረዉ የወያነ ትግራይ መንግሥታዊ አስተዳዳር ሃገሪቱ ወደ ከፋ ትርምስ እና ቀዉስ ይዟት ከመሄዷ በፊት የትግራይ ምሁራን/ኢሊቶቹ ስርዓቱን የመቃወም ሓላፊነት ቸል ብለዉታል ብቻ ሳይሆን ሆን ብለዉ የሥርዓቱ ጠበቆች እና ገምቢዎች እንደመሆናቸዉ መጠን ለብዙ ዓመታት የዘለቀዉ የወያነ ትግራይ ደጋፊነታቸዉም ሰብረዉ የመዉጣት አቅማቸዉ አሁኑኑ ማሳየት እንዳለባቸዉ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ አጥብቀዉ እንዳስገነዘቡ ተከታትለናል፣፣ በሌላ በኩል የመለስ ዜናዊን መንግሰሥት በሕግ አማካሪነት እያገለገሉ ቆይተዉ “ኢሕአዴግ” ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ከላካቸዉ በሗላ የፖለቲካ ጥገኝነት በመጠየቅ እዚሁ አሜሪካ በመቅረት ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በሕግ ሞያ ተሰማርተዉ የሚኖሩት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊም “ከሌላዉ ጎሳ በተለየ ለምን የትግራይን ምሁር እና የትግራይ ተወላጅ ብቻ በዚህ እየተወቀሰ ዓይን ዉስጥ ታስገቡታላችሁ? ወዘተ….የሚል ክርክር አንስተዉ መከራከራቸዉንም ጭምር እናስታዉሳልን፣፣ ሥርዓቱ በፈጠረዉ የጎሳ ፌደራሊዝም ምክንያት በመዋደድ እና በመከባባር በጋብቻ እና በፍቅር ተሳስሮ አምላኩን እያመሰገነ በግብርና ሞያ ተሰማርቶ በሰላም ሲኖር የነበረዉ ኢትዮጵያዊ አራሽ የገበሬዉ ሕብረተሰብ ለግጭት እንደዳረገዉ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ ያብራሩትን የተከሰተዉ ሁኔታ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ባለፈዉ ሰሞን ዓምዳችን ላይ፣- በወያነ ትግራይ ፖሊሲ ምክንያት በአማራዉ ሕዝብ ላይ የተነጣጠረ ጥቃትም በፎቶግራፍ የተደገፉ የግጭቱ ሰለባዎችና ሰለባዎቹ የደረሰባቸዉ ጥቃት ሞትና መፈናቀል ከአንደበታቸዉ የተገኘዉ ቃለ መጠይቅ በማስረጃ አስደግፌ እንዳቀረብኩም ይታወሳል፣፣ በስፋት የተቸሁበትን ያለፈዉ ሳምንት ዓምድ በማስታወስ ከዚያዉ በመነሳት ጥሪዉ “የትግራይ ምሁራን ለምን በብዙ ሰዎች ሕሊና እንዲተኮርባቸዉ ሆነ?” ለሚለዉ እሮሮ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም የወያኔ ፖሊሲን ከመደገፍ ይልቅ የትግራይ ምሁራን ወደ ኢትዮጵያዊነት ጎራ እንዲቀላቀሉ ከመቸዉም ጊዜ ዛሬ ጥሪዉ የበረታበት ምክንያት አገሪቱ ከቀዉስ ወደ ቀዉስ እየተረማመደች እንደመሆንዋ መጠን፣ ወያኔም በትግራይ ተወላጆች ድጋፍ ደም እና ላብ ተመስርቶ የተገገነባ ድርጅት በመሆኑ፣አገር ዉስጥ ያለዉን የትግራይ ሕዝብ ላሁኑ ወደ ጎን በመተዉ ለዛሬ የምናተኩረዉ ዉጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እንደሚታወቀዉ ከወያኔ ቁጥር ዉጭ ቢሆኑም፣ አብዛኛዉ የወያኔ ደጋፊዎች እንደነበሩ ይታወቃል፣፣ ወያነ ለሁለት ከተሰነጠቀ በሗላ ግን ከአንድነት ሃይሎች ጋር የጋራ ዉይይት መስርተዉ አንዳንዴም ለኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎች የገንዘብ ዕርዳታ እያደረጉ ግንኙነታቸዉ በማጠንከር ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል አሳይተዉ ነበር፣፣ከጊዜ በሗላ ግን ተመልሰዉ ወደ እዛዉ ወደ ወየኔ ቀስ በቀስ ወደ መለስ ጎራ ሲቀላቀሉ አብዛኛዉ ክፍል ግን ወደ ገብሩ አስራት “የዓረና ወያኔ”፣ ደጋፊ በመሆን የፋሺስቶቹ የአንቀጽ 39 ድጋፍ ሰጪዎች ሆነዉ አረፉት፣፣ በዚህም ድጋፋቸዉ አሳሳቢነት ምክንያት ነዉ ዛሬም በጎሳ እና በወንዝ ልጅ ዙርያ ያለዉ ጠባብ ጭንቅላት እና መሰባሰብ ሰብረዉ መዉጣት ካልቻሉ ከመቸዉም በበለጠ አሳሳቢና አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም የምንልበት ምክንያቶች አሉን ፣፣ በዚህ ዓምድ የምንመለከተዉ የትግራይ ተወላጆች/Community (መሰረታዊ ማሕበራት የሚሉዋቸዉ) እና የትግራይ ምሁራን ሊሂቁ/ኤሊቱ እንዴት የወያኔ መገልገያ ሆኖ እንደቆየ ማሕደሩን እንፈትሻለን፣፣ ለዚህም በርካታ የትግራይ ተወላጆች የሚሰጡት መከራከያ “ምሁሩ ዝም ስላለ ወያኔን ደግፏል ማለት አይደለም”፣ እያሉ “ከናንተ ከአንድነት ሃይሎች ስንት ኦሮሞ ስንት ጉራጌ ስንት ሶማሌ ስንት …ስንት,…. ስንት….. በቁጥር ጸረ ወያኔ ሆኖ በግልጽ የሚቃወም ኖሮ ነዉ የትግራይን ምሁር/መሰረታዊ ማሕበራትን ዓይን ዉስጥ ለማስገባት የምትሞክሩት? ትግል በጎሳ እየተቆጠረ ‘ከእገሌ ስንት መጣ ከእገሌ ስንት ጩኸቱን አሰማ… እየተባለ ሳይሆን በፍላጎት ነዉ ትግል የሚቀጥለዉ” የሚሉት “አዲስ አዚም” የመከራከሪያ ነጥብ ይዘዉ “Defensive” (የማምለጫ መአዘን/መጠምዘኛ)መሸሽያ በመፈለግ ሲከራከሩ የሚደመጡት ወንድሞቻችን ስሕተታቸዉን ለማሳት ካለፈዉ ማሕደራቸዉ እንጀምራለን፣፣ ከሁሉም እስገራሚዉ ጉዳይ ደግሞ የባሕር ወደብ እንድናጣ ተከራክሮ እና ለጠላት ወግኖ ተዋግቶ አገሪቱን አምቆ ያስጨነቃት አደገኛ ቡድን ወያኔ መሆኑን ቢያዉቁም “የተቃዋሚ ሃይሎች ደጋፊም፣ተቃዋሚም አይደለሁም፣ የመንግሥት ደጋፊም ተቃዋሚም አይደለሁም” የሚለዉ ሌላኛዉ የልደቱ አያሌዉ ዓይነት “አዲስ ፈሊጥ” እነኚህ የትግራይ ተወላጆችም ይህንኑ ጅላጅልነት በማስተጋባት አቅጣጫቸዉ ሁሉ ከመቸዉም አስቸጋሪ እየሆነ ስላገኘነዉ፣ የደረስንበት ግንዛቤ አብዛኛዎቹ የትግራይ ምሁራን ለጠባብ ጎሳ (ናሮዉ ናሺናሊዝም)ያላቸዉ ፍቅር ከዉስጥ የተከናነበ በሃይለኛ ያካባቢነት ሰሜት የሚሰቃዩ ናቸዉ ወይንም በግልጽ የወጣ ጎሰኛነት እያጠቃቸዉ ነዉ፣ ወደ ሚል ድምዳሜ ያደርሰናል፣፣ ለዚህም መስረጃዎቻችን ከማሕደሮቻቸዉ ፈትሸን የት ነበሩ አሁንስ የት ነዉ ያሉት? ለሚለዉ መልስ የምናገኘዉ የትግራይ ምሁራን ኢትዮጵያዊያን ወላጆቻቸዉ የእነ አሉላ አባ ነጋ የነ ዮሐንስ አጥንት እና ደም የፈሰሰበትን የምጽዋን ዶጋሊን መሬት እና ባሕር ከጠላት ጋር ወግኖ ኢትዮጵን ወግቶ የትግራይ ህጻናትን እንደ ሙሶሎኒ በቦምብ ለደበደበዉ ለሻዕቢያ ወደቦቻችንን ተከራክሮ ላስረከበ “ለህዝባዊ ወያነ ሓርንት ትግራይ” ያለ ምንም ሓፍረትና ድጋፍቹን በመለገስ እንኚህ ምሁራን ለዚህ ድርጀት ያላቸዉ ያልተሸራረፈ የሰመመን ፍቅር ያሳዩበትን “አሳፋሪ ማሕደራቸዉ” መፈተሽ የነበሩበትን እና አሁን የቆሙበት መድረክ ለመረዳት እንዲያስችለን ላንዴም ቢሆን ወደ ሗላ መለስ ብለን መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፣፣ ከዚህ በታች የሚቀርበዉ ዓምድ “የትግራይ ምሁራን አሳፋሪ ማሕደር” ከሚለዉ አምዳችን ቀንጭቤ አንዳንዱን ለናሙና ላቅርብ፣፣ ታሪክ ዘጋቢዎችም ለምትጽፏቸዉ ታሪካዊ ሰነዶች ይረዷችሁ ዘንድ እነሆ፣፣ በቅድሚያ ቀንጨብ አድርጌ ለናሙና የማቀርበዉ የትግራይ መሰረታዊ ማሕበራት ወያኔ እንዴት ይገልገልባቸዉ እንደነበር አዲስ አበባ ሲታተም በነበረዉ በዜጋ መጽሄት በቁጥር አንድ መስከረም ጥቅምት 1994 ዓ.ም (በፈረንጅ 09/05/2001) ብርበራ በተባለዉ ዓምድ “ጋዶ እዩ! ጋዶ! ጋዶ! (የሁሉም ደጋፊዎች አይደለንም?) በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ዉጭ አገር በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መሰረታዊ ማሕበራት ተጠሪዎች ወያኔዎች ለሁለት ሲሰነጠቁ ያስደመጡን አቋማቸዉ ምክንያት አድርጌ እላይ በተመለከተዉ ርዕስ በወቅቱ እኔ የተቸሁበት አምድ አንዷን ክፍል በጥቅስ ይቀርባል፣፣ ሌላዉ ሁለተኛዉ ደግሞ “ትግራይን ለማዉደም ለምን ፈለጋችሁ? ከትግራዊያን ፕሮፉሽናሎች” በሚል የቀረበ ጋዜጣዊ መግለጫቸዉ ከሰፊዉ ሀተታቸዉ ጥቂት ነገሮችን ብቻ በመጥቀስ አቀርበዋለሁ፣፣ ሦስተኛዉ በጣም ጠቃሚ የነበረዉ በዜጋ መጽሄት የታተመ “ሃሎ! ሃሎ! መቐለ ድዩ? ሃሎ! ሃሎ!መቀሌ ነዉ? በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ያኔ ወያኔ ተሰነጠቀ ሲባል የትግራይ ተወላጆች ከዓለማቱ ተሰባስበዉ ያሰሙት በጣም አስገራሚ የሆነ የተሰማቸዉ ድንጋጤ የሚያንጸባርቁ ልዩ ልዩ መግለጫቸዉን ላቀርብላችሁ ብየ መጽሄቱ ብፈልገዉ ለጊዜዉ አላገኘሁትም፣፣ ሲገኝ ሌላ ጊዜ አስነብባችሗለሁ፣፣ አሁን ወደ ሁለቱም መረጃዎች እንለፍ፣፣መጀመሪያ ከኔዉ ሕትምት “ጋዶ እዩ! ጋዶ! ጋዶ!የሁለቱም ደጋፊዎች አይደለንም?” ከሚለዉ ቀንጭቤ ላስነብባችሁ፣ “……አብዛዠኛዎቹ ዉጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለድርጅቱ/ለወያኔ ፖሊሲ ዕድገትና ጥንካሬ የመንፈስ፣ የሰዉ ጉልበት እና የቁሳቁስ ድጋፍ በመለገስ ድርጅቱን የአትክልት “ዉሃ” ሆነዉ ይህ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን አሁን ወደ አደገበት ደረጃ እንዲያድግ ያልተቆጠበ ድጋፍ ለረዢም ዓመታት ድጋፍ ሰጥተዋል፣፣ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ከወያኔ ጋር ያላቸዉ ግንኙነት “ከልማት ያላለፈ ግንኙነት” እንዳልነበራቸዉ ይገልጻሉ፣፣ እያንዳንዱ መሠረታዊ ማሕበራት ለትግራይ ልማት ዕድገት ሰበብ ሲሰባሰብ፣ በልማት ስም ጎሰኛነትን እንዲጠነክር መግቢያ በር እንደነበር ካንዳንዶቻችን የትግራይ ተወላጆች ዓይን እና ሕሊና የተሰወረ አይደለም፣፣ በትግራይ ኮሚኒቲ የልማት ስብሰባ በሚዘጋጁት መድረኮች ወያነ ትግራይ የዉሸት ሰበካ በማሰራጨት ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የፍትህ፣የልማት ዕድገትና እኩልነት እንዳጎናጸፋቸዉ የሚሰብክበት መድረክ እንደነበረም መረጃ ማቅረብ ይቻላል፣፣ መሰረታዊ ማሕበራት የሚላቸዉ የሴቶች፣የወጣቶች ማህበራት ሁሉ በልማት ስም የስርዓቱ አቀንቃኞች መጠቀሚያ እና የዉሸት ቅስቀሳ ማስተጋቢያ መስመሮች/ቻነሎች ሆነዋል፣፣ ለምሳሌም አንድ ማስረጃ ለማቅረብ ከተፈለገ “አቶ ካሕሳይ በርሄ “The national Movement in Tigray Myth and Realities –February 1991)(ብሔራዊ እንቅስቃሴዉ በትግራይ አፈታሪክ እና እዉነታዎች-1983) በአቀረቡት ጽሁፋቸዉ ላይ እንዲህ ብለዉ ነበር፣፣ “ብዙሃኖቹ ድርጅቶች በዉጭ ከህወሓት ጋር የተቆራኙ የተለያዩ የትግራዊያን ማሕበራት በዚሁ ድርጅት ለሚመራዉ ብሔራዊ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፣፣ ከየግል ገቢዎቻቸዉ የሚያዋጡት ወርሃዊ የገንዘብ መዋጮ የፕሮፖጋንዳ ሥራ (ዉጭ ሰዎችን በመቀስቀስ እና በማሰባሰብ) ከሕወሓት የማሰባሰቢያ ድርጅት ሥር ሆነዉ እንዲሰሩ ለማድረግ፣ ወዘተ…ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል፣፣ በዉጭ የሚገኘዉ የትግራይ ማሕበረሰብ ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠዉ አስተዋጽኦ ያደረገዉ ለ1977-78 ዓ.ም. የሕዝብ ረሃብ በሰጠዉ ወደር የለሽ ምላሽ ነበር፣፣ ከግል ገቢያቸዉ ካዋጡት ጠቀም ያለ መዋጮ ሌላ የገንዘብ ማሰባሰብያ ዝግጅቶችን በያካባቢዉ በማድረግ ዝናብ እና የበረዶ ክምር በሚያስቸግሩባቸዉ ወቅቶች፣ በአዉሮጳ እና በአሜሪካ አዉራ ጎዳና ላይ ከአላፊዉ አግዳሚዉ ገንዘብ አሰባስበዉ በጣም ከፍተኛ ገቢ አስገኝተዋል፣፣ በትግራይ የተከሰተዉን የረሃብ መቅሰፍት ለማስወገድ በርካታ የትግራይ ልጆች ሥራቸዉና ትምህርታቸዉን መስዋእት አድርገዋል፣፣የትግራይ ምሁራንም የዕርዳታ ድርጅቶችን በማነሳሳት እና በማስተባበር የአስቸኳይ ጊዜዊ ዕርዳታ ሊገባ የሚችልበትን ስልት በመቀየስ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፣፣ በብሔራዊ ትግሉ ፖለቲካ እና ድርጅታዊ ሕይወት ዉስጥ እኒህ ማሕበራትም ልክ በነፃዎቹ ክልሎች እንዳሉት ብዙሃን ድርጅቶች ሁሉ ተሳትፎአቸዉና ሚናቸዉ የተጠናከረ ሳይሆን በጣም ዉሱን የነበረ ነዉ፣፣ ህወሓት እንዚህን ማሕበራት የተሳሳቱ መረጃዎችን በመስጠት በአሻጥርና በተንኮል፣ በማስፈራራት እና ከሕብረተሰቡ በማግለል የገቢ ምንጭ እና የዝምታ አሜን ባዮችና ተመልካቾች ብቻ ሆነዉ እንዲቀሩ ለማድረግ ተችሎታል፣፣ “ኢትዮጵያዊያን ራሳቸዉን ለማደራጀት የሚያደርጉትን ማንኛዉንም ሙከራ ለማሰናከልና ለማምከን ህወሓት እንደ መሣሪያ ይጠቀምባቸዋል፣፣” (ቅንፍ እና ኢታሊክ የኔ) ባጠቃላይ በዉጭ የሚገኙ በርካታ የትግራይ ካሉ ዘመዶቻቸዉ ጋር ለመገናኘት ሚችሉት በህወሓት በኩል ሲሆን ብቻ ነዉ፣፣ ይህንን አጋጣሚ/ሁኔታ በመጠቀም ለብዙሓን ማሕበሮቹ በድርጅት አባልነት እንዲመዘገቡ ተጽእኖ ያደርግላቸዋል፣፣ ያስገድዳልም፣፣ ማንም ከዉጭ የመጣ እና በትግራይ ያሉትን ዘመዶቹን ለመጠየቅ የሚፈልግ ሰዉ (ሴት -ወንድ) ከመጣበት ሃገር ካለዉ የህወሓት ብዙሃን ማህበራት የመሸኛ ደብዳቤ ከያዘ እና ሱዳን ከሚገኘዉ የህወሓት ጽ/ቤት ማቅረብ እና ማረጋገጥ ከቻለ ብቻ ነዉ ወደ ትግራይ የመግባት ፈቃድ ለሰጠዉ የሚችለዉ፣፣ ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ትግራይ ሊገባ አይችልም, ማለት ነዉ፣፣ በእነዚህ የብዙሃን ማህበራት አባላት ዘንድ የህወሓት ፖሊሲዎች እና ኢዲሞክራሲያዊ ልምዶች የተቸ ሁሉ የትግራይ እና የትግሉ ጠላት ተደርጎ ታይቷል” (ትርጉም ጎህ 1985)፣፣ የትግራይ ሕብረተሰብ ማሕበራት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አስከዛሬ ድረስ (በተመሳሳይ ሞኝነት “ገዛ ተጋሩ ፓል-ቶክ” “አይጋ ፎረም” “ዩትና” ተብለዉ በሚታወቀዉት መድረኮች በስሜት የሚጋልብ አባል የሚጨፍርበት ጨምሮ ያንኑ የዉሸት ቅስቀሳቸዉ ሕብረተሰቡ በስሜት እያጋለ የዉሸት ሰላባቸዉ እየሆነ እንዳለዉ ጭምር) የወያኔ የገቢ ምንጭ በልማት ስም የወያኔ የዉሸት ፕሮፖጋንዳ ማስጋቢያም ጭምር እንደነበሩ ከላይ ተመልክተናል፣፣ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ “ትግርራይን ለማዉደም ለምን ፈለጋችሁ?” (ከትግራዊያን ፕሮፌሽናሎች) በሚል ለምኒሊክ መጽሄት ተልኮ በሚያዚያ 1993 የትግራይ ኤሊቶች/ምሁራን አንጃዉን በመደግፍ ለሕትምት ካበቁት አንዱን ላቅርብ፣፣ “በድርጊታችሁ የተበሳጨን ትግራዊያን ነን፣፣ እኛን ጣል እርግፍ አድርጋችሁ የጣላችሁንና የተከዳን ትግራዊያን ጓዶቻችሁ ነን፣፣ሕዝባችንና ድርጅታችንን ከልባቸዉ ከሚመኙትና ከሚጠይቁት ዓላማ ዉጭ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዓላማና አጀንዳ የሌለን ትግራዊያን ፕሮፈሽናሎች ነን፣፣ ቁጣችንን በምንም ዓይነት መልኩ ማቀዝቀዝም ሆነ በሱኳር ማጣፈጥ አንችልም፣፣ከልባችን ቀጥተኛ የሆነ ንግግር እንዲኖረን እንፈልጋለን፣፣ ቁጣና ንዴታችንም እዚህ ላይ ነዉ፣፣ አቶ መለስ ጥቂት ጥያቄዎች አሉን፣፣ምን ዓይነት የጨለመ ተግባር ነዉ እየፈጸማችሁ ያላችሁት?ሕሊናችሁ አጥታችሗል እንዴ? ልበቢስ እንዴት ልትሆኑ ቻላችሁ? አለመጨነቅ፣ በጣም ሚዛናዊ አለመሆን፣ ኢትዮጵያችንና ትግራይን ለማዉደም የብረት ሳህን ላይ ለማስቀመጥ መቻኮል ለምን ፈለጋችሁ? ምን ያህል ደንታ ቢስ እና ሓላፊነት የማይሰማችሁ ናችሁ? ከሕዝባችን ጥቅም ይልቅ ራሳችሁን ጥቅም ማስቀደም እራስ ወዳድት እና ምን ያህል የሥልጣን ጥም ቢኖርባችሁ ነዉ? ከድርጅቶቻችን (ህወሓት እና ኢሕአዴግ) ከትግራይ እና ኢትዮጵያ ጥቅም አስፈላጊነት ዉጭ የሆነ ስራ ለመስራት እንዴት ፈለጋችሁ? የ40,000 ሰማዕታትን ለአረሜናዊ ኢሰብአዊ እና በተስፋ ለሚኖር ሥርዓት መስዋዕትነት ወደ ጎን መተዋችሁ ምን ያህል የሓዘን ስሜት የማይሰማችሁ እና ምን ያህል ዓላማ የለሽ ብትሆኑ ነዉ? የሕዝባችን ክብር ለማዋረድ ስትመርጡ ስታበላሹና በዉጪዉ ዓለም ዘንድ አስጊ ደረጃ ላይ መሆናችንን በሰሙ ሁሉ አስፈሪ የምታስደርጉን ምን ያህል ሕሊና ቢስ ብትሆኑ ነዉ? ምን ያህልስ ምክንያት ቢስ ሰዎች ናችሁ? ለክፈለ ዘመን ሕዝባችን ታግሎ ያገኘነዉን ድል ፍሬ አልባ በማድረግ እመቃብር አፈፋ ላይ እንዲዳረግ ስታደርጉት ምን ያህል ሓላፊነት የጎደላችሁ ብትሆኑ ነዉ? ኢፍትሓዊ የሆኑ ለመዋጋት ብዙ መሠረተ ልማቶችን በዓለም ደረጃ የጣለዉን ሕዝባችንን የሞት አፋፍ ላይ እንዲደርስ ስታደርጉ ምንስ ያህል ስሜት የለሽ ብትሆኑ ነዉ? “ጀግኖቻችንስ “የማያስፈልጉ”፣ “አፈንጋጮች”፣ “ሴረኞች” እና “በጥላቻ የተሞሉ” በማለት ዝናቸዉን የምታጠፉትና የምታዋርዷቸዉ ለምንድነዉ? እንዴት እንዲህ ልትሉ ቻላችሁ?የሕዝባችን ስቃይና ሰቆቃ ለማስቀረት ሲሉ የተሰዉ መሆናቸዉንስ እንዴት ዘነጋችሁት? የሰማዕቶቻችን ኑዛዜ፣ምኞት የመሞትስ ምክንያት መሆኑን ምን ያህል ልበ ቢስ ብትሆኑ ነዉ? ምን ያህል ከተያቂነት ነፃ ብትሆኑና ንቀት ቢኖራችሁ ነዉ? በሰማዕቶች ሞት የተመሰረተዉ ህወሓትሕግ መሪዎቻችን በህወሃት ሕገ መንግሥት ላይ ልትዘምቱበት የቻላችሁበት ምን አህል ማን አለብኝነት ቢሰማችሁ ነዉ? አቶ መለስ አስፈላጊ አይደለም ያሏቸዉ ሰዎች ለማገድና ዋጋ የለሽ ማድረግን ወይም የማዉረድን ሥራ ሲሰሩ ምን ያህል ሓላፊነት ቢጎልዎት ነዉ ብለን ልንጠይቀዎ እንፈልጋለን፣፣ እንደዚህ ማዋረድ ማንቋሸሽ ስም ማጥፋትና እገዳ አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ለይ የሚጠበቅ ይመስለዎታልን? በህወሓት -ኢሕአዴግ በሃገራችን ደረጃ በእሳት ተፈትነዉ የወጡትን ጠቃሚ ጀግኖች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እና እንዲሁም አባቶቻችንና እናቶቻችን ላይ የጥላቻ ነበልባልዎን በመርጨት በማዛመት የሚገልጹት ለምንድነዉ? ለምን የነዚህ ጥሩ ሰዎችና ጀግኖቻችን በዓላማ የታነጸዉን ጥሩ ስም ለማጥፋት ለምን ፈለጉ? የእነዚህን የወያኔዎች አለኝታዎች ስም በማጥፋት፣ ለሰዉ መጥፎ አሳቢ እንዲመስሉ የተሳሳቱ እና በጥባጮች እንደደሆኑ አድርገዉ ይገልጿቸዋል? ሥልጣን በራስዎት መንገድ እንደካሁን ቀደሙ ያደርጉት እንደነበረዉ ሁሉንም ነገር በነፃነት የመስራት ጥማት አለበዎት? ለሕዝባችን ፍላጎት፣ለሐገራችን ጥቅም ለአርባሺዎቹ ሰማዕታቶች ሞት እና ዝክር-አልቆሙምን?የትግራይጀግኖችሲያገልሉ የሕዝባችንና የሰማዕቶቻችንም ከብር ማግለልዎ መሆኑንስ በቅጡ ተረድተዉታል? ተገንጣዮቹ ለእዉነት ለሕዝባችን ፍላጎት፣ለሃገራችን ጥቅም ለአርባሺዎቹ ሰማዕታቶች ሞትና ዝክር አልቆሙምን? ያቁሙ አቶ መለስ!! የእርስዎ የግል ፍላጎት ከሰማዕታቶች ከሕዝቡና ከሃገራችን ፍላጎትና ጥቀም ማስቀደምዎት ያቁሙ! “አቶ መለስ ያቁሙ!!..... አሁን አፈንጋጭ የሚሏቸዉ ሰዎች በአንድ ወቅት የሞሶሎኒን ርዕዮተ ዓለም ያራምዱ የነበሩትን ሰዎች ለመጣል የረጂም ጊዜ ትግልና መስዋዕት የከፈሉ መሆናቸዉን አያዉቁምን? ለምን ፋሺዝም በሕዝባችን ላይ እንዲነግሥ ፈለጉ? የክብራችን፣የማንነታችን ባህላችን መከታ በሆኑት ላይ የሚዘምቱበት ምክንያት ምንድ ነዉ?ለምንስ ነዉ ትግራይ የወለደቻቸዉ ብርቅየ ሰዎች ለማባረር የፈለጉት? ይመልሱ እንጂ አቶ መለስ፣የህወሓት ሊቀመንበር? ህወሓት ማለት ለትግራይ ሕዝብ ማንኛዉም ነገር ማለት እንደሆነ ልናስታዉስዎ ይፈልጋሉ እንዴ አቶመለስ?በመጀመሪያ በአቋማቸዉ ፀንተዉ እንዲቆዩ ያደረጋቸዉ ነገር ይህ ዕነቁ ነገር ነዉ፣፣ በዚህ ትልቅ እና “ዕንቁ ድርጅት” የፈለገዉ ዓይነት ሊከሰት ይችላል፣፣ ህወሓት ለህይወታችን ወሳን የሆኑና ዋና ዋና ዉድ ነገሮችን ሰጠን ብቻ ሳይሆን አንድ ህይወትን እራስዋን አድኖልናል ብንል ማጋነን አይሆንም.፣፣ ድርጅታዊ መርሕ አለን በራሳችን እንድንተማመን፣ጠንካሮች ጠንቃቆችና የሕግ ዜጎች እንድንሆን ትልቅ ትምህርት አስተምሮናል፣፣ የሕግ ሰዎች ብቻ እንድንሆን ብቻ ሳይሆን እኛን ለመከላከል የፍትሕ ምሰሶም አቁሞልናል፣፣ ተወዳጁ ድርጅታችን፣፣ ይህ ትልቅ የህወሃት የሕግ ምሰሶ፣ሕገ መንግሥት፣አካሄዶች፣ፕሮቶኮሎች (ሁሉ) የኛ ከለላ ነቸዉ፣፣ ይህንኑን ነዉ እርስዎ በመፈንቀልና እንዲጠላ በማድረግ የእኛን የወደፊት ሁኔታ ትልቅ ጉዳት እና አስጊ ደረጃ ላይ የጣሉት፣፣ በእነዚህ የተስፋ እና የፍትሕ ምሰሶዎች ላይ ነዉ እንደ መናኛ ነገር “ዕቃ -ዕቃ” እየተጫወቱባቸዉ እየሆኑ እንዳሉ ልናስታዉሰዎት ይፈልጋሉ? በጥንካሬያችን፣በተስፋችንና በፍላጎታችን ላይም… በሃገር ዉስጥ ላይ ባሉት ህዝቦች ብቻ ሳይሆን በመላዉ ዓለም ላይ ተበታትነን በምንኖሮዉም ላይ ዕቃ-ዕቃ እየተጫወቱብን ነዉ፣፣ በችግረኞች ትግራዉያን ሕዝቦች እና አርባ ሺሕ ሰማዕታት አርበኞች የተሰጡንን እንዚህ መሠረታዊ መብቶችን እንንከባከባቸዋለን፣፣በኛ በኩል ባሉት እነዚህ ምሰሶዎች፣ሚዛናዊ ጨዋታ ህልቆ-መሳፈርት የሌላቸዉን ምኞቶቻችን ተስፋዎች እናልማለን፣ ወደ ሃገራችን በመሄድም ለህዝባችን ዕድገት አስተዋጽኦ እናደርጋለን፣፣ እናም አቶ መለስ ያቁሙ! ይህን የሕዝባችን ሕልምና ራዕይ ወደ ገደል አይክተቱት፣፣ “… በእርስዎ መካከል እና እርስዎ “አንጃዎች”በሚሉዋቸዉ መሃል ምን እንደተፈጠረ እናዉቃለን፣፣ በምንም ዓይነት አንጃዎች አይደሉም፣፣በፍሰጹም! አቶ መለስ! በፍጹም “ተገንጣዮች አንጃዎች” አይደሉም! እዉነታዉ “ተገንጣዮቹ” ሕጉ በሰማእታት ደም እንደተጻፈዉ ሁሉ አክብረዉ ስለያዙት እና ከእርስዎ አፍራሽ ዓላማ ጋር ለመጓዝ ፈቃደኞች ባለመሆናቸዉና ከሰማዕቶቻችን ከሕዝባችን ለተረከብነዉ ሕግ ስለተገዙና አክብረዉ ስለያዙት ብቻ ነዉ፣፣ እኛ በተሻለ እናዉቃቸዋለን፣፣ እነዚህ ቀናኢ ወንድና ሴቶች ሰዎች፣ ሙሉ መስዋዕትነት የሚያደርጉ ጀግኖች እንደሆኑ እናዉቃለን፣፣ ለገንዘብና ለሥልጣን ብለዉ ሙስና የሚፈጽሙ እንዳልሆኑ ጠንቅቀን እናዉቃለን፣፣ለዚህም ነዉ እናንተ በፈረንሳይ ሱፍ ስትዘንጡና ፋሺን ስታማርጡ እነሱ ግምባር በነበሩበት ጊዜ የለበሱት ቲ- ሸርት አሁንም ድረስ ታንቀዉ ያሉት፣፣ከዚህ በላይ እንኚህ ትጉ ጀግኖቻችን ከመጀመሪያ አንስቶ ተወዳጁ ድርጅታችን የሆነዉ ህወሓት ከመመስረት ጀምሮ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ከማነጽ እና በዛዉ ሳይወስን ድርጅቱን ወደ አስተማማኝ ደረጃ እንዲደረስ ከተረባረቡበት ወቅት ጊዜ ጀምሮ እናዉቃቸዋለን፣፣ አሁንም “ተገንጣዮቹ” “ተራሮችን ያንቀጠቀጠዉ ትዉልድ”The (Generation That Shook the Mountain)ናቸዉ”፣፣ ማለቂያ የሌለዉ የክርክር ባህል ምን ሆነ? የሃሳብ መረዳዳት እና አንድ ሃሳብ እና አመለካካት ላይ መድረስን ምን በላዉ? ቢያንስ ከተመሳሳይ መጽሓፍ የማንበብ ባሕል ማን ወሰደዉ? የድርጅታችን በራስ መተማምንና የሕዝባችን ምንጭ ምልዑነት ግን ሁሉም ነገር እንዲፈጠር አደረገ፣፣የድርጅታችን ፖሊሲ ለዚህ አብቅቷል፣፣መስፍን ኢንጂነሪንግ (ለሎች ኢኮኖሚ ተቋማትን) ብንመለከት ከማንም የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ሃይል ወይም ከማንም ሀገር የተሰጠ አይደለም፣፣ የማይነቃነቀዉ መርሆአችን እና በራስ መተማመን እና ብሎም አንጸባራቂ ነፃነታችን የመንፈስ ፈጠራ ፣የጥሩ ዉጤት ምኞት የመስዋዐትንት ፍሬ (ያስገኘዉ) ነዉ፣፣ ለመሆኑ አቶ መለስ ለምንድነዉ ወንድም በወንድም እህት በህትዋ ላይ ፊት እንዲዟዟሩ ያደረጉበትን ሁኔታ ለምንድነዉ ሊፈጥሩት የፈለጉት? አቶ መለስ እንደሚያዉቁት፣ ህወሓት ካስተማረን በርካታ ነገሮች አንዱ “ሃቅን” መፈለግ ነዉ፣፣ ድርጅታችን ተጠያቂነትና ታማኝነት ያለዉ ሕሊና እንዲኖረን አስተምሮናል፣፣ እናም ህዝባቸን አንድን ነገር ከፊቱ አይቶ ሳይሆን መርምሮ እንዲገዛ አስችሎታል፣፣ በማለት የዛሬዎቹ ባለ አንቀጽ 39ኞቹ እነ ግበሩ አስራት በአንጃነት ከመለስ ዜናዊ ሲለያዩ የትግራይ ፕሮፌሽናል ነን የሙለት እነኚህ ከላይ ያስነበበቡን ደጋፊዎቻቸዉ ሰፊ እሮሮ ካስሰሙን በሗላ የመለስ ዜናዊ አስተዋጽኦ ናቸዉ በማለት ብዙ ነጥቦች ከዘረዘሯቸዉ ነጥቦች አንዱ እነኚህ ምሁራን ነን የሚሉት ሰዎች አሁን መለስን በሚከስሱበት ጉዳይ በወቅቱ እተደረገ በነበረበትም ሆነ ድርጊቱ ከተፈጸመ በሗላም ቢሆን ለበርካታ ዓመታት በመለስ መሪነት አምነዉ አክብረዉ ድጋፋቸዉ ሲለግሱ እንደነበር እናዉቃለን፣፣ አንደኛዉ ክስሳቸዉ እንዲህ ሲሉ መለስን ይከስሳሉ፣፣ “በእርስዎ ሰዓት (የስልጣን ጊዜ) ትልቁ ቁስል የሚሆነዉ የህወሓት ሙዚቀኞች ለኤርትራ ባንዴራ ክብርና ስም መዘመራቸዉ ነዉ፣፣ በትግራዊት እናት ክብር ሥም ሳይሆን ለኤርትራዊት እናት ዝና እና ክብር መዘመራቸዉ ነዉ፣፣ለኛዉ ታጋዮች ክብር ሳይሆን ለሻዕቢያ ታጋዮች ነበር የተዘፈነዉ፣፣ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፣፣መቁጠሩ የሕመም ስሜት ያሳድራል፣፣ በእርስዎ ዘመን ምን ያልሆነ ነገር አለ? ….ስለዚህ በዝነኞቻችን (ተገንጣይ አንጃዎች) ሕይወት ላይ ቁማር እንዲጫወቱ አንፈልግም፣፣ይበቃወታል እና ይግቱት!ለማመን ያዳግታል ልክ እንደ ሕልም ነዉ! እነዚህ ሰዎች ባርማጌዶን ጊዜ በእሳት ተጠብሰዉ፣ተፈትነዉ ያለፉ ጀግኖቻችን “ንጉሶቻችን” ናቸዉ፣፣ ሕዝባችን ወደ ነፃነት መድረክ ያመጡ የተከበሩ እና ሓላፊነት የሚሰማቸዉ “እንፀባራቂ ከዋክብቶች” ናቸዉ፣፣” አቶ መለስ ህወሓት ትግራይን ይቅርታ ይጠይቁ! አንጃዎቹ ወደ ድሮ ቦታቸዉ ይመለሱ እርቁን ይጀምሩ አቶ መለስ!.....ወዘተ በማለት ወያኔ ተሰነጠቀ አገር ጠፋ! ትግራይ ለነፍጠኛ ተጋለጠ! ወዘተ እያሉ የተደመጡበትን “የትግራይ ሊሂቃን ቆሻሻ ማህደር” ጋዜጣዊ መግለጫቸዉ ይህን ይመስላል፣፣ በወያኔ ፖሊሲ እና ባንዳንድ የግንጠላ ፖለቲካ በሚያራምዱ መሪዎች ምክንያት የተካሄደዉ የጎሳ እልቂት እና የጠፋዉ ንብረት እና ሕይወት ተጠያቂዎች ሁሉ ወደ ዓለም ፍርድ ቤት የሚከሰሱበትን ዘመቻ ምሁራን እና የሕግ ሊቃዉንት ካሁኑኑ እንድትዘጋጁበት ዛሬም ደግሜ ደጋግሜ እወተዉታለሁ፣፣ ሕዝብ እንደ ጤዛ እያሳጨዱ፣በደም የተነከረዉ እጃቸዉ እያወራጩ ወደ ፖለቲካ መድረክ ገብተዉ አዳራሽ ተፈቅዶላቸዉ ያንኑ ፋሺስታዊ ፖለቲካቸዉ እንዲረጩ መፍቀድ መፍቀድ ጅልነት ነዉ፣፣ ጊዜዉ ይረዝም እንደሆን እንጂ ወንጀለኞች-ለሕግ-ይቀርባሉ!አመሰግናለሁ፣፣ ጌታቸዉ ራዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com
Monday, June 29, 2009
Subscribe to:
Posts (Atom)