Wednesday, November 9, 2011

አገሬ ዛሬስ ምነው እንዲህ አንጀቴን በላሺው!?


To see the page/font with a wider range, please press the key Ctrl and + sign. To view the page/font with a narrow range, please press the key CTRL and _ sign.ከታች የሚታየው የወያኔ ገበና ማህደር አዲሱ መጽሐፍ ለመግዛት $30.00 ዶላር ሲሆን የአምናው ይድረስ ለጎጠኛው መምህር መጽሐፍ ደግሞ $25.00 ወይንም ሓይካማ የሚል የትግርኛ መጽሐፌ ደግሞ $15.00 ዶላር ብትልኩ መጽሐፎቹን ማግኘት ትችላላችሁ።
Getachew Reda P. O.Box 2219 San Jsoe, CA 95109
Phone (408) 561 4836
      አገሬ ዛሬስ ምነው እንዲህ አንጀቴን በላሺው!?

    ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ)

በጣሊያን አገር Come Un Uomo Sulla Terra (እንደ ሰው በምድር) የሚለውን ዳግማዊ በተባለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የዘገበው አሳዛኝ የኢትዮጵያውያን የስደተኞች ታሪክ በዚህ ድረ ገጽ በስዕለ ድምጽ/ቪዲዩ ክፍል ከወደ ቀኝ የተለጠፈውን አሳዛኝ ዘገባ የተመለከታችሁ የዚህ ድረ ገጽ ተከታታዮች እምባ ሲተናነቃችሁ ገዢዎቻችን ምን ያህል ጥልቀት ያለው ግድያ እንደገደሉን የለካችሁበት አጋጣሚ ያገኛችሁበት ትዝብት ብቻ ሳይሆን ያለምንም ማንገራገር ምንኛ ተንጋለን አንገታችን ለስለታቸው እንደተመቻቸላቸውም የሚጠቁም አንጀት የሚበላ አሳዛኝ የሞት ሞት የሞትንበት የቁም ሞታችንን የሚጠቁም ነው።
ፊልሙን ለማየት የበቃሁት በአንድ አገር ወዳድ ወዳጄ በኩል የተሰጠኝ ጥቆማ ነበር። የታሪኩ ዘጋቢ እና ዋና አቅራቢው ዳግማዊ  ይመር ይባላል። ዘገባው የተቀነባበረበት ቋንቋ ጣሊያንኛ ነው። ወጣት ዳግማዊ የጣሊያኖቹን ቋንቋ በጥራት ይናገረዋል። “እንደ ሰው በምድር” (ትርጉም የኔ) የሚያሳየን ነገር ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርቡ በታሪኩ ውስጥ የተካተቱ የታሪኩ ተሳታፊ እውነታኛ ሰዎች ስም ዝርዝር ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው ብቻ ሳይሆን የተገፈፈው ስብእናቸውም ጭምር ተነጥቆ ሰው በመሸጥ እና በመግዛት የተሰማሩ “አረመኔ ጌቶች” የፈቀዳቸውን ነገር በላያቸው ላይ ሲፈጽሙባቸው ቸልታ ስለተመለከትነው እኛ እና የዓለም ሕዝብ ድርጊቱ እንዲቀጥል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ አድርገናል።


በስዕለ ድምፁ/አውዲዮ ቪዲዮው ውስጥ የሚታዩዋቸው ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ዜጎቻችን ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ዓለም ወደ ስደት ሲሰደዱ ሰው በመሸጥ እና በመለወጥ በአረመኔዎች የንግድ ህዋስ በተሰማሩ “አረመኔ ግለሰዎች ” ከሱዳን እስከ ሲናይ አልፎም እስከ ሊቢያ ድረስ እየተሸጡ ከሊቢያ በፖሊሶች በኩል እንደገና ወደ መጡበት ወደ ሱዳን አልፎም ወደ ምድረበዳ ደግም ዙሮ መልስ ሦስቴ እና አምስቴ ካንዱ ባርያ ፈንጋይ ወደ ሌላኛው በሰሃራ ምድረ በዳ እየተሸጡ እንደ ዕቃ ነፋስ በማይገባበት ዝግ የካርጐ መኪና ታሽገው እየተሸጋገሩ ወንዶቹ በግርፋት ሲሰቃዩ ሴቶች እህቶቻችንም በቆሻሾች እየተደፈሩ ስብዕናቸው ተገፎ አንጀታቸው ባልተወለደ አረመኔዎች  ለስቃይ ተዳርገው የነበሩ ኢትጵያውያን ሰለባዎች ታሪካቸውን የነገሩን በፊልሙ ውስጥ ያሉት ባለታሪኮቹ ተሳታፊዎች ስም ዝርዝር እነሆ፡

፦ ፍቅርተ እንግዳ፤ ዳዊት ስዩም፤ ሰናይት ተስፋየ፤ትዕግስት ወልዴ፤ጸጋየ ነዳ፤ደም መላሽ አምታታው፤ዮሐንስ እዮብ፤ጸጋየ ታደሰ ነጋ ድምጼ እንዲሁም እራሱ ዳግማዊ ይመር… ወዘተ ናቸው።
ይህ ጉድ ስትመለከቱ ኢትዮጵያ የውሃ እምባ ብቻ ሳይሆን ደም ስታለቅስ ታያላችሁ። በነዚህ ዜጎች ክብር እና ሕይወት ላይ የውርደት እና የሞት ስለት የፈረደው ክፍል ማን ነው? በማንስ ምክንያት ነው? ተጠያቂዎቹስ እነ ማን ናቸው? መልሱ ወያኔዎች እና ሻዕቢያዎች ናቸው። እንዚህ ውብ ቆንጀዎች እና ጉብል ወጣት ኢትዮጵያውያን ከአገር ጀምሮ ከአዲስ አበባ፤ከትግራይ ፤ሱዳን እስከ ሰሓራ እስከ ሊቢያ ድረስ የተዘረጉት አረመኔ ጌቶች  ሲደፈሩ እያወቅን ዝምታው እስከ መቸ መቀጠል አለበት? ይህ የቁም ሞታችን በዋዛ ፈዛዛ የምንታዘበው የሙታን መቃብራችን ጸጥ ብሎ እኛኑን ለመዋጥ አድብቶ እየተከታተለን ያለው ሰፊ ጉድጓድ ድንገት ሊደፍረን አንገታችን ስር ላይ ነው ያለው። ታዲያ የሕግ እና የወታደራዊ ባለሞያዎች ይህ እንደ ረግረግ ቀስ እያለ እየዋጠን ያለው ጉድጓድ ለመድፈን ምን እያረጉ ነው?

 ምን ሆኖ ነው እንዳትሉኝ እንጂ በቀላሉ ልቅሶ ልቅሶ ይለኛል፤ሆዴ በትንሽ ነገር ባር ባር ይለዋል። ትላንት የገጠመኝ እንቅልፍ የነሳኝ ትዕይንት ልንገራችሁ። ይህ ታሪክ ስጽፍ ሳልወድ በምጥ ነው እየጻፍኩ ያለሁት። እምባ እየታገለኝ፤ ስዕሉ እፊቴ ላይ ተገትሮ  ይደበዝዛል እንደገና ይመጣል። ፓስታ ቤት ደርሼ አንድ ቦታ ላይ ደርሼ እቤት ከመሄዴ በፊት ነዳጅ ቀድቼ አውራ ጎዳና ላይ ስገባ መኪኖች በፍጥነት ጎዳናውን ያጣድፉታል ፤እጅግ ይበራሉ ፤ እኔም አብሬ እከንፋለሁ። ሽው ብየ ሳልፍ የትራፊክ መብራት ማቆሚያው ምሶሶው ላይ እመሃል ቆሞ ትንሽ ብጣሽ ካርቱን  ለመጽዋች ዓይን የምትስብ ደረቱ ላይ ለጥፎ በሁለት እጁ ደግፎ ካርቱኗን እቅፍ አድርጎ ይዟታል። ሳላስበው ዓይኔ ዞር ብሎ እሱ ጋር ሲያርፍ ፤ ሰውየው ድንገት ድንግጥ ብሎ ኩሩ እና የማይደፈር ቁመናው የሚያማምሩ ዓይኖቹ እና ቅንድቡ በድንጋጤ ሲከፈቱ አየሁት፤ ይህ አከላዊ ድንጋጤው ሆድ እቃየ ያቀፈው ባሕር ውስጥ ሲወረውርብኝ አንጀቴ ደግፈው የያዙት ግድግዳዎች እና ወለሎቹ ተናግተውብኝ አንዳች ነገር ከሆዴ ቧ ብሎ ሲነዝረኝ መሪውን ያያዘው እጄ ስለዛለብኝ ወደ ዳር መኪናውን አዙሬ አንድ ቦታ በመቆም እራሴን ማረጋጋት እና ድንገት የተናነቀኝ አንባ አልቆም ብሎኝ ጊዜ ወሰድኩ። የክፋቱ ብዛት ራሴን በዛ ማዕበል አስገብቼ እንባየን መቆጣጠር እንዲያቅተኝ ገፊ ሃይል የሆነው ደግሞ “አላዋጣኝም” የሚለው የቤተሊሔም አክሊሉ ዘፈን እያዳመጥኩ ነበር ስነዳ የነበርኩት። ዜማው አንጀቴን ከሚበሉት አንዷ ነበረችና ይህ እኔ የገረፈኝን ድንጋጤ ጋር ተጨምሮበት ፤ሰውየው ባእድ አገር እንዲህ ሆኖ ሳየው ዜሜው ላይ ተቀለቅሎ ቆሞ የያዘውን ካረቱን ደረቱ ላይ እንደለጠፈው ያየሁትን ካይኔ አልጠፋ ብሎኝ ይውጣልኝ ብየ ዜማውን ለቅቄ “ስቅስቅ ብየ ነበር ያለቀስኩት”። ዜማዋን ዩ ቱብ ገብተው ይህን ቅጅ ቀድተው ያድምጡ።Bethlehem Aklilu – alawatngem (http://youtu.be/XuW4Okinl8Q) እንደ እኔ ስስ አንጀት ካለዎት ግን ባያዳምጡት እመክራለሁ።

 በጣም የሚከነክነው ደግሞ ለልምና የቆመበት የትራፊክ ቦታ ለመጽዋች አያመችም። ለልመና እና ለዚህ አሳር መከራ መጋለጡ  የመጀመሪያው በመሆኑ የት ቆሞ እንደ ሚመጸወት ስላለወቀበት አጉል ቦታ ነበር የቆመው።

ይህ ሰው ማን ነው? ቢያንስ የአምሳ ዓመት ወይንም አርባ ስምነት አካባቢ ዕድሜ ያለው፤ እኔ ከምሰራበት አካባቢ አጠገብ በኮንትራት ተቀጥሮ ሲሰራ እንደነበር  ካንድ ዓመት በፊት ሳየው የነበረ ኢትዮጵያዊ ነው። ትውውቅ አልነበረንም። ላንድ ሁለት ዓመት አለፍ ላፍ ብየ አየው ስለነበር ሰውየው ትሁት እና በቀላሉ የማይደፈር ደንዳና ኢትዮጵያዊ ይሁን እንጂ ስትጠጋው የእርግብ ያህል የዋህ እና ትሁት ሰላምተኛ ሰው ነው። ከቁመናው እና ከቆፍታናነቱ እና ከኩራቱ ሳየው አገር ውስጥ “ብርቱ ወታደር” ባለ ማዕረግ የነበረ ይመስላል።  ከዛ ሁሉ ጊዜ  አንድ ሦስቴ ሰላም ብየው ሳልፍ ብቻ በሩቅ ነበር ያወቁት። በዚህ አስቸጋሪ ኑሮ ከስራ ወጥቶ ለልመና መዳረጉ እኔን ሲያይ የተሰማው ድንጋጤ ከተቸገረው በላይ ደንዳና ክብሩ ለልመና ተጋልጦ ባገሩ ልጅ ዓይን መታየቱን ደንግጦ ነበር የሚያማምሩ ዓይኖቹ እና ቅንድቡ ደነግጠው እኔኑን በመወርወር ወግተው ያስደነገጡኝ።ምን ላድርግ? ተመለስሼ ዞሬ እሱን ፍለጋ ለማግኘት በሌላ መንገድ መዞር ስለነበረብኝ ዞሬ እስክመለስ እቦታው ላይ አጣሁት። ባገኘውስ ምን አቅም አለኝ እና ነው ካለው ሲኦል እና ውረደት ማላቀቅ የምችለው? እንዲሁ አልቅሼ በደከመው ጉልበቱ እሱንም ላስለቅሰው ካልሆነ በስተቀር!

 እኔ የምጠይቃችሁ ምን እየሆንን ነው? ምን ቢደረግ ይሻላል? አገርም ሞት፤ አዚህም ውርደት እና ሞት ናፍቆትና ትዝታ ሁሉ ተደራርበው የቁም ሞት መትን። ኢትዮጵያ በጭካኔ እና በጥይት በጫካ ባሩድ በሰከሩ ህሊናቸው በተዛባ ክራባት እና ሱፍ በለበሱ ወረበላዎች ተይዛ ፤አገራችን እንዳንኖር የትም ተበትነን የማንም አረመኔ መጫወቻ ሆነን እንቀጥል?  አምላክ እንደጨከነብን ብናውቅ ይፍቱኝ ይፍቱኝ ብለን የምንማጸናቸው የፈጣሪ ወኪሎች እኛ ጋር የሉም እንዳንል፤ አሉ፡ ግን  እነሱም እኛ ጋር አብረው ተቀብረዋል። ጉድጓዱም እኛም እነሱንም እየተከታተለ ይቃጣናል።  አገሬ ምነው አንጀቴ እንዲህ ጨክነሽ በላሺው? Bethlehem Aklilu – alawatngem (http://youtu.be/XuW4Okinl8Q ጌታቸው ረዳ