Thursday, August 29, 2019

ዘረኝነት ትልቁ ዕብደት - (ከሰሞኑ አንኳር አሣዛኝ ክስተቶች ጥቂቶቹ) ምሕረት ዘገዬ (mz23602@gmail.com) Posted at Ethio Semay


ዘረኝነት ትልቁ ዕብደት - (ከሰሞኑ አንኳር አሣዛኝ ክስተቶች ጥቂቶቹ)
ምሕረት ዘገዬ (mz23602@gmail.com) 
Posted at Ethio Semay
ብዙ የዕብደት ዓይነቶች አሉ፡፡ ከያዙ የማይለቁ፣ ከሰው ወደ ሰው ወይም ከእንስሳ ወደ እንስሳ የሚተላለፉ፣ ልብስ እያስወለቁ መለመላን የሚያስኬዱ፣ ጥሩ ልብሶችን እያስለበሱ አእምሮን ግን የሚያስቱ፣… የዕብደት ዓይነቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከሁሉም ዕብደቶች በክፉነቱና ሳይገድል እንደማይለቅ በህክምና ታሪክ የተዘገበው ግን የውሻ ዕብደት ነው፡፡ የውሻን ዕብደት መቶ ፐርሰንት ዕብደት ይሉታል የተማሩቱ፡፡

በዘመናችን ግን ያን የውሻ ዕብደት በዕጥፍ የሚያስከነዳ ሌላ ዓይነት ዕብደት ተከስቶ ሀገርና ሕዝብን ጉድ እያሰኘ ነው፡፡ እሱም ዘረኝነት ነው፡፡ መድኃኒት የሌለውና የይሉኝታና ሀፍረት ገመዶችን በጣጥሶ በመጣል ሰውን መሣቂያና መሣለቂያ የሚያደርግ ነው የዘረኝነት ዕብደት፡፡ ዘረኝነት በተራው የብዙ ነገሮች መባቀያ ነው - ለምሣሌ ለሙስና፣ ለድንቁርና፣ ለታኅተ-እንስሳዊ ባሕርያት ወዘተ.፡፡ ዘረኝነት የሁሉም ነውሮች፣ ወንጀሎችና ኃጢኣቶች መፍለቂያ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን በሽታ እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም አይስጥ፡፡

በዚህ አሳሳቢ ወቅት ወያኔ የሰቀለውን ማውረድ አቅቶን በጭንቀት እየዋለልን እንገኛለን፡፡ ወያኔ የወለደውና ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት ሀገራችንን ሲያምሳት የኖረው የዘረኝነት ዕብደት እጅግ ተላላፊ እንደመሆኑ ሀገራችንን ጫፍ እስከ ጫፍ ወርሮ እንደሰደድ እሳት እያንገበገባት ነው፡፡ ካለ ፈጣሪ ዕርዳታም የሚቆም አይመስልም፡፡ ስለሆነም በተለይ  በገዳማትና በዋሻዎች ዘግታችሁ የምትገኙ የእግዚአብር ሰዎች ለዚህች በሞት አፋፍ ላይ ሆና ለምታቃስትና ለምታጣጥር ሀገር አጥብቃችሁ ጸልዩ፡፡ ክፉን ያርቅልን እንጂ ሀገራችን ለይቶላት እንደሦርያና ኢራቅ ከሆነች መመለሻው ከባድ ነው፡፡ እነጃዋር እንደሆኑ እሳቱን ከለኮሱ በኋላ ጃዝ ያሏቸው ሰዎች ይወስዷቸውና በሞቀ ቤት ያሯቸዋል - ይህ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በሁለትና በሦስት ዜግነት እንደሚቀማጠሉ እናውቃለን፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የቆረጠ ሰው የቢሊዮን ዶላር ሎተሪ እንደወጣለት ይቆጠራል፡፡ የዋናው ሣጥናኤል ቢሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ በሰው አምሣል የተፈጠሩ ሰይጣኖች በሰዎች መሀል እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱትም በዚህችው ጉደኛ ሀገራችን ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ህገ ልቦናና ህገ መሬት ወሰማይ የሚጣስባት ብቸኛ ሀገርም ትመስለኛለች፡፡

አንዳንድ ሰሞነኛ የዘረኝነት ልክፍት ውጤቶችን እንመልከት፡፡ (ብዙዎቹ በሚዲያ የተነገሩ እውነተኛ መረጃዎች ናቸው፡፡) 

1.     ባለፉት ሁለት ቀናት ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ ልደታ መሀል ከተማ ላይ፡፡ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ አንድ አሽከርካሪ መቆም በማይፈቀድ ቦታ አቁሞ ሰው ይጠብቃል፡፡ ወዲያው ከመቆሙ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ይመጣና ሰላምታ ከሰጠው በኋላ በኦሮምኛ ያናግረዋል፡፡ ሹፌሩ ግራ ይጋባና “ኧረ ኦሮምኛ አልችልም የኔ ወንድም!” ይለዋል፡፡ ትራፊክ ፖሊሱም በቅጽበት - “ባንድ አፍ!” እንደምንለው ዓይነት በግሩም አማርኛ “ኦሮምኛ ካላወቅህማ የሚያግባባን ሌላ ነገር አለ” በማለት በወገቡ የያዘውን የደምብ ተላላፊዎች መቅጫ ወረቀት አውጥቶ ግጥም አድርጎ ይጽፍበታል፡፡ ቢለምነው … ቢለምነው… በአቡየ በጂዮርጂስ ቢለው ወይ ፍንክች! በዘረኝነት ደዌ ተለክፎ አብዷላ! እነጃዋርና እነበቀለ ገርባ ምን ሲሰሩ ከረሙና! እነሕዝቅኤል ጋቢሣ ምን ሲተክሩ ቆዩና! ያቺ የኦሮምኛዋ መግቢያ ወገንን መለያ ኮድ መሆኗ ነው፡፡ ለዚህም ደርሰናል! አዲዮስ ኢትዮጵያ፡፡

በበኩሌ ሰውዬው አይቀጣ አልልም፡፡ ችግሩ ሰውዬውን ያስቀጣው ደምብ መተላለፉ ሳይሆን ኦሮሞ አለመሆኑ ወይም አለፍ ሲልም ኦሮምኛን መናገር አለመቻሉ ብቻ ነው፡፡ “የሚያግባባን ሌላ ነገር አለ” የሚለው የዘረኝነት ደዌ መገለጫ ብዙ ነገር ይጠቁመናል፡፡ የአዲስ አበባና የፌዴራል ተብዬው የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ ሳለ ኦሮምያን ገና ከአሁኑ ያለ ዐዋጅና ያለማስጠንቀቂያ በዚህ መልክ ወደ አዲስ አበባ አስገብቶ ሕዝብን ማወክና በማንአለብኝነት እስከዚህ ድረስ በግልጽ ማዳላት ምን ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል አይገባኝም፡፡ የሚመለከተው አካል ይህን ወጥ ረገጥነት ቢመለከተውና ነገሮች ከቁጥጥር ሳይወጡ ዕልባት ቢበጅላቸው መልካም ነው፡፡ ለኦሮሞም ሕዝብ ይህ ነገር የሚጠቅመው አይመስለኝም፡፡ ወያኔዎች በልበ ድፍንነት ያደረጉት የዘረኝነት መድሎ ሁሉ ዛሬ ለጸጸትና እንደፈሳች ዝንጀሮ ለመገለል እንደዳረጋቸው ሁሉ ይህ ዓይነቱ ኦሮሟዊ ፈር የለቀቀ አሠራርም ይዋል ይደር እንጂ እየተለመደ በመጣው የጋራ አገላለጽ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በነገራችን ላይ ያ ኦሮምኛ ያልቻለ ሰው እኮ ኦሮሞም ሊሆን ይችላል፡፡ ኦሮምኛን አለመቻል በራሱ ኦሮሞነትን ሊከለክል አይችልም፡፡ አማርኛ የማይችሉ ብዙ አማሮች አሉ፤ ትግርኛ የማይችሉ ብዙ ትግሬዎች አሉ፤ ኦሮምኛ የማይችሉ ብዙ ኦሮሞዎች አሉ፡፡ ቋንቋ በዘር የማይተላለፍና በመልመድ ወይም በመማር የሚገኝ ማኅበረሰብኣዊ ዕሤት ነው፡፡ ይህን ሃቅ ያለማወቅ ችግር ነው እነበቀለንና ሕዝቅኤልን አሳውሮ ገደል እየከተታቸው ያለው፡፡ እነሱም ያሣዝናሉ፡፡ ቀድሞ አለመለከፍ ነው እኮ እናንተዬ፡፡

2.    አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ወጥቷል አሉ፡፡ በዚያ ፍኖተ ካርታ አማርኛ ቋንቋ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በሁሉም ክልሎች እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ እንደ አማራ እኔን አስደንግጦኛል፡፡ መሆን የሌለበትና የአክራሪዎችን ፍላጎት ያላገናዘበ ነው፡፡ “የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንደሚባለው ለዚህ ለተገፋ የአማራ ሕዝብ ሌላ ችግር የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ እነሕዝቅኤልንና ጃዋርን የመሰሉ “የሀገር መሪዎችን” አናት ላይ አስቀምጦ የፈለገውን ያህል ጠቃሚ ሃሳብ ቢሆንም ይህን መሰል ድፍረት ማሳየት ለቅጽፈት ነው፡፡ ይሄውና ከትግራይ ጫፍ እስከ ወለጋ ጫፍ እየተሰማ ያለው ሮሮም የዚሁ ደምብ ውጤት ነው፡፡ በደናቁርትና በዕብዶች በተሞላች ሀገር ውስጥ እንዲህ ያለ ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ ቤዛና መድኅን ሊሆን የሚችል መመርያ ማውጣት ስህተት ነው፡፡ ቢያንስ ጊዜው ገና ነው፡፡ መሆኑ ግን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደሀገር መቀጠል ካለባት አንድ የጋራ መግባቢያ አስፈላጊ ነው - ያ የጋራ መግባቢያ ደግሞ ኦሮምኛ ወይም ሱማሊኛ ወይም ጉራግኛ ወይም ሃዲይኛ… እንጂ ኪሱዋሂሊ ወይም ቤንጋሊ ሊሆን አይችልም፡፡ በአማርኛ ጥላቻ ያበዱ ሰዎች አብዛኛውን የፖለቲካ ልጓም በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ይህን ደምብ ማውጣት እነሱን ብቻ ሣይሆን እኔን መሰል የዋሆችንም ቢያስደነግጥ ትክክል ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት የጨረባ ተዝካር ዓይነት የኳስ አበደች ሀገራዊ ሁኔታን ነው፡፡ የነሱ ህልምና ምኞት ኢትዮጵያን ባቢሎን ማድረግ ነው፡፡ ግን በሁለት ተቃራኒ ዓለማት ተሰንቅረው የሚሰቃዩም ይመስሉኛል፡፡ ለሥልጣንና ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያን ይፈልጓታል፡፡ አማራን ስለሚጠሉ ደግሞ የኢትዮጵያን ኅልውና አይፈልጉም፡፡ ግራ ተጋብተው ግራ አጋቡን፡፡


ጃዋርና ጃዋራውያን እንግሊዝኛንና አማር|ኛን አጣርተው ይናገራሉ፡፡ በዚህም ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱም፡፡ አንድ ኃይል መጥቶ “ የምትጠሉት ከሆነ እንግዲያውስ ይህን ቋንቋ ከአእምሯችሁ ጓዳ እሰርዛለሁ!” ቢላቸው ተንበርክከው እያለቀሱ ይለምናሉ፡፡ አንድ ሰው የሚጠቀምበትን ነገር ሌላ ሰው እንዳይጠቀምበት መከልከል ደግሞ ንፉግነትና የለዬለት ምቀኝነት ነው፡፡ በመሠረቱ ከ87 ሀገራዊ ቋንቋዎች መካከል ይሰጠው በነበረውና አሁንም እየሰጠ ባለው አገልግሎት ምክንያት አማርኛን ከሌሎች ለይቶ የሀገሪቱ ዜጎች እንዲያውቁት ማድረግ እሰየው የሚያስብል እንዲያውም ዘግይቷል የሚያሰኝ እንጂ እንደዚህ ቡራ ከረዩ የሚያስብል አልነበረም፡፡ እነሱ ራሳቸው አማራ ከሚባለው የሚጠሉት ዘር እንዳልተወለዱና ቋንቋውንም ጥርት አድርገው እንደማይናገሩ የተልእኳቸው አንዱ አካል አማራንና አማርኛን ማጥፋት ስለሆነ ብቻ እየሠሩት ያሉትን የዕብድ ሥራ ይሠራሉ፡፡ በየትም ሀገር ያልተመዘገበ ዕብደት በመሆኑ ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ቢመዘግበው ደስ ይለኛል፡፡ ኢሬቻና አሸንዳየን ከማስመዝገብ ይልቅ ይሄኛው ይመዝገብልን፡፡ የትግራዮቹ ማፈሪያዎች የሰጡት ተቃውሞ ደግሞ ያስቃል፡፡ “አማርኛና ትግርኛ ስለሚመሳሰሉ ልጆቹ ይደነጋገራሉ፡፡” ብለዋል አሉ፤ ጉድ ያለው ገንፎ አድሮ ይፋጃል፡፡ ይህን ፍኖተ ካርታ የነደፉ ሰዎች የቸገረ ቢቸግራቸው እንጂ ለአማራ ወይም ለአማርኛ ባላቸው ፍቅር አይደለም ለአማርኛ ቦታ እንዲሰጠው ያደረጉት፡፡ የቋንቋን ጥቅም እንዳለማወቅ የመሰለ ድንቁርና የለም ወገኖቼ፡፡

3.    ሰሞኑን ጠ/ሚንስትሩ የተገኘበት አንድ የምሁራን ስብሰባ ነበር አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼስ ማፈሪያው እየበዛ ተቸግረናል፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ አንዱ አሻቃባጭና እወደድ ባይ “ምሁር” ይነሳና “ላለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ መሪ አልነበራትም፡፡ አሁን መሪው ሲገኝ ሕዝብ በተራው ጠፋ፡፡” ይህ አነጋገሩ ጠ/ሚኒስትሩን በቁም የሚገድል ነው፡፡ በሀገራችን እየተሠራ ያለውን የዘር መድሎና በአንድ ነገድ ላይ ያነጣጠረ የዘር ፍጅት ለምንከታተል ወገኖች የዚያ ምሁር ተብዬ አሽቃባጭነት ለሀገሪቱም ለሕዝቡም ለጠሚው ለራሱም ትልቅ ስድብ ነው፡፡ ሰዎች በስብሰባዎችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ወቅት የሚናገሩትን ነገር በደምብ ቢያስቡበት ለእንደዚህ ዓይነት ውርደትና ቅሌት አይዳረጉም ነበር፡፡ ከመናገራችን በፊት ደጋግመን ብናስብ ይልበጥ ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን፡፡

4.    እነጃዋር አማርኛን ባለመናገር ይተባበሩን፡፡ እነሱ በአማርኛ በተናገሩ ቁጥር በሀፍረት እየተሸማቀቅሁ አለቅሁ፡፡ የነፍጠኛ ቋንቋ፣ የቅኝ ገዥ ቋንቋ፣ የሚጠሉትን ሕዝብና ሀገር ቋንቋ እየተናገሩ ሥነ ልቦናቸውን መጉዳት የለባቸውም፡፡ ዓለማችን የማንም ያልሆኑና ማንም በባለቤትነት የመጠየቅ መብት የሌላቸው ከሰባት ሽህ አንድ መቶ በላይ ቋንቋዎች አሏት፡፡ እነዚህ ዕብዶቻችን የያዛቸው በሽታ እስኪወስዳቸው ድረስ አማርኛን ሳይጨምር ከነዚያ ልሣናት ለምሣሌ እግሊዝኛን ወይ ዐረብኛን መጠቀም ይችላሉ፡፡ አማርኛን ግን በሚወዱት ይሁንባቸውና ይተውልን፡፡ አማርኛን የሚጠላ ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ከጭንቅላቱ እንዲያወጣው በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ የምትጠላውን ነገር አለመጠቀም ይመረጣል፡፡ ኦሮምኛን የሥራ ቋንቋ ማድረግ ከተፈለገ ደግሞ ይቻላል፡፡ አማሮችንና አማርኛን ከማሰቃየት በደፈናው ፓርላማን ሰብስቦ በአንድ ጭብጨባ መወሰን ነው - የኛ ዕንቅልፋም ፓርላማ ደግሞ በዚህ አይታማም፤ በቃ፡፡ ከዚያም እንዳመጣብን እኛ ሽማግሎቹም ብንሆን ተምረን “አካም ቡልቴ ነጉማ” ማለት አያቅተንም፡፡ … ነገ ጧት የምናፍርባቸው ብዙ ዝግንትል ቅሌቶች አሉ(ብ)ን፡፡
5.    ይሄ “አዲስ አበባ የማን ናት?” የሚሉት የጅሎች ጥያቄ ደግሞ ያስገርማል፡፡ ለመሆኑ “ናይሮቢ የማን ናት?” “ቡዡምቡራ የማን ናት?” “ሆኖሉሉ የማን ናት?” “ኒውዮርክ የማን ናት?” “ዋሽንግተን ዲሲ የማን ናት?” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ምን ዓይነት ገልቱነት ነው ወደ ሀገራችን የገባው? ለኬ እውነቱን ነው “ና አልመታህም” ቢለው “ ‹ና አልመታህም›ን ምን አመጣው?” ብሎ አጥብቆ የሸሸው - አንዱ፡፡ ይሄ ጅልነታችንስ ያስጠላልና እንተወው፡፡ ለሰሚም ግራ ነው፡፡ “ይህች መኪና የማን ናት?” “ያ መኪና የማን ነው?” “ያቺ ቆንዦ የማን ምሽት ናት?” ቢባል ያስኬዳል፡፡ የሚሊዮኖችን መኖሪያ የማን ነው ብሎ መጠየቅ? ከዚያም በሚቃረኑ መልሶች እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ በከንቱ መጨቃጨቅና ሥራ መፍታት? አሻ! ይህንን ዘመንስ ከአምስት ዓመታት በላይ ኮማ ውስጥ እንደከረመው ኤሪየል ሻሮን በሰመመን ማለፍ ነበር! ኢትዮያ ስትነሳ ደግሞ መነሳት፡፡ ይሄን ዕድል ማን ያገኘዋል!

6.   “የጨነቀው እርዝ ያገባል” ይባላል፡፡ የባሰበትም እመጫት፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወያኔዎችና የነሱ ፍጡራን የሆኑ “-ፓ”ዎች ወዳስኮረፉት ሕዝብ ልብ የገቡ እየመሰላቸው በዓላትን በከፍተኛ ወጪ በድምቀት ማክበርና በዩኔስኮና በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ኹነቶችን መዝጋቢ ድርጅቶች ማስመዝገብን ሥራየ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ይሄ ማስመዝገብ የሚሉት ፈሊጥ ደግሞ ቅጥ አምባሩ እየጠፋ ነው፡፡ የውሸት ሣቁንም፣ ዕንቅልፉንም፣ የከንፈርና ጆሮ ትልትሉንም፣ የመጠጥ ገልባጭነቱንም፣ የምግብ አግበስባሽነቱንም፣ አጭርና ረጂም ቁመቱንም… ምኑንም ምኑንም መመዝገብ የለመደው ጊነስ ቡክ ይሁን ዩኔስኮ የኛንም ኢሬቻ ሊመዘግብ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ መመዝገብ መቼም አይሰለቸውም፡፡ አስመዝጋቢው ካላፈረ መዝጋቢው አያፍርምና የመሽኒያችንንም መጠን ትልቅነትና ትንሽነት ከነወርድ ስፋቱ መዝግብልን ካልነው ይመዘግባል፡፡ ፈረንጅ ምን ገዶት! እያሾፈብህ ይመዘግብልሃልኝ - ሊያስቅብህ፡፡

የሆኖ ሆኖ እነዚህ አሸንዳየና ኢሬቻ የሚሏቸው ነገሮች እጅግ እየተጋነኑ ነው - ለጤና አይመስልም፡፡ በሀገራችን ሁሉም ነገር ወደ ፖለቲካነት እየተለወጠ (politicized, even over-politicized እየሆነ) ብዙ ነገር በ“እነሱ”ና በ“እኛ” መካከል በሚፈጠር ቅራኔ ስለሚወጠር ችግሮች እየተባባሱ ነው፡፡ ከፖለቲካ ውጪ መኖር አልቻልንም - የሀገራችን ፖለቲካ ደግሞ ከሌሎች ሀገሮች በባሰ የዮሐንስ ራዕዩ 666 ሆኖብናል፡፡ ከፖተለክን እንኖራለን - ካልፖተለክን አንኖርም ወይም አነስ ሲል መኖር ይቸግረናል፡፡ የጭንቀት ዘመን፡፡ፖለቲካ ደግሞ የፖለቲከኞችን ጥቅምና ፍላጎት እንጂ ሀገር አያውቅም፡፡ ሃቀኛ ፖለቲከኛ ሆድ እንጂ ሀገር የለውም፡፡ የሥልጣንና የዝና፣ የሀብትና የገንዘብ ፍቅር እንጂ የወገንና የሀገር ፍቅር አለው ተብሎ እምብዝም አይገመትም፡፡ በመሆኑም አንድም ቀን ተወስተው የማያውቁ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ዕሤቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል እጅግ እየተጋነኑ ሥራ አስፈቺ እየሆኑ ነው፤ መንገድ በመዝጋትም የጉዞ መጨናነቅን በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ ብዙ ወጪም አላቸው፡፡ የሀገሬ ሙስሊም “ሸርተት ያረጋቸውና ሸሬላን ያበዛሉ” ይላል፡፡ ማሰብ ቀድሞ ነው፡፡ መጥኖ መደቆስም ቀድሞ ነው፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ከመስመር ከወጣና ከተበለሻሸ በኋላ አሸንድየና ሶለል ቢሉት፣ በጣዖታዊ የግምባር ላይ ደም ቅብ የዛፎችን ቆሌ ባዲገዝ ቢለማመኑ፣ በጨምበላላ ሰበብ መስክ ላይ ቢያረግዱ ዋጋ የለውም፡፡ ሀገር የሚተዳደረው በዕውቀትና በጥበብ እንጂ በስሜትና ውዥንብርን በማስፈን በሚከሰት ግርግር አይደለም - ግርግር ለቀጣፊ ብቻ ነው እሚመች፡፡

ከዚህ በተያያዘም ኢሬቻን በአዲስ አበባ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን እየሰማን ነው፡፡ በግሌ ደስ ይለኛል፡፡ የወንድሞቼ በዓል የራሴውም ነው፡፡ ከ150 ዓመታት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ይከበር ነበር ተብሏል፡፡ መረጃ አላየሁም፡፡ ይሁን እንመነው፡፡ ግን ለምን አሁን? አሁን ምን ተገኝቶ ነው ከደብረ ዘይት ወደ አዲስ አበባ ሊዛወር የቻለው? ገና ለገና ኦህዲድ/ኦዴፓ/ኦነግ ሥልጣን ስለያዙ? በዓሉ ሲከበርስ ውኃው ከየት ሊመጣ ነው? ጊዜያዊ ኩሬና ሐይቅ በመስቀል አደባባይ ለመሥራት ታስቦ ይሆን? የሰውን ልጅ ከንቱነትና ተመፃድቆ ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ያቺን የተማሪውን ደብተር የምታበለሻሽ መጨረሻዋ ግን ያላማረ ኮራጅ ጦጣ ታሪክ አስታወሳችሁልኝ? የዚህን ኦሮሟዊ ፖለቲካ ጉዞ መጨረሻ ማየት ናፍቆኛል፡፡ ደግነቱ በቅርብ ሩጫውን የሚጨርስ ይመስለኛል፡፡ “ካነጋገር ይፈረዳል፤ ካያያዝ ይቀደዳል፡፡” ይላል ብሂሉ፡፡ የፖለቲካው ነጸብራቅ የሆነው የኑሮ ውድነቱ ብቻ ኦህዲድን በታትኖ ይጥለዋል፡፡ “ቱ!” ‹ምሕረት ምን አለ!› በሉ፡፡

በመሠረቱ አንድን ነገር ማድረግ ስለቻልክ ብቻ አታደርግም ወይም አታድርግ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ከምክንያትና ከዕውቀት ወጥተህ የስሜትህ ተገዢ ሆነሃል ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ኒውስዊክ መጽሔት ላይ ያነበብኩት አንድ ጽሑፍ አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ጋዜጠኛው ሣይንቲስቱን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል - “ወንድን ወደ ሴት ለውጦ እንዲወልድ ማድረግ ይቻላል ወይ?” ሣይንቲስቱም እንዲህ ሲል መለሰ “አዎ፣ በትክክል ይቻላል፡፡ ግን ለምን? ምን አስገደደንና እንዲህ እናደርጋለን? ሴቶቻችን ‹እምቢዬው፣ አንወልድም› ቢሉን ግዴለም ይሁን ይባላል…”፡፡ ሌላም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ ቻይና ኅዋ ውስጥ በ800 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረቻትን ሣተላይት “አሜሪካንን ሳታስፈቅድ” ከምድር ወደ ሰማይ በሚወነጨፍ ሚሣይል አደባየቻት፡፡ በቻይና የ‹ፐርፌክሽን› ጥበብ ዓለም ጉድ ተሰኘ፡፡ አሜሪካ ግን አበደች፡፡ የውሽማ ሞት አስተኔ ሆነባት - አያለቅሱት ወይ አይተውት፡፡ እናም አለች - “ክብርት ቻይና ሆይ! እንደዚያ ማድረግ እንደምትችይ እናውቃለን፤ ማወቃችንንም እንደምታውቂ እናውቃለን፡፡ እናም ይህን አሁን ለምን እንዳደረግሽ ማብራሪያ እንድትሰጭን እንፈልጋለን፡፡” አያድርስ እኮ ነው! ቻይኒትም ጊዜ አልፈጀችም፡፡ እንዲህ ስትል ወዲያውኑ መግለጫ አወጣች፡፡ “ቺን ቺንጓም ቹ ቻይኗቹኑንሃም ዱምቹንግ አሜሪክቹም ዱችኑግ ቺን ቿ…” በእንግሊዝኛው አሸንዳ አልፎ ወዳማርኛው ሲተረጎም “ ይህ የቻይና እንጂ የአሜሪካ ጉዳይ ስላልሆነ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ለማንም አንሰጥም፡፡ ‹ሥራ ፈቶች!›”፡፡ ቻይንኛ ይችላል ብላችሁ ደግሞ አሟርቱብኝ አሉ፡፡ ሲያምረኝ ይቅር፡፡ በእግረ መንገድ ግን ማድረግ መቻልን ለማሳወቅ የሚኬደውን ርቀት መገንዘቡ አይከፋም እላለሁ፡፡ ቻይናና ኦነግ ማነው ኦህዲድ ግና ሲመሳሰሉ!

“ዘራፍ እኔ ወንዱ!
የሞተ ፈረስ ጋላቢ፤
የደረቀ ወንዝ ተሻጋሪ፤
ትኋን ገዳይ በርግጫ፤
ቁንጫ ገዳይ በጠበንጃ...
ዘራፍ ዘራፍ እትትትት....” እያለ የሚፎክር አጎት ነበረኝ፡፡

ደስ ሲል! በሞተች ሀገር ላይ የፈለጉትን ቁማርና ሰኞ ማክሠኞን መጫወት ማን ያቅተዋል? ወያኔስ በተንጋለለችዋ ኢትዮጵያ ከሩቅ የሚገማ ሰይጣናዊ የመርገምት ሽንቱን ሲያርከፈክፍባት 27 ዓመታትን ዘልቆ የለምን? ቀን ነው፡፡ ለሁሉም ቀን አለው፡፡ ቀን ይሰጣል፤ ቀን ይነሳል፡፡ ቀንን በአግባቡ አለመጠቀም ግን ሞኝነት ነው - ከሞኝነቶች ሁሉ ላቅ ያለና በኋላ የሚያስቆጭ ሞኝነት ለዚያውም፡፡

ኢሬቻ መስቀል አደባባይ ይቅርና አንዋር መስጊድና ሥላሤ ካቴድራል ውስጥም ይከበር ቢባል ዕድሜ ሁሉንም ሥልጣን በእጁ ላስገባው ኦነግ ማለትም ኦዴፓ የማይቻለው ነገር የለም - ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኚህ ሁለትም አንድም የሆኑ ድርጅቶች ያምታቱኛልኝ፡፡ እንግዲህ ይህንና ከዚህም በላይ ማድረግ መቻሉ ከታወቀ ያን በዓል በተለመደበት ቦታ ቢያከብሩ ከትዝብት ይድናሉ ባይ ነኝ፤ የሀገርን አድባር እስከዚህ እየተዳፈሩ መፈታተን የኋላ ኋላ መዘዝ አለው፡፡ መዘዝም ባይኖረው ከፍ ሲል እንደገለጽኩት በቀትረ ቀሊልነት ያስፈርጅና ለትዝብት ይዳርጋል፡፡

“ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል” ይባላል፡፡ አማረብኝ ብለህ በሱሪህ ላይ ቡታንታህን አጥልቀህ ቢሮ አትገባም፡፡ አሳዳሪው ነኝ ብለህ አሽከርህ ጭንቅላት ላይ አትጸዳዳም፡፡ ነውርም፣ ኃጢኣትም፣ ወንጀልም ነው፡፡ ልክህን ማወቅ ብልኅነት ነው፤ ጥፋትህን ሰው ላይነግርህ ይችላል - በመፍራት ወይም በማክበር ወይም በይሉኝታ ወይም ሥራህ እንዲያጋልጥህና በጊዜ ሂደት እንድትዋረድ ብሎ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሣ ሰዎች ጉድህን ላይነግሩህ ይችላሉ፡፡ አንተ ግን ጎበዝ ሁንና ደካማና ጠንካራ ጎንህን ዕወቅ፡፡ ከዚያም ለራስህ ቀይ መስመር አብጅ፡፡ ሰዎች ቀይ መስር እስኪያበጁልህና እስኪያዋርዱህ አትጠብቅ፡፡ ደግመህ ላታገኛት የምትችላትን ፀሐይህን በቅጡ ተጠቀምባት እንጂ አታባክናት፡፡

ታውቃለህ - አክሱም ጽዮን የምትከበረው በለመደባት በአክሱም ነው፤ ግሸን ደብረ ከርቤ ስትከበር የሚያምርባት በግሸን ተራራ ላይ ነው፤ ቁልቢ ገብርኤል ሲከበር ደስ የሚለው በቁልቢ ነው (ነፍስ ይማር ኦነግ እንዳስገደላቸው የተነገረላቸው የደብሩ አበምኔት)፡፡ አየህ - “አባት ሳለ አጊጥ፣ ጀምበር ሳለ ሩጥ” የሚለውን ብሂል አለወጉ መተግበር ቢያንስ የትዝብትን ዕዳ ያስከትላል፡፡ በዚህች የኦነግ ውሳኔ ከንፈሩን ያላንሻፈፈና አፉን በመዳፉ አፍኖ ያልሳቀ አሽሟጣጭ ቢገኝ እቀጣለሁ፡፡ አይ… እውነቴን ነው… ይች ፍየል ከመድረሷ… ዓይነት ነገር በዛች፡፡ ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያን በንግሥናም ይሁን በፕሬዝደንትነትና በጠ/ሚኒስትርነት ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር ኢትዮጵያን እየገዛና እያስተዳደረ እዚህ ያደረሰ ኦሮሞ ዛሬ ገና ሥልጣን ላይ እንደወጣ ለማስመሰል የሚደረገው የደምባሮችና የአክራሪዎች ሩጫ ሊገታ ይገባዋል፡፡ የልጆች ጨዋታ አታድርጉት፡፡ እዚህ ሊነገሩ የማይገባቸው ብዙ ነውሮችን የሚፈጽሙ ጊዜ ሰጠን ያሉ ኦነጎችና ኦህዲዶች አሉና ሃይ ይባሉ፡፡ ዕዳ እያከማቹ መሆናቸው ይነገራቸው፡፡ ዕዳውን ደግሞ እነሱ ወይም ቀጣይ ትውልዳቸው የሚከፍለው እንጂ አየር ላይ ተንሣፍፎ የሚቀር አይደለም፡፡ ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡
Posted at Ethio Semay