Tuesday, May 12, 2009

ቤተ መንግሥትም ቤተክህነትም በምንደኞች ይመራሉ

ቤተ መንግሥትም ቤተክህነትም በምንደኞች ይመራሉ
( ትችቴ በአቶ ኤፍሬም ማዴቦ)
ከጌታቸዉ ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com
ይህ ትችት ለኢትዮሜድያ አዘጋጅ በደብዳቤ መልክ ለአንባቢዎች እንዲነበብ በግማሽ ገጽ ቀለል ባለ ምዕዳን /ትችት ልኬ እንደዘወትሩ አዘጋጁ ካልወደዱት አንባቢዎቻቸዉ ትችቱን የማንበብ ዕድል እና መብቱ ታግደዋልና በደብዳቤ መልክ የተላከዉ ትችት ሰፋ ባለ መልኩ እንዲቀርብ በመወሰን ሰፋ ባለ መልኩ አቅርቤዋለሁ። እነሆ። ቅንጅትን በማፈራረስ እና በዉጭ ያለነዉ ኢትዮጵያዊያንን በማራራቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወተዉ ካገር ፈርጥጦ አሜሪካ እና ለንደን መቀመጫቸዉ ባደረጉ ጥቂት ግለሰቦች የሚመራ ለዉጥን ባጭር ጊዜ በብረት ታግየ አዲስ ስርዓት አመጣለሁ የሚለዉ ግንቦት 7 የተባለዉ አዲስ ድርጅት፣ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ዉስጥ በጠራዉ ስብሰባ በእንግዳነት ይሁን ወይንም በአባልነታቸዉ፣ በመድረክ ተናጋሪነት ከጠሩት ሰዎች መሃከል አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ዳኛ ፍረህይወት ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አቶ ሙሉነህ እዮኤል ተባሉ ሲሆኑ ፣ የእለቱ የመድረክ አዘጋጁ አቶ አበበ በለዉ ነበር ። በወቅቱ ተነጋሪዎቹ ለተሰብሳቢዎቻቸዉ-ያቀረቡት-ንግግርበአዉዲዮድምጽተቀርጾ “www.Ethiomedia.comየህዋ ሰሌዳ ተለጥፎ ሕዝቡ እንዲያደምጠዉ ቀርቦ ነበር። እኔም አድመጬዉ- ከተናጋሪዎቹ አንዱ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ያቀረቡትን ሃይመኖትና ፖለቲካን በሚመለከት ባቀረቡት ንግግር/ትችት ላይ አንድ ለማለት እፈልጋለሁ። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ብዙዎቻችሁ ጽሁፎቻቸዉ ካሁን በፊት አንብባችሗልና አዲስ እንግዳ አይሆኑባችሁም ብየ እገምታለሁ። አቶ ኤፍሬም የሚከተሉት ሃይማኖት የየትኛዉ አማኒ ወይንም የሃይማኖት ሰባኪ ወይም የሃይማኖት ምሁር ይሁኑ አይሁኑ ባለዉቅም ፖለቲካ እና ሃይመኖትን በሚመለከት አንስተዉ የተቹባቸዉ ጉዳዮች አብዛኛዉ እሳቸዉ ስማቸዉ ባልጠቀሱዋቸዉ “ሦስቱ ሃይማኖቶች”በሚሉዋቸዉ ላይ ጠንከር ያለ የተዛባ ወቀሳቸዉ ሲያነጣጥሩ “የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንን”ግን በበጎ አርአያነት ሲያሞግሷት ተደምጠዋል። በተለይም ትችታቸዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ያነጣጠረ በመሆኑ እኔም የዚሁ ሃይማኖት ተከታይ በመሆኔ ቅሬታየን በተቹት ላይ ለማቅረብ መብቴ ነዉና አብረን አንመለከት። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እስኪ ከተናገሩት አንዳንዶቹን መበጥቀስ ለ አንባቢዎቼ ላስነብብና ልተችበት።ስጠቅስ እሳቸዉ ባቀረቡት ቃላት እና አባባል ቃል በቃል ነዉ። አንዳንድ ቦተዋችም አባባለቸዉ ግልጽ ለማድረግ በቅንፍ ስተች ታነብቡኛላችሁ። ልጥቀስ፣- “…ኢትዮጵያ ዉስጥ የሃይመኖት ነፃነት/ኢንዲፔንደንስ አለመኖሩ ነዉ። ለምሳሌ በ2005 (በፈረንጅ አቆጣጠር) ሠልፍ በወጣበት ጊዜ ትናንሽ ልጆች በጥይት እሩምታ ሸሽተዉ ያመለጡበት አካባቢ እንዱ የቤተክርስትያን አካባቢ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲፈጸም እጅዋን ዘርግታ ምትቀበል ቤተክርስትያን ነች። ነገር ግን ባወጣ ያዉጣ ብላ የጥይት እሩምታ የሚወርድባቸዉ ልጆች…አጋልጣቸዋለች። ይህ ሲፈጸም የሃይማኖት መሪዎች ማዉገዝና ፊት ለፊት ሲገባቸዉ፣ይሀንን ማድረግ አልቻሉም። በተሌይም ሦስቱ ትላልቆቹ የሃይማኖት ድርጅቶች ይህንን ማድረግ አልቻሉም።…” አቶ ኤፍም ንግራቸዉን በመቀጠል“…ፊት ለፊት በግልጽ ጥፋት ተፈጽሟል በግልጽ፣ የተናገረችዉ አንዲት ብቻ “የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ብቻ ናት”። ይሄ ደግሞ እንዲሁ ብቻ አይደለም።ምክንያቱም በኢትዮጵያ ዉስጥ ነፃነት ያላት ድርጅት የካቶሊክ ቤተክርስትያን ብቻ በመሆኗ ነዉ።ምክንያታዩም …ጳጳሱ የፈለጉት ቢናገሩ (የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጳጳስ ማለታቸዉ ነዉ)፣ ነገ ጳጳስ አይደሉም። ይወርዳሉ ካቶሊክ ቤተክርስትያን በሚመለከት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ካርዲናል ሊሾምባቸዉ አይችልም። ካርዲናል ሊሾምባቸዉ የሚችለዉ አንዲት ቫቲካን ብቻ ነች። ያንን “እንዲፔንደንት”ተጠቅመዉ ድምጻቸዉን አሰምተዋል። ስለዚህ ነፃነት እንዴት ዓይነት የድምፅ ማስሰሚያ ሃይል መሆኑ ያሳየናል። ይህ ሃይል ነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የታመቀዉ።የሃይማኖት መሪዎች ሚናቸዉ ሊጫወቱ ያልቻሉበት ምክንያት (ይሄ ነዉ)።” ብለዋል። ወንድም አቶ ኤፍሬም ( ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እንደ ጥንቱ በግብፅ እጅ አዙር አገዛዝ አይነት “ድፔንዳንት/ጥገኛ በመሆን”በዉጭ ሃይል ጳጳስ እንዲሾም ቢደረግ “ነጻነቱ ተጠቅመዉ”እንደካቶሊኮቹ መንግሥትን ያወግዙ ነበር ማለታቸዉ ይመስላል።ያ ደግሞ ወደ እጅ አዙር ጥገኛነት እንጂ ወደ ነፃነት እንደማያመራ ብናዉቅም፣በግብጽ/ምሥር መንግሥት የሚሾሙት የኤርትራ ፓትርያሪኩም ከኢሳያስ በትር እንዳላመለጡ ዜናዎቹ የተከታተላችሁ ይመስለኛል። “አስማሪኖ ዳት ካም” በሚባለዉ የኤርትራዊያኖች ሰሌዳ መመልከት ትችላላችሁ። ኣቶ ኤፍሬም ማዴቦ እንደ ካቶሊኮቹ በዉጭ ሃይል ስለማይሾሙ “ነጻነቱ ስለሌላቸዉ” መንግሥት በዜጎች የሚፈጽማቸዉ በደሎች መቃወም/ማዉገዝ አይችሉም፣ ባሉበት አንደበታቸዉ ዞር ሳይሉ በሴኮንድ ዉስጥ “ሊያወግዙ ያልቻሉበት ምክንያት እንደገና በነሱ ላይ ዉግዘቱን እንዲህ በማለት ያወርዱባቸዋል“የሃይማኖት መሪዎች ሚናቸዉ ሊጫወቱ ያልቻሉበት ምክንያት “እኛ ፖለቲካ አይመለከተንም የሚል ነዉ”፣ በማለት ያወግዟቸዋል። ይቀጥሉና እንደ ደቡብ አፍሪካዊዉ ካቶሊኩ “ዲስሞን -ቱቱ” ለዘረኛ መንግሥት አልገዛም ብሎ መቆም አልያም እንደ ኢትዮጵያዊዉ ፕሮቴስታንቱ/ጴንጤዉ(?) “ቄስ ጉዲና ቱምባ” አልገዛም ብሎ ካገር እንደወጡ መቅረት በማለት አቡነ ቴዎፍሎስንና አቡነ ጴጥሮስን በአርአያነት በመጥቀስ ከ35 ዓመት ወዲህ ያሉትን የሃይማኖት ግንመሪዎች ግን ሕዝብ ሲበደል አያገባንም ብለዉ አፋቸዉ ዘግተዋል በማለት እንደሚከተለዉ ይተቻሉ።ልጥቀስ። “ መሪዎቹ ሚናቸዉን ሊጫወቱ ያልቻሉበት ምክንያት እኛ ፖለተካ ዉስጥ አያገባንም በሚል ነዉ። ሃይማኖትና ፖለቲካ ይቀላቀል ሚል እምነት ባይኖረኝም እንደ ቄስ “ዲስሞን ቱቱ” በነጭ አልረገጥ ብሎ ለሕዝብ መቆም እንደ “አቡነ ቴዎፍሎስ” እና እንደ “ቄስ ጉዲና ቱምባ” እዉነትን በዉሸት አልለዉጥም ብለዉ “እንደወጡ መቅረት”፣እንደ “አቡነ ጴጥሮስ” አገሬ በፋሺስት አትገዛም ብሎ በጥይት ተደብድቦ መሞት ለእዉነትና ለአገርና ለሕዝብ መቆም ነዉ እንጂ ፖለቲካ መሆን አለመሆን የሃይማኖት መሪዎች አጥብቀዉ ሊረዱ ይገባል።” በማለት እንደካቶሊኮች ነጻነት ስለሌላቸዉ መናገር አልቻሉም ያሉዋቸዉን ምስኪኖች ተመልሰዉ “ፖለቲካ ዉስጥ አንገባም ብለዉ የሕዝብን ግፍ እያዩ ባይተዋር ሆነዉ ጥግ ሆነዉ የሕዝቡን ግፍ እየተመለከቱ ነዉ በማለት ልክ ተመችቶአቸዉ እንዳሉ በማድረግ አቶ ኤፍሬም በዉሸት በመመርኮዝ “አይመለከተንም” እያሉ ነዉ ሲሉ አላግባብ ሁሉንም በጥቅል ሲተቿዋቸዉ ማድመጥ ፣እጅግ በጣምኑ ነበር የገረመኝ። ከተነጋሪዉ ይልቅ የገረመኝ ደግሞ “የግንቦት 7 ታዳሚዎች የደመቀ ጭብጨባ ሲለግሷቸዉ በመስማቴ ዉሸትን እዉነትንም ቢደባለቅ ባይደባለቅ የጭብጨባ ሱሰኞች የሆኑት የዚህ ቡድን አምላኪዎች እንደዘወትሩ ለዉሸት ትችት በማንጨብጨብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ያዉ አድሮ ቃርያ መሆናቸዉን ያመለክታል።እዉነት እዉነት እላችሗለሁ -አዘንኩ! አቶ ኤፍሬም ምሁር ናቸዉ።ያቀረቡት ያልተመጣጠነ ለሕዝብ የሚተላለፍ ትችት ግን የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም ሆነ ሌሎች በስም ያልጠቀስዋቸዉ ሁለት “ትላልቅ ሃይማኖቶች” በተለይም ወያኔ በተዋሕዶ ቤተክርስትያን ላይ ያደረገዉ ግፍ ያወቁት አልመሰለኝም፣ ካወቁት ደግሞ ለካቶሊክ ካረዲናሉ እና የካቶሊክ ሰባኪያን ምእመናኖች ብቻ አርአያነቱን በመጥቀስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከ35 ዓመት ወዲህ ቤተክርስትያኒቱ ማንም መሪ “በአርአያነት” ሊጠቀስ የሚችል ካህን/ሰባኪ/መሪ/ቄስ እንዳላወጣች አድርገዉ የተዛባ ትችት መተቸቱ ከአንድ ምሁር የሚጠበቅ አይደለም። እንኳን እና እየሞቱ እየታሰሩ እየተሰደዱ ያሉት ምዕመናን እና መሪዎቻቸዉ፣ እንደ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እንደ ቄስ ጉዲና ተሰድደዉ እንደማንም ዜጋ ዉጭ ቢቀሩና ቢኖሩ ለብቻቸዉ ልዩ ታምር ይስሩ የሚለዉ ሕግ ማነዉ ያወጣዉ? አገሪቱ ለካህናቱም ሆነ ለማንም ዜጋ ዕኩል ስለምትደርስ ለብቻቸዉ ልዩ ሸክም ይሸከሙ፣ይሙቱ፣ይታሰሩ፣ እኔ ግን ልተችባቸዉ የሚል ትችት ሚዛናዊ አይመስለኝም። እኛ ያላደረግነዉ አንዳንዶቹ የቤተክርስትያኒቱ መነኮሳት/መሪዎች /ባሕታዊያን ግንባራቸዉን ለአረር አጋልጠዉ ሰጥተዋል።እዉነት ለመናገር ከሆነ እኛ ተቺዎችም የተተቹት ነገሮች በአርአያነት ማሳየት ይጠበቅብናልና፣ እነሱም ያንኑ አደርገዋል ፣ከማደረግም ወደ ሗላ ያሉበት ጊዜ የለም። በመሰረቱ ወያኔ እንደገባ በአንዋር መስጊድ ያደረሰዉ ግድያ ያስታዉሱታል? በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያን እና ገዳማት ቅጥር ግቢ የተፈጸሙት ግድያዎችስ ያዉቁት ይሆን?የሚል ጥያቄ አድሮብኛል። ያገሪቱ ሕጋዊ ፓትርያሪክ አቡነ መርቀሬዎስ እና ካህናቱ ከስደት አስከ ሞት እንግልትና ግፍ ደርሶባቸዋል። ባይተዋር፣ ዳር የቆሙ አይደሉም። ሰለባዎች ናቸዉ ። በባሕታዊ ፈቀደ ስላሴ እና አባ አማሃ እየሱስ እና በመቶዎቹ መምህራን ሰባኪያንና ካሕናት ላይ የደረሰዉ ግፍ የሕዝቡንና የቤተክርስትያኒቱን መብት ለመጠበቅ አልገዛም በማለት ከሕዝቡ ጎን በመቆም እንደሆነ አቶ ኤፍሬም ያዉቁታል የሚል ግምት አለኝ። የካቶሊኮቹ ትግል ካወቁ ያኦርቶዶክሶቹና የሌሎቹ መስዋዕትነት የሚያጡት አይመስለኝም። የተዋሕዶ ኦርቶዶክስ መሪዎች ስለ ሕዝብ እና ቤተክርስትያኒቱ መብት በመናገራቸዉ ስደትና ሞት እንግልት ከሥራ መፈናቀል ሲደርስባቸዉ (አቶ ኤፍሬም ቢዘነጉትም)ካቶሊኮቹ ሙሉ ነጻነት ስላላቸዉ የደረሰባቸዉ በደል እንደሌለ በራሳቸዉ አንደበት አረጋግጠዋል።ታዲያ ሦስቱ ትላልቆቹ ሃይማኖቶች በተዛባ ትችት እና በማይገባ ፖለቲካ አያገባንም እያሉ ግፍ ሲፈጸም እያዩ ቆሞ ተመልካች ሆነዋል ማለታቸዉ ከምሁር አንደበት ሊወጣ የማይገባ በመሆኑ፣ በላይ ላንዲት ደቂቃ እና እንዲት ሃረግ እንኳ “በዚህ መጥፎ ሚና የሚጫወቱና ተጠያቂ የሆኑትን የወያኔዉ ጳጳስ አባ ገብረመድህን/አባ ጳዉሎስ አልጠቀሱዋቸዉም። ሰማቸዉ አንኳ በካሃዲነት ወይንም በግፍ ሰራቸዉ አንስተዉ ሲያወግዟቸዉ አልሰማንም።ለምን? ሃይሞኖቱ ተቅዋሙ በደፈና ከመተቸት ለዚህ ጥፋት ተጠያቂ የሆኑትን በስም መጥቀስ ለምን አልቻሉም?ለማንኛዉም ስለ ወጣት ተማሪዎች የደረሰባቸዉ በደል አንስተዉ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ተጠያቂ በማድረግ /ለመዉቀስ “አያገባኝም አለች”የሚሉን አባባል፣ቤተክርስትያንና አባ ጳዉሎስ ለየብቻ መሆናቸዉ ካወቁ (እንደሚያዉቁት ተስፋ አለኝ) እሳቸዉን በስም እየጠቀሱ ከማጋለጥ እና ከመተቸት ይልቅ በገፈኞች መሪዎች ላይ 35 ዓመት ምንም ያለቺዉ ነገር የለም በማለት እራስዋ እግቢዋ ዉስጥ በመግባት የራስዋን ካህናትና ምዕመናን በጥይት ሲቆሉባት አቅም እንደሌላትና “እንደማንኛችን ዜጎች”ሁሉ እስዋም ተጠቂ እንጂ ቆማ በባይተዋር በምን አገባኝነት ግፍን እንዳላስተናገደች እያወቁ በጠቅላላ የሦስቱ ትላልቅ ሃይሞናት መሪዎችን መተቸት አግባብነት የለዉም። አብዛኛዎቹ ካህናትም ፖለቲከኞችም እንደሚሉት አባ ጳዉሎስ የመንግሥቱ ካድሬ አንጂ የቤተክርስትያኒቱ ሕጋዊ ተወካይ እንዳልሆኑ እየታወቀ ስማቸዉን ላለማንሳት እየሸሹ በደፈናዉ ሁሉንም በዉግዘት መቀጥቀጡ አይገባም ። አንግዲህ ነገርን በማስረጃ ነዉና ፣እኔ ተራዉ ሰዉ ታሪኩን ከምነግር የችግሩ የእንግልቱ የሞቱና ስደቱ ተጠቂዎች እና ቀማሾች የሆኑት በቤተክርስትያኒቱ መሪዎች አንደበት ካደረጉዋቸዉ ቃለ መጠይቆች አቶ ኤፍሬም ማዴቦን ላስተናግድ እና አንባቢ በቂ ግንዛቤ እንዲያደርግና የግንቦት7-የጭብጨባ ሱሰኞችም ትንሽ ቢማሩበት (የሚያዳምጥ ልቦና ካላቸዉ) እነሆ። ቤተ ክህነትም ቤተ መንግሥትም በምንደኞች እየተመሩ ስለሆነ ቤተክርስትያኒቱን በጥቅል እንዳለ መዉቀስ አይቻልም፣የሚሉት በአሀገረ አሜሪካ በስደት የሚኖሩ ብጹእ አቡነ መልከፄዴቅ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ምክትል ፓትሪያሪክ ናቸዉ (ስለ ማዕረጋቸዉ ከተሳሳትኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ እርምቱን ላኩልኝ)፣ ሕጋዊዉ ፓትርያሪኩ ደግሞ ከላይ በፎቶግራፋቸዉ የሚታዩት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቀሬዎስ ናቸዉ። ብፁእ አቡነ መልከፄዴቅ ሕዳር ወር 1993ዓ.ም ኢትኦጵ ከሚባለዉ መጽሄት ጋር አድረገዉት የነበረዉን ቃለ ምልልስ አንኳር አንኳሩን ላስነብባችሁ። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ቄስ ጉዱና ቱምባን አልገዛም ብለዉ እንደወጡ መቅረት በማለት ያሞገሷዋቸዉን ቄስ አንገዛም ብለዉ ብለዉ ከመንበረስልጣነቸዉ የተገለበጡና የግፍ ተባባሪ አንሆንም ያሉት ምእመናኖች የሞት ስደት ሰለባዎችም እንዲያዉቁዋቸዉ ምእመናኖቻችንም እነሆ ላስነብበዎት። አቡነ መልከፄዴቅ፣- “በርካታ ዉሳኔዎችን አሳልፈናል። አንደኛ አዲስ አበባ ያለዉ ሲኖዶስ አለመሆኑን ምዕመናን ሁሉ እንዲያዉቁና ቤተክርስትአን በስደት ላይ እንዳለች እንዲረዱ በአገር ቤት የምትገኘዉን ቤተክርስትያን ደግሞ ባላባቱ ወንዱ ሴቱ ሕዝቡ እንዲጠብቅ ምንደኞች ቤተክርስትያንዋን የማይወክሉ መሆናቸዉን ሁለት ሦስት ጊዜ ባደረግነዉ ስብሰባ ገልጠናል። ሁለተኛ፣- በዉጭ አገር በምንደኞቹ የሚደፈርሰዉ የምእመናን አንድነት አንድ እንዲሆን ምእመናንን በማስተባበር ሲኖዶሱ ራስ እንዲኖረዉ የተለያየ ራስ አንዳይኖረዉ ለማድግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።ሦስተኛ፣-ባገሪቱ ዉስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሳቅርሶች እየተሸጡ እየተለወጡ ካገር እየወጡ ይገኛሉ።የህንን ከፍተኛ ሓላፊነት ሕዝቡን ለማስተማርና ለማስጠንቀቅ ብዙ ሊሰሩ የሚገባቸዉ ዉሳኔዎችን አሳልፈናል። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚያሰኛት ቢሔራዊ ቅርስዋ ነዉ። አሁን የመጣዉ መንገሥትና አሁን ያለቺዉ ቤተክርስትያን መሪ ነኝ የሚሉ ምንደኞች ስለሆኑ ለጥፋቱ ግድ የሌላቸዉ ስለሆኑ ሕዝቡ በአትኩሮት እንዲመለከተዉና እንዲጠብቅ መላልሰን ዉሳኔዎችን አሳልፈናል ፣አሳስበናል። ኢትኦጵ፣- በአገር ቤት በተለይ በጎንደር አደባባይ ኢየሱስ፣ በ አሰቦት ገዳም በአርሲ እንዲሁም በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርሰትያን (በአባ ፈቃደስላሴ ላይ የደረሰዉ)አሳዛኝ ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰደዉ አ ቋም ምን ነበር? ድርጊቱንስ አዉግዞ በአጠቃላይ ያደረገዉ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? አቡነ መልከፄዴቅ.- በአሰቦት።፣ በአርሲ፣ በሐረር ስለደረሰዉ በደረሰበት ወቅት እንዲሁ ተበታትነን በያገሩ ስለነበርን በዚሁ ላይ በሲኖዶሱ ዉስጥ ዉሳኔ ማሳለፍ አልቻልም ፣ እኔም በግሌ ከስራ ዉጭ ሆኜ በሀዘን ላይ ስለነበርኩ፣-ሥራ ፈትቼ (ተግዤ ልበለዉ)የነበረ ስሆን፣ ሲሆን ደረሰዉን የወገን እልቂት ግን በጣም አሳዛኝ ነበርና ሠላም አይሰጥምና ቤተክህነት እየሄድኩ “አረ ባይሆን ፍትሃት ይደረግላቸዉ” እል ነበር። ተቀባይነት አላገኘሁም።ተቀባይ አላገኘሁም እንጂ።አንድም ለስደት የዳረገን ቤተክርስትያንዋም ቤተክርስትያን አይደለችም። አገሪቱ ከእንግዲህ ወዲህ ወገን የሚከበርባት አገር አይደለችም ብየ ነዉ! ስለዚህ በወቅቱ እዚያዉ አዲስ አበባ ስላልነበርኩ በሲኖዶስ መልክ ለማየት አልቻልኩም ። ስለ አደባባይ ኢየሱስና ስለ አባ ፈቃደ ስላሴ በእዉነቱ በጠም የሚያሳዝን ነዉ። አሁንም ደግሜ የምናገረዉ ጣሊያን እንኳ በቤተክርስትያን ዉስጥ ሰዉ አልፈጀም፣ አልገደለም ፣- በእርግጥ በአንድ ቦታ ላይ በጦርነት የተነሳ ቦምብ እየጣለ ቤተክርስትያን አቃጥሏል፣ሰዎችም ሊሞቱ ችለዋል። አላማ አድርጎ ግን በመትረየስ ቤተክርስትያን ዉስጥ ፍጅት አላደረገም። የደብረሊባኖስ መነኮሳት ቢፈጅ ወደ ሰላሌ ወስዶ ሜዳ ላይ ነዉ፣ የዙቋላ መነኮሳትም ቢገድል ሞጆ ወስዶ ነዉ። ወያኔ ግን ቤተክርስትያን እንዳሉ ነዉ የገደላቸዉ። ቤተክርስትያን የሚፀለይበት፣ የፈራ የሚሸሸግበት ፣የሚጠለልበት ቦታ ሲሆን፣-ተደፍሮ የሬሳ ማከማቻ አድርገዉታል። ያንን አዉግዘናል፣አስተላልፈናል እንደዉም እኔ ራሴ በግሌ ሕዝብ ሰብስቤ፣ሰልፍ አድርጌ በዲስኩር ኢሕአዴግንና ያለዉን ፓትርያረክ ነኝ ባዩን አወግዣለሁ፣ እንዲወገዝም አድርጌአለሁ። ምክንያቱም የቤተክርስትያን ጠባቂ በመሆን ፈንታ በጎንደር የደረሰዉን ዕልቂት ከ “ዴቪድ ኮረሽ”-አሟሟት በማመሳሰል አንድ በ “ካልት””ተቃጥሎ የሞተ ሰዉንና ወያኔ የገደላቸዉን ባሕታዊ አነፃፅሮ ተናግሯል።እንደገና ምንም ሰዉ እንዳልተጎዳ ተናግሯል። የሞቱትስ አረፉ።የሚገርመዉ ደግሞ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የታሰሩት ናቸዉ። አንዱ አባ አምሃ እሱስ የሚባሉ ናቸዉ።ከእርሳቸዉ ጋር የታሰሩት ወጣቶች እስካሁን ድረስ እንደታሰሩ አሉ። ፍርድም አላገኙም፣የሚጮህላቸዉ የሚናገርላቸዉም የለም።ወያኔ ደግሞ ለዚህ ደንታ የለዉም።አስሮ አስቀምጧቸዋል። ይህንን መላልሰን ጽፈናል አዉግዘናል። አስካሁን ድረስ ምንም የተደረገ ነገር የለም።በአባ ፈቃደ ስላሴ ሞት ደግሞ ዓለም ነዉ ያዘነዉ። የኛ ቤተክርስትያን ሆን ብላ ያደረገችዉ ስለሆነ ተገቢ ሞት እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል። በቀድሞዉ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጊዜ ቋንጃ የቆረጠ፣ነፍስ የገደለ ቤተክርስትያን ገብቶ “ደወል” ከደወለ ማንም አይነካዉም ነበር።በተለይ “ዳሩ እሳት መካከሉ ገነት” ተብሎ የሚነገርላቸዉ የታወቁ ደብሮች አሉ። እዛ ሄዶ ከደወለ “እገሌ ደዉሏል አይነካም” ተብሎ ከዚያ ቦታ እንዳይወጣ ይታገዳል እንጂ አይነካም ነበር ከዚያ ቦታ ሲወጣ ደግሞ መንኩሶ የሚወጣ ከሆነ ሞቷልና አይነካም ይባላል።ዝም ብሎ ሸልኮ ከወጣ ነዉ የሚያዘዉ ይያዛል ከነዚህ ሁሉ ለመዳን የነብስ ገዳይ ቋንጃ ቆራጅ ሰዉየዉን ይዞ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ ያስታርቃል ወይም በፍርድ እንዲቀጣ ያስደረጋል። ንጉሠነገሥቱ እንኳን ደፍሮ ሠራዊት ልኮ ቤተክርስትያን አያስደበድብም፣ ሕዝብም አያስጨርስም ነበር። ይሄ ሁሉ ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ በዚህ በወያኔ ጊዜ መኖክሴ ቤተክርስትያን አገልጋይን በአዉደ ምሕረት አስገደሉ ገዳዩም የፓትርያሪክ ሰዎች ወይም ራሳቸዉ ናቸዉ እየተባለ ነዉ የሚነገረዉ ። በሕታዊዉ የሞቱት በቤተክርስትያን ቅፅር በአዉደ-ምህረቱ፣ታቦቱ ካለበት ከመጋረጃዉ ላይ መሆኑ ለሰሚዉ ግራ ነዉ። እግዚኦ! በዘመኔ እኔ ባለሁበት ወንድሜ ተገደለብኝ” ብሉ ሙሾ ማዉረድ የሚገባቸዉ አባ ጳዉሎስ ነበሩ። እዉነተኛ ክርስትያን ቢሆኑ እሳቸዉም ሆነ ግብራበሮቻቸዉ አንድ እርምጃ ሳይወስዱ ለጊዜዉ አንድ ግለሰብን “ገዳዩ እሱ ነዉ” ብለዉ እንዲታሰር አደረጉ። በሗላ ደግሞ አለፍርድ ፈትተዉ ለቀቁት። ሆን ተብሎ በትዕዛዝ የተደረገ ይመስላል። የሚያሳዝነዉ ባእነሱ ላይ ሳይሆን በቤተክርስትያኒቱ ላይ ጥቁር ነጥብ ማረፉ ነዉ። ቄሶች እንዲህ አደረጉ እየተባለ እኛንም ሁሉ በስመ ቄስ ሊያስተቸን በቅቷል ይህ የተፈጸመዉ ግን በምንደኛዉ ሲኖዶስ እንጂ በስደተኛዉና በእዉነተኛዉ ሲኖዶስ ባለመሆኑ የእኛን ነፃነት አላሳጣም ። ኢትኦጵ፣- እርሰዎበመላ ሐገሪቱ በተለይም በቤተክርስትያኒቱ የሚሰራዉ ትከክል አይደለም ብለዉ ተሰድደዋል። ይሁን እንጂ በስደት ላይ ባሉበት ጊዜ በተደጋጋሚ አማላጅ እንደተላከበዎ ይሰማል በርግጥ ተልኳል? አባ መልከፄዴቅ፣- ሳልሰደድ ከስራ ዉጭ ካለሁበት ወቅት ነዉ ዘጠኝ ጊዜ አማላጅ የተላከብኝ።የመጡበት ምክንያት “ያባ ጳዉሎስን ሹመት ተቀበል፣የወያኔ መንግሥት አትክሰስ፣ አትዉቀስ፣ ተባብረህ ሥራ ወደ ቀድሞ ሥልጣንህ ትመለሳለህ” የሚል ነበር ። የኔ ምላሽ ደግሞ “እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ነኝ፣ብሞትም ብኖርም ምንም ዋጋ የለዉ፣የምጠይቀዉ ስላገሬ ነዉ፣ሕዝብ በነፃ እርምጃ አይገደልም፣ቁጥቋጥ አይደለም አይጨፈጨፍም” የሚል ነበር። በመቀጠልም “ሕግ አይፈርስም በአንድ ራስ ሁለት ምላስ አይኮንም በአንዲት ቤተክርስትያን ሁለት ፓትርያሪክ አይሾምም”-እያልኩ ሁሉንም መልሻቸዋለሁ። ሽማግሌ የሚባሉትም የኔን፣ምላሽ አይናገሩም፣ እዛ የሚጫኑትን ብቻ አምጥተዉ “ምን ቸገረህ? መስለህ ተመሳስለህ ኑር” ሲሉኝ ቆዩ “እንዴት አይቸግረኝም? ቸግሮኝ እኮ ነዉ ከናንተ ጋር የማልሆነዉ፣ እናንተ ባይቸግራችሁ እኔ ይቸግሮኛል”-እያልኩ እመልሳቸዉ ነበር።ከተሰደድኩም በሗላ መምጣቱ ይመጣሉ፣፣ ፊት ለፊት አይናገሩንም እንጂ “እሱ ነገር ያከርራል፣እሱን ትተን በዙርያዉ ያሉትን እናነጋግር እያሉ ሌሎችን እያነጋገሩ ይሄዳሉ። ያነጋገሯቸዉ ባልደረቦቼም “እሱ ከሌለ መልስ አንሰጥም” እያሏቸዉ ይመለሳሉ እንጂ አስከ መጨረሻዉ ወደ እኔ አልቀረቡም።” በማለት ሰፊዉን ያላቀረብኩላችሁ ቃለ መጠይቁ በዚች ብፁእ አባታችን በተናገሯት ሐረግ ልዝጋ “… በዚህ ወቅት ተወላጅ ንን ብለዉ ኢትዮጵያዉአኖቹ ኢትዮጵያን ሊአጠፉ ሲነሱ ግራኝን ይበልጣሉ፣ ጉዲተን ይበልጣሉ ነዉ ምለዉ፣፣ እነዚያ ባይማሩ የሃገር ፍቅር ባይኖራቸዉ ነዉ፣፣ እነዚህ ግን ተምረዉ የሀገር ፍቅር በመያዝ ፈንታ የሃገር ጥላቻ፣ የወገን ጥላቻ ያደረባቸዉ ከነዚያ የባሱ አረመኔዎች ናቸዉ ብየ እናገራለሁ።”በማለት የወያኔ ጨቋኝ እና ጨካኝ መንግሰሥት ወያኔ ከሾማቸዉ የራሱ የቤተክርስቲያኒቱ ሕገ ወጥ ሹማምንትን በማዉገዝ ቃላቸዉን ጮክ አድረገዉ በማሰማት ከሕዝብ ቆን ከቆሙት ከሺዎቹ ካሕናት እና መነኮሳት ጳጳሳት መካከል አንዱ አቡነ መልከፄዴቅ የቤተክርስቲያኒቱ አቁዋምና ኑሮ ፣እንግልት ፣እየደረሰባት ያለዉ ግፍ አስረድተዋል። ወንድሜ አቶ ኤፍሬም ማዴቦም ከዚህ ቃለ መጠይቅ ምን ትምርት እንደሚቀስሙ ባላዉቅም ፣ በደፈናዉ ቤተክርስትያኒቱን ከመኮነን ፣ አጥፊዎችን በስም እየጠቀሱ ትችቱን ወደ መተቸት የሚገባዉ ክፈልና ግለሰብ ብያደርጉ ለወደፊቱ የተሻለ ነዉ ብየ ወንድማዊ ምዕዳኔን ለመለገስ እወዳለሁ። ተጠቂዎችን እንደ ቆሞ ተመልካች ማድረጉና መወንጀሉን ይቅርብን ማለቴ ነዉ። በቤተክርስትያን አለቆችና ምዕመናን እየደረሰ ያለዉ ግፍ ከሕዝቡ የቀለለ ሳይሆን የከፋ መሆንና ግፉን እየቀመሰች እና እያወገዘች መሆኑን ሕዝቡ እንዲያዉቀዉ ማድረግ የምሀራን ሓላፊነት ነዉና፤ በሁኔታዉም ታሪክ እየመዘገበን ነዉና ; “ከቄስ ጉዲና” ወይንም “በባቲካን ከመሾሙት ከካቶሊኩ ዲስሞን ቱቱ” ባልተናነሰ ያዉም በደመቀ አኩሪ አርአያነት ህይወታቸዉ ለፍትህ የሰጡ ባህታዊ መሪዎቻችንና ቀሳዉስቶች መነኮሳትና ካህናት ኢትዮጵያዉያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አገልጋይ ዜጎቻችንም ስላሉን በዚህ አጋጣሚ ዕዉነት በዕዉነት እየመስከርን ዉለታቸዉን እና መስዋዕትነታቸዉን በክብር እንዲዘከር የተማረዉ ክፍል ልብ እንዲለዉ አደራ እላለሁ። አመሰግናለሁ። የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ ንግግር ለማዳመጥ በተጠቀሰዉ በwww.Ethiomedia.com ድረገጽ ወይንም www.Ecadforum.com በተባለዉ የግንቦት 7 እና መሰሎቹ ድረገጽ ደጋፊ በመጎብኘት ያድምጡ። ጌታቸዉ ረዳ (ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ) www.Ethiopiansemay.blogspot.com