Monday, December 7, 2009

በደረቀ ወንዝ መሻገር የሚቀናቸዉ ተቃዋሚዎች

በ18 ዓመት ምን ያልተፎከረ፣ ያልተነገረ፣ ያልተዛተ ነገር አለ? የቀረ የለም! ያ ሁሉ ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ ነዉ፣፣ በራሳቸዉ ብዕር “አርበኛ” ነኝ እያሉ ስለራሳቸዉ አርበኝነት የሚጽፉ ብዙ አሉ፣፣ እነዚህ ሰዎች ወያኔን በመጣል በኩል የሚደረገዉ ትግል በሞቀ ቤት ዉስጥ ቁጭ ብለዉ የአየር ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ በተተከለበት መኖርያ ቤቶቻቸዉ ሆነዉ አሰልቺ 20 ገጽ ስለራሳቸዉ አርበኝነት እና በወያኔ ላይ የስድብ ዶፍ በማዉረድ ብቻ ወያኔን ከሕዝብ ጫንቃ እንዴት መወገድ እንዳለበት የሚነግሩን በሀገራችን የትግል ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የትግል ዘዴ እያየን ነዉ፣፣ በእነዚህ ክፍሎች የሚሰነዘሩት በየስድብ ግጥሞች እና አስነዋሪ ዘለፋዎች በወያኔ ሳይሆን ወያኔን ለመጣል በአገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሰዉ በጣም ሰፊ ድጋፍ እና ቀዳሚ ተቃዋሚ በመሆን የታወቀዉ በ97 ምርጫ ቅንጅትን ቅንጅት ያሰኘዉ በ “ታላቁ -መኢአድ” ጭምር ነዉ፣፣ ጥያቄ አለንም በማለት ራሳቸዉን በጠየቁት ጥያቄአቸዉ ላይ ራሳቸዉን በድርጊቱ አስሰልፈዉ የራሳቸዉን ጥያቄ ራሳቸዉ እንዲመልሱት የማይፈልጉ “ጠያቂዎችም” በየማአዝናቱ ብቅ በማለት ጠያቂዎቻቸዉን እየለጠፉ ነዉ፣፣ይሄ የጉድ ጉድ ተሰምቶም ታይቶም አይታወቅ፣፣ “እኔ ስራ አለኝ እና አንቺ ጋግሪሊኝ” እያለች ታላቋን እህቴን ሁሌም በጥያቄ የምታሰለቻት ጎረቤት ነበረችን፣፣ የነኚህ ጠያቂዎች ጉድ ስታዘብ “ያገራችን ጠላት መች ወያኔ ብቻ ምስጢሩ ረቂቅ ነዉ ጊዜ ይስጠን ብቻ” በማለት የገጠሙት የአንድ ገጣሚ ግጥም ትዉስ አለኝ፣፣ እነኚህ ጠያቂዎች “የማን ወጥ ሊያማስሉ” ነዉ፣ ለመኢአድ እና ለመኢአድ መሪዎች እና የመኢአድ ደጋፊዎች እያሉ በሞቀ ቤት ቁጭ ብለዉ “ራሳቸዉ በግብር የማይተረጉሙዋቸዉ ጥያቄዎችን” በማዘጋጀት እኛም ሆንን የመኢአድ መሪዎች ለጥያቄአቸዉ መልስ ለመመለስ የምንገደደዉ? እናንተስ ዉጭ ያላችሁት ሕብረተሰቡን አንድ ለማድረግ ምነዋ አቃታችሁ? በተቃዋሚነት 18 ዓመት የሻገታችሁበት መንበር ያዘጋጀዉ ተዋጊ ሰራዊታችሁ በየትኛዉ ጨረቃ ላይ ወጥቶ እየተታኮሰ ነዉ? ቢባሉ መልሳቸዉ ምን ይሆን? 18 ዓመት መኢአድን ተጠያቂ ሊያደርጉት ይሆን? እኮ ምንድር ነዉ ነገሩ! ራስን መጠየቅ አያሻም? ሀፍረት ምን ማለት እንደሆነ የማያዉቅ በዉጭ አገር የሚኖር የወያኔ ተቃዋሚ እርስ በርሱ እንኳ እንዴት መስመር እንደሚችል የማያዉቅ “18 ዓመት “ባለህበት” የረገጠ” የሻገተ ግብዝ ተቃዋሚ” ዛሬ ደርሶ በመኢአድ ላይ ብሔራዊ ስሜት የሌለዉ፣ አገር የከዳ፣ ለወያኔ ያጎበደደ …ወዘተ ወዘተ በማለት በመኢአድን አንጋፋ መሪዎች ላይ የሚያወርደዉ ዘለፋ መነሻዉ ምንድነዉ ብለን መጠየቅ የለብንም፣፣እንጠይቅም! ዉጭ አገር ሚኖረዉ ኤሊት/ምሁሩና አጋፋሮወቹ የፖለቲካ ተፎካካሪ ሃይል መሆኑን ካቆመ 18 ዓመት ሆኖታላ! ሞቷል! ተራ ስጋ ነዉ! በክት ነዉ! በሰብሷል እኮ፣ ግማቱ አያስጠጋማ! መልክዕቱ ከተግባር ጋር ስለማይያያዝ መጓዙን አቁሟል፣ ወገብ የለዉም! ሰባራ ወገቡ በመኢአድ ላይ ሊሞረከዝ ይፈልጋል! ሁለመናዉ ሳየዉ ወደ ሓላም ወደፊትም መጓዝ ያቀተዉ ሰባራ ባሊስትራ ይመስለኛል፣፣ ነገረ ስራዉ “የሚያሰራጫቸዉ የራዲዮን እና የጽሁፍ ቅስቀሳዎች ባማሩ ሐረጎች እና በተዋበ የጽሁፍ ቅንብር ማቆነጃጀት እና ሕዝቡን መሸንገልና ማሞኘት ሰባራ ወገቡን መሸፈኛ አድርጎታል፣፣የተቀናጀ ስልትና መሪ ስለሌለዉ ግብተኛ እና ስሜተኛ በመሆኑ ክፉኛ የተበላሸ ነዉ፣፣ ደግነቱ ዉጭ በመኖሩ እንጂ አናረኪነቱ አገር ዉስጥ ቢሆን በጣም አስፈሪ የሶማሊ ስርኣተ አልባ ባሕሪ በማስፈን አገሪቱን ከወያኔ ባልተናነሰ ድርጊት ያዉክ ነበር፣፣ ዉጭ አገር የሚኖረዉ ሊሂቁ ክፍል ስነ ሃሳብ እና ተግባር ማገናኝት አቅቶት ክፉኛ ሲጮህም ይደመጣል፣፣ ከጭንቅላቱ የበሰበሰ ሊሂቅ ራሱን ለመሸጥ ራሱን ማግለል ወይንም ማጽዳት እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ይህኛዉ ክፈል ራሱን ከሚመስል ማራባት ካልሆነ አዲስ አስተሳሰብ እና የትግል ስልት ማዘጋጀት አልቻለም፣፣ የተደጋገመ የፖለቲካ ትርዒቱ “እጅ እጅ” ይላል፣፣ ድንግል ስልት መፍጠር እና ድርጊቱን ራሱን በተግባር አስግብቶ እስካላሳየ ጊዜ ራሱን መፈተን ያልቻለ ጠየቂ ሌሎች እንዲመልሱለት ስለ ፖለቲካ ማዉራቱ ቢያቆም ይመረየጣል፣፣የአምባ ገነኖች ዕምሪ (ነብስ) እንኳን በስሜት ሊወገድ በዓረር ጥይትም ቢበሳ ከጠንካራ ጅማት የተሰራ ነዉና በሳላ ፣ጠንካራ እና በስልት የሚንቀሰቀስ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪ ያስፈልጋል፣፣ ለዚህም መኢአድን በግምባር ቀደም መደገፉ አሁን ላለንበት የትግል ደረጃ እና አማራጭ “አማራጭ የሌለዉ ወቅታዊ” ነዉ፣፣ ሊሂቁ 18 ዓመት ለሱስ ብቻ ፖሊካን የሕሊና መዝናኛዉ አድረጎት እያየን ነዉ፣፣ሳይታሰር፣ሳይንገላታ፣ ጥይትና የጸጥታ ሰዎች ማስፈራራትን ሳያጅበዉ ፖለቲካ ማዉራት ሱስ አድረጎታል፣፣ ይህ ሱስ ደግሞ በሕክምና እንጂ እንዲሁ በዋዛ የሚለቅ ሱስ አይመስለኝም፣፣ እጥጥ ሙጥጥ ብሎ ከተግባር የራቀ በስድብ እና በግጥም እየታጀቡ በየራዲዬኑ እና በየሬስቶራንት የክብ ጠረጴዛ ስብሰባዎች መጯጯህ ፣ ወረቅት በየመንደሩ በየሱቁ እና በየምግብ ቤቱ ወረቀት እየበተኑ “ከሃዲዉ ሃይሉ ሻዉልን እንዴት ተመለከትክልኝ? ወያኔን መዉጫ መዉጫ ቀዳዳ እያሳጣዉ ያለዉ ሸጋዉ የግንቦት7 ጦር መሪ ብርሃኑ ነጋ አወድስልኝ! በሻዕብያ የሚቀለበዉ አርበኞች ግንባር አዲስ አባባ የወያኔን ጦር በማንቁርቱ አንቆ ከምኒሊክ ቤተመንግስት ወደ እስር ሊወረዉረዉ ተቃርቧል፣….. አዲጎሹ፣ ሁሞራን ተቆጣጥሮታል! በድል መግባቱ አይቀሬ ነዉ ! ስየን ነጋሶን፣ መራራን፣በየነን የጋራ ግንባር ፈጥረዉ “አዲሲቱን ኢትዬጵያ በወርቅ ሳህን ሊለግሱን ነዉ ፣ ኢትዬጵያዊነት እያሸነፈ ነዉ! እያለ ሙታን ለሙታን በሚደረገዉ ንግግር ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እንደ ፖለቲካ ትግል ማሰራጨት ለኢዬጵያ ሕዝብ የሚፈይደዉ አንዳችም ቁም ነገር የለም፣፣ በሲያትል ኢትዬጵያዊያን የተደረገ ጥናት በማለት ድረገጽ የተሰራጨዉ “ጥናት” ስንመለከት ዉጭ ያለዉ ተቃዋሚ - ከዚያ ያለፈ ስራ መስራት እንደማይችል ያመለክታል፣፣ ያንን ፕሮፖጋንዳ ለማሰራጨትም “ከጊዜ እጥረት አኳያ” ማቅረብ ያለብን ይሄዉ ነዉ በማለት የችን ያክል መራመድ እንደሚሄድ ገልጿል፣፣ የወያኔን መንግሥት ለማጣል አገር ዉስጥ ሆነዉ እንደ እነ መኢአድ ቢታገሉ ከጊዜ እጥረት አኳያ ወያኔን እንዴት ታግለዉ መጣል ይችሉት እንደነበር አመላካች ሚዘን ይመስለኛል፣፣ ይሄ ግብረን ያላቀናጀ ትግል እና በመኢአድ ላይ ያነጣጠረ ፕሮፖጋንዳ እና ዘለፋ ትልቁ አዲሱ በሸታቸዉ እየሆነ መጥታል፣፣ ይህ በሽታ ደግሞ በቀላሉ የሚገላገሉት ሱስ አይሆንም፣፣ ከምር የኢትዬያን ሕዝብ እንወደዋለን፣እንስገበገብለታለን እያሉ በየድረገጾች ፣በሲዲ እና መጻሕፍቶች ግጥምና ሀታታ እንደሚያዥጎደጉድለት ሁሉ ፍቅራቸዉን በግበር ለማሳየት አገር ዉስጥ መግባት እና ሃይሉ ሻዉል እያደረጉት ያሉትን ነገር አልወደድነዉም እያሉ የሚጮሁበት ሁኔታ መለወጥ ይጠበቅባቸዋል፣፣ እንስገበገብልሃለን እያሉ ለሚጽፉለት እና በወያኔ እየተሰቃየ ነዉ እያሉ ለሚጨሁለት ህዝብ ከጩኸት ያለፈ ግብር ማሳየት እና ነጻ ማዉጣት ካለባቸዉ ራሳቸዉን ከሙታን መድረክ ማስወገድ እና ሕይወት ባለዉ መድረክ ራሳቸዉን መክትት እና ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፣፣ ከብዙ ዓመት ትዝብት አና አታካራ የቀሰምኩት ልምድ እዚህ አገር ሆነን ሙታን ለሙታን የምንለዋወጥበት አታካራ ከፖለቲካ እይታ ስንመለከተዉ ሱስ ማብረጃ ካልሆነ ላገሪቱ የሚፈይደዉ እምብዛም እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፣፣ ሃይሉ ሻዉል ወደ ወያኔ አጎበደደ፣ ታዬ ወልደሰማያት ወያኔን “አንቺ” ሲላት የነበረ “የወያኔ መንግሥት” ማለት ጀመረ እያሉ በቃላት ስንጠቃ የሚጫወቱ “የፖለቲካ ዶንቆሮች” እና ያድማስ ባሻገር “በላይ ዘለቀዎች” ወደ መቃብሩ ወርዶ አፈር ሊለብስ ተቃርቦ የነበረዉ መዐሕድን ወደ ሕብረ-ብሔራዊነት ተሸጋግሮ ብዙ መሰናክሎችን አልፎ መኢአድን “ቅንጅት” አሰኝቶ ኣኢላፍ ተከታዬችን አፍርቶ ሕዝብን ያንቀሳቀሰዉ መሪ ሃይሉ ሻዉልና አባይነህ ብርሃኑ እንጂ የቁም ሙታኖች በተጠለሉባቸዉ ክፍለ ዓለማት ጥርሳቸዉን እየፋቁ በድምጽ ማጉያ ራዲዬኖች እና በየንተረኔት ሰሌዳዎች ስለ ሃይሉ ማንነት እና ስለ ታየ ወልደሰማያት ማንነት ማብለጥለጥ “በደረቀ ወንዝ መሻገር የሚቀናቸዉ ተቃወሚዎች” የሚያሰሙት ሃሳዊ መሲህ ሁሉ፣ የሃይሉን የታየን እና የአባይነህን ያክል አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፣፣ ታየ ወያኔን “አንቺ” እያለ በአንሰት ቃል መጥራት የጀመረዉ ዲሲ ማይክሮፎን አፍ ዉስጥ ተጠግቶ ሳይሆን እዛዉ ወያኔ ባለበት አገር አዲስ አባባ ከተማ ነዉ! ታየ እዚህ ሙታኖች በሚኖሩበት ዓለም ወያኔን “መንግሥት” ብሎ ቢጠራዉ/ቢጠራት እኔም ጥያቄ አለኝ! ታየ “ወያኔን” “መንግሥት” ብሎ በክበር ጠራዉ እያሉ የሚመጻደቁት እንማን ናቸዉ? ወያኔን መንግሥት ብለን አንጠራዉም ሲሉን ከማህደራቸዉ ፈልገን ፣ወያኔን “መንግሥት” እያሉ የተጣሩበት ምላሳቸዉን አያገኙትም ብለዉን ይሆን? መንግስት ማለት ክብር አይደለም፣፣ ስልጣን ነዉ፣፣ ህዝብንና አገርን በኒኩልየር ቦምብ፣በርዝ፣ በአይሮፕላን መድፎች ህጻናት እና አዛዉንት እመቻት እና እርጉዞች በሚኖሩባቸዉ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባቸዉ ከተሞችን እየደበደቡ በሰዉ ልጆች ላይ ግፍ የፈጸሙ እና ዛሬም እየፈጸሙ ያሉት እንደነ አሜሪካ፣ ከጃፓን፣ ቻይና…..በመንግስትነት ከተጠሩ እ ወያኔዎችም ቢሆን “መንግሰት’ ቢባሉ “መንግሰት” ምን ማለት ነዉ? እነኚህ ፖለቲከኞች ወደ ሃገር ቤት ዘልቀዉ ወያኔን አንቺ ብሎ መጥራትስ ይቅር እና ለአምስት ዓመታት በጨለማ እስርቤት መንገላታት ይቅር እና ወያኔ አዲስ አባባ ደረሰ ሲባል ወደ ኬንያ እና ጅቡቲ ያቀኑት የዛሬዎቹ ያድማስ ባሻገር “በላይ ዘለቀዎቻችን” ምን ስለሆኑ ነዉ? ወያኔ ሲገባ የሸሹ ሸሺዎች አገሪቷን ለማን ጥለዉ ነብረ የሄዱት? ለታየ! ታየ እንዲሞትላቸዉ? እንዲታሰርላቸዉ? ታሰረላቸዉኮ! ሞተላቸዉ እኮ! ተንገላታላቸዉ እኮ! ምንድር ነዉ ነገሩ! አንተ ታሰር እኛ ከሩቅ ዓለም ሆነን ጥርሳችን ጥዋት ጥዋት በመፋቂያ እያሳመርን አንጮህልሃለን ሲሉ ምን እሚሉት ኢትዬጵያዊ ሞራል ነዉ? አስፈታንህ ብሎ መመጻደቅስ ምን እሚሉት ወረዳነት ነዉ? ራሱን ማስፈታት ያልቻለ የቁም ሙት ሃላፊነቱን ለመወጣት በተንገላታ ሰዉ ላይ አስፈታንህ ብሎ መመጻደቅ ብልግናቸዉ አልዘለለም? ወያኔ ሲገባ አገሩቷን እንደፈለገቺዉ ትሁን እኔ ብቻ እግሬን ላዉጣ ብሎ የሸሸ ክፍል ሁሉ በምን ሞራሉ ነዉ፣ ማን እየተንገዳገደ እዛዉ አገር ቆሞ ባቆየለት አገር እና ፖለቲካ ሆኖ ነዉ የተነገላቱት ሰዎች አስፈታናችሁ እያለ መመጻደቅ የጀመሩት? ሃይሉ ሻዉል ከዉጭ በማስመጣት “መዐሕድ” ወደ ሃጋረዊ ድርጅት ለማሸጋገር በድብቅ እና በይፋ የሚሰራ ቡድን በማዋቀር ጊዜዉም ሲደርስ ሁለቱን በማገናኘት የካሄደዉ የሰከነ የስልት ተግባር የመሪዉን ብልህነት ያረጋገጠ ማን ነበር፣፣ዛሬም በድጋሚ አረጋግጣል!ይረጋገጣልም!ባይሳካም ያድማስ ባሻገር “በላይ ዘለቀዎች” ጥፋት እንጂ የሃይሉ ብቻ ሊሆን አይችልም፣፣ እንዴት ተኩኖ ሊሆን ይችላል? ለመሆኑ እነ አባይነህ እና እነ ዶከተር ታየ ሕዝብን ሲያደራጁ የተቻላቸዉን ሲሰሩ እና ሲንገላቱ ዛሬ ዉጭ አገር ከሞኖሩ ከሸሺዎቹ ጋር የተለየ አገርና ሃላፊነት ነበራቸዉ? ለመሆኑ ቤቱን ጥሉ የሸሸ ሰዉ ቤቴን እያፈረስክልኝ ነዉ የማለት መብት አለዉ? መብትስ ቢኖረዉ? እኔን ከመዝለፍ ወደዚህ ና እና ቤትክን እንዳይፈርስብህ በገዛ ራስህ ተከላከል ተብሎ “አሻፈረኝ” ላለ ባለቤት ማንን ነዉ መጀመርያ በሃላፊነት መዉቀስ ያለበት? የገዛ ራሱን ነዋ! ለመሆኑ እነዚህ ገንዘብ እንስጣችሁ እና ስለ እኛ ተሰዉልን የሚሉት “የፖለቲካ ታጁሮች” የሚፈሩት አምላክ አላቸዉ? አይመስለኝም፣፣ “የፍጥረት ሁሉ ተጠሪ አንድ አይደለም ፈጣሪ” ብሏል አንድ “አጋር” የተባለ ገጣሚ፣፣ እንዴ- ፈጣሪን ፍሩ እንጂ! ላስነብባችሁ፣፣ የፍጥረት ሁሉ ተጠሪ አንድ አይመስለኝም ፈጣሪ ፍጡራን ሁሉ እንዳቅማቸዉ አንድ አምላክ አላቸዉ፣፣ ለያንዳንዱ በነፍስ ወከፍ ምንም ሳያጎድል፣ ምንም ሳያተርፍ ፍጡር ሁሉ አምላክ አለዉ አካል በአምሳሉ የፈጠረዉ፣፣ በየፍጥረት ሁሉ ተጠሪ በእዉነት ነዉ በእዉነት አንድ አይመስለኝም ፈጣሪ ሰማይ እና ምድር,,,, እሳትና ዉሃ፣ ሀብታምና ድሃ ሌባና ነባይ ሟችና ገዳይ ሁሉም አምላክ አለዉ እሱን የሚያህለዉ እሱን የሚመስለዉ፣፣ የሌባ አምላክ ቀመኛን የሃሰት አምላክ ሽፍጠኛን ፈጠረ እንጂ ተጠንቅቆ ባሕሪ ግበሩን ጠብቆ የማንም አምላክ አላበደም የማይመስለዉን አልፈጠረም፣፣ በእዉነት ነዉ በእዉነት…. የፍጥረት ሁሉ ተጠሪ አንድ አይመስለኝም ፈጣሪ፣፣ ከነፍሱ ነፍስ ነስቶ ከባሕሪዉ ዉሃ ቀድቶ፣ በአካል በአምሳሉ የፈጠረዉ፣ ፍጥረት ሁሉ ለየራሱ አምላለክ አለዉ፣፣ የፍጥረት ሁሉ ተጠሪ በእዉነት አንድ ነዉ ፈጣሪ? (አጋር ጦቢያ ቁጥር 3- 1992 ከቋንቋ ቃና ገጽ 34) ጌታቸዉ ረዳ Devcember 7, 2009 (በፈረንጅ አቆጣጠር) www.Ethiopiansemay.blogspot.com