Friday, April 24, 2009

አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን (ላድርባይ የኪነት ሰዎችና፤ ለገዢዉ ቡድን ብርጭቆ አጣቢ ምሁራን) ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/ ለዛሬ የማስተናግዳችሁ ከላይ የተመለከተዉ ርዕስ የተገኘዉ ከሶፎንያስ ነዉ። ሶፎኒያስ እና ቀርሜሎስ “አቢሲኒያ”-በመባል የሚታወቀዉ የአማርኛ የግል- መጽሔት ታዋቂ አምደኞች የነበሩ ናቸዉ። እንደ ዱሮዉ ብዙ ባይሆኑም ዛሬም አንዳንድ የፖለቲካ መበለቶች ከየአቅጣጫዉ ብቅ እያሉ “ኣለና!” በማለት የጫካ ፋሽስት-ቡድን አወዳሽ ሆነዉ ስመለከት የሲፎኒያስ ትችቶችን ትዝ አሉኝና፣ “የሚረግጥ ሲመጣ- የሚረገጥ ገላ አለን ብለዉ ለሚመጣዉ ሁሉ ገላቸዉን የሚያስረግጡ ” ለትግራይ ጠባብ ብሄረተኛ የፋሺስት መንጋዎችን በማገልገል ላይ የሚገኙ የኪነት ባለሞያዎች፤የመገናኛ ብዙሃን አለቅላቂዎች፤ የፖለቲካ አጋፋሪዎች እና አልባሌ ሰዎች በጥቅሉ “ከርሳሞችና ሃሳዊ መሲሃን ክፍሎችን” በሰላ ብዕሩ “አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን”-በማለት ሶፎንያስ የሰመረበትን ላስነብባችሁ ፈለግሁ። ረዢሙ ሐተታዉ አሳጥሬዋለሁ። እንዲህ ይላል።በ ሦስት አመላካች ጥቅሶቹን ልጀምር ። “በአደባባይ ድፍረትን ሰብከዉ በጓሮ በኩል በፍርሃት የሚሾልኩ ፍርሃትንና ተቻችለን እንገዛ ቃላቸዉን እየረጩ የወያኔ ኢሕ አዴግ ባለስልጣናት አረቄ መሸጫ ቤት ዉስጥ ጠርሙስ መደርደሪያዉ ሥር ተቀምጠዉ ለባለስልጣናት የእንገዛ መጠጥ የሚያንቆረቁሩ ወገኖች እንዳሉ ታስታዉሳላችሁ?” “የገዢዉ ቡድን ጥርሱን ከገለጠላቸዉ ሌላዉ የእንባ ጅረት ሰርቶ በችግሩ ቢዋኙ የቁም ሙታን ናቸዉና ሃዘን አይታይባቸዉም።” “የእንሰሳ ባሕሪ ያላቸዉ ስለሆኑ ሲያባርሩት ተቅለስልሶ እንደሚመለስ ዉሻ ወደ አባረሩአቸዉ ጎብጠዉ እየተመለሱ በሌሎች ወገናቸዉ ላይ ሞት ለማወጅ ቀና የሚሉ ወገኖቻችን ዛሬም ይታያሉ” ለመሆኑ ተቻችለን “እንገዛ”-የሚሉን እነኚህ የወያኔ የፋሽስት ብርጭቆ አጣቢዎች፣ ሳይሞቱ የቁም ሞታቸዉ መሞት የጀመሩት መቸ ነዉ? መልሱ ከሲፎኒያስ ትችት- እነሆ ። “ከአባታችን አዳም ከእናታችን ሔዋን አፈጣጠር ጀምሮ እንሰሳም አራዊትም ተንቀሳቃሽ ነፍሳትም ዉሃ እየተመገበ አፈር እየላሰ አድጎ ፍሬዉን የሚያበላን አትክልትም በሞት መስፈሪያ እየተለኩ ሞትን የቀመሱት ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ነዉ?የሚል ጥያቄ ለመጠየቅ አስቤ ነበር። ነገር ግን አንትሮፖለጂስቶች ቀድመዉኝ ፈጣን መልስ ስለሚሰጡኝ ጥያቄዉን ለመጠየቅ ዉስጤ ሳይፈቅድ ቀረ።ለምን ቢሉ የሞት አመጣጥ የተፈጥሮ ሕግ ናዉና ጠየቅኩም አልጠየቅኩም ስለ አጀማመሩ አወክዩም አላወኩም ዉስጤን የሚለዉጠዉ ፋይዳ አይኖርምና ከንቱ ድካም ስለሚሆንብኝ ትቸዋለሁ። እኔን የሚያሳስበኝ አድርባዮች ሆዳቸዉን ከሕሊናቸዉ አርቀዉ በሆዳቸዉ ህሊናቸዉን ለዉጠዉ መቸ መሞት እንደጀመሩ ከማወቁ ላይ ነዉ። ሳይሞቱ የሞቱ ተብለዉ አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን መሆናቸዉ የቁም ሞታቸዉን የጀመሩት መቼ ነዉ? የቁም ሞታቸዉን ለማወቅ አለመቻሌ ነዉ። ዉስጤ ዉስጤን ስለጠየቀዉ የኔ ዉስጥ ይህን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ ስነ ስብ አፈጣጠር ተመራማሪዎች ሞት ዘዉዱን ጭኖ በፍጡራን ሕይወት ላይ ሞት በቃ እየተፈረደ መግደል የጀመረበትን ጊዜ እንዲነግሩኝ ሳይሆን አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን የሚባሉ እንደሰዉ ተፈጥረዉ እንደ እንሰሳ ማሰብ የጀመሩት መቸ ነዉ? በዚህ ዓይነት አሟሟት ጀምሮ ሞትን ለመሞት በሰልፍ መሰመር ላይ እንደቆሙ የሚያዉቁት ካለ እንዲነግሩኝ አበክሬ እጠይቃለሁ። የሞት መሃከለኛ መንገዱን ሄዶ ከመጨረሻ ግቡ ለመድረስ በእኔ እስኪመጣ ድረስ ሞትን በሌሎች ስለማየዉ የሞት ጨካኝነትና አገዳደሉን መናገር አያስቸግረኝም፡፡ ከሗላየ ተነስተዉ ከፊቴ በመቅደም የሞታቸዉን መጨረሻ ያየሁላቸዉ ሞትን የሞቱ ወገኖቼ በከርሰ መቃብር ዉስጥ አፈር ስለሆኑ ስለ አሟሟታቸዉ አሁን ላነሳ አልፈልግም:። ስለዚህም ክፉዉን የሞት አሟሟት መግለጫ መስጠት ጉንጭ አልፋ ስለሚሆን አፈር ስላልተመለሰባቸዉ ሙታን የምገልጸዉን እንድትሰሙኝ በመግለጫ ወንበሬ አጠገብ እንድትሆኑ ወንበሬ ጠባብ አይደለምና ከጎኔ ተቀምጣችሁ የሞትን ወግ እንድትከታተሉ እጋብዛችሗለሁ። አፈር ያልተመለሰባቸዉ ግን የሞቱ የሚመስሉ ስላሉ ተመራማሪዎቹ መልስ እስኩሰጡኝ ድረስ የራሴን ገለጻ እቀጥላለሁ። በቤታቸዉ ጎጆ ሻማ ለኩሰዉ በሻማዉ ብርሃን የሞት ጉድጓዳቸዉን ጨለማ በምናባቸዉ እያሰቡ ነብሴን በገነት አኑራት በማለት ለፈጣሪ ማመልከቻ የሚያቀርቡ ወገኖች እንዳሉ አዉቃለሁ።ከማመልከቻቸዉም በሗላ ወደ ዉጭ ወጥተዉ ጨረቃን ተመልክተዉ የሚመለሱ በሕይወት መኖራቸዉን የጭንቀት ጡጦ በማጥባት ፍርሃትን ለማሳደግ የሚተጉ እንዳሉ አዉቃለሁ። ቀን ከሰዉ ጋር ተደባልቀዉ በፍርሃት ላይ ይፎክራሉ። ደፋር ለመምሰልም ጠንካራ ገደል እንኳን ቢያገኙ ገደሉን ንደዉ ሜዳ ሊያደርጉት እንደሚችሉ የጉብዝና ዲስኩር ያሰማሉ።ጀግና ቆሞ እንዳይራመድ ባላወቁት ድፍረት ዉስጥ ተሰግስገዉ ፈሪ በመቀፍቀፍ ጀግናን በወሬ እያራዱ ተራማጅ እግሩንና ጣጣር ክንዱን መድሃኒት እንደጠፋለት በሽታ ደካማ ለማድረግ የማስመሰል ምሽግ ሲያመቻቹ የሚዉሉ አሉ። ኢትዮጵያ በብዙ መመዘኛ ጀግና እንደነበራትና ሁሉ ባልተፈለገ ዉዳቂ ሚዛን ፈሪ ቀፍቅፋ እያስመዘነች መቀመጣን እየተመለከትን ነዉ። እነዚህ የፍርሃት መርገምት ሆነዉ በዋሉበት እያደሩ ዉሸትን ሲኮተኩቱ የሚያነጉ የዉሸት አዋቂዎች በሃገራችን በዝተዉ እንደሚገኙ መመስከር እንችላለን። ሌሎቹም እንዲሁ ምናቸዉ ምናቸዉም ሆድና ጉሮሮረ ብቻ የሆኖባቸዉ ወገኖችም አሉ። የሞቱ-“ግን”ያሉ የሚመስሉ አፈር ያሸተቱ እንጂ አፈር ያልቀመሱ የትዉልድ በሽተኞች ሃገራችን እንደፈጠረች ማወቅ ይገባናል። የሚረግጥ ሲመጣ የሚረገጥ ምቹ ገላ አላቸዉ። ክብርን የሚገፍ ሲነሳ ራቁታቸዉን ሆነዉ ድሮም ራቁታችንን ነዉ የተፈጠርነዉ በማለት በራቁትነት መፈጠራቸዉን ዋቢ አደርገዉ አካላችን የክብር ልብስ ለብሶ ስለማያዉቅ ከኛ የሚገፈፍ ክብር የለም ብለዉ ሁሉም ሰዉ ራቁቱን መፈጠሩን መጀመሪያ ይወቅ ብለዉ በገዢዎች ትናግ ዉርደትን ያንቋርራሉ። እነዚህ አስተሳሰባቸዉ ደራሲ ከበደ ሚካኤል የፈጠሩት አዝማሪ ዓይነት ይመስሉኛል”” አዝማሪዉ መንገዱን ሲሄድ ወራጅ ዉሃ ካለበት ወንዝ ይደርሳል። ካሁን አሁን ዉሃዉ ይጎድልልኛል ብሎ ቢጠብቅ ዉሃዉ ሳይጎድል ይቀራል። አስኪ በዜማ ላባብለዉ ይልና ግጥም እየደረደረ ማሲንቆ እየገዘገዘ የወንዙን መጉደል ቢጠብቅ የሰማዉ እየሄደ ያልሰማዉ ይመጣል እንጂ ዉሃዉ አልጎደለለትም። ያዝማሪዉ ሁኔታ ያየ ሰዉ ጠጋ ብሎ እንዲህ አለዉ “ ወዳጄ ስራህ ከንቱ ሆነብኝ፤ግጥምህም ከማያፈራ ጭንጫ ላይ የወደቀ በር መሰለኝ፤ዜማህም ወራጁ ዉሃ አላጎደለዉም፤ማሲንቆህ ይጮሃል እንጂ ዉሃዉን አላሰማም፤ያልሰማዉ መጥቶ ሰምቶ ይሄዳል። ያለ አዋቂ ዜማ ስታዜም ከሚመሽብህ ሌላ መንገድ ይሻላል” አለዉ። በዘመናችን የሚገኙ አንዳንድ ወገኖች በዘመናቸዉ የዕድሜ ጅረት ለሂያጁና ለመጪዉ ሲዘፍኑ ሲቀኙ ዘመን መጥቶ የሄደባቸዉን እስኪያስታዉሱ ለመጣዉ እያጎነበሱ ጥሏቸዉ ሲሄድ በአዲስ መጪ እየተደቆሱ ዘመን የባጀባቸዉንስ እናዉቃለን?በቤትም በጎረቤትም፤በደጅም፤በሩቅ ስፍራም አሉና እነሱንም ማስታወስ ይገባል። ላዲስ መጪዎች አዲስ ቅኝት የምስጋና ክራር የሚያከሩ ዘፋኞች ትላልንት ሞተን ነበር፤ ዛሬ ግን ለሰዉ ልጅ ፍትህና ሰላም ተማጓች በማግኘታችን ከሞት ተነሳን ብለዉ ማሲንቆ የሚገዘግዙ “የነፋስ መጋዞች” አታዉቁም? አንዱ ገጣሚ ከሌላዉ ተቀኝ፤አንዱ አድር ባይ ከሌላዉ አጎንበሽ ለመብለጥ እየተወዳደሩ ከሄደዉ ሳይማሩ ለሚመጣዉ የዉርደታቸዉን ሰርትፊኬት በማሳየት እንደ ወደዳችሁ ግዙን እንደወደዳችሁም አስሰሩን። በወደዳችሁትም የስራ መስክ ቅጠሩን እናገልግላችሁ ብለዉ በወገናቸዉ መሰቃየት ለመኖር ብቻ የዉርደት ዲግሪያቸዉን ለገዢዉ መደብ አቅርበዉ ከዉርደት ድንኳን ስር የሚገኙ ወገኖች አታወቁም?ምኞት አስክሯቸዉ በነሱ የምኞት አረቄ ጤናማዉ ሰዉ ሰክሮ እንዲዋሃዳቸዉ የሚጎተጉቱ የገዢ ቡድን ብርጭቆ አጣቢዎችስ አላያችሁም? በአደባባይ ድፍረትን ሰብከዉ በጓሮ በኩል በፍርሃት የሚሾልኩ ፍርሃትንና ተቻችለን እንገዛ ቃላቸዉን እየረጩ የወያኔ ኢሕአዴግ ባለስልጣናት አረቄ መሸጫ ቤት ዉስጥ ጠርሙስ መደርደሪያዉ ስር ተቀምጠዉ ለባለስልጣናት የእንገዛ መጠጥ የሚያንቆረቁሩ ወገኖች እንዳሉ ታስታዉሳላችሁ? ታሪክን ጊዜ ገልብጦት ታሪክ ጊዜ ሲያነሳዉ ለማየት የታሪክ ምክንያት ሊሆዩ የሚችሉ ወገኖች በጊዜ መጋረጃ ተሸፍነዉ የችግራቸዉን ዉስጥ እንዳናይ በዉጭዉ እይታችን ላይ አስፈሪዉን የትሞታላችሁ ጨረር እየወረወሩብን ሁላችን የዓይናችንን ለማሳወር ድፍረት በሚሉት መድሃኒት ላይ ዋጋ ይሰቅሉብናል። የገዢዉን ቡድን እኩይ ሥራ እንዳንመለከት ሁላችንም ዕዉራን ተብለን እኛም እንደነሱ አፈር ያልተመለሰብን ሙታን እንድንባል በገዢዉ ጠመንጃ ጉልበት ወደ ጨለማዉ ያስጠጉናል። እነሱ ስለጠገቡ በሌላ ዘንድ ረሃብ አለ ብለዉ አያምኑም። የገዢዉ ቡድን ጥርሱን ከገለጠላቸዉ ሌላዉ የእንባ ጅረት ሰርቶ በችግሩ ቢዋኙ የቁም ሙታን ናቸዉና ሃዘን አይታይባቸዉም። ከ አድርባይ ቡድናቸዉ ተሰላፊ እንዱ ቢዋረድ እነሱ መሽቶ እስኪነጋ በጥጋብ ይዘላሉ እንጂ ነግ በእኛም የሚል ሰዋዊ አስተዉሎት አይመጣላቸዉም። እንዲህ መሰል የእንሰሳ ባሕሪ ያላቸዉ ሶዎች ስለሆኑ ሲያባርሩት ተቅለስልሶ እንደሚመለስ ዉሻ ወደ አባረሩአቸዉ ጎብጠዉ እየተመለሱ በሌሎች ወገናቸዉ ላይ ሞት ለማወጅ ቀና የሚሉ ወገኖቻችን ዛሬም ይታያሉ።ከነዚህ በተጓዳኝ የትም ዉለዉ የትም ቢያመሹ ሆዳቸዉን እንኳ ለማሸነፍ የማይቸገሩ ፕሮፌሰሮች፤ዶክተሮች ከእዉቀት አልባ ቡድኖች ጋር ገጥመዉ ቀና ሰዎችን ጥለዉ ለማለፍ የአድርባይነት ተጠባባቂ ተጫዋች በመሆን በተቀያሪነት ለመለወጥ በየቢሮአቸዉ መሽገዉ የአሰልጣኝ ድምጽ የሚጠባበቁ አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን አሉ። የወፍጮ እህል አስፈጪዎች፤ቧምቧ አቃኝዎች እንደጠመንጃ ጥይት ወገንን የሚያስፈሩ የጦር አባላቶች፣ እንኳን ዘፍነዉ ቢያለቅሱም እንኳ የምግብ መኖ የማያጡ ዘፋኞች፤ኳስ አባርረዉ ኳስ ለግተዉ በእግራቸዉ ገንዘብ ሊሰሩ የሚችሉ ስፖርተኞች ፣በሰዉ አስቀዉ በእነርሱም ተስቆ ህይወትን በሁለትዮሽ መግለጥ የሚችሉ የኪነ ጥበብ ሰዎች፤በማስመሰል ልቅ አድርባይነት ለገዢ መደብ አጎንብሰዉ የገዢ መደብ ጭቆና በዜጎች ላይ እንደ አረግራጊ ፍራሽ ሲያረገርጉበት የጥጋባቸዉ ክብደት ለማወቅ ሚዛን ፍለጋ ሽቅብ ቁልቁል ይላሉ። እንደ ሰጎን ያጎነበሱ እንደ ሰንበሌጥ የተኙ ወገኖች መቼ ነዉ ቀና ብለዉ አልሞትንም የሚሉት?ብለን በጥያቄ ሌላዉን እናስከትል -“ዓይናችን እያየ አታዩም የሚሉን፤ አናይም ስንላቸዉ ታያላችሁ ብለዉ የሚሞግቱን፤ችግራችንን እየተናገርን ‘የምትሉትን አንሰማም’የሚሉን የዘመኑ ገዢዎች መቸ ነዉ ከእዉነት ማማ ላይ ወጥተዉ የሚታዩት?እኛ እንደሆን የራሳችነን ጥላ እየሸሸን ባለንበት ወቅት የመንቀሳቀስ ነፃነት ሰጥተናችሗል ቢሉን የምናምናቹወ አለመሆናችንን ሊያዉቁልን ይገባል። ይህንን ሳያዉቁ ያልናቸዉን ይቀበላሉ በሚል ደነዝ አስተሳሰብ ሕሊናቸዉን አደንዝዘዉ ፍርሃት ለቀዉብን የደም ብዛት እንደያዘዉ በሽተኛ ግማሽ አካላችን በድን ሆኖ ክንዳችንን ሊያሳጥፉን መመከራቸዉ መቼ ነዉ የሚያቆሙት? ገዢዉን መደብ ጥያቄ ስናቀርብለት ለገዢዉ መደብ ወግ ነዉ የአህያ ተረት እየተረቱ በደመነፍስ የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችን አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙት መሆናቸዉን መቼ ነዉ የሚገነዘቡት? ገዢዎች ጠግበዉ በተራበ ጉልበት ላይ የጎሳ ጥበትን እያሰፉ እንደጋሪ ፈረስ እንድ አቅጣጫ (እሱም ድንቁርና ነዉ) እያሳዩን ለረሃብ ምጣድ ጀርባችንን ሰጥተን የተስፋ እንጀራ በላያችን ሲጋግሩ የምናስተዉል የዚች አገር ዜጎችስ መቼ ነዉ የጀርባችንን እሳት የምናጠፋዉ? እነዚህን አስተያየቶች ስናነሳ አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን አልሞትንም ይሉን ከሆነ በየፈርጁ ያስቀመጥናቸዉን መጠይቆች ልብ ብለዉ እንዲያጤኑ እንጋብዛቸዋለን?እኛም ጠያቂዎቹ የሕብረትንና የእምቢ ባይነትን፤ አድርባይነትን በሆድ አድሮ መኖር ክብር እንደሌለዉ አዉቀን የጠየቅናቸዉ ባይመልሱ እኛ ጠያቂዎቹ መልስ መስጠት ይገባናል። አስከዚያዉ መለስ የሚሰጥበት ጥያቄ ልጠይቅ አፈር ያልተመለሰባቸዉ ሙታን ርዕሴን አጠቃልየ እደመድማለሁ። 1- ገበያ ወጥቶ ዋጋ የማይጠይቅ ምንድነዉ? 2- በልቶ የማያመሰግን ማነዉ? 3- ያመረተዉ የማይበላስ ምንድነዉ? መልሱን በሚቀጥለዉ ይዤ አስክመለስ ድረስ- አስከዛዉ በየቤታችን፤በየማሕበራችን፤በየእድራችን ማንነታችንን ማንነትና ሀገራዊ እድገታችንን ወይንም ዉድቀታችንን እየተነጋገርን ካቀረቀርንበት “ድዉይ የመገዛት መንፈስ” መላቀቂያዉን እንፈልግ በማለት ሃሰቤን እገታለሁ”።//-/ http://www.ethiopianseemay.blogspot.com/