Saturday, December 4, 2021

ለሕግ የማይገዛ መሪ በሕግ የማይገዙ ፖሊሶችን ይንከባከባል ጌታቸው ረዳ ETHIO SEMAY 12/04/2021

 

 

ለሕግ የማይገዛ መሪ በሕግ የማይገዙ ፖሊሶችን ይንከባከባል

ጌታቸው ረዳ

ETHIO SEMAY

12/04/2021

የሰለጠኑ ሰዎች የሰው ልጅ ኑሮ ቀላል ለማድረግ በበሽታና በተፈጥሮ የሚከሰቱ የአካል ስቃዮችና መጣመሞችን ለማስወገድ የተሳካ በሚባል ግኝት በቂ ጥረት እያደረጉ ነው። ጠበብቶች አካላዊ ስቃይን በፍጥነት ለማስታገስ ብቻ ሳይሆን ያለጊዜው የሚከሰትን ሞት መቆጣጠርንም ችለዋል።በአንፃሩ አገራችን በተፈጥሮ የሚከሰቱ የሕመም ስቃዮችን የማስታገስ ፍላጎትን ተውትና በዜጎች ላይ “ስቃይና መከራ” የሚፈጥሩ “መሪዎችና ገራፊዎችን ” በመፍጠሩ ሂደት ዓለም በማስገረም ላይ እንገኛለን።

የለጠፍኩት የትግሬዎች የጅምላ ድብደባና እስር ስትመለከቱ እስከ አሁን ድረስ በድንጋይ ዘመን እንጂ በሰለጠነ ዘመን እየኖርን ያለን አይመስልም። በማህበራዊ እውቀት ላይ ያለን ጉድለት ዝቅተኛ በመሆኑ ስቃይን የሚያባብሱብንን መሪዎች የማሞገስ ክስተት ስመለከት እጅግ አዝናለሁ።

ብዙ ሰዎች በማሕበራዊ ድረገጾች በተለይ ፌስቡክ ላይ ፎቶግራፎቻቸውን የአብይ አሕመድ ፎቶ እንደ ራሳቸው መለያ በማድረግ ተክተው “በማምንታቸው ሳይሆን በመሪው ምስል ራሳቸውን በመቅረጽ” ሂደት የመገኘቱ ክሰተት ስመለከት ለ30 አመት የተጓዝንመብትን መከራ ነገም ቀጣይነት እንዳለው እንደ የሙቀት መለኪያው “ቴርሞሜትራችን” የማያጠራጥር አመላካች ሂደት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በቪዲዮው የምትመለከቱት ትግሬዎች በፋሺሰቱ ኦሮሙማ ሥርዓት እጅ ወድቀው ፖሊሶች ከሕግ በላይ በመሆን ተፈጥሮአዊና ዓለማዊን ሕግ በመጣስ አረመኔአዊ ድብደባ አቅም በሌላቸው ሴቶች ላይ ሳይቀር ሲፈጽሙ የሚያሳይ ማስረጃ ሳሳያችሁ፤ ለተደብዳቢዎቹ እንድታዝኑ ብየ ሳይሆን አገራችሁ ኢትዮጵያ የፈረሰች አገር መሆንዋን ለማሳየት ነው።

ይህን ጭካኔ እየተፈጸመ ትግራይ ኢትዮጵያ አካል ሆና ትቀጥላለች ብላችሁ የምትመኙ ሰዎች ካላችሁ ፤ እንደ እኔው እርማችሁን ብታወጡና ከዚያስ እንዴት እንደምትኖሩ ብትቀይሱ ካሁኑኑ ለመንገር ነው። ያለቀ ነገር መሆኑን ነው እየነገርኳችሁ ያለሁት። ውጭ አገር የምትኖሩ “ፌዝ” ነው ብላችሁ ብትቀልዱ ስለማትኖሩበት የሚጠበቅ ነው። እዛው መሬት ላይ ለሚኖር ግን መጪው “ጭለማ” ነው።

ትግራይ ተገንጥላ ትኑር እያልኩ ሳይሆን እውነታው ግን “እኔ ለኢትዮጵያ ከምመኝላት በተጻራሪ የሚያሳይ ክስተት በመከሰቱ ነው። አብይ ጦር ሜዳ ሄዶ በሄልኮፕተር እየተመላለሰ ይህንን ተራራ አስለቀቀ ተብሎ የሚጨፈርበት ጭፈራ ወራሪው ወያኔ ከያዛቸው አማራዊና አፋራዊ “ክልልሎች” ማስወጣት የሚያበስር እንጂ ትግራይን ወደ ኢትዮጵያዊነትዋ የሚያስቆይ” ብስራት አይደለም። አስቀድማችሁ እንድትረዱት ነው እያስጠነቀቅኳቸሁ ያለሁት።

በቪዲዮው ላይ የምታዩት ሥራ አብይ አሕመድና ተከታዮቹ ትግራይ እንድትገነጠል በአዋጅ የደነገጉት ሴራ ስለሆነ፤አብይ የጦር ልብስ ለብሶ በሄሊኮፕተር እየተመላለሰ “ይህንን ተራራ ዛሬ ነገ ደግሞ ያኛው ተራራ ነጻ አውጣለሁ” እያለ የተክለሰውነት ቀረጻውን ተቀብላቸሁ ጭፈራችሁን ማቅለጥ መብታችሁ ቢሆንም “ስሜታችሁ” በልክ ካላደረጋችሁት፤ ትግራይ ሕዝብ ለማሳመን የማይቻልበት ክስተት ውስጥ ስለገባን (ቪዲዮውን ተመልከቱት ደጋግማችሁ) ትግሬዎች በሚወስዱት የግንጣላ እርምጃ ስትመለከቱ “እንዴት ሊሆን ይችላል” ብላችሁ እንዳትገረሙ በሚል ነው።

 አገር ሲፈርስ ቀስ በቀስ ነው።ሙታኖች ዳግም ትንሳኤ እንደማይኖራቸው ሁሉ አገር ከፈረሰም ዳግም ለመስራት አይቻልም። ሃቁን ስለነገርኳችሁ ልትጠሉኝ ልትሰድቡኝ ትችላላችሁ። ያ ለኔ ምንም ማለት አይደለም። ይልቁኑ ይህ ሕግ የጣሰ የኢንተርሃሙዌ ጌስታፖዎች አረመኔአዊ ድብደባና የጅምላ እስር እንዴት እንደምታስቆሙት ብታተኩሩ የሚሻል ይመስለኛል።

እምሮውን ዘግቶ በአይኑ ብቻ የሚያይ በርካታ ማሕበረሰብ እዚህ ፌስቡክ ላይ ስመለከት የማውቃት አገሬ ኢትዮጵያ እንደማትኖር ሳስበው እምባ ይተናነቀኛል።

Tigrayans are beaten harassed and arrested by Abiy Ahmed security forces for their identity as Tigra

https://youtu.be/b0Cr8NqJkSI

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ  ETHIO SEMAY