Sunday, May 15, 2022

በጫካ እንዋጋ? ወይስ በዤኔቭ እንሟገት? ክፍል 2 መልስ ለመምህርት መስከረም አበራ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 5/15/2022 (ግንቦት 2015ዓ.ም)

 

በጫካ እንዋጋ? ወይስ በዤኔቭ እንሟገት?

ክፍል 2 መልስ ለመምህርት መስከረም አበራ

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

5/15/2022 (ግንቦት 2015ዓ.ም)

ባለፈው ክፍል 1 መልስ ለመምህርት መስከረም አበራ ለጀኔራል አበባው ታደሰ ያሁኑኑ መንግሥታዊ አካሄድና ሰውየው እየተከተለው ያለው የተሳሳተ አካሄድ በማስመልከት ስለጻፈቺለት ግለጽ ድብዳቤ አስመልክቶ ከዚያው ደብዳቤ በማያያዝ ስለ ቀዳማዊ ኃይለለስላሴ ከማይጨው መሸሽ የተቸቻው አላግባብ ትችት መልስ ሰጥቻለሁ።

ለብዙ አመታት የተደረገባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻ ዛሬም እንደ መምህርት መስከረም አበራ የመሳሰሉ ወጣት ምሁራን እየተደገመ በንጉሡ ላይ የተደረገው አልግባብ የስም ማጥፋት የተደረገባቸው ዘመቻ እርስዋም ስትሰማ የደገቺበትን ዘመነ ወያኔ የስም ማጥፋት ዘመቻ እና በዛው በንጉሡ ዘመን ተገጠመ ብላ የተገጠመላቸው የአንድ ስም አጥፊ ገጣሚ (ያውም ስብሰባው እና ውሳኔው ላይ ያልነበሩ ገጣሚ) የገጠሙባቸውን እውነት መስሏት ግጥሙን በመድገም በመተቸትዋ፤ ትችትዋን ለመቃወም በዚህ ክፍል ሁለት መልሴ ውስጥ በወቅቱ የነበሩ የአገሪቱ ታላላቅ  የጦር አለቆችና ሹማምንቶች በሹማንቶቹ የሓሳብ ግፊት ተገድደው ወደ ውጭ አገር እንዲሄዱና ለዓለም መንግሥታት ስለ መርዛማው የአውሮፕላን ጥቃት በማጋለጥ እንዲያመለክቱ ተገፋፍተው እንዲሄዱ የተደረገው ውሳኔ መሆኑን ዛሬ በዚህ ክፍል ሁለት መልሴ ለየት ያለ ንጉሡ እምቢ ያሉበትን በላ በግፊት የተቀበሉትን እሺታቸውን እና የሹማምንቱ ሙግት በማስረጃ “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግሥት” ዘወዴ ረታ (2012 በፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር) የታተመ መጽሐፍ በጻፉት ሰነድ ከገጽ 251 ጀምሮ ያለውን እንመልከት።

“በጫካ እንዋጋ? ወይስ በዤኔቭ እንሟገት?” የሚለው ርዕስ በንጉሡ እና በሹማምንቱ መካከል የተደረገውን ክርክር እነሆ እንዲህ ሲሉ ዘግበውታል፡

“እንደ ኢ/አቆ ሚያዚያ 22 ቀን 1928 ዓ.ም  ንጉሠ ነገሥቱ ከዘመቻው ተመልሰው አዲስ አበባ በገቡበት ዕለት፤ ለእንግዲህ ወዲህ ለነፃነት የሚደረገው ትግል በምን መልክ መሆን እንዳለበት ተነጋግሮ ለመወሰን በታላቁ ቤተመንግሥት እልፍኝ አዳራሽ ከፍተኛ ጉባኤ ተደርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ተካፋይ ሆነው የነበሩ ወደ 43 የሚሆኑ  ታላላቅ መኳንንትና የጦር አለቆች፤ሹማምንትና የቤተመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፤በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አባባ ቆይተው አንዳንድ ከፍተኛ የሃኃላፊነት ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩት ባለሥልጣኖች ናቸው። በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲመክርባቸው የቀረቡት ዋና ዋናዎቹ ሓሳቦች፡

                   (1ኛ)- ከእንግዲህ ወዲህ ሦስት ቀናት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የጠላት ጦር መናገሻ ከተማውን እንደሚይዝ ስለታወቀ            

                          የመንግሥት መምሪያ ከአዲስ አበባ ወደ ጎሬ የሚዛወርበትን

                  (2ኛ)- በሁለት ግምባር ጦር ማዘጋጀትና የመጀመሪያው በበረሀና በጣርማ በር በኩል ሁለተኛው በአህያ ፈጅና አፋፍ በኩል ተመድበው ጠላትን ለመውጋት እንዲችሉ የሚደረግበትን፤

                  (3ኛ)- በሁለት ግምባር ውጊያ ለመክፈት በቂ ጦርና ሠራዊት ለማግኘት ካልተቻለ፤ትግሉ በጫካ በሽፍትነት መልክ  የሚከናወንበትን፤

                   (4ኛ)- የዓለም መንግሥታት ማህበር ምንም እንኳ እስከዛሬ ድረስ የቃል ድጋፍና ፍርድ ከመስጠት በስተቀር ፤ የጠር ኃይል ዕርዳታ ነፍጎን የቆየ ቢሆንም፤ምናልባት ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ማህበሩ ሥራውን በሚመራበት ዤኔቭ ላይ ተገኝተው ከአምሳ በላይ ለሆኑት የመንግሥታት እንደራሴዎች ቢያመለክቱ፤ ጠቃሚ ነገር ለማግኘት የሚቻልበትን ንግግር ለመወሰን ነው።  

በእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አስተያየት እንዲሰጥባቸው በተጠየቀ ጊዜ የስብሰባው ተካፋዮች የሆኑት ሰዎች ቁጥራቸው ከመብዛቱ የተነሳ፤ለመደማመጥና ለፍሬ ነገሮች ማሠሪያ ለማግኘት ስለአስቸገረ፤ አንዳንዶችም እርምጃ ሳይወሰድ ጉኤባው ለማግሥቱ እንዲቀጥል ተወስኗል በሚል መግለጫ ተበተነ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከተካፈሉት አብዛኛዎቹ ከእልፍኝ አዳራሽ ወጥተው ወደየ ቤታቸው ከሄዱ ከጥቂት ጊዜ በላ በልዑል ራስ ካሳ አማካይነት 15 ባለሥልጣኖች ከመሳፍንት፤ ከመኳንንቱ ፤ከሚኒስትሮች፤ ከጦር አለቆች መካካል  እየተውጣጡ ከምሽቱ ከሁለት ሰዓት ጀምሮ ጃንሆይ በተገኙበት እራት እየተበላ እንድ የተለየ ስብሰባ እንዲካሄድ ተደረገ። በዚህ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በመሩት ጉባኤ ላይ ንግግር የተደረገባቸው ጉዳዮች ፤ ቀደም ሲል የተከናወነው የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ ከቀረቡት የተለዩ አልነበሩም። ልዩነታቸው ከተካፋዮቹ ቁጥር ማነስ የተነሣ በቀለጠፈ ውይይት መደረጉና፤ መጨረሻውም አስፈላጊው ውሳቤ መስጠቱ ነበር። በዚህ መሠረት፤

1-     እንግዲህ ወዲህ ጦር አሰባስቦ ጠላትን ፊት ለፊት ለመግጠም የሚያስችል መሣሪያም ሆነ በቂ ሠራዊት ስሌለ፤ ለነፃነት የሚደረገው ትግል በጫካ የሽምቅ ውጊያ በአርበኝነት ከማድረግ በስተቀር ሌላ አማራጭ መንገድ አሰለመኖሩን ሁሉም ተስማምተውበት በሙሉ ድምፅ ተወሰነ።

2-    ጠላት ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተቃረበ ስለሆነ፤ንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት መምሪያ ሳይውል ሳያድር ወደ ይልባቦር ጠቅላይ ግዛት ጎሬ ከተማ እንዲዛወር ተወሰነ። በዚህም ጊዜ ጎሬ ላይ ለሚካሄደው የመንግሥት አስተዳዳር ቢትወደድ ወልደጻድቅ ጎሹ፤ የቀዳማዊ  ኃይለስላሴ እንደራሴ ሆነው ተሾሙ።

3-   በመጨረሻው ብዙ የሓሳብ ልውውጥ የተደረገበት ትልቁ ጉዳይ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በዠኔቭ ሄደው የዓለም መንግሥታትን እርዳታ ቢጠይቁ ይጠቅማል ወይስ አይጠቀምም በሚለው ሓሳብ ላይ ነው። በዚህ ጉዳይ ሦስት ሰዎች በየተራ የገለጽዋቸው አስተያየቶች የሁሉንም ሓሳብ በማስተባባር ለውሳኔ ያመቻቸ ሆኖ ተገኘ።

ሀ/ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ (የሰላሌና የቤገምድር ገዥ)፤

“…….መቸም አገራችን ላይ ትልቅ አደጋ ወድቋል። ይህም አደጋ ነፃነታችንን የሚጋፍ ስለሆነ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ እስኪፈቅድልን ዕድሜ ድረስ፤ ያለማቋረጥ ተጋድሎ ማድረግ አለብን። የምናደርገውም  ተጋድሎ ሕይወታቸውንን በሚያሳጥር መንገድ ሳይሆን፤ነፃነታችንን እስከምናስመልስ ድረስ በተቻለ መጠን ራሳችንን እየጠበቅን መሆን አለበት። ማይጨው ዘመቻ ላይ ሆነን፤ ባሉን መሣሪያዎችና ባሉን ተዋጊዎች ጠላታችንን በሚገባ ማጥቃታችን አልቀረም ነበር። ጠላታችን ግን ፊት ለፊት ከመዋጋት ይልቅ በአይሮፕላን መርዝና እሳት በሕዝባችን ላይ መርጨትን እንደ ጀግንነት ሥራ አድርጎ ስለቆጠረው ልንቋቋመው በማንችለው መንገድ ሠራዊታችንን ጨረሰብን። በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ የበለጠ አደጋ ላይ እንደሚጥለን በማየት የተረፈውን ጦራችንን ወደኋላ እንዲያፈገፍግ አድርገን ለውጊያችን ዘዴ ብንፈልግለት ይሻላል በማለት ለጃንሆይ አመለከትናቸው። ጃንሆይ “ምቢ” አሉን። እምቢ ሲሉም እንዲሁም ለይስሙላ እምቢ ብለዋል ለመባል አልነበረም። በጉዳዩ አስበውበት ነው። ንጉሡም እንዲህ አሉን፤

“እኔ የመጣሁት ከጠላት ጋር ተዋግቼ ድል ለማድረግ ብቻ ሳይሆን መሸነፍንም መኖሩንም ሳልረሳ ነው። ስሸነፍም እስከ መጨረሻው ተዋግቼ ደሜን ለማፍሰስ ቆርጬ ስለሆነ፤የፈለገ ከእኔ ጋር ይሙት። ነፍሱን የወደደ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሶ ለመዳን ይሞክር።…”

ብለው ምቢታቸውን አጠነከሩብን:፡ በዚህ ጊዜ ሁላችንንም እጅግ አሳሰቡን። ቢቸግረን ሁላችንም አጥብቀን መለመኑን ቀጠልን፡

“ጃንሆይ! ሞትን እኮ ምንጊዜም ያገኙታል። እኛም የምንለምንዎ ሞትን በእግዚአብሔር እርዳታ እየዘገዩ ለአገርዎ ነፃነት የሚያደርጉትን ተጋድሎ እንዲቀጥሉ ነው አልናቸው።”

እግዚአብሔር ይመስገን! ልመናችንን ሰምተውልን ይኼው ዛሬ ከማይጨው እልቂት ድነን አዲስ አበባ ተመልሰን በጃንሆይ ዙሪያ ለመሰብሰብና ለዛሬውና ለነገው የምናደርገውን ተነጋግረን ለመወሰን ዕድል አግኝተናል።

አሁን ብዙ ቁም ነገሮችን ተወያይተን ከወሰንን በኋላ፤አንድ እልባት ሳናደርግለት የቆየነው ጉዳይ፤ጃንሆይ የዓለም ነገሥታት ባቋቋሙት ማህበር ቤት ተገኝተው በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን መከራ ቢያስረዱና ዕርዳታ ቢጠይቁ ይጠቅማል? ወይስ አይጠቅምም? በሚለው ሓሳብ ላይ ነው። እንደ እኔ እንደ እኔ ከሆነ፤ጃንሆይ ሄደው ቢያመለክቱ የሚበጅ ይሆናል። ዕድሉ ከቀናቸው፤ጠላታችንን የምንወጋበት ዕርዳታ አግኝተው ይመጡ ይሆናል። ካልሆነ ደግሞ፤ በሚያመቸው በአንደኛው ጠረፋችን በኩል ወደ አገራቸው ተመልሰው አርበኝነታቸውን ይቀጥሉበታል……” አሉ፤

 ቀጥለውም እነ

ለ/ ---- ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)

ሐ/……..አቶ መኰንን ሀብተ ወልድ (የንግድ ሚኒስትርና የፖስታ ቴሌፎን ሚኒስትር

        በተጠጠባባቂነት የሚመሩ)

የመሳሰሉ ባለሥልጣኖችና ጦር አዋጊዎች በየተራ እየተነሱ ጃንሆይን ወደ ውጭ አገር ወደ ዠኔቫ ሄደው ለተባበሩት መንግሥታት እንዲያመለክቱ ሲወተውትዋቸው ጃንሆይም ያንን ካደመጡ በኋላ የሚከተለውን ተናግረው ውሳኔ ሰጡ።

Ø “…. ሁላችሁም ለአገራችን ነፃነት የምትሰቃዩና መሥዋዕት ለመሆንም ወደ ኋላ የማትሉ ናችሁ። በዚህም አኳሃን የምታቀርቡልን ምክር ሁሉ እውነተኛውንና በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ዘንድ የሚከበረውን ስለሆነ ሙሉ ዕምነት እናሳድርበታን።  

Ø ራስ ካሣ በተናገርካቸው ብዙዎች በሆኑት ፍሬ ነገሮች ውስጥ፤ዠኔቭ ሄደን የምናቀርበው አቤቱታ አድማጭ ካጣ በአንደኛው ጠረፍ በኩል ወደ አገራችን ተሻግረን የአርበኝነት ተግባር ለመፈጸም ይቻላል ያልከው ከሐሳባችን ጋር የተገጣጠመ ሆኖ ስላገኘነው ደስ ብሎናል።

Ø ሕሩይ በተናገርከው ውስጥ፤ ለነፃነት መዋጋት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን፤በፖለቲካውም በፕሮፓጋንዳውም በኩል መሆን አለበት ያልከው የምንስማማበት መልካም አስተያየት ነው።

Ø መኰንን ሀብተውልድ የተናገርከው ከጠበቅነው በላይ ነው። ዠኔቭ ሄደን አቤቱታችንን የምናቀርብለት የመንግሥታት ማህበር ጠላታችንን ከአገራችን ለማስወጣት በጦር ሠራዊት ሆነ በመሣሪያ ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንደማይሰጠን ተስፋህን ቆርጠሃል። እንዳልከው፤ እኛም ይህንን ያህል እናገኛለን ብለን ተስፋ አላደረግንም።

Ø  ተክለ ሐዋርያት በዤኔቭ በመጨረሻ ቀኑ ስለተናገረው የጠቀስከው ማለፊያ ነው። መቸም እሱ በጠባዩ ጥሩ ነገር ሲሰራ አይናገርም። እኛ የሰማነው እሱ ነግሮን አይደለም።የሚያሳዝነው ይህንን የመሰለ ንግግር አድርጎ ከአዳራሽ ሲወጣ ከጓደኞቹ የመንግሥት እንደራሴዎች መካከል ያመሰገነውም ያደነቀውም አለመኖሩ ነው። ከዚህ ሌላ በተናገርከው ውስጥ ፈረንሳይ በሙሴ ሳቫል  መንግሥት ጉዳት ቢያደርስብንም እንግሊዝም ፊት ለፊት ተጋፍጦ ጠቃሚ ዕርዳታ ባይሰጠንም ከአሜሪካም የጠበቅነውን ባናገኝም የወደፊቷ ኢትዮጵያ በማሰብ፤ተስፋ መቁረጥ የለብንም። እነዚህ አገሮች ሁሉ ለዛሬው ባይሆኑንም ነገ ተመልሰው አገራችንን ሊጠቅሙ ይችሉ ይሆናል ብለን ማሰብ ይሻለናል። ዛሬ ያለንብት ሁኔታ በሞትና በሕይወት መካካል የሚያጣጥር ነው። የጦር መሣሪያ ባጠረን ጊዜ ሠራዊታችንም ተበታትኖ በተዳከመበት ሰዓት፤ ጥቂት ተዋጊዎች ይዘን ጠላትን እንመክታለን ብለን ብንነሣ፤በመጀመሪያ ሠላማዊውን የአዲስ አበባ ሕዝብ እናስጨርሳለን።  እኛም እናልቃለን፡ ስለዚህ መንግሥታችን ወደ ጎሬ (ይልባቦር) ተዛውሮ በቢትወደድ ወልደጻድቅ ጎሹ እየተመራ እንዲቆይና፤ እንዳላችሁት እኛም ለዓለም መንግሥታት ማህበር ለማቅረብ ወደ ዠኔቭ እንድንሄድ ያቀረባችሁልንን ሓሳብ ተቀብለናል። በዚህ መሠረት ቤተመንግሥታችንን ለቅቀን እንድንወጣ፤ጠላት የአዲስ አበባን ሕዝብ በመርዝና በጋዝ እንዳይፈጀው ከተማው “ነፃ ከተማ”  ተብሎ ይታወጅ።”

ንጉሠነገሥቱ ይህንን ተናግረው ስብሰባውን ሲዘጉ ጊዜው ውድቅት ሌሊት ለመሆን ተቃርቦ ነበር። በማግስቱ ዓርብ ሚያዝያ 23 ሙሉውን ቀን በቤተመንግሥቱ የጉዞው ዝግጅት ሲጠናቀቅ ከቆየ በላ ለቅዳሜ ሚየዚያ 24 አጥቢያ ሌቱን ንጉሠ ነገሥቱ ንጉሣውያን ቤተሰቦቻቸውና አንዳንድ ታላላቅ ሰዎችን አስከትለው በልዩ ባቡር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ አመሩ።

ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ የንጉሡን ስም ለማጠልሸት ከተሸነፈው ጣሊያን ጀምሮ እስከ የ60ዎቹ ዉዥምብራም የተማሪዎች ማሕበር እስከ አክራሪ ኤርትራ ባላባቶች እንዲሁም እስከ ወያኔና ኦነግ ዛሬ ደግሞ በዘመነ ወያኔ ተወልደው ያደጉ ያንኑ የውሸት ስም ማጠልሸት ሲጋቱ ያደጉት እንደ መምህርት መስከረም አበራ የመሳሰሉ አዲስ ትውልዶች መቀጠሉ ያሳዝናል። እኔ የገረመኝ ተማርን የሚሉ ሊሂቃን በገፍ የተዘረጉ ማስረጃዎ እያሉ፤ ማለትም በስብሰባው ላይ የነበሩት እንደ እነ  አቶ መኰንን ሀብተወልድ እንዲሁም ከላይ የጠቀስኩት በቅርቡ 7 አመት በፊት የታተመው የክቡር አቶ ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ምን እንደሚል አንብቦ መረዳት እንዴት ያቅታቸዋል?

አንባቢ ሆይ! ሰነዱን ለማሃይሙ አዲሱ ትውልድ እንዲደርስ “አዳርሱት” ሼር አድርጉት

የምስኪኑ ንጉሥ ነብስ በሰላም ትረፍ!

አበቃሁ!


ጌታቸው  ረዳ (Ethiopian Semay ድረገጽ አዘጋጅ )