Saturday, February 27, 2021

ተቃወሚዎቹ ቻሜሎኖች ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) Ethio Semay 2/27/2021

 

ተቃወሚዎቹ ቻሜሎኖች

ጌታቸው ረዳ

 (ኢትዮ ሰማይ) Ethio Semay

2/27/2021


ቻሜሎን የሚለው የእንግሊዝኛው ቃል በአማርኛ  "እስስት" ተብሎ የነበብ። የኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምንግሥት በተለዋዋጠ ቁጥር እንደ “ቻሜሎኖቹ” ቀለማቸው እየለዋወጡ አገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ እንዳታገኝ እንቅፋት ሆነዋል።

በቅርቡ እየታየ ያለው የተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ተመዝግቦ መግባት ካበሳጩኝ ቀዳሚው ነገር ነው። ሥልጣን ላይ ያለው “የኦሮሙማው ፋሺሰታዊ የነገድ ፖለቲካ አቀንቃኙ መሪ አብይ አሕመድ” ባዘጋጀላቸው ምርጫ ተብየው ዘልለው ለመግባት እያነፈነፉ ያሉት ተቃዋሚዎች ምን ለመለወጥ ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት መሰረታዊ ነው።

መንግሥት/ሥርዓት/ሕገ መንግሥት ለመለወጥ ወይስ የፋሺቶቹን ዕድሜ ለማስረዘም? እነዚህ ከሆነ እርማቸውን ማውጣት አለባቸው። ካለፈው ምንም አልተማሩም። ወያነ በምርጫ እንዳልተለወጠ ሁሉ የወያኔው ዲቃላ “የኦሆዴድ መንግሥት” በሽግግር መንግሥትና በአመጽ ካልሆነ በምርጫ ሊለወጥ እንደማይችል እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? ለውጥና ሕገ መንግሥት የሚመጣው በምርጫ ሳይሆን፤ ወያኔን በሕዝብ አመጽ አስጨንቆ ሥልጣኑን እንዳስለቀቀው ሁሉ ሥልጣን ላይ የሚገኙት የዛሬዎቹ “የወንጀለኞችና የሙስና ንጉሦች ስብስብ” የሆነው “ኦሆዴድን/ብልጽግናን” በምርጫ አይለቅም። የሚለቀው ተቃዋሚዎቹ ሕዝብን ለሰለማዊ አመጽ በማስነሳት ለሽግግር መንግሥት በር እንዲከፍት ካልተገደደ “አሻጋሪያችሁ እኔ እና እኔ ብቻ ነኝ” የሚላቸው አብይና አብይ ባዋቀራቸው “የምርጫ ጋሪዎች” ተቀምጦ ወደ ለውጥ መጓዝ ፈረንጆቹ “ጃክ ኣስ” (jack ass) ወይንም moronic የሚሉት የሞኝ ሞኝ የመሆን ዕብደት ነው። አህን ፈረንጁ እንደሚለው “ቱ ሌት” ጊዜው አልፏል።

ተቃዋሚዎቹን ለምን በቻሜሎን መሰልኳቸው? ቻሜሌኖች ቀለማቸውን በማሳመርና ላለመታወቅ አከባቢውን ለመመስል እንደሁኔታው ቀለማቸውን በመለዋወጥ የታወቁ ብቸኛ እንስሳት ናቸው ፡፡ ተቃዋሚዎቹ በሥርዓቱ ሲሰቃዩ የግዳጅ አያያዝ ነውና ልክ ቻሜሎኖችም በግድ ሲያዙ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ የጩኸት እና መንከስ አጸፋ ያሳየሉ፡፡ ሆኖም የቻሜሎኖቹ መንከስ የሚያሠቃይ ቢሆንም ለሰዎች መርዛማ ወይም ጎጂ እንዳልሆነ ሁሉ ተቃዋሚዎችም ልክ እንደ ቸሜሎኖቹ የሚያሰሙት የጩኸት ድምጽ ሥርዓቱን ለአደጋ አጋልጦ ከሥሩ ገርስሶ የሚጥል አጸፋ አይሰነዝሩም ፡፡ ብዙዎቹ ቻምሌኖች የተለያዩ ባህሪ እንዳላቸው ሊቃውንት ይናገራሉ - አንዳንዶቹ ሲስተናገዱ በደስታ ይቀበላሉ ፣ ሌሎቹ ግን እንዳይነኩ ይመርጣሉ ፡፡ እንዳይነኩ ሲመርጡ ግን ብዙዎቹ የሚለቁት መርዝ ገዳይ እንዳልሆነ ሁሉ ቢያንገራግሩም “ዝግምተኞች” ስለሆኑ በቀላሉ ይያዛሉ። ተቃዋሚዎቹም በገዢው መንጋ በተለያየ ጥቅም ተስተናግደው ሲያዙ (ልክ የኪነቱ ሰው “አቶ ደበበ እሸቱ” እንዳለው “ቤተመንግሥት እንደገባና እንድጎበኝ ያደረገኝ እኮ የኔው መሪ አብይ አሕመድ ነው” እንዳለው ሁሉ በቀላሉ የሚያዙ ተቃዋሚዎችም እንዲሁ አሉ።

ተቃዋሚዎቹ ለከፈሉት መስዋእት ምስጋና የሚገባቸው ቢሆንም የሕዝቡን እሮሮና ፍላጎት ግቡ ድረስ እናደርሰዋለን ካሉ አሁን እየገቡበት ባለው መንገድ ግቡ ሊደርስ አይችልም። መጀመሪያ እየታገሉት ያለውን ሥርዓትና መሪ ማወቅ በተገባቸው ነበር፡ ሆኖም አላወቁትም። አገራችን በከፋ መልኩ የዘር ጭፍጫፋ “ጀነሳይድ” እየተካሄደ ባለበት አገር እና ለዚህ ወንጀል ተባባሪ የሆነው መሪውና ሥርዓቱን ለመጣል ሕዝባዊ አመጽ ወይንም ሰላማዊ አመጽ ለመጥራት አመቺ መንገድና በቂ ምክንያት ተከፍቶ እያለ ለ3 አመት ያህል ያንን ክፍተት ሊጠቀሙበት ፍላጎት አላሳዩም።

የሃይማኖት ተቋማት እየተቃጠሉ፤ ጥንታዊ ቅርሶች እየፈረሱ፤ በተለይ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ አማኞች የአንገታቸው ማተብና መለያቸው የሆነውን ሰንደቃላማቸው እየተነጠቁ ለማመን በሚያስቸግር የመብት ግፍተራ እየተፈጸመባቸውም ቢሆን ምንም ሳይሉ “ሃይላችን ፈጣሪ ነው” የሚለው “ራስን መከላከል ወንጀል ነው ብሎ ፈጣሪያቸው የነገራቸው ይመስል” ራስን የማታለያ መንገድ መርጠው “የቅኝ ግዛት አይነት” “ዘግናኝ ግፉን” አሜን ብለው መቀበላቸው አላንስ ብሎ ተቃዋሚውም እራሱ “ዓድዋ” ላይ ወራሪዎችን ያሸነፈቺው አርማችንን ይዘው ሲገኙ “እየተነጠቁ፤ ሲታሰሩና ሲደበደቡ” አመጽ ያስነሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከነጭራሹ “ወደ ምርጫ” መግባት ብቸኛው አማራጭ ነው ብለው ሥልጣኑን የያዘ “የወንጀለኞችና የሙሰኞች ስብስብ” ዕድሜን ለማራዝም የሚያስከትለው ሰበብ “ኢትዮጵያ” የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደምትበታተን ይታየኛል። የቻሜሎኑ ተቃዋሚ ውሳኔ ጊዜው ቢዘገይም ተሎ ከነቃ ‘አሁን ከገባበት ጨዋታ ተሎ ወጥቶ’ “ሰላማዊ አመጽ” ካላስነሳ እየቀፈፈኝ እና እየዳዳሁም ቢሆን  “ኢትዮጵያ መዳኛ የላትም” ወደ ማለት እየዳዳኝ ነው።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) (Ethio Semay)