መልስ ለመምህርት መስከረም አበራ ስለ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና የማይጨው ጦርነት
ጌታቸው
ረዳ
(Ethiopian
Semay)
5/13/22
አስቀድሜ ስለ መምህርት መስከረም አበራ ያለኝን አጠቃላይ እይታ ልግለጽና ከዚያም ትናንት ይድረስ ለጀኔራል
አበባው በሚል መልዕክት ስታስተላልፍ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የማይጨው ጦርነትን ጥለው ሸሽተዋል ብላ ስለተቸቻቸው የተሳሳተ ትችትዋን እተቻለሁ።
መምህርት መስከረም አበራ ባለፉት
ጥቂት አመታት ስትከተላቸው በነበሩት የተሳሳቱ መስመሮችዋን በብዕሬ ትችት ውስጥ ስተቻት እንደነበር የምትከተሉኝ አንባቢዎች ታስታውሳላችሁ።
ጥቂቶቹን ላስታውስ። በ1983 ዓ.ም ወያኔ እና ኦነግ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲህ የተፈጠረው አረባቢው “ቀይ ነጭና ጥቁር” ባንዴራ
ሕጋዊ ባንዴራና መለያ ተደርጎ በኦሮሞ አክራሪ እስላሞችና አባ ገዳ ተብለው በሚጠሩ ባሕላዊ የኦሮሞ ማሕበረስብ መሪዎች ተቀባይነት አግኝቶ ሲሸበረቅበት እነሆ በሕጋዊነት 30 አመት ሆኖታል። ይህ
ሕገወጥ ባንዴራ ኦሮሞዎች ዘንድ የኢትዮጵያብ ሰንደቃላማ ተክቶ ከሚከበሩት የኦሮሙማዎች ባንዴራ አንዱ ነው። ራሱን “ጀኔራል” ብሎ
የሰየመ ብዙ አማራ የጨፈጨፈ “የእስላማዊት ኦሮሞ አገር ነፃ አውጪ” መሪ ነኝ ሲል የነበረው ሟቹ አብደል ከሪም ኢብራሂም ሐሚድ
በቅል ስሙ “ጃራ አባ ገዳ” ስያውለበልበው የነበረው የድርጅቱ መለያ
ምልክት እንደነበርም ይታወሳል።
አክራሪዎቹ እነ መረራ ጉዲናም
የሚያውለበልቡትና በሸሚዝና በየክራባቶቻቸው ሲሽቀረቀሩበት የነበረውን ባንዴራ እህታችን መምህርት መስከረም አበራም እንዲሁ በዛው ባማረው
ውበትዋ ተላብሳው ባህላዊ ልብስ አድርጋ የተነሳቺውን ፎቶ አይተናል፡ በዚህ “ካልቸራል ሳብቨርዥን” ተቃውሞየን ጽፌባታለሁ።
በመቀጥልም ጽረ አማራው አንዳርጋቸው
ጽጌንና ብርሃኑ ነጋን በማመጎስና በመከተል ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳና ድጋፍ በማድረግ በየዋሁ ሕዝባችን ተቀባይነት እንዲኖራቸው የተቻላትን
ሁሉ አድርጋ በብዕሬ ተተችታለች። ሌላም ሌላም።
ያ እንደዚያ ሆኖ በዝግታ የተቀላቀለቺውን
አማራን የማዳን ዘመቻ ማሕበረሰቡን በፍጥነት እንዲነቃ ማንም መሞገት የማይችለውን ብርቱ የሙግት ችሎታዋን በማበርከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ
እያደረገች መሆንዋንም ከልቤ የምወድላትን አስተዋጽኦና የብልህነት ምጥቀትዋን አደንቃለሁ። ሙግቶችዋን ለመስማት ሁሌም በጉጉት ከምጠብቃቸውና
ከማደምጣቸው ሁለት ሚዲያዎች አንድዋ ነች። ሁላችንም ከድክመታችን እየተማርን እንጓዘለን። ይህ ካልኩኝ አሁን ወደ ትችቴ ልግባ።
ድሮ የወያኔ አገልአይ የነበረ
ዛሬ ደግሞ የኦነግ አባልና መሪ የሆነው የአብይ አሕመድ አሽከር በመሆን ፋኖን ለማዳከም እየሰራ ያለው ጀኔራል አበባው የተባለው
አጭበርባሪ ብሶት የወለደውን “ፋኖ” በመባል የሚጠራው ኢትዮጵያዊ የአማራ ሕዝባዊ ሃይልን በማዳከም አማራውን በወያኔና በኦነግ ማሕበረሰብ
እንዲጨፈጨፍ በመስራት ላይ እንደሆነ የታዘበቺው መምህርት መሰረት አበራ በጻፈቺለት የቅሬታ ይፋዊ ደብዳቤ ውስጥ ከሙሶሎኒ የጣሊያን
ወታደሮች ጋር የተደረገው በማይጨው ጦርነት ላይ ንጉሱ ሸሽተው ወደ ውጭ አገር በመሄዳቸው “እንደ ካሃዲ” አድርጋ የሳለቻቸውን አላግባብ
ትችትዋን እተቻለሁ።
ይህ ስም ማጥፋት መስከረም አበራ አልተጀመረም። የወያኔ ካድሬዎች አማራ ብለው በሚጠሩዋቸው ነገሥታትን ቁቡልነታቸውን ለማጣጣል ሰበብ ይፈልጉላቸዋል። የወያኔ ጋዜጠኛ የነበረው ዛሬ ደግሞ አስተዳዳር ውስጥ ተመድቦ ከጦርነቱ ወዲህ መቀሌ ተቀምጦ እየጮኸ ያለው ሙሉጌታ ደባልቀው “ጋላህቲ ሠጊ” (ዕንቅፋት ጠራጊ) በተባለው የትግርኘኛ መጽሐፉ ላይ ደራሲው እና መሰሎቹ አሁን ደግሞ መሰረት አበራ እየደገመቺው ያለውን የተሳሳተ ትችት ሲስተጋባ እናያለን ።
መስከረም አበራ እየደገመቺው ያለውን
የወያኔው ሙሉጌታ ደባልቀውና የመምህር ገብረኪዳን ደስታ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት የነበሩም እንዲሁ ብዙ ኢትዮጵያዊያን
ይህንን መስመር ሲያስተጋቡ አዲስ አይደለም ።
ለምሳሌ ጋልህቲ ሠጊ ደራሲ እንዲህ
ይላል።
“በ1928 ዓ.ም. መጋቢት ወር
ውስጥ ከወራሪው ኢጣሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ንጉሡ ከማይጨው ጦርነት በመሸሽ ሕዝብን ለጠላት አገርን ለውርደት አጋልጠው ሰጥተዋታል፤
በታሪካችን ከጦርነት አውድማ የሸሸ መሪ ማየት የመጀመሪያው ንጉሥ ናቸው…” በማለት ከእርሱ በፊት የጣሊያን ፕሮፓጋንዳ አራጋቢዎችና
ሌሎችም እንዲሁ የመጀመሪያው ወያኔ መሪ የነበሩት እንደ እነ ‘’ብላታ ኃይለማርያም ረዳ’’ የመሳሰሉት ለየግል ምክንያታቸው ውዥምብር ሲነዙ የነበሩትንም ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማድመጣችን አዲስ አይደለም። ታሪኩ ግን
ሐቅ ሆኖ መመዝገብ አስፈላጊ ስለሆነ፤ ንጉሡን በሚያሞግስ በሌሎች ወገኖች በኩል የተዘገቡትን የታሪክ ሰነዶች ስንመለከት
"ሸሹ" ሚለው ቃል አከራካሪ ቢሆንም ሸሽተው ሲያበቁ በዚያው ተውጠው ቀሩ ወይስ ምን ሥራ ሠሩ የሚለው አብሮ ሲመረመር
ያስገኙት ገንቢ ውጤት ‘ሸሹ’ ከሚለው ጋር ተጻራሪ ነው። ንጉሡ እንግሊዝን ይዘው ስለመጡ ኢትዮጵያን ነፃ አላወጥዋትም ነፃ ያወጣት
አርበኞችዋ ተጋድሎ ነው የሚለው እኔ አልቀበለውም። ጠሊያን በተለይ በከረን በኩል ያሳየው ብርታት እንግሊዞች ጋር የተደረገው ውግያ
አበሻ ኤርትራ ቀርቶ ኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ተዋግቶ በምንም መልኩ አይሮፕላን ከያዙ ጣሊያኖችን በ5 አመት ሊያሸንፍ ከቶ አይቻለውም
ነበር። ይህ በውጭ አገር የታሪክ ጸሓፊ የተጻፈ መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ ማስረጃወን አቀርባለሁ።
አሁን ወደ ክርክሩ ልግባ።
"ከማይጨው (የሰሜኑ) ጦርነት በፊት ንጉሡ ቆራሔ (ምሥራቅ) ላይ ከጣሊያን ጦር ጋር ገጥመው ድል ማድረጋቸውን እንደመነሻ አድርገን ጠላት በእግር ጦር አልሆንለት ሲል ጥቅምት 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ቦምብና መትረየስ የጫኑ 20 አይሮፕላኖችን በማሰለፍ ቆራሄ ላይ ብዙ ጀግኖችን በአይሮፕላን ገድሏል። ከነሱ መሃል አገራቸውን ኢትዮጵያን ሲከላከሉ በውጊያ ላይ የሞቱት ጀግና ግራዝማች በኋላ ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት የማዕረግ ስም ለመሥጠት ንጉሡ ጂጂጋ ተመልሰው በመሄድ የደጃዝማችነት ማዕረግ ሠጥተዋቸው ተመለሱ። ከነፃነት በኋላም ለሟቹ ጀግና ለደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት መታሰቢያ እንዲሆን ጂጂጋ ላይ ሐወልት አቆሙላቸው። ሐወልቱ ግን ወያኔዎች መንግሥት ሆነው ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለደጃዝማቹ የቆመውን ሐወልት በ1983 እንዲፈርስ ሆኗል።
ያልታደሉት ንጉሥ ከጦር ዓውድማ
ሸሹ እያሉ ብዙ መልክ ያላቸው ሰዎች መሳለቂያቸውና መተቻ አድርገዋቸው ማድመጥ ደስታ አጥሰጥም ። በተለይ ወያኔ የተባለ ነውረኛ
27 አመትና ከዚያም በፊት የሰራው ነውርና የፈጸመው አገራዊ ክሕደት ንጉሡን የመውቀስ ሞራል የለውም።
የማደንቃትን ውቢትዋ መምህርት
መሰረት አባራ የሚከተለው ሰንድ እንዳነበበቺው እርግጠኛ ነኝ፤ ሆኖም ለጸሐፊዋ ሳይሆን በጻፈቺው ላይ ለሚያምኑ ወጣቶች ትምህርት
እንዲያገኙ የሚከተለውን ሰነዳዊ ማስረጃ ልለግስ።
ለመሆኑ የማይጨው ጦርነት እንዴት
ነበር?
"መጋቢት 22 ቀን
1928 ዓ.ም. ማክሰኞ ጣሊያን መሽጎ ወደ ተቀመጠበት የኢትዮጵያ ሠራዊት ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ ውጊያውን እንዲጀመር ንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ሠጡ። ሠራዊቱም በትእዛዙ መሠረት በየአለቃው እየተመራ 3 ኪሎ ሜትር
ተጉዞ ጧት ለ12 እሩብ ጉዳይ ሲሆን ጦርነቱ ተጀመረ።
ንጉሠ ነገሥቱም ትእዛዝ ሰጥተው
አልቀሩም፤ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከነበሩበት ሠፈር መሐን ከተባለው ተነሥተው ወደ ጦርነቱ ቦታ ተጓዙና ጦርነቱን ተቀላቀሉ። በጦርነቱ ሰዓት ከንጉሠ ነገሥቱ
ጋር የነበሩት የሆለታ ምሩቃን የክብር ዘበኞች ወደ ፊት ገፉ። ስለነዚህ ጀግኖች ማርሻል ባዶሊዮ እንዲህ ሲል መስክሮላቸዋል፡
" የአየር ኃይላችን ማጥቃት እንደጀመረ ጠቅላላው የክቡር ዘበኛ ወታደር ሦስት
ሰዓት ሲሆን በደጀን ተኳሾች ተከልሎ ሊያጠቃን መጣ። በጥሩ የጦርነት ትምሕርት የሰለጠኑ መሆናቸው የሚያስመሰክር ውጊያ ተዋጉን።
10ኛውን ባታሊዩን በመግደልና በማቁሰል ጨረሱት። እየፎከሩ አሻፈረኝ የሚል ዘፈን እየዘፈኑም ያሉበትን ምድር በጥሩ የጦርነት ታክቲክ ተጠቀሙበት፡ከአደጋ ተጠንቅቀው አደጋ መጣል የሚያስችል ትምህርት
የሰለጠኑ መሆናቸውን አወቅሁ። (ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ የጣሊያን ጦርነት ገጽ 118)
የኢትዮጵያ ጦር በጧቱ ይህን የመሰለ አኩሪ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ከረፋዱ ላይ ደጀን የነበረው የጠላት ጦር ለእርዳታ ደረሰ። እነዚያ የፈሪ በትር የሆኑት አይሮፕላኖችም ደርሰው ቦንቡን ያወርዱት መርዙንም ያዘንቡት ጀመሩ። ጣሊያን ጦርነቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ክፍል ከመሽጉ ወጥቶ መርዝ የሚረጩትን አይሮፕላኖቹን ትቶ ያንን ዘመናዊ የሆነውን መሳሪያ ይዞ ጦርነት አድርጎ አንዲት ጊዜም ድል ያደረገበት ቀን የለም።"
ጦርነቱ እየተቀጣጠለ ሲሄድ ጣሊያኖች
እየደከሙ ሲሄዱ ጣሊያኖች 150 ተዋጊ አይሮፕላኖች በማሰለፍ ዓለም በከለከለው “ኤፕሪት” የተባለው “የመርዝ ጋዝ እና ዘይት” ከሰማይ
በአይሮፕላን ማፍሰስ ጀመሩ። "ሁሉም አይሮፕላኖች ባንድነት እየተነሱ ከላይ የተነገረውን ዓይነት የበዛውን ቦምብና የኤፕሪት
መርዝ በኢትዮጵያ ወታደር ላይ ሙሉውን ቀን አዘነቡት። በዚህ ጊዜ የክብር ዘበኛውና ሌለውም የሲብሉ ጦር በንጉሠ ነገሥቱ እየተመራ
ያለቀው እያለቀ የተረፈው ሲዋጋ ሌላው የሲቢሉ ጦር በንጉሠ ነገሥቱ እየተመራ ሌላው የሲቪሉ ሠራዊት በዚህ መርዝና በጋዝ መርዝ ስለተሸበረ
ወደ ኋላ መመለስ ጀመረ።
በዚህ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ጎራዲያቸውን መዝዘው የቦንብና የመድፍ ነበልባል የመትረየስና
የጥይት በራሪ በሚያፏጭበት መሀከል ገብተው ወዲያና ወዲህ እየተንጎራደዱ በሚዋጉበትና በሚያዋጉበት ሰዓት የሚሸሸውን ጦር አይተው፤
"በአዳራሹ ምን ብለህ ፎክረኽልኝ ነበር? አሁን እኔ ንጉሠ ነገሥትህ ፊቴን ሳልመልስ
በመሃከል ሁኘ በመዋጋት ላይ እያለሁ እንዴት እኔን ጥለህ ወደኋላ ታፈገፍጋለህ?"
ብለው ሲወቅሱት ይህ ንግግራቸው
የሠራዊቱን ልብ እንደጦር ስለወጋው እንደገና እየተመለሰ በጦርነቱ ውስጥ እየገባ ብዙ ሥራ ሲሠራ ታይቷል። …
ይህንም የመሰለ ታላቅ ጦርነት
የተደረገው የወታደርነት ክብር እንዳይዋረድና የኢትዮጵያም የዠግንንት ታሪክ እንዳያድፍ ለመጋደል ነበር እንጂ የድሉ አክሊል በጣሊያን
እጅ የሆነው ጣሊያን በብሬቪና በቶሪኖ ፋብሪካ አቋቁማ መድፍ መመትረየስ ታንክና ቦምብ የጋዝ መርዝና አይሮፕላን በሠራ ጊዜ ነው።
እንዲያው ለነገሩ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ጦርነት ካደረጉት ጀምሮ በማይጨው የተደረገውን የመሰለ ጦርነት ከቶ ተደርጐ አያውቅም ይባላል።
እንዲህ ሆኖም መጋቢት 24 ሐሙስ
“ምክክር” ተደርጐ ጦሩ ከማክሰኞ ሌሊት ጀምሮ ወደ ባዕታዋዮ ስለተጓዘ ወደዛው ወታደር ወዳለበት እንሂድና ጦሩን አሰባስበን ቦታም
ይዘን እንዋጋ። አሁን ካለንብት ቦታ ሁነን ለመዋጋት አንደኛ የአለን ጦር አነስተኛ ነው። ሁለተኛም ቦታው አመች አይደለም የሚል
ሓሳብ ከጦር አለቆች ቀረበ። ንጉሠ ነገሥቱ ግን “እግራችንን ከዚህ ከነቀልን እንደገና የተበተነን ሠራዊት ሰብስቦ መዋጋቱ የሚሣካ
አይመስለኝምና ከዚህ ያለነው እኛው ብንዋጋ መልካም ነው”፤ የሚል ሓሳብ ቢያቀርቡም ባዕታዋዮ ሄደን ከዚያው ሁነን ብንዋጋ ይሻላል
የሚለው ድምፅ ስላመዘነ መጋቢት 24 ቀን ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከመሐን ተነስተው ወደ ባዕታዋዮ ሔዱ።
ባዕታዋዮ እንደደረሱ ከዚያው
ሠፈር ተደርጐ ምክር ተደረገና ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ 4 ቦታዎች ተመረጡ፤ አራት የጦር አዋጊዎችም ተመደቡ። በዕቅዱ መሠረት ጦሩ ወደተመደበበት
ቦታ ከመሄዱ በፊት የጣሊያን ጦር ከነበረበት ጉድቢያ እየወጣ ጃንሆይ ከነበሩበት ወደ መሐን ተራራ መጥቶ ሲገባ ታየ። መሐንና አሁን
ጃንሆይ ያሉበት ባዕታዋዮ ቅርብ ለቅርብ ስለሆነ፤ የጠላት ጦር ከጉድቢያው ወጥቶ በእግር ከመጣ በአራቱ ቦታ ተመድቦ ጦር መሄዱ ቀርቶ
ከዚህ በአንድ ላይ ሆነው ሲጠባበቁ ጣሊያን በእግር መምጣቱን አቁሞ እንደተለመደው በአይሮፕላን ቦንብና መርዝ ማፍሰሱን ጀመረ። በዚህ
ጊዜ በጦሩ ላይ ብዙ ጉዳት ስለደረሰበት ጦሩ አሁንም ተፈታና ፊቱን አዙሮ ወደ ኰረም ጉዞውን ቀጠለ።
ከዚያ በኋላ ሠራዊቱ ከጠላት
አይሮፕላን ለመዳን ጉዞውን በሌሊት ቢያደርግም ቀደም ሲል ጣሊያን የሰበካቸው መሣሪያ ያስታጠቃቸው ገንዘብ የሰጣቸው “የራያና ዓዘቦ
ኦሮሞዎች” በየቦታው እያደፈጡ ሠራዊቱን ይፈጁት ጀመር (የልጃቸው
ሬሳ ለማየት ሲጓዙ የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ማን እንደገደቸው ልብ ይለዋል)። አቶ በሪሁን ከበደ "የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ
በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 211 "የሰውን አገር ሊቀማ ነፃነት ለገፍ ከመጣው የጋራ ጠላት ጋር ሲዋጋ ቆይቶ ድል ሁኖ ለሚመለስ
ወገን እህል ውሃ ማቀበል ይኸውም ቢቀር መንገድ መርቶና ሸኝቶ መሰደድ ሲገባ ቁስለኛ ተሸክሞ በደከመ ጉልበቱ በተራበ አንጀቱ የሚጓዘውን
ሠራዊት በየቦታው እያደፈጠ መግደል ይቅርታ የማይሰጠው የጭካኔ (እና አገር የመክዳት)ታሪክ ነው። ይላሉ (ቅንፍ የተጨመረ)።
ታዲያ ጣሊያን ቀን ከጫካ እየዋለ
ጉዞውን በሌሊት ማድረጉን የተረዳው ጣሊያን"እኛ የምንፈልገው
ንጉሡን እንጂ እናንተን ወታደሮች አይደለም ከናንተ ጋር ጠብ ስለሌለን ማታ ማታ አርፋችሁ እየተኛችሁ ቀን ቀን በብርሃን በሠላም
መጓዝ ትችለላችሁ አንነካችሁም" ብሎ ወረቀት ሲበትን አቶ በሪሁን ከበደ እንዳሉት "እንኳን ከአንድ መንግሥት ከጓደኛው
እንኳ የተነገረውን ቃል በገርነት ማመን ልማዱ ስለሆነ እውነት መስሎት ከተደበቀበት ጫካ ወጥቶ በቀን ጉዞ ሲጀምር 150 አይሮፕላኖች
ቦንቡንና መርዙን ጭነው ምድር ለመንካት 10 ሜትር እስኪቀራቸው ድረስ ዝቅ ብለው በመርዝ እና በመትረየስ ይፈጁት ጀመር። ከዚህ
እልቂት በኋላ ከላይ እንደተገለጸው ፊቱን አዙሮ ከሞት የተረፈው ሠራዊት መጋቢት 27 ቀን ወደ ኰረም ጉዞውን ቀጠለ።
ኰረም ሲደርስ ጥቂት ሲቀረው
የኰረም ከተማ በጣሊያኖች መያዙን ሰማ። አሁን ወደ ኰረም መሄዱን ትቶ ንጉሠ ነገሥቱ የሚሄዱበትን አቅጣጫ እየጠየቀ ተጉዞ ሚየዚያ
7 ቀን ላሊበላ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተገናኙ።
እግራችን ከዚህ ከነቀልን ጦሩ አይቆምልንም እባካችሁ ሳንርቅ ከዚህ ሁነን እንዋጋ እያሉ ንጉሠ ነገሥቱ ‘ማይጨው’ ቀጥሎ ‘መሐን’ ቀጥሎ ‘ባዕታዮ’ ላይ ሲለምኑት ጠላት በአይሮፕላን የሚያዘንበውን መርዝ በመሠቀቅ ጥያቄአቸውን ሳይቀበል ትቶአቸው የሄደ መሆኑንም አቶ በሪሁን ከበደ "የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ" በሚል መጽሐፋቸው በምዕራፍ 21 በሰፊው ተገልጿልና ለዝርዝር ታሪኩ እዚያው ይመልከቱ።
እንግዲህ በብዙ መቶ የተገመተው የጋዝና የዘይት መርዝ ባይሮፕላን ሲነሰነስ አልሞት ባይ ተጋዳይ የሞቶ ሞቶ የቆሰለ ቆስሎ ያመለጠም አምልጦ ተመልሳ የዳነችው አገርና ወድቃ የቆመቺውን ሰንደቃላማ በወያኔ ፓርላማ ውስጥ ስትዋረድ ፤ የውጭ ዓለም ጋዜጠኞችና ፈረንጆች በእንግዳነት ተጋብዘው ለመታዘብ በተገኙበት አዳራሽ ውስጥ “ሰንደቃላማይቷን” በትልቅ “ጥቁር ቀለም” በተቀባ አግዳሚ ሠረዝ ማህል ለማሃል ላይ ተሰርዞባት ውበትዋ መጥፋት አለበት ሲባል (እንዲህ የሚለው በዕድሜው ወጣት የሆነ የሶማሌ ተወካይ ነው)፤ በዚች ባንዴራ ምክንያት ዓለም አዋርዶናል ሲሉ በይፋ የወያኔ ኦሮሞዎችና ሶማሌዎችና ኢትዮጵያዊነታቸውን የካዱ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድኖችና ግለሰዎች እንዲሳለቁባት የፈቀደው ህወሓት እና በህወሓት ዘመን አድገው ይህ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲመገቡ ያደጉ የዛሬ ወጣቶች ስለ ንጉሡ ከጦርነት መሸሽ አለመሸሽ የመተቸት መብቱም ሞራሉም የላቸውም።
እንኳን እና ወያኔ የኢትዮጵያዊነት ኮቴ ያልተከተለው ቡድን ቀርቶ ወያኔንም ሆነ ደርግን
እንፋለማለን ብለው ከአገር እየሸሹ ወደ ውጭ አገር ኑሯቸው ያደረጉት/ያደረግነው በሙሉ ንጉሡ ከጦር ሜዳ ከትግል ሸሹ የማለት መብት
የለንም። ንጉሡ ወደ አገራቸው ለመመለስ ባይሮፕላን እና በመርዝ የታጠቀ
የውጭ ጠላት ወራሪን ለማስወገድ አምስት አመት ሲፈጅባቸው የውስጥ አደገኛ የሕዝብ ጠላት ለማስወገድ ግማሾቻችን ወያኔን
እየተለማመጥን እያጎበደድን የሕዝብ ስቃይ አይተን የሚለብሰውን ልብስ እየለበስን እና የሚያውለበልቡትን ባንዴራን እያውለበለብን የኦነግንና
የወያኔን ጭካኔ እንዳላየን ሆነን አገር ቤት እየተመላላስን ግማሾቻችን ደግሞ ይኼው እስከ ዛሬ ድረስ ሽበት አውጥተን እርስ በርሳችን
እየተራቆትን አገር ለ30 አመት ስትታመስ አገር ነፃ ለማውጣት አምሰት አመት የፈጀባቸውን ንጉሥ የመተቸት ሞራል የለንም።
(ምንጭ ድሮ የንጉሡ ዘመን የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ በሪሁን ከበደ እና ከራሴው መጽሐፍ “የወያኔ ገበና ማህደር” ደራሲ ጌታቸው ረዳ አሜሪካ)
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)