Wednesday, June 2, 2021

ክፍል 3 የትግራይ ተዋጊ ሃይሎች የእርስ በርስ የመታኮስ አይቀሬ እጣ ፈንታ ትንበያ ጌታቸው ረዳ ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay) 6/2/2021

 

ክፍል 3

የትግራይ ተዋጊ ሃይሎች የእርስ በርስ የመታኮስ አይቀሬ እጣ ፈንታ ትንበያ


ጌታቸው ረዳ


ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay)

6/2/2021


የትግራይ ሕዝብ እና “የትግራይ ትዕወት ህጻናት”

ትግራይ ውስጥ ዛሬ እየተካሄደ ያለው ወያኔ የለኮሰው የትግራይ ሪፑብሊክ የመመስረት ጦርነት መነሻው ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። ብዙ ሰዎች፤ ያወም መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ሳይቀር “የጦርነቱ መነሻ” መቸ እንደተቀሰቀሰ እና ማን እንደጀመረው በማተኮር ብቻ የተወሰነ ነው። በዚህ እሳቤ መንግሥትም ሆነ ብዙ ሕዝብ “ለጀሮ ብቻ” የሚጥም “ራስን በራስ የመወሰን” ማርክሳዊ ሌኒናዊና እስታሊናዊ’ መርሆ ያደረገ የቆየውን የ1968 “የትግራይ ሪፑበልክ ምስረታ” ዋናውን ድብቁ የወያኔዎች ፍላጎት የጦርነቱ “ዋናው አስኳል” መነሻ እንደሆነ የተገነዘቡ አይመስልም።

በክፍል 2 እንደገለጽኩት እና ከስብሓት ነጋም በግልጽ እንደተነበየው ሥልጣናቸውን ሲነጠቁ ወደ ጫካ እንደሚወጡና የትግራይ ሪዩብሊክ መስርተው ፤ “ብሔር” (አገር) ናችሁ ብሎ ያዋቀራቸው 9ኙ ብሔሮች/ክልሎች/ እነሱም ወደ እየመንደራቸው እንደሚሄዱ የገለጸው ባለፈው ገልጫለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሕገመንግሥት ብሎ ወያኔ ከጫካ ይዞት የአገሪቱ ሕግ ሆኖ በወያኔ ትዕዛዝ የጸደቀው ሕገ መንግሥት አንቀፅ 39 ማንኛቸውም በሕገመንግሥቱ የተሰየሙ “9ኙ ብሔሮች/ክልላዊ መዋቅሮች” (አገሮች) የመገንጠል መብት እንዳላቸው አስቀምጧል።

 ይህ አገር አፍራሽ በዓለም የሌለ አደገኛ ሕግ ሰርዘው ተብሎ ሲጠየቅ “በመቃብሬ ላይ” ብሎ ሥልጣኑ ሲነጠቅ የመገንጠሉን መብት የሚያስከብርለትን አንቀጽ ለ27 አመት (ዛሬም 3 አመት ጨምሩበት፡ አሁንም ‘አብይ አሕመድ’ በደምና በላብ የመጣ “ሕገመንግሥቴ ነው” ያንን ያላከበረ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ የለበትም’፤ እስከማለት ንግግር የተናገረለት የወያኔ ሕገመንግሥት ዛሬም ኦሮሞዎቹና ሌሎቹ እንዲጠቀሙበት ህያው እንደሆነ አለ) ። በዚህ እሳቤ የጦርነቱ መነሻ ትግሬዎች በኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን ላይ ለዘላለም ይኑሩ ካልሆነም ሪፑብል እንመሰርታለን ከሚል የተቀሰቀሰ ጦርነት መሆኑን ለአንዲት ደቂቃም ብትሆን አትዘጉ።

በደምና በላብ የተገነባ ድንቅ ሕገመንግሥት እያለ የሚናገር ከጎልማሳ የህጻን ሕሊና ያልወጣው “ፒኮኩ ንጉሥ” በአገር ፍቅር የነደደ ብርቱ መሪ ቢሆን ኖሮ “መከላከያ ሃይሉን” ስለመታብን ነው ጦርነቱን ያካሄድነው ከማለት አልፎ ትግሬዎች እየተዋጉት ያለው መነሻቸው “አገር ለመመስረት” እንደሆነ ለዓለም በማሳወቅ “ሉአላዊ-አገር” የማስከበር “ዓለምአቀፋዊና አገራዊ መብት” እንዳለው መከራከር ይችል ነበር። ሆኖም ‘ህጻኑ ንጉሥ’ ጊዜ በንግግሩ እየተፈላሰፈ፤ መከላከያውን እስኪያጠቁት ድረስ “አበባ እና የመናፈሻ ፓርክ” እያቆነጃጀ መሆነን ስላዩት ፡ጮሌዎቹ ወያኔዎች “ቅጽበታዊ” ብሎው የሚጠሩት የሽብር ግድያ በመከላከያው ላይ ፈጸሙ።

ያ ሁሉ ፈጽመው ጮሌዎቹ ወያኔዎች ለብዙ አመታት ስለሰሩበት የፕሮፓጋንዳው የበላይነት በመያዝ “በወንጀል የተጨማለቀው” ገመናቸው እስር ቤት ውስጥ ላለመበስበስ ሲሉ  “ትግራይ ትዕወት” (ትግራይ ታሸንፋለች) በሚል አገር የመመስረት መፈክር እየተመሩ አዲሱን ወጣት ትውልድ ለወንጀላቸው መሸፈኛ እንደሚያመች አድርገው ዛሬም በመለስ “የገለባ እሳቤ” አስልተው እሳት ውስጥ ማገዱት።

 አብዛኛው የትግራይ ህዝብ አሁን ያለው ስሜት “ብሔረተኛ” ነው። የትግራይ ማህበረሰብ ከፋፍለን ብንመለከተው ወያኔ ከመመስረቱ በፊትም ሆነ ወያኔ ጫካ በነበረበት ወቅት በወያኔ ዓላማ አልጓዝም ብሎ አስቸግሮ የነበሩት አውራጃዎች “ዓጋመ/ዓጋሜ አውራጃ፤እንደርታ አውራጃ እና ተምቤን፤ እንዲሁም ሁለት አውላዕሎ” አውራጃ ነበሩ። በነዚህ አውራጃዎች በተለይ አምንቲላ (እንደርታ ድድባ ደርጋ ዓጀን) በተባለው የገጠማቸው የሕዝቡ ተቀዋውሞ “መላው የወያኔ ተዋጊ ከነ ነብሱ ወደ ገድል እየገባ ለሞት ተዳርጎ አንዳንዶቹም ተማርከው ጥቂቶቹ አምልጠው ወደ ዓፋር በረሃ ሄደው ፍዳቸውን አይተዋል) ። ይህ የሆነው በዘመነ ደርግ ነው።

እንደምታውቁት ወያኔ ትግሉን የጀመረው በሽሬ አውራጃ ደደቢት በረሃ ሲሆን ቀስ እያለ ከ” ጸጉረ ለወጥነት” ወደ “ተጋደልቲ/ታጋዮች” ስም እየተጠራ በሕዝቡ ታውቆ ቀስ እያለ ወደ ተጠቀሱት አውራጃዎች ሊስፋፋ ቻለ። ወደ ተጠቀሱት አውራጃዎች ከመንሰራፋቱ በፊት ግን እዛው አካባቢ በተለይ “ሰለኽለካ” በሚባለው አካባቢ እና ምናልባትም አለፍ አለፍ ብሎም ጠንካራ በሆኑ አገር ወዳድ የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንደ እነ አርበኛው “መምህር አብርሃ በላቸው” የመሳሰሉ በሚመራው “ሕዝባዊ መከታ” ፤ (አብርሃ በላቸው የሰለኽለኻ መምህር እና አውራጃ አስተዳዳሪ የነበረ ነው። ሥልጣን ሲይዙ እስርቤት አስገብተው ዕድሜ ልክ ፈርደውበታል) እየተመራ ገበሬውና የመንግሥት ሰራተኛው ከፍተኛ የሆነ ጦርነት አድርጎ ወያኔዎችን አንገዳግዷቸው ነበር።

ተምቤን ለመግባት በጣም ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ እና (አንዳንዶቹ 15 ጊዜ በላይ እንደሆነ ይናገራሉ- ወያኔዎች በተደጋጋሚ ወደ “ዓብይ ዓዲ’ እና አካባቢው እየመጡ ሕዝቡ ቶክስ እየከፈተባቸው እየተመለሱ ነበር) በተደጋጋሚ አስገባኝ አላስገባም በውግያው ምክንያት ዋና ከተማዋን ‘ዓብይ ዓዲ” እያንዳንዱ የውስጥና የደጅ ግድግዳ ቤቶች በጥይት ተነዳድሎ ለማየት የሚገርም አስደንጋጭ የሙታን ከተማ እንደነበረች እኔም ጦርነቱን ተካፍየ በዓይኔ ስላለየሁት መላው የከተማው ቤቶቹ በጥይት ተነድሎ/ስለተቀዳደደ ምክንያት “የቡቶች መዝግያ በሮች እና ግድግዳዎቹ የተቦጫጨቀ ጨርቅ” አስመስሏቸው እንደነበር የጦርነት አስከፊነቱን አስታውሳለሁ።

ክርቢት በሚባል ነብሰገዳይ አሸባሪ ቡድን “ገበሬዎን እና የከተማ ሰዎችን” በውድቅት ሌሊት በአጥር ዘልለው እየገቡ እያፈኑ በመውሰድ ሰዎች በፍርሃት ማቅ አስገብተው፤ ወያኔን የመቃወም ስሜታቸው “እየቀዘቀዘ” ልጆቻቸውን በማሰር፤ በሬ፤ፍየልና አህዮቻቸውን እየወረሱ ሲያስቸግሯቸው፤ መቃወማቸውን አቁመው በወያኔ ቁጥጥር ውስጥ ገቡ። ባጭሩ ለማስቀመጥ እዚህ ላይ ማስተወስ የምፈልገው የትግራይ ወጣትና ገበሬ ወያኔን ለመቋቋም ያልተመዘገበ ከፍተኛ መስዋዕት መክፈሉን ልነግራችሁ እሻለሁ። “የትግራይ ወጣቶች ጸረ ወያኔ ትግል” በሚል ያዘጋጀሁት ኢትዮጵያ ውስጥ የታተመ ጽሑፍ እንደነበረኝ አስታውሳለሁ። ያንን አንድ ቀን በሕሊናየ ከማስታውሰው ቀንጭቤ አቀርባለሁ። ይንን እንዳልረሳው አስታውሱኝ።

ቀስ በቀስ ወደ እነዚህ አውራጃዎች ዘልቆ በመግደልም፤በማፈንም ንብረታቸውን በመቀማትም ሆነ በመግረፍ እና ቀስቃሽ ሙዚቃ በሰፊው በማቅረብ ገበሬው የወያኔ ዓላማ እና ትምህርት እንዲቀበሉ በማድረግ በዝግታ “ነገር ግን” በማይቀሬው “ፋሺስታዊ ትግራዋይነት ብሄረተኛ ስሜት” ተቀላቀላቸው። የእነዚህ አካባቢዎች ትግርኛ “ዓሽኣ” (ዓድዋ ሽሬ አክሱም) በሚበላው አካባቢ የትግርኛ ለዛ/አነጋገር የተለየ በመሆኑ፤ ከላይ የጠቀስኳቸው የነዚያ አካባቢ ኗሪ ትግርኛ የበላይነት እየያዘ ቀስ በቀስ የኤርትራ የበረሃ/የታጋዮች/አረቦች/ ትግርኛም የተደበላለቀበት የአነጋጋር ዘይቤ/ልሳን/ የበላይነት መያዝ ጀመረ።

መንግሥትነቱን ከያዙ በ27 አመት ውስጥ በባሰ መልኩ ርዕሰ ከተማዋ መቀሌ እና አንደርታ እንዲሁም ራያ/ማይጨው/ በሚባለው አካባቢ ጨርሶ በበታችነት ስሜት ተውጠው ፤ “ትግርኛ ትግርኛ ነው” በሚል “ሽፋን” የ ዓ.ሽ.ዓ. እና የታጋዮች የአነጋገር ዘይቤ የሌላውን ባሕላዊና ነባሩን “ለዛ” እየሰለቀጠ በአሃዳዊነት ስር በዘዴ ደፍጥጦ “የትግራዋይነት ትግርኛ” “አሃዳዊነት” እና የወያነ ትግራይ ዘላለማዊ “መጻኢት ትግራይ” ለማነጽ 27 አመት የሕሊና ቀረጻ ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ውሃ ስትጠጣ የነበረቺው “የመጻኢት ትግራይ” እፅዋት በ “ትግራይ ትዕወት” መፈክር እየተሸኘች በገሃድ ብቅ ብላለች።

የትግራይ ትዕወት መሪዎች የምታውቁዋቸው በወንጀል የተጨማለቁ “የታሪክ ፍርድ ቤት” በቁራኛ ዓይን የሚያያቸው “ወረበላዎች” ናቸው። ይህ “የትግራይ ትዕወት መፈክር” ሌላ ቀርቶ በስሜት የሚነዱት እነ አብርሃ በላይ (የኢትዮ-ሚዲያ ድረገጽ ባለቤት) የመሳሰሉ ሳይቀሩ የተቀለቀሉበት እና መፈክሩን በየድረገጻቸው አሸብረቀውበት የሚፈክሩበት አዲስ ፋሺስታዊ የግንጠላ አቀንቃኝነት ስሜት የተጠናወተው “የትግራይ ብሔረተኞች” መፈክር ነው።

ትግራይ አገርነት “የትግራይ ሕዝብ” ይቀበላል ወይ የሚለው ከባዱ ጥያቄ የሚመለሰው አሁን ሳይሆን “እውነታውና መከራው” ሲጋፈጡ የሚመለስ መልስ ነው። ለሚዛናችሁ መነሻ እንዲሆን ግን የትግራይና ኤርትራ ማሕበረሰብ እጅግ “ሲበዛ” ወገንተኛ በመሆኑ “ልጁ ፤ ወንድሙ እህቱ የእህቱ ልጅ…ወዘተ//ወዘተ…” ወደ በረሃ ወጣ ሲባል ‘ፖለቲካው’ ምን ይሁን ምን “በሥጋ ግንኙነት” ብቻ በማየት ድጋፉን ይሰጣል። አንዳንድ ቆራጥ ሽማግሌዎችና ወጣቶች “ኢትዮጵያዊነትን” አንተውም ብለው የሚጋፈጡ ከተገኙ ቀዝቀዝ የማለትና የመለሳለስ ዝንባሌ ያሳያሉ (በተለይ መንግሥት የምግብ፡የንግድ ሸቀጣሸቀጥ እና የመሳሰሉ አቅርቦት በተገቢው ካቀረበላቸው።)

                       የደብረጽዮን “ትግራይ ትዕወት!” ሽምቅ ተዋጊ

ሁለት ዓለም አቀፍ የሽምቅ ተዋጊ መሪዎች “ያለቲን አሜሪካው ጎቬራ እና የቻይናው ማኦ ሴቱንግ” በብዙ ነገሮች ላይ የተስማሙ ቢሆኑም የተለያዩ ልምዶቻቸው ግን በስልታቸው ውስጥ በርካታ ተመሳሳይ ስልቶች ቢከተሉም አስፈላጊ ልዩነቶች እንዲኖራቸው የየራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም ለሽምቅ ተዋጊ ስኬታማ ግብ መምቺያዎች ሁለት አሉ። “ጠንካራ ተዋጊ” ወይንም “የተማረ ጠንካራ መሪ” ናቸው። ጠንካራ ተዋጊ ለግብ ያደርሳል የሚለው አንደኛው “በቼ ጎቬራ” እሳቤ ሲሆን በመሪ ብቃት የሚጠናቀቀው የሽምቅ ውግያ ወሳኝነት አለው የሚለው የቻይናው የሽምቅ መሪ የነበረው “የማኦ ሴቱንግ” መንገድ ነው።

“የትግራይ ትዕወት” የወያኔ አዲሱ የሽምቅ ተዋጊ ሃይል ጥንካሬ ይኖሮው ይሆናል ብለን እንገምትና፤ በእርግጠኛነት ግን “ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ እንዳጣች ሁሉ ፤ ልክ ትግሬዎችም እንዲሁ  “ጠንካራ መሪ የላቸውም”። እንደሚታወቀው ወያኔን ለዚህ ሁሉ ውርደት ያጋለጠው የጠንካራ መሪያቸው የመለስ ዜናዊ በሞት ማጣት ነው።

አሁን ያላቸው አማራጭ የቼ ጎቤራን የአንድ አመት ልምድ ያካበተበትን ምክር “በጠንካራ ተዋጊ” መተማመን ብቻ ነው።

አስቀድሜ በሌላ ትችቴ በጻፍኩት “የኮካ ኮላው ትውልድ” ረዢሙና አሰልቺው ትግል “በተአምር” ጠንካራ ተዋጊ ሆኖ ይዘልቃል ብለን እንተንብይና ተሳክቶላቸው ተዋጊው ሃይል “እንደፈረስ ጋልቦ” የፕሩሲያው ጀኔራል “Clausewitz” እንዳለው “ጦርነት በሌላ መንገድ የፖለቲካው ቀጣይነት ነው” ፡ በሚለው እሳቤ “የትግራይ ትዕወት” ተዋጊ ሃይል ተዋግቶ በፖቲካው ሜደ እቦታው ላይ ቢያደርሳቸውም ፤ በፖለቲካው ሜዳ ሲደርሱ ተዋጊዎቹ የግንጣላ መስመራቸውና “አማራ” ወይንም “ኢትዮጵያ ወርራናለች” የሚለው “ድርቅ ያለው” መከራከሪያ ፖለቲካቸውና በዘር ማጣፍት የተካፈሉበት ወንጀላቸው ተጨምሮበት “ምን ያህል ርቀት ተሟግተው በምን የታሪክ እሳቤ እና ችሎታ ተደራድረው ግባቸው ሊመቱ ይችላሉ?” የሚለው የመሪዎቻቸው ከባዱ የሚገጥማቸው ፈተና ነው።

በዚህ ላይ በተለያዩ ወንጀሎች የመዘፈቃቸው የጀርባ ማሕደራቸው ተጨምሮ ለድርድር የሚያበቃቸው ኩሩ መሪ ከየት ተፈልጎ ይገኛል? የሚለው ጥያቄ ሌላው ከባዱ የቤት ስራቸው ነው።

 በዚህም ሆነ በዛ “ጫካ ለመውጣት የሰጡት የሽፋን “ምክንያት” አጠያያቂ ነው። የሚከተሉት ጥያቄዎች ጠይቄ መልስ ልስጥባቸው።

ስለዚህ ለወደፊቱ (አገር ውስጥ) ተቀባይነታቸው ምን ያህል ነው? “0” ባዶ! ። ተጋዮቹ “በመስመራቸው የጸኑ ናቸው”? አዎ። የዕዝ ሰንሰለታቸው ጠንካራ ነው? በምደር ላይ ማንኛውም ሃይል አያንበረክከንም በሚል ከፍተኛ ትጥቅ በመታጠቃቸውና የ17ቱ አመት የጫካ ጦርነታቸው እያስታወሱ “በትዕቢት የተወጠረ” ባሕሪና “ፖለቲከኞቹ” ወታደራዊ ሃይሉን እያዘዘ “የተዘበራረቀ አመራር” ስለነበራቸው በዚህ ዝብርቅርቅ ትምክሕት “መንካት ያልነበራቸው” “የሰሜኑ ዕዝ በመንካታቸው” ወር ባልሞላ ጦርነት “አፈር ልሰው ኩፍኛ ተመትተው” መሪዎቻቸው ብዙዎቹ ተደምስሰውና ተማርከው ደንግጠው ለጊዜው “አይጥ” ሆነው ነበር።

አሁን “በወታደራዊ - ዕዝ” ስር ስለሚመራ የተዋጊዎቹ ግንኙነት የተለቀበና እንደገና ህይወት እየዘራ የመጣ ይመስላል። ስሊዚህ መልሱ “አዎ” ነው። አገራዊ ማለትም (ኢትዮጵያ ውስጥ) እና አለም አቀፍ ተቀባይነት አላቸው? አለም አቀፍ ለጊዜው ተቀባይ አግኝተዋል። በአገር አቀፍ ግን ሕዝቡ የ27 አመት ግፍ ስለሚያስታውስ በሽብርተኛነት የመፈረጁ አግባብነት ተቀብሎ የመደምሰሳቸው ምኞቱ ከፍተኛ ሆኖ ተቀባይነታቸው “0” ነው።

 የትግሬዎች ድጋፍስ? እንደ ዱሮው 99% ነው።  ዓላማቸው “ወራሪ” የሚሉት “አማራ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች” ከትግራይ ለማስወጣት ነው ወይስ ነፃነት የሚለው እውን ለማድረግ ነው? ገፍቶ ለማስወጣት በጣም ከባድ ሊሆንባቸው ነው። ከባድ የሚያደርገው ደግሞ “ኤርትራን ጨምሮ” በዙሪያቸው ያሉት “የአማራ ማሕበረሰብ ክልሎች” ጋር ከመለሳለስ ይልቅ አማራን እንደ “ጠላት፡ እና እንደ “ወራሪ” በማስቀመጣቸው ውግያቸው እንደ ጥንቱ ሳይሆን እጅግ የከፋ የምግብ አቅርቦት እጥረትና ከፍተኛ የሰው ሃይል መስዋእት የሚጠይቅ ትግል ከፊት ለፊታቸው ረዢምና መራራ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

በፖለቲካው ረገድ የከፋ ፈተና የሚጋርጣቸው ደግሞ “አገር ለመመስረት” እንጂ ትግላቸው በመንግሥት ለውጥ ያተኮረ ስላልሆነ” ቀስ ብሎ የሕዝቡ ስሜት “ከችግር መበራከት እና እውነታውን መጋፈጥ” አኳያ ጋር “ተዋጊው ወደ ትግሉ ሲቀላቀል በነበረው ስሜት ሳይቆይ ቀስ ብሎ እየተሸረሸረ” በጸረ አገር ምስረታ ክርክር የመቆሙ ክስተት አይቀሬ ሲሆን ድጋፉ እየቀነሰ ይመጣል።

እኔ ትግሬ እንደመሆኔ የማውቀውን ልንገራችሁ። በጉልህ ማየት የሚቻለው የዛሬ ትግሬ ወጣት ባሕሪ “ብዙዎቹ” የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ክፍል “ብልጣብልጥ ፤ ታታሪ ፤ ዘረኛ ፤ ምቾትና ድሎት የቀመሰ፤ ወገንተኛና አውራጃዊ” በመሆኑ አገራዊ ስሜቱ የዘቀጠ በጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራነት የተቀረጸ ትውልድ ስለሆነ “ኣንፕረዲክት ሶሳይቲ” ሆኖ ይታያል። የመገለባበጥ ባሕሪው መቸ እንደሚከሰት አያስታውቅም። ሁኔታዎች ሲለወጡ የሙቀቱ ከፍና ዝቅታ እንደ ሜሪኩሪው ንጠረ ነገር ማሳያ “በቀላሉ” “ኣፌክትድ” ይሆናል።

መሪዎቹ የሚናገሩት ያለ ተቃውሞ ይቀበላል፡ ሃይል ስያዩ ከሃያሉ ጋር የመወገን ባሕሪ ይታይባቸዋል። የመሃል አገር ነጸብራቅ በባህልም ሆነ በፖለተካ ትግሬዎችም ሲያጠቃቸው ይታያል (የአዲስ አበባ ወይንም የዩኒቨርሲቲ ወጣቶች ረብሻ ካነሱ እነሱም ያነሳሉ፤ የጎንደር ወጣቶች ከኤርትራ የስፖርት ጨዋታ ለማድረግ ግንኙበት ሲያደርጉ እነሱም ያንኑ ይደግማሉ) የጸና መስመር አይከተሉም።ይህ ባሕሪ የመጻኢት ትግራይ ትግል ሊያደናቅፈው ይችላል።

“የምግብ” አቅርቦት እና “መሳሪያ” አቅርቦታቸው እንዴት ነው? ምግብ የለም!!! እንዴት እንደሚመገቡ ባለፈው በክፍል 2 አቅርቤዋለሁ። መሳሪያ በሚመለከት ‘ከመከላከያ ዘርፈው የታጠቁዋቸው ታንኮች፤ ሚሳይሎች’ በአገር በመከላከያ አይሮፕላኖችና ‘ድሮኖች’ ጋይተዋል። አሁን የያዙት መሳሪያ “ተራ መትረየስ” እና “እንደ ብትር በጫንቃ የሚያዝ ደብቀው ያቆይዋቸው በጣም ጥቂት ተመዘግዛጊ “አርቢጂ” የሚባል ተተኳሽ የእጅ ሮኬት” ብቻ ይዘው ቀርተዋል።

የዜና ማሰራጫ እና የፕሮፓጋንዳ ‘ሚዲያ’ አላቸው? ከመንግሥት በለይ 21 ን የሰማይ ፕላኔት ሰንጥቀው ‘ብላክ ሆል’ እስከተባለው “ገሃነማዊ ሰማየ ሰማያት” የሚደርስ  ጩኸት የሚጮሁ በጣም “ዘረኞች” እና ዋሾ” ሚዲያዎች ውጭ አገር አሉዋቸው።

በትግራይ መቀሌ ከተማ ውስጥ ያሉት ሚዲያዎችንም ስንመለከት “በውስጥ አርበኞች የተበከለ ስለሆነ ሰራተኛ ቢለዋወጥም አሁንም ከወያኔ ደጋፊዎች ሊጸዳ አልቻለም። ሚዲያው እንደ ጦርነቱ ጊዜ ባይፈጅም ችግር ይታይበታል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ጥይት ሳይፈሩ ትግራይ ውስጥ ተጋፍጠው በየወረዳውና አውራጃ እንዲሁም አስተዳዳሪዎች ሆነው የተሾሙ ሰዎች “ለአብይ አሕመድም” ያገልግሉ “ለማንም” ፤ “ምንም ይሁን ምንም” ለድፍረታቸው ግን ከፍተኛ አክብሮት እሰጣቸዋለሁ። ወያኔዎች በቅርብ ስለማውቃቸው በሩቅ አፍ መከፍት እና ፊት ለፊት ወያኔን መጋፈጥ እጅግ ለየብቻ ነው። ወያኔ ማለት የታሊባን ያህል እጅግ በቀልተኛ ፤ጨካኝ፤ እንዲሁም አሸባሪዎች እና ወንጀለኞች የሚመሩት ቡድን በመሆኑ፤ፊት ለፊት ፖለቲካቸውን የሚጋፈጣቸው ሁሉ ዋጋ ያስከፍላል። ስለሆነም ሳይደናገጡ ለሚጋፈጡዋቸው አርበኞች ሁሉ አክብሮት አለኝ። ይህ የመቃወም የመጀመሪያ የትግል ምዕራፍ ጀማሪዎችና “በሲኦል ምድር የሚደረግ ግብግብ” በመሆኑ ስለ ጀግንነታቸው አድናቆት ይገባቸዋል።

ወደ ርዕስ ስመለስ “ወያኔዎች” ይህ ሁሉ “አዎንታና ድጋፍ” ስላላቸው፤ ጠንካራ አገራዊ መሪ ስለሌላቸው አሁን የሚመራቸው ወታደራዊ መምሪያ (እነሱ ‘ኮማንድ ፖስት’ ብለው የሰየሙት) ወታደራዊ ሃይሉ በሚያሰማራቸው የትግል ውግያ ብቻ ያተኮሩ ስለሆኑ ወያኔዎቹ ከሽምቅ ተዋጊነታቸው ትንሽ ላቅ ብለው ሊወጡ ይችላሉ።

ለዚህም፤ መዘንጋት የሌለበት ነገር፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ኖረም አልኖረም፤ ሰብሓት እንዳለው (በክፍል ሁለት ጽሑፌ ይመልከቱ) በተለይ ኢሳያስ “አንድ ነገር ቢሆን” “ትግላቸው ወደ ኤርትራ ያሻግሩታል” ። “በተአምር” ድንገት ካልተቀጩ” ትግሉ እጅግ መራራና ረዢም ስለሚሆን አማራጭ የመዋጊያ እና የምግብ አቅርቦት የሚረዳቸው ‘ቤዝ’ ፍለጋ፤ እየቆረጡ ድምበር ጥሰው መግባት ይጀምራሉ።

የዚህ ግፊት ዋና ምክንያት “ጠላት” ብለው በሚጠርዋቸው “የአማራ ክልሎች” ዙርያ መለሽ “በመከበባቸው” ኤርትራን የወያኔዎች የመዋጊያ ቤዝና የሱዳን የኤርትራ በሮችና የባሕር በሮችን ለምግብ ማስገቢያቸው ስለሚረዳቸው “የተማረኩ ኤርትራ ወታደሮችና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን” በማሰባሰብ ትኩረታቸው ወደዚያው ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ትግሬዎች ለአብይ አሕመድ “የመረረ ጥላቻ ስላላቸው” እና አበባና ፓርክ በማቆነጃጀት ጊዜውን የሚያባክነው አብይ አሕመድ “አገሪቱ ውስጥ የተንሰራፉ የተለያዩ ተዋጊ ሃይሎችን” ፈጥኖ ጊዜ ሳይሰጥ የመምታትና የመቆጣጥር ችሎታ ብቃት ስለሌለው በአብይ አሕመድ ከተመራች ትግሬዎች የመገንጠል ግባቸው ባይሳካም “እንደ ብርቱ ሽፍታ” ሁከት በመፍጠር እየበረቱ መምጣታቸው አይቀሬ ነው።

ያም ሆነ ይህ በዚህ ክስተት ሕዝቡ ምን ዓይነት ስሜት አለው?  አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የትግራይ ሕዝብ ብሔረተኛ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ ብትጠይቁ መልሱ “አዎ” ነው። ከዚህ አዎንታ በመነሳት ተዋጊዎቹ የሚያገኙት ለጊዜውም ቢሆን የሕዝቡ ድጋፍ መገመት አይከብድም። ነገር ግን የትግራይ ሪፑብሊክ ዓላማ ይደግፋል ወይ? የሚለው ግን በግልጽ እንዳስቀመጥኩላችሁ “እውነታውና መከራው” ሲጋፈጡ የሚመለስ መልስ ነው። ወጣት ተዋጊዎች ግን በመጉረፍ ላይ ናቸው።  

የትግራይ ወጣት “ወያኔ ከተመሰረተበት” ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሲነገራቸው ያደጉበት ትምህርት የትግራይ ብሔረተኞች ዓላማ ነው። ስለዚህ የትግራይ ማሕበረሰብ ብዛት ስናሰላው ወጣቱ 80 ከመቶ ነው ካልን 80 ከመቶው የወያኔ አቀንቃኝ ሆኖ ወደ ጫካ ባይወጣም በያለበት ከተማ እና ክ/ ዓለም ደጋፊ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ሆኖም ደህና አድርጌ ላሰምርበት የምፈልገው ግን “እውነታውና መከራው” ሲጋፈጡ የሚለወጡበት ሁኔታ እንዳለ እና እንደሌለ ግን ለናንተው ግምገማ ልተው።

 የጊዜ ጉዳይ እንጂ በተዋጊዎች ላይ የመለያየት እና ከጥንት ጀምሮ በወላጆቻችን የጀመረው ታሪካዊ የግጭት ባህላችን በቀዳማይ ወያነም በዳግማይ ወያኔም አሁንም በነዚህም ይደገማል፡ አይቀሬ ነው። የመስመር እርቅ ሳያደርጉ ወደ ጫካ የሁዱት 4ቱ የተለያዩ የትግራይ ብሔረተኛ ፓርቲዎች እና “ኢትዮጵያዊነታችንን” አንለቅም የሚሉ “ስብሰባ ውስጥ ጥያቄ” የሚያበዙና ከትግሉ አካሄድ ከጊዜ ብዛት የሚነቁ፤ ወይንም ወያኔ በትግሉ ጊዜ ሲፈጽመው የነበረው እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለሚያቀርቡ “ሓንፋሺ” (በታኝ) በሚል ስም እየሰጠ “የመረሸንና የእስራት አፋና” ባሕሪው ከጀመረ “ትግሉ በሚያፈራቸው” ለወደፊቱ የሚከሰቱ ወጣት ተቃዋሚዎች በሚፈጠረው የወደፊት ፍጥጫ ድርጅቱ ለሁለትና ለሦስትም ሊከፍለው ይችላል። (በወያኔ የ17 አመት ትግልም ታይቶ ብዙ ታጋዮች ተረሽነዋል) ።

ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ (የባድሜን ሁኔታ አስታውሱ የታየው መከፋፈል፤ ከሥልጣን ማባረር) እነ ጻድቃን እነ አበበ ተ/ሃይማኖት…፤ እነ ስየ በሌብነት ተወንጅለው ወደ እስርቤት መወርውርና መወነጃጀል፤ እንዲሁም በወያኔ የ17 አመቱ ዘመን ትግል የታየው መገዳደልም ሆነ መከፋፈል እና ትግሉን ጥለው ወደ ከተማ እና ሱዳን እየሸሹ እጃቸውን ወደ “መንግሥት የመስጠት” ክስተት የታየ እውነታ ስለሆነ፤ ዛሬም በዚህ “ትግራይ ትዕወት” አዲሱ የትግራይ ሪፑብሊክ ትግል የማይከሰትበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ይህ እንዴት እንደሚከሰት በሚቀጥለው ክፍል 4 በሰፊው እንመለከታለን።

ያም ሆኖ ወጣቱ ትግሉን እየተቀላቀለ ነው። አዎ! ለምን? ግልጽ ነው። በጦርነቱ የተከሰተው አስከፊ የሰው መብት መደፈርም ሆነ የተለያዩ ወንጀሎች በመፈጸሙ “ብቻ” መነሻ አድርገው ሳይሆን አስቀድሞ እንደገለጽኩት “በወጣቶች ሕሊና ተቀርጾ የነበረው” የወያኔ አምልኮተ ትምህርት ወሳኝ ሚና ስለነበረው እንጂ “የሴቶች መደፈር የዘር ጭፍጨፋ” ወሳኝ ምክንያት (ድራይቪንግ ፎርስ) አይደለም። ምክንያቱም፤ የሴቶች መደፈር መነሻቸውና ቁጭታቸው ቢሆን ኖሮ፤ ይህ ግጭት ከመከሰቱ በፊት በወያኔ አስተዳደርም ብዙ ሴቶች እስከ 60 እና ከዚያም በላይ በባለስልጣናት እና በመሳሰሉ ሲደፈሩ እንደነበርና ለዚህም ሴቶች መቀሌ ከተማ ሰላማዊ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር ይታወሳል። ወጣት ወንዶች በሰላማዊው ሰልፍ ሲወጡና ሲደግፉ አልታዩም። ስለዚህ የሴቶች መደፈር ወያኔዎችን (ወንጀለኞችን) ተከትለው ወደ በረሃ ሊያስወጣቸው የቻለ ቀዳሚ መነሻቸው ሊሆን ከቶ አይችልም።

 ያ ክስተት አቀጣጣይ ነዳጅ ሆኖ ተከሰተ እንጂ “በራሱ ገፊ ሃይል” ቢሆን ኖሮ “ማይካድራ” ላይ እና በሰሜን ዕዝ ወታደሮች ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግልጽ የሆነ ጥቃት እና በተለይ ደግሞ ማይካድራ ላይ “አማራን” ለይተው የፈጸሙት የወያኔ “ሁቱዎች” (ሳምሬዎች) በማውገዝ ጭምር አቤቱታቸውን ለዓለም ማሰማት ይችሉ ነበር። ሆኖም “ሕሊናቸው በብሔረተኞቹ ውሃ” እያበበ ያደገ “የብሔረተኞቹ ችግኝ” ሆነው ስለበቀሉ “ውጭ አገር” በሚኖሩ “ብሔረተኛ ትግሬዎች ምሁራን” እና አገር ውስጥ ባሉ “አርቲሰቶች” የሚሏቸው ተዋናዮች፤ ሙዚቀኞች’ ጋዜጠኞች’፤ እንዲሁም በእስፖርተኞች በኩል እጅግ በሚገርም አስደናቂ የሚዲያ ጩኸትና ቅስቀሳ በ“ትግራይ ሴቶች ተደፈሩ” አቤቱታ “ብቻ” ተመርኩዘው “የ12/14/15/16 አመት ያላቸው የትግራይ ወጣቶች ሳይቀሩ ትግሉን ተቀላቅለውታል ።

እነኚህን ወጣቶች የሚመሩ እነማን ናቸው?  በትግሉ ወቅት ሲገድሉ ሲያፍኑና ሲገርፉ የነበሩ ገራፊዎች እና መንግሥት በነበሩበት ወቅትም የምናውቃቸው “ሌቦች” እና “ወንወጀለኞች” ሆነው የዘለቁ ለወደፊትም በወንጀል ከመዘፈቅ ወደ ሗላ የማይሉ የወያኔ መሪዎች የነበሩ ናቸው። ጥያቄ ጠይቀን አሳዛኝ መልስ የምናገኘው የእነዚህ ወጣቶች ህይወት የሚመለከትዋቸው እንደ ሰው እሳቤ፤ ወይንስ “በገላባ እሳቤ”? የሚለው ይሆናል።

የገለባ እሳቤ

የወያኔ መሪዎች ከታሪካቸው የሚታወቁት ታጋዮችን የሚጠቀሙባቸው “በገለባ እሳቤ” ውስጥ ነው።

የገለባ እሳቤ” ምንድን ነው?

“የገለባ እሳቤ” ማለት ወደ ደደቢት በረሃ ከወጡት 11ዶቹ መስራቾች አንዱ የነበረው “አስገደ ገብረስላሴ” ሰለ ገለባ እሳቤ እንዲህ ይላል፡

“መለስ እጅጉ ጨካኝ ሰው ነበር። አንድ ጊዜ አብዛኛዎቹ የማሌሊት ከፍተኛ ታማኝ ካድሬዎች ተሰብስበው ሲወያዩ፤ ከእንግዲህ ወጣቱን ማታገል ይበቃል፤ ከአንድ ቤት ከ2 እስከ 6 ከዛም በላይ ወጣት ታግሏል። በየቤቱ የቀረ ጥቂት ወጣት ካፈስነው/ከቤተሰብ ነጥቀን ካታገልናቸው/ ወላጆች ባዶ እጃቸው ይቀራሉ የሚል ተቃውሞ መጣ። መለስ የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነበር።

“አሁን ያለን ሠራዊት ወታደራዊ ሳይንስን አውቆ የሚዋጋ ቢሆን ኖሮ በቂ ነበር። ነገር ግን አሁን ያለው ሠራዊት ዝም ብሎ እንደ ገለባ እየተቃጠለ ጠላትንም እያቃጠለ መጨረሻ ተቃጥሎ ይቀራል። ህ.ወ.ሓ.ት. ም ትቃጠላለች፤ስለሆነም ያለን ገለባ ተቃጥሎ ከማለቁ በፊት እሱን የሚተካ ብዙ ገለባ እየሰበሰብን አሰልጥነን ማዘጋጀት አለብን። ደርግን ልናሸንፈው የምንችለው ገለባው በማብዛት ነው።” አለ። ሲል የገለባ እሳቤ ያብራራዋል።

የትግራይ ወጣቶች በ17 አመት የትግል ታሪክ “ገለባ” ሆነው የእነ መለስ ዜናዊ ልጆች የነጻድቃን እና የነ ስየ፤ የነ ጌታቸው አሰፋ፤ የነ ደ/ር አድሓኖም… ወዘተ ወዘተ…ልጆች የትምህርት ዕድል ማመቻቻ ሆነው ተቃጥለው የመኖራቸው ታሪክ ስትመለከቱ አሁን ያለው “የትግራይ ትዕወት” ታጋይ “ከገለባ እሳቤ” ዕጣ ፈንታ የተለየ ምን ይጠብቃቸዋል? የሚል ጥያቄ ብትጠይቁኝ፤

 መልሱ፡ የኤርትራ ታጋይ ወጣቶች 30 አመት ሙሉ እንደ ገላባ ተቃጥለው ገዳያቸውን “ኢሳያስን” ወደ ሥልጣን እንዳመጡት ሁሉ የወያኔ መሪዎች “ትግራይ ሪፑብሊክ” ምስረታ እውን እንደማይሆን እና ብዙ ደም የመፍሰስና የንብረት ውድመት የሚጠይቅ መሆኑን ቢያወቁም የ ህ. ወ. ሓ. ት. መሪዎች በርካታ የሆኑ “አገራዊ እና ሰብኣዊ ወንጀል” መፈጸማቸው ስለሚረዱና ያንን ወንጀላቸው ለፍርድ ስለሚያጋልጣቸው ከፍርድ ለመሸሽ ሲሉ ለዘመናት ሲያዘጋጅዋቸው የነበሩ እነዚህ ምሰኪን ወጣቶችን ወደ ጫካ በማስገባት፤ “ሴቶችን ለዝሙት ማርኪያቸው” እየተጠቀሙ ወጣት ወንዶችም እንደ ገለባ ወደ እሳት ጨምረው እንዲቃጠሉ ከማድረግ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም።

የትግራይ ወጣቶች ወደ ጭለማው ዘመን የማፈግፈጋቸው አሳዛኙ የዘመናችን ክስተት ሳስበው ይዘገንናል።

በመጨረሻ የትግራይ ምሁራንም እንደ  ““ሂትለር”

“We did not lose the world war! We were betrayed by the Jews. They are enemies of the German people. The German people are strong again. We will right the wrongs that were done to us twenty years ago in 1918”

በሚለው ሂትለር ለአይሁዶች ያስተላለፈው የራዲዮ ቅስቀሳ፤ ዛሬ ውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ምሁራንም በሂትለር መንገድ እና እሳቤ እየተጓዙ “በአማራ” እና “ኢትዮጵያ” ያላቸው ጥላቻ ወጣቱን ትውልድ እሩቅ ሆነው በመቀስቀስ “የቪክትማይዘሽን” (የተጎድተናል) ቁዘማ እያስሰሙ ወጣቶች ወደ ሗላኛው ዘመን እየተመለከቱ “ወደ ጫካ” እንዲጎርፉ በማድረገቻው ታሪክ ይቅር አይላቸውም።

ክፍል 4 ይቀጥላል…… “ሼር” አድርጋችሁ ተቀባበሉት፤ ሕዝቡ ይማርበት። አመሰግናለሁ።

ጌታቸው ረዳ

ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay)