አንተን ያብቃህ እንጂ ታጥቆ ለመነሳት….
ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com
በዚህ ወር ተደጋግሞ በዉጭ አገር በሚኖሩ ኢትዬጵያዊያን መካከል እየተደረገ ያለዉ የዉይይት አትኩሮት በጠመንጃ ሃይል ተደግፎ (Break through coup’deta ) ወደ ስልጣን የወጣ የሽምቅ ተዋጊ ሃይል፣ በጎሳ እና በቤተሰብ ዙርያ እንዲሁም በጓዳዊና ባምቻ ጋብቻ ትስስር በጥብቅ የተሳሰረ “ማፍያዊ” ቅረጽ እና ተግባር ያለዉ “የወያነ ትግራይ ነጻ አዉጪ ድርጀት መንግሥት” በታሪክ ግዴታ ወድዶም ሆነ ተገድዶ የፈቀደዉ ሥልጣን ለመያዝ በሚደረገዉ የሳጥን ድምጽ ምርጫ እና በዚህ ሂደት እንወዳደራለን በማለት ስለ ምርጫዉ ባሕሪ ድርደር ገብተዉ በተፈራረሙ ያገር ዉስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ያተኰረ ነዉ፣፣
በዉጭ ሃገር ያለዉ አብዛኛዉ የወያኔ ተቃወሚ ነኝ የሚል ኢትዬጵያዊ ከላይ የተጠቀሰዉ የምርጫ ሂደት ስምምነት አስመለክቶ ከፍተኛ ቅሬታ አለን በማለት የተቃዉሞ፣ የዘለፋ እና የጩኸት አንዳንዴም የፈጠራ ዉንጀላ እና ከፖለቲካ ዉጭ የሆነ ግላዊ እና ቤተሰብ ነክ የስም ማጥፋት ዘመቻ ያሰራጭ እንደነበረ በእየ ኢንተረኔቱ የተዘገቡት የጽሁፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፣፣ በዚህ ግልብ የሃሰት፤የግምት እና ዉዥምብር ዘመቻ የመጀመርያዉ ሰለባዎች የ “መኢአድ” አመራሮች እና ከፍተኛ የድርጅቱ ቁልፍ ሰዎች ሲሆኑ ወቀሳዉ እና ዘለፋዉ ያነጣጠረዉ በአብዛኛዉ ግን በድርጅቱ መሪ በኢንጂኔር ሃይሉ ሻዉል እንደነበርም ባለፈዉ ጊዜ ያወሳነዉ ጉዳይ ነዉ፣፣
ለሳምንታት እንደ እሳት ሲፋጅ የነበረዉ ግልብ ስሜት እና የስም ማጉደፍ ዘመቻዉ ጋብ በማለቱ በዉዥምብሩ ስበት ተስበዉ የነበሩ አንዳንድ ግለሰዎች ወደ እዉነታዉ የተመለሱ ይመስላሉ፤፤ በመሆኑም የመኢአድን መሪዎች ስም በማይገባ ሲያጥላሉና ለዘመቻዉም ሰፊ መድረክ በመፍቀድ ሲያስጯጩሁ የነበሩ የኢንተርኔት መድረኮች ትንሽ በረድ ያሉ ይመስላሉ፤፤ የኢንተርኔቱ መድረክ ከስም ማጥፋቱ ዘመቻ የተቆጠበ ቢመስልም ፓልቶክ እየተባለ የሚጠራዉ መድረክ ግን ብሶበት ፈጣሪን ጭምር የሚዘረጠጥበት መድረክ ሆኗል፤፤ ይህ ግላዲያተሮች እርስበርስ የሚተራረዱበት “ኮሊዜ” (ካላስዮም) የተባለዉ የጥንቷ ሮም የመተራረጃ የጨዋታ ሜዳ የሚመሰለዉ ፡ ዘመኑ የለቀቀብን “ፓልቶክ” የተባለዉ ገመድ አልባ የስልክ መስመር ብዙ ስላለጎበኘዉ አለፍ ብየ ግን ግላዲያተሮቻችን ሰይፎቻቸዉን እርስ በርሱ ሲያጋጩት የሚሰማዉ ድምጽ ለማዳመጥ ስል ሰሞኑን ድንገት ዘዉ ብየ ነበር፣፣ አብዛኛዎቹ የፓልቶክ መድረኮቹ ለሓሳዊ፣ለፈሪ፣ለቂመኛ፣ለትምክህተኛ፤ለተንኮለኛ እና ለጉረኛ” እጅግ የተመቻቹ መድረኮች እንደሆኑ ልብ እንዳላችሗቸዉ እገምታለሁ፣፣ እነኚህ የፓልቶክ ግላዲያተሮች፤መድረኩን ለፖለቲካ ዉይይት ሲጠቀሙበት “በሕሊና” ብቻ ሳይሆን “በአካልም በግብርም” “ኢትዬጵያ ዉስጥ” ሆነዉ እንዳሉ መስለዉ ነዉ የሚጠቀሙበት፣፣ መኢአድን ማአከላዊ ጠላት አድርገዉ በመክበብ “ጅብ” አንደከበባት “ላም” ለማስደንገጥ የማይፎሉሉት ፉከራ የለም፣፣ ደግነቱ ጅቦቹ የሚኖሩት እዚህ ለሚቷ የምትኖረዉ ኢትዬጵያ መሆኑን በጀ እንጂ፣፣
በጥሞና በመከታተል ያዳመጥኳቸዉ ሁለት መስመሮች/ክፍሎች ከነባራዊዉ ሁኔታ እጅግ የተነጠለ ስሜት የገዛቸዉ ተናጋሪዎችን ሳዳምጥ የሰላማዊ ትግል ትርጉሙም ሆነ ለትግሉ የሚቀድድ ጎዳና መንገዱ አልጋ ባልጋ ሆኖ ተነጠፎ የሚኬድበት የመሰላቸዉ አዳዲስ የዋሃንም ሆኑ ለእሩብ ዘመን ታግለናል ሲሉ ያዳመጥኳቸዉ ባለ ልምዶችም ጭምር መኢአድ የተስማማባቸዉ ስነምግባር ዶሴዎችን እንደጸጉር በመሰንጠቅ “ራዲካል ቸንጅ” ስለማያመጣ ምርጫ ዉስጥ ከመግባት “ቦይካት” (ልገማ) እንዲደረግ አጥብቀዉ ይወተዉታሉ፤፤ ቦይኮቱን ለመምራት እና በሰበቡ ለሚከተለዉ መስዋእትንት ለመካፈል በአካል መሳተፍ ይችሉ እንደሆነ ቢጠየቁ ግን ጠያቂዉን በቀይ መብራት እንዲወገድ ያደርጋሉ፤፤ፓልቶኩን የሚያዝዙት ግለሰዎች ባህርያቸዉ ሁሉ ስታዘበዉ የጥንት ምሰለኔዎች እና ባለጉልቶች ያስመስላቸዋል፤፤ይዝታሉም፤በትእቢትም የወጠራሉ፣፣ በስሜት ተገፋፍተዉ መጪዉ የመንግሥት ዙፋን ላይ የሚያወጡዋቸዉ ሰዎች እና በምናባቸዉ የሚያስወግዷቸዉ ድርጅቶች በዛቺዉ መድረክ ሲወስኑ ሳዳመጥ ሰዎቹ ምን ያህል ቅዠት ዉስጥ እንዳሉ ይገርሙኛል፣፣ መኢአድን በመቃወም “መድረክ” የተባለዉ ድርጅት ለኢትዬጵያ መንግሥታዊ ዙፋን ማብቃት እንችላለን! መኢአድ የቆመዉ እዉጭ ባለነዉ ኢትዬጵያዊያን እንክበካቤ እና የብዙ ኣመት የድጋፋችን ልፋት ዉጤት፤በመሆኑ፤ ዛሬ ግን ኢንጂነሩ ሕዘቡን ከድተዉና አሞኝተዉ ወያኔ የጻፈላቸዉ የስነምግባር ዶሴ በመፈራረማቸዉ፣“ሃይሉ ሻዉልን ለፖለቲካ ብርድ” ማጋለጥ ነዉ ሲሰነዘር አድምጬአለሁ፤፤ይህ “የፓልቶክ ግላዲያቶር” የዛተዉን ዛቻ ሳዳምጥ፡ ከመገረም አልፌ ንግግሩ በአንድ የቀልድ አምድ መጽሄት ዉስጥ ያነበብኩትን ቁም ነገረኛ ቀልድ እንዳስታዉስ የጫረብኝ ንግግር ነበር፣፣
የቀልዱን ቁምነገርንት ሳልነግራችሁ ባልፍ ግራ እንዳትጋቡ ቀልዱን ከናንተዉ ጋር ልጋራዉ፣፣ “የመወሻሸም ጣጣ” በሚል ነበር ቀልደኛዉ ተራኪ እንዲህ ሲል የተረከዉ፣- “ጥንት በገጠሩ ሕብረተሰብ ዘንድ የሌሊት ልብስ አይገዛም ነበር፣፣ ከሴቲቱ የሥራ ድርሻ አንዱ የቀን ኩታ የሌሊት ልብስ መፍተል ነዉና፣፣ከነዚህ እንስቶች አንደኛዋ ይህን ማድረግ ባለመቻሏ የባልዋን ሱሪ ለብሰዉ ነበር የሚያድሩት፣፣ በዚህ ምክንያት ጐሚ ያደረበት አባወራ፣- “ድንገት ወደ ማዶ፣ የተጮኸ እንደሆን ሱሪየን ስገፍሽ፣ ምን ይዉጥሽ ይሆን?” ብሎ ሥጋቱን ገለጸ፣፣ አባባሉ የከነከናት ሚስትም የባሏን ወንድነት መናቅዋን ስትገልጽ፣- “አንተን ያብቃህ እንጂ ታጥቆ ለመነሳት፣ እኔስ ኮተት ብየ እሞቃለሁ እሳት፣፣” አለቺዉ ይባላል፣፣
የፓልቶክ ግላዲያተሮች የመኢአድን መሪ በአሉባልታ ፕሮፓጋንዳ ለፖለቲካ ብርድ ማጋለጥ የሚቻላቸዉ ከሆነ በአካል ወደ ምደሪቱ በመሄድ መሪዉ ባሉበት ምድር ተገኝቶ እንጂ “ግላዲአቶሮቹ በሚጯጯሁበት “ኮሌዞ” ዉስጥ የሚያመጣዉ እድምታ በጊዜያዊ ሆሆታ ብቻ ተወስኖ እንደሚቀር እንዴት መገመት እንዳቃታቸዉ ለኔ እንቆቁልሽ ነዉ፣፣ ዕዉነት ለመናገር ከሆነ፤- ጸረ መኢአድ ክፍሎች ሱሪያቸዉን ለመታጠቅ ያብቃቸዉ እንጂ ይኼዉና ከወደ ማዶ “የድረሱልን ጥሪ ጩኸት ተጪሗል” (ከተጮኸ 18 ዓመት ቢሆንም)፣፣ ፈረሱም ሜዳዉም ይሄዉና ተብሏል፣፣ “ባለ ሱሪ ወንድም በሱሪዉ”፣ “በጥበብ በስልት በጥንቃቄ ዕባቡን መያዝ” የሚሉትን ታጋይ ጥበበኞችም በጥበባቸዉ፤ በተቀደደዉ በር ገፍተሮ በጥበብ ለመግባት እንዲቻል ሁሉም በየብልሃቱ የየራሱ ዘዴ ለመጠቀም እንዲመቸዉ ጩኸቱ ወደ ተበራከተበት ምድር በማቅናት በየራዲዮኑ እና ፓልቶኮቹ ነጋ ጠባ ስለ አርበኝነትና ስለ ድፍረት የሚፎክረዉ የድምጽ ማጉያና ፉከራ “ከምናብነት” ወጥቶ “ግብራዊነቱ” እንዲያሳየን ጩኸቱ ወደ ተበራከተበት ምድር ይገስግስ እንላለን፣፣ ጩሆቱን ሰምተዉ በተጨሆበት ምድር ተገኝተዉ የሕዘቡን አጋርነታቸዉ ለማረጋገጥ ሕዝቡ ባሸናፊነት እንዲወጣ የበኩላቸዉ ጥረት በማበርከት ላይ የሚገኙትን ኢንጂኔር ሃይሉ ሻዉል በሰሞኑ ቃለ መጠይቃቸዉ የተናገሩትን ንግገር ጠቅሼ ልሰናበታችሁ “ፈሪ ፖለቲካ ዉስጥ መግባት የለበትም” (ሃይሉ ሻዉል)፣፣www.Ethiopiansemay.blogspot.com