Saturday, September 11, 2021

ከገዥው አካል አስተዳደራዊ ጽ / ቤቶች የሚታዘዙ የባሕርዳር ከተማ ጎስታፖዎች በንጹሃን የትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ መፈጸማቸውን ዛሬም እየቀጠሉበት ነው! ከጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ስማይ ድረገጽ ዋና አዘጋጅ) መስከረም 1/2014 ዓ.ም

 

ከገዥው አካል  አስተዳደራዊ   / ቤቶች የሚታዘዙ የባሕርዳር ከተማ ጎስታፖዎች በንጹሃን የትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ መፈጸማቸውን ዛሬም እየቀጠሉበት ነው!

ከጌታቸው ረዳ

(ኢትዮ ስማይ ድረገጽ ዋና አዘጋጅ)

መስከረም 1/2014 ዓ.ም



ከ2013 አመተ-ፍዳ ወደ 2014 አመተ-ሲኦል የአብይ አሕመድ እና የደመቀ መኮንን ኦሮሙማ ሥርዓተ መንግሥት ገብተናል። ጦርነቱ ያለ ተጠያቂነት የፈረንጅ ክራባት እና ሱፍ በለበሱ በሁለቱ ሰው መሳይ “የወያኔ እና ኦፒዲኦ” ዱርየ መሪዎች እየተመራ ሕብረተሰብ በሁነኛ መሪ እጦት ምክንያት--ሞቱ፤ስቃዩ፤ማልቀሱ፤እየራበው መኖር እና መንገላታቱን ቀጥሏል።

 የትግሬ መንግሥት የነበረው የወያነ ፋሺስት ሥርዓት ለ27 አመት ሙሉ  “ልዩ ሃይል ፤ ፖሊስ፤ ደህንነት ፤ፌደራል ፤ የክልል ፤ ወዘተ… በሚል የተለያዩ ስሞች በመሰየም “የሕግ ትርጉም የማያውቁ” የታጠቁ የመንግሥት ደምብ ልብስ የለበሱ ጎስታፖዎች (ዱርየዎችን) አስታጥቆ በየከተማውና ገጠሮች ውስጥ በማሰማራት የኢትዮጵያን ዜጎች ቀጥቅጠው ጭለማ ውስጥ አስገብተው ከገዙት በሗላ፤ ለባለተራዎቹ ለኦሮሞዎች ከለቀቁም ወዲህ ወደ ባሰ ገሃነም ገብተናል።

እንደምን ከረማችሁ ልበል።

ከመድረክ ከጠፋሁ ቆየት ብያለሁ። አገራችን ለ30 አመት ሙሉ እንዲህ የልጆች እና የዱርየ መንግሥት መጫወቻ ሆና በመቅረትዋ  ነገረ አለሙ ስላበሳጨኝ ከመጻፍ ትንሽ ታግሼ ነበር። በኢመይል እና በስልክ ላላገኛችሁኝ ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ትንሽ በመበሳጨቴ አገሪቱ መውደቅዋ አላሰችል ብሎኝ ገለል አልኩኝ።በብስጭት ያለ ዕድሜአችን እንዳንሰናበት ብቻ ያሰጋል።

አገሪቷ በኩታራዎች እጅ ነች። መሪ ነኝ የሚለው ቅጠል በመትከል እያላገጠ የሚውል ህጻን ነው። ሥልጣን የተረከቡት አብይ አሕመድ አሊ እና ደመቀ መኮንን አሊ በኩተራነት ዕድሜአቸው ጀምረው በአሽከርነት ዘመናቸው የተማሩትን ጎስታፖዎችን አሰማርቶ ዜጎችን ከህግ ውጭ መግረፍ፤ማሰር፤ማንገላታት፤መጥለፍ፤መሰወር፤መግደል፤ድብደባ መፈጸም በከፋ መልኩ ቀጥለውበታል። ዛሬም ምንም ሊታረሙ አልቻሉም።

እንደምታውቁት ታናሽ ወንድሜ ሕግ ሲተላላፍ በመገኘቱ ሳይሆን በነገዱ ከትግሬ ዘር በመወለዱ ብቻ በትግሬነቱ አስረው እያሰቃዩት ነው። ካሁን በፊት ተከታዮቼ ይህንን መግለጼ ታስታውሱታላችሁ። ድሮ የወያኔ ታጋይ ከነበረ እማ “አንድ ነገር ይኖረዋል” የሚል ጥርጣሬ ያሳደሩ ሰዎችም አልጠፉም።ይህም ቢሆን ወያኔ የነበረ ንጹህ ሰው ሊሆን አይችልም የሚል የጅምላ ፍረጃ ያነብኩባቸው ሰዎችም አልጠፉም። ይህ እምነት ሩዋንዳ ውስጥም በደርግ ጊዜም  ተከስቷል። ቱትስ ከሆነ ‘ቱትሲ’ ነው፤ ሁቱ ከሆነ ‘ሁቱ’ ነው፤ ወደ እሚለው የጅምላ (ፕረጂደስ) ፍርድ መግባት ነው። ያም ሆነ ይህ  ለመርዳት የተባበራችሁኝ ከውጭም ከወስጥ አገር ያላችሁ ውድ የምወዳችሁ ኢትዮጵያዊያኖች እጅግ አመሰግናለሁ። በሁለተኛ መስመር ያወቅኩሃችሁ አንዳንድ ቅን የሆናችሁ የባሕርዳር ፖሊሶችም  ሙከራችሁ ባይሳካላችሁም “እጅግ” አመሰግናለሁ።

ስለ ወንድሜ ትንሽ ልበል።

ቤተሰቦቹ እንዳይጠይቁት ታግደው፤ ፍረድቤትም ይሁን ከታሰረበት “ሳባታሚት” በሚባል እስርቤት ሄደው እንዳይጠይቁት ወይንም ፍርድቤት እንዳይገኙ ታግደዋል። ሲታሰርም ሆነ ከታሰረም ወዲህ ያለ መንግሥት መጥርያና መያዢያ ሳይዙ ከቤቱ በመውሰድ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረው ካንገላቱት በሗላ ከዚያም ፍርድቤት ያለምንም የፍርድ ሂደትና ጠበቃ ሳያቆሙለት ይሄው ዛሬም “ሳባታሚት” ወህኒ ቤት ታስሮ እንዳለ በወሬ ተግሮናል። በህይወት ይኑር፤አይኑር ይደብድቡት፤አይደብደቡት የምናውቀው ነገር የለም።

ይባስ ብሎ ታስሯል ከሚባልበት ከታሰረበት እስርቤት ዘንድ ቤተሰቦቹ አዲሱን አመት እንድናየው መንግሥት ይፈቅድልን ይሆን ብለው ሲሄዱ እዚህ ልጽፈው የማልፈልገውን ሕግ የተላለፈ ድርጊት ተፈጽሞባቸው እንዳይጎበኙት ተደረገው አባርረዋቸዋል።

ይህንን በሚመለከት ከወር በፊት የኢትዮጵያ ሰብአዊ ጉዳይ ተብየው ማፈሪያው ዶክተር ተብየው ዶ/ር ዳኒኤል በቀለ ወደ እሚመራው አዲስ አባባ ኮሚሽን ጽ/ቤቱ አቤቱታ ብልክም እንመለከተዋለን ተሎ መልስ እንሰጣለን ከማለት ውጪ እንኳን ሊመለከቱት ቀርቶ የሰጠሁትን የቤተሰብ ስልክ እንኳ ደወሎ ጉዳዩ ሊያጣራ ፈቃደኛ አይደለም። እኔ ጌታቸው ረዳ እንኳን ለወንድሜ ለመላውቃቸው የመን  የነበሩ እና ጃፓን የነበሩ ዜጎች ደርሻለሁ። ለዜጎቼ በመቆም እንደ አንድ ደራሲ እና ጸሓፊ የሰብአዊ ጠበቃ ነኝ ከሚል “ከዳኒኤል በቀለ” በበለጠ ብዙ ሰብአዊ ስራ ሰርቻለሁ።

ከሃዲው እና ዛሬ የአብይ አሕመድ አሽከር ሆኖ ከጎስታፖ ሰር ጎን ቆሞ በየሚዲያው የምትሰሙት አልቃሻው እና አጭበርባሪው  ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም የዛሬ አያርገው እና ከሰብአዊ ድርጀቶች አሜሪካ ኤምባሲዎች ከሕንድ (ኒው ደልሂ) ፖሊስ ኮሚሽነሮች የተጻጻፍኩት፤ በሚዲያ ዜገች እንዲያውቁት እና በገንዘብም በስነ ልቦናም ጭምር እንዲረዱት አድርጌ ከሕንድ አገር ያስመጣሁት እኔ ጌታቸው ረዳ ነኝ። ያለ እኔ ድጋፍ ከሕንድ አገር ወደ አሜሪካ መምጣት እንደማይችል ለማየት የምትፈልጉ ሰዎች ካላችሁ የራሱ የእጅ ጽሑፍ ደብዳቤ የጻፈልኝን ኮፒውን መለጠፍ እቻለለሁ።  አሁን ስለዚህ ከሃዲ ልጅ ለማውራት አይደለም፤

ነገር ግን አሁን እነ ዶ/ርዳኒኤል በቀለ ባሕርዳር ውስጥ የሚገኙ ትግሬዎች ምን ያህል  መንግሥታዊ ሽብር፤ ፍርሃት እና ግፍ እየደረሰባቸው እንደሆነ አያውቀውም፤ እንደተረዳሁት መረጃው ቢሰጠውም ግዱም አይደለም። ዶ/ር ዳኔአል በቀለ በወያኔ ጎስታፖዎች “ሲታሰር” መታሰሩት በመቃወም ስጮህ ከነበሩት አንዱ እኔ ነበርኩ። ዛሬ ግድየለሽ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች  ኮሚሽነር ሆኖ የአብይ አሕመድ ተቀጣሪ ሆኗል። ሰለ ጽ/ቤቱ በዙ የምለው ስላለኝ በመጽሀፍ መልክ በማስረጃ  ስለማቀርበው ዛሬ ምንም አልልም።

አብይ አሕመድ፤ ደመቀ መኮንን የወያኔ ወንጀል ተጋሪዎች እና  መንትያዎች ናቸው። በሕገ -ወጥ ወይም በዘፈቀደ በፀጥታ ኃይሎች እና በግል አካላት፤ ስማቸው ባልታወቁ የታጠቁ  ቡድኖች ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ (ወያኔ ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ) በመንግስት ትዕዛዝ ሕግ ባልተከተለ የእስረኞች አያያዝ በባሕር ዳር ከተማ እርስር ቤቶች ቀጥሏል።

ከአዲስ አባባ ወደ ባሕርዳር ከተማ ዘመድ ጥየቃ የሄደች (ወላጅ አባትዋ ድሮ የታወቁ የትግራይ ከፍተኛ ሰው የሆነች ልጅ)፤ ትግሬ ስለሆነች ብቻ 6 ቀን ታስራ አብይ አሕመድ ስለሚያውቃት ተሎ እንድትፈታ ሲደረግ፤ ታስራበት ከነበረው ጣቢያ “ትግሬ ታሳሪዎች” “ጁንታ” የሚል ቅጥያ ስም ተለጥፎባቸው ደም በደም ሆነው እንደተደበደቡ በጆሮዋ ሲጮሁ እንደሰማች ዓይንዋ እንዳየች እና ይህንንም ለዶ/ዳኒኤል ጽ/ቤት በኢመይል ብጠቁመውም፤ ዳኒኤል እና አባላቶቹ ከጉዳይም አልቆጠሩትም። ዳኒኤል “እስቶክሆልም ሲንድሮም” ይዞታል።

በዚህ አጋጣሚ ሁለት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ሳላመሰገን አላልፍም። እነሱም ወዳጄ ያሬድ ሃይለማርያም እና ሃና አንዳርጋቸው ናቸው። ይህን ጉዳይ አሳውቄአችሁ ከአቅማቸው በላይ ቢሆንባችሁም ላሳያችሁኝ ክብር እና እገዛ ግን ለትብብራችሁ በጣም አመሰግናለሁ።

እንዲሁም የመረጃ ቲቪ ዋና አዘጋጅ “አበበ በለው” የወንድሜን “ተክላይ” መታሰር አስመልክተህ ስላስተላለፍከው የሃዘኔታ ስሜት እጅግ ከልቤ አመሰግንሃለሁ። ወዳጀቹ ካላችሁ የአመሰግናለሁ መልዕክቴን አስተላልፉልኝ።

ለውጥ ሲመጣ እመኑኝ፤ ጎስታፖዎች በሕግ እፋረዳቸዋለሁ። ይህ የኔ ቃል ነው! በፈጠሪ ፊት ማሃላ እገባለሁ!! የጊዜ  ጉዳይ ነው!

 ዛሬ ኦሮሙማው የሚመሩት አብይ አሕመድ እና አሽከሩ ደመቀ መኮንን “ኢትዮጵያ ውስጥ” ፖሊሶችና እስርቤት ዘበኞች “ፍርድቤት ሳያዛቸው” እስረኞችን ማሰቃየት፤ ጎብኚዎችን መደብደብና መዝለፍ የተለመደ ነው።

 ፖሊሶች ከሕግ በላይ ናቸው። ማንም ታጣቂ ከሕግ በላይ ነው። የወንድሜ ቤተሰቦች እባክህን አትጻፍባቸው “እኛን እንዳይበቀሉን” በማለት በፍርሃት ተውጠዋል። ፍርሃታቸው ተገቢ ነው። ሆኖም የጎስታፖ ስርዓት ዝም ብትልም ባትልም ስርዓቱ ባህሪ ነው እና ሰላማዊውን ዜጋ መበቀሉና ማሰቃየቱ አይቀርም። ወንድሜ ሕግ ሳይተላለፍ በትግሬነቱ ብቻ ነው እያሰቃዩት ያለው።

የጀርመን ሂትለር የፀጥታ ኃይሎች ፤ የዱር አራዊት ባሕሪ የተላበሱ ነበሩ። በነገዳቸው አይሁዶች የሆኑ ጀርመኖች የጎስታፖዎች ትኩረት ነበሩ። ዛሬም ባሕርዳር ይህንን እየተንጸባረቀ ነው። አንዳንዶቹ ሊያዩት አይችሉም፡ ነገዳቸው እነሱን ስለማያጠቃ። ሆኖም አሳምነው ጽጌ ስም ጠርተሃል ተብሎ አንድ ታዋቂ ዘፈኝ በነገዱ “አማራ” መታሰሩን ሰምተናል። ጎስታፖ ሰልጣኑን ስትነቅፍ አይወድም። ጀርምኖች ናዚን ከተቃወሙ ይሁዳ  ይሁኑ አይሁኑ ሁሉንም ይገድላል። የደመቀ መኮንንም ሆነ አብይ አሕመድ ርዕዮት ሊሻሻል፤ሊለወጥ አይችልም። ፋሺሰቶች ናቸው።

 አሳዛኙ ደግሞ  በይነመረቡን እና የማህበራዊ ሚዲያ ራዲዮ እና ቴ/ቪዥን ጣቢያዎች በጎስታፖ የአብይ አሕመድ አሽከሮች መጥለቅለቁን ስመለከት “ኢትዮጵያዊያን ከጭለማ ወደ ጭለማ እየተጓዙ ቢሆኑም ብልህ ማሕበረሰብ እንዳልሆነ የ3 አመት ጉዞ የታየ ማስረጃ ነው።”

 ደደብ ማሕበረሰብ እራሱን ለተገዢነት ሲያዘጋጅ ምንም ቅር አይለውም። 27 አመት ታግለን ዛሬም ትግላችን ከአለቅላቂዎች እንደሚሆን ከግንቦት 7 እና ኢሳት ጋር ጸብ ስገጥም ከለውጡ በፊት የተነበይኩት ትንቢት ነበር። ይኼው ከድጡ ወደ ማጡ ገብተን “ትግላችን” ተጠልፏል!

ብዙ ኢትዮጵያዊ ስለ ጀርመኖች የናዚ ታሪኮች ስላላነበበ፤ ግራ ገብቶት እመለከታለሁ። ግማሹ ደጋፊ ሆኖ አያለሁ! የአብይ አሕመድ እና ደመቀ መኮንን በፍትሕ ዘርፎች ያሰማርዋቸው ጎስታፖዎች ካለፉት የወያኔ ጎስታፖዎች በቀርጽም በባሕሪም አንድ ናቸው።  ትምህርት እንዲሆናችሁ ይህንን ልጥቀስ።

 በወያኔ ጊዜም ሆነ በኦፒዲኦ ኦሮሙማ አብይ አህመድና ደመቀ መኮንን ስርዓት እየተካሄደ ያለው አካሄድ ‘ናዚያዊ’ ስርዓት ነው።  ናዚ ጎስታፖን ባይዝ ስልጠን ላይ አይወጣምም ፤ አይቆይምም ነበር። ለምሳሌ 1933 እስከ 1945 ድረስ የነበረው “ጎስታፖ” በጀርመን ሕዝብ መካከል ፍርሃት፤ መጠራጠር እና ሽብርን አስፍኗል። ይህ የጌስታፖዎች ሕግ እየጣሱ ዜጎችን ማሸማቀቅ እርምጃ “ናዚዎችን” በብቃት አጀንዳቸውን  እንዲፈጽሙ ረድቷቸዋል።

ይህ የታጠቀ የናዚ ልዩ ሃይል እና የፍትሕ ዘርፍ (ፍትሕ ዘርፍ ቢባልም የዱርየ ዘርፍ ማለቱ ይቀላል) በአይሁዶች እና በሌሎች የአገዛዙ “ጠላቶች” ላይ ጡንቻውን ያዳበረ ነበር። የዚህ ድርጅት ዋናው ተልዕኮ ሂትለርን ( የአርያን ዘር የበላይነትን) በበላይነት አንግሶ የቀረውን የጀርመን ማህበረሰብ በሰመረለት መስመር ላይ ማቆየት ነው። በናዚ ሂትለር ወቅት ጎስታፖዎች ጀርመን ውስጥ በጣም ከሚፈሩት ቡድኖች አንዱ ሆኖ እስከዛሬ ድረስ ይታወሳል።

የናዚ አገዛዝ በጀርመን ላይ ያደረሰው ሽብር የዓለም  ታሪክ ስነልቦና ምሁራን በሰፊው ቢዘግቡትም ኢትዮጵያ ውስጥ ለ46 አመት ዛሬም እየቀጠለ ያለው ይህ ተመሳሳሳይ የጎስታፖ ሽብር የኢትዮጵያ ምሁራንም ሆኑ (በጣት የሚቆጠሩ አሉ) የታሪክ እና የስነልቦና ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች የፍላጎት ርዕስ አይደለም። አሳዛኙ ነገር ይህ ነው።

ሽብር በኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን እንደሆነ ምሁራኖቻችን ልብ አላሉትም። ይልቁንም ምሁራኖች የሽብርተኛው ስርዓት ደጋፊዎች ሆነው “በመተካካት” ተረኛ “ደጋፊ” ሆነው በመቀጠል ላይ ናቸው። ዜጎች የሽብር ሰለባ የሚሆኑበት ምክንያት ”ምሁራን ሕዝቡን በሚክዱበት ወቅት ነው።”

በጌስታፖ ኮቴ ተተክቶ ላለመሮጥ የወሰዱት እርምጃ አንድም ባህሪያቸው አለመለወጡ የሚገርም ነው። ይህ ስርዓት የወደቀ መንግሥት ነው። እንደምንሰማው አዲስ አባባ የጌስታፖ ብቻ ሳትሆን “ከናይጀሪያ ጋር የተጣመሩ ጋንግስተሮች” የባሱ አጭበርባሪዎች የተባዙባት ከተማ ሆናለች ይባላል። ይህንን ከተመስገን ደሳለኝ መጽሄት ተመለክተናል።

የጎስታፖዎቹ መንግሥት እነዚህን ዱርየዎችንና የዱርየ ፖሊሶች ወዳጆችን ማሰር እና መቆጣጠር አቅቶት ሳይሆን ህዝብን በፍርሃት መንፈስ በመቆጣጠር ሕዝቡ ለታጠቁ የስርዓቱ የጎስታፖ ሕግ አስከባሪዎች እንዲታዘዝ የሚጠቀምበት  ዘዴ ነው። በፍርሃት የተዋጠ ዜጋ ማመጽ አይችልም።

 የመንደር ጋንግስተሮችን አምጾ መቆጣጠር የማይችል ማሕበረሰብ መንግሥትን ማመጽና መቃወም አይችልም። ይልቁንም ሕዝቡ መንግሥት መኪኖቹን እና ቦርሳውን የሚነጥቁትን የመንደር ጋንግሰተሮችን እንዲያስቆምለት በመማጸን ጊዜው ሲያባክን ማየት የመንግሥት ዋናው የትኩረት ማስቀየሪያ ሰልት ነው።

አብይ አሕመድ እነዚህን ዱርየዎች (ኦ ኤል ኤፍ/ኦነግ/ ከልባችሁ ሳታወጡት እንደተቀማጭ ዱርየ ያዙልኝ እና) ሊቆጣጠራቸው የማይፈልግበት ምክንያት ልክ እንደ ሂትለር ተቃዋሚውን እንዲያጠቁለት ሊጠቀምባቸው ነው። ወያኔ ይህንን አድርጓል። እስርቤት ውስጥ ዱርየዎችን ከፖለቲከኞች ጋር በመቀላቀል ተቃዋሚዎችን ሲያስደበድብ ነበር። በምርጫ 97 ዱርየዎች አብቶብስ እንዲሰባብሩ መንግሥት ገንዘብ ይሰጣቸው  እንደነበረ የምታስታውሱት ታሪክ ነው።

የጀርመን ዜጎች በሂትለር ጫማ ሊወድቁ የቻሉት ምክንያት ዱርየዎችና ጨካኝ ሰዎችን አሰባስቦ ፓርላማውን ስለ ተቆጣጠረ ነው። መንግሥት ሲሆንም ተቃዋሚዎችን  እንዲያጠቁለት ተጠቀመባቸው።

ዛሬም  እነሆ ከገዥው አካል አስተዳደራዊ  እና የደህንነት ጽ / ቤቶች የሚታዘዙ “ስም ያልወጣላቸው” የመንግሥት ባለሥልጣኖች እና ፖሊሶች፤ በጠቅላላ የታጠቀም ፤ ያልታጠቀም ዜጎችን በማስጨነቅ ላይ ይገኛል። ጦርነቱም እንደምታዩት ወያኔ እየሳቀበት፤እያሾፈ፤እያላገጠ ነው። ወያኔ ትግራይን ለማስገንጠል የትግራይ ህጻናትን እንደ ሂትለር ልጆች በግፍ እየሰበሰበ እሳት ውስጥ ጨምሮ እያስፈጃቸው ነው። አብይ አሕመድ ደግሞ  በጦፈ ጦርነት ወቅት “መስቀል አደባባይ ሄዶ ቅጠል ለቃቅሞ እንደህጻን ፎቶግራፍ ሲነሳ ይውላል”። አንዳንዶቹ ወታደራዊ አዛዦችም ወታደሩን እና ሲቪሉን ከወታደራዊ ብቃትና ማስተባባር ስልት ማነስ እንዲሁም “ድብቅ ሴራ” ታክሎበት ምስኪን ገበሬና  ምስኪን ተራ ወታደሩን እያስፈጁት ይገኛሉ። “ተጠቂ” እንጂ “ተጠያቂ” የለም።

መሪው እና አሽከሮቹ እነሱም በፈንታቸው ጊዜአቸው ደርሶ ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ፤ ታሪክ እንዲፈሩ እና ከገዥው አካል አስተዳደራዊ ጽ / ቤቶች የሚታዘዙ የባሕርዳር ከተማ ጎስታፖዎች በንጹሃን የትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ መፈጸማቸውንና መንገድ ላይ እያስቆሙ ማስፈራራት እንዲያቆሙ እና ንጸሁን እና የዋሁን ወንድሜንም በቤተሰቡ እንዲገበኝ ያድርጉ እላለሁ።

ጽሑፉን በማሰራጨት በሃገራዊ ፍቅር ተባበሩ!

አመሰግናለሁ።

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ  ሰማይ  ዋና አዘጋጅ )