Saturday, March 21, 2009

ያገር ታሪክ ተጣራሪ፣ የክሕደት በቀል አርማ ይዞ “መሪ!”

ያገር ታሪክ ተጣራሪ፣ የክሕደት በቀል አርማ ይዞ “መሪ!”
ጌታቸዉ ረዳ
ቀደም ብየ በተለያዩ ጽሑፎቼ እንደገለጽኩት፣ ለአንድ አገር ዉርደት ወይንም ኩራት በግለሰብ ወይንም በቡድን ተደራጅተዉ ከፍተኛ ያገሪቱ መንበረ ስልጣን ተቆጣጥረዉ ላገሪቱ ህልዉና በሚነድፉት መመሪያ ምክንያት ነዉ። የአገሪቱ ህልዉናም ሆነ ከበሬታ የሚወስነዉ ግለሰብ መሪዉ ወይንም ቡዱኖቹ ላገሪቱ ባላቸዉ “የፍቅር መጠን” ነዉ። “ፍቕሪ ዑዉር” ይሉታል በትግርኛ። “ፍቅር ኡዉር ነዉ” እንደሚለዉ አማርኛዉ። ፍቅር ኡዉር ሆኖ ለምያፈቅሩት ሰዉ፣ለሚያፈቅሯት አገር የተቻለህን ፣የጠየቀችዉን እንድታደርግ የሚያስገድድ ስሜት ቢሆንም፡በዛዉ አንጻር “ዑወር ጽልኢ”/ “ኡዉር ጥላቻ” ም በተቃራኒ ሰዉን አገርን ያጠፋል።መለስ ዜናዊ ከነድርጅቱ ተከታዮች እየተከተሉት ያለዉን ጎዳና ለኢትዮጵያና ሰንደቃላማዋ ያላቸዉ ክብር ተጻራሪ የሆነ “ኡዉር-ጥላቻ” ነዉ። ከላይ የምትመለከቱት ፎቶግራፍ መለስ ዜናዊ ነዉ። ከጠረፔዛዉ በስተጀርባ ከጎን በኩል የሚታየዉ ባንዴራ “የተሓህት” የመለስ ዜናዊ ፓርቲ/ድርጅት ባንዴራ ነዉ። ፎቶግራፉ የተነሳዉ ወያኔ የተባለዉ “የባንዳ ድርጅት” ጸረ ኢትዮጵያ ሆኖ በትግራይ ክፍለሃገር ተመስርቶ “ለኤርትራ የቆመበት” 33ኛዉን ዓመተ-ልደቱን መለስ ዜናዊ በማክበር “ገባር ሽረ” (የሽሬ ጭሰኛ) በተባለዉ ሆቴል ዉስጥ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ኗሪዎችን በመሰብሰብ በወያነ ትግራይ ድርጅት “ሽፋን” ስለ ኢትዮጵያ መንበርከክ እና ከኢትዮጵያ “ኮሎኒያሊስቶች”-ኤርትራን ነጻ የማዉጣት ገድል ባሸናፊነት መዉጣቱን ንግግር ሲያደርግ ነዉ።በዚህ ስብሰባ ላይ በክብር ከባንዳዉ ጎን የተቀመጠዉ ባንዴራ የኢትዮጵያ ብሔራዉ ሰንደቃላማ ሳይሆን ከላይ እንደገለጽኩት በአፍዓበት እና ምጽዋ የመጨረሻ የሞት የሸረት ገድል ሲደረግ ፣ምንም እንኳ በአምባገነኑ መንግስቱ ሃይለማርያም ቢመሩም ኢትዮያዉያን ወታደሮች የአባቶቻችን የአሉላን የዮሐንስን የአምደጽዮን የቴዎድሮስ የካሌብ ሕዝብና መሬት ለዉጭ ቅጥረኞች አናስነጥቅም “ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አትሆንም” በማለት ደማቸዉን እንደ ጎርፍ ሲፈስስ በነበረበት በዛ አሰቀያሚ የመገዳደል ጦርነት ወያኔዎችና ሻዕቢያዎች በአሜሪካኖች ሳተላይት ፈጣን መረጃ እየተመሩ መጽፅዋን ሲይዙ ፣በኢትዮጵያዉያን ሬሳ ላይ ሲዉለበለብ የነበረዉ የጠላት ባንዴራ ይህ መለስ ዜናዊ ከጎኑ በክብር ተቀምጦ የሚታየዉ “የትሓህት” ባንዴራ ነበር። ይህ አስቀያሚ ትምክህት ስትመለከቱ አንድ የአገር መሪ ነኝ ከሚል ለይስሙላ ተብሎ እንኳ በሰማያዊ ቀለም ያጨማላቃትን ብሄራዊ ባንዴራ ከጎኑ ስታጡ እዉን ይህ ኩታራ ኢትዮጵያዊ ነዉ ወይስ “ሙሶሎኒ” እንደምትሉ ይገባኛል። በአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ፀጋየ ገብረመድህን አርአያ የብዕር ጥያቄ ብንጠይቅ “አቶ መለስ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርነት እንወቃቸዉ ወይስ የትግራይ ጠቅላይ ገዥ አድርገን?” ይህ በአንቱታ የሚጠራዉ፣ የአንቱታ ትርጉም የማያዉቀዉ፣ያገር ክብር ትርጉም ከቶ ያልተማረ “የዓድዋዉ ኩታራ” ኢትዮጵያን የምታከል ታላቅ አገር እየገዛ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ በድርጅት አርማ ለዉጦ ሲኮፈስ “ይህ የትግራይ ልጅ ተወልጄነት፣ ያንጋፋነትና የገዢነት ዕብጠት” ሄዶ ሄዶ አንድ ቦታ ላይ ሲደርስ እንደ ባሉን መተንፈሱ ባይቀርም፣ አስከሚተነፍስ ድረስ ግን የኢትዮጵያን ልጆት አንጀት ማሳረሩ አልቀረም። እያንዳንዳችሁ አገር ወዳዶች እና የ አርበኞች ልጆች ያገራችሁን ሰንደቅ በኩታረዎች ሲናቅ እና ሲወገድ የሚሰማችሁ ንዴትና የዉስጥ ስቃይ ምንኛ አሳማሚ መሆኑን ስለምታዉቁት የቁጭቱ የስቃይ መጠን ለባለቤቶቹ ላናንተ በመግለጽ ጊዜአችሁን አላባክንም። ዛሬ የሚታየዉ የወርቅ ፍልቃቂዎቹ ጉራና ትምክሕቱ፣ ተቆልሎ ሞልቶ “የማን አህሎን” ዕብጠቱ የሰማዩን ጣራ እየነካ ያለዉ ግብር፣ አስቀድሞ ከበራሃ ትግላቸዉ የደም ጥራቱ፣ የአጥንት ንጣቱ፣ ያዉራጃዊነት ወርቃማ ጉልላት ልዩነቱና የበላይነቱ በኢትዮጵያ ትግሬዎችና- በወያኔ ትግሬዎች” የታየዉ ፍጥጫ ወያነ ትግራይ “በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ” ላይ የወያኔ ባንዴራ” የበላይነት ለመስጠት የተደረገዉ ትግል ነበር። ልዩነታችን በጣም ግልጽና የማያሻማ ሲሆን “የወርቅ ፍልቃቂዎዩቹ እና የአጥንተ ንፁሆቹ”-ዓላማ “ብሔራዊ መንደርተኛ ስሜት ያጀበዉ ስልጣንን ማራመድ”-ሲሆን በኛዉ “በኢትዮጵያ ትግሬዎች”-በኩል የነበረዉና ያለዉ አቋም “ኢትዮጵያዊነትን/ሃገራዊነትን እና ኢትዮ አዊ ሰንደቃላማን” ማስቀደም ነበር።
ይህ ሆኖም ፣ድብልቅ የሌላቸዉ “የወረቅ ፍልቃቂዎቹ”፣ አስከ’ዚህ ድረስ ያደረሰዉ መንገዳቸዉ በታሪክ ማሕደር ሲፈተሽ “የተጓዙት ጉዞ”-“የኢትዮጵያ ትግሬዎችን”በማግለል፤ሰም በማጥፋት፤ ትግሬዎች አይደላችሁም በማለት፣ በመግደል፣በማሰቃየት፣በመሰወርና በመደብደብ በኢሰብአዊ ጭካኔ የታጀበ በሰዉ ልጆች (በዜጎች) ህይወት ላይ ወንጀል የፈጸሙበት ጉዞ ነበር። በወንጀል የታጀበ የጠረና የደም ጉዞ!
ኢትዮጵያንና ሰንደቃላማዋን ያከበሩና የድረጅት ባንዴራ አናመልክም ባሉት “በኢትዮጵያ ትግሬዎች” ላይ ባንዳዎቹ (ዩወያኔ ትግሬዎቹ) ያደረሱባቸዉ የግፍ ግፍ የኢድሕ/አዲዩ ታጋይ የነበረዉ የ “አሞራ” መጽሃፍ ደራሲ አቶ ግደይ ባሕሪሹም ሁኔታዉን ላላያችሁና ላልሰማችሁ አዳዲስ ባለጀሮዎች ብትኖሩ እንደሚከተለዉ ያቀርብላችሗል።
\<<…የሻዕቢያ ቅጥረኛ ወያኔም ትግራይ ዉስጥ በገጠሩ ኢትዮጵያዊነቱን ያልካደና እምነታቸዉን ያላመነዉን ገበሬ የከተማ ወዝአደር፣ምሁር “ኮራኹር አምሓሩ” “ሽዋዉያን ተጋሩ” (የአማራ ቡቹሎች ፤ሽዋዉያን ትግሬዎች) እያለች፣ የኢድሕ ታጋይ ቤተሰብ ዘመድና አዝማድ የተባሉትን ሁሉ በጠቅላላ በረና ላሙን፣በግና ፍየሉን፣ አሀያና በቅሎዉን ዶሮና የጎተራ እህሉን፣ማርና ቅቤዉን እየወረሰች ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር… >> ይላል። ከቅርብ አዋቂዉ፣ከወያኔ ትግሬዎች ጋር እጅ ለእጅ ሳንጃ ባፈሙዝ ተሞሻልቆ ኢትዮጵያዊነቱንና የሃገሩን ሰንደቃላማ ላለመዋረድ የታገለዉ ግደይ ባሕሪሹም ምስክርነት የምንረዳዉ ነገር ቢኖረ “ከመጀመሪያ እካሁን በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ነዉ።…”ኢትዮጵያዊ ስያሜ”-የትግራይም ተወላጅ እንዳይጠራበት ለረዥም ዘመን ከነበራቸዉ ስሜት በመነሳት … “ስለትግራይ ሕዝብ ወርቅነት ወዘተ..”ይሆናል አቶ ግደይ ባሕሪሹም “አሞራ”በተባለዉ መጽሐፋቸዉ “ የትግሬና በ አማራ መካከል የከረረ ጠብ ተፈጥሮ የትግራይ ህዝብ ከመሃል አገር የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እየተጋጨና እየተቧጨቀ እንዲኖር ግፋ በል…” የሚሉ የዚህን ጥላቻ አስፋፊ ስድስት ዋነኛ ሰዎችን ይጠቅሳል። የዛሬዉ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ግን ከነዚህ ተራ ዉስጥ ያሉ ሲሆኑ፣ ግዴይ ባሕሪሹም በህወሓት (TPLF) ዉስጥ በኤርትራዊነት ከተፈረጁትም መካካል አንደኛዉ ያደርጋቸዋል።”) ጸጋየ ገብረመድህን አርአያ (ክቡር ሆይ! ዝንጀሮዉ እያሳቀብን ነዉ…ይበልጥ በእርስዎ! ጦቢያ መጽሄት ሓምሌ 1989)
ኢትዮጵያና ኢትዮጵአዊነትን እየገደሉ ለኤርትራ ሲሉ የሞቱትና የቆሰሉ ለስላሳ ልብ ያሳዩት የትሓት ታጋዮችና መሪዎች ጭካኔአቸዉ በትግራይ ገበሬ ብቻ ሳይወሰን በድያቆናትና በቀሳዉስቱም ጭምር “የባዕድ ብትር”ሰንዝሮባቸዋል።ብርሃነ ገብረህይወት የተባለዉ የወያነ ሰለባ ፣ኢትዮጵያዊነታችን አንክድም ባሉ የትግራይ ድያቆናትና ቀሳዉስት የነበረዉ ግንኙነት እንዲህ ይገልጸዋል፦ “… ቅስና እና ድቁና የተቀበሉ ከ50 በላይ የሆኑ ሰዎች ታስረዉ ነበር። እነሱም ከእስራትና ከቅጣት በሗላ መታወቂያቸዉ ተቀምተዋል። ከዚያ እዚያዉ ቆይተን በ1981 ዓ/ም በግድ ወደ ግንባር ዝመቱ አሉን። …እኛ “አንታገልም፤እናንተ ታገሉ፡ እኛ ድሆች ነን፡ ገና ዳቦ አንኳን አልጠገብንም”ስንላቸዉ፡”ማን አጥንቱን ከስክሶ ሊያኖርህ ፈለግክ?” በማለት በተለይም “ቢሄን” የተባለ ታጋይ አፈር በእጁ ከመሬት ቆንጥሮ በማፈስ ወዳፍንጫችን አስጠግቶ እንድናሸት አስፈራራን። በአገራችን መኖር ካልቻልን ተሰድደን እንሄዳለን፡ ይለፍ ብቻ ስጡን ስንል ስትፈልጉ በሰማይ ሂዱ እንጂ አይሰጣችሁም፡ እያሉ ያፌዙብን ነበር።“ታዲያ የት እንድረስ?” ስንላቸዉ “የራሳችሁ ጉዳይ!ከፈለጋችሁ አገራችሁን ነፃ አዉጡ። ነፃ አናወጣም የምትሉ ከሆነ ግን የዚህችን “ምድር በረት” አትረግጡም። አሉን። “ከማን ነዉ ነፃ የምናወጣት?” ደርግም ኢትዮጵያዊ ነዉ እናንተም ኢትዮጵያዊያን ናችሁ።” ስንል “ከበስተጀርባችሁ የሆነ ነገር አላችሁ!” በማለት ማሰር እና መቅጣት ጀመሩን …(1500 እንሆናለን)።ወላጆቻችን ታሰሩ። የእርሻ ማሳዎቻችንም ተወረሰ። ቀንደኛ አድመኞች ናችሁ በተባልን በተወሰንን ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት ተፈጸመብን። ከ6 ወር አስከ ዓመት በእስራትና በግርፋት ተቀጥተናል። ክንዶቹ ለረዥም ጊዜ በቀጭን ጅማት ነገር በመታሰራቸዉ ምክንያት ጣቶቹ ደም አስከ ማንጠባጠብ የደረሰ ጓደኛችንም ነበረ። በግርፋት አንድ እጁ እና አንድ እግሩ ሽባ የሆነ ጓደኛየ ሃለቃ ሓዲሽ የባላል። ቢዚያን ወቅት ‘ሙሹሮችና ካህናት’ ሳይቀሩ ‘በህማማት ጊዜ ከቤተክርስትያን’ ተወስደዉ ከሽማግሌዎች በቀር ሁሉም ታፍሶ ተወሰደ። ለመሸሽ የሞከረዉን እንደጅግራ እያሯሯጡ በጥይት ያሳድዱት ነበር። ይህ ሁሉ የተፈጸመዉ የካቲት ወር 1981 ዓ.ም ጀምሮ ማለት ነዉ።ትግራይ ነፃ ከወጣች በሗላ ማለት ነዉ:: ከዚያ… ሰዉ እንደ አዉሬ በአካባቢዉ እየተበተነ በአካባቢዉ በቀን ሰዉ የሚባል አይታይም ነበር። እነሱም እንደ ጅግራ እያደኑ ይዉላሉ፤መሬታችንም ለታጋይ ቤተስብ ታድሎ የምንቀምሰዉ የምንልሰዉ አልነበረም።ከቀበሌ ወደ ቀበሌ የሚያስተላልፉ የነሱ ካድሬዎች ካዩን ጥይት ይተኩሱብናል፤ የተኮሱብን ጥይት አልመታንም እንጂ ቁጥር የለዉም። ከዚያ በሗላ እየተንከራተትንና እየተራብን ቆይተን ህዳር 21/1983 ዓ.ም ገረዳ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ለአቶ በርሄ እህል ስንሸከምላቸዉ ዉለን፤ቤት ገብተን ገበታዉ ቀርቦ እህል ልንበላ ስንል ቤቱ ተከበበ። የማይታወቁ ታጣቂዎች ናቸዉ። ከተሰበሰበዉ ሰዉ እኔን ጠሩኝና ዉጣ አሉኝ። መጀመሪያ እህል ይብላ እና ዉሰዱት ብለዉ የቤቱ ባለቤት ቢጠይቁም “አስቸኳይ መልዕክት ስላለን ነዉ፤አሁን ይመለሳል” ብለዉ ወሰዱኝ።ሌሎችም ከያቅጣቻዉ ተሰበሰቡ።ወደ 5 እንሆናለን። ሁላችንም በስብሰባ ላይ የምንከራከራቸዉ ነበርን። “እነዚህ ካልጠፉ ወጣቱ አይታገልም፤በታኞች ናቸዉ፤ከደርግ ለይተን አናያቸዉም” በማለት ከዚያ በፊት እንዳጠፏቸዉ ወጣቶች እኛንም ለማጥፋት ተዘጋችተዉ እየወሰዱን ሳለ፤ እርስ በርሳችን እንነጋገር ነበር። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ይሆናል።…ጫካ ነዉ፤ እኛ አናዉቀዉም። ኢሳ የሚባል በረሃ ነዉ። ምን ይሻላል? ለመሞት ለመሞት እዚሁ እንሙት እየተባባልን እንደገና ጉዞ ጀመርን። አልፎ አልፎ ነዉ እንጂ እኛን ባንድ ላይ አይወስዱንም ነበር። አንድ እዚህ፤ አንድ ደግሞ ራቅ አድርገዉ ሊወስዱን ከፊት ያለዉን ገፍቼ ሸሸሁ። ቁጥር የሌለዉ ጥይት እላየ ላይ ዘነበ። ፀጉሬ ላይ ትንሽ ነካኝ እንጂ አልመታኝም። አምልጬ ሕግ ያለ መስሎኝ ወደ ዋናዉ አለቃ ሄጀ “የማይታወቁ ታጣቂዎች ሌሊት መጥተዉ በደል አደረሱብኝ፤ በነዚህ ሰዎች ላይ ክትትል ይደረግልኝ፤ከየት እንደመጡ ማን እንደላካቸዉ ይጣራልኝ”ብየ አቤቱታ ሳቀርብ፡ “እኛ እናጣራዋለን፤ እንከታተላቸዋለን” የሚል መልስ ሰጡኝ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ጥር 23 ቀን 1981 ዓ.ም ሥራ አድሬ ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ወደቤቴ ስሄድ……..(ለመኖርያ ቤት ፤ቤት በደቦ ስንሰራ) ደክሞኝ እዚያ አድሬ ነበር። አባቴ ሞቷል..እናቴ አለች፤ የእናቴ ትንሽ መሬት ነበረችን፡ ቤቴ እንደደረስኩ በረቱን ከፍቼ ለበሬዎቹ ድርቆሽ ልሰጣቸዉ ስል….የ.ማላዉቃቸዉ ሰወች ብትንትን ብለዉ ተኝተዉ አገኘሗቸዉ። ቤቱ ተከቦ ነዉ ያደረዉ። እናንተ እነማን ናችሁ? ስላቸዉ አንዱ እያናገረኝ ሌላኛዉ በሰባት ጥይት መታኝ። በሆዴ እና በአንጀቴ ላይ ደሙ እየተንዠቀዠቀ ሲፈስ እናቴ እንዳታይና እንዳትጮህ ውስጥ ግቢ አሏት። ከዚያ በሗላ “እግሬና እጄን አንጠልጥለዉ ጎትተዉ ጫካ ዉስጥ ጣሉኝ”። አንጀቴ ተበጥሷል። እንጀቴ ይታያል፡ቅጠላቅጠል አልብሰዉኝ ተሰወሩ…” ይህ ከላይ ያነበባችሁት የተለያዩ ምስክርነቶች ፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተደረጉ ግፎች ናቸዉ። ዛሬ መለስ ዜናዊ ያ ሁሉ ግፍ “በኢትዮጵያዉያን ትግሬዎች” ላይ ያለ ምንም ተጠያቂነት ሲፈጽም እና ስያስፈጽም ቆይቶ፣ የህዝብ ሥልጣን ከነጠቀ በሗላም በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ያገሪቷን ሰንደቃላማ ከማክበር ይልቅ ከጎኑ እንዳትታይ በማስወገድ ወይንም አርቆ በማስቀመጥ በምትኳ የራሱን የድርጅቱን ባንዴራ እንደ ብሔራዊ ሰንደቃላማ በመቁጠር እጎኑ በማኖር ብበቱ ስር ታቅፎ በፎቶግራፍ ቀራጮች አማካይነት ሆን ተብሎ የድርጅቱ ባንዴራ በታሪካዊ የፎቶግራፍ ማሕደሮች እንዲቀረጽ በማድረግ የ“መጪዋ” “ሪፑብሊካዊት ዓባይ ትግራይ” /የታላቁዋ ሪፑብሊካዊት ትግራይን ብሄራዊ ሰንደቃላማ እንደምትሆን እና ወያኔ ወልዳ ወያኔ ያሳደገቻቸዉ “ሰገናት/ብርኪ ሰገናት” የተባሉ “ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶች” እንዲሰግዱላትና “ኢትዮጵያዉያን የትግራይ አርበኞች”አባቶቻችንና እናቶቻችን የተዉልንን የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ከእነዚህ ታዳጊ ህጻናት ሕሊና ዉስጥ እንድትፋቅ እየተደረገ ያለዉ “ተሓህት ዉስጥ የተሰገሰጉ የባንዳዎች” ሴራ መሆኑን የትግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያዉያን በአጽንኦት እንድትረዱት ሳሳስብ፤
በተጨማሪም ካሁን በፊት ታጋያይ አሉላ ካሳ የተባለ የወየነ ትግራይ ታጋይ “ክርቢት” ተብሎ በሚጠራዉ የወያኔ መቺ ሃይል ተምድቦ እየሰራ በነበረበት ጊዜ፤ ጥበቃ በላላባቸዉ ከተሞች ቡዱኔ ተሸሽጎ በድብቅ ወደየ ከተሞቹ ዘልቆ በመግባት፤ የኢትዮጵያን ሰንደቃላማን በማዉረድ የወያኔን ባንዲራ ሰቅለዉ ይሰወሩ እንደነበር ከድምጺ ወያነ ትግራይ ራዲዮ ጋር ያደረገዉ ቃለ መጠይቅ አቅርቤላችሁ እንደነበረ ስታገናዝቡት፤ መለስ ዜናዊ ዛሬ ከጎኑ ያስቀመጠዉ ባንዴራዉ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለዉን ንቀትና ለድርጅቱ ባንዴራ ያለዉ ፍቅርና አክብሮት ምን እንደሆነ እላይ ካቀረብኩላችሁ ፎቶግራፉ መረዳት እንደምትችሉ ተስፋ አለኝ።
ጌታቸዉ ረዳ መጋቢት 2002 ዓ.ም (March 19, 20092009) www.Ethiopiansemay.blogspot.com