Friday, August 7, 2020

ስላለፈው ጽሑፌ እንዳብራራ ለጠየቃችሁኝ አንባቢዎች መልስ ይኼው! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) Friday, August 07, 2020



ስላለፈው ጽሑፌ እንዳብራራ ለጠየቃችሁኝ አንባቢዎች መልስ ይኼው!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)
Friday, August 07, 2020
ባለፈው ስለ ቅኝ ገዢነት አስመልከቼ የለጠፍኩት አንዳንድ ሰዎች ግራ የገባቸው ይመስላል፡ ቅኝ ገዢነትን አጭር ትርጉሙ ጥገኛ የሆነ ክልልን መፍጠር ነው። ይህንን ቆይቼ አብራራለሁ። ትግሬዎች እና ኦሮሞዎች የሚለው መጠሪያ ስጠቀም ያልተስማማቸውም አሉ። ፖለቲካ ኮሬክትነስ የሚባለው “ሽፍንፍን” እየተጠቀሙ ወያኔዎች ባስተዳደሩት ዘመን “ትግሬዎች አልተጠቀሙም ወይንም ኦሮሞዎች አልተጠቀሙም የተጠቀሙት ጥቂቶች ናቸው እያሉ የሚጃጃሉ አሉ። እኔ ከነዚህ እለያለሁ። አንድ ማሕበረሰብ ተጠቀመ ስንል በብዙ መልኩ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ ቅድሚያ ዕድል ያገኘ ማለት እንጂ 6 ሚሊዮን ከሆነ 6 ሚሊዮን ተጠቀሚ ነው ማለት አይደለም። ሰው ሲሞት ሁሉም አይሞትም፤ ጦርነት ሲገባ ሁሉም አይገባም፡ ሲጠቀምም እንደዚሁ። ኦሮሞ እና ትግሬው በጸረ ኢትዮጵያ ቅኝት የተቃኘው ሥልጣን በመቆጣጠራቸው በታሪካችን እንደ ዛሬው ዘመን ትግሬዎችም ሆኑ ኦሮሞዎች ከማንኛውንም ማሕበረሰብ በገሃድ ኢ-ህጋዊና በሕጋዊ መንገድ ተጠቃሚዎች ናቸው ብየ እሞግታለሁ። ስለዚህ ትግሬዎችም አሮሞዎችም በዚህ ይገለጻሉ።

 ባለፍው ጽሑፌ አንዳንድ ሰዎች “ቅኝ ገዢነት” ሥልጣንን ለተቆጣጠሩ  ለትግሬዎች (በድርጅታቸው በወያኔ በኩል) እና ኦሮሞዎች (ብዙ ስም በሚጠሩ ግን አንድ  ይነት ፍላጎት ባላቸው  ድርጅቶቻቸው በኩል) ሥልጣን ተቆጣጥረው የውስጥ ቅኝ ገዢነታቸውን እንዴት አንደተጠቀሙበት ለወደፊቱ በማሳትመው መጽሐፍ እንደሚገለጽ በለጠፍኩት ጽሑፍ ላይ ያልጣማቸው አንዳንድ ሰዎችን በመልእክታቸው አንብቤአለሁ።

የውስጥ ቅኝ አገዛዝ የሚባለው ጽንሰ ሓሳብ ለመጀመሪያ የተጠቀመበት ሩስያዊው የታሪክ ምሁሩ ‘ልዩቸቭስኪ’ ነው የሚሉ አሉ ሆኖም ብዙ ጸሐፍቶች ደግሞ ቃሉ በለኒን (አሊያኖቪች) ነው ይላሉ። ያም ሆነ ይህ የአፍሪካ ምሁራን ይህንን ቃል መቸ መጠቀም እንደጀመሩ በዳሰስኳቸው አንዳንድ ምልክቶች የሚያሳዩት “በሓምሳዎቹ” እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ይህንንም አፍሪካ ውስጥ ይበልጥ በግሀድ ለመድረክ ውይይት ያቀረበው “የዳች ዘር” ያለበት ደቡብ አፍሪካዊው የሰብአዊ መብት ጠበቃው “ማርኮድ  ልዮፐርድ” (1957) እንደሆነ የነገራል።

‘ሊዮ’ ይህንን ውይይት ያቀረበው “የደቡብ አፍሪካ የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ለመመርመር” በተካሄደው እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 16 ቀን 1957 ሂደዲ በተባለ አዳራሽ ተገኝቶ እራሱ “የደቡብ አፍሪካ የዘር ግንኙነት ምክር ቤት አባል” በሆነበት ማሕበር ውስጥ (1957) በተደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ያቀረበው ጥልቅ ምርምር እንደነበር ብዙዎቹ ያትታሉ። ያም ሆነ ይህ ቅኝ ገዢነት በተለይ ‘የውስጥ ቅኝ ገዢነት’ ለ29 አመታት እስካሁን ድረስ እያየነውም ቢሆን ልናውቀው ባለመቻላችን እጅግ የምንገርም ድንዙዝ ማሕበረሰቦች መሆናችንን ያሳያል።

ከዚህ አልፎም አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቼም በጣሊያን እንዳልተገዛን ተቃውሞአቸውን ጽፈውልኝ አንብቤአለሁ። ይህ ግን ከስሜት እና አገራዊ ብርታትነት /አልበገርም ባይነት የመነጨ እንጂ ከእውነታው አይገናኝም። ጣልያን ወደድንም ጠላንም እየተዋጋንም ቢሆን ለ5 አመት አስተዳድሯል፤ ጎዳናዎች ቀይሶ፤ ድልድዮች ገንብቶ፤ ዳኞችን አሰማርቶ፤ ሴት እናቶቻችንን አግበቶ “ደቅሎ፤ ገዝቶናል። ከፊሉ ግዛታችንና ሕዝባችንን ከነ ባሕር ወደቦቻችን ተቆጣጥሮት ነበር። ያገሪቱ ታላላቅ መኳንንቶች አስሮ ወደ ጣሊያን አገር አስሮ አሻግሮአቸዋል። ጎዳናዎቻችን፤ገበያዎች፤መናሃርያዎች በጣልያንኛ ስም ተሰይመው ዛሬም እየተጠሩበት እና እየጠቀምንባቸው አንገኛለን።

 የቅኝ ግዛት ቅሬቶች ዛሬም ህያው ሆነው እያተራመሱን ነው። ሁሉም የቅኝ ተገዢዎች ሲገዙ ላለመገዛት ያደረጉዋቸው ጦርነቶች ሁሉ ላለመገዛት የተደረጉ ጦርነቶች እንጂ “አልተገዙም” ማለት አይደለም። ሳይዋጋ የሚገዛ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ላለመገዛት ዳተኛነትን ያሳየ በታሪክ ያለ አይመስለኝም። ሱዳኖች… አልጀሪያ… ወዘተ… ከእንግሊዝና ከፈረንሳዮች ቅኝ ገዢዎች መራራ ትንቅንቅ አካሂደዋል፤ተዋግተዋል፤ግን በቅኝ ገዢዎች አልተገዛንም ሊሉ አይችሉም።  “ዘ-‘ሬፕ’ ኦፍ ኢትዮጵያ” የሚለው መጽሐፍ ስንመለከት አርበኞቻችን ከጣሊያን ጋር ሲዋጉ እጅ ስጡ ሲባሉ “ንጉሳችን ቆመን እንጂ ተምበርክከን እንድሞት አላዘዘንም” ብለው አስገራሚ ፍልምያ አድርገዋል በእምቢተኝት ተዋድቀው ታሪክ ያነሳቸዋል። ያ አገር ወዳድ አልበገሬነት እንጂ “ጣሊያን አላስተዳደረም/አልገዛንም ማለት አይቻልም” (“ብሪፍ” ኮሎኒያሊዝም ጎብኝቶናል)። ሱዳን፣ አልጀሪያ ወዘተ ወዘተ…ያደረጉት ኢትዮጵያም እንደዚሁ። ማንም ቅኝ ገዢ “ተደላድሎ አይገዛም”፡ በከፊልም ሆነ በሞላ ግዛት ተቆጣጥሮ መዋቅሩን አፈራርሶ፤ መሪዎችን አሳድዶ ካስተዳደረ “ቅኝ” አደረገ ማለት ነው። ይህንን ለማባርራት ሰፊ ሐተታ ይጠይቃል። ስለ ወዳጆቼ ተቃውሞ እዚህ ላቁም እና የቅዥ ገዢነት እና የውስጥ ቅኝ ተገዢነት ትንሽ ላብራራ።

አንድ አስተያየት ሰጪም ትግሬ በመሆኔ የቃሉ አጠቃቀም እንዳላወቅኩት ፈገግ እንድል አድርጎኛል። ትግሬ በመሆኔ አማርኛን ከማወቅ ያገደኝ ነገር የለም። ትምህርት ቤት አማርኛ ተምሬአለሁ። መጽሐፍቶችን አንብቤአለሁ። ብዙ ትግሬዎች አማርኛ ከሚናገሩ ተናጋሪ አማራዎች የበለጠ ችሎታ ያላቸው ትግሬዎች እንዳሉ ይህ ወገን የሚያውቅ አልመሰለኝም። ቋንቋ ዘርን አይለይም’ ቋንቋ ትምህርት ነው፤ እውቀትና ምርምር ነው። ወዳጄ በዚህ ይገባዋል ብየ እገምታለሁ። አሁን ስለ ጽንሰ ሓሰቡ ትንሽ ልበልና ልደምድም።

የቅኝ ግዛት ጽንሰ ሓሳብ ምንነት ከማሳየቴ በፊት “ቅኝ” የሚለው ቃል ምንድነው? ቅኝ ማለት ቃኘ ከሚል የመጣ ነው ‘ቃኝቶ’ የጎበኘውን ያለመውን ያጠናውን የዳሰሰውን፤ “በልቡ ያለመውን/የተመኘውን” መሬት፤አካባቢ፤ ባሕር፤ ሃብት፤ ሕዝብ፤ ድምበር ተቆጣጥሮ “ማቅናት” “መግዛት” ማለት ነው። ቃኚ/ቅኝ/ቃኘው… የሚለው ብዙ ትርጉም አለው። ላሁኑ በዚህ ቅኝ በሚለው “በቁጥጥር” ትርጉም እንሂድ።

ትግሬዎች የአማራና የሌሎች ህዳጣን ማሕበረሰቦችን ለም መሬት  ፤ በጠመንጃ አስገድዶ ለምሳሌ በጎንደር በኩል “ወልቃይት” እና በወሎ በኩል ያሉ ለም መሬቶችን ወደ ትግራይ “ክልል” አስገብቶ ያጠቃለለበት ባሕሪና ያንን ተከትሎ “ዘርን” የማስወገድና የማጽዳት የተከተለው ተግባር “ቀጥተኛ የቅኝ ገዢነት” መገለጫ ነው። እዚህ ላይ የተነጠቀው/ቅኝ ውስጥ የገባው ለም መሬት/ ተጠቃሚው ማነው? መልሱ “ትግሬዎች”። ምክንያቱም መንግሥታቸው የትግሬ ስለሆነ/ ከታች እስከ ላይ ትግሬዎች ስልጣኑን በተዋረድ ስለተቆጣጠሩት ለሕዝባቸው ለትግራይ ሕዝብ ከጎንደር መሬት ነጥቀው እንዲጠቀሙ አድረገዋል! የትግራይ ሕዝብም “በደስታ ተቀብሎ እያረሰ እየተጠቀመ ይገኛል! አምቢ የወንድሞቻችን እህቶቻችን መሬት አንወስድም አላለም። ያለበት ወቅት ካለም ንገሩኝ።  ምከንያቱም መንግሥታዊ መዋቅሩ ከላይ እስከ ታች ትግሬዎችና ኦሮሞዎች ተቆጣጥረውታል:: አሁን ማን ተካቸው? ኦሮሞዎች! ኦሮሞዎችና ትግሬዎች በተስማሙት "ቅርምት" ኦሮሞዎች ያልነበራቸው ሰፊ ግዛት “ኦሮምያ” የሚል ስያሜ ሰጥተው የሌሎችን አካባቢዎች ውጠው ለ29 አመት አሁንም ሰፊ ግዛት ተቆጣጥረው ነባሩን ሕዝብ እያስወጡ አካባቢውን በቅኝ ይዘውታል! ኦሮሞዎችም፤ ተነጥቆ የተሰጣቸው መሬትም ሆነ ላቲናዊ የመጻፍያ ቋንቋ ተቀብሎ “ኦሮሚያ” የሚለው የክልል ስያሜ ተቀብሎ አጽድቆታል። እምቢ ስሊ አልሰማሁም።

ሁለቱም ትግሬዎች እና ኦሮሞዎች ለ29 አመት ትናንትም ዛሬም “የያዙት ኢ-ሕጋዊ መሬት በይዞታቸው ለማቆየት ሲሉ” ምንም ቢጣሉም በባሕሪና በዓላማ አንድ ናቸው፡ አብረውም እየሰሩ እያየን ነው።  ለዚህ ነው አንድን ቦታ ወይንም ሕዝብ “ቅኝ” ማድረግ  የገዢዎች አይነተኛ ባሕሪ ነው የምለው።

ቅኝ ገዢዎች ለቁጥጥር በሚቃኙት (በሚመኙት) ሕዝብም ሆነ መሬትና ባሕር ወይንም ድምበር  ወደ ራሳቸው ግዛትነት ወይንም ጠቀሜታነትን ማስገዛትን ያካትታል፡፡ የቅኝ ገዢነት ዓላማ በስራቸው እና በሰዎቻቸው የሚተዳደር ጥገኛ የሆነ ክልልን መፍጠር ነው። ያንን “ለምን ዓላማ? ብለን ካልን ዓላማው “ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ  አውታሮችን” መዳፋቸው ውስጥ ለማስገባት ነው። ሥልጣን እና የሃብት ቁጥጥር የቅኝ ገዢዎች “መነሻዎች” ናቸው።

ውስጣዊ ቅኝ ግዛት (ኢንተርናል ኮሎኒያላይዘሽን) ማለት በክልላዊ ማዕቀብ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ልማት ያልተመጣጣኑ ተፅእኖዎች ማከናወን ማለት ነው። የትግሬዎች መንግሥት እና ኦሮሞዎች ተዳብለው ባስተዳደሩት የ29 አመት ጥምር ሥርዓት ሁለቱ ነገዶች “ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ “ሰፋፊ ድምበሮችን ወደ እነሱ አጣቃልለው አዲስ የክልላቸው ቅርጽ ቀይሰው፤ አዲስ ባንዴራዎቻቸውን ፈጥረው “ዛሬ የምናያቸው “ሰፋፊ ክልሎቻቸው” ካሁን በፊት በታሪክ ያልነበሩ ናቸው። ይህን ተረዱልኝ። ክርክሬ ከዚህ የመነጨ ነው።

ለ29 አመት ያየነው እና አሁንም ያለው ህይወት በአገራችን ሰፊው ማህበረሰብ ውስጥ አናሳም ሆነ በክልሉ የተጠቃለሉ ነገዶች መበዝበዝ፤ማባረር፤መግደል፤ ዘር ማጥፋት፤ንብረታቸው እንዲወድም እና እንዲዘረፍ ተፈጽሟል። ለ3000 አመት እንገዛችሗለን እያለ በግልጽ የሚዝቱብንን የአብይ አሕመድ አማካሪ "ሌንጮ ባቲ" የዚህ መገለጫ አይነተኛ ሰው ነው። አሁን የታየው ጭፍጨፋ ይህ ሁሉ ሊፈጸም አንቀሳቃሹ በተረኛነት የመግዛት ስሜት የተጠናወታቸው ስልጣን ላይ ያለው በውስጥ ቅኝ ገዢ ስሜት እየተነዳ ያለው የኦሮሞው አብይ አሕመድ ቡድንም ሆነ ከሥልጣኑ ተባርሮ ወደ መቀሌ የሸሸው ቡድን የጋራ ወንጀልና የውስጥ ቅኝ ገዢነት ፖሊሲ ያስከተለው ውጤት ነው።

ለ29 አመት በኢፍትሃዊነት በመመራት ምክንያት “ያልተመጣጠነ ልማት” በአገራችን ተካሂዷል። የጎንደር አማራ በወልቃይት ጸገዴና በተወረሩ መሬቶች በትግሬዎች ቅኝ ገዢነት የተካሄደ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተካሁዷል ብለን እኔም ሆንኩ አገር ወዳዶች እስኪሰለቻችሁ ድረስ አውነቱን ተናገሬአለሁ። ይህ ወንጅል ከቅኝ ገዢነት በጣም የባሰ ነው። ይህ የቅኝ ገዢነት “ወንጀል” ምን ብላች እንደምትጠሩት ንገሩኝ እና “ቅኝ ገዢነት” የሚለው ልሰርዝ።

በሚገርም ሁኔታ የአብይ ደጋፊዎች እና የወያኔ ደጋፊዎች “ኦሮሞዎችና ትግሬዎች” የሚከተሉት የቅኝ ገዢነት ጎሳ/ነገዳዊ/ ሕገ መንግሥት እንዲቀጥል እየታገሉሉት ያለው የውስጣዊ ቅኝ ግዛት ጽንሰ-ሀሳብ እንደ ገንቢ አድርገው ይመለከቱታል።ይህ የደደብ ማሕበረሰብ አመላካች ክስተት ነው። በተለይ ሁለቱም ነገዶች እንዲህ የሙጥኝ ሚሉበት ምክንያት በጂኦግራፊያዊ ቅርበት ያላቸው አካባቢዎች ብዙዎች ወደ እነሱ ክልል አስገብተው “ውጠዋቸዋል”። ስለዚህ “ያደመቁዋቸው የቅኝ ግዛት መስመሮቻቸውን” ላለመልቀቅ ዛሬም እየታገሉ ነው። ትግሬዎች እና ኦሮሞዎች ሁለቱም የተጓዳኝ አካባቢ ለም መሬቶችን “ውጦ የመወፈር”  ወንጀል ላይ ተጠቃሚዎች ናቸው። 

አገራችን ውስጥ በኒዮኮሎኒያዊነት እና በውስጥ የቀጥታ ቅኝ ግዛትነት ያለው ልዩነት የብዝበዛ ምንጭ በጥምረት በመካሄድ “በባህል ወረራ፤በሞራል ዝቅጠት” የሚቃኝ ክስተት ሕያው ሆኖ አስጊ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ በቅኝ ገዢነት ፖሊሲ ስለተመራን ትክክለኛውን የታሪክ መጠምዘዣው ምልክቱን “ስቶ” ወደ እልቂትና መፈራረስ የሚወስደውን አቅጣጫ ሄዷል። በቀድሞው ጊዜ መቆጣጠሪያው ፖሊሲው የሚመነጨው ከሀገር-ግዛት ውጭ ሲሆን በኋለኛው ደግሞ ከውስጥ ነው። ይህም እነሱ “ኬኛ” የሚሉት የተጓዳኝ አካባቢ ለም መሬቶችን “ውጦ የመወፈር” አባዜ የቅኝ ገዢነት ርዕዮት ነው የምለው ለዚህ ነው።
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ