Tuesday, June 26, 2018

ትናንትም ዛሬም ነገም ለወደፊቱም የገዳያቻን የሻዕቢያ ባንዴራ ብንሞትም አናውለበልብም - ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

ከአንባቢዎች የተሰጠ አስተያየት።
1- አቶ ጌታቸዉ ምን እየተሆነ ነዉ? ጠ/ሚኒስትሩ የአፈወርቂን ጉልበት እስማለሁ የሚያሰኝ ሁኔታ ባለመፈጠሩ አገርና ወገንን የማያሳፍር ስራ ባይሰራ መልካም ነዉ። መሪ እንጂ ፓስተር አይደለም ስለ ኤርትራዉያን የሚደለቀዉ ከበሮ መስመር እየሳተ መሰለኝ ይባስ ብሎ ዛሬ ግርማ ካሳ ፓስፖርት ተሰጥቷቸዉ እየገቡ ይፈንጩበት የሚል ጥቆማ አድርጓል አማርኛ የሚችሉ መርዘኛ ኤርትራዉያን ሰሞኑን ይህንን በማራገብ ጉዳዬ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲፀድቅ ያደርጉታል። ነገ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት የኢሳይያስ አፈወርቅ ልጂ እንደሚሆኑ አትጠርጥር።
የዚህ ነገር አካሄድ አልገባኝም አንድ መሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር ለመቀበል አየር ማረፊያ ድረስ ምን ያስኬደዋል? ኤርትራዉያን የልብ ልብ ተሰምቷቸዉ እንዴት በንቀት መሰለህ የሚያዩን ለምን በታሪኳ ላይ ጠባሳ ጥለዉ ያልፋሉ? እነዚህ ሰዎች ትላንት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲፈጁ ከርመዉ በእርግጥ ዛሬ ይህ የክብር አቀባበል ይገባቸዉ ነበር? ያሳዝናል እዚህ ሁሉ ዉስጥ የከተተን ህወሃት ነዉ። በሩ ድርስ መጡለት ይህ ታላቅ አገር በማይረቡ ዜጎች ላይ መዉደቁ ያሳዝናል። ምናልባት እኔ ባየሁበት መንገድ ላታየዉ ትችላለህ። በእርግጥ አዝኛለሁ። የሚቀጥለዉ ትዉልድ ጉዳዩን እንዳያነሳዉ የሁሉም ነገር ፋይል በአብይና ከጀርባዉ ባሉ ሀይሎች ተዘግቷል ወደባችን ባስተማማኝ ሁኔታ ለሻቢያ ተችሯል።
 አመሰግናለሁ።

2-
ጌትሽ አምላክ ካንተው ጋር ይሁን። መቸም አንተን የመሰሉ ስላልዋት ሰንደቃላማችን ወድቃ አትወድቅም።
በርታ! አይዞህ!

3-ጌትዬ አንደምን አለህ?
የኢትዮጵያ ወታደሮች ሁሌም ይዘክሩሃል። የቁርጥ ቀን የምየ ልጅ በርታልን።

  ከተረሱት ጀግኖች አንዱ!

ትናንትም ዛሬም ነገም ለወደፊቱም የገዳያቻን የሻዕቢያ ባንዴራ ብንሞትም አናውለበልብም!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

MERCENARIES ምጽዋ ላይ የፈሰሰው የጀግሞች ደም አርካሽ ትውልድ!
አብይ አሕመድ የጥገና ለውጥ አራማጅ መሆኑን አልተቃወምንም፤በስሜት የሚጋልቡ ልጓመ-ቢስ አሻቃባጮች ግን እስከመቸም ድረስ እንታገላቸዋለን። በሚሊዮን ሕዝብ የደገፈው አብይ መደገፍ አይጠብቅብንም። ፖለቲካም እንደ መንጋ ባሕሪ ኣይሰራም። እየሰራቸው ያለው አንዳንድ ልቅ እና ስሜታዊ እርምጃዎች ዘለቄታ እንደማይኖራቸው ስለምናውቅ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ ስንተች “አሻቃባጮች” በኛ ላይ የማሾፍ ነጸብራቅ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ያም መብታቸው ነው። ሆኖም አሽቃባጮች እና ስሜተኞች ብለው ብለው እንደሚዳቋ መዝለላቸው ሳያንሳቸው መድረክ ላይ ወጥተው የዲሲ ግብረሃይል ሰልፈኛ የእልፍ ኣእላፍ ወገኖቻችንን ህይወት ተጠያቂ የሆነውን ሻዕቢያ ባንዴራ ከኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ጋር በክብር ይዘው ሰገነት ላይ ወጥተው ማውለብለብ ማየት ከሚያም በላይም የሚያም አሳፋሪ ቅጥረኛ አሽቃባጭነት ነው። አሽቃባጭነት ብቻ ሳይሆን በከርሰ መቃብር እና በኢትዮጵያ ወታደሮች በድን ሬሳ ላይ ተሸክላ የተውለበለበቺው የጣላታችንን ባንዴራ በሕዝባችን እና በዓለም ሕዝብ ፊት በሙታኖቻችን ታሪክ ላይ እያሾፉ ያውለበለቡብን የሰልፉ አስተባባሪዎች ሕግ ቢኖር በአገር ክሕደት በወንጀል እንፋረዳቸው ነበር። ሆኖም ዘመኑ የወገን ደም ረስቶና አንኳስሶ ገዳዮችንና ወረበሎችን የሚያወድስ ትውልድ እና ጥርሰ-ቢስ ተሸብራኪ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ዘመን ስለሆነ ብረዛው፤ክሕደቱ እና ንቀቱ ኢትዮጵያን የሚያዋርድ ክስተት መሆኑን ታሪክ እንዲመዘግበው አብየቱታችንን እናስመዘግባለን።
ይህ ክስተት የተጀመረው ዛሬ አይደለም። የፖለቲካ ተቃዋሚ ድረገጾች እንዲሁም ግንቦት 7 የተባለው እና ኢሳት የተባለው የሻዕቢያ አፈቀላጤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከሻዕቢያ ባንዴራ ጋር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከኦነግ ባንዴራ ጋር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከኦጋዴን ሶማሊ ነፃ አውጪ…. ወዘተ… ወዘተ..ጋር እያውለበለቡ የሕዝብ ሕሊና ሲበርዙ እንደነበር እናስታውሳለን። አንድ ድርጅት እና ሚዲያ ወይንም ሰልፈኛ የራሱን ክብር እና የራሱን አርበኞች የሞቱላትን ሰንደቅ ዓላማ ማክበር ማውለብለብ እና ማክበር እንጂ ኣእላፍ ዜጎቻችንን ሲረሹኑ የተውለበለበች የጠላት ባንዴራ ማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ አሳፋሪ ክስተት የታየው በዓለም ውስጥ በኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ላለፉት 15 አመታት ሲሰሩት የነበረው የጠላቶቻችንን ባንዴራዎች እና ፕሮፓጋንዳዎችን ቀዳሚ ስራቸው አድርገው ለሕዝብ በማሰራጨት “የሳብቨርዥን ስራ እየሰሩ” ሕዝብን ሲበርዙ ነበር።
የተቃዋሚ ሚዲያዎች እና ተቃዋሚዎች በሰልፋቸው እና ስብሰባዎቻቸው ውስጥ ላለፉት 15 አመታት የኤርትራውያንን ባንዴራ ሲያውለበልቡ የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ግን ኮምቢሽታቶ አስፋልት ላይ ሰንደቃላማችን ምራቅ እየተተፋባት በሰልፈኛ እየተረገጠች አንድትቦጫጨቅ ተደርጓል። በዚህ ብዙ ተችተንበታል። ያም አይተው ተቃዋሚዎች እና ሚዲያዎቻቸው የጠላቶቻችንን ባንዴራ እና ፕሮፓጋንዳ እያውለበለቡ የሻዕቢያን መርዝ በመንዛት እና በማሰራጨት ከመተባባር እስከዚች ደቂቃ ድረስ አልቦዘኑም። ቬሮኒካ መላኩ፤ ተስፋየ ገብረአብ፤ሶፊያ ተስፋማርያም፤በእደማርያም ወዘተ….ወዘተ…..የመሳሰሉ የሻዕቢያ ካድሬዎች እና ሰላዮች የትግራይን ሕዝብ ሲሰድቡ፤ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያፈርሱ ፕሮፓጋንዳዎች መጻሕፍቶች ከማሰራጨት፤ የመጻሕፍቶቻቸውን መቅድም ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ከማሻሻጥ ደርስ ሚና የተጫወቱት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች እናተቃዋሚ ድረገጾች እንደሆኑ የማይካድ ነው።
ያም ሆነ ይህ ‘ሻዕቢያ ሰላም ያመጣል’ ብለው ከአብይ ጀምሮ እስከ አስቃባጮቹ ድረስ የሚቦተሉኩት ፕሮፓጋንዳ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን ስሜተኛ እና የቀን ሕልመኛ ብቻ መሆን ነው። የሻዕቢያ እና “የሻዕቢያ ኤርትራኖች ሳይክ” ያለማወቅ መሆኑን ስንታዘብ እንዴት እንደምናስተምራቸው አቅላችን ይጨነቃል። ወደዳችሁም ጠላችሁም ‘ኢሳያስ አፈወርቂ’ በሕይወት እስካለ ድረስ አሽቃባጮች የምታልሙት ሕልም አይተገበርም። እርማችሁን አውጡ። እኛ እንደሆነ በመስመራችን ላይ ጸንተን የሺሕ ኣእላፍ ወገኖቻችን ደም እና አጥንት አናራክስም። ለጊዜኣዊ ፖቲካ ጥቅም ማስገኚያ ስንል ትናንትም ዛሬም ነገም ለወደፊቱም የገዳያቻን የሻዕቢያ ባንዴራ ብንሞትም አናውለበልብም። አሽቃባጮች ሰንደቃላማችንን እና አርበኞቻችንን ከማዋረድ ታቀቡ!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)