Monday, September 27, 2021

የፊት ወዳጅህን በምን ቀበርከው በሻሽ፤ የኋላው እንዳይሸሽ!!! በዶ/ር አሰፋ ነጋሽ አምስተርዳም (ሆላንድ) መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ. ም

 

የፊት ወዳጅህን በምን ቀበርከው በሻሽ፤ የኋላው እንዳይሸሽ!!!

በዶ/ር አሰፋ ነጋሽ

 አምስተርዳም (ሆላንድ) 

መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ. ም

Email Address: Debesso@gmail.com

 

ስለ አቶ ጌታቸው ረዳ ወንድም መታሰር አስመልክቶ ያለኝ አስተያየት።

የትግል አጋራችን የሆነው ትህነግን ለ30 አመት የታገለ ወንድማችን አቶ ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ-ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) ባሕርዳር ከተማ ውስጥ ስለ ወንድሙ መታሰር አስመልክቶ በጻፈው ጉዳይ ወንድሙ ያለ ምንም ወንጀል መታሰሩ ያለፍትሕ ነው በማለት ዛሬም በተደጋጋሚ አነሆ ለ3 ወራት ያህል  ኢትዮጵያ አዲስ አባባ ላለው “ኢሰመጉ” ጽ/ቤት ቢያመለክትም ሰሚ አላገኘንም፤ በማለት ምሬቱን ለሕዝብ እያስሰማ እንደሆነ ከጻፋቸው መልእክቶቹ ተመልከቻለሁ። የዚህ መንግሥት ምንነት ለማስተማር ብዙ ጥረናል።በተለይ ደግሞ ብ.አ.ዴ.ን. የተባለው የዚያ አካባቢ አስተዳዳሪ ድርጅት፤ እንኳን ለሌላው ነገድ ለራሱ እወክለዋለሁ ለሚለው ለአማራው ነገድም ጭምር ሰቀቀን እንደሆነበት ለ30 አመት አይተነዋል። ይህ ድርጅት በሕዝብ ሕሊና የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ከላይ ከኦሮሙማው ማዕከላዊ መንግሥት በሚሰጠው ትዕዛዝ ብቻ የሚንቀሳቀስ መሆኑ በብዙ ማስረጃ የተረጋገጠ ነው።

ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ያስተዋወቀን የኢትዮጵያ ጉዳይ

ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ያስተዋወቀን ሁለታችንም የወያኔን መንግሥታዊ ሥርዓት ተቃዋሚ መሆናችን ነው። ይህ ወንድማችን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ባለሰለሰና ተከታታይነት ባለው መንገድ የወያኔን መንግሥት ሀገር-በታኝ ፓሊሲዎችና ድርጊቶች ሲቃወምና ሲያጋልጥ ቆይቷል። አቶ ጌታቸው ረዳ የአክሱም ተወላጅ ሲሆን እሱ ከወጣበት የትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ የወጡት አብዛኞቹ የተማሩ፤ ያወቁና የበቁ ናቸው የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች ለዚህ በፋሽስታዊ ፍልስፍና ለሚመራው የወያኔ መንግሥት በደመነፍስ (instinctively) ያልተቆጠበ ሙሉ ድጋፋቸውን ሲሰጡት ታዝበናል፤ አይተናል። አቶ ጌታቸው ረዳ ግን ማናቸውንም በእሱና በቤተሰቡ ላይ የሚደረጉ ማህበረሰባዊ ተፅዕኖዎችን (መገለልን፤ መሰደብንና መንጓጠጥን፤ የማስፈራራት ዛቻን ወዘተ) ተቋቁሞ ይህንን ፋሽስታዊ የወያኔ ሥርዓት በቆራጥነትና በአይበገሬነት መንፈስ ተቃውሟል። የዚህን መሰሪ የሆነ በጥላቻና ልዩነትን በማስፋፋት የተጠመደን ሥርዓት ወግ ባለው መንገድ አጋልጧል። አቶ ጌታቸው ይህንን ለማድረግ ሲል በተከታታይ ከጻፋቸውና “ኢትዮጵያ ሰማይ” በሚል (Blog) ብሎግ አማካይነት ካስነበበን ጽሁፎች በተጨማሪ የሚከተሉትን መጽሃፍቶች በመጻፍ ትህነግን፤ ፓሊሲዎቹንና ድርጊቶቹን ሞግቷል፤ የዚህን ፋሽስታዊ ሥርዓት ክፋት አጋልጧል። እስቲ በማሳያነትና በአስረጂነት የሚከተሉትን የጽሁፍ ሥራዎቹን ላቅርብላችሁ።


1 - ይድረስ ለጎጠኛው መምህር በ2003 ዓ. ም. የታተመ መጽሃፍ፤ (አቶ ገብረኪዳን ደስታ የተባለው የትግራይ አክራሪ ብሄረተኛ “የትግራይ ህዝብና የትምክህተኞች ሴራ” በሚል ለጻፈው እጅግ ዘረኛን ጽንፈኛ ለሆነ ሀሰተኛ መጽሃፍ የሰጠው ምላሽ ነው።

 

2 - የወያኔ ገበና፤ ማህደር - በ2004 ዓ. ም. የታተመ መጽሃፍ፤

 

3 – ወያኔዎች የደበቁት የፕሮቴስታንት ታሪክ በትግራይ፤ ህዳር 2004 ዓ. ም. የታተመ መጽሃፍ፤

 

4 – የትግራይ ብሄረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው? 2010 ዓ. ም. የታተመ መጽሃፍ፤

 

አሳዛኙ ነገር እነዚህ መጽሃፍቶች በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን አያውቋቸውም ማለት ይቻላል።

ይህን የድጋፍ ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ምክንያት፤

ሰሞኑን አቶ ጌታቸው በባህርዳር ነዋሪ የሆነውና ቀደም ሲል የትህነግ ተዋጊ የነበረው፤ ኋላም ከትህነግ ወጥቶ የራሱን የግል ህይወት ይመራ የነበረው ታናሽ ወንድሙ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ መታሰሩን ገልጾልናል። አቶ ጌታቸው ታናሽ ወንድሙ ቀደም ሲል ሲያገለግለው የነበረውን ትህነግን እርግፍ አድርጎ በመተው ትዳር መስርቶ በባህርዳር እንደሚኖር፤ የወያኔንም መንግስት ዓላማ እንደማይደግፍ ገልጾልናል። በባህርዳር የሚገኙ የአማራ ክልል መንግሥት ባለሥልጣኖች የአቶ ጌታቸውን ወንድም በምን ምክንያት እንዳሰሩት ባላውቅም አቶ ጌታቸው ስለ ወንድሙ የሰጠውን ምሥክርነት ልጠራጠር አልችልም።

የወያኔ ትግሬዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የሚቃወሟቸውን የትግራይ ተወላጆች የእነሱ ድርጊት ተባባሪ እንደሆኑ አድርገው በማስወንጀል በደርግ መንግስት እንዲታሰሩና እንዲገደሉ ያደርጉ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። ዛሬ ትህነግ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ውስጥ ባለበትና በርካታ የትግራይ ተወላጆችን ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊያጠፋህ ነው እያለ በሚያነሳሳበት ሰዓት አቶ ጌታቸው ረዳን የመሳሰሉትን ሀቀኛ የትግራይ ተወላጆች ለመጉዳት ሲል ምናልባትም ትህነግ የአቶ ጌታቸውን ወንድም የሚያስጠረጥርና የሚያሳስር መረጃ ለመንግሥት አቀብሎ ታናሽ ወንድሙን ሊያሳስር ይችላል ብዬ እገምታለሁኝ። ይህንን ካደረገ በኋላ ትህነግ ዞር ብሎ “ተመልከቱ ይህ መንግሥት ትግሬ የሆነውን ሁሉ፤ ሌላው ቀርቶ እኛን ወያኔዎችን የሚቃወሙትን የትግራይ ተወላጆች እንኳን በማንነታቸው ምክንያት ሰብስቦ እያሰረ ነው” እያለ ተከታዮቹን ሊቀሰቅስበት ይችላል።

ትህነግና የትግራይ ተወላጆች፤

ትህነግ ከተመሰረተበት ወቅት ጀምሮ በትግራይ ማንነት ላይ የተመሰረተ አክራሪ ብሄረተኛነትን ላለፉት አርባ ሰባት ዓመታት ሲያስፋፋ የቆየ ጽንፈኛ(ultra-nationalist) የፓለቲካ ድርጅት ነው። አክራሪ ብሄረተኛነት የሰውን ልጆች ከሰውነት ደረጃ ዝቅ በማድረግ ሰዎችን እንደ እንደ እንስሶች በደመነፍስ የአምባገነን መሪዎቻቸውን ሃሳብ ካለ አንዳች ጥርጣሬ ተቀብለው በመንጋነት እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ አቅም አለው። አንድ በአክራሪ ብሄረተኛነት ፍልስፍና የሚመራ ህዝብ በአስተሳሰቡ ከሰውነት ደረጃ ዝቅ በማለት በስሜታዊነትና በደመነፍስ በሚንቀሳቀስ እንስሳ ሊመሰል ይችላል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ህዝብ ክፉና ደጉን ለይቶ እንዲያውቅ የሚያስችለውን ህሊናውን አሽቀንጥሮ እንደሚጥል የአክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚፈጥረውን የስነልቦና ተፅዕኖ ያጠኑ ምሁራን በተደጋጋሚ ባደረጓቸው ጥናቶች አረጋግጠዋል። ሂትለር የሚመራው የናዚ ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ብዙዎቹ የጀርመን ተወላጆች ለሂትለር የሰጡት ድጋፍ፤ ሙሶልኒ የሚመራው የፋሽስት ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አብዛኞቹ የጣሊያን ተወላጆች ለሙሶልኒ ፓርቲ የሰጡት ድጋፍ፤ ባለፉት 30 ዓመታት ደግሞ አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ለፋሽስቱ ትህነግ ሲሰጡት ነበር። የቅርብ ጊዜውን እንኳን ለማስታወስ ያህል በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከሥልጣን ተገፍትኖ ወደ መቀሌ እንዲፈረጥጥ ከተደረገ በኋላ በመቀሌ ስታዲዮም በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ተሰብስበው “አይዞና” እያሉ ለደብረጽዮን የእብሪት ንግግር ድጋፋቸውን የሰጡበት ድርጊት በትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት ያበደው ህዝብ የገባበትን ጥልቅ የስነልቦና ዝቅጠት የሚያሳይ ሥዕል ይሰጠናል።

በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ለ47 ዓመታት በኃይልና በፕሮፓጋንዳ አማካይነት በተስፋፋው የትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት ፍልስፍና ምክንያት እንደ አንድ ነጻ ግለሰብ ሳይሆን እንደ መንጋ አንድ-ወጥ በሆነ የቡድን አመለካከት የሚመሩና የሚንቀሳቀሱ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር እጅግ በዝቷል። ከዚህ በተጨማሪ ትህነግ ሥልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት በመሰረተው የአፓርታይድ ሥርዓት አማካይነት የትግራይ ክልልና ነዋሪዎቹን ልዩ ተጠቃሚ ያደረገበት ሁኔታ፤ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ነገዶች በተለየ በተፈጠረላቸው በአድልዎ ላይ የተመሰረተ ሥርዓት ተጠቃሚ ሆነው በኢኮኖሚው ዘርፍ ጎልተው የታዩበት ሁኔታ፤ የትግራይ ተወላጆች “የእኛ መንግሥት ነው” ለሚሉትና ይህንን መንግሥት ሲመራ ለነበረው የትህነግ ድርጅት ሰፊ ድጋፍ እንዲሰጡት አድርጓቸዋል።

ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ሃቅ ደግሞ በትግርኛ ተናጋሪዎች ባህል ውስጥ ጸንቶ የቆየው አንድ ትግርኛ ተናጋሪ ከምንም በላይ ለቤተሰቡና ለጎሳው ፍላጎትና ፍቃድ ተገዢ እንዲሆን የሚያስተምረው የልጆች አስተዳደግ ልማድ ነው። አንድ ታዳጊ ልጅ ከቤተሰቡ፤ ከማህበረሰቡና ከጎሳው ፍላጎትና ፍቃድ ውጭ የፈለገውን ነገር በግሉ አስቦ፤ አቅዶና ወስኖ እንዳይንቀሳቀስ የሚያዘው/የሚያስገድደው በትግራይ ባህል ውስጥ ጎልቶ የሚታይ የልጆች አስተዳደግ አንድ ግለሰብ ከምንም በላይ ለወጣበት ጎሳ ታማኝ መሆንን በመርሆነት በመስበክ የልጆችን አይምሮ ያንጻል። በዚህ ዓይነት ከህጻንነት ጀምሮ የልጆችን አይምሮና አስተሳሰብ የሚቀርጽ የልጆች አስተዳደግ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ሰው ነጻ ግለሰብ ሆኖ ከተወለደበትና ካደገበት ማህበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት ባሻገር ያሉ ወገኖችን ጥቅምና ፍላጎትም ባካተተ መልኩ እንዳያስብ ያደርጋል። ይህ “ከምንም በላይ ለተፈጠርክበትና ለተወለድክበት ጎሳ ታማኝ ሁን” የሚለው በልጅነት አይምሮ የሚቀረጽ አስተሳሰብ ተማሩ ተመራመሩ፤ ዶክተር፤ፕሮፌሰር፤ ሳይንቲስት፤ ፓፓስ፤ ሼክ ወዘተ ሆኑ የሚባሉ ግለሰቦችን ጭምር አይምሮ በመበከል አንድ ግለሰብ እንደ አንድ በራሱ እንደሚተማመን ሰው በነጻነት፤ አመክንዮታዊ (in a rational way)  በሆነ መንገድ የእውነትን ፈለግ እንዳይከተልና ለእውነት እንዳይቆም ያደርጋል።

የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ሥራዎችና የተጻፉበት የጎሰኛነት ቅኝት እንደ ማሳያ 

የታሪክ ፕሮፌሰር የሆነውና ከሰላሳ ዓመታት ያላነሰ በአሜሪካን ሀገር በዩኑቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት ያገለገለው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ (የአክሱም ተወላጅ የሆነ ሰው) በ2009 ዓ. ም. እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በጻፈው(The Ethiopian Revolution,War in the Horn of Africa)  በሚለው መጽሃፉ “አዜብ መሥፍን እንደ ባሏ አዋቂ የሆነች ሴት ከመሆኗም በላይ በኢትዮጵያ ታሪክ በእነ እቴጌ ጣይቱ ደረጃ የምትታይ ሰው ነች” ብሎ ጽፎ ነበር።

“Success stories abound of women in the army and in the business world.  Nationally, they are represented by talented and influential persons, including most notably Azieb Mesfin, Meles Zenawi’s equally savvy wife. No politically prominent woman since Queen Taitu Bitul, Emperor Menelik’’s wife has been so actively and visibly engaged in the public arena. A former liberation fighter, she is emblematic of the liberated Ethiopian woman”.

እንግዲህ የኢትዮጵያን ህዝብ ንብረት በመዝረፍ የምትታወቅ አንድ ምግባረ-ቢስ የሆነች ሴት እንዴት ተደርጎ ነው ከታላቋ ኢትዮጵያዊት ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ልትወዳደር የቻለችው? ገብሩ የአፓርታይድና የፋሽስት ሥርዓት መሰረት የሆነውን በጎሳ ማንነት ላይ የተመሰረተ ወያኔ-ሰራሽ የፓለቲካ ሥርዓት በሚከተለው መንገድ አንቆላጵሶና አስውቦ ጽፏል። ገብሩ ይህን መሰል ውዳሴ ለአንድ ፋሽስታዊ ለሆነ የአፓርታይድ አራማጅ ሥርዓት ሲያቀርብ ካለ አንዳች እፍረትም ሆነ ምሁራዊ ቁጥብነት (unabashedly and without any intellectual restraint tempered by reason) ነው። ገብሩ የአፓርታይድን የፓለቲካ ሥርዓት በሚከተለው መልክ ነው አሽሞንሙኖ ያቀረበው።

 “The federal constitution of 1995 represented the most determined effort to create a democratic framework in which Ethiopia’s intractable national cleavages could find a permanent solution”.

ገብሩ በመቀጠልም የሚከተለውን ሃሰተኛ ትንበያ በድፍረት ጻፈ።

 “The Ethiopian ethnic-based federalist system is a novel and fascinating  political experiment laden with potential problems, but one tha may prove to be the historical exception”.

በጎሳ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ ሥርዓት ውጤቱ ፋሽስታዊ ሥርዓት፤ ጦርነትና የጋራ ጥፋት ማስከተሉን ገብሩ ታረቀም ሆነ እሱን የመሰሉ የትግራይ ልሂቃን የሚያጡት አይመስለኝም። የገብሩ ታረቀን ህሊና ያሳወረው በከፊል ያ ባደገበት የትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ዋሽተህና ያፈጠጠውን እውነታ ክደህም ቢሆን ለወገንህ፤ ለጎሳህ አድላ፤ “ቀጥፈህም ቢሆን የጎሳህን ጥቅም በማናቸውም መንገድ አስከብር” የሚለውና ከልጅነት ጀምሮ እንደ እሴት አዳብሮት ያደገው እምነቱ ነው። በተደጋጋሚ ጊዜያት ታሪክ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር የአንድን ህዝብ ማንነት ማዕከል ያደረገ አክራሪ ብሄረተኛነት የማሰብ ችሎታቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይችሉትን ገብሩ ታረቀን የመሰሉ አወቁ፤ በቁ የሚባሉ ምሁራንን እንኳን ህሊናቸውን አሽቀንጥረው ጥለው በስሜታዊነትና በደመነፍስ የአንድ የፋሽስት ድርጅት ደጋፊና አፈቀላጤዎች እንደሚያደርጋቸው ነው። አክራሪ ብሄረተኛነት አንድ ግለሰብ ራሱን ከሰውነት ደረጃ አውርዶና የሰውነት መገለጫ የሆነውን ህሊናውን አሽቀንጥሮ ራሱን ወደ ደመነፍሳዊ ፍጡር በመቀየር እንደ እንስሳ መንጋ በጭፍን የአንድ ፋሽስታዊ ድርጅት ጀሌና ተከታይ ያደርገዋል። ገብሩ ታረቀም ሆነ ብዙዎቹ የትግራይ ልሂቃን በእነዚህ ከላይ በገለጽኳቸው ምክንያቶች ህሊና አሳዋሪ የሆነው የትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት ሰለባ ለመሆን በቅተዋል።

ይህ በገብሩ ታረቀ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ የትግራይ ልሂቃኖች ዘንድ የምናየው ፋሽስታዊ የራስን ጎሳ ማንነት አምልኮ የትግራይን ልሂቃን በአመክንዮ አሳምነን ከትህነግ ደጋፊነትና አምልኮ ራሳቸውን ሊያወጡ ይችላሉ የሚለውን ተስፋ የሚያመነምን ከንቱ ምኞት ነው። የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳን የፋሽስቶችም ፍጻሜ የመጣው ጸረ-ፋሽስቶችና ዲሞክራቶች በስሜታዊነትና በኢ-አመክንዮ አስተሳብ (sentimental and irrational discourse)  የሚመሩትን አክራሪ ብሄረተኖችን/ፋሽስቶችን በአመክንዮ (rational discourse) ገጥሞ በመከራከርና በመርታት ሳይሆን የፋሽስቶች ሥርዓት መተማመኛ የሆነውን የወታደራዊ ኃይል እንዳይነሳ ተደርጎ በመምታት፤ ይህን መርዘኛና ከፋፋይ የሆነ የፋሽስት ፍልስፍና መሰረት ያደረገም ማናቸውም ዓይነት የፓለቲካ አደረጃጀት ህገወጥ አድርጎ ህልውናው እንዲከስም በማድረግ ነው። በምዕራቡ ዓለም የናዚም ሆነ የፋሽስት ሥርዓቶች ግብዓተ-መሬት የተፈጸመው በኃይል ነው። የትግራዋይነትን ፋሽስታዊ ማንነት የሚያራምዱት የትግራይም ሆኑ ኦሮሞማን የሚያስተናግዱት ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት የኦሮሞ ፋሽስቶች ይህ ከሰላሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተተከለው ጎሰኛ ሥርዓት እንዲቀጥል እንጂ እንዲጠፋ ስለማይፈልጉ ለእነዚህ ኃይሎች ህልውና መሰረት የሆነው ጎሳን መሰረት ያደረገው ህገመንግስት እስከ ቀጠለ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ መከራና ሥቃይ ይቀጥላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

በርካታ የትግራይ ልሂቃንን ያለ አንዳች ይሉኝታ (ይሉኝታ በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ብዙም የሚታወቅና ሥር የሰደደ እሴት አይደለም ብዬ አምናለሁኝ) ትህነግን በመደገፍ ያሳዩን ባህርያቸው በተወሰነ ደረጃ ከዚህ ጎሰኝነትንና ለራስ ጎሳ ታማኝነትን በአስተዳደግ ደረጃ ከሚያሰርጽ የትግራይ ባህል የመነጨ ነው ብዬ እከራከራለሁኝ። ጎሰኛነትን መመሪያው ባደረገ ማህበረሰብ ውስጥ አመክንዮታዊ በሆነ መንገድ ነገሮችን አይቶና አስልቶ የራስን ውሳኔ መስጠትና የራስን ህይወት ለመምራት መሞከር ከማህበረሰብ አባልነት ያስገልላል፤ ያስወግዛል።በጎሰኛ አስተሳሰብ የሚመራ ማህበረሰብ የግለሰብ ነጻነቴን አስከብሬ፤ እኔ ያመንኩበትንና እውነት ነው ያልኩትን ነገር አደርጋለሁ የሚልን አንድ ግለሰብ ቤተክርስቲያን እንደገባች ውሻ ከማህበረሰቡ ተነጥሎ እንዲሳደድ፤ እንዲወገዝ ያስደርጋል። አቶ ጌታቸው ረዳን የመሰሉ ብርቅዬ ዜጎች በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ የገጠማቸው ይህን መሰል መገለል ነው።

በቅርቡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በብዛት በመንቀሳቀስ (human wave) ለዘረፋ፤ ለግድያና ንብረት ለማውደም ሥራ በአማራና በአፋር ክልል ሰፊ ዘመቻ ጀምረዋል። በዚህ ዘመቻ የትግራይ ቤተከርስቲያን ቀሳውስት ጭምር በአማራ ክልል ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን፤ ቅዱስ መጽሃፍትን ሌሎችም የሃይማኖታዊ ቅርሶችን በመዝረፍ ሥራ ተሰማርተዋል። የመስፍን ኢንጂነሪንግና ተመሳሳይ የትግራይ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ቴክንሺያኖች ጭምር በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን በመነቃቀል (የወልዲያ ዩኑቨርሲቲ ንብረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ነቃቅለው መወሰዳቸውን ልብ ይሏል) ወደ ትግራይ ወስደዋል። ት/ቤቶችን፤ ሆስፒታሎችን፤ መስሪያ ቤቶችን፤ የማምረቻ ተቋሞች ንብረቶች ተዘርፈውና ተነቅለው ወደ ትግራይ ተወስደዋል። የትግራይ የህክምና ባለሙያዎች ደግሞ ህክምና መሳሪያዎችን/መድሃኒቶችን እየመረጡ በመዝረፍ ወደ ትግራይ በማጋዝ ተግባር ላይ እጅ ተሳትፈዋል። በቤተክርስቲያናትና ገዳማት ውስጥ የሚያገለግሉ የአማራ ቀሳውስትና መነኮሳት በትግራይ ፋሽስቶች ተገድለዋል፤ ታርደዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናት ቤተመቅደሶች ሳይቀሩ እንዲረክሱ ተደርገዋል፤ የትግራይ ፋሽስቶች በቤተ መቅደስ ውስጥ ቀሳውስ በግ አርደው በልተዋል፤ በዖም ላያ ያሉ የአማራ ክልል ቀሳውስት በትግራይ ፋሽስቶች ተገደው ሥጋ እንዲበሉ ተደርገዋል።

ይህ የትግራይ ተወላጆች በዘመቻ መልክ በስፋት ተንቀሳቅሰውና የመሪ ድርጅታቸውን የትህነግን ትዕዛዝ በመቀበል የአማራና የአፋር ግዛቶችን በመውረር እየፈጸሙት ያለው ፋሽስታዊ ድርጊት፤ (ዓቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሙማው መንግስት “ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠትና የትግራይ አርሶ አደሮች መሬታቸው ጦም እንዳያድር ብሎ ጦሩን ከትግራይ አውጥቶ ያልታጠቀውን የአማራ አርሶ አደር ለጥቃት ካጋለጠው በኋላ) የተከሰተ ነው። ይህ ፋሽስታዊ ወረራና ያስከተለው ጥፋት በዘመን ርዝመት ከህሊና የማይጠፋ ሲሆን ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና ብተቀጥልም ሆነ ብትገነጠልም በወጉ ተሰንዶና ተዘግቦ ለተከታታይ ትውልዶች በመማሪያነት ሊተላለፍ የሚገባው የክፉ ታሪካችን አንድ አካልነው።

የትግራይ ፋሽስቶች እያካሄዱት ያለው የጅምላ የዘር ፍጅት፤ የንብረት ዘረፋ፤ የታሪካዊ ቅርስ ዘረፋ፤ የታሪካዊ ቅርሶች ውድመት (ምሳሌ ከሺህ ዓመታት ያላነሰ እድሜ ያለው የጨጨሆ መድኃኒ ዓለም ታሪካዊ ደብር)፤ የተቋሞች ውድመት (ት/ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ክሊኒኮችና  ወዘተ)፤ የቤት እንስሳትን መግደል ወዘተ ለ47 ዓመታት በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ሲሰበክ የነበረ ህሊናን የሚያስት የአክራሪ ብሄረተኛነት ጫፍ የሆነ የፋሽስት ፍልስፍና መስፋፋት ውጤት ነው። እስቲ የቤት እንሥሣት በምን ምክንያት ነው የሚገደሉት? እንስሶቹም  በትግራይ አክራሪ ብሄረተኞች ዘንድ እንደ አማራ ባለቤቶቻቸው የአማራ ማንነት ያላቸው “ትምክህተኞችና የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላቶች” ሆነው ይታዩ ይሆን? ይህ የትግራይ ተወላጆች በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸውን የጥላቻ መጠን በጉልህ የሚያሳይ ነው። በጋሊኮማ በአፋር ተወላጆች በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ፤ በጭና፤ በቆቦ፤ በወልድያ፤ በመርሳ፤ በሰቆጣ፤ በጎብዬ፤ ወዘተ የተፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋዎች ከወል ትውስታችን ሊወጡ የማይገባቸው የትግራይ ፋሽስቶች ድርጊቶች ናቸው። አንባቢ ዛሬ የትግራይ ፋሽስቶች እየፈጸሟቸው ያሉትን ጭፍጨፋዎች የጣሊያን ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት በያዙበት ጊዜ ከፈጸሟቸው ድርጊቶች ጋር እንዲያነጻጽር የሚከተሉትን የጣሊያን ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚያወሱ መጽሃፍት እንዲያነብ እጋብዛለሁኝ።

1 – ህይወቴ (ግለታሪክ)፤

አቶተመስገን ገብሬ የተባሉ የዚህ ታሪክ ባለቤት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ. ም. እ. ኢ. አ. በአዲስ አበባ በተፈጸመው የጣሊያን ፋሽስቶች ጥቃት ሰለባ የነበሩና ከጅምላው ፍጅት የተረፉ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ከገጽ 92-118  ባለው የዚህ መጽሃፍ ክፍል ውስጥ የተዉት እጅግ አሳዛኝ የሆነ የሥቃይ ማስታወሻ ሰፍሮ ስለሚገኝ ፈልገው ያንብቡት።

2 – Ethiopian Under Mussolini, Fascism and the Colonial Experience: by Alberto Sbacchi, 1986

 

3 – Legacy of Bitterness; Ethiopia and Fascist Italy, 1935-1941 by Alberto Sbacchi, 1997

 

4 – The Plot to Kill Graziani, the Attempted Assassination of Mussolini’s Viceroy - by Ian Campbell, 2010

 

5 – The Massacre of Debre Libanos by Ian Campbell - published in 2014

 

6 – The Addis Ababa Massacre by Ian Campbell - published in 2019

 

7 – Fascist Italian Brutality in Ethiopia, 1935-1937 - An Eye Witness Account by Saska Laszlo (aka Ladislas Sava)

 

የትግራይ ፋሽስቶች ባለፉት 30 ዓመታት፤ በወልቃይት ደግሞ ባለፉት ለአርባ ዓመታት የፈጸሟቸው ፋሽስታዊ ድርጊቶች፤ በተለይ ደግሞ የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጀውና ለይተው ያደረጉት ጥፋት ከላይ በገለጽካቸው የጣሊያን ፋሽስቶችን ድርጊቶች በሚያወሱ መጽሃፍቶች ውስጥ ከተቀሱት ድርጊቶችም በላይ የከፉ ናቸው። ስለ ጣሊያን ፋሽስቶች ታሪክ ባነበብኳቸው በርካታ መጽሃፍት ውስጥ ጣሊያኖች እንደ ትግራይ ፋሽስቶች የኢትዮጵያ ተወላጆችን አስረው የግብረሰዶማዊ ጥቃት ሰለባ አደረጓቸው የሚል አንዳችም ዘገባ አላነበብኩም። የጣሊያን ፋሽስቶች የትግራይ ፋሽስቶች እንዳደረጉት በኢትጵያውያን ወንዶች  ብልት ላይ በውሃ የተሞላ ጠርሙስ አስረው ስለማሰቃየታቸው እስካሁን ያነበብኩት ወይም የሰማሁት ታሪክ የለም። እነዚህ ጸያፍ ድርጊቶች ግን በትግራይ ፋሽስቶች ለ27 ዓመታት ሲፈጸሙ ነበር።

የትግራይ ተወላጆች ሃሺሽ እያጨሱ ነውን?

ትህነግ ህጻናትን የዚህ አውዳሚ ጦርነት አካል አድርጎ በግንባር ቀደም ያሰለፈው አንዳንድ ስለ አክራሪ ብሄረተኝነትም ሆነ ፋሽዝም እውቀት-አጠር ምሁራን፤ የተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅት መሪዎችም(intellectuals and opposition political leaders who lack knowledge about ultra-nationalism and its offshoot i.e. fascsm) ሆነ የማህበረሰብ አንቂዎች(social activists) እንደሚነግሩን “ትህነግ የትግራይን ተወላጆች ሀሺሽ ከሻይ ጋር እየቀላቀለ ስላጠጣቸው ወይም በአንገታቸው ላይ ጥይት አይገድላችሁም የሚል መከላከያ ስላሰረላቸው አይደለም። የትግራይ ተወላጆች ዛሬ ይህን መሰል በምንም ዓይነት በታሪካችን ተወዳዳሪ የሌለው የጥላቻ ድርጊት እየፈጸሙ ያሉት ጋኔል ስለሰፈረባቸው፤ሰይጣን ስላሳሳታቸው ወይም የ666 አባላት ስለሆኑም አይደለም። ይልቁንስ በርካታዎቹ የትግራይ ማህበረሰብ ተወላጆች ዛሬ የትህነግን ፋሽስታዊ ትዕዛዝ ካለአንዳች ማንገራገር እየተከተሉና እየፈጸሙ ያሉት ለ47 ዓመታት በቀጠለውና ህሊናን በሚያስተው የአክራሪ የትግራይ ብሄረተኝነት ስብከት አብደው ነው። ይህ አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነትና በእሱ ላይ መደላድል ላይ የቆመው የፋሽስት/የናዚ ፍልስፍና የአንድን ጎሳ የወል ማንነት ወደ ጭፍን አምልኮ ወይም ህሊና አሳዋሪ እምነት በመቀየር እንደ አክራሪ ኃይማኖት በተከታዮቹ ዘንድ እንዲናኝና እንደ ተላላፊ በሽታ እንዲተላለፍ ያደርገዋል። የዚህ የአዲሱ የፓለቲካ ሃይማኖት ሥም “ፋሽዝም/ናዚዝም” ተብሎ የሚታወቅና በዓለም ታሪክ ውስጥ በጀርመን ናዚዎችና በኢጣሊያ ፋሽስቶች ሲሰበክ ቆይቶ በአውሮፓ ከ70 ሚሊዮን በላይ ቁጥር ያለውን የአውሮፓውያን ህዝብ ለፍጅትና ለሞት የዳረገ “መርዘኛ ፍልስፍና” ነው። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ትግራዋይነትና ኦሮሙማ የተባሉት የአክራሪ ብሄረተኛነት መገለጫ ማንነቶች የፋሽስት/ናዚ ፍልስፍና መገለጫዎች ናቸው።

በዚህ የፋሽዝም የፓለቲካ ኃይማኖት ተጠምቀው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የጣሊያን ፋሽስቶች በሀገራችን በቆዩባቸው አምስት አመታት ሰባት መቶ ሰላሳ ሺህ (730000)ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፍጭፈው ገድለዋል። ከዚህ የፋሽስቶች ጥፋት ያልተማረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ባለፉት 47 ዓመታት ሀገር-በቀል በሆኑና በአብዛኛው አያቶቻቸው የጣሊያን ፋሽስቶች ግብረ-አበር ባንዳዎች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በተመራው የትህነግ ፋሽስታዊ ድርጅት ጣሊያኖች የፈጸሙትን ግፍ በብዙ እጅ የሚያስከነዳ ጥፋት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፤ በተለይም በግምባር ቀደምትነት የጥቃት ዒላማ ባደረጉት በአማራው ህዝብ ላይ ፈጽመዋል። አንባቢ ልብ እንዲል የምፈልገው በርካታዎቹ የትህነግ መሪዎች አባቶችና አያቶች የጣሊያን ፋሽስቶች ታማኝ አገልጋዮች በመሆን ትላንት ኢትዮጵያን የወጉ የመሆናቸው እውነታ ነው። በምሳሌነትም የስብሃት ነጋ፤ የመለስ ዜናዊ፤ የሥዩም መስፍን፤ የኃያሎም ዓርዓያ፤ የቴዎድሮስ ሀጎስ ወዘተ ቤተሰቦች በባንዳነት የሚታወቁ ናቸው። ባንዳነት በዘር የሚተላለፍ ነገር ባይሆንም የጣሊያን ፋሽስቶች ለትህነግ መሪ ወላጆች ያስጠኗቸውን የኢትዮጵያ ጥላቻ፤ እነዚህ የትግራይ ባንዳዎች ልጆቻቸው ለሆኑት የትህነግ መሪ ሆነው ለመጡት ወጣቶች በምድጃ ሥር እየነገሩ የጣሊያን ፋሽስቶችን ጥላቻና መርዝ ማስተማራቸው አሌ የማይባል ሃቅ ነው። በጥላቻ ያደጉ ልጆቻቸውም ኋላ ላይ አድገው ይህን ጥላቻ ወደ ተግባር መተርጎማቸው አስገራሚ አይሆንም።

ይህ በናዚ ጀርመኖችና በጣሊያን ፋሽስቶች ዘንድ ያየነው እብደት ነው ባለፉት 47 ዓመታት በትግራይ ውስጥ በትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት ስም ተስፋፍቶ እዚህ ዛሬ የምናየው ደረጃ ላይ የደረሰው። ዛሬ የተስፋፊው የትህነግ ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ቀሳውስት፤ ዲያቆናት በአማራ ክልል የሚገኙ ገዳማትንንና ደብሮችን በማውደም፤ በመዝረፍ፤ በማቃጠል ተባባሪ የሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። “ዛሬ ለብዙዎቹ የትግራይ ተወላጆች አዲሱ ኃይማኖት ትግራዋይነት የሚለውና የትግራዋይነትን የወል ማንነት በኃይማኖታዊ አምልኮ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንዲመለክ ያደረገው የፋሽስት እምነት ነው እንጂ ክርስትና ወይም እስልምና አይደለም ብዬ እሞግታለሁኝ።” ምክንያቱም የክርስትናም ሆነ የእስልምና ኃይማኖቶች ሰላምን እንጂ ጸበኛነትን፤ የዘር ጥላቻን፤ ተስፋፊነትን፤ ጦረኛነትን፤ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ላይ የተመሰረተ ውሸትን፤ ህሊናቢስነትን፤ ነውረኝነትን፤ ይሉኝታቢስነትን፤ ህገ-ወጥነትን፤ ግብረገብ-የለሽነትን፤ ተንኮልን፤ ስግብግብነትን፤ ራስ ወዳድነትን፤ ጭካኔን፤ ዘረፋን፤ እኔ ብቻ በልቼ ልሙት የሚለውን በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ክፋት የሚሰብኩ ኃይማኖቶች አይደሉም።

በዛሬው ጊዜ ግን አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች እንደ ጣዖት በሚያመልኩት “ትግራዋይነት” በሚሉትና በኩራት መጠሪያችን ነው ብለው በሚመኩበት የወል ማንነታቸው ሥም የህይወት መመሪያቸው አድርገው የያዙት በትግራይ አክራሪ ብሄረተኛነት ላይ የቆመው የፋሽስት ፍልስፍናና እምነት ይዘት እነዚህን ከላይ በጥቂቱ የዘረዘርኳቸውን የክፋት እሴቶች የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ የትግራይ ተወላጆች የሚያመልኩትና የትግራይን የወል ማንነት እንደ ጣዖት እንዲያመልኩት ያደረጋቸው አዲሱ ኃይማኖት ፋሽዝም ይባላል። ይህ አዲሱ ኃይማኖታቸው “እኛ ትግሬዎች ከሌሎች ሁሉ የተለየ ወርቅ ማንነት ያለን፤ ከሌሎች ጎሳዎች ሁሉ የተሻልን ነን በሚል ፋሽስታዊ እብሪት ተወጥረው የበላይነታቸውን በሌሎች የኢትዮጵያ ጎሳዎች ላይ ለመጫን አነሳስቷቸዋል። ይህ አዲሱ የ”ትግራዋይነትን” የወል ማንነት ጭቭን አምልኮን የሚያስፋፋው ፋሽስት ኃይማኖት በዘፈን፤ በሽለላ፤ በአሸንዳ በዓላት፤ በጠመንጃ ጭምር በመታጀብ ጦረኛነትን፤ ማንአህሎኝነትን እየሰበክ ብዙዎቹን የትግራይ ተወላጆች የስሜታዊነትና የህሊናቢስነት ሰለባ በማድረግ መቀሌ በሚገኘው የሮማናት አደባባይ ላይ ሲያሳብዳቸው በቴሌቪዥን መስኮት በተደጋጋሚ አይቼያለሁኝ፤ ታዝቤያለሁኝ።

++++የጀርመን ናዚዎች የሶቪዬት ህብረትና ታንኮች በርሊን ገብተው ሲርመሰመሱ የጀርመንን ህጻናትና እናቶች ከቤት ወጥተው መንገድ ላይ ድንጋይ በመኮልኮል የሶቬዬት ህብረትን ጦር እንዲዋጉ አሰልፈው ነበር። የትግራይ አክራሪ ብሄረተኞችም ህጻናትንና እናቶችን ከጦሩ ፊት አስቀድመው ወደ አማራና አፋር ክልል የላኩበት ሁኔታ ከዚህ ከጀርመን ናዚዎች ድርጊት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።

 ይህ ህሊናን የሚያሳውር የፋሽስት እምነት የትግራይ ተወላጆች ትላንትና አቅፎና ደግፎ፤ ሲቸገሩ በችግራቸው ደራሽ በሆነው የጎንደር፤ የወሎ፤ የአፋር ህዝብ ላይ ምንጊዜም ከህሊና ሊጠፋ የማይችል የዘር ፍጅት እንዲፈጽሙ አድርጓል። የትግራይ ፋሽስቶችና ተከታዮቻቸው ዛሬ እየፈጸሙ ያሉት ወረራ፤ የጅምላ ፍጅት፤ ዘረፋ ወዘተ ነገ የትግራይ ህዝብ በተለይ ጎረቤቱ ከሆነው የአማራና የአፋር ህዝብ ጋር “በአንድ ሀገር ውስጥ በሰላም አብሮ የመኖሩን ነገር ጥያቄ ውስጥ እያስገባ የሆነ ድርጊት መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁኝ”። እዚህ ላይ ባያምኑበትም ጥቂት የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች በግዴታ የትህነግ ፍቃድን ምኞት ፈጻሚ መሆናቸውን ለማስገንዘብ እፈልጋለሁኝ። እጅግ ጥቂት የሚባሉት ደግሞ ፊት ለፊት ወጥተው የዚህን የጥፋት መንገድ ለመቃወም ባይችሉም የወያኔ ትግሬዎች በሚፈጽሙት የፋሽስት ድርጊት ተባባሪ ላለመሆን እንደሚጥሩ መገመት አለብን (በማይካድራ የዘር ማጽዳት ድርጊት የአማራን ተወላጆች ደብቀው ያዳኑ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች እንደነበሩ መዘንጋት አያስፈልግም)። ለእነዚህ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ሰብዓዊ ድርጊት አክብሮት አለኝ።

የትግራይ ፋሽስቶች ላለፉት አርባ ዓመታት ወልቃይትን በወረራ ይዘው በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን ሲገድሉ፤ የአማራ ተወላጆችን ጉድጓድ ውስጥ ከተው በእርጥብ እንጨት ጭስ እንዲታፈኑ አድርገው ሲፈጁ፤ የአማራ ወንዶችን ዘር እንዳይተኩ አድርገው ሲያኮላሹ፤ የአማራን ወንዶች ገድለው ሴቶቻቸውን አስገድደው ሲደፍሩ፤ ሲያረክሱ፤ ካለፍላጎታቸው ሲያስወልዷቸው፤ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡትን አማራዎች ደግሞ ከተወለዱበትና ዘር ማንዘራቸው ለሺህ ዘመናት ከኖሩበት ለሙ የወልቃይት ምድር ሲያፈናቅሉ ቆይተዋል። እዚህ ላይ በዚህ ፋሽስታዊ የወያኔ ትግሬዎች ድርጊት ተባባሪ አልሆንም ብለው አሻፈረኝ በማለት በአቋማቸው በመጽናት ከተጠቂዎቹ የአማራ ተወላጆች ጎን የቆሙና በዐጼ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከሽሬ መጥተው ወልቃይት ላይ የኖሩ የትግራይ ተወላጅ በምሳሌነት ላነሳ እፈልጋለሁኝ። እኚህ ህሊና ያላቸው ብርቅዬ የትግራይ ተወላጅ በቅርቡ የወልቃይት ተወላጆች የወያኔዎችን አስተዳደር አሽቀንጥረው ሲጥሉ ላሳዩት ርዕታዊነታቸው  ከፍተኛ ምስጋና አግኝተዋል። ከእነሱ ጋር አካባቢውን ከትህነግ ወረራ እንዲጠብቁ በወልቃይት የሚገኙ የአማራ ተወላጆች  እኚህን የትግራይ ተወላጅ ትጥቅ አስታጥቀዋቸዋል። እኚህ ሰው እዚያው ከወልቃይት አማሮች ጋር በኖሩበትና በከበዱበት ቦታቸው ላይ በክብር እንዲኖሩ ተደርገዋል። አማሮች ውለታ የማይረሱ መሆናቸውንም በዚህ ዓይነት በድጋሜ በተግባር አረጋግጠዋል።

ምሳሌያዊነቱ የገዘፈው የአቶ ጌታቸው ረዳ ምግባርና የደረሰበት ተፅዕኖ።

ትህነግ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሚቃወሙትን የትግራይ ተወላጆች (በሀገር ቤትም ሆነ በውጭው የስደት ሀገር) በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዲገለሉ በማድረግ ተፅዕኖ ሲያደርግባቸው ቆይቷል፤ በዚህም የተሳካ ውጤትን አምጥቷል። በእጅ የሚቆጠሩ ጥቂቶች ግን ይህንን የመሰለውን የወያኔ ተፅዕኖ በቆራጥነትና ተወዳዳሪ በማይገኝለት የአልበገሬነት መንፈስ ተቋቁመው በአመኑበት ኢትዮጵያዊ አቋማቸው ጸንተዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ረገድ በአሜሪካን ሀገር ውስጥ ከሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች በብቸኝነት የምመሰክርለት ድንቅ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነው።

ከምንም በላይ ለጎሳህ ታማኝነትህን አሳይ ከሚል የትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ የወጣ ሰው ያንን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የጸና ባህላዊ ግዴታ አሻፈረኝ ብሎ ለእውነት መቆም ታላቅ ቆራጥነትና የመንፈስ ልዕልናን የሚጠይቅ ድርጊት ነው። የአቶ ጌታቸውን ምሳሌነት ደጋግሜ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የማነሳውም በዚህ ምክንያት ነው። ዛሬ ከትግራይ ማህበረሰብ ውጭ ያለነው ኢትዮጵያውያን ከአቶ ጌታቸውም ሆነ እንደ እሱ በግል ፀረ-ወያኔ አቋማቸው ጸንተው የቆሙ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጀርባ ልንቆም የሚገባን እሱን የመሰሉ ጥቂት የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሰው ልጅ መሸከም የማይችለውን የመገለል ዘመቻ(ostracization, isolation) ለበርካታ ዓመታት ተቋቁመው ለኢትዮጵያ መስዋዕት ስለከፈሉ ነው። ከትግራይ ማህበረሰብ ውጭ የመጣነው ኢትዮጵያውያን በትክክለኛ ኢትዮጵያዊ አቋማቸው ምክንያት ለአስርት ዓመታት ቤተክርስቲያን እንደ ገባች ውሻ እንዲቆጠሩ ተደርገው ከትግራይ ማህበረሰብ እንዲገለሉ የተደረጉትን አቶ ጌታቸውን የመሰሉ ቆራጥ ግለሰቦችን የመደገፍና የመንከባከብ ሰብዓዊ፤ ሞራላዊና ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብን ብዬ አምናለሁኝ።

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትመራበትና ባለፉት 30 ዓመታት ትህነግና ኦነግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሉት የጎሳ ማንነት መሰረት ያደረገ አክራሪ ብሄረተኛነት መገለጫ የሆነው የፋሽስት ሥርዓት እጅግ ጽንፍ የረገጡ ፓለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎችን በመፍጠር የምንኖርበትን ማህበራዊ ዓለም (the social world we live in)  በጥቁርና በነጭ፤ በጠላትና በወዳጅ፤ በአጥፊና ጠፊ ወዘተ ዓይን እንድናይ አስገድዶናል። የህዝበኝነት ፓለቲካ (populist politics) በሚሰበክባትና ጦርነት የሚሊዮኖች ንጹሃንን በር እያንኳኳ ህዝቧን ለጅምላ ፍጅትና መፈናቀል በዳረገበት ሀገር ውስጥ ከዚህ በአጥፊና ጠፊ ተቃርኖ የታጀበ ፓለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሁኔታ ባሻገር ነገሮችን በሚዛናዊነትና ከስሜት በራቀ መንገድ ማየትም ሆነ መዳሰስ ከባድ ነው።

ስለ ትህነግ ከመቼ ጀምሮ መከታተል ጀመርኩኝ?

ትህነግን መቃወም የጀመርኩት ሥልጣን ላይ ከወጣ ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ አይደለም። ስለ ትህነግ በቅርብ መከታተል የጀመርኩበት ከ1974 ዓ. ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር (እ.ኢ.አ.) ጀምሮ በተለይም እዚህ ሆላንድ ሀገር በስደተኛነት መኖር ከጀመርኩኝ በኋላ ነው። በመጋቢት 1976 (እ.ኢ.አ.)በምኖርበት በሆላንድ ዋና ከተማ በአምስተርዳም ውስጥ ዶ/ር ሰለሞን ዕንቋይ የሚባል በዐጼ ኃይለሥላሴ መንግስት ዩኑቨርሲቲ መምህር የነበረ(Haile Selassie University, Education Faculty Staff Member)፤ የኢትዮጵያን አብዮት መምጣት ተከትሎ በሶቪዬት ህብረት የኢትዮጵያ ኤምባሴ የባህል አታሼ የነበረና ኋላምከዚያ ከድቶ ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሰደድትህነግን ተቀላቅሎየትግራይ የረድኤት ድርጅት(Relief Society of Tigrai) የሚባል የልመና ድርጅትይመራ የነበረ ሰው አምስተርዳም መጥቶ ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ። ይህ ከምዕራብ መንግስታትና ተቋማት ምፅዋት እየለመነ ትህነግን ያስታጥቅ የነበረ ሰው ንግግር ወደሚያደርግበት “ትሮፒካል ኢኒስትትዩት” የሚባል ተቋም የስብሰባ አዳራሽ አብሬው እንድንሄድ የጋበዘኝ አንድ በዚሁ በአምስተርዳም የሚኖር፤ ቀደም ሲል የኢህአፓ አባል ነበርኩ የሚል ሰለሞን ደስታ (ዘመንፈስ በሚባል ሥምም ይጠራል) የሚባል የአዲግራት ከተማ ተወላጅ ነው። ይህ የትግራይ ተወላጅ ያኔ የትህነግ ተቃዋሚ ነኝ የሚል የነበረ ሲሆን ወያኔ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ቀንደኛ የሆነ የትህነግ ደጋፊ ነው። በዚያ ስብሰባ ላይ ሰለሞን ዕንቋይ ንግግሩን ያደረገው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሲሆን በተለይ ደርግን የአማራ መንግስት አድርጎ በመሳል ያስተዋወቀበትን፤ እሱ የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ በትግሬነቱ ምክንያት የአማሮች መንግሥት በሆነው የደርግ መንግስት ተንኮል ወደ ሶቪዬት ህብረት በትምህርት አታሼነት (Educational Attache) ሥም በግዞት መላኩን ተናገረ።

በመቀጠልም በስብሰባው ላይ ለነበሩ የደች ተወላጆችና እኔን ለመሰሉ በስብሰባው ላይ ለነበርን ኢትዮጵያውያን ለአማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻ ካላኣንዳች ይሉኝታ አቀረበ (አንባቢ የሰለሞን እንቋይን ውሸታምነትና ለአማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻ ለማወቅ ከፈለገ “Tigrai – the Agony and Ecstacy”በሚል ርዕስ ከ14 ዓመት በፊት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ጽፎ ያሳተመውን መጽሃፍ እንዲያነብ እጋብዛለሁኝ። እኔም እሱ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ እጄን አንስቼ በመናገር እሱ ያቀረበውን ሀሰተኛ ትረካዎችና መከራከሪያዎች ማስረጃ እየጠቀስኩ በማጋለጥ ምላሽ መስጠት አቅቶት አንገቱን በሃፍረት እንዲደፋ ማድረጌ ትዝ ይለኛል። አንድ በዚያ ስብሰባ ላይ የነበሩ የትግራይ አዛውንት ከዚያ ዕለት ጀምሮ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ስብሰባዎች ላይ በምሰጣቸው አስተያየቶች ምክንያት “አሰፋ የአንተን ተከራካሪነትና የማስረጃ አቀራረብ ስመለከት አንተ ህክምና ሳይሆን ህግ ነበር ማጥናት ያለብህ” እያሉ በተደጋጋሚ ይነግሩኝ ነበር። እኚህም ሰው በወቅቱ ወያኔን እቃወማለሁ እያሉ የሚነግሩኝና በተለይ ትህነግ በትግራይ አዛውንቶች ላይ ይፈጽም የነበረውን ግፍ ይነግሩኝ የነበረ ሲሆን ፤ ትህነግ ሥልጣን ሲይዝ ሸርተት ብለው የዚህ ድርጅት ደጋፊ ሆነው አገኘኋቸው። ከዚህ የመጋቢት ወር 1976 ዓ.ም. እ.ኢ.አ.የወያኔ ወኪሎች የጠሩት ስብሰባ ጀምሮ የወያኔ መሪ ካድሬዎች የሆኑት ብርሃኔ ገ/ክርስቶስን (በደርግ ዘመን የሮም የትህነግ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበረ፤ ኋላ ወያኔ ሥልጣን ላይ ከወጣ በሁላ በዋሽንግተን ዲሲና በቤልጀም - ብራስልስ ከተማ የወያኔ አምባሳደር የነበረ የትህነግ መሪ ካድሬ ነው)፤ አሰፋ ማሞ (አፈር ይቅለለው ሞቷል) እና ነጋሽ ተክሉ የተባሉ የትህነግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች፤ ተፈራ ወልዋንና እነዚህን ሁሉ የመሰሉ ሙያ-አይጠሬዎች የሆኑ የወያኔና የብአዴን ካድሬዎች ይህንን ፋሽስታዊ ድርጅት በመወከል ሆላንድ እየመጡ ስብሰባ ሲጠሩ፤ በስብሰባዎቻቸው ላይ ሁሉ እየተገኘሁኝ የትህነግን እኩይ ድርጊት ሳጋልጥ ቆይቼአለሁኝ።

 

ስለ ትግራይ ብሄረተኝነት ይበልጥ ለመረዳት እንድችል የትህነግ ካድሬዎች፤ እንደዚሁም ትህነግን የሚደግፉ የትግራይ ልሂቃን ባለፉት 30 ዓመታት የጿፏቹውን በቁጥር ከ60 በላይ ብዛት ያላቸውን፤በአመክንዮ ሳይሆን በተረትና በጥላቻ የተሞሉ መጽሃፍቶቻቸውን አንብቤአለሁኝ። ትህነግን በተመለከተ ባደረግሁት ንባብና ጥናት፤ ስለ አክራሪ ብሄረተኝነት በርካታ መጽሃፍትን በማንበብ ከገበየሁት እውቀት በመነሳት፤ በተለይ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች  ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ትህነግን በመደገፍ በተግባር ካሳዩት አፍቃሪ-ትህነግ (pro-TPLF stance and fanatically unabashed support) ድጋፍ በመነሳት አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች የትህነግ ደጋፊ ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ደርሼአለሁኝ። ይህንንም በአደባባይ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መድረኮች ላይ ገልጫለሁኝ፤ጽሁፎችም ጽፌያለሁኝ።

በዚህም የትግራይን አክራሪ ብሄረተኛነት ፋሽስታዊ ባህርይ ባልተገነዘቡ የፓለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ነን በሚሉ መሪዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ነን በሚሉ ግለሰቦች፤ በእወደድ-ባይነትና በህዝበኝነት ስሜት(populist sentiment) የትግራይ ህዝብ ለትህነግ የሚሰጠውን ግልጽ ድጋፍ ለመካድና ለመሸፋፈን የሚጥሩ ዋሾዎችና የፓለቲካ ትክክለኛነት አራማጆች (promoters of political correctness) እንደዚሁም በየዋህ ኢትዮጵያውያንና በተለይም በአብዛኛው እዚህ በምኖርበት ሀገር በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ተቃውሞዎችን አስተናግጃለሁኝ። “ትህነግ አዲስ አበባ ሲገባ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ወያኔዎች እንደ ውጭ ወራሪ ኃያል (እንደ ጣሊያን ፋሽስቶች) በመቁጠር መዋጋት አለበት፤ የወያኔ ትግሬዎች የሚመሩበት የፋሽስት ፍልስፍና፤ ድርጊታቸው፤ ለኢትዮጵያ ያላቸው እጅግ የከረረ ጥላቻ ምክንያት በምንም መለኪያ ከጣሊያን ፋሽስቶችና ከውጭ ወራሪዎች ተለይተው መታየት የለባቸውም” የሚል አቋም አራምጃለሁኝ።

ትህነግ ከሻቢያ ጋር ኢትዮጵያን ለ7 ዓመታት በጋራ ሲዘርፍና ሲያፈርስ ቆይቶ በጥቅም ሲጣሉ ባድሜ ተወረረ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ባድሜ ሲዘምት የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን ደግፎ ባድሜ ላይ ደሙን ማፍሰስ የለበትም ብዬ ተከራክሬያለሁኝ። በባድሜ ላይ የተደረገው ጦርነት ትህነግና ሻቢያ ኢትዮጵያን በጋራ ወረው ከያዙ በኋላ በዘረፋው ተጣልተው የተከሰተ ጦርነት እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ የጋራ ጥቅም የሚመለከት ጦርነት እንዳልሆነ ጠንቅቄ አውቅ ነበር (ይህንን ትህነግና ሻቢያ ኢትዮጵያን እንደ ጠላት አገር ቆጥረው ንብረቷን በመዝረፍ ወደ ትግራይና ኤርትራ ያጋዙበትን ሂደት በሚመለከት አንባቢ“The Pillage of Ethiopia” የሚለውንና ከ25 ዓመታት በፊት የጻፍኳትን መጽሃፍ እንዲያነብ እጋብዛለሁኝ)።

 

የመሃል ኢትዮጵያ ህዝብ ባድሜ ድረስ ዘምቶ ለወያኔዎች ጥቅም ሲል ደሙን በማፍሰሱና ከሰማንያ ሺህ ያላነሰ ወጣት ህይወት የትግራይ ፋሽስቶችን ጥቅም ለማስከበር ሲል ህይወቱን በመገበሩ እስከዛሬ የምቆጭ ሰው ነኝ። በእነዚህ አቋሞቼ ምክንያት ለትግራይ ተወላጆች ጥላቻ ያለኝ ሰው ተብዬ“ጸረ-ትግሬ” የሚል የቅጽል ሥም ወጥቶልኛል። ያ አላስከፋኝም። የዋሁ የኢትዮጵያ ህዝብ “ወንድሞቻችን” እያለ ሲጠራቸው የነበሩትን ሀገር-በቀል ፋሽስቶች ተፈጥሮ ባለመገንዘቡና የትህነግን ፋሽስታዊ ማንነት ለመረዳት በወሰደብን ረጅም ጊዜ ምክንያት ኢትዮጵያ ሀገራችን ላለፉት 30 ዓመታ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች።

 ይህ በትግራዋይነት ማንነቱ ይኩራራ የነበረው ትግሬዎች የመሩት የፋሽስት ሥርዓት በመኃል ሀገር ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና ተቃውሞ (አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በምንም መልኩ ወያኔን ለመጣል በተደረገው የ27 ዓመታት ትግል ውስጥ ድርሻ አልነበረውም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ) ከሶስት ዓመታት በፊት ከሥልጣን ተገሏል። ይሁን እንጂ ትህነግ ከሥልጣን ላይ እዲገለል ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስታዊ መዋቅርም ሆነ ይዘት አልተቀየረም። ይልቁንም “ትህነግና ኦነግ ከሰላሳ ዓመት በፊት የተከሉት የጎሳ ማነንትን መሰረት ያደረገ የአፓርታይድ/የፋሽስት አገዛዘ የትህነግ አቻ በሆነውና በዓቢይ አህመድ በሚመራው ኦሮሙማ በሚባለው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የኦሮሞ የበላይነትን እያሰፈነና እየተገበረ ባለው ፋሽስታዊ ሥርዓት ተተክቷል”። ይህ የኦሮሙማን ፋሽስታዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ የጫነው አክራሪ ብሄረተኛ ሥርዓት የወያኔን የአፓርታይድ የፓለቲካ ሥርዓት ሳይሸራረፍ እንዳለ አስቀጥሏል። በዚህም ምክንያት የትህነግን ፋሽስታዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለመጣልና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት የተደረገው የህዝብ ትግል መክኖ ዛሬ ኢትዮጵያ በሁለት ፋሽስታዊ ኃይሎች መካከል (በትህነግና በዓቢይ አህመድ በሚመራዊ የኦሮሙማ መንግስት) መካከል በሚካሄድ የሥልጣን ሽኩቻ በተፈጠረ ጦርነት እንድትማገድ እየተደረገ ነው።

ትላንት ለ27 ዓመታት ትግራዋይነትን የሚባለውን የትግራይ ጎሳ ተወላጆችን ማንነት የበላይነት የሚሰብክና የሚተገብር ፋሽስታዊ የፓለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫኑት የትግራይ ተወላጆች፤ አሁን ደግሞ በተረኛነት ስሜት ኦሮሙማ የተባለውን የኦሮሞን የበላይነት የሚሰብክና የሚተገብር የአክራሪ ብሄረተኛነትን ሥርዓት ለማስቀጠል ትግል ላይ ካለው የዓቢይ አገዛዝ ጋር በሚያደርጉት ሽኩቻ ሁለቱም ፋሽስታዊ ኃይሎች (ትግራዋይነትና ኦሮሙማ) ኢትዮጵያዊነትን በመውደዱ፤ ጎሰኛነትን በመጠየፉ ምክንያት በግንባር ቀደምነት የለዩትንና የሚጠሉትን  የአማራ ክልል ህዝብ (የአማራን፤ የአገውን፤ የቅማንትን ህዝብ) የጋራ ጠላታቸውና የጦርነት ሰለባ አድርገውታል። የአፋርም ህዝብ ለድርድር በማይቀርብ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አቋሙ ምክንያት የጥቃት ሰለባ ተደርጓል።

 የአማራ ህዝብ ትህነግ ለ27 ዓመታት ያደረሰበት የጅምላ ፍጅት፤ መፈናቀል፤ የዘር የማሳሳት(systematic policy of depopulating the Amaras) ፤ የማደህየት (deliberate and systematic policy of impoverishment) ጥቃት አንሶት እነሆ እነዚህ ባለፉት 30 ዓመታት ሆን ተብሎ እንዳይለማና እንዲቀጭጭ የተደረገው የአማራ ክልል ዛሬ የጦርነት አውድማ እንዲሆን ተደርጓል። የአፋር ክልልም በተመሳሳይ መንገድ የጦርነትና የጥፋት አውድማ እንዲሆን ተፈርዶበታል።

የትግራዋይነትም ሆነ የኦሮሙማ ፋሽስታዊ ማንነቶች መሰረት በኢትዮጵያ የዛሬው ገዢ የፓለቲካ ፍልስፍና የሆነውና የነገድ ማንነትን ዋነኛ የሀገሪቱ ፓለቲካ ሥርዓት መመሪያ ያደረገው ህገ-መንግስት ሲሆን የትግራዋይነትም ሆነ የኦሮሙማ ፋሽስታዊ ማንነቶች አራማጅ የሆኑት ትህነግም ሆነ ኦህዴድ ይህን ፋሽስታዊ የሆነ የአፓርታይድ የፓለቲካ ሥርዓት በማስቀጠል በኩል ያላቸው ቁርጠኘትና አቋም አንድ ዓይነት ነው። በዚህም ምክንያት ነው ይህ ዛሬ የፍልሚያና የጥፋት ቀጠናውን ወደ አማራና አፋር ክልሎች ያዞረው ጦርነት በትህነግም ሆነ በኦህዴድ ኃይሎች ፍላጎት የሚቆም ሳይሆን እንዲያውም እንዲቀጥል የሚፈለግ ነው። ይልቁንም በመላው ኢትዮጵያ በማንነቱ ምክንያት ተለይቶ የጥቃት ዋነኛ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ ለ27 ዓመታት ከተፈጸመበት ግፍና በደል በላይ ዛሬ እደጁ ድረስ መጥቶ ሴት ልጆቹን፤ ሚስቱን፤ እናቱን፤ ቤተሰቡን እየደፈረ፤ እየፈጀ፤ ታሪካዊ፤ ባህላዊና የእምነት መገለጫ ቅርሶቹን እየዘረፈ፤ እያወደመ ያለውን የትግሬ ፋሽስት ሰራዊትም ሆነ ይህንን እያመቻቸ ያለውን የኦሮሙማ መንግስት ሊዋጋ የሚችለው የኦሮሙማ መንግስት ወኪልና ትዕዛዝ ፈጻሚ በሆነው ብአዴን እየተመራ ሊሆን አይችልም።

የኦሮሙማን መንግሥት መመሪያ ተቀብሎ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ እንዲገደል ካደረገ በኋላ ለአማራ ህዝብ ልዕልና የቆሙ የአማራ መኮንኖችን በዓቢይ አህመድ ቀጭን ትዕዛዝ ባህር ዳር ላይ አስሮ የሚያሰቃየው ብአዴን የአማራን ህዝብ አይታደግም። የዲሞክራሲ መገለጫ የሆኑትን የዜጎችንና የግለሰቦችን መብት ልዕልና መከበር በግንባር ቀደምትነት የታገሉት እነ አቶ እስክንድር ነጋን፤ አቶ ስንታየዩ ቸኮልንና ባልደረቦቻቸውን በሃሰት ወንጅሎ ያሰረ፤ አቶ ታዴዎስ ታንቱ በዚህ ፋሽስታዊ ሥርዓት ላይ ያለውን ህጋዊ ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመግለጹ ያሰረው የኦሮሙማ መንግስትም ሆነ የእሱ ተላላኪ ሆነው የአማራን ክልል የሚያስተዳድሩት የብአዴን መሪዎች የሆኑት ባለሥልጣናት በፍትኃዊነትና በህግ ያምናሉ ብዬ አላምንም። ይሁን እንጂ “እነዚህ መንግሥታዊ አካሎች ቢያንስ የጻፉትንና በወረቀት ላይ ያሰፈሩትን መብት እንዲያከብሩና የአቶ ጌታቸው ረዳን ታናሽ ወንድም ጉዳይ ከጅምላ አስተያየት ባሻገር እንደ አንድ ግለሰብ አይተውና የታሰረበትን ምክንያት አጣርተው፤ ከትህነግ ድርጊት ጋር ንክኪ እንደሌለውና ንህጽናው ከተረጋገጠ በአስቸኳይ እንዲፈቱት ጥሪ አደርጋለሁኝ”።

እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ራሱን ለሀገር የወል ጥቅም ሲባል ቤዛ ያደረገ፤ ከብዙዎቻችን በተሻለ ስለ አማራውም ሆነ ስለሌሎች ድምፅ-አልባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ድምጹን ጮክ አድርጎ የታገለ ወንድማችንን በዚህ ጊዜ ቢያንስ ስነልቦናዊ ድጋፍ በመስጠት ከጎኑ ልንቆም ይገባል። አማሮች “የፊት ወዳጅክን በምን ቀበርከው በሻሽ፤ የኋላው እንዳይሸሽ” ይላሉ። ዛሬ የአቶ ጌታቸው ረዳ ቤተሰብ አባል የሆነው ታናሽ ወንድሙ ካለ አግባብ በትህነግ ደጋፊነት ተጠርጥሮ ሲታሰር ዝም የምንል ከሆነ ነገ ይህን የሚመለከቱ ሁሉ ለካ ከትግራይ ውጭ ያሉት ኢትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ አማሮች እንደዚህ ናቸው ብለው ጣት ይጠቋቆሙብናል።

ዛሬ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጎን በመቆም ድምጻችንን ስናሰማ ለካንስ እነዚህ ሰዎች በክፉ ጊዜ ከአጠገባችን ሊቆሙና ልንመካባቸው የምንችል ታማኝ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው በማለት በእኛ ላይ ያላቸውን እምነት ሊያጸኑ ይችላሉ። የአማራ ህዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ ሆኖም እንኳን በተደጋጋሚ ጊዜዎች ቁምነገረኛነቱንና ውለታ አክባሪነቱን አስመስክሯል። የወያኔንና የሻቢያን ጦርነት ተከትሎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች በወያኔ ትግሬዎች መንግሥት ሲባረሩ፤ ሀብት ንብረታቸው በትህነግ ባለሥልጣናትና በትህነግ አባላት ሲወረስ፤ የአማራ ህዝብ ግን ከወቅቱ የፓለቲካ ትኩሳት ባሻገር አርቆ በመመልከት፤ሰብዓዊ ግዴታውን ሳይረሳ፤ኤርትራውያን በአደራ እንዲጠብቁለት አምነው የተዉለትን ንብረት ለሃያ ዓመታት ያህል ጠብቆ፤ በተቸገሩበት ጊዜ በአደራ የጠበቀላቸውን ንብረት መልሶ አስረክቧል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን በደሴ፤ በአዲስ አበባ፤ በጎንደር፤ በባህርዳር ወዘተ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን ከሃያ ዓመታት በኋላ ከኤርትራ ተመልሰው ለአማሮች በአደራ የሰጡትን ንብረታቸውን መረከባቸው በመገናኛ ብዙሃን ጭምር መዘገቡ ነው።ስለዚህ የአማራ ክልል መንግሥት የአቶ ጌታቸውን ታናሽ ወንድም ጉዳይ አጣርቶ ከእስር እንዲፈታ እንዲያደርግ ግፊት እንድናደርግ እጠይቃለሁኝ። በዚህ ፈታኝ ወቅት ፈጣሪ አምላክ ለአቶ ጌታቸው ረዳና ቤተሰቡ ጥንካሬውንና ብርታቱን እንዲሰጠጥልኝ እመኛለሁኝ።

አሰፋ ነጋሽ - ከአምስተርዳም (ሆላንድ)